የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w99 6/1 ገጽ 28-31
  • የጳውሎስ የሥራ ባልደረቦች እነማን ነበሩ?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • የጳውሎስ የሥራ ባልደረቦች እነማን ነበሩ?
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1999
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • የጉዞ ጓደኞችና እንግዳ ተቀባይ የሆኑ ወንዶችና ሴቶች
  • በጣም ብዙ ጓደኞች
  • በእስር ላይ እያለ በታማኝነት ደግፈውታል
  • “ከአምላክ ጋር አብረን የምንሠራ ነን”
  • “በሚገባ . . . መመሥከር”
    ‘ስለ አምላክ መንግሥት በሚገባ መመሥከር’
  • አትፍራ፣ ይሖዋ ረዳትህ ነው
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2020
  • ‘ከሰው ሁሉ ደም ንጹሕ ነኝ’
    ‘ስለ አምላክ መንግሥት በሚገባ መመሥከር’
  • ጳውሎስ በሮም
    የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች መማሪያ መጽሐፌ
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1999
w99 6/1 ገጽ 28-31

የጳውሎስ የሥራ ባልደረቦች እነማን ነበሩ?

የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በሆነው በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍና በጳውሎስ ደብዳቤዎች ላይ የመጀመሪያው መቶ ዘመን የክርስቲያን ጉባኤ አባላት የሆኑ “የአሕዛብ ሐዋርያ” ከሆነው ከጳውሎስ ጋር ግንኙነት የነበራቸው ወደ አንድ መቶ የሚጠጉ ግለሰቦች ተጠቅሰዋል። (ሮሜ 11:​13) ከእነዚህ ውስጥ ስለ አብዛኞቹ በሰፊው የሚታወቅ ነገር አለ። አጵሎስ፣ በርናባስና ሲላስ ስላከናወኗቸው ሥራዎች የምታውቀው ነገር ሳይኖር አይቀርም። በአንጻሩ ደግሞ ስለ አክርጳ፣ ቅላውዲያ፣ ደማሪስ፣ ሊኖስ፣ ጠርሲዳ፣ ጱዴስና ሱሲጳጥሮስ እንብዛም የምትናገረው አታገኝ ይሆናል።

በተለያዩ ወቅቶችና ሁኔታዎች ስር በርካታ ግለሰቦች የጳውሎስን አገልግሎት በመደገፍ ረገድ ጉልህ ሚና ተጫውተዋል። እንደ አርስጥሮኮስ፣ ሉቃስና ጢሞቴዎስ የመሳሰሉ አንዳንድ ግለሰቦች ለበርካታ ዓመታት ከሐዋርያው ጎን ሳይለዩ አገልግለዋል። አንዳንዶች ጳውሎስ በእስር ላይ በነበረበት ጊዜ አሊያም ከቦታ ቦታ ሲጓዝ የጉዞ ጓደኞቹ በመሆን ወይም ቤታቸው በማስተናገድ ከእርሱ ጎን ሆነዋል። እንደ እስክንድሮስ፣ ዴማስ፣ ሄርዋጌኔስ እና ፊሎጎስ የመሳሰሉት በክርስቲያናዊ እምነት አለመጽናታቸው ደግሞ ያሳዝናል።

ከሌሎች በርካታ የጳውሎስ ጓደኞች መካከል እንደ አስቀሪጦን፣ ሄርሜን፣ ዩልያና ፍሌጎን ያሉትን ጥቂቶቹን ካነሳን ከስማቸው በስተቀር ብዙም የምናውቀው ነገር የለም። የኔርያን እህት ወይም የሩፎን እናት ወይም የቀሎዔ ቤተሰብን በተመለከተ ደግሞ ጭራሽ ስማቸውን እንኳ አናውቅም። (ሮሜ 16:​13-15፤ 1 ቆሮንቶስ 1:​11) የሆነ ሆኖ ወደ መቶ ስለሚጠጉት ስለ እነዚህ ግለሰቦች ያለንን ጥቂት መረጃ መመርመራችን ሐዋርያው ጳውሎስ ሥራውን ስላከናወነበት መንገድ ግንዛቤ እንድናገኝ ያስችለናል። በተጨማሪም በርካታ ቁጥር ባላቸው መሰል አማኞች ዙሪያ መገኘትና ከእነርሱ ጋር በቅርብ መሥራት ስለሚያስገኛቸው ጥቅሞች የሚያስገነዝበንም ነገር ይኖራል።

የጉዞ ጓደኞችና እንግዳ ተቀባይ የሆኑ ወንዶችና ሴቶች

የሐዋርያው ጳውሎስ አገልግሎት ብዙ መጓዝን የሚጨምር ነበር። አንድ ጸሐፊ እንዳሰሉት ከሆነ ሌላውን ሳንጨምር በሐዋርያት ሥራ ላይ ተመዝግቦ በሚገኘው መሠረት ብቻ ጳውሎስ በየብስና በባሕር ያደረገው ጉዞ ርቀት ወደ 16,000 ኪሎ ሜትር ይጠጋል። በዚያ ዘመን የሚደረግ ጉዞ አድካሚ ብቻ ሳይሆን አደገኛም ነበር። ካጋጠሙት የተለያዩ አደጋዎች መካከል የመርከብ መሰበርን ጨምሮ በወንዝ፣ በወንበዴዎች፣ በምድረበዳና በባሕር የደረሱበት አደጋዎች ይገኙበታል። (2 ቆሮንቶስ 11:​25, 26) ጳውሎስ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላው ብቻውን የተጓዘው ከስንት አንዴ ብቻ መሆኑ ከሁኔታው ጋር የሚጣጣም ነበር።

ከጳውሎስ ጋር አብረው የተጓዙ ሰዎች የጉዞ ጓደኛ ከመሆን በተጨማሪ የማበረታቻና በአገልግሎቱ ተግባራዊ እርዳታ ይሰጡት ነበር። በአንዳንድ አጋጣሚዎች ጳውሎስ የጉዞ ጓደኞቹ በቅርብ አማኝ የሆኑ ሰዎችን መንፈሳዊ ፍላጎቶች ማሟላት እንዲችሉ እዚያው ትቷቸው ይሄድ ነበር። (ሥራ 17:​14፤ ቲቶ 1:​5) ሆኖም ለደኅንነቱም ሆነ ጉዞው የሚያስከትልበትን ፈታኝ ሁኔታ እንዲወጣ ለመርዳት አብረውት የሚጓዙ ሰዎች መኖራቸው በጣም አስፈላጊ ነው። በመሆኑም የጳውሎስ የጉዞ ጓደኞች እንደሆኑ የምናውቃቸው እንደ ሱሲጳጥሮስ፣ ሲኮንዱስ፣ ጋይዮስና ጥሮፊሞስ የመሳሰሉ ግለሰቦች በአገልግሎቱ ስኬታማ እንዲሆን ትልቅ አስተዋጽዖ አድርገው ሊሆን ይችላል።​—⁠ሥራ 20:​4

በተጨማሪም እንግዳ ተቀባይ የሆኑ ወንዶችና ሴቶች ያደረጉለት ድጋፍ በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ለስብከት ዘመቻም ይሁን ወደ ሌላ ቦታ በሚሄድበት ጊዜ በዚያ ሌሊቱን ለማሳለፍ ጳውሎስ ወደ አንዲት ከተማ ሲደርስ ቅድሚያ የሚሰጠው ነገር የሚያርፍበትን ቦታ መፈለግ ነበር። መቼም እንደ ጳውሎስ ብዙ ቦታ የተጓዘ ማንኛውም ሰው በጣም ብዙ ጊዜ የተለያየ አልጋ ላይ መተኛቱ የግድ ነው። ጳውሎስ በሄደበት ሁሉ ቤርጎ ማረፍ ይችል ነበር። ሆኖም እንደ ታሪክ ጸሐፊዎች አባባል ከሆነ እንዲህ ዓይነቱ ቦታ “አደገኛና ከሥነ ምግባርም አንጻር መጥፎ” ስለነበረ ጳውሎስ በተቻለ መጠን መሰል አማኞች ጋር ማረፍ ይመርጥ እንደነበር መገመት ይቻላል።

ጳውሎስን በእንግድነት የተቀበሉትን የአንዳንዶቹን ወንዶችና ሴቶች ስም እናውቃለን። ከእነርሱ መካከል አቂላና ጵርስቅላ፣ ጋይዮስ፣ ኢያሶን፣ ልድያ፣ ምናሶን፣ ፊልሞና እና ፊልጶስ ይገኙበታል። (ሥራ 16:​14, 15፤ 17:​7፤ 18:​2, 3፤ 21:​8, 16፤ ሮሜ 16:​23፤ ፊልሞና 1, 22) ጳውሎስ በፊልጵስዩስ፣ በተሰሎንቄና በቆሮንቶስ ያረፈባቸው ቤቶች ሚስዮናዊ እንቅስቃሴውን ለማደራጀት እንደ ማዕከል ሆነው አገልግለዋል። ሐዋርያው በቆሮንቶስ ከአንድ መነሻ ቦታ ስብከቱን ማካሄድ የሚችልበት ሥፍራ እንዲያገኝ ኢዮስጦስ በቤቱ እንዲያርፍ ፈቅዶለታል።​—⁠ሥራ 18:​7

በጣም ብዙ ጓደኞች

ጳውሎስ ወዳጆች ያፈራው በልዩ ልዩ አጋጣሚዎች እንደመሆኑ መጠን የሚታወሱትም በተለያዩ መንገዶች እንደሚሆን መገመት እንችላለን። ለምሳሌ ያህል መሰል አማኞች የሆኑት ማርያ፣ ጠርሲዳ፣ ፌቤን፣ ፕሮፊሞናና ጢሮፊሞሳ ሁሉም ሴቶች ሲሆኑ ላከናወኑት ሥራና ላሳዩት ትጋት ተመስግነዋል። (ሮሜ 16:​1, 2, 6, 12) ጳውሎስ ቀርስጶስን፣ ጋይዮስንና የእስጢፋኖስን ቤተሰቦች አጥምቋል። ዲዮናስዮስና ደማሪስ ደግሞ የእውነትን መልእክት ከጳውሎስ በአቴና ሰምተዋል። (ሥራ 17:​34፤ 1 ቆሮንቶስ 1:​14, 16) ከጳውሎስ በፊት አማኞች የሆኑትና “በሐዋርያት መካከል ስመ ጥሩዎች” የነበሩት አንዲራኒቆና ዩልያ ‘አብረውት መታሰራቸው’ ተገልጿል። ምናልባትም በአንድ ወቅት ከእርሱ ጋር ታስረው ሊሆን ይችላል። ጳውሎስ እነዚህ ሁለት ሰዎች እንደ ሄሮድዮና፣ ኢያሶን፣ ሉቂዮስና ሱሲጴጥሮስ ‘ዘመዶቹ’ እንደሆኑ ተናግሯል። (ሮሜ 16:​7, 11, 21) እዚህ ላይ የተሠራበት የግሪክኛ ቃል “የአገር ልጆች” ማለት ሊሆን ቢችልም የቃሉ መሠረታዊ ትርጉም “አንድ ትውልድ ያላቸው የሥጋ ዘመዳሞች” ማለት ነው።

አብዛኞቹ የጳውሎስ ጓደኞች ምሥራቹን ለማዳረስ ሲሉ ከቦታ ቦታ ተጉዘዋል። በደንብ ከሚታወቁት የጉዞ ጓደኞቹ በተጨማሪ ከጳውሎስ ጋር ስለ ጉባኤያቸው መንፈሳዊ ሁኔታ ለመማከር ከቆሮንቶስ ወደ ኤፌሶን የተጓዙት አካይቆስ፣ ፈርዶናጥስና እስጢፋኖስ ይገኙበታል። አርጢሞንና ቲኪቆስ በቀርጤስ ደሴት እያገለገለ ወደነበረው ወደ ቲቶ ለመሄድ ተዘጋጅተው የነበረ ሲሆን ዜማስ ደግሞ ከአጵሎስ ጋር ሆኖ ለመጓዝ ተዘጋጅቶ ነበር።​—⁠1 ቆሮንቶስ 16:​17፤ ቲቶ 3:​12, 13

ጳውሎስ አንዳንድ አጫጭርና ማራኪ የሆኑ መግለጫዎች የተናገረላቸው ሰዎችም አሉ። ለምሳሌ ያህል አጤኔጦን ‘የእስያ በኩራት፣’ ኤርስጦስ በቆሮንቶስ “የከተማው መጋቢ፣” ሉቃስ ባለ መድኃኒት፣ ልድያ ቀይ ሐር ሻጭ እንደሆኑና ጳውሎስ ለሮሜ ክርስቲያኖች የላከውን ደብዳቤ ለመጻፍ የተጠቀመው በጤርጥዮስ እንደሆነ ተገልጾልናል። (ሮሜ 16:​5, 22, 23፤ ሥራ 16:​14፤ ቆላስይስ 4:​14) ስለ እነዚህ ግለሰቦች ይበልጥ ለማወቅ ለሚፈልጉ ሁሉ በዚህ መልክ የቀረቡት እነዚህ አጫጭር መረጃዎች የሰዎቹን ልብ ሰቅለው ያስቀራሉ።

ከጳውሎስ የጉዞ ጓደኞች መካከል አንዳንዶቹ አሁን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሰፍረው የሚገኙ በግል የተላከላቸው መልእክት ደርሷቸዋል። ለምሳሌ ያህል ጳውሎስ ለቆላስይስ ሰዎች በጻፈላቸው ደብዳቤ ላይ አክሪጳን “በጌታ የተቀበልኸውን አገልግሎት እንድትፈጽመው ተጠንቀቅ” ሲል አሳስቦታል። (ቆላስይስ 4:​17) ኤዎድያና ሲንጤኪ ሊያስወግዱት የሚገባ አንድ ዓይነት ግጭት በመካከላቸው እንደነበር ከሁኔታዎቹ መረዳት እንችላለን። በመሆኑም ጳውሎስ ‘በሥራው አብሮ የተጠመደ’ በፊልጵስዩስ የሚገኝ በስም ያልተጠቀሰ ሰው አማካኝነት “በአንድ አሳብ በጌታ እንዲስማሙ” ጥብቅ ምክር ልኮላቸዋል። (ፊልጵስዩስ 4:​2, 3) በእርግጥም ይህ ለሁላችንም የሚሆን ጥሩ ምክር ነው።

በእስር ላይ እያለ በታማኝነት ደግፈውታል

ጳውሎስ ብዙ ጊዜ ታስሯል። (2 ቆሮንቶስ 11:​23) በእነዚህ ጊዜያት በአካባቢው የሚኖሩ ክርስቲያኖች ካሉ የደረሰበትን ችግር መወጣት እንዲችል የሚችሉትን ሁሉ ለማድረግ ሳይሞክሩ አይቀርም። ጳውሎስ ለመጀመሪያ ጊዜ በሮም ታስሮ በነበረበት ወቅት ለሁለት ዓመታት ያህል የራሱን ቤት ተከራይቶ እንዲቀመጥ የተፈቀደለት ሲሆን ወዳጆቹም መጥተው ሊጠይቁት ይችሉ ነበር። (ሥራ 28:​30) በዚህ ወቅት በኤፌሶን፣ በፊልጵስዩስና በቆላስይስ ለሚገኙ ጉባኤዎች እንዲሁም ለፊልሞና ደብዳቤዎች ጽፏል። እነዚህ ደብዳቤዎች ጳውሎስ በእስር ላይ በነበረበት ወቅት ከእርሱ ጋር የቅርብ ግንኙነት ስለነበራቸው ሰዎች ብዙ የሚያሳውቁን ነገር አለ።

ለምሳሌ ያህል ከፊልሞና ጠፍቶ የሄደው አናሲሞስ የሚባል ባሪያ እንደ ቲኪቆስ ሁሉ በሮም ከጳውሎስ ጋር የተገናኘ ሲሆን ወደ ጌታው ለመመለስ በሚያደርገው ጉዞም ቲኪቆስ አብሮት ሄዷል። (ቆላስይስ 4:​7-9) በተጨማሪ ከጉባኤው የተላከውን ስጦታ ለማድረስ ከፊልጵስዩስ ተነስቶ ረጅም ጉዞ ያደረገውና እዚያ ሲደርስ የታመመው አፍሮዲጡም ይገኝበታል። (ፊልጵስዩስ 2:​25፤ 4:​18) አርስጥሮኮስ፣ ማርቆስና ኢዮስጦስ የተባለ ኢያሱ ከጳውሎስ ጋር ሮም ውስጥ በቅርብ ይሠሩ የነበረ ሲሆን ጳውሎስ “በእግዚአብሔር መንግሥት ከእኔ ጋር አብረው የሚሠሩት እነዚህ ብቻ ናቸው፣ እኔንም አጽናንተውኛል” ሲል ስለ እነርሱ ተናግሯል። (ቆላስይስ 4:​10, 11) ከእነዚህ ታማኝ ወዳጆቹ በተጨማሪ በደንብ የሚታወቁት ጢሞቴዎስና ሉቃስ እንዲሁም ዓለምን በመውደዱ ጳውሎስን ትቶት የሄደው ዴማስ ይገኙበታል።​—⁠ቆላስይስ 1:​1፤ 4:​14፤ 2 ጢሞቴዎስ 4:​10፤ ፊልሞና 24

በግልጽ መረዳት እንደሚቻለው ከእነዚህ መካከል አንዳቸውም ቢሆን የሮም ነዋሪዎች አይደሉም፤ ሆኖም በዚያ ከጳውሎስ ጋር ነበሩ። ምናልባትም አንዳንዶቹ ወደዚያ የሄዱት በታሰረበት ወቅት እርሱን ለመርዳት ብለው ይሆናል። አንዳንዶቹ የእርሱ የቃል መልእክተኞች እንደነበሩ፣ ሌሎቹ ተልእኮ ተሰጥቷቸው ራቅ ወዳሉ ቦታዎች እንደተላኩና የተቀሩት ደግሞ ጳውሎስ ደብዳቤ ለመጻፍ እንደተጠቀመባቸው ምንም አያጠራጥርም። ይህም እነዚህ ሰዎች ለጳውሎስም ሆነ አምላክ ለሰጣቸው ሥራ ያላቸውን ከፍተኛ ፍቅርና ታማኝነት የሚያሳይ እንዴት ያለ ግሩም ማስረጃ ነው!

ከአንዳንድ የጳውሎስ ደብዳቤዎች መደምደሚያ በመነሳት ከምናውቃቸው ጥቂት ስሞች በተጨማሪ በርካታ ቁጥር ያላቸው ክርስቲያን ወንድሞችና እህቶች በዙሪያው ሊኖሩ እንደሚችሉ መገንዘብ እንችላለን። በተለያዩ አጋጣሚዎች ላይ “ቅዱሳን ሁሉ ሰላምታ ያቀርቡላችኋል” እንዲሁም “ከእኔ ጋር ያሉት ሁሉ ሰላምታ ያቀርቡልሃል” ሲል ጽፏል።​—⁠2 ቆሮንቶስ 13:​13፤ ቲቶ 3:​15፤ ፊልጵስዩስ 4:​22

ጳውሎስ ለሁለተኛ ጊዜ በሮም በታሰረበትና ሰማዕት የሚሆንበት ጊዜ በተቃረበበት አሳሳቢ ወቅት አብረውት ስለሚያገለግሉት ሰዎች ያስብ ነበር። በዚህ ጊዜም ቢሆን ቢያንስ የአንዳንዶቹን እንቅስቃሴ በመከታተልና በማደራጀት ይሠራ ነበር። ቲቶና ቲኪቆስ ተልዕኮ ተሰጥቷቸው ሄደዋል፣ ቄርቂስ ወደ ገላትያ ሄዷል፣ ኤርስጦስ በቆሮንቶስ ቀርቷል፣ ጥሮፊሞስ ታምሞ በሚሊጢን ቀርቷል፣ ማርቆስና ጢሞቴዎስ ደግሞ ወደ እርሱ ለመምጣት ተዘጋጅተዋል። ይሁን እንጂ ሉቃስ ከጳውሎስ ጋር ነበር። በተጨማሪም ሐዋርያው ለጢሞቴዎስ ሁለተኛውን ደብዳቤ ሲጽፍ ኤውግሎስን፣ ጱዴስን፣ ሊኖስንና ቅላውዲያን ጨምሮ ሌሎች በርካታ አማኞች ከእርሱ ጋር ስለነበሩ ሰላምታ ልከዋል። ጳውሎስን ለመርዳት የተቻላቸውን ሁሉ ያደርጉ እንደነበር አያጠራጥርም። በዚህ ጊዜ ጳውሎስ ራሱ ለጵርስቅላና ለአቂላ እንዲሁም ለሄኔሲፎሩ ቤተ ሰዎች ሰላምታ ልኳል። ይሁን እንጂ በዚህ ፈታኝ ወቅት ዴማስ ትቶት መሄዱና እስክንድሮስ ደግሞ በእርሱ ላይ ብዙ ጉዳት ማድረሱ የሚያሳዝን ነው።​—⁠2 ጢሞቴዎስ 4:​9-21

“ከአምላክ ጋር አብረን የምንሠራ ነን”

ጳውሎስ ስብከቱን ሲያከናውን አብዛኛውን ጊዜ ብቻውን አልነበረም። ኢ ኤርል ኤሊስ የተባሉት ተንታኝ እንዲህ ብለዋል:- “ስለ ጳውሎስ ሲነሳ ወደ አእምሯችን የሚመጣው አንድ ብዙ ጓደኞች ያሉት ሚስዮናዊ ነው። በእርግጥም ጳውሎስ ብቻውን የነበረበት ጊዜ በጣት የሚቆጠር ነው።” ጳውሎስ በአምላክ መንፈስ ቅዱስ አመራር ስር ሆኖ በርካታ ሰዎችን ለሥራ ማንቀሳቀስና ውጤታማ የሆኑ ሚስዮናዊ ዘመቻዎችን ማደራጀት ችሏል። የቅርብ የሥራ ጓደኞቹ፣ አልፎ አልፎ የሚረዱት ሰዎች፣ ጠንካራ ስብዕና ያላቸው አንዳንድ ሰዎችና በርካታ ቁጥር ያላቸው ትሑት አገልጋዮች ከጳውሎስ ጋር አብረው ነበሩ። ሆኖም እነዚህ እንዲሁ የሥራ ባልደረቦች ብቻ አልነበሩም። እነዚህ ሰዎች ከጳውሎስ ጋር አብረው የሠሩት ወይም አብረው የቆዩት ምንም ያክል ይሁን ምን በመካከላቸው ክርስቲያናዊ ፍቅርና ወዳጅነት እንደነበር ግልጽ ነው።

ሐዋርያው ጳውሎስ “ወዳጅነት የመመሥረት ተሰጥኦ” ነበረው። ምሥራቹን ለአሕዛብ ለማዳረስ ከፍተኛ ጥረት ቢያደርግም ብቻውን ለመሥራት ግን አልሞከረም። ከተደራጀው የክርስቲያን ጉባኤ ጋር ተባብሯል እንዲሁም ሙሉ በሙሉ ጥቅም አግኝቶበታል። ጳውሎስ ለተገኘው ውጤት ለራሱ ምስጋና እንዲሰጠው አልፈለገም፤ ከዚህ ይልቅ እርሱ ባሪያ መሆኑንና ሙሉ በሙሉ መመስገን ያለበት ለእድገቱ ምክንያት የሆነው አምላክ እንደሆነ በትሕትና ገልጿል።​—⁠1 ቆሮንቶስ 3:​5-7፤ 9:​16፤ ፊልጵስዩስ 1:​1

ጳውሎስ የነበረበት ዘመን እኛ ካለንበት የተለየ ቢሆንም እንኳ ዛሬ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ያለ ማንኛውም ሰው በራሱ ሐሳብ መመራት እንደሚችል ወይም እንዳለበት አድርጎ ማሰብ የለበትም። ከዚህ ይልቅ ሁልጊዜ ከአምላክ ድርጅት፣ በአካባቢያችን ከሚገኘው ጉባኤና ከመሰል አማኞች ጋር ሆነን መሥራት አለብን። በጥሩም ሆነ በአስቸጋሪ ጊዜ የእነርሱ እርዳታ፣ ድጋፍና ማበረታቻ ያስፈልገናል። ‘በዓለም ዙሪያ ያለ የወንድማማች ማኅበር’ ክፍል የመሆን ውድ መብት አግኝተናል። (1 ጴጥሮስ 5:​9 NW) ጳውሎስ እንዳደረገው ሁሉ እኛም ከወንድሞቻችን ጋር በታማኝነትና በፍቅር አብረናቸው በመሆን ተባብረን የምንሠራ ከሆነ ‘ከአምላክ ጋር አብረን የምንሠራ ነን’ ለማለት እንችላለን።​—⁠1 ቆሮንቶስ 3:​9 NW

[በገጽ 31 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

አጵሎስ

አርስጥሮኮስ

በርናባስ

ልድያ

ሄኔሲፎሩ

ጤርጥዮስ

ቲኪቆስ

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ