ይሖዋ በመንገዱ ስለሚመራን ደስተኞች ነን
“የአምላክ መንገድ ፍጹም ነው፤ የእግዚአብሔር ቃል የነጠረ ነው።”—2 ሳሙኤል 22:31
1, 2. (ሀ) የሰው ልጅ ከሚያስፈልጉት መሠረታዊ ነገሮች አንዱ ምንድን ነው? (ለ) የማንን ምሳሌ መኮረጅ ይኖርብናል?
መመሪያ የሰው ልጅ ከሚያስፈልጉት መሠረታዊ ነገሮች አንዱ ነው። ስለሆነም ሕይወታችንን በተቃና መንገድ ለመምራት እርዳታ ያስፈልገናል። እርግጥ ነው፣ ይሖዋ ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር መለየት የምንችልበት በተወሰነ ደረጃ የማስተዋል ችሎታና ሕሊና ሰጥቶናል። ይሁን እንጂ ሕሊናችን እምነት የሚጣልበት መሪ ሆኖ እንዲያገለግለን መሠልጠን ይኖርበታል። (ዕብራውያን 5:14) እንዲሁም ጥሩ ውሳኔዎችን ለማድረግ እንድንችል አእምሯችን ትክክለኛ የሆነ መረጃ ማግኘትና ያገኘውንም መረጃ የመገምገም ችሎታ እንዲኖረው መሠልጠን ይኖርበታል። (ምሳሌ 2:1-5) እንደዚያም ሆኖ በሕይወታችን ውስጥ ስለሚገጥሙን ነገሮች እርግጠኛ መሆን ስለማንችል ያደረግናቸው ውሳኔዎች እንደፈለግነው ላይሰምሩልን ይችላሉ። (መክብብ 9:11) የወደፊቱ ጊዜ ምን ነገሮችን እንደያዘ ለማወቅ የሚያስችለን የራሳችን የሆነ አስተማማኝ መንገድ የለንም።
2 በእነዚህና በሌሎች በርካታ ምክንያቶች የተነሳ ነቢዩ ኤርምያስ “አቤቱ፣ የሰው መንገድ ከራሱ እንዳይደለ አውቃለሁ፣ አካሄዱንም ለማቅናት ከሚራመድ ሰው አይደለም” በማለት ጽፏል። (ኤርምያስ 10:23) እስከ ዛሬ ከኖሩት ሁሉ የሚበልጠው ኢየሱስ ክርስቶስ መመሪያ ተቀብሏል። እንዲህ አለ:- “አብ ሲያደርግ ያየውን ነው እንጂ ወልድ ከራሱ ሊያደርግ ምንም አይችልም፤ ያ የሚያደርገውን ሁሉ ወልድ ደግሞ ይህን እንዲሁ ያደርጋልና።” (ዮሐንስ 5:19) እንግዲያው የኢየሱስን ምሳሌ በመኮረጅ አካሄዳችንን እንዲመራልን ወደ ይሖዋ ዞር ማለታችን ምንኛ ጥበብ ነው! ንጉሥ ዳዊት “የአምላክ መንገድ ፍጹም ነው፤ የእግዚአብሔር ቃል የነጠረ ነው፤ በእርሱ ለሚታመኑት ሁሉ ጋሻ ነው” በማለት ዘምሯል። (2 ሳሙኤል 22:31) በራሳችን ጥበብ ከመመራት ይልቅ በይሖዋ መንገድ ለመመላለስ የምንመርጥ ከሆነ ፍጹም አመራር አገኘን ማለት ነው። የአምላክን መንገድ ወደ ጎን ገሸሽ ማድረግ ጥፋት ያስከትላል።
ይሖዋ መንገዱን ይመራናል
3. ይሖዋ ለአዳምና ለሔዋን መመሪያ የሰጣቸው እንዴት ነበር? ምን ዓይነት ተስፋ ከፊታቸው ዘርግቶላቸው ነበር?
3 የአዳምንና የሔዋንን ሁኔታ ተመልከት። ኃጢአተኞች ያልነበሩ ቢሆኑም እንኳ መመሪያ ማግኘት ያስፈልጋቸው ነበር። ይሖዋ አዳምን ከፈጠረው በኋላ ውብ በሆነው የኤደን የአትክልት ሥፍራ ውስጥ ሆኖ የራሱን እቅድ እያወጣ እንዲኖር አላደረገውም። ከዚህ ይልቅ ሥራ ሰጥቶት ነበር። በመጀመሪያ አዳም ለእንስሳት ስም ማውጣት ነበረበት። ከዚያም ይሖዋ ለአዳምና ለሔዋን ለረዥም ጊዜ የሚዘልቁ ግቦች አወጣላቸው። ምድርን መግዛት፣ በሚወልዷቸው ልጆች መሙላትና የምድርን እንስሳት መንከባከብ ነበረባቸው። (ዘፍጥረት 1:28) ይህ ትልቅ ፕሮጄክት የነበረ ቢሆንም መጨረሻ ላይ ከእንስሳት ጋር ስምም ሆኖ በሚኖር ፍጹም የሆነ ሰብዓዊ ዘር የተሞላ አንድ ዓለም አቀፋዊ ገነት ያስገኝ ነበር። እንዴት ያለ ግሩም ተስፋ ነበር! ከዚህም በላይ አዳምና ሔዋን በታማኝነት በይሖዋ መንገድ እስከተመላለሱ ድረስ ከእርሱ ጋር መነጋገር ይችሉ ነበር። (ከዘፍጥረት 3:8 ጋር አወዳድር።) ከፈጣሪ ጋር ቀጣይ የሆነ የግል ዝምድና መሥርቶ መኖር ተወዳዳሪ የማይገኝለት መብት ነው!
4. አዳምና ሔዋን እምነትና ታማኝነት እንደጎደላቸው ያሳዩት እንዴት ነው? ይህስ ምን ውድቀት አስከተለባቸው?
4 ይሖዋ በኤደን ውስጥ ከነበረው ክፉና ደጉን ከሚያስታውቀው ዛፍ እንዳይበሉ የመጀመሪያዎቹን ባልና ሚስት አዘዛቸው፤ ይህም በታዛዥነት በይሖዋ መንገድ ለመመላለስ ፍላጎት እንዳላቸው ለማረጋገጥ የሚያስችል ጥሩ አጋጣሚ ከፍቶላቸው ነበር። (ዘፍጥረት 2:17) ሆኖም ብዙም ሳይቆይ ታዛዥነታቸው ፈተና ላይ ወደቀ። ሰይጣን የማታለያ ቃላቱን በሰነዘረ ጊዜ አዳምና ሔዋን ታዛዥ እንደሆኑ ለመቀጠል እንዲችሉ ለይሖዋ ታማኝ ሆነው መገኘትና ቃል በገባቸው ተስፋዎች ማመን ነበረባቸው። የሚያሳዝነው ግን ታማኝነትና እምነት የጎደላቸው ሆኑ። ሰይጣን ሔዋንን ቀርቦ በማነጋገር በራሷ እንድትመራ ሐሳብ ሲያቀርብላትና ይሖዋን ውሸት እንደተናገረ አድርጎ በሐሰት ሲወነጅለው ሔዋን ተታልላ በአምላክ ላይ ዓመፀች። አዳምም በኃጢአት ድርጊት ተባበራት። (ዘፍጥረት 3:1-6፤ 1 ጢሞቴዎስ 2:14) ይህ ሁኔታ ከፍተኛ ኪሣራ አስከትሎባቸዋል። በይሖዋ መንገድ ላይ በመመላለስ ፈቃዱን ደረጃ በደረጃ ፈጽመው ቢሆን ኖሮ እያደር እየጨመረ የሚሄድ ደስታ ማጨድ ይችሉ ነበር። በዚያ ፈንታ ግን ሞት እስኪወስዳቸው ድረስ ሕይወታቸው ሐዘንና ሥቃይ የሞላበት ሆነ።—ዘፍጥረት 3:16-19፤ 5:1-5
5. ይሖዋ የረዥም ጊዜ ዓላማው ምንድን ነው? ታማኝ ሰዎች የዚህን ዓላማ ፍጻሜ መመልከት እንዲችሉ የሚረዳቸውስ እንዴት ነው?
5 ያም ሆኖ ይሖዋ፣ ምድር ኃጢአት በሌለባቸው ፍጹማን ሰዎች የተሞላች ገነት እንድትሆን ለማድረግ ያወጣውን ዓላማ አልለወጠም። (መዝሙር 37:11, 29) እንዲሁም በመንገዱ ለሚመላለሱና የዚህን ተስፋ ፍጻሜ ለማየት ለሚናፍቁ ሰዎች ፍጹም የሆነ መመሪያ መስጠቱን አላቋረጠም። የሚሰማ ጆሮ ላለን ሁሉ የይሖዋ ድምፅ ከኋላችን ሆኖ “መንገዱ ይህች ናት በእርስዋም ሂድ” ይለናል።—ኢሳይያስ 30:21
አንዳንዶች በይሖዋ መንገድ ተመላልሰዋል
6. በይሖዋ መንገድ የተመላለሱት ሁለቱ ጥንታዊ ሰዎች እነማን ናቸው? ይህስ ምን ውጤት አስገኝቶላቸዋል?
6 በመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ መሠረት ከአዳምና ከሔዋን ዘሮች መካከል በይሖዋ መንገድ የተመላለሱት ሰዎች ጥቂቶች ናቸው። ከእነዚህ ጥቂት ሰዎች መካከል የመጀመሪያው አቤል ነው። ያለ ዕድሜው በሞት የተቀጨ ቢሆንም የይሖዋን ሞገስ አግኝቷል። እንዲሁም አምላክ የወሰነው ጊዜ ደርሶ ‘ጻድቃን ከሙታን በሚነሡበት ጊዜ’ እርሱም ከሞት የመነሳት የተረጋገጠ ተስፋ አለው። (ሥራ 24:15) ይሖዋ ለምድርና ለሰው ዘር ያለው ታላቅ ዓላማ የመጨረሻ ፍጻሜውን ሲያገኝ ይመለከታል። (ዕብራውያን 11:4) በአምላክ መንገድ የተመላለሰው ሌላው ሰው ደግሞ ስለዚህ የነገሮች ሥርዓት የመጨረሻ ድምዳሜ በትንቢት የተናገራቸው ቃላት በይሁዳ መጽሐፍ ውስጥ የተመዘገቡለት ሄኖክ ነው። (ይሁዳ 14, 15) ሄኖክም ቢሆን ሊኖር የሚችለውን ያህል ዕድሜ አልኖረም። (ዘፍጥረት 5:21-24) እንደዚያም ሆኖ “እግዚአብሔርን ደስ እንዳሰኘ ተመስክሮለታል።” (ዕብራውያን 11:5) ከዚህ ዓለም በሞት በተለየ ጊዜ ልክ እንደ አቤል እርሱም ከሞት የመነሳትና የይሖዋ ዓላማ ፍጻሜውን ሲያገኝ ከሚመለከቱት ሰዎች መካከል የመሆን እርግጠኛ ተስፋ ነበረው።
7. ኖኅና ቤተሰቡ ለይሖዋ ያላቸውን ታማኝነትና በእርሱ ላይ መታመናቸውን ያሳዩት እንዴት ነበር?
7 የጥፋት ውኃ ከመምጣቱ በፊት በነበረው ዓለም ክፋት እየተባባሰ ሲሄድ ለይሖዋ ታዛዥ ሆኖ የመገኘቱ ጉዳይ ከባድ የታማኝነት ፈተና እየሆነ መጣ። ያ ዓለም ሊጠፋ በተቃረበበት ወቅት በይሖዋ መንገድ እየተመላለሰ የነበረው አንድ ትንሽ ቡድን ብቻ ነበር። ኖኅና ቤተሰቡ አምላክን ከማዳመጣቸውም በላይ የተናገረውን አምነዋል። እንዲሠሩት የተሰጣቸውን ሥራ በታማኝነት ከመፈጸማቸውም በላይ በዚያ ዘመን በነበረው ዓለም ይዘወተሩ በነበሩ እኩይ ምግባሮች ተስበው እንዳይወሰዱ ከፍተኛ ጥንቃቄ አድርገዋል። (ዘፍጥረት 6:5-7, 13-16፤ ዕብራውያን 11:7፤ 2 ጴጥሮስ 2:5) በእምነትና በታማኝነት ታዛዥ ሆነው በመገኘታቸው አመስጋኝ ልንሆን እንችላለን። በዚህ የተነሳ ከጥፋት ውኃው በሕይወት ተርፈው የእኛ ቅድመ አያቶች ለመሆን በቅተዋል።—ዘፍጥረት 6:22፤ 1 ጴጥሮስ 3:20
8. እስራኤላውያን በአምላክ መንገድ ለመመላለስ ምን ማድረግ ነበረባቸው?
8 ከጊዜ በኋላ ይሖዋ ከታማኙ የያዕቆብ ዝርያዎች ጋር ቃል ኪዳን በመግባቱ የእርሱ ልዩ ሕዝብ ሆኑ። (ዘጸአት 19:5, 6) ይሖዋ ለቃል ኪዳን ሕዝቡ በጽሑፍ በሰፈረ ሕግ፣ በክህነት አገልግሎትና ያለማቋረጥ በሚተላለፍ ትንቢታዊ መመሪያ አማካኝነት አመራር ሰጥቷል። ሆኖም ይህን አመራር መከተል አለመከተሉ ለእስራኤላውያኑ የተተወ ነበር። ይሖዋ በነቢዩ በኩል እስራኤላውያንን እንዲህ ብሏቸው ነበር:- “እነሆ፣ እኔ ዛሬ በፊታችሁ በረከትንና መርገምን አኖራለሁ፤ በረከትም፣ እኔ ዛሬ ለእናንተ የማዝዘውን የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ብትሰሙ፤ መርገምም፣ የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ባትሰሙ፣ ዛሬም ካዘዝኋችሁ መንገድ ፈቀቅ ብትሉ፣ ሌሎችንም የማታውቋቸውን አማልክት ብትከተሉ ነው።”—ዘዳግም 11:26-28
አንዳንዶች ከይሖዋ መንገድ የወጡበት ምክንያት
9, 10. እስራኤላውያን በይሖዋ የመታመንና ለእርሱ ታማኝ የመሆን ባሕርይ መኮትኮት የነበረባቸው በምን ሁኔታ ሥር ስለነበሩ ነው?
9 ከአዳምና ከሔዋን ይጠበቅ እንደነበረው ሁሉ እስራኤላውያንም ታዛዥ ሆነው ለመቀጠል በይሖዋ መመካትና ለእርሱ ታማኝ ሆነው መገኘት ነበረባቸው። እስራኤላውያን ጠበኛ በሆኑ ጎረቤት አገሮች የተከበቡ አናሳ ሕዝብ ነበሩ። በደቡብ ምዕራብ በኩል ግብፅና ኢትዮጵያ፣ በሰሜን ምሥራቅ በኩል ደግሞ ሶርያና አሦር ይገኙ ነበር። ፍልስጤም፣ አሞን፣ ሞዓብ እና ኤዶም ደግሞ በዙሪያቸው ነበሩ። እነዚህ ሁሉ አገሮች በተለያዩ ጊዜያት የእስራኤል ጠላት መሆናቸውን አሳይተዋል። ከዚህም በላይ ሁሉም የሐሰት አምልኮ ተካፋዮች ነበሩ። የጣዖት አማልክት አምልኮ፣ ኮከብ ቆጠራና በአንዳንድ ወቅት ደግሞ አስጸያፊ የፆታ ብልግናና ልጆችን በጭካኔ መሥዋዕት አድርጎ ማቅረብን የሚጨምር የአምልኮ ሥርዓት ነበራቸው። የእስራኤላውያን ጎረቤት አገሮች ብዙ ልጆች ለመውለድ፣ ብዙ ምርት ለመሰብሰብና በጦርነት ድል ለማግኘት አማልክቶቻቸውን ይለማመኑ ነበር።
10 ይሖዋ የተባለውን አንድ አምላክ የሚያመልኩት እስራኤላውያን ብቻ ነበሩ። ሕጎቹን ከታዘዙ ብዙ ልጆችን፣ የተትረፈረፈ ምርትና ከጠላቶቻቸው እረፍትን በመስጠት እንደሚባርካቸው ቃል ገብቶላቸው ነበር። (ዘዳግም 28:1-14) የሚያሳዝነው ግን በእስራኤል የሚኖሩ በርካታ ሰዎች ሕጉን ሳይጠብቁ ቀርተዋል። በይሖዋ መንገድ የተመላለሱት ደግሞ የታማኝነት አቋም በመያዛቸው ምክንያት ብዙ መከራ ተቀብለዋል። እንዲያውም አንዳንዶቹ በአገራቸው ሰዎች ተሠቃይተዋል፣ መዘበቻ ሆነዋል፣ ተገርፈዋል፣ ታስረዋል፣ በድንጋይ ተወግረዋል ከዚያም አልፎ ተገድለዋል። (ሥራ 7:51, 52፤ ዕብራውያን 11:35-38) ይህ ለታመኑት እስራኤላውያን ከባድ ፈተና ነበር! ይሁን እንጂ ብዙዎች ከይሖዋ መንገድ አፈንግጠው የወጡት ለምን ነበር? ከእስራኤላውያን ታሪክ መካከል ሁለት ምሳሌዎች መመልከታችን የነበራቸውን የተሳሳተ አስተሳሰብ እንድናስተውል ይረዳናል።
የአካዝ መጥፎ ምሳሌነት
11, 12. (ሀ) አካዝ ሶርያውያን ባስጨነቁት ጊዜ ምን ለማድረግ ፈቃደኛ ሳይሆን ቀረ? (ለ) አካዝ ደህንነት ለማግኘት የሞከረው ከየትኞቹ ሁለት ምንጮች ነበር?
11 አካዝ በስምንተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ ደቡባዊውን የይሁዳ መንግሥት ይገዛ የነበረ ንጉሥ ነው። የግዛት ዘመኑ ሰላም የሰፈነበት አልነበረም። በአንድ ወቅት ሶርያ እና ሰሜናዊው የእስራኤል መንግሥት ግንባር ፈጥረው ሊወጉት በመጡ ጊዜ “የእርሱም ልብ የሕዝቡም ልብ . . . ተናወጠ።” (ኢሳይያስ 7:1, 2) ይሁን እንጂ ይሖዋ ሊረዳው በፈለገበትና እንዲፈትነው ግብዣ ባቀረበለት ጊዜ አካዝ ግትር አቋም በመያዝ አሻፈረኝ አለ! (ኢሳይያስ 7:10-12) በዚህም የተነሳ ይሁዳ በጦርነቱ ተሸንፋ ከፍተኛ ጉዳት ደረሰባት።—2 ዜና መዋዕል 28:1-8
12 አካዝ ይሖዋን ለመፈተን እምቢ ይበል እንጂ የአሦር ንጉሥ እንዲረዳው መጠየቁ አልቀረም። በዚህም ጊዜ ቢሆን ይሁዳ ጎረቤት አገሮች ከሚሰነዝሩባት ጥቃት ልታመልጥ አልቻለችም። አሦር ራሱ በአካዝ ላይ ተነስቶ ‘ባስጨነቀው’ ጊዜ ንጉሡ “ለመቱትም ለደማስቆ አማልክት:- የሶርያን ነገሥታት አማልክት ረድተዋቸዋልና እኔን ይረዱ ዘንድ እሠዋላቸዋለሁ ብሎ ሠዋላቸው።”—2 ዜና መዋዕል 28:20, 23
13. አካዝ ወደ ሶርያውያን አማልክት ዞር ማለቱ ምን ያሳያል?
13 ከጊዜ በኋላ ይሖዋ “የሚረባህን ነገር የማስተምርህ በምትሄድባትም መንገድ የምመራህ አምላክህ እግዚአብሔር ነኝ። ትእዛዜን ብትሰማ ኖሮ፣ ሰላምህ እንደ ወንዝ ጽድቅህም እንደ ባሕር ሞገድ በሆነ ነበር” በማለት ለእስራኤላውያን ተናግሯል። (ኢሳይያስ 48:17, 18) አካዝ ፊቱን ወደ ሶርያ አማልክት ማዞሩ ‘ሊሄድበት ከሚገባው መንገድ’ ምን ያህል እንደ ራቀ የሚያሳይ ነው። ከይሖዋ ሳይሆን ከሐሰት የደህንነት ምንጫቸው እርዳታ ለማግኘት በመጣር በአሕዛብ አስተሳሰብ ሙሉ በሙሉ ተታልሎ ነበር።
14. አካዝ ወደ ሐሰት አማልክት ዞር ለማለት ምንም ሰበብ ሊያቀርብ የማይችለው ለምንድን ነው?
14 የሶርያ አማልክትን ጨምሮ አሕዛብ የሚያመልኳቸው አማልክት ምንም ነገር መፈየድ የማይችሉ ‘ዋጋ ቢስ’ መሆናቸው የታየው ከብዙ ጊዜ በፊት ነበር። (ኢሳይያስ 2:8 NW) ቀደም ሲል በንጉሥ ዳዊት የግዛት ዘመን ሶርያውያን የዳዊት ገባሮች በሆኑ ጊዜ ይሖዋ ከሶርያውያን አማልክት እጅግ የላቀ እንደሆነ በግልጽ ታይቷል። (1 ዜና መዋዕል 18:5, 6) እውነተኛ ደህንነት ሊሰጥ የሚችለው “የአማልክት አምላክ የጌቶችም ጌታ፣ ታላቅ አምላክ ኃያልም የሚያስፈራም” የሆነው ይሖዋ ብቻ ነው። (ዘዳግም 10:16, 17) ሆኖም አካዝ ደህንነት ለማግኘት ፊቱን ወደ አሕዛብ አማልክት በመመለስ ለይሖዋ ጀርባውን ሰጥቷል። በመጨረሻ ግን ይህ ሁኔታ በይሁዳ ላይ ጥፋት አስከትሏል።—2 ዜና መዋዕል 28:24, 25
አይሁዳውያን ኤርምያስን ይዘው ወደ ግብፅ በሄዱበት ጊዜ
15. በኤርምያስ ዘመን በግብፅ ምድር የነበሩት አይሁዳውያን ኃጢአት የሠሩት በምን መንገድ ነው?
15 ሕዝቡ የለየለት ከሃዲ በሆነ ጊዜ ይሖዋ በ607 ከዘአበ ባቢሎናውያን ኢየሩሳሌምንና ቤተ መቅደሷን እንዲያጠፉ ፈቀደላቸው። አብዛኛው ሕዝብ በግዞት ወደ ባቢሎን ተወሰደ። ሆኖም ነቢዩ ኤርምያስን ጨምሮ አንዳንዶች እዛው አገራቸው ቀርተው ነበር። ገዥው ጎዶልያስ በተገደለ ጊዜ ግን ይህ ቡድን ኤርምያስን ይዞ ወደ ግብፅ ኮበለለ። (2 ነገሥት 25:22-26፤ ኤርምያስ 43:5-7) እዚያም ለሐሰት አማልክት መሥዋዕት ማቅረብ ጀመሩ። ኤርምያስ እነዚህ ታማኝ ያልሆኑ አይሁዳውያን የሚሠሩት ሥራ ልክ አለመሆኑን አጥብቆ ቢነግራቸውም ግትሮች ሆኑ። ወደ ይሖዋ ለመመለስ አሻፈረን በማለት “ለሰማይ ንግሥት” ማጠናቸውን እንደሚቀጥሉ ገለጹ። ለምን? ምክንያቱም እነርሱም ሆኑ አባቶቻቸው ‘በይሁዳ ከተሞችና በኢየሩሳሌም አደባባዮች ይህን ያደርጉ በነበረበት ወቅት እንጀራ ይጠግቡና መልካምም ይሆንላቸው እንደነበረ እንዲሁም ክፉም ከቶ እንዳላዩ’ አድርገው በማሰባቸው ነው። (ኤርምያስ 44:16, 17) በተጨማሪም አይሁዳውያን “ለሰማይ ንግሥት ማጠንን ለእርስዋም የመጠጥን ቁርባን ማፍሰስን ከተውን ወዲህ ግን፣ እኛ በሁሉ ነገር ተቸግረናል፣ በሰይፍና በራብ አልቀናል” ብለው እስከ መናገር ደርሰው ነበር።—ኤርምያስ 44:18
16. በግብፅ የነበሩት አይሁዶች ፈጽሞ የተሳሳተ አስተሳሰብ ነበራቸው የምንለው ለምንድን ነው?
16 አይሁዳውያን የሚያስታውሱት ይህን ብቻ መሆኑ የሚያስገርም ነው! ሐቁ ግን ምን ነበር? አይሁዳውያን ይሖዋ በሰጣቸው ምድር ላይ ለሐሰት አማልክት መሠዋታቸው እውነት ነው። አንዳንዴም በአካዝ ዘመን እንደሆነው ሁሉ የፈጸሙት ክህደት ሥቃይ ያስከትልባቸው ነበር። ይሁን እንጂ ይሖዋ የቃል ኪዳን ሕዝቡን ‘በትዕግሥት’ ይዟቸው ነበር። (ዘጸአት 34:6፤ መዝሙር 86:15) ንሥሐ እንዲገቡ ለማነሳሳት ሲል ነቢያቱን ልኮላቸዋል። አንዳንዴ ንጉሡ ታማኝ በሚሆንበት ጊዜ ይሖዋ ይባርከዋል፤ በዚህም የተነሳ ምንም እንኳ አብዛኛው ሰው ታማኝ ባይሆንም ሕዝቡ ከዚያ በረከት ተጠቃሚ ይሆን ነበር። (2 ዜና መዋዕል 20:29-33፤ 27:1-6) እነዚያ በግብፅ የነበሩ አይሁዳውያን በትውልድ አገራቸው ያገኟቸው የነበሩት ብልጽግናዎች ከሐሰት አማልክቶቻቸው የመጡ እንደሆኑ አድርገው መናገራቸው ትልቅ ስህተት ነበር!
17. ይሁዳ ምድሯንና ቤተ መቅደሷን ያጣችው ለምን ነበር?
17 ይሖዋ 607 ከዘአበ ከመድረሱ አስቀድሞ ለአይሁዳውያን የሚከተለውን ማሳሰቢያ ሰጥቷቸው ነበር:- “ቃሌን ስሙ፣ እኔም አምላክ እሆናችኋለሁ እናንተም ሕዝብ ትሆኑኛላችሁ መልካምም ይሆንላችሁ ዘንድ ባዘዝኋችሁ መንገድ ሁሉ ሂዱ።” (ኤርምያስ 7:23) አይሁዳውያን ‘ይሖዋ ባዘዛቸው መንገድ ሁሉ ሳይሄዱ’ በመቅረታቸው ቤተ መቅደሳቸውንና ምድራቸውን ሙሉ በሙሉ አጥተዋል። እንዲህ ያለ የጥፋት አካሄድ እንዳንከተል እንጠንቀቅ።
ይሖዋ በመንገዱ የሚመላለሱትን ይባርካቸዋል
18. በይሖዋ መንገድ የሚመላለሱ ሁሉ ምን ማድረግ ይገባቸዋል?
18 እንደ ቀድሞው ሁሉ ዛሬም በይሖዋ መንገድ ለመመላለስ ታማኝ መሆን ማለትም እርሱን ብቻ ለማገልገል ቁርጥ ውሳኔ ማድረግ ይጠይቃል። በይሖዋ ላይ መታመን ማለትም ይሖዋ የሰጠው ተስፋ እምነት የሚጣልበት እንደሆነና ፍጻሜውን እንደሚያገኝ ሙሉ በሙሉ ማመን ይጠይቃል። በይሖዋ መንገድ ለመመላለስ ወደ ግራ ወይም ወደ ቀኝ ሳይሉ ሕግጋቱን በመከተልና ከፍተኛ የአቋም ደረጃዎቹን በመጠበቅ መታዘዝ ይጠይቃል። “እግዚአብሔር ጻድቅ ነውና፣ ጽድቅንም ይወድዳል።”—መዝሙር 11:7
19. በዛሬው ጊዜ የሚኖሩ በርካታ ሰዎች የትኞቹን አማልክት ያመልካሉ? ከምንስ ውጤት ጋር?
19 አካዝ ደህንነት ለማግኘት ፊቱን ያዞረው ወደ ሶርያውያን አማልክት ነበር። ወደ ግብፅ የወረዱት እስራኤላውያንም ‘የሰማይ ንግሥት’ ተብላ የምትታወቀው በጥንቱ የመካከለኛው ምሥራቅ በስፋት የምትመለከው የሴት አምላክ ቁሳዊ ብልጽግና ታመጣልናለች ብለው ተስፋ አድርገው ነበር። በዛሬው ጊዜ ያሉት አብዛኞቹ አማልክት ቃል በቃል ጣዖታት አይደሉም። ኢየሱስ ከይሖዋ ይልቅ ‘ለገንዘብ’ መገዛትን አውግዞ ተናግሯል። (ማቴዎስ 6:24) ሐዋርያው ጳውሎስ ‘ጣዖትን ማምለክ ስለሆነው ስለ መጎምጀት’ ተናግሯል። (ቆላስይስ 3:5) “ሆዳቸው አምላካቸው” ስለሆነ ሰዎችም ተናግሯል። (ፊልጵስዩስ 3:19) አዎን፣ በዛሬው ጊዜ በዋነኛነት ከሚመለኩት አማልክት መካከል ገንዘብና ቁሳዊ ነገሮች ይገኙበታል። እንደ እውነቱ ከሆነ ሃይማኖታዊ ዝንባሌ ያላቸው ሰዎችንም ጨምሮ በርካታ ሰዎች ‘ተስፋቸውን የጣሉት በሚያልፍ ባለ ጠግነት’ ላይ ነው። (1 ጢሞቴዎስ 6:17) ብዙዎች ላባቸው ጠብ እስኪል ድረስ በመሥራት እነዚህን አማልክት ያገለግሏቸዋል። አንዳንዶች ምርጥ በተባሉ ቤቶች ውስጥ በመኖር፣ ውድ የሆኑ ነገሮች በማካበትና የቅንጦት ምግቦች በመመገብ የልፋታቸውን ዋጋ አግኝተዋል። ይሁን እንጂ እንዲህ ያለው የተንደላቀቀ ኑሮ ያላቸው ሁሉም አይደሉም። እንዲህ የመሰለው ኑሮ ያላቸውም ቢሆኑ ውለው አድረው እነዚህ ነገሮች በራሳቸው እርካታ እንደማያመጡ ይገነዘባሉ። እንዲህ ያለው ኑሮ አስተማማኝ ያልሆነ፣ ጊዜያዊና መንፈሳዊ ፍላጎቶችን የማያሟላ ነው።—ማቴዎስ 5:3
20. ሚዛናችንን መጠበቅ ያለብን እንዴት ነው?
20 እውነት ነው፣ በዚህ የነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ ላይ ስንኖር ሚዛናዊ መሆን ይኖርብናል። የቤተሰቦቻችንን ቁሳዊ ፍላጎቶች ለማሟላት ምክንያታዊ የሆኑ እርምጃዎች መውሰድ ይኖርብናል። ይሁን እንጂ አምላክን ከማገልገል ይልቅ ለከፍተኛ የኑሮ ደረጃ፣ ለገንዘብ ወይም ለሌሎች ተመሳሳይ ነገሮች ትልቅ ግምት የምንሰጥ ከሆነ በአንድ ዓይነት የጣዖት አምልኮ የተጠላለፍን ከመሆኑም በላይ በይሖዋ መንገድ መመላለሳችንን አቁመናል ማለት ነው። (1 ጢሞቴዎስ 6:9, 10) ይሁን እንጂ የጤንነት፣ የገንዘብ ወይም ሌላ ዓይነት ችግር ቢደርስብንስ? አምላክን በማገልገላቸው ምክንያት ችግር ውስጥ እንደገቡ ሆኖ የተሰማቸውን በግብፅ የነበሩትን አይሁዳውያን አንምሰል። ከዚህ ይልቅ ከአካዝ በተለየ መልኩ ይሖዋን እንፈትነው። በታማኝነት ከይሖዋ አምላክ መመሪያ ለማግኘት ጣሩ። ምንም ሳትጠራጠሩ መመሪያዎቹን በሥራ ላይ አውሉ፤ እንዲሁም የሚገጥማችሁን ማንኛውንም ዓይነት ሁኔታ መወጣት የሚያስችላችሁን ጥንካሬና ጥበብ እንዲሰጣችሁ ጸልዩ። ከዚያም በልበ ሙሉነት የይሖዋን በረከት ተጠባበቁ።
21. በይሖዋ መንገድ የሚመላለሱ ሁሉ ምን በረከቶች ያገኛሉ?
21 መላው የእስራኤል ታሪክ እንደሚያሳየው ይሖዋ በመንገዱ የተመላለሱትን ሁሉ አትረፍርፎ ባርኳቸዋል። ንጉሥ ዳዊት “አቤቱ፣ ስለ ጠላቶቼ በጽድቅህ ምራኝ” በማለት ዘምሯል። (መዝሙር 5:8) ይሖዋ ከጊዜ በኋላ አካዝን ባስጨነቁት አጎራባች ብሔራት ላይ ወታደራዊ ድል አጎናጽፎት ነበር። በግብፅ የነበሩት አይሁዳውያን የተመኙትን ሰላምና ብልጽግና ቀደም ሲል በሰሎሞን ግዛት ዘመን የነበሩት እስራኤላውያን አግኝተውት ነበር። ይሖዋ የአካዝ ልጅ ሕዝቅያስ ኃያል በሆነው በአሦር ላይ ሳይቀር ድል እንዲቀዳጅ አድርጎታል። (ኢሳይያስ 59:1) አዎን፣ ‘በኃጢአተኞች መንገድ’ ላይ ከመቆም ይልቅ በአምላክ ሕግ ደስ ይላቸው ለነበሩት ታማኝ ሰዎች የይሖዋ እጅ አላጠረም። (መዝሙር 1:1, 2) ዛሬም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። ታዲያ በዛሬው ጊዜ የምንኖረው እኛ በይሖዋ መንገድ ላይ እየተመላለስን እንዳለን እርግጠኞች መሆን የምንችለው እንዴት ነው? ይህ በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ይብራራል።
ታስታውሳለህን?
◻ በይሖዋ መንገድ መመላለስ እንድንችል የትኞቹ ባሕርያት ያስፈልጉናል?
◻ የአካዝ አስተሳሰብ ትክክል ያልነበረው ለምንድን ነው?
◻ በግብፅ የነበሩት አይሁዳውያን አስተሳሰብ ስህተት የነበረው ለምንድን ነው?
◻ በይሖዋ መንገድ ለመመላለስ ያደረግነውን ቁርጥ ውሳኔ ማጠናከር የምንችለው እንዴት ነው?
[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አካዝ እርዳታ ለማግኘት የሞከረው ከይሖዋ ሳይሆን ከሶርያውያን አማልክት ነበር