በይሖዋ ደስ ይበላችሁ ሐሤትም አድርጉ
አንድ ጠቃሚ የሆነ ውጥን በተሳካ ሁኔታ መጠናቀቁ ሁልጊዜም ለደስታ ምክንያት ይሆናል። በኒው ዮርክ፣ ፓተርሰን በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ የትምህርት ማዕከል መጋቢት 13, 1999 የተካሄደው የምረቃ ፕሮግራም ከጊልያድ የመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት ለተመረቁት ለ48ቱ የ106ኛው ክፍል ተማሪዎች ሁኔታው ተመሳሳይ እንደነበር የተረጋገጠ ነው።
የአስተዳደር አካል አባል፣ የጊልያድ የሰባተኛው ክፍል ምሩቅና የምረቃው ሥነ ሥርዓት ሊቀ መንበር የነበረው ቴዎዶር ጃራዝ በመክፈቻ ንግግሩ በመዝሙር 32:11 ላይ የሚገኙትን “ጻድቃን ሆይ፣ በእግዚአብሔር ደስ ይበላችሁ ሐሤትም አድርጉ” የሚሉትን ቃላት ጎላ አድርጎ ገልጿል። ሁሉም በዚህ ወቅት መደሰታቸው ተገቢ መሆኑን ሲያብራራ “እንዲህ በመሳሰሉ አጋጣሚዎች የምንደሰተው የጊልያድ ተማሪዎቻችንን ጨምሮ ይሖዋ ቅን ልብ ባላቸው ሰዎች አማካኝነት እያከናወነ ባለው ነገር ምክንያት ነው” ብሏል። ምንም እንኳ ተማሪዎቹ ወደ ጊልያድ ትምህርት ቤት ለመምጣትና ለሚስዮናዊ አገልግሎት ብቁ ለመሆን ከፍተኛ ጥረት ቢያደርጉም ሁሉም ነገር በተሳካ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ ያደረገው ይሖዋ ነው። (ምሳሌ 21:5፤ 27:1) ወንድም ጃራዝ ‘በይሖዋ የምንደሰትበት’ ምክንያት ይህ መሆኑን ጎላ አድርጎ ገልጿል።
በዚህ አስደሳች ክንውን ተካፋይ ለመሆን በፓተርሰን የመሰብሰቢያ አዳራሽ ከተሰበሰቡት መካከል ከ12 አገሮች የመጡ የተማሪዎቹ ቤተሰቦችና እንግዶቻቸው ይገኛሉ። በስልክ መስመርና በቪዲዮ አማካኝነት ዝግጅቱን ይከታተሉ የነበሩትን በብሩክሊን፣ በፓተርሰንና በዎልኪል የሚገኙትን የቤቴል ቤተሰብ አባላት ጨምሮ 5,198 የሚሆኑ ሰዎች ፕሮግራሙን በጉጉት ይጠባበቁ ስለነበር ደስተኛ መንፈስ እንደሚኖራቸው የተረጋገጠ ነው።
ደስተኛ መንፈስ ይዞ ስለመቀጠል የተሰጠ ማሳሰቢያ
ወንድም ጃራዝ የመክፈቻ ንግግሩን ካጠናቀቀ በኋላ ለጊልያድ ተመራቂዎች ብቻ ሳይሆን ፕሮግራሙን ለሚከታተሉት በሙሉ የሚጠቅሙ አበረታች ቅዱስ ጽሑፋዊ ማሳሰቢያዎችን ለማቅረብ ተዘጋጅተው የነበሩትን የመጀመሪያዎቹን አምስት ተናጋሪዎች አስተዋወቀ።
የመጀመሪያው ተናጋሪ የጊልያድ 34ኛ ክፍል ተመራቂ የነበረውና በአሁኑ ጊዜ ለአስተዳደር አካል የትምህርት ኮሚቴ ረዳት ሆኖ በማገልገል ላይ ያለው ዊልያም ማለንፎንት ነበር። መክብብ 1:2ን መሠረት ካደረገው “‘ሁሉም ነገር’ ከንቱ አይደለም!” ከሚለው የንግግሩ ጭብጥ ጋር በተያያዘ “ሰሎሞን ጭራሽ ሁሉም ነገር ከንቱ ነው ማለቱ ነበርን?” የሚል ጥያቄ አንስቶ ነበር። መልሱን ሲሰጥ “እንደዚያ ማለቱ አልነበረም። ከንቱ የተባሉት ነገሮች መለኮታዊውን ፈቃድ ወደ ጎን ገሸሽ የሚያደርጉ ሰብዓዊ ውጥኖችና ከመለኮታዊው ፈቃድ ጋር የሚቃረኑ ድርጊቶች ናቸው።” ከዚህ በተቃራኒ ግን እውነተኛውን አምላክ ይሖዋን ማምለክም ሆነ የአምላክ ቃል የሆነውን መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናትና ለሌሎችም ማስተማር ከንቱ ነገሮች አይደሉም። አገልጋዮቹ የሚያደርጓቸውን እነዚህን የመሳሰሉ ጥረቶች አምላክ አይረሳም። (ዕብራውያን 6:10) በአምላክ ፊት ሞገስ ያገኙ ሰዎች መከራ ቢደርስባቸውም እንኳ ሕይወታቸው ‘በይሖዋ ዘንድ ባለ የሕይወት ከረጢት እንደታሰረ’ ያክል ይሆናል። (1 ሳሙኤል 25:29 NW) ይህ እንዴት የሚያስደስት ነው! ሁሉም የይሖዋ አምላኪዎች እነዚህን ነጥቦች ማስታወሳቸው ደስተኛ መንፈስ ይዘው እንዲቀጥሉ ሊረዳቸው ይችላል።
የአስተዳደር አካል አባል የሆነው ጆን ባር “በሚስዮናዊ ምድባችሁ ደስታን አግኙ” በሚለው ንግግሩ ተመራቂዎቹን አበረታቷል። ሚስዮናዊ አገልግሎት ይሖዋ አምላክ ምንጊዜም ከፍ አድርጎ የሚመለከተው ነገር መሆኑን ገልጿል። “ይሖዋ ለዓለም ያለውን ፍቅር ከገለጸበት ነገር ጋር በጥብቅ የተሳሰረ ነው። አንድያ ልጁን ወደዚህ ምድር ልኮታል። ታላቁና ከሁሉ የላቀው ሚስዮናዊ ኢየሱስ ነበር።” ፈቃደኛ የሆኑ ሰዎች ሁሉ የኢየሱስ ሚስዮናዊ አገልግሎት ካስገኛቸው ጥቅሞች ተካፋይ ለመሆን የሚችሉበት አጋጣሚ ዛሬም ክፍት መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ተመራቂዎቹ ሚስዮናውያን ኢየሱስ በምድር ላይ የተሰጠውን የሥራ ምድብ በተሳካ ሁኔታ ማከናወን ምን ለውጥ ማድረግ እንደጠየቀበት በማሰላሰል ተጨማሪ ጥቅም ሊያገኙ ይችላሉ። ወንድም ባር ይህ የሆነበት ምክንያት ኢየሱስ የአምላክን ፈቃድ በማድረግ ስለሚደሰትና የሰው ልጆችንም ስለሚወድድ ነው ብሏል። (ምሳሌ 8:30, 31) ወንድም ባር የሥራ ምድባቸውን የሙጥኝ እንዲሉ ተመራቂዎቹን ያሳሰበ ሲሆን ይህን የሚያደርጉት ደግሞ መጽናት ስላለባቸው ብቻ ሳይሆን ይህን ማድረጋቸው ስለሚያስደስታቸው መሆን እንዳለበት ነግሯቸዋል። “በይሖዋ ታመኑ፤ እርሱም ይደግፋችኋል” በማለት የክፍሉን ተማሪዎች ተማጽኗል።—መዝሙር 55:22
ሌላው የአስተዳደር አካል አባል የሆነው ሎይድ ባሪ ለንግግሩ የመረጠው ጭብጥ “በይሖዋ ስም ለዘላለም መመላለስ” የሚል ነበር። ከጊልያድ 11ኛው ክፍል ከተመረቀ በኋላ ለ25 ዓመታት በጃፓን ሚስዮናዊ ሆኖ ያገለገለው ወንድም ባሪ ከቀደምት ሚስዮናውያን የተገኙ አንዳንድ ተሞክሮዎችን የተናገረ ሲሆን የገጠሟቸውንም ተፈታታኝ ሁኔታዎች ገልጿል። ተመራቂው ክፍል ተግባራዊ ሊያደርገው የሚችለው ምን ምክር ነበረው? “ከምንም ነገር በላይ መንፈሳዊነታችሁን ጠብቁ። በተጨማሪም ቋንቋውንና ባህሉን ተማሩ። ተጫዋቾች ለመሆን ሞክሩ። እንዲሁም በሥራችሁ ጽኑ፤ አትሰላቹ ወይም አትታክቱ።” ወንድም ባሪ ተመራቂዎቹ በሚመደቡባቸው አገሮች የተለያዩ አማልክትንና ጣዖታትን የሚያመልኩ ብዙ ሰዎችን እንደሚያገኙ ለተመራቂዎቹ ከነገራቸው በኋላ የሚከተሉትን የሚክያስ ቃላት አስታውሷቸዋል:- “ሕዝብም ሁሉ እያንዳንዱ በየአምላኩ ስም ይሄዳል፣ እኛም በአምላካችን በእግዚአብሔር ስም ለዘላለም እንሄዳለን።” (ሚክያስ 4:5) በእርግጥም የቀደምት ሚስዮናውያን ምሳሌ የአምላክ አገልጋዮች የሆኑ ሁሉ በይሖዋ ስም መመላለሳቸውንና እሱን በታማኝነት ማገልገላቸውን እንዲቀጥሉ የሚያነሳሳ ኃይል አለው።
በፕሮግራሙ መሠረት ቀጣዩን ንግግር ያቀረበው የጊልያድ አስተማሪ የሆነው ሎውረንስ ቦወን ነበር። የትምህርቱ ጭብጥ “ምን ዓይነት ሰዎች ትሆኑ ይሆን?” የሚለውን ጥያቄ ያነሳ ነበር። በአምላክ አገልግሎት ስኬታማ መሆናችን የተመካው በይሖዋ ላይ ባለን እምነትና ትምክህት መሆኑን ገልጿል። ንጉሥ አሳ ሙሉ በሙሉ በይሖዋ መመካቱ አንድ ሚልዮን ሠራዊት ባሰለፈ የጠላት ጦር ላይ ከፍተኛ ድል እንዲቀዳጅ አስችሎታል። ይሁንና ነቢዩ ዓዛርያስ ‘አንተ ከእግዚአብሔር ጋር ስትሆን እርሱ ከአንተ ጋር ነው’ በማለት በአምላክ ላይ መመካቱን እንዲቀጥል አሳስቦት ነበር። (2 ዜና መዋዕል 14:9-12፤ 15:1, 2) ይሖዋ የሚለው የአምላክ ስም ዓላማውን ለማስፈጸም መሆን የሚያስፈልገውን ሁሉ ይሆናል ማለት ሲሆን ይህ ደግሞ አስፈላጊ ሆኖ ካገኘው ሰጪ፣ ጠባቂ ወይም ሌላው ቀርቶ ፍርድ አስፈጻሚ የመሆን ችሎታውን የሚያሳይ በመሆኑ በይሖዋ ላይ የሚመኩና ከዓላማው ጋር ተስማምተው የሚሠሩ ሚስዮናውያን በምድባቸው ላይ ስኬታማ ሊሆኑ ይችላሉ። (ዘጸአት 3:14) ወንድም ቦወን ሲያጠቃልል “የይሖዋን ዓላማ ሥራዬ ብላችሁ ከያዛችሁ ሥራችሁን ለማከናወን የሚያስፈልገውን ሁሉ እንድትሆኑ ሊያደርጋችሁ እንደሚችል በፍጹም አትዘንጉ” ሲል ደምድሟል።
በዚህ ፕሮግራም ላይ የመጨረሻው ተናጋሪ የነበረው ቀደም ሲል ሚስዮናዊ በመሆን ያገለገለው በአሁኑ ጊዜ የትምህርት ቤቱ ሬጂስትራር ሆኖ የሚሠራው ዋላስ ሊቨረንስ ነበር። “የአምላክ ቃል በውስጣችሁ ሕያው እንዲሆንና እንዲሠራ አድርጉ” የሚል ርዕስ ያለው ንግግሩ ወደ ፍጻሜው በመገስገስ ላይ በሚገኘው መሬት ጠብ በማይለው መልእክቱ ወይም ተስፋው ላይ እንዲያተኩሩ አድርጓል። (ዕብራውያን 4:12) ፈቃደኛ በሆኑ ሰዎች ሕይወት ላይ በጎ ተጽእኖ ሊያሳድር ይችላል። (1 ተሰሎንቄ 2:13) ይህ ቃል በውስጣችን ሕያው ሊሆንና ሊሠራ የሚችለው እንዴት ነው? መጽሐፍ ቅዱስን በትጋት በማጥናት ነው። ወንድም ሊቨረንስ የአምላክን ቃል ማንበብን እንዲሁም የመልእክቱን መንፈስና ተግባራዊ የሚሆንበትን መንገድ ማብራራትን ጨምሮ በጊልያድ የተማሯቸውን መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት የሚረዱ ዘዴዎች ተመራቂዎቹን አስታውሷቸዋል። የአስተዳደር አካል አባልና ከዛሬ 50 ዓመት በፊት የጊልያድን ትምህርት ቤት ያቋቋመው ኮሚቴ ሊቀ መንበር ሆኖ ያገለገለውን የአልበርት ሽሮደርን ቃላት ጠቅሷል:- “አንድ ሰው ከጥቅሱ ዙሪያ ያለውን ሐሳብ በመጠቀም አምላክ በቃሉ አማካኝነት ያቀረበውን ሙሉና ትክክለኛ መንፈሳዊ ኃይል ሊያገኝ ይችላል።” መጽሐፍ ቅዱስን በዚህ መንገድ ማጥናት የአምላክን ቃል ሕያውና የሚሠራ እንደሆነ እንዲቀጥል ያደርገዋል።
አስደሳች ተሞክሮዎችና ቃለ ምልልሶች
ከንግግሮቹ ቀጥሎ አድማጮች ከተማሪዎቹ የተገኙ አስደሳች ተሞክሮዎችን አዳምጠዋል። ቀደም ሲል ሚስዮናዊ በነበረውና በአሁኑ ጊዜ የጊልያድ አስተማሪ በሆነው በማርክ ኑሜር መሪነት አንድ የተማሪዎች ቡድን በተለያዩ ሁኔታዎች ሥር ምሥክርነት ለመስጠት እንዴት እንደሚጥሩ የተናገሩ ሲሆን ሠርቶ ማሳያም አሳይተዋል። አንዳንዶች በክልሉ ውስጥ የሚገኙ ሰዎችን ሁኔታና ስሜት በመመልከት እንዲሁም በግል አሳቢነታቸውን በማሳየት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ለማስጀመርና ለማስጠናት ችለዋል። በመሆኑም ተማሪዎቹ ‘ለራሳቸውና ለማስተማር ሥራቸው ጥንቃቄ’ የሚያደርጉ ሲሆን ሌሎችም መዳንን እንዲያገኙ የመርዳት ጽኑ ፍላጎት ነበራቸው።—1 ጢሞቴዎስ 4:16
ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉ ብዙ ሐሳቦች የቀረቡ ሲሆን በመጠበቂያ ግንብ የትምህርት ማዕከል ለቅርንጫፍ ኮሚቴ አባላት የሚሰጠውን ማሰልጠኛ በመከታተል ላይ የሚገኙ ተሞክሮ ያካበቱ በርካታ ወንድሞች የሚስዮናዊ አገልግሎት አስደሳች መሆኑን የሚያረጋግጡ አስተያየቶች ሰጥተዋል። በዋናው መሥሪያ ቤት የሚሠሩት ወንድም ሳሙኤል ኸርድና ሮበርት ጆንሰን በቦሊቪያ፣ በዚምባብዌ፣ በኒካራጉዋ፣ በማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ፣ በዶሚኒካን ሪፐብሊክ፣ በፓፕዋ ኒው ጊኒና በካሜሩን ከሚገኙት የማኅበሩ ቅርንጫፍ ቢሮዎች ከመጡ ተወካዮች ጋር ደስ የሚል ቃለ ምልልስ አድርገው ነበር።
ከተሞክሮዎቹና ከቃለ ምልልሶቹ ቀጥሎ የጊልያድ የ41ኛው ክፍል ምሩቅና በአሁኑ ጊዜ የአስተዳደር አካል አባል የሆነው ጌሪት ሎሽ “‘የተወደዳችሁ’ ናችሁን?” በሚል ስሜት ቀስቃሽ ጭብጥ የመጨረሻውን ንግግር ሰጠ። ወንድም ሎሽ ፍጹም የሆነው የአምላክ ልጅ በሰዎች ዘንድ ተፈላጊ እንደሆነ ተደርጎ ከመቆጠር ይልቅ “የተናቀ ከሰውም የተጠላ” እንደነበር አሳስቧል። (ኢሳይያስ 53:3) ስለዚህ በዛሬው ጊዜ በአብዛኛው የዓለም ክፍል ሚስዮናውያኑ ተቀባይነት የሌላቸው ወይም የማይፈለጉ ተደርገው መታየታቸው ምንም አያስደንቅም። በሌላ በኩል ደግሞ ዳንኤል በባቢሎን ባሳለፈው ረጅም የአገልግሎት ዘመኑ በአንድ መልአክ አማካኝነት ፈጣሪ “እጅግ የተወደድህ” ብሎ ሦስት ጊዜ ጠርቶታል። (ዳንኤል 9:23፤ 10:11, 19) ዳንኤል እንዲህ እንዲሆን ያደረገው ምንድን ነው? ራሱን ከባቢሎን ባህል ጋር ሲያስማማ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን በፍጹም አልጣሰም፤ ሥልጣኑን የግል ፍላጎቱን ለማሟላት የማይጠቀም በማንኛውም መንገድ ሐቀኛ የሆነ ሰው ነበር፤ እንዲሁም የአምላክን ቃል በቅንዓት ይማር ነበር። (ዳንኤል 1:8, 9፤ 6:4፤ 9:2) ዘወትር ወደ ይሖዋ ይጸልይ የነበረ ሲሆን ላገኛቸውም ስኬቶች ሁልጊዜ ለይሖዋ ክብር ይሰጥ ነበር። (ዳንኤል 2:20) የአምላክ አገልጋዮች የዳንኤልን ምሳሌ በመከተል በዓለም ዘንድ ተወዳጅ ባይሆኑም በይሖዋ አምላክ የተወደዱ ሊሆኑ ይችላሉ።
በዚህ በመንፈሳዊ ገንቢ በነበረው ፕሮግራም መቋጫ ላይ ሊቀ መንበሩ ከዓለም ዙሪያ የተላኩ ቴሌግራሞችንና መልእክቶችን አነበበ። ከዚያም 24ቱ ጥንዶች ዲፕሎማቸውን የተቀበሉ ሲሆን የተመደቡባቸውም አገሮች ተነገረ። በመጨረሻ አንድ የክፍሉ ተወካይ ባለፉት አምስት ወራት ውስጥ የክፍሉ ተማሪዎች ላገኙት ሥልጠናና ዝግጅት ያላቸውን አድናቆት የገለጹበት ለአስተዳድር አካልና ለቤቴል ቤተሰብ የተጻፈ ደብዳቤ አነበበ።
ፕሮግራሙ ሲጠናቀቅ በመለያየት ላይ ከነበሩት ተሰብሳቢዎች ‘የደስታና የምስጋና’ ድምፅ ይሰማ ነበር።—ነህምያ 12:27
[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ስለ ተማሪዎቹ የቀረበ አኃዛዊ መረጃ
የተውጣጡባቸው አገሮች ብዛት:- 10
የተመደቡባቸው አገሮች ብዛት:- 19
የተማሪዎቹ ብዛት:- 48
ባልና ሚስት የሆኑ ብዛት:- 24
አማካይ ዕድሜ:- 33
በእውነት ውስጥ የቆዩባቸው ዓመታት በአማካይ:- 16
በሙሉ ጊዜ አገልግሎት የቆዩባቸው ዓመታት በአማካይ:- 13
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የጊልያድ የመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት 106ኛ ክፍል ተመራቂዎች
ከዚህ በታች ባለው ዝርዝር ለእያንዳንዱ ረድፍ ተራ ቁጥር የተሰጠው ከፊት ወደ ኋላ ሲሆን ስሞቹ የሰፈሩት ከግራ ወደ ቀኝ ነው።
(1) ዲከን ዲ፣ ፑኦፖሎ ኤም፣ ላጉና ኤም፣ ደቮልት ኤስ፣ ዶሚንገስ ኢ፣ በርክ ጄ (2) ጋውተ ኤስ፣ ቫስኬስ ደብልዩ፣ ሲብሩክ ኤ፣ ሞስካ ኤ፣ ሄሊ ኤል፣ ብሩወርድ ኤል (3) ብራንደን ቲ፣ ኦሊቫረስ ኤን፣ ኮልመን ዲ፣ ስኮት ቪ፣ ፒተርሰን ኤል፣ መክሎውድ ኬ (4) መክሎውድ ጄ፣ ቶምፕሰን ጄ፣ ሉበሪስ ኤፍ፣ ስፔታ ቢ፣ ሌቲማኪ ኤም፣ ላጉና ጄ (5) ጋውተ ዩ፣ ዶሚንገስ አር፣ ሄሊ ኤፍ፣ ስሚዝ ኤም፣ ባየር ዲ፣ ሞስካ ኤ (6) ስኮት ኬ፣ ሲብሩክ ቪ፣ ስፔታ አር፣ ኮልመን አር፣ ብሩወርድ ኤል፣ ደቮልት ደብልዩ (7) ስሚዝ ዲ፣ ሌቲማኪ ቲ፣ ፒተርሰን ፒ፣ ቶምፕሰን ጂ፣ ቫስኬስ አር፣ ባየር ኤ (8) ሉበሪስ ኤም፣ ዲከን ሲ፣ ብራንደን ዲ፣ ፑኦፖሎ ዲ፣ ኦሊቫረስ ኦ፣ በርክ ኤስ