እኩዮች ከሚያሳድሩት ተጽዕኖ ጥቅም ማግኘት ይቻል ይሆን?
በእኩዮቻችን ዘንድ ተቀባይነት ማግኘት የሁላችንም ተፈጥሯዊ ፍላጎት ነው። ሌሎች ሲጠሉት ወይም ሲያገሉት የሚወድ ማንም የለም። በመሆኑም መጠኑ ይለያይ እንጂ እኩዮቻችን ተጽዕኖ ያሳድሩብናል።
እኩያ “ከሌላ ጋር እኩል ደረጃ ያለው፣ . . . በተለይ ደግሞ በአንድ ማኅበራዊ ቡድን ውስጥ የሚገኙ በዕድሜ፣ በደረጃ ወይም በሥልጣን እኩል የሆኑ ሰዎች” የሚል ትርጉም ተሰጥቶታል። ስለዚህም የእኩያ ተጽዕኖ ማለት እየታወቀንም ይሁን ሳይታወቀን ከእነርሱ አስተሳሰብ ወይም ድርጊት ጋር ተመሳስለን እንድንኖር የሚያስገድደን ኃይል ማለት ነው። የእኩያ ተጽዕኖ ብዙውን ጊዜ የሚታየው በአሉታዊ ጎኑ ነው። ሆኖም ቀጥለን እንደምንመለከተው አዎንታዊም ጎን ሊኖረው ይችላል።
በየትኛውም የዕድሜ ክልል በሚገኙ ላይ ያለ ተጽዕኖ
የእኩያ ተጽዕኖ ወጣቶችን ብቻ ሳይሆን በየትኛውም የዕድሜ ክልል የሚገኙ ሰዎችን የሚነካ ነው። እንደሚከተሉት ያሉ ጥያቄዎች ወደ አእምሯችን ከመጡ በተጽዕኖው እየተነካን ነው ማለት ነው:- “ሁሉም ያደርገዋል፣ እኔስ የማላደርገው ለምንድን ነው?” “ለምን ሁልጊዜ ከሌሎች የተለየሁ እሆናለሁ?” “እንዲህ ባደርግ ሌሎች ምን ይላሉ ወይም ምን ያስባሉ?” “ጓደኞቼ ሁሉ ከተቃራኒ ፆታ ጋር እየተቀጣጠሩ ይጫወታሉ ከዚያም ያገባሉ። እኔ ግን ለዚህ አልታደልኩም። አንድ ዓይነት ጉድለት ይኖርብኝ ይሆን?”
ምንም እንኳ ሌሎችን መስሎ የመኖር ተጽዕኖ በየትኛውም የዕድሜ ክልል የሚገኙ ሰዎችን የሚነካ ቢሆንም በጉርምስና እድሜ ላይ በሚገኙ ወጣቶች ላይ አየል ይላል። ዘ ወርልድ ቡክ ኢንሳይክለፒዲያ “በጉርምስና እድሜ ላይ የሚገኙ አብዛኞቹ ወጣቶች በዕድሜ እኩዮቻቸው ማለትም በጓደኞቻቸው ሙሉ በሙሉ ይዋጣሉ። እነዚህ በአሥራዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ወጣቶች ከወላጆቻቸው ይልቅ በእኩዮቻቸው ዘንድ ተቀባይነት ማግኘት ይፈልጋሉ። ለዚህም ሲሉ ጠባያቸውን ሊለውጡ ይችላሉ” በማለት ተናግሯል። አክሎም በአሥራዎቹ ዕድሜ ክልል የሚገኙ ወጣቶች “የዕድሜ እኩዮቻቸው ከተቀበሏቸውና ከወደዷቸው እድገታቸው ጤናማ እንደሆነ አድርገው ያስባሉ።” ይህንንም ለማሳካት “አለባበስን፣ የመሪነት ችሎታንና ከተቃራኒ ፆታ ጋር ተቀጣጥሮ መጫወትን ለመሳሰሉ በሌሎች ዘንድ ያለንን ተቀባይነት ይነካሉ ብለው ለሚያስቧቸው ነገሮች ከፍተኛ ትኩረት ይሰጣሉ።”
የትዳር ጓደኛሞችም በሚገዙት ወይም በሚከራዩት የቤት ዓይነት፣ በሚያሽከረክሩት የመኪና ዓይነት፣ ልጆች ለመውለድ ወይም ላለመውለድ እንዲሁም ለሌሎች በርካታ ጉዳዮች በሚያደርጉት ውሳኔ ላይ የዕድሜ እኩዮቻቸው ተጽዕኖ እንደሚያሳድሩባቸው ይገነዘቡ ይሆናል። በሚኖሩበት ማኅበረሰብ፣ በጓደኞቻቸው ወይም በጎሳቸው ዘንድ ተቀባይነት ባሏቸው ነገሮች ይመሩ ይሆናል። ሌላው ቀርቶ አንዳንድ ቤተሰቦች በቁሳዊ ሃብት ከጎረቤቶቻቸውና ከእኩዮቻቸው አንሰው ላለመታየት ሲሉ ከፍተኛ ዕዳ ውስጥ ይዘፈቃሉ። አዎን፣ ብዙውን ጊዜ ግባችን፣ አስተሳሰባችንና ውሳኔያችን የእኩዮች ተጽዕኖ ምን ያህል ስውር ኃይል እንዳለው የሚያሳይ ሊሆን ይችላል። የእኩዮች ተጽዕኖ ይህን ያህል ከፍተኛ ኃይል ያለው ከሆነ ልንሄድበት በምንፈልገው አቅጣጫ መሄድ እንድንችል ይረዳን ዘንድ በጥሩ ጎኑ ልንጠቀምበት እንችላለንን? አዎን፣ እንችላለን!
በጎ ተጽዕኖ ከሚያሳድሩ እኩዮች መጠቀም
ሐኪሞችና ሌሎች የጤና ባለሙያዎች በሽተኞቻቸውን አዎንታዊ አመለካከት ካላቸው ሰዎች ጋር እንዲውሉና በጎ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ ሌሎች ሁኔታዎች እንዲሟሉላቸው ማድረግ ያለውን ጠቀሜታ በሚገባ ያውቃሉ። እንዲህ ያለው ሁኔታ ከበሽታ ለመዳን አስተዋጽኦ ሊያደርግ ይችላል። ለምሳሌ ያህል እጃቸውን ወይም እግራቸውን በሆነ ምክንያት ያጡ ሰዎች ተመሳሳይ የአካል ጉዳት የደረሰባቸውን ሌሎች ሰዎች አርአያ እንዲከተሉና የእነሱን ማበረታቻ እንዲያገኙ በማድረግ ረዘም ያለ ጊዜ የሚወስድ አካላዊና ስሜታዊ ተሃድሶ ፕሮግራም ይሰጣቸዋል። በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው አዎንታዊ አመለካከት ያላቸውንና ጥሩ አርአያ ሊሆኑ የሚችሉ ሰዎችን ጨምሮ ጤናማ አስተሳሰብ ካላቸው ሰዎች ጋር ወዳጅነት መመሥረት ከእኩዮች በጎ ተጽዕኖ መጠቀም የሚቻልበት አንደኛው መንገድ ነው።
ይህ መሠረታዊ ሥርዓት ለክርስቲያን ጉባኤም ይሠራል። ይሖዋ ሕዝቦቹ አንድ ላይ አዘውትረው እንዲሰበሰቡ ያዘዘበት አንደኛው ምክንያት እኩዮች ከሚያሳድሩት አዎንታዊ ተጽዕኖ ጥቅም እንዲያገኙ ለማድረግ ነው። አምላክ ‘ለፍቅርና ለመልካም ሥራ እንድንነቃቃ እንዲሁም እርስ በርሳችን እንድንበረታታ’ አዝዞናል። (ዕብራውያን 10:24, 25) ይህ ዓለም ተስፋ በሚያስቆርጡና መጥፎ በሆኑ ተጽዕኖዎች የተሞላ ስለሆነ እንዲህ ዓይነቱ ማበረታቻ ያለው ጥቅም ከምንም ነገር ጋር ሊወዳደር አይችልም። እነዚህ ተጽእኖዎች ስላሉ ክርስቲያኖች በመንፈሳዊ ጠንካራ ሆነው ለመኖር ‘መጋደል’ አለባቸው። (ሉቃስ 13:24) በመሆኑም ከእምነት ባልደረቦቻችን የምናገኘው ፍቅራዊ ድጋፍ ያስፈልገናል ደግሞም እንዲህ ዓይነቱን ድጋፍ እናደንቃለን። በተጨማሪም አንዳንዶች ካለባቸው ‘የሥጋ መውጊያ’ ጋር ምናልባትም ከሕመም ወይም ከአካል ጉዳት ጋር መታገል ያስፈልጋቸው ይሆናል። (2 ቆሮንቶስ 12:7) ሌሎች ደግሞ ያሉባቸውን መጥፎ ልማዶች ወይም ጭንቀቶች ተቋቁመው ለማሸነፍ ይታገሉ ይሆናል፤ ወይም ዕለት ተዕለት ኑሮን ማሸነፍ ከባድ ሆኖባቸው ይሆናል። ስለዚህ ወደ ይሖዋ አምላክ ተጠግተው ከሚኖሩና እርሱን ማገልገል ከሚያስደስታቸው ጋር አብሮ መሆን ጥበብ ነው። እነዚህ እኩዮች መንፈሳችንን ያነቃቁታል እንዲሁም ‘እስከ መጨረሻው በታማኝነት እንድንጸና’ ይረዱናል።—ማቴዎስ 24:13
ስለዚህ ትክክለኛ እኩዮችን በመምረጥ በእኛ ላይ የሚያሳድሩትን ተጽዕኖ ልንቆጣጠር እንችላለን። በተጨማሪም በክርስቲያን ስብሰባዎች ላይ የሚቀርቡት ግሩም የሆኑ መንፈሳዊ ምግቦችና ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉ መመሪያዎች በግለሰብ ደረጃ ከእኩዮቻችን የምናገኘውን ማበረታቻ ያጠናክሩታል።
እርግጥ ነው፣ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መገኘት ሁልጊዜ ቀላል አይደለም። አንዳንዶች የትዳር ጓደኞቻቸው የሚሰጧቸው ድጋፍ በጣም ውስን ሊሆን ወይም ምንም ዓይነት ድጋፍ ላይሰጧቸው ይችላሉ፤ ሌሎች ደግሞ ልጆቻቸውን ወደ ስብሰባ ለመውሰድ ማዘገጃጀት ይኖርባቸው ይሆናል፤ እንዲሁም ሌሎች የመጓጓዣ ችግር ይኖርባቸው ይሆናል። ሆኖም እስቲ ቆም ብላችሁ አስቡ:- እነዚህ መሰናክሎች ከስብሰባ እንዲያስቀሯችሁ ካልፈቀዳችሁላቸው ምሳሌነታችሁ ተመሳሳይ ችግሮችን እየታገሉ ያሉትን ሰዎች መንፈስ ሊያድስ ይችላል። በሌላ አባባል እናንተም ሆናችሁ እናንተን የመሰሉ ሌሎች በዚህ ረገድ ጥሩ ምሳሌ ከመሆናችሁም በላይ ሌሎችን ሳታስገድዱ በጎ የሆነ ተጽዕኖ የምታሳድሩ እኩዮች ልትሆኑ ትችላላችሁ።
ብዙ ችግሮችንና መሰናክሎችን ታግሎ ማሸነፍ የነበረበት ሐዋርያው ጳውሎስም ቢሆን የእርሱንም ሆነ የሌሎች የጎለመሱ ክርስቲያኖችን ጥሩ ምሳሌ እንዲከተሉ ክርስቲያኖችን አበረታቷል። “ወንድሞች ሆይ፣ እኔን የምትመስሉ ሁኑ፣ እኛም እንደ ምሳሌ እንደምንሆንላችሁ፣ እንዲሁ የሚመላለሱትን ተመልከቱ” በማለት ተናግሯል። (ፊልጵስዩስ 3:17፤ 4:9) በመጀመሪያው መቶ ዘመን በተሰሎንቄ የነበሩ ክርስቲያኖች የጳውሎስን መልካም ምሳሌ ተመልክተዋል። ጳውሎስ ለእነርሱ ሲጽፍ “ደግሞ እናንተ ቃሉን በብዙ መከራ ከመንፈስ ቅዱስ ደስታ ጋር ተቀብላችሁ፣ እኛንና ጌታን የምትመስሉ ሆናችሁ፤ ስለዚህም በመቄዶንያና በአካይያ ላሉት ምእመናን ሁሉ ምሳሌ ሆናችሁላቸው” ብሏል። (1 ተሰሎንቄ 1:6, 7) እኛም የምናሳየው አዎንታዊ አመለካከትና ምሳሌነት በባልንጀሮቻችን ላይ ተመሳሳይ የሆነ ውጤት ሊያስከትል ይችላል።
ከአሉታዊ ተጽዕኖዎች መራቅ
እኩዮች ከሚያሳድሩት ጤናማ ያልሆነ ተጽዕኖ ለመራቅ ከፈለግን “እንደ ሥጋ ፈቃድ የሚኖሩ” ሰዎች የሚያሳድሩትን ተጽዕኖ መከላከል አለብን። (ሮሜ 8:4, 5፤ 1 ዮሐንስ 2:15-17) ያለበለዚያ ግን እኩዮች የሚያሳድሩት ጎጂ ተጽዕኖ ከይሖዋና ጥበብ ከሞሉበት ምክሮቹ ሊያርቁን ይችላሉ። ምሳሌ 13:20 “ከጠቢባን ጋር የሚሄድ ጠቢብ ይሆናል፤ የሰነፎች ባልንጀራ ግን ክፉ መከራን ይቀበላል” ይላል። እኩዮች በሚያሳድሩት ጤናማ ያልሆነ ተጽዕኖ የተሸነፈ ሰው ታውቃለህ? ለምሳሌ ያህል አንዳንድ ክርስቲያኖች በእኩዮቻቸው ግፊት በፍቅረ ንዋይና በፆታ ብልግና ወጥመድ ውስጥ ወድቀዋል ወይም በዕፅና በአልኮል መጠጥ አላግባብ መጠቀም ጀምረዋል።
በመንፈሳዊ ደካማ የሆኑ ግለሰቦችን ለባልንጀርነት ከመረጥናቸው በክርስቲያን ጉባኤ እንኳ ሳይቀር እኩዮች በሚያሳድሩት ጎጂ ተጽዕኖ ሥር ልንወድቅ እንችላለን። (1 ቆሮንቶስ 15:33፤ 2 ተሰሎንቄ 3:14) አንዳንዶች ስለ መንፈሳዊ ጉዳዮች አንስተው መወያየት አይፈልጉም፤ እንዲያውም መንፈሳዊ ጉዳዮችን አንስተው በሚያወሩ ላይ ይቀልዱ ይሆናል። እነዚህን ግለሰቦች የቅርብ ወዳጆቻችን እንዲሆኑ ብንመርጥ የእኩዮች ተጽዕኖ በተመሳሳይ መንገድ እንድንቀረጽ ሊያደርገን ይችላል። እንዲያውም በአጭር ጊዜ ውስጥ የእነርሱን ዓይነት አስተሳሰብና አመለካከት ልናንጸባርቅ እንችላለን። ከዚያም አልፎ እውነተኛ እምነት ያላቸውንና በመንፈሳዊ እድገት ለማድረግ የሚፍጨረጨሩትን ማጥላላት ልንጀምር እንችላለን።—1 ጢሞቴዎስ 4:15
እንግዲያው ይሖዋን ለማስደሰት ከሚጣጣሩትና በመንፈሳዊ ነገሮች ከሚደሰቱ ሰዎች ጋር ለመወዳጀት ጥረት ማድረጉ ምንኛ ጥበብ ነው! እንዲህ ያለው ወዳጅነት ‘ላይኛይቱን ጥበብ’ እንድናንጸባርቅ ይረዳናል። እርሷም “በመጀመሪያ ንጽሕት ናት፣ በኋላም ታራቂ፣ ገር፣ እሺ ባይ፣ ምሕረትና በጎ ፍሬ የሞላባት፣ . . . ግብዝነት የሌለባት ናት።” (ያዕቆብ 3:17) ይህ ግን መንፈሳዊ አስተሳሰብ ያላቸው ሰዎች ከመንፈሳዊ ጉዳዮች ሌላ ስለ ምንም ነገር አያውቁም ማለት አይደለም። ሐቁ ከዚህ የራቀ ነው! እንደ ንቁ! መጽሔት ባሉ የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ጽሑፎች ላይ የሚወጡትን የተለያዩ ስሜት ቀስቃሽ ርዕሶች አስብ። ገንቢ የሆኑ ነገሮችን አንስቶ ለመጨዋወት የሚያስችሉ ቁጥር ስፍር የሌላቸው ርዕሰ ጉዳዮች አሉ። የተለያዩ ነገሮችን በሚዳስሱ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ለመጨዋወት ፍላጎት ማሳየታችን ለሕይወትና ለይሖዋ የእጅ ሥራዎች ፍቅር እንዳለን የሚያሳይ ነው።
አንድ የጠረጴዛ ኳስ ተጫዋች ችሎታውን ለማሻሻል ሲል ከሌላ ጎበዝ የጠረጴዛ ኳስ ተጫዋች ጋር እንደሚጫወት ሁሉ ትክክለኛ ወዳጆች አስተሳሰባችንን፣ ስሜታችንንና መንፈሳዊነታችንን ያጎለብቱልናል። በሌላው በኩል ደግሞ መጥፎ ወዳጆች ሁለት ዓይነት ኑሮ እንድንኖር በማድረግ የግብዝነት ጎዳና እንድንከተል ሊያደርጉን ይችላሉ። ከራስ አክብሮት ጋር ንጹሕ ሕሊና ይዞ መኖር ምንኛ የተሻለ ነው!
አንዳንዶች ያገኙት ጥቅም
ብዙ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶችና በውስጡ የያዛቸውን ሥነ ምግባራዊና መንፈሳዊ ደንቦች መማሩ ያን ያህል ከባድ እንዳልሆነ ያውቃሉ። ከባድ የሚሆነው ግን እነዚህን ነገሮች ተግባራዊ ማድረጉ ነው። ቀጥሎ ያለው ተሞክሮ እንደሚያሳየው እኩዮች የሚያሳድሩት በጎ የሆነ ተጽዕኖ ይሖዋን በሙሉ ነፍስ እንድናገለግል ሊረዱን ይችላሉ።
ከባለቤቱ ጋር በሙሉ ጊዜ አገልግሎት እየተካፈለ ያለ አንድ ምሥክር የእኩዮቹ ምሳሌነት በሕይወቱ ውስጥ ባወጣው ግብ ላይ ተጽዕኖ እንዳሳደረበት ተናግሯል። ልጅ በነበረበት ጊዜ የሚደርሱበትን ጎጂ ተጽዕኖዎች መቋቋም አስፈልጎት ነበር። በአገልግሎትና በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች አዘውታሪ እንዲሆን ከሚያበረታቱ ክርስቲያኖች ጋር ወዳጅ መሆንን መረጠ። እነዚህን ወዳጆቹን የሙጥኝ ብሎ መያዙ መንፈሳዊ ጉልምስና ላይ ለመድረስ በሚያደርገው ጉዞ እገዛ አድርገውለታል።
ሌላ ምሥክርም የሚከተለውን ጽፏል:- “እኔና ባለቤቴ ከተጋባን በኋላ የዘወትር አቅኚ ሆነው የሚያገለግሉ በእኛ ዕድሜ የሚገኙ አንድ ባልና ሚስት ወደሚገኙበት ጉባኤ ተዛወርን። የእነርሱ ምሳሌነት የሙሉ ጊዜ አገልግሎት እንድንጀምር አስተዋጽኦ አበርክቶልናል። ከዚያም በጉባኤው ውስጥ የአቅኚነት መንፈስ እንዲቀጣጠል አብረን ሠርተናል። በመጨረሻም ሌሎች በርካታ ሰዎች ከእኛ ጋር አቅኚ ሆነው ማገልገል ጀመሩ።”
ቲኦክራሲያዊ ግቦች ካላቸው ጋር ባልንጀራ መሆናችን ይሖዋን መታዘዝ ቀላል እንዲሆንልን ሊያደርግ ይችላል። ይህም እኩዮች ከሚያሳድሩት በጎ ተጽዕኖ ሌላው ጥሩ ጎን ነው። በወጣትነቱ የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ጀምሮ ከጊዜ በኋላ በተጓዥ የበላይ ተመልካችነት ያገለግል የነበረ አንድ ምሥክር በአሁኑ ወቅት በአንዱ የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ በማገልገል ላይ ይገኛል። እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ልጅ በነበርኩበት ጊዜ የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች እቤታችን አዘውትረው ይመጡ እንደነበረ እስከ አሁን ድረስ አስታውሳለሁ። ሁልጊዜ አብሮን የሚመገብ ሰው ከቤታችን አይጠፋም ነበር። የአሥር ዓመት ልጅ በነበርኩበት ወቅት አንድ የወረዳ የበላይ ተመልካች የአገልግሎት ቦርሳ ሰጠኝ። ያ ቦርሳ እስከ አሁን ድረስ ከእኔ ጋር አለ።”
ይህ ምሥክር በአሥራዎቹ የእድሜ ክልል ውስጥ በነበረበት ወቅት ስላሳለፈው ጊዜ ሲናገር እንዲህ ብሏል:- “በጉባኤ ውስጥ የነበሩ በርካታ ወጣቶች ጥሩ እንቅስቃሴ ማድረግ ጀመሩ፤ በዚህ መንገድ ያሳዩት ምሳሌነት ሌሎቻችንም ተመሳሳይ ምኞት እንዲያድርብን አደረገ።” በጎ ተጽእኖ የሚያሳድሩ እኩዮች ይህ ወጣት ልክ እንደ አንድ ዛፍ ቀጥ ብሎ እንዲያድግ ረድተውታል። እናንት ወላጆች፣ በልጆቻችሁ ላይ አዎንታዊና ገንቢ ተጽዕኖ ሊያሳድሩ የሚችሉ ሰዎችን እቤታችሁ ትጋብዛላችሁ?—ሚልክያስ 3:16
እርግጥ ነው፣ ሁላችንም ከላይ እንደተጠቀሱት ሰዎች በሙሉ ጊዜ አገልግሎት መካፈል አንችል ይሆናል። ይሁን እንጂ ‘በፍጹም ልባችን፣ በፍጹም ነፍሳችንና በፍጹም አሳባችን’ ይሖዋን መውደድ ልንማር እንችላለን። (ማቴዎስ 22:37) ወዳጅ ለማድረግ የምንመርጣቸው እኩዮች ይህ ዓይነቱን ፍቅር ለማሳደግም ሆነ ወደፊት የዘላለም ሕይወት ለመውረስ እንድንችል ከፍተኛ ሚና ይጫወታሉ።
መዝሙራዊው ሕይወትን የተሳካ ለማድረግ የሚያስችለውን ቀላልና ውጤታማ የሆነውን ዘዴ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል:- “ምስጉን ነው በክፉዎች ምክር ያልሄደ፣ በኃጢአተኞችም መንገድ ያልቆመ፣ በዋዘኞችም ወንበር ያልተቀመጠ። ነገር ግን በእግዚአብሔር ሕግ ደስ ይለዋል፣ ሕጉንም በቀንና በሌሊት ያስባል። እርሱም በውኃ ፈሳሾች ዳር እንደ ተተከለች፣ ፍሬዋንም በየጊዜዋ እንደምትሰጥ፣ ቅጠልዋም እንደማይረግፍ ዛፍ ይሆናል፤ የሚሠራውም ሁሉ ይከናወንለታል።”—መዝሙር 1:1-3
ይህ እንዴት ያለ አስደናቂ ዋስትና ነው! ምንም እንኳ ፍጹም ያልሆንና ስህተቶች የምንሠራ ብንሆንም ይሖዋ እንዲመራን ከፈቀድንለትና አምላክ የሰጠንን በጎ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ እኩዮች የሞሉበትን ማለትም ‘ዓለም አቀፉን የወንድማማች ማኅበር’ በአግባቡ ከተጠቀምንበት ሕይወታችን የተሳካ ይሆናል።—1 ጴጥሮስ 5:9
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ጉባኤ በጎ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ እኩዮች የሚገኙበት ቦታ ነው
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ወላጆች፣ ልጆቻችሁ ከሚያንጹ እኩዮች ጋር እንዲውሉ አበረታቷቸው