ከቤተሰባችሁ ጋር የተወሰነ ጊዜ ታሳልፋላችሁን?
“ጃፓናውያን አባቶች ሥራ የሚበዛባቸውና ከልጆቻቸው ጋር የማይጫወቱ ቢሆኑም የተወደዱ ናቸው።” ይህ ርዕስ ከጥቂት ዓመታት በፊት ማይኒቺ ሺምቡን በተባለ ጋዜጣ ላይ ወጥቶ ነበር። መንግሥት በጃፓናውያን ልጆች ላይ ያደረገውን ጥናት መሠረት ያደረገው ይህ ጋዜጣ 87.8 በመቶ የሚሆኑት ወደፊት አባቶቻቸውን የመጦር ምኞት ያላቸው መሆኑን ዘግቧል። የዚህ ጋዜጣ የእንግሊዝኛ እትም ይህንኑ ጉዳይ በሌላ ርዕስ ሥር አውጥቶ ነበር። ርዕሱ “ልጆቻቸውን ቸል የሚሉ አባቶች” የሚል ነበር። ይህ ጋዜጣ ከጃፓንኛው እትም በተለየ መንገድ በዚያው ጥናት ላይ የታየውን ሌላ ገጽታ ጎላ አድርጎ ገልጿል:- በእያንዳንዱ የሥራ ቀን ጃፓናውያን አባቶች ከልጆቻቸው ጋር የሚያሳልፉት ጊዜ 36 ደቂቃ ብቻ ነው። ከሌሎች አገሮች ጋር ሲወዳደር በምዕራብ ጀርመን ያሉ አባቶች በሥራ ቀን ከልጆቻቸው ጋር የሚያሳልፉት ጊዜ 44 ደቂቃ ሲሆን በዩናይትድ ስቴትስ ደግሞ አኃዙ ወደ 56 ደቂቃ ይደርሳል።
ከልጆቻቸው ጋር አነስተኛ ሰዓት የሚያሳልፉት አባቶች ብቻ አይደሉም። ከጊዜ ወደ ጊዜ ቁጥራቸው እያደገ የመጣ በርካታ እናቶች ከቤት ውጪ ይሠራሉ። ለምሳሌ ያህል በርካታ ነጠላ እናቶች ቤተሰቦቻቸውን ለመደገፍ ሲሉ ሰብዓዊ ሥራ ለመሥራት ተገድደዋል። በዚህም የተነሳ ወላጆች ማለትም አባቶችም ሆኑ እናቶች ከልጆቻቸው ጋር የሚያሳልፉት ጊዜ አነስተኛ እየሆነ መጥቷል።
በአሜሪካ በሚኖሩ ቁጥራቸው ከ12,000 በላይ የሆነ በአሥራዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ በሚገኙ ወጣቶች ላይ በ1997 የተደረገ አንድ ጥናት ከወላጆቻቸው ጋር የቀረበ ግንኙነት ያላቸው ወጣቶች በስሜት ላይ በሚደርስ ውጥረት የመሠቃየት፣ የራስን ሕይወት ለማጥፋት የመነሳሳት፣ በዓመፅ ድርጊት የመካፈል ወይም ሱስ የሚያስይዙ ንጥረ ነገሮች የመውሰድ ዕድላቸው በጣም አነስተኛ እንደሆነ አመልክቷል። በዚህ ሰፊ ጥናት ከተካፈሉት ምሁራን መካከል አንዱ “ለልጆቻችሁ ራሳችሁን እስካልሰጣችሁ ድረስ የጠበቀ ግንኙነት ሊኖራችሁ አይችልም” ብለዋል። ከልጆቻችሁ ጋር ጊዜ ማሳለፋችሁና ከእነርሱ ጋር መነጋገራችሁ ከፍተኛ ለውጥ ያመጣል።
ለሐሳብ ግንኙነት እንቅፋት የሚሆን ነገር
የአንድ ቤተሰብ ወላጅ በሥራ ምክንያት ከቤተሰቡ ተለይቶ በሚኖርበት ጊዜ በቤተሰቡ መካከል የሚኖረው የሐሳብ ግንኙነት ሊቋረጥ ይችላል። እርግጥ ነው፣ ለሐሳብ ግንኙነት እንቅፋት የሚሆነው አንድ ወላጅ ከቤተሰቡ ተለይቶ መኖሩ ብቻ አይደለም። አንዳንድ ወላጆች እቤት የሚኖሩ ቢሆኑም ልጆቻቸው ከእንቅልፍ ከመነሳታቸው በፊት ወደ ሥራ ይሄዳሉ እንዲሁም ልጆቻቸው ከተኙ በኋላ ወደ ቤት ይመለሳሉ። አንዳንድ ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር ሳይተያዩ የሚያሳልፉትን ጊዜ ለማካካስ ሲሉ ቅዳሜና እሁድ እንዲሁም በበዓል ቀናት ከቤተሰቦቻቸው ጋር ይውላሉ። ከልጆቻቸው ጋር “ጥሩ” ጊዜ እንዳሳለፉ ሲናገሩ ይሰማሉ።
ይሁን እንጂ ጥሩ የተባለው ጊዜ ሳይተያዩ ያሳለፉትን ጊዜ ሊያካክስ ይችላልን? ሎረንስ ስታይንበርግ የተባሉ ተመራማሪ እንዲህ በማለት መልሱን ይሰጣሉ:- “በጥቅሉ ሲታይ ከወላጆቻቸው ጋር ረዘም ያለ ጊዜ የሚያሳልፉ ልጆች ጥቂት ጊዜ ከሚያሳልፉት የተሻለ ነገር ማከናወን ይችላሉ። ያንን የጎደለ ጊዜ ማካካስ የሚቻል ነገር አይመስልም። ጥሩ ጊዜ ማሳለፍ የሚለው አባባል በጣም የተጋነነ ነው።” የበርማ ተወላጅ የሆነች አንዲት ሴትም ያላት አስተያየት ከዚህ የተለየ አይደለም። እንደ አብዛኞቹ ጃፓናውያን ወንዶች ሁሉ የእሷም ባል ሁልጊዜ ከሥራ ወደ ቤት የሚመለሰው ከሌሊቱ ሰባት ወይም ስምንት ሰዓት ላይ ነው። ምንም እንኳ ቅዳሜና እሁድን ከቤተሰቡ ጋር የሚያሳልፍ ቢሆንም ባለቤቱ እንዲህ ትላለች:- “ቅዳሜና እሁድ ቤት መዋሉ በቀሩት የሳምንቱ ቀናት ከቤተሰቡ ጋር ያልዋለባቸውን ጊዜያት ሊያካክሰው አይችልም። . . . ከሰኞ እስከ አርብ ምግብ ሳትመገቡ ቆይታችሁ ቅዳሜና እሁድ ሁሉንም አንድ ላይ ልትመገቡ ትችላላችሁ?”
በደንብ የታሰበበት ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል
በቤተሰብ ውስጥ ጥሩ የሐሳብ ግንኙነት እንዲኖር ማድረግ እንዲህ እንደምንናገረው ቀላል አይደለም። መተዳደሪያ አግኝቶ ቤተሰቡ የሚያስፈልገውን ቁሳዊ ነገር ለማሟላት የሚደረገው ትግል አንድ አባት ወይም ከቤት ውጭ የምትሠራ አንዲት እናት ከቤተሰባቸው ጋር ሆነው የሚያሳልፉት ጊዜ እንዲያጡ ሊያደርጋቸው ይችላል። በሁኔታዎች አስገዳጅነት ከቤተሰቦቻቸው ርቀው የሚኖሩ ብዙዎች ስልክ በመደወል ወይም ደብዳቤ በመጻፍ ከቤተሰቦቻቸው ጋር አዘውትረው ይገናኛሉ። ይሁን እንጂ ከቤተሰብ ጋር አንድ ላይ የሚኖሩ ቢሆኑም ባይሆኑ በቤተሰብ ውስጥ ያለው ጥሩ የሐሳብ ግንኙነት ሳይስተጓጎል እንዲቀጥል ለማድረግ በደንብ የታሰበበት ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል።
ከቤተሰባቸው ጋር የሐሳብ ግንኙነት የማድረግን አስፈላጊነት ቸል ያሉ ወላጆች ይህ ሁኔታ የሚያስከትልባቸውን ኪሳራ መቀበላቸው አይቀሬ ነው። ከቤተሰቡ ጋር እምብዛም ጊዜ የማያሳልፍና ሌላው ቀርቶ ምግብ እንኳ አብሯቸው የማይመገብ አንድ አባት አስከፊ መዘዝ ደርሶበታል። ወንድ ልጁ ተደባዳቢ ሆነ፤ ሴት ልጁ ደግሞ ከሱቅ ዕቃ ስትሰርቅ ተይዛለች። አንድ እሁድ ጠዋት አባትዬው ጎልፍ ለመጫወት ከቤት ሊወጣ ሲል ወንድ ልጁ የታመቀ ስሜቱን መቆጣጠር ተስኖት “እዚህ ቤት እማዬ ብቻ ነች እንዴ ወላጅ?” በማለት ጠየቀ። “በቤተሰባችን ውስጥ በማንኛውም ጉዳይ ላይ ውሳኔ የምታደርገው እማዬ ናት። አባባ፣ አንተ ፈጽሞ . . .” በማለት የተሰማውን ሐዘን ገለጸ።
እነዚህ ቃላት አባትዬውን በጣም ከነከኑት። በመጨረሻም ቁርጥ ውሳኔ አደረገና ከቤተሰቡ ጋር ቁርስ መመገብ ጀመረ። መጀመሪያ ላይ ይመገብ የነበረው ከባለቤቱ ጋር ብቻ ነበር። ቀስ በቀስ ልጆቹም ከእነርሱ ጋር በመቀላቀላቸው የቁርስ ሰዓቱ ሞቅ ያለ ጭውውት የሚያደርጉበት ጊዜ ሆነ። ይህ ጅምር እራትም አንድ ላይ እንዲመገቡ መንገድ ከፈተ። በዚህ መንገድ አባትየው የቤተሰቡን ሕልውና ከውድቀት ለመታደግ የበኩሉን ጥረት አድርጓል።
ከአምላክ ቃል የሚገኝ እርዳታ
ወላጆች ጊዜ ወስደው ከልጆቻቸው ጋር እንዲነጋገሩ መጽሐፍ ቅዱስ ያበረታታቸዋል። በነቢዩ ሙሴ በኩል እስራኤላውያን እንዲህ ተብለው ታዝዘው ነበር:- “እስራኤል ሆይ፣ ስማ፤ አምላካችን እግዚአብሔር አንድ እግዚአብሔር ነው፤ አንተም አምላክህን እግዚአብሔርን በፍጹም ልብህ በፍጹምም ነፍስህ በፍጹምም ኃይልህ ውደድ። እኔም ዛሬ አንተን የማዝዘውን ይህን ቃል በልብህ ያዝ። ለልጆችህም አስተምረው፣ በቤትህም ስትቀመጥ፣ በመንገድም ስትሄድ፣ ስትተኛም፣ ስትነሣም ተጫወተው።” (ዘዳግም 6:4-7) አዎን፣ ወላጅ የሆንን ሁላችን በልጆቻችን አእምሮና ልብ ውስጥ የአምላክን ቃል ለመቅረጽ ከቤተሰቦቻችን ጋር ጊዜ ለማሳለፍ ቀዳሚ ሆነን መገኘት ይኖርብናል።
ቀደም ሲል የተጠቀሰው ከ12,000 በሚበልጡ አሜሪካውያን ወጣቶች ላይ በ1997 የተካሄደው ጥናት “ሃይማኖት እንዳላቸው ከተናገሩት መካከል 88 በመቶ የሚሆኑት . . . ሃይማኖትና ጸሎት ጥበቃ ያስገኛል የሚል እምነት እንዳላቸው” አመልክቷል። እውነተኛ ክርስቲያኖች በቤት ውስጥ የሚሰጥ ትክክለኛ ሃይማኖታዊ መመሪያ ወጣቶችን ሱስ ከሚያስይዙ ነገሮች፣ በስሜት ላይ ከሚደርሱ ቀውሶች፣ ራስን ከመግደል፣ በዓመፅ ድርጊቶች ከመካፈልና ከመሳሰሉት ድርጊቶች እንደሚጠብቃቸው ይገነዘባሉ።
አንዳንድ ወላጆች ለቤተሰባቸው የሚሆን ጊዜ ማግኘት የሚቻል አይመስላቸውም። በተለይ ደግሞ ከልጆቻቸው ጋር መዋል እየፈለጉ ሰብዓዊ ሥራ የመሥራት ግዴታ ያለባቸው ነጠላ ወላጆች እንዲህ ዓይነት አመለካከት አላቸው። ታዲያ ያለቻቸውን ጊዜ በማብቃቃት ከቤተሰባቸው ጋር ለመሆን የሚያስችላቸውን ውድ ጊዜ ሊያገኙ የሚችሉት እንዴት ነው? መጽሐፍ ቅዱስ “መልካም [“ተግባራዊ፣” NW] ጥበብንና ጥንቃቄን [“የማሰብ ችሎታን፣” NW] ጠብቅ” በማለት ማሳሰቢያ ይሰጣል። (ምሳሌ 3:21) ወላጆች ‘በማሰብ ችሎታቸው’ ተጠቅመው ለቤተሰባቸው የሚሆን ጊዜ ማግኘት ይችላሉ። እንዴት?
ሥራ የምትውይ እናት ከሆንሽና ወደቤት ስትመለሺ ከፍተኛ ድካም የሚሰማሽ ከሆነ ምግብ በምታዘጋጂበት ጊዜ ልጆችሽም አብረውሽ እንዲሠሩ ለምን አትጠይቂያቸውም? በዚህ ወቅት አብራችሁ ሆናችሁ የምታሳልፉት ጊዜ ይበልጥ እንድትቀራረቡ አጋጣሚውን ይከፍትላችኋል። ልጆችሽ በሥራው መካፈላቸው መጀመሪያ ላይ ተጨማሪ ጊዜ እንዲወስድብሽ ሊያደርግ ይችላል። ሆኖም ብዙም ሳይቆይ አስደሳችና አልፎ ተርፎም ጊዜ የሚቆጥብ ሆኖ ታገኚዋለሽ።
ቅዳሜና እሁድ የሚሠሩ በርካታ ሥራዎች ያሉብህ አባት ልትሆን ትችላለህ። ከልጆችህ ጋር ሆነህ አንዳንድ ሥራዎችን ለምን አታከናውንም? እየሠራችሁ እያለ ከልጆችህ ጋር ልትነጋገርና በዚያውም ጠቃሚ የሆነ ሥልጠና ልትሰጣቸው ትችላለህ። በልጆቻችሁ ልብ ውስጥ የአምላክን ቃል እንድትቀርጹ የሚያሳስበው የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ‘በቤት ውስጥ ስትሆኑም ሆነ በመንገድ ላይ ስትሄዱ’ በአጠቃላይ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ከልጆቻችሁ ጋር እንድትነጋገሩ የሚያበረታታ ነው። አንድ ላይ ሆናችሁ በምትሠሩበት ጊዜ ከልጆቻችሁ ጋር መነጋገራችሁ “ተግባራዊ ጥበብ” እንዳላችሁ የሚያሳይ ነው።
ከቤተሰባችሁ ጋር ጊዜ ማሳለፋችሁ የኋላ ኋላ ዘላቂ የሆነ ጥቅም ያስገኝላችኋል። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ “እርስ በርስ በሚመካከሩ ዘንድ . . . ጥበብ ይገኛል” ይላል። (ምሳሌ 13:10 NW) ከቤተሰባችሁ ጋር ለመነጋገር ጊዜ መመደባችሁ በዕለታዊ ሕይወት ውስጥ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመወጣት የሚያስችል ጥበብ የሞላበት መመሪያ እንድትሰጡ ያስችላችኋል። በአሁኑ ጊዜ እንዲህ ዓይነት መመሪያ በመስጠት ወደፊት ሊባክን የሚችልን ጊዜ ከማዳናችሁም በላይ ከከባድ ሃዘን ልትጠበቁ ትችላላችሁ። ከዚህም በተጨማሪ እናንተም ሆናችሁ ልጆቻችሁ ደስተኞች እንድትሆኑ አስተዋጽኦ ሊያበረክት ይችላል። እንዲህ ያለውን መመሪያ ለመስጠት በአምላክ ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን የተትረፈረፈ ጥበብ ቀድታችሁ መውሰድ ይኖርባችኋል። ልጆቻችሁን ለማስተማርና የቤተሰባችሁን እርምጃ ለማቅናት ተጠቀሙበት።—መዝሙር 119:105
[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከወላጆቻቸው ጋር የተቀራረበ ግንኙነት ያላቸው ወጣቶች ለስሜት ውጥረት እምብዛም የተጋለጡ አይደሉም
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ጥሩ የሐሳብ ግንኙነት ማድረግ በቤተሰብ ኑሮ ውስጥ ከፍተኛ ጥቅም ያስገኛል
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከልጆቻችሁ ጋር አብራችሁ ስትሠሩ ልታነጋግሯቸውና ጠቃሚ የሆነ ስልጠና ልትሰጧቸው ትችላላችሁ