የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w99 5/15 ገጽ 15-20
  • በይሖዋ መንገድ መመላለሳችሁን ቀጥሉ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • በይሖዋ መንገድ መመላለሳችሁን ቀጥሉ
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1999
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • በይሖዋ ላይ የመታመንና ለእርሱ ታማኝ የመሆን አስፈላጊነት
  • በአምላክ መንገድ ለመመላለስ የሚያስችል እርዳታ
  • የአቋም መግለጫ
  • ‘አምላክ ከእኛ ጋር ነው’
  • ከአምላክ ጋር ትሄዳለህ?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2005
  • አካሄድን ከአምላክ ጋር ማድረግ —የመጀመሪያዎቹ እርምጃዎች
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1998
  • በእምነት እንጂ በማየት አትመላለሱ!
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2005
  • አካሄዳችሁን ከአምላክ ጋር አድርጉ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1998
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1999
w99 5/15 ገጽ 15-20

በይሖዋ መንገድ መመላለሳችሁን ቀጥሉ

“እግዚአብሔርን ደጅ ጥና፣ መንገዱንም ጠብቅ፣ ምድርንም ትወርስ ዘንድ ከፍ ከፍ ያደርግሃል።”​—⁠መዝሙር 37:​34

1, 2. ንጉሥ ዳዊት በይሖዋ መንገድ ለመመላለስ ምን ማድረግ አስፈልጎት ነበር? በዛሬው ጊዜ የምንኖረው እኛስ ምን እንድናደርግ ይጠይቅብናል?

“ነፍሴን ወደ አንተ አንሥቻለሁና የምሄድበትን መንገድ አስታውቀኝ።” (መዝሙር 143:​8) በዛሬው ጊዜ የሚኖሩ ክርስቲያኖች ንጉሥ ዳዊት የተናገራቸውን እነዚህን ቃላት ከልብ በመነጨ ስሜት ያስተጋባሉ። ይሖዋን ለማስደሰትና በመንገዱ ለመመላለስ ልባዊ ፍላጎት አላቸው። ይሁን እንጂ ይህ ምን ማድረግን ያጠቃልላል? ይህ ለዳዊት የአምላክን ሕግ መጠበቅ ማለት ነበር። ከብሔራት ጋር ከመወዳጀት ይልቅ በይሖዋ ላይ መታመን ማለት ነበር። አዎን፣ የጎረቤት አገር ሕዝቦችን አማልክት ሳይሆን ይሖዋን በታማኝነት ማገልገል ማለት ነበር። ለክርስቲያኖች ደግሞ በይሖዋ መንገድ መመላለስ ከዚህ የበለጡ ነገሮችን ይጨምራል።

2 አንደኛ ነገር፣ በዛሬው ጊዜ በይሖዋ መንገድ መመላለስ ማለት ኢየሱስ ክርስቶስ “መንገድና እውነት ሕይወትም” መሆኑን አምኖ በመቀበል በቤዛዊ መሥዋዕቱ ማመን ማለት ነው። (ዮሐንስ 3:​16፤ 14:​6፤ ዕብራውያን 5:​9) በተጨማሪም አንዱ ለሌላው በተለይ ደግሞ ለኢየሱስ ቅቡዓን ወንድሞች ፍቅር በማሳየት ‘የክርስቶስን ሕግ’ መፈጸም ማለት ነው። (ገላትያ 6:​2፤ ማቴዎስ 25:​34-40) በይሖዋ መንገድ የሚመላለሱ የእርሱን መሠረታዊ ሥርዓቶችና ትእዛዞች ይወድዳሉ። (መዝሙር 119:​97፤ ምሳሌ 4:​5, 6) በክርስቲያናዊ አገልግሎት የመካፈል ውድ መብታቸውን ከፍ አድርገው ይመለከቱታል። (ቆላስይስ 4:​17፤ 2 ጢሞቴዎስ 4:​5) ጸሎት የሕይወታቸው ቋሚ ክፍል ነው። (ሮሜ 12:​12) እንዲሁም ‘ጥበብ እንደሌላቸው ሳይሆን እንደ ጥበበኞች በመሆን ለአካሄዳቸው ይጠነቀቃሉ።’ (ኤፌሶን 5:​15) ቁሳዊ ሃብት ለሚሰጠው ጊዜያዊ ጥቅም ወይም ሕገ ወጥ ለሆነ ሥጋዊ ደስታ ሲሉ መንፈሳዊ ሃብታቸውን ፈጽሞ መሥዋዕት አያደርጉም። (ማቴዎስ 6:​19, 20፤ 1 ዮሐንስ 2:​15-17) ከዚህም በላይ በታማኝነት ከይሖዋ ጎን መቆምና በእርሱ መታመን እጅግ አስፈላጊ ነው። (2 ቆሮንቶስ 1:​9፤ 10:​5፤ ኤፌሶን 4:​24) ለምን? ይህ የሆነበት ምክንያት ያለንበት ሁኔታ በጥንት ጊዜ ከነበሩት እስራኤላውያን ጋር በጣም ተመሳሳይ በመሆኑ ነው።

በይሖዋ ላይ የመታመንና ለእርሱ ታማኝ የመሆን አስፈላጊነት

3. ታማኝነት፣ እምነትና ትምክህት በይሖዋ መንገድ መመላለሳችንን እንድንቀጥል የሚረዱን እንዴት ነው?

3 እስራኤል ልቅ በሆኑ የጣዖት አምልኮ ሥነ ሥርዓቶች ላይ በሚካፈሉና የጠላትነት ስሜት ባላቸው ጎረቤት አገሮች ተከቦ የሚኖር አነስተኛ ሕዝብ ነበር። (1 ዜና መዋዕል 16:​26) እውነተኛውንና በዓይን የማይታየውን አምላክ ይሖዋን ያገለግል የነበረው እስራኤል ብቻ ሲሆን እርሱም ከፍተኛ የሥነ ምግባር አቋሞችን አክብረው እንዲኖሩ ይጠብቅባቸው ነበር። (ዘዳግም 6:​4) በተመሳሳይም በዛሬው ጊዜ ይሖዋን የሚያመልኩት ሰዎች በጥቂት ሚልዮን የሚቆጠሩ ሲሆኑ ከእነርሱ የተለየ የአቋም ደረጃና ሃይማኖታዊ አመለካከት ያላቸውን ወደ ስድስት ቢልዮን የሚጠጉ ሰዎች ባቀፈ ዓለም ውስጥ ይኖራሉ። በእነዚህ በጥቂት ሚልዮን በሚቆጠሩ ሰዎች መካከል የምንገኝ ከሆነ በዓለም መጥፎ ተጽዕኖዎች እንዳንሸነፍ መጠንቀቅ ይገባናል። እንዴት? በታማኝነት ከይሖዋ አምላክ ጎን በመቆም፣ በእርሱ በማመንና የገባቸውን ተስፋዎች እንደሚፈጽም በመተማመን ነው። (ዕብራውያን 11:​6) ይህም ዓለም ተስፋ በሚያደርጋቸው ነገሮች ላይ እምነታችንን ከመጣል ይጠብቀናል።​—⁠ምሳሌ 20:​22፤ 1 ጢሞቴዎስ 6:​17

4. አሕዛብ ‘ልባቸው ሊጨልም’ የቻለው ለምንድን ነው?

4 ሐዋርያው ጳውሎስ እንደሚከተለው ብሎ በጻፈ ጊዜ ክርስቲያኖች ምን ያህል ከዓለም የተለዩ መሆን እንዳለባቸው አመልክቷል:- “እንግዲህ አሕዛብ ደግሞ በአእምሮአቸው ከንቱነት እንደሚመላለሱ ከእንግዲህ ወዲህ እንዳትመላለሱ እላለሁ በጌታም ሆኜ እመሰክራለሁ። እነርሱ ባለማወቃቸው ጠንቅ በልባቸውም ደንዳንነት ጠንቅ ልቡናቸው ጨለመ፣ ከእግዚአብሔርም ሕይወት ራቁ።” (ኤፌሶን 4:​17, 18) ኢየሱስ “እውነተኛው ብርሃን” ነው። (ዮሐንስ 1:​9) እርሱን የማይቀበሉ ወይም በእርሱ አምናለሁ እያሉ ‘ለክርስቶስ ሕግ’ የማይታዘዙ ሁሉ ‘ልቡናቸው ጨልሟል።’ በይሖዋ መንገድ ከመመላለስ ይልቅ ‘ከእግዚአብሔር ሕይወት ርቀዋል።’ በዓለማዊ መንገድ ምንም ያህል ጠቢብ እንደሆኑ አድርገው ሊያስቡ ቢችሉም ይሖዋ አምላክንና ኢየሱስ ክርስቶስን በማወቅ የዘላለም ሕይወት የሚያስገኘውን ብቸኛ እውቀት ‘የማያውቁ’ ናቸው።​—⁠ዮሐንስ 17:​3፤ 1 ቆሮንቶስ 3:​19

5. የእውነት ብርሃን በዓለም ዙሪያ በማብራት ላይ ያለ ቢሆንም የብዙ ሰዎች ልብ ደንዳና የሆነው ለምንድን ነው?

5 ሆኖም የእውነት ብርሃን በዓለም ዙሪያ በማብራት ላይ ይገኛል! (መዝሙር 43:​3፤ ፊልጵስዩስ 2:​15) “ጥበብ በጎዳና ትጮኻለች።” (ምሳሌ 1:​20) ባለፈው ዓመት የይሖዋ ምሥክሮች ስለ ይሖዋ አምላክና ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ለጎረቤቶቻቸው ለመንገር ከአንድ ቢልዮን የሚበልጥ ሰዓት አውለዋል። በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ጥሩ ምላሽ ሰጥተዋል። ታዲያ ሌሎች በርካታ ሰዎች ጥሩ ምላሽ ሳይሰጡ መቅረታቸው ሊያስደንቀን ይገባልን? በፍጹም። ጳውሎስ ‘ስለ ልባቸው ደንዳናነት’ ተናግሯል። አንዳንዶች ራስ ወዳዶች ወይም የገንዘብ ፍቅር የተጠናወታቸው በመሆናቸው ልባቸው ደንድኗል። ሌሎች ደግሞ የሐሰት ሃይማኖት ወይም በዛሬው ጊዜ ተስፋፍቶ የሚገኘው ዓለማዊ አመለካከት ተጽዕኖ አሳድሮባቸዋል። ብዙ ሰዎች በሕይወታቸው ውስጥ ያጋጠሟቸው አስቸጋሪ ሁኔታዎች ጀርባቸውን ለአምላክ እንዲሰጡ አድርገዋቸዋል። ሌሎች ደግሞ ይሖዋ ያወጣቸውን ከፍተኛ የሥነ ምግባር ደረጃዎች ለመጠበቅ አይፈልጉም። (ዮሐንስ 3:​20) በይሖዋ መንገድ እየተመላለሰ ያለ ሰው በእነዚህ አቅጣጫዎች ልቡ ሊደነድን ይችላልን?

6, 7. እስራኤላውያን የይሖዋ አምላኪዎች የነበሩ ቢሆኑም እንኳ በየትኞቹ ወቅቶች ላይ ተሳስተው ነበር? ለምንስ?

6 እንዲህ ያለው ሁኔታ በጥንቱ እስራኤል ላይ ደርሶ እንደነበር ሐዋርያው ጳውሎስ አመልክቷል። እንዲህ ሲል ጻፈ:- “እነዚህም ክፉ ነገር እንደ ተመኙ እኛ ደግሞ እንዳንመኝ ይህ ምሳሌ ሆነልን። ሕዝብም ሊበሉ ሊጠጡም ተቀመጡ ሊዘፍኑም ተነሡ ተብሎ እንደ ተጻፈ ከእነርሱ አንዳንዶቹ እንዳደረጉት ጣዖትን የምታመልኩ አትሁኑ። ከእነርሱም አንዳንዶቹ እንደ ሴሰኑ በአንድ ቀንም ሁለት እልፍ ከሦስት ሺህ እንደ ወደቁ አንሴስን።”​—⁠1 ቆሮንቶስ 10:​6-8

7 በመጀመሪያ ጳውሎስ እስራኤላውያን በሲና ተራራ ግርጌ የወርቅ ጥጃ ሠርተው ያመለኩበትን ወቅት ጠቀሰ። (ዘጸአት 32:​5, 6) ይህ ድርጊታቸው ከጥቂት ሳምንታት ቀደም ብሎ እንደሚታዘዙ ቃል የገቡትን አንድ መለኮታዊ ትእዛዝ በቀጥታ የሚጻረር ነበር። (ዘጸአት 20:​4-6፤ 24:​3) ከዚያም ጳውሎስ እስራኤላውያን ከሞአብ ሴቶች ጋር ለበኣል የሰገዱበትን ጊዜ ጠቀሰ። (ዘኁልቁ 25:​1-9) የጥጃ አምልኮ ፈንጠዝያ በሞላበት ‘ዘፈን’ የሚታጀብ ነው።a በበኣል አምልኮ ወቅት ደግሞ አስጸያፊ የፆታ ብልግና ይፈጸም ነበር። (ራእይ 2:​14) እስራኤላውያን እነዚህን ኃጢአቶች የፈጸሙት ለምን ነበር? ልባቸው ‘ክፉውን ነገር’ ማለትም የጣዖት አምልኮውንም ሆነ በጣዖት አምልኮው ወቅት የሚፈጸመውን ልቅ የብልግና ድርጊት ‘እንዲመኝ’ ስለፈቀዱለት ነው።

8. እስራኤላውያን ከገጠሟቸው ሁኔታዎች ምን ልንማር እንችላለን?

8 ጳውሎስ ከእነዚህ ታሪኮች ትምህርት መቅሰም እንዳለብን ጠቁሟል። የምንማረው ግን ምንድን ነው? አንድ ክርስቲያን ለአንድ የወርቅ ጥጃ ወይም ለጥንቱ የሞዓባውያን አምላክ እንደማይሰግድ የታወቀ ነው። ይሁን እንጂ ስለ ፆታ ብልግና ወይም ከልክ በላይ ለራስ ፍላጎት ተገዢ ስለመሆን ምን ለማለት ይቻላል? እነዚህ ነገሮች በአሁኑ ጊዜ የተለመዱ ሆነዋል። ልባችን እነዚህን ነገሮች እንዲመኝ ከፈቀድንለት ከይሖዋ ጋር ያራርቁናል። ውጤቱ ተመሳሳይ ነው። የጣዖት አምልኮ እንደፈጸምን ያህል ከአምላክ እንድንርቅ ያደርጉናል። (ከቆላስይስ 3:​5 እና ከፊልጵስዩስ 3:​19 ጋር አወዳድሩ።) ጳውሎስ በዚያን ወቅት ተከስተው ስለነበሩ ጉዳዮች የሰጠውን ማብራሪያ የደመደመው ለእምነት ባልደረቦቹ “ጣዖትን ከማምለክ ሽሹ” የሚል ማሳሰቢያ በመስጠት ነው።​—⁠1 ቆሮንቶስ 10:​14

በአምላክ መንገድ ለመመላለስ የሚያስችል እርዳታ

9. (ሀ) በይሖዋ መንገድ መመላለሳችንን እንድንቀጥል የሚያስችል ምን እርዳታ እናገኛለን? (ለ) ‘ከኋላችን ያለውን ቃል’ የምንሰማበት አንደኛው መንገድ ምንድን ነው?

9 በይሖዋ መንገድ መመላለሳችንን ለመቀጠል ቁርጥ ውሳኔ ካደረግን እርዳታ እናገኛለን። ኢሳይያስ “ወደ ቀኝም ወደ ግራም ፈቀቅ ብትል ጆሮችህ በኋላህ:- መንገዱ ይህች ናት በእርስዋም ሂድ የሚለውን ቃል ይሰማሉ” በማለት ተንብዮአል። (ኢሳይያስ 30:​21) ይሁን እንጂ ‘ጆሯችን ከኋላችን’ ያለውን “ቃል” የሚሰማው እንዴት ነው? በአሁኑ ጊዜ የአምላክን ድምፅ ቃል በቃል ሊሰማ የሚችል ወይም አምላክ በቀጥታ መልእክት የሚልክለት ሰው የለም። የሚሰማው “ቃል” ለሁላችንም የሚደርስበት መንገድ አንድ ነው። በአንደኛ ደረጃ ‘ቃሉ’ የሚመጣው አምላክ ሐሳቡን ባሰፈረባቸውና ከሰዎች ጋር ያደረገውን ግንኙነት አካትተው በያዙት በመንፈስ አነሳሽነት በተጻፉት ቅዱሳን ጽሑፎች ማለትም በመጽሐፍ ቅዱስ በኩል ነው። ‘ከአምላክ ሕይወት ከራቁ’ ምንጮች ለሚነዛው ፕሮፓጋንዳ በየዕለቱ የተጋለጥን እንደመሆናችን መጠን በመንፈሳዊ ጤናሞች ሆነን ለመኖር እንድንችል አዘውትረን መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብና ባነበብነው ነገር ላይ ማሰላሰል ይኖርብናል። ይህም ‘ከንቱ የሆኑ ነገሮችን’ እንድናስወግድና ‘ፍጹምና ለበጎ ሥራ ሁሉ የተዘጋጀን እንድንሆን’ ይረዳናል። (ሥራ 14:​14, 15፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:​16, 17) እንዲሁም ያጠነክረናል፣ ያጸናናል ‘መንገዳችንንም ያቀናልናል።’ (ኢያሱ 1:​7, 8) በዚህም የተነሳ የይሖዋ ቃል “አሁንም ልጆቼ ሆይ፣ ስሙኝ፤ መንገዴንም የሚጠብቁ ምስጉኖች ናቸው። ትምህርቴን ስሙ፣ ጠቢባንም ሁኑ፣ ቸል አትበሉትም” በማለት አጥብቆ ያሳስበናል።​—⁠ምሳሌ 8:​32, 33

10. ‘ከኋላችን ያለውን ቃል’ የምንሰማበት ሁለተኛው መንገድ ምንድን ነው?

10 ከዚህም በተጨማሪ ‘ከኋላችን ያለው ቃል’ ‘በጊዜው ምግብ በሚያቀርበው በታማኝና ልባም ባሪያ’ በኩል ይመጣል። (ማቴዎስ 24:​45-47) ይህ ምግብ የሚቀርብበት አንደኛው መንገድ ታትመው በሚወጡ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች ሲሆን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የዚህ ምግብ አቅርቦት በእጅጉ ጨምሯል። ለምሳሌ ያህል ስለ ትንቢቶች ያለን ግንዛቤ በመጠበቂያ ግንብ መጽሔት አማካኝነት የበለጠ ተሻሽሏል። የሰዎች ግዴለሽነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ያለ ቢሆንም በዚህ መጽሔት አማካኝነት በስብከቱና ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ እንድንጸና ማበረታቻ ይሰጠናል፤ ስውር ከሆኑ ወጥመዶች እንድንርቅ እርዳታ ይሰጠናል እንዲሁም መልካም ክርስቲያናዊ ባሕርያትን እንድናሳድግ ማሳሰቢያ ይሰጠናል። በተገቢው ጊዜ የሚቀርበውን እንዲህ ያለውን ምግብ እንደ ውድ ሀብት አድርገን እንቆጥረዋለን!

11. ‘ከኋላችን ያለውን ቃል’ የምንሰማበት ሦስተኛው መንገድ ምን እንደሆነ አብራራ።

11 ታማኝና ልባም ባሪያ ዘወትር በሚደረጉ ስብሰባዎች በኩልም ምግብ ያቀርብልናል። እነዚህ ስብሰባዎች የጉባኤ ስብሰባዎችን፣ በዓመት ሁለት ጊዜ የሚደረጉ የወረዳና የልዩ ስብሰባ ቀናትን እንዲሁም በየዓመቱ የሚደረጉ ትላልቅ ስብሰባዎችን ያካተቱ ናቸው። እነዚህን ስብሰባዎች ከፍ አድርጎ የማይመለከት ታማኝ ክርስቲያን ይኖራልን? በይሖዋ መንገድ ላይ መመላለስ እንድንችል ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ። ብዙዎች በሥራ ወይም በትምህርት ቤት እምነታቸውን ከማይጋሩ ሰዎች ጋር በርካታ ሰዓታት ለማሳለፍ ስለሚገደዱ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ አዘውትረው መገኘታቸው ቃል በቃል ሕይወት የሚያድን ነው። ስብሰባዎች ‘ለፍቅርና ለመልካም ሥራዎች እንድንነቃቃ’ ጥሩ አጋጣሚ ይሰጡናል። (ዕብራውያን 10:​24) ወንድሞቻችንን ስለምንወዳቸው ከእነርሱ ጋር መሰብሰቡን እንወደዋለን።​—⁠መዝሙር 133:​1

12. የይሖዋ ምሥክሮች ምን ለማድረግ ቆርጠዋል? በቅርቡስ ይህን አቋማቸውን የገለጹት እንዴት ነበር?

12 በእነዚህ መንፈሳዊ ምግቦች በመጠናከር በዛሬው ጊዜ የሚገኙ ወደ ስድስት ሚልዮን የሚጠጉ ሰዎች በይሖዋ መንገድ እየተመላለሱ ሲሆን ሌሎች በሚልዮን የሚቆጠሩ ደግሞ በዚህ መንገድ ላይ እንዴት መመላለስ እንደሚችሉ ለመማር መጽሐፍ ቅዱስ በማጥናት ላይ ናቸው። በቢልዮን ከሚቆጠሩት የምድር ነዋሪዎች ጋር ሲወዳደር በጣም አነስተኛ ቁጥር ያላቸው መሆኑ ተስፋ እንዲቆርጡ ወይም እንዲዳከሙ አድርጓቸዋል? በጭራሽ! በታማኝነት የይሖዋን ፈቃድ በማድረግ ‘ከኋላቸው ያለውን ቃል’ በትኩረት መከታተላቸውን ለመቀጠል ቁርጥ ውሳኔ አድርገዋል። በ1998/99 “የአምላክ የሕይወት መንገድ” በሚል ጭብጥ በተካሄዱት የአውራጃና ብሔራት አቀፍ ስብሰባዎች ላይ የተገኙት ልዑካን ጠንካራ አቋማቸውን የሚገልጽ መግለጫ በማውጣት ይህን ውሳኔያቸውን በይፋ አሳውቀዋል። የአቋም መግለጫው ሙሉ ቃል ከዚህ ቀጥሎ ሰፍሯል።

የአቋም መግለጫ

13, 14. የይሖዋ ምሥክሮች የዓለምን ሁኔታ በተመለከተ በሐቅ ላይ የተመሠረተ ምን አመለካከት አላቸው?

13 “‘የአምላክ የሕይወት መንገድ’ በተባለው የአውራጃ ስብሰባ ላይ የተገኘን እኛ የይሖዋ ምሥክሮች የአምላክ መንገድ ከሁሉ የላቀ የሕይወት መንገድ እንደሆነ በሙሉ ልብ እንቀበላለን። ሆኖም አብዛኛው የሰው ልጅ ከዚህ የተለየ አቋም እንዳለው ተረድተናል። የሰው ዘር ማኅበረሰብ የተሻለ የሕይወት መንገድ ይሆናሉ ብሎ ያሰባቸውን የተለያዩ ንድፈ ሐሳቦች፣ ፍልስፍናዎችና ሃይማኖታዊ አስተሳሰቦች ሞክሯል። የሰውን ልጅ ታሪክና ዛሬ ያለውን የዓለም ሁኔታ በሐቀኝነት መለስ ብለን ስንመለከተው ግን በኤርምያስ 10:​23 ላይ የተነገሩት መለኮታዊ ቃላት እውነተኝነት ቁልጭ ብለው ይታያሉ:- ‘አቤቱ፣ የሰው መንገድ ከራሱ እንዳይደለ አውቃለሁ፣ አካሄዱንም ለማቅናት ከሚራመድ ሰው አይደለም።’

14 “በየዕለቱ የእነዚህን ቃላት እውነተኝነት የሚያረጋግጡ ተጨማሪ ማስረጃዎችን እንመለከታለን። አብዛኛው የሰው ዘር ማኅበረሰብ የአምላክን የሕይወት መንገድ ቸል ብሏል። ሰዎች ለእነርሱ ቀና መስሎ የታያቸውን ነገር ይከተላሉ። ይህ ደግሞ አሳዛኝ የሆኑ ውጤቶችን አስከትሏል:- የቤተሰብ ሕይወት መፈራረስ ልጆችን ያለ መመሪያ አስቀርቷቸዋል፤ ቁሳዊ ነገሮችን ያለገደብ ማሳደድ የከንቱነትና የተስፋ መቁረጥ ስሜት አሳጭዷል፤ ጭካኔ የተሞላበት ዓመፅና ወንጀል ለብዙ ሰዎች መቅሰፍት ምክንያት ሆኗል፤ የጎሳ ብጥብጦችና ጦርነቶች የብዙ ሰዎችን ሕይወት እንደ ቅጠል አርግፏል፤ የፆታ ብልግና በእጅጉ መስፋፋቱ የአባለዘር በሽታዎች እንደ ወረርሽኝ እንዲዛመቱ አድርጓል። እነዚህ የሰው ልጅ ደስታ፣ ሰላምና መረጋጋት ለማግኘት ያደረጋቸውን ሩጫዎች መና ካስቀሩት እጅግ በርካታ ውስብስብ ችግሮች መካከል ጥቂቶቹ ብቻ ናቸው።

15, 16. የአምላክን የሕይወት መንገድ በተመለከተ በአቋም መግለጫው ውስጥ ምን ቁርጥ ያለ አቋም ተገልጿል?

15 “የሰው ልጅ ከሚደርስበት አሳዛኝ መከራና አርማጌዶን (ራእይ 16:​14, 16) በመባል የሚታወቀው ‘ሁሉን ቻይ የሆነው የአምላክ ታላቅ የጦርነት ቀን’ ከመቅረቡ አንጻር እኛ የይሖዋ ምሥክሮች የሚከተለውን የአቋም መግለጫ አውጥተናል:-

16 “አንደኛ:- በግለሰብ ደረጃ ራሳችንን ለይሖዋ ያላንዳች ገደብ ወስነን የእርሱ ንብረቶች መሆናችንን እናምናለን፤ እንዲሁም ይሖዋ በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት ባደረገልን የቤዛ ዝግጅት እስከ መጨረሻው የማይናወጥ እምነት ይዘን እንቀጥላለን። የአምላክ ምሥክሮች በመሆንና በኢየሱስ ክርስቶስ አገዛዝ በኩል ለሚንጸባረቀው የይሖዋ ሉዓላዊነት ሙሉ በሙሉ ራሳችንን በማስገዛት በአምላክ የሕይወት መንገድ ለመጓዝ ቆርጠናል።

17, 18. የሥነ ምግባር ደረጃንና ክርስቲያናዊ ወንድማማችነትን በሚመለከት የይሖዋ ምሥክሮች ምን ዓይነት አቋም ይዘው ይኖራሉ?

17 “ሁለተኛ:- የመጽሐፍ ቅዱስን የላቁ መንፈሳዊና ሥነ ምግባራዊ ደረጃዎች የሙጥኝ ብለን መከተላችንን እንቀጥላለን። አሕዛብ በአእምሮአቸው ከንቱነት ከሚመላለሱበት ጎዳና ለመራቅ ቁርጥ ውሳኔ አድርገናል። (ኤፌሶን 4:​17-19) ከዚህ ዓለም እድፍ ራሳችንን ጠብቀን በይሖዋ ፊት ንጹህ ሆነን ለመኖር ቁርጥ ያለ አቋም ወስደናል።​—⁠ያዕቆብ 1:​27

18 “ሦስተኛ:- በዓለም አቀፍ ክርስቲያናዊ ወንድማማችነት ማኅበር የታቀፍን እንደመሆናችን መጠን ቅዱስ ጽሑፋዊ አቋማችንን አጥብቀን እንይዛለን። ከዘር፣ ከብሔር፣ ከጎሳ ጥላቻ ወይም መከፋፈል በመራቅ በመንግሥታት ዘንድ ክርስቲያናዊ ገለልተኝነታችንን እንጠብቃለን።

19, 20. (ሀ) ክርስቲያን ወላጆች ምን ያደርጋሉ? (ለ) ሁሉም ክርስቲያኖች የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት መሆናቸውን ማሳየት የሚቀጥሉት እንዴት ነው?

19 “አራተኛ:- እኛ ወላጆች የሆንን በልጆቻችን ልብ ውስጥ የአምላክን መንገድ እንተክላለን። ዘወትር መጽሐፍ ቅዱስን በማንበብ፣ የቤተሰብ ጥናት በማድረግና በሙሉ ልብ በክርስቲያን ጉባኤና በመስክ አገልግሎት በመካፈል በክርስቲያናዊ አኗኗር ምሳሌ እንሆናለን።

20 “አምስተኛ:- ሁላችንም ፈጣሪያችን በምሳሌነት የሚያንጸባርቃቸውን አምላካዊ ባሕርያት ለመኮትኮትና ኢየሱስ እንዳደረገው የእርሱን ባሕርያትና መንገዶች ለመኮረጅ ከልብ እንጥራለን። (ኤፌሶን 5:​1) ሁሉን ነገር በፍቅር በማድረግ የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት መሆናችንን ለማሳየት ቆርጠናል።​—⁠ዮሐንስ 13:​35

21-23. የይሖዋ ምሥክሮች ምን ማድረጋቸውን ይቀጥላሉ? በምን ነገርስ አጥብቀው ያምናሉ?

21 “ስድስተኛ:- ያለማሰለስ አዳዲስ ደቀ መዛሙርት ማፍራታችንንና የአምላክን መንግሥት ምሥራች ማወጃችንን እንቀጥላለን፤ ስለ አምላክ የሕይወት መንገድ እናስተምራቸዋለን እንዲሁም በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ተጨማሪ ሥልጠና እንዲያገኙ እናበረታታቸዋለን።​—⁠ማቴዎስ 24:​14፤ 28:​19, 20፤ ዕብራውያን 10:​24, 25

22 “ሰባተኛ:- በግለሰብ ደረጃም ሆነ በሃይማኖታዊ ድርጅት መልክ በሕይወታችን ውስጥ የአምላክን ፈቃድ በአንደኛ ቦታ ማስቀመጣችንን እንቀጥላለን። ቃሉን መጽሐፍ ቅዱስን እንደ መመሪያችን አድርገን በመጠቀም ወደ ቀኝ ወይም ወደ ግራ ሳንል ቀጥ ብለን በመሄድ የአምላክ መንገድ ከዓለም መንገድ እጅግ የላቀ መሆኑን እናረጋግጣለን። ዛሬም ሆነ ለዘላለም የአምላክን የሕይወት መንገድ በታማኝነት ያለማወላወል ለመከተል ቁርጥ ውሳኔ አድርገናል!

23 “ይህንን የአቋም መግለጫ ያወጣነው የአምላክን ፈቃድ የሚያደርግ ለዘላለም ይኖራል በሚለው ይሖዋ በሰጠን ፍቅራዊ ተስፋ ላይ ሙሉ ትምክህት ስላለን ነው። ይህንን የአቋም መግለጫ ያወጣነው ቅዱስ ጽሑፋዊ መሠረታዊ ሥርዓቶችን፣ ምክሮችንና ማሳሰቢያዎችን ተከትሎ መኖር በዛሬው ጊዜ የተሻለ ሕይወት ለመምራትና ወደፊትም እውነተኛውን ሕይወት አጥብቀን ለመያዝ እንችል ዘንድ መልካም መሠረት እንደሚጥልልን አጥብቀን ስለምናምን ነው። (1 ጢሞቴዎስ 6:​19፤ 2 ጢሞቴዎስ 4:​7, 8) ከሁሉም በላይ ይህን የአቋም መግለጫ ያወጣነው አምላካችንን ይሖዋን በሙሉ ልባችን፣ ነፍሳችን፣ ሐሳባችንና ኃይላችን ስለምንወድ ነው!

24, 25. ለቀረበው የአቋም መግለጫ የተሰጠው ምላሽ ምን ይመስል ነበር? በይሖዋ መንገድ የሚመላለሱት ሁሉ ምን ለማድረግ ቁርጥ ውሳኔ አድርገዋል?

24 “በዚህ ስብሰባ ላይ የተገኛችሁ ተሰብሳቢዎች ሁላችሁ ይህን መግለጫ የምትደግፉ ከሆነ እባካችሁ አዎን በማለት ምላሽ ስጡ!”

25 በስብሰባው ላይ የተገኙ ሁሉ በሚያስገመግም ድምፅ “አዎን!” በማለት ምላሽ ሲሰጡ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ በመቶዎች የሚቆጠሩ አዳራሾችና ስታዲየሞች በከፍተኛ ድምፅ አስተጋብተዋል። የይሖዋ ምሥክሮች በይሖዋ መንገድ መመላለሳቸውን እንደሚቀጥሉ ምንም ጥርጥር የለውም። ሙሉ በሙሉ በይሖዋ ላይ ይታመናሉ እንዲሁም የሰጣቸውን ተስፋዎች እንደሚፈጽም ያምናሉ። ምንም ይምጣ ምን በታማኝነት ከእርሱ ጎን ይቆማሉ። እንዲሁም ፈቃዱን ለመፈጸም ቁርጥ ውሳኔ አድርገዋል።

‘አምላክ ከእኛ ጋር ነው’

26. በይሖዋ መንገድ የሚመላለሱ ሰዎች በምን ዓይነት የሚያስደስት ሁኔታ ላይ ይገኛሉ?

26 የይሖዋ ምሥክሮች መዝሙራዊው “እግዚአብሔርን ደጅ ጥና፣ መንገዱንም ጠብቅ፣ ምድርንም ትወርስ ዘንድ ከፍ ከፍ ያደርግሃል” በማለት የሰጠውን ምክር ያስታውሳሉ። (መዝሙር 37:​34) ጳውሎስም የተናገራቸውን የሚያበረታቱ ቃላት አይረሱም:- “እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ከሆነ ማን ይቃወመናል? ለገዛ ልጁ ያልራራለት ነገር ግን ስለ ሁላችን አሳልፎ የሰጠው ያው ከእርሱ ጋር ደግሞ ሁሉን ነገር እንዲያው እንዴት አይሰጠንም?” (ሮሜ 8:​31, 32) አዎን፣ በይሖዋ መንገድ መመላለሳችንን ከቀጠልን ‘ለደስታችን ሁሉን ነገር አትረፍርፎ’ ይሰጠናል። (1 ጢሞቴዎስ 6:​17 NW) ውድ ከሆኑት ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ጋር እጅ ለእጅ ተያይዘን በይሖዋ መንገድ ከመጓዝ የተሻለ ምን ነገር ሊኖር ይችላል! ይሖዋ የወሰነው ጊዜ ሲደርስ የገባቸውን ተስፋዎች ሙሉ በሙሉ እንደሚፈጽም እርግጠኞች በመሆን ይሖዋ ከጎናችን ሆኖ በሚሰጠን ድጋፍ እየታገዝን በዚሁ መንገድ ላይ ለመጓዝና እስከ መጨረሻው ድረስ ለመጽናት ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ።​—⁠ቲቶ 1:​2

[የግርጌ ማስታወሻ]

a አንድ ተንታኝ እዚህ ላይ “ሊዘፍኑም ተነሱ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል በአረማውያን በዓላት ወቅት የነበረውን ጭፈራ የሚያመለክት እንደሆነ ገልጸው “በሰፊው እንደሚታወቀው አብዛኞቹ ጭፈራዎች ልቅ የጾታ ስሜት ለማነሳሳት የታለሙ ናቸው” በማለት አክለው ተናግረዋል።

ታስታውሳለህን?

◻ አንድ ክርስቲያን በይሖዋ መንገድ መመላለስ እንዲችል ምን ማድረግ ይጠበቅበታል?

◻ በይሖዋ ላይ የመታመንንና ለእርሱ ታማኝ የመሆንን ባሕርይ መኮትኮት የሚኖርብን ለምንድን ነው?

◻ በይሖዋ መንገድ ስንመላለስ ምን ዓይነት እርዳታ እናገኛለን?

◻ “የአምላክ የሕይወት መንገድ” በሚል ጭብጥ በተካሄዱት ስብሰባዎች ላይ ከወጣው የአቋም መግለጫ ውስጥ ጎላ ያሉ ጥቂት ነጥቦች ጥቀስ።

[በገጽ 18 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

“የአምላክ የሕይወት መንገድ” በሚል ጭብጥ በተካሄዱት የአውራጃና ብሔራት አቀፍ ስብሰባዎች ላይ በጣም አስፈላጊ የሆነ የአቋም መግለጫ ወጥቷል

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ