ኢየሱስ ሕይወትህን ሊለውጥ የሚችለው እንዴት ነው?
ኢየሱስ ክርስቶስ ከ2,000 ዓመት ገደማ በፊት በጳለስጢና ይኖር የነበረ ታላቅ አስተማሪ ነው። ስለ ልጅነት ሕይወቱ ብዙም አይታወቅም። ይሁን እንጂ ዕድሜው 30 ዓመት አካባቢ ሲሆን ‘ለእውነት ለመመስከር’ አገልግሎቱን መጀመሩ በሚገባ የተረጋገጠ ነው። (ዮሐንስ 18:37፤ ሉቃስ 3:21-23) የእርሱን የሕይወት ታሪክ የጻፉት አራት ደቀ መዛሙርት ከዚያ በኋላ ባሉት ሦስት ተኩል ዓመታት ላይ ትኩረት አድርገዋል።
ኢየሱስ ክርስቶስ በአገልግሎቱ ወቅት በዓለም ላይ ለሚገኙ ለአብዛኞቹ ችግሮች መፍትሄ የሚሆን ትእዛዝ ለደቀ መዛሙርቱ ሰጥቷቸዋል። ትእዛዙ ምን ነበር? ኢየሱስ “እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ፣ እንደ ወደድኋችሁ እናንተ ደግሞ እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ አዲስ ትእዛዝ እሰጣችኋለሁ” ብሏል። (ዮሐንስ 13:34) አዎን፣ የሰው ዘር ለገጠሙት ለአብዛኞቹ ችግሮች መፍትሄው ፍቅር ነው። በሌላ አጋጣሚ ኢየሱስ ከሁሉ የሚበልጠው ትእዛዝ የትኛው እንደሆነ ሲጠየቅ “ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ በፍጹም ነፍስህም በፍጹም አሳብህም ውደድ። ታላቂቱና ፊተኛይቱ ትእዛዝ ይህች ናት። ሁለተኛይቱም ይህችን ትመስላለች፣ እርስዋም:- ባልንጀራህን እንደ ነፍስህ ውደድ የምትለው ናት” የሚል መልስ ሰጥቷል።—ማቴዎስ 22:37-40
ኢየሱስ ለአምላክና ለሰዎች ፍቅር ማሳየት የምንችልበትን መንገድ በቃልም ሆነ በተግባር አሳይቶናል። እስቲ ጥቂት ምሳሌዎች እንውሰድና ከእርሱ ምን ልንማር እንደምንችል እንመልከት።
ያስተማራቸው ነገሮች
በታሪክ ውስጥ የላቀ ቦታ ከሚሰጣቸው ስብከቶች መካከል በአንዱ ላይ ኢየሱስ ክርስቶስ ለተከታዮቹ እንዲህ ሲል ነግሯቸዋል:- “ለሁለት ጌቶች መገዛት የሚቻለው ማንም የለም፤ ወይም አንዱን ይጠላል ሁለተኛውንም ይወዳል፤ ወይም ወደ አንዱ ይጠጋል ሁለተኛውንም ይንቃል፤ ለእግዚአብሔርና ለገንዘብ [“ለሀብት፣” NW] መገዛት አትችሉም።” (ማቴዎስ 6:24) ብዙ ሰዎች ገንዘብ ማንኛውንም ችግር ይፈታል ብለው በሚያምኑበት በዛሬው ጊዜ ኢየሱስ በሕይወታችን ውስጥ አምላክን ስለማስቀደም የሰጠው ትምህርት ተግባራዊነት አለውን? እውነት ነው፣ የሚያስፈልጉንን ነገሮች ለማሟላት ገንዘብ ያስፈልገናል። (መክብብ 7:12) ሆኖም “ሀብት” ጌታችን እንዲሆን ከፈቀድንለት “ገንዘብን መውደድ” መላ ሕይወታችንን በመቆጣጠር ባሪያ ያደርገናል። (1 ጢሞቴዎስ 6:9, 10) በዚህ ወጥመድ ውስጥ የወደቁ ብዙዎች ውሎ አድሮ ቤተሰባቸውን፣ ጤንነታቸውን እንዲሁም ሕይወታቸውን ሳይቀር አጥተዋል።
በሌላ በኩል አምላክን ጌታችን አድርገን መመልከታችን ለሕይወታችን ትርጉም ይሰጠዋል። ፈጣሪ እንደመሆኑ መጠን የሕይወት ምንጭ እርሱ ነው። ስለዚህ አምልኮታችን የሚገባው እርሱ ብቻ ነው። (መዝሙር 36:9፤ ራእይ 4:11) ስለ እርሱ ባሕርያት ተምረው ለእርሱ ፍቅር ያደረባቸው ሰዎች መመሪያዎቹን ለመጠበቅ ይገፋፋሉ። (መክብብ 12:13፤ 1 ዮሐንስ 5:3) እንዲህ በማድረግ ራሳችንን እንጠቅማለን።—ኢሳይያስ 48:17
በተጨማሪ ኢየሱስ በተራራ ስብከቱ ላይ ደቀ መዛሙርቱ ለሰው ልጆች ፍቅር ማሳየት የሚችሉበትን መንገድ አስተምሯቸዋል። እንዲህ አላቸው:- “እንግዲህ ሰዎች ሊያደርጉላችሁ የምትወዱትን ሁሉ እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉላቸው።” (ማቴዎስ 7:12) ኢየሱስ እዚህ ላይ የተጠቀመበት “ሰዎች” የሚለው ቃል የአንድን ሰው ጠላቶችም ይጨምራል። በዚሁ የተራራ ስብከት ላይ እንዲህ ብሏል:- “ጠላቶታችሁን ውደዱ፣ . . . ስለሚያሳድዱአችሁም ጸልዩ።” (ማቴዎስ 5:43, 44) እንዲህ ዓይነቱ ፍቅር በዛሬው ጊዜ ለሚያጋጥሙን ለአብዛኞቹ ችግሮች መፍትሄ አይሆንምን? የሂንዱ መሪ የሆኑት ሞሃንዳስ ጋንዲ እንዲህ ዓይነት አመለካከት ነበራቸው። እንደሚከተለው ብለው መናገራቸው ይጠቀስላቸዋል:- “[እኔም ሆንኩ እርስዎ] ክርስቶስ በዚህ በተራራ ስብከት በገለጸው ትምህርት ብንመራ . . . የመላውን ዓለም ችግሮች ለመፍታት እንችላለን።” ኢየሱስ ስለ ፍቅር የሰጠው ትምህርት በተግባር ከዋለ አብዛኛዎቹን የሰው ልጅ ችግሮች ሊፈታ ይችላል።
ያከናወናቸው ነገሮች
ኢየሱስ ፍቅር ማሳየት የሚቻልበትን መንገድ በተመለከተ ጥልቅ እውነቶችን በማስተማር ብቻ ሳይወሰን ያስተማረውን በሥራም አሳይቷል። ለምሳሌ ያህል ከራሱ ጥቅም ይልቅ የሌሎችን ያስቀድም ነበር። አንድ ቀን ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ሰዎችን በመርዳት በሥራ ተጠምደው ስለነበር ምግብ ለመመገብ እንኳ ፋታ ሳያገኙ ቀሩ። ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ ጥቂት ማረፍ እንዳለባቸው ስለተሰማው ጸጥ ወዳለ አካባቢ ወሰዳቸው። ሆኖም እዚያ ሲደርሱ ብዙ ሕዝብ እየጠበቃቸው እንዳለ ተመለከቱ። አንተ ጥቂት ማረፍ እንዳለብህ ተሰምቶህ እያለ ሥራህን እንድትቀጥል የሚጠባበቅ ሕዝብ ብታይ ምን ምላሽ ትሰጥ ነበር? የሆነ ሆኖ ኢየሱስ “አዘነላቸው” እንዲሁም “ብዙም ነገር ያስተምራቸው ጀመር።” (ማርቆስ 6:34) ኢየሱስ ለሌሎች የነበረው አሳቢነት ምንጊዜም እነርሱን ለመርዳት አነሳስቶታል።
እንዲሁም ኢየሱስ ለሰዎች ተግባራዊ እርዳታ በመስጠት ከማስተማር የበለጠ አድርጎላቸዋል። ለምሳሌ ያህል በአንድ ወቅት እስከ ቀኑ መገባደጃ ድረስ ሲያዳምጡት የነበሩትን ከ5,000 ሰዎች በላይ መግቧል። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ለሦስት ቀናት ያህል ሲያዳምጡት የነበሩትንና ይዘው የመጡት ምግብ በሙሉ ያለቀባቸውን ከ4,000 የሚበልጡ ሰዎች መግቧል። በመጀመሪያው አጋጣሚ አምስት እንጀራና ሁለት ዓሣ የተጠቀመ ሲሆን በሁለተኛው ጊዜ ደግሞ ሰባት እንጀራና ጥቂት ትንንሽ ዓሣዎች ተጠቅሟል። (ማቴዎስ 14:14-22፤ 15:32-38) እነዚህ ተአምራት ናቸው? አዎን፣ እርሱ ተአምር አድራጊ ነበር።
ከዚህ በተጨማሪ ኢየሱስ ብዙ በሽተኞችን ፈውሷል። ማየትና መስማት የተሳናቸውን፣ አንካሶችንና የሥጋ ደዌ የነበረባቸውን አድኗል። ሌላው ቀርቶ ሙታንን እንኳ አስነስቷል! (ሉቃስ 7:22፤ ዮሐንስ 11:30-45) በአንድ ወቅት የሥጋ ደዌ የያዘው አንድ ሰው “ብትወድስ ልታነጻኝ ትችላለህ” ሲል ለመነው። ኢየሱስ ምን ምላሽ ሰጠ? “ኢየሱስም አዘነለት እጁንም ዘርግቶ ዳሰሰውና:- እወድዳለሁ ንጻ አለው።” (ማርቆስ 1:40, 41) በእነዚህ ተአምራት አማካኝነት ኢየሱስ መከራ ለደረሰባቸው ሰዎች ያለውን ፍቅር አሳይቷል።
ኢየሱስ የፈጸማቸውን ተአምራት ማመን ያስቸግርሃል? አንዳንዶች ይቸገራሉ። ሆኖም ኢየሱስ ተአምራቱን የፈጸመው በሕዝብ ፊት እንደነበረ አስታውስ። ሌላው ቀርቶ በእያንዳንዱ አጋጣሚ ስህተት ይፈላልጉበት የነበሩት ተቃዋሚዎቹ እንኳን ተአምር አድራጊ እንደነበረ መካድ አልቻሉም። (ዮሐንስ 9:1-34) ከዚህም በላይ ያከናወናቸው ተአምራት ዓላማ ነበራቸው። ተአምራቱ ሰዎች በአምላክ የተላከ መሆኑን ለይተው እንዲያውቁ አስችለዋል።—ዮሐንስ 6:14
ኢየሱስ ተአምራት በማከናወን የሰዎችን ትኩረት ወደ ራሱ ለመሳብ አልፈለገም። ከዚህ ይልቅ እርሱ ለነበረው ኃይል ምንጭ የሆነለትን አምላክ አወድሷል። በአንድ ወቅት በቅፍርናሆም እርሱ የነበረበት ቤት በሰዎች ተጨናንቆ ነበር። አንድ ሽባ ሰው ለመፈወስ ቢፈልግም እንኳ ወደ ውስጥ መግባት አቃተው። ስለዚህ ጓደኞቹ አልጋ ላይ አስተኝተው በጣሪያው በኩል ወደታች አወረዱት። ኢየሱስ እምነታቸውን አይቶ ሽባውን ፈወሰው። ከዚህ የተነሳ ሰዎቹ “እንዲህ ያለ ከቶ አላየንም” በማለት “እግዚአብሔርን አከበሩ።” (ማርቆስ 2:1-4, 11, 12) ኢየሱስ ያደረጋቸው ተአምራት ለአምላኩ ለይሖዋ ውዳሴ ከማስገኘታቸው በተጨማሪ በችግር ላይ የነበሩትን ሰዎች ጠቅሟቸዋል።
ሆኖም በሽተኞችን በተአምራዊ መንገድ መፈወስ የኢየሱስ አገልግሎት ዋና ዓላማ አልነበረም። የኢየሱስን የሕይወት ታሪክ የጻፈ አንድ ሰው እንዲህ ሲል ገልጿል:- “ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ ታምኑ ዘንድ፣ አምናችሁም በስሙ ሕይወት ይሆንላችሁ ዘንድ ይህ ተጽፎአል።” (ዮሐንስ 20:31) አዎን፣ ኢየሱስ ወደ ምድር የመጣው በእርሱ የሚያምኑ ሰዎች ሕይወት ያገኙ ዘንድ ነው።
የከፈለው መሥዋዕት
‘ለመሆኑ ኢየሱስ ወደ ምድር የመጣው ከየት ነው?’ ብለህ ትጠይቅ ይሆናል። ኢየሱስ ራሱ እንዲህ ሲል ተናግሯል:- “ፈቃዴን ለማድረግ አይደለም እንጂ የላከኝን ፈቃድ ለማድረግ ከሰማይ ወርጃለሁና።” (ዮሐንስ 6:38) ሰው ከመሆኑ በፊት የአምላክ አንድያ ልጅ ሆኖ ይኖር ነበር። ታዲያ እርሱን ወደ ምድር የላከው አካል ፈቃድ ምን ነበር? ከወንጌል ጸሐፊዎች አንዱ የሆነው ዮሐንስ እንዲህ ይላል:- “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና።” (ዮሐንስ 3:16) ይህ እንዴት ሊሆን ቻለ?
መጽሐፍ ቅዱስ ሞት ለሰው ልጆች የማይቀር ዕጣ የሆነበትን መንገድ ይገልጻል። አምላክ ለመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት ለዘላለም የመኖር ተስፋ ያዘለ ሕይወት ሰጥቷቸው ነበር። ሆኖም በፈጣሪያቸው ላይ ለማመፅ መረጡ። (ዘፍጥረት 3:1-19) የመጀመሪያው የሰው ልጅ ኃጢአት በሆነው በዚህ ድርጊት የተነሳ የአዳምና የሔዋን ዘሮች አስከፊ የሆነውን የሞት ቅርስ ወረሱ። (ሮሜ 5:12) የሰው ዘር እውነተኛ ሕይወት ማግኘት እንዲችል ኃጢአትና ሞት መወገድ አለባቸው።
የትኛውም የሳይንስ ሊቅ በአንድ ዓይነት የጄኔቲክ ምሕንድስና ሞትን ሊያስወግድ አይችልም። ሆኖም የሰው ዘር ፈጣሪ ታዛዥ የሆኑ ሰዎች ለዘላለም መኖር እንዲችሉ እነርሱን ወደ ፍጽምና የሚያመጣበት መንገድ አለው። መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይህ ዝግጅት ቤዛ ተብሎ ተጠርቷል። የመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት ራሳቸውንም ሆነ ዝርያዎቻቸውን ለኃጢአትና ለሞት ባርነት ሸጠዋል። ለአምላክ ታዛዥ በመሆን የነበራቸውን ፍጹም ሕይወት ከአምላክ ተነጥለው በሚመሩት ሕይወት በመለወጥ ትክክልና ስህተት በሆኑት ነገሮች መካከል የራሳቸውን ውሳኔዎች ማድረግ ጀመሩ። ፍጹም ሰብዓዊ ሕይወት መልሶ ለመግዛት የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን ላጠፉት ፍጹም ሰብዓዊ ሕይወት ተመጣጣኝ የሆነ ዋጋ መከፈል ነበረበት። ሰዎች አለፍጽምና በመውረሳቸው ምክንያት ይህን ዋጋ ለመክፈል ብቁ ሳይሆኑ ቀሩ።—መዝሙር 49:7
በመሆኑም ይሖዋ አምላክ እርዳታ ለመስጠት ጣልቃ ገባ። የአንድያ ልጁን ፍጹም ሕይወት ኢየሱስን ወደወለደችው ድንግል ማህፀን አዛወረው። ከተወሰኑ አሥርተ ዓመታት በፊት ድንግል ትወልዳለች የሚለውን ሐሳብ ላትቀበል ትችል ይሆናል። ይሁን እንጂ በዛሬው ጊዜ ሳይንቲስቶች አጥቢ እንስሳዎችን ፅንስ አስይዘዋል፤ እንዲሁም ከአንዱ እንስሳ ወደ ሌላው በራሂ (gene) አዳቅለዋል። ታዲያ ፈጣሪ ከተለመደው የመዋለድ ሂደት የላቀ ነገር ማድረግ አይችልም ብሎ ሊከራከር የሚችል ይኖራል?
ፍጹም ሰብዓዊ ሕይወት በመፈጠሩ የሰው ልጆችን ከኃጢአትና ከሞት ለመዋጀት የሚያስችል ዋጋ ተገኘ። ሆኖም ምድር ላይ ኢየሱስ ተብሎ የተወለደው ሕፃን የሰዎችን ችግር የሚያስወግደውን “መድኃኒት” ማስገኘት የሚችል “ሐኪም” ለመሆን ማደግ ነበረበት። ይህን ያደረገው በኃጢአት ያልተበከለ ፍጹም ሕይወት በመምራት ነው። ኢየሱስ በኃጢአት ስር የሚገኘው የሰው ዘር የሚደርስበትን ሰቆቃ ከማየቱም በላይ ሰው መሆን የሚያስከትላቸውን አካላዊ ገደቦችም ቀምሷል። ይህ ደግሞ ይበልጥ ሩኅሩኅ ሐኪም እንዲሆን አስችሎታል። (ዕብራውያን 4:15) ኢየሱስ ምድር ላይ ባሳለፈው ሕይወት ያከናወናቸው ተአምራዊ ፈውሶች በሽተኞችን ለማዳን ፍላጎትም ሆነ ኃይል እንዳለው አረጋግጠዋል።—ማቴዎስ 4:23
ኢየሱስ በዚህ ምድር ላይ ለሦስት ዓመት ተኩል ካገለገለ በኋላ በተቃዋሚዎቹ እጅ ተገደለ። አንድ ፍጹም ሰው እጅግ ከባድ ፈተናዎች ቢደርሱበትም እንኳ ለፈጣሪው ታዛዥ መሆን እንደሚችል አሳይቷል። (1 ጴጥሮስ 2:22) መሥዋዕት ሆኖ የቀረበው የእርሱ ፍጹም ሰብዓዊ ሕይወት የሰው ልጆችን ከኃጢአትና ከሞት ማዳን የሚችል የቤዛ ዋጋ ሆኗል። ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲህ ብሏል:- “ነፍሱን ስለ ወዳጆቹ ከመስጠት ይልቅ ከዚህ የሚበልጥ ፍቅር ለማንም የለውም።” (ዮሐንስ 15:13) ከሞተ ከሦስት ቀን በኋላ ኢየሱስ መንፈሳዊ ሕይወት ይዞ ከሞት የተነሳ ሲሆን ከተወሰኑ ሳምንታት በኋላ ደግሞ የቤዛውን ዋጋ ለይሖዋ አምላክ ለማቅረብ ወደ ሰማይ አረገ። (1 ቆሮንቶስ 15:3, 4፤ ዕብራውያን 9:11-14) እንዲህ በማድረግ ቤዛዊ መሥዋዕቱ የሚያስገኘውን ጥቅም እርሱን ለሚከተሉ ሰዎች ማቅረብ ችሏል።
መንፈሳዊ፣ ስሜታዊና አካላዊ በሽታዎች ፈውስ ከሚያገኙበት ከዚህ መንገድ ጥቅም ለማግኘት ፈቃደኛ ትሆናለህ? እንዲህ ለማድረግ በኢየሱስ ክርስቶስ ማመን ያስፈልጋል። አንተ ራስህ ለምን ወደ ሐኪሙ አትመጣም? ይህን ማድረግ የምትችለው ስለ ኢየሱስ ክርስቶስና እርሱ ታማኝ የሰው ልጆችን በማዳን ረገድ ያለውን ሚና በመማር ነው። የይሖዋ ምሥክሮች አንተን ለመርዳት ደስተኞች ናቸው።
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢየሱስ በሽተኞችን ለማዳን ፍላጎትም ሆነ ኃይል አለው
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የኢየሱስ ሞት አንተን የሚነካህ እንዴት ነው?