የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w99 8/1 ገጽ 26-31
  • የይሖዋን አመራር በደስታ መቀበል

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • የይሖዋን አመራር በደስታ መቀበል
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1999
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • የሕይወት አቅጣጫዬን ማስተካከል
  • አቅኚ ሆነን ያገኘነው ጠቃሚ ሥልጠና
  • ውጭ አገር ለማገልገል ራስን ማቅረብ
  • አንዴ ዋሽንግተን፣ ሌላ ጊዜ ጊልያድ
  • በዓለም አቀፉ ዋና መሥሪያ ቤት ማገልገል
  • በጊልያድ በቋሚነት መመደብ
  • ከተማሪዎቹ ጋር መሥራት
  • የወደፊቱን ጊዜ በጉጉት መጠባበቅ
  • የ50 ዓመት ዕድሜ ያለውና አሁንም በተሳካ ሁኔታ በመሥራት ላይ የሚገኘው የጊልያድ ትምህርት ቤት
    መጠበቂያ ግንብ—1993
  • ለምድር አቀፉ የሰብል መሰብሰብ ሥራ የሚያገለግሉ ተጨማሪ ሚስዮናውያን
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1991
  • የጊልያድ ትምህርት ቤት ዓለም አቀፋዊ ተደራሽነት
    የምታደርጉት መዋጮ ጥቅም ላይ እየዋለ ያለው እንዴት ነው?
  • ከጎበዝ ተማሪነት ወደ ውጤታማ ሚስዮናዊነት
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1997
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1999
w99 8/1 ገጽ 26-31

የይሖዋን አመራር በደስታ መቀበል

በዩሊሴዝ ቪ ግላስ እንደተነገረው

በዓይነቱ ልዩ የሆነ ሥነ ሥርዓት ነበር። የሚመረቁት ተማሪዎች 127 ብቻ ሲሆኑ በምረቃው ፕሮግራም ላይ ግን ከተለያዩ አገሮች የመጡ 126,387 ደስተኛ ሰዎች ተገኝተው ነበር። ይህ አስደሳች ክንውን ሐምሌ 19, 1953 በኒው ዮርክ ያንኪ ስታዲዮም የተካሄደው የጊልያድ የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት የ21ኛው ክፍል የምረቃ ሥነ ሥርዓት ነበር። ይህ የምረቃ ሥነ ሥርዓት በሕይወቴ ውስጥ ከፍተኛ ትርጉም ያዘለ ክንውን የሆነው ለምንድን ነው? እስቲ ከዚያ በፊት ትንሽ ስለ አስተዳደጌ ልንገራችሁ።

ራእይ 12:​1-5 ላይ የተገለጸው መሲሐዊ መንግሥት ከመወለዱ ከሁለት ዓመት ገደማ በፊት የካቲት 17, 1912 በቪንሴንስ፣ ኢንዲያና፣ ዩ ኤስ ኤ ተወለድኩ። ወላጆቼ እኔ ከመወለዴ በፊት በነበረው ዓመት የቅዱሳን ጽሑፎች ጥናት በተባሉት ጥራዞች አማካኝነት መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ጀምረው ነበር። ሁልጊዜ እሁድ እሁድ ጠዋት አባቴ ከእነዚህ መጻሕፍት አንዱን ለቤተሰቡ ካነበበ በኋላ በሐሳቡ ላይ እንወያይ ነበር።

እናቴ የተማረችውን ነገር የልጆችዋን አስተሳሰብ ለመቅረጽ ትጠቀምበት ነበር። ደግና ሌሎችን ለመርዳት ወደኋላ የማትል በጣም ጥሩ ሰው ነበረች። ለልጅ ያላት ፍቅር በአራት ልጆቿ ብቻ የተወሰነ ሳይሆን የጎረቤቶቻችንን ልጆች ጭምር የሚያቅፍ ነበር። አብራን ጊዜ ታሳልፍ ነበር። የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮችን ለእኛ መንገርና አብራን መዘመር ያስደስታት ነበር።

በተጨማሪም በስብከቱ ሥራ የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች የነበሩ የተለያዩ ወንድሞችን እቤታችን ትጋብዝ ነበር። አብዛኛውን ጊዜ ስብሰባዎች እየመሩና ንግግሮች እየሰጡ ለአንድ ወይም ለሁለት ቀናት ያህል እኛ ቤት ያርፉ ነበር። በተለይ ምሳሌዎች የሚጠቀሙትንና ታሪክ የሚነግሩንን ወንድሞች በጣም እንወዳቸው ነበር። አንድ ወቅት በ1919 አንደኛው የዓለም ጦርነት ካበቃ ከአንድ ዓመት ገደማ በኋላ ሊጎበኘን የመጣ አንድ ወንድም ያቀረበው ንግግር በተለይ በልጆች ላይ ያተኮረ ነበር። ዛሬ ይበልጥ በትክክለኛ አጠራር ራስን መወሰን ብለን ስለምንጠቅሰው ለአምላክ የተለዩ ስለመሆን በማብራራት ጉዳዩ ከሕይወታችን ጋር ምን ዝምድና እንዳለው እንዲገባን ረድቶናል። የዚያኑ ዕለት ምሽት ከመተኛቴ በፊት ወደ ሰማያዊ አባቴ ጸለይኩና ዘወትር እርሱን ማገልገል እንደምፈልግ ገለጽኩለት።

ሆኖም ከ1922 በኋላ በሕይወቴ ያጋጠሙኝ ሌሎች ጉዳዮች ያደረግሁትን ውሳኔ በአንደኛ ደረጃ እንዳላስቀምጥ አደረጉኝ። ከቦታ ቦታ እንዘዋወር የነበረ ሲሆን ከይሖዋ ሕዝቦች ጉባኤ ጋር የነበረንንም ግንኙነት አቋርጠን ነበር። አባቴ በአንድ የባቡር ኩባንያ ውስጥ ተቀጥሮ ስለሚሠራ ቤት አይቀመጥም ነበር። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችንም ቋሚ አልነበረም። የንግድ ዕቃዎች አሻሻጭ ለመሆን በማሰብ የትምህርት ምርጫዬን ከዚያ አኳያ አደረግሁና ዕውቅ ወደ ሆነ ዩኒቨርሲቲ የመግባት እቅድ አወጣሁ።

የሕይወት አቅጣጫዬን ማስተካከል

በ1930ዎቹ አጋማሽ ላይ ዓለም እንደገና ዓለም አቀፍ ወደሆነ ጦርነት ማምራት ጀምሮ ነበር። በኦሃዮ ክሌቭላንድ ሳለን አንድ ቀን አንድ የይሖዋ ምሥክር እቤታችን መጥቶ አነጋገረን። ከዚያን ጊዜ ወዲህ ልጆች ሳለን ስለተማርናቸው ነገሮች ይበልጥ በቁምነገር ማሰብ ጀመርን። በተለይ ታላቅ ወንድሜ ራስል ቁም ነገረኛ ስለነበረ ከሁላችንም በፊት የተጠመቀው እርሱ ነው። ምንም እንኳ የእርሱን ያህል ቁም ነገረኛ ባልሆንም እኔም የካቲት 3, 1936 ተጠመቅሁ። ራስን ለይሖዋ መወሰን ምን ነገሮችን እንደሚያካትት ያለኝ ግንዛቤ እያደገ የመጣ ከመሆኑም በላይ የይሖዋን አመራር መቀበልን ተማርኩ። በዚያው ዓመት ካተሪንና ገርትሩድ የሚባሉት ሁለቱ እህቶቼም ተጠመቁ። ከዚያም ሁላችንም አቅኚ በመሆን የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ጀመርን።

ይህ ማለት ግን ስለ ሌላ ነገር ፈጽሞ አናስብም ነበር ማለት አይደለም። የወንድሜ ሚስት፣ እውነትን ከሰማችበት ጊዜ አንስቶ “በጣም ስለተደሰተችው” እና እኛ ቤት ለስብሰባ ስለምትመጣው አን ስለምትባለው በጣም ቆንጆ ልጃገረድ ስትነግረኝ ጆሮዬ ቀጥ አለ። በዚያን ወቅት አን በአንድ የሕግ ቢሮ በጸሐፊነት ትሠራ የነበረ ሲሆን በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ተጠመቀች። የማግባት እቅድ ያልነበረኝ ቢሆንም አን እውነትን ከልቧ እንደምትወድ ግልጽ ነበር። በይሖዋ አገልግሎት ሙሉ በሙሉ መጠመድ ትፈልግ ነበር። “ይህን ለማድረግ አቅሜ ይፈቅድልኛል?” የምትል ዓይነት ሴት አልነበረችም። ከዚህ ይልቅ “ይህን ነገር ለማድረግ ከሁሉ የተሻለው መንገድ የትኛው ነው?” በማለት ትጠይቃለች። ከዚያም ነገሩን ዳር ለማድረስ ቆርጣ ትነሳለች። ይህ አዎንታዊ አመለካከቷ ሳበኝ። ከዚህ በተጨማሪ በጣም ቆንጆ ሴት ነበረች፤ አሁንም ቆንጆ ነች። በመጨረሻ የትዳር ጓደኛዬ ሆነች፤ ከዚያ ብዙም ሳይቆይ በአቅኚነት አገልግሎት አብራኝ መካፈል ጀመረች።

አቅኚ ሆነን ያገኘነው ጠቃሚ ሥልጠና

አቅኚ ሆነን ስናገለግል ቁሳዊ ነገሮችን ስናገኝም ሆነ ስናጣ ባለን ነገር እንዴት ረክተን መኖር እንደምንችል ተምረናል። (ፊልጵስዩስ 4:​11-13) አንድ ቀን ቤታችን ውስጥ የሚላስ የሚቀመስ ነገር አልነበረም፤ ቀኑ ደግሞ እየመሸ ነበር። በእጃችን ላይ የነበረን ገንዘብ ደግሞ አምስት ሳንቲም ብቻ ነበር። ወደ አንድ ሉካንዳ ቤት ገባንና “የአምስት ሳንቲም ሥጋ ልትሰጠን ትችላለህ?” ስል ጠየቅሁት። በመገረም አየት አደረገንና አራት ቁራጭ ሥጋ ሰጠን። ሥጋው ከአምስት ሳንቲም በላይ እንደሚያወጣ እርግጠኛ ነኝ፤ ሥጋውን ተመግበን መጠነኛ ብርታት አገኘን።

አገልግሎታችንን ስናከናውን ከባድ ተቃውሞ ማጋጠሙ ያልተለመደ ነገር አልነበረም። አንድ ቀን በኒው ዮርክ ሲራኩስ አቅራቢያ በሚገኝ አንድ ከተማ ውስጥ አንድን ልዩ የሕዝብ ንግግር ርዕስ የሚያስተዋውቅ ከፊትና ከኋላ በትከሻ ላይ የሚንጠለጠል ማስታወቂያ አንግተን በራሪ ወረቀቶችን እናሰራጭ ነበር። ሁለት ጠብደል ሰዎች አፈፍ አድርገው ያዙኝና ያንገላቱኝ ጀመር። አንደኛው የፖሊስ መኮንን ቢሆንም የደንብ ልብሱን አልለበሰም ነበር። መታወቂያውን እንዲያሳየኝ ላቀረብኩት ጥያቄ ጨርሶ ጆሮም አልሰጠው። በዚህ ጊዜ ብሩክሊን ቤቴል የሚያገለግለው ግራንት ሱተር እንደ አጋጣሚ መጣና ችግሩን ለመፍታት ወደ ፖሊስ ጣቢያ መሄድ እንዳለብን ተናገረ። ከዚያም ብሩክሊን ወደሚገኘው የማኅበሩ ቢሮ ስልክ ደወለና በዚያው ዕለት እኔና ባለቤቴ ከፊትና ከኋላ የሚንጠለጠል ማስታወቂያ አንግተን እንዲሁም የስብሰባ መጋበዣ ወረቀት ይዘን እንድንወጣ መመሪያ ተሰጠን። ይህ የተደረገው ተጨባጭ ማስረጃ ለማግኘት ነበር። እንደተጠበቀው ሁሉ ተይዘን ታሰርን። ሆኖም ያላግባብ በማሰራቸው ፖሊሶቹን እንደምንከሳቸው ስንነግራቸው ለቀቁን።

በሚቀጥለው ቀን በአንድ ቄስ ቆስቋሽነት ሥርዓት አልበኛ የሆኑ በርካታ ጎረምሶች የተሰበሰብንበትን ቦታ ወረሩ። በአካባቢው አንድም ፖሊስ አልነበረም። ዱርዬዎቹ ሳንቃውን በቤዝ ቦል መጫወቻ ዱላ ከመደብደባቸውም በላይ አንዳንድ አድማጮችን ከአግዳሚ መቀመጫዎች ላይ ይጥሏቸው ጀመር። እንዲሁም መድረኩ ላይ የአሜሪካ ባንዲራ ይዘው ወጥተው “ለባንዲራው ሰላምታ ስጡ!” እያሉ ጮኹ። በዚህም አላበቁም “ቢር ባረል ፖልካ” የተባለውን ዘፈን መዝፈን ጀመሩ። ስብሰባውን ሙሉ በሙሉ አስቆሙን። ኢየሱስ “ነገር ግን እኔ ከዓለም መረጥኋችሁ እንጂ ከዓለም ስለ አይደላችሁ ስለዚህ ዓለም ይጠላችኋል” ሲል የተናገረው ነገር የያዘውን ትርጉም በራሳችን ላይ ከደረሰው ሁኔታ አይተናል።​—⁠ዮሐንስ 15:​19

የሕዝብ ንግግሩ በወቅቱ የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ፕሬዚዳንት የነበረው ወንድም ጄ ኤፍ ራዘርፎርድ የሰጠው ንግግር የሸክላ ቅጂ ነበር። እኔና አን በዚያ ከተማ ለጥቂት ቀናት የቆየን ሲሆን ሰዎች ቤታቸው ሆነው ንግግሩን የመስማት አጋጣሚ እንዲያገኙ ሄደን አነጋግረናቸዋል። ጥቂቶች ይህን ግብዣ ተቀብለዋል።

ውጭ አገር ለማገልገል ራስን ማቅረብ

ከጊዜ በኋላ አዳዲስ የአገልግሎት መስኮች ተከፈቱ። ወንድሜ ራስልና ባለቤቱ ዶሮቲ በ1943 በጊልያድ ትምህርት ቤት የመጀመሪያ ክፍል እንዲሳተፉ ተጋበዙና ከዚያም ሚስዮናውያን ሆነው ወደ ኩባ ተላኩ። እህቴ ካተሪን ደግሞ አራተኛውን ክፍል ተካፈለች። እርሷም ብትሆን ወደ ኩባ ተላከች። ከጊዜ በኋላ በዶሚኒካን ሪፑብሊክ የተመደበች ሲሆን ከዚያም ወደ ፖርቶ ሪኮ ተላከች። እኔና አንስ?

ስለ ጊልያድ ትምህርት ቤትና ማኅበሩ ወደ ሌሎች አገሮች ሚስዮናውያን መላክ እንደሚፈልግ ስንሰማ ለውጭ አገር አገልግሎት ራሳችንን ማቅረብ እንዳለብን ተሰማን። መጀመሪያ በራሳችን ወጪ ምናልባት ወደ ሜክሲኮ ብንሄድ ይሻላል ብለን አሰብን። ከጊዜ በኋላ ግን በጊልያድ ትምህርት ቤት ከተካፈልን በኋላ ማኅበሩ ቢመድበን የተሻለ ሊሆን እንደሚችል ወሰንን። ይሖዋ እየተጠቀመበት ያለው ዝግጅት ይህ መሆኑን ተገነዘብን።

በአራተኛው ክፍል የጊልያድ ትምህርት ቤት እንድንሳተፍ ተጋበዝን። ሆኖም ትምህርት ቤቱ ከመከፈቱ ከጥቂት ጊዜ በፊት በወቅቱ የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ፕሬዚዳንት የነበረው ኤን ኤች ኖር፣ አን በልጅነቷ ይዟት የነበረው ፖልዮ ያስከተለባትን የአቅም ማነስ ይበልጥ አስተዋለ። ይህን ጉዳይ በተመለከተ እኔን አነጋገረኝና እኛን ሌላ አገር ሄደን እንድናገለግል መላክ ጥበብ እንደማይሆን ወሰነ።

ከሁለት ዓመት ገደማ በኋላ ወንድም ኖር ለአውራጃ ስብሰባ በሚደረግ ቅድመ ዝግጅት ላይ ስሠራ አገኘኝና አሁንም በጊልያድ የመካፈል ፍላጎት እንዳለን ጠየቀኝ። በአእምሮው የያዘው ሌላ ነገር ስላለ በጊልያድ ብንካፈልም እንኳ ወደ ውጭ አገር እንደማንላክ ነገረኝ። ስለዚህ ዘጠነኛው ክፍል የካቲት 26, 1947 ላይ ሲመዘገብ እኛም የተማሪዎቹ ዝርዝር ውስጥ ተጨመርን።

በጊልያድ ያሳለፍናቸው እነዚያ ጊዜያት ፈጽሞ የማይረሱ ናቸው። ትምህርቶቹ መንፈሳዊ ጥልቀት ነበራቸው። የዕድሜ ልክ ወዳጆች አፍርተናል። ሆኖም ከትምህርት ቤቱ ጋር የነበረኝ ቁርኝት ከዚያ በላይ አልፎ ሄዷል።

አንዴ ዋሽንግተን፣ ሌላ ጊዜ ጊልያድ

በዚህ ጊዜም የጊልያድ ትምህርት ቤት ከሌሎች አንጻር ሲታይ አዲስ ነበር። የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት ስለ ትምህርት ቤቱ ዓላማ በቂ ግንዛቤ ስላልነበረው ብዙ ጥያቄዎች ይነሱ ነበር። ማኅበሩ በዋሽንግተን ዲ ሲ ወኪል ለማስቀመጥ ፈለገ። ከጊልያድ ከተመረቅን ከጥቂት ወራት በኋላ ወደዚያ ተላክን። ከሌሎች አገሮች ወደ ጊልያድ እንዲመጡ የተጋበዙ ወንድሞች ቪዛ እንዲያገኙና ተመራቂዎቹን ለሚስዮናዊነት ሥራ ወደ ውጭ አገር መላክ እንዲቻል ሕጋዊ ሰነዶች እንዲያገኙ መርዳት ነበረብኝ። አንዳንድ ባለ ሥልጣኖች የማያዳሉና በጣም ተባባሪዎች ነበሩ። ሌሎች ደግሞ ለይሖዋ ምሥክሮች ከፍተኛ ጥላቻ ነበራቸው። አክራሪ ፖለቲካዊ አመለካከት የነበራቸው ጥቂት ባለ ሥልጣኖች አስጊ እንደሆኑ ከሚቆጥሯቸው ቡድኖች ጋር ግንኙነት እንዳለን በጽኑ ያምኑ ነበር።

ለሥራ ጉዳይ ወደ ቢሮው ሄጄ የነበረ አንድ ሰው ለባንዲራ ሰላምታ ስለማንሰጥና ወደ ጦርነት ስለማንሄድ ክፉኛ ወቀሰን። ስለዚህ ጉዳይ ለተወሰነ ጊዜ ደንፍቶ እስኪጨርስ ከጠበቅሁት በኋላ እንዲህ አልኩት:- “የይሖዋ ምሥክሮች በዚህ ዓለም ላይ ከማንም ጋር እንደማይዋጉ እንድታውቅ እፈልጋለሁ፤ ደግሞም ይህን አሳምረህ ታውቀዋለህ። እኛ በዓለም ጉዳዩች ውስጥ ጣልቃ አንገባም። በሚያካሂዱት ጦርነትና ፖለቲካ ውስጥ እጃችንን አናስገባም። ሙሉ በሙሉ ገለልተኞች ነን። እናንተ የሚገጥሟችሁን ችግሮች ገና ድሮ ተወጥተናቸዋል፤ ድርጅታችን ውስጥ አንድነት አለ። . . . ታዲያ ምን እንድናደርግ ነው የምትፈልገው? የእኛን መንገድ ትተን እናንተ ወደምትከተሉት መንገድ እንድንመለስ ትፈልጋለህ?” ከዚህ በኋላ አንዲት ቃል ትንፍስ አላለም።

በመንግሥት ቢሮዎች እየሄድኩ ሥራ ለማስፈጸም በሳምንት ሁለት ሙሉ ቀን መድቤ ነበር። ከዚህ በተጨማሪ በልዩ አቅኚነት እናገለግል ነበር። በዚያን ጊዜ ይህ ሥራ በመስክ አገልግሎት ላይ በየወሩ 175 ሰዓት ማሳለፍ ይጠይቅ ነበር (ከጊዜ በኋላ ወደ 140 ሰዓት ተቀይሯል)። ስለዚህ አብዛኛውን ጊዜ እስከ ማታ ድረስ እናገለግል ነበር። ያሳለፍነው ጊዜ አስደሳች ነበር። የቤተሰቡ አባላት በሙሉ የሚሳተፍበት በርካታ ግሩም ጥናቶች የመራን ሲሆን እነርሱም ጥሩ እድገት አድርገዋል። እኔና አን ልጆች ላለመውለድ የወሰንን ቢሆንም በመንፈሳዊ ሁኔታ ግን ልጆች ብቻ ሳይሆን የልጅ ልጆችና የልጅ ልጅ ልጆች አሉን። እነርሱን በማግኘታችን ልባችን ምንኛ በደስታ ተሞልቷል!

በ1948 ማብቂያ ላይ ተጨማሪ ሥራ ተሰጠኝ። ወንድም ኖር በዚያን ወቅት የጊልያድ ትምህርት ቤት ሬጂስትራርና አስተማሪ የሆነው ወንድም ሽሮደር ሌላ አንገብጋቢ ሥራ ሊጀምር እንደሆነ ከገለጸልኝ በኋላ በሚያስፈልግበት ጊዜ ሁሉ እሱን ተክቼ እንዳስተምር ጠየቀኝ። ልቤ በፍርሃት እየመታ ታኅሣሥ 18 ቀን ከአን ጋር በደቡብ ላንሲንግ ኒው ዮርክ ወደሚገኘው ጊልያድ ተመልሼ መጣሁ። መጀመሪያ ላይ፣ ወደ ጊልያድ ስንሄድ ለጥቂት ሳምንታት ብቻ በዚያ እንቆይና ከዚያም ወደ ዋሽንግተን እንመለስ ነበር። ሆኖም ውሎ አድሮ በዋሽንግተን ከማሳልፈው ጊዜ ይልቅ በጊልያድ የማሳልፈው ጊዜ ይበልጥ ጀመር።

አስቀድሜ በመግቢያዬ ላይ እንደጠቀስኩት የ21ኛው ክፍል የጊልያድ ተማሪዎች ኒው ዮርክ ውስጥ በያንኪ ስታዲዮም የተመረቁት በዚህ ወቅት ነበር። ከአስተማሪዎቹ አንዱ በመሆን በዚያ የምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ የመካፈል መብት አግኝቼ ነበር።

በዓለም አቀፉ ዋና መሥሪያ ቤት ማገልገል

የካቲት 12, 1955 ሌላ የአገልግሎት ምድብ ተቀበልን። በዓለም አቀፋዊው የሚታየው የይሖዋ ድርጅት ዋና መሥሪያ ቤት ውስጥ የቤቴል ቤተሰብ አባላት ሆንን። ሆኖም ይህ ምን ያካትታል? በመሠረቱ የተመደበልንን ማንኛውንም ዓይነት ሥራ ለመሥራት ፈቃደኛ መሆን እንዲሁም ከሌሎች ጋር ተባብሮ መሥራት በሚጠይቁ ፕሮጀክቶች መሳተፍን ይጨምራል። እርግጥ ከዚህ ቀደም በዚህ መልክ የሠራን ቢሆንም አሁን ግን በጣም ሰፊ የሆነው የዓለም አቀፉ የቤቴል ቤተሰብ ክፍል መሆናችን ነው። ይህን አዲስ የሥራ ምድብ የይሖዋ አመራር መኖሩን የሚያሳይ ማረጋገጫ አድርገን በደስታ ተቀበልነው።

ሥራዬ በአብዛኛው ከመገናኛ ብዙሐን ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን የሚያካትት ነበር። ጋዜጠኞች የሰዎችን ትኩረት የሚስብ ነገር መጻፍ ስለሚፈልጉና ለእኛ መሠረተ ቢስ ጥላቻ ካላቸው ምንጮች መረጃ ስለሚያገኙ ስለ ይሖዋ ምሥክሮች አንዳንድ መጥፎ ነገሮች ይጽፉ ነበር። ይህን ሁኔታ ለማሻሻል እንጥር ነበር።

ወንድም ኖር ሁላችንም በቂ ሥራ እንዲኖረን ስለሚፈልግ ሌሎች ሥራዎችም ነበሩን። ከእነዚህ ሥራዎች አንዳንዶቹ የንግድ ዕቃዎች አሻሻጭ ሆኜ ስሠራ ያካበትኳቸውን ሙያዎች እንድጠቀም አድርገውኛል። የምሠራቸው ሌሎች ሥራዎች ከማኅበሩ የራዲዮ ጣቢያ ከደብሊው ቢ ቢ አር ጋር ግንኙነት ነበራቸው። ማኅበሩ ከሚያዘጋጃቸው ተንቀሳቃሽ ፊልሞች ጋር በተያያዘ የሚሠራ ሥራ ነበር። ቲኦክራሲያዊ ታሪክ በጊልያድ ከሚሰጡ ትምህርቶች አንዱ እንደነበር የታወቀ ነው። አሁን ግን ተጨማሪ ቁጥር ያላቸው የይሖዋ ሕዝቦች ዘመናዊውን የቲኦክራሲያዊ ድርጅት ታሪክ በዝርዝር እንዲያውቁና ለሕዝብም እንዲዳረስ ለማድረግ ልዩ ልዩ ፕሮጀክቶች ተጀምረው ነበር። ሌላው በጊልያድ የሚሰጥ ሥልጠና የሕዝብ ተናጋሪነትን ይጨምር ነበር። እንዲሁም በየጉባኤዎች ላሉ ወንድሞች ለሕዝብ ተናጋሪነት የሚያስፈልጉ ተጨማሪ መሠረታዊ ነገሮች ለማዘጋጀት መሠራት ያለበት ሥራ ነበር። በመሆኑም ብዙ የሚሠራ ነገር ነበር።

በጊልያድ በቋሚነት መመደብ

በ1961 ለተጓዥ የበላይ ተመልካቾችና ለቅርንጫፍ ቢሮ አባላት የሚሰጠው ሥልጠና ተቃርቦ ስለነበር የጊልያድ ትምህርት ቤት፣ የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ዋና ዋና ቢሮዎች ወደሚገኙበት ወደ ብሩክሊን ተዛወረ። እንደገና ወደ ትምህርት ቤቱ የተመለስኩ ሲሆን በዚህ ጊዜ ግን በተተኪ አስተማሪነት ሳይሆን የፋኩልቲው ቋሚ አባል ሆኜ ነበር። እንዴት ያለ መብት ነው! ጊልያድ ትምህርት ቤት የሚታየውን የይሖዋን ድርጅት ባጠቃላይ የጠቀመ ከእርሱ የተገኘ ስጦታ እንደሆነ በጽኑ አምናለሁ።

በብሩክሊን በተካሄዱት የጊልያድ ክፍሎች የተማሩት በቀድሞዎቹ ክፍሎች የነበሩ ተማሪዎች ያላገኟቸውን አጋጣሚዎች አግኝተዋል። ተጋብዘው የሚመጡ ተጨማሪ አስተማሪዎች ነበሩ፣ ከአስተዳደር አካሉ ጋር የቅርብ ግንኙነት ማድረግ እንዲሁም በዋናው መሥሪያ ቤት ካለው የቤቴል ቤተሰብ ጋር ሰፊ ወዳጅነት መመሥረት ይችሉ ነበር። ከዚህ በተጨማሪ ተማሪዎቹ የቢሮ አሠራር፣ የቤቴል ቤቶች ሥራ የማካሄድና የተለያዩ የፋብሪካ ሥራዎች ሥልጠና ያገኙ ነበር።

ላለፉት ዓመታት የተማሪዎቹም ሆነ የአስተማሪዎቹ ቁጥር ከፍ ዝቅ ይል ነበር። ትምህርት ቤቱ የነበረበት ቦታም ብዙ ጊዜ ተቀያይሯል። አሁን ትምህርት ቤቱ ፓተርሰን ኒው ዮርክ ውስጥ በአንድ የሚያምር አካባቢ ይገኛል።

ከተማሪዎቹ ጋር መሥራት

እነዚህን ክፍሎች ማስተማር እጅግ አስደሳች ነበር! እዚህ የሚመጡት ወጣቶች በአሮጌው ሥርዓት ውስጥ ያሉ ነገሮችን የመሥራት ፍላጎት የላቸውም። ቤተሰባቸውን፣ ጓደኞቻቸውን፣ ቤታቸውን እንዲሁም የእነርሱን ቋንቋ የሚናገር ሕዝብ ትተው ይመጣሉ። የአየሩ ጠባይ፣ ምግቡ እንዲሁም ሌላው ነገር ሁሉ የተለየ ይሆናል። ሌላው ቀርቶ ወደየትኛው አገር እንደሚላኩ እንኳ አያውቁም፤ ሆኖም ሚስዮናውያን የመሆን ግብ አላቸው። እንደዚህ ዓይነቶቹን ሰዎች ለሥራ መገፋፋት አያስፈልጋችሁም።

ለማስተማር ወደ ክፍል ስገባ ምንጊዜም ተማሪዎቹ ዘና ብለው እንዲማሩ የማድረግ ግብ ነበረኝ። ማንኛውም ሰው በሐሳብ ተወጥሮና ተጨንቆ በጥሩ ሁኔታ ሊማር አይችልም። አስተማሪ መሆኔ የታወቀ ነው፤ ሆኖም ተማሪ መሆን ምን ማለት እንደሆነ አይረሳኝም። በአንድ ወቅት እኔም ተማሪ ነበርኩ። እርግጥ ነው፣ በጊልያድ ቆይታቸው በትጋት ያጠኑና ብዙ ትምህርት ይሸፍኑ የነበረ ቢሆንም በዚያ የሚያሳልፉት ጊዜ አስደሳች እንዲሆንላቸው ፍላጎት ነበረኝ።

ወደ ምድብ ቦታቸው ሲሄዱ ስኬታማ ለመሆን አንዳንድ ነገሮች እንደሚያስፈልጓቸው አውቃለሁ። ጠንካራ እምነት ያስፈልጋቸዋል። በከፍተኛ መጠን ትሕትና ማዳበር ያስፈልጋቸዋል። ከሌሎች ሰዎች ጋር ተግባብቶ መኖርን፣ በሕይወታቸው የሚያጋጥሟቸውን ሁኔታዎች መቀበልን እንዲሁም በነፃ ይቅር ማለትን መማር ነበረባቸው። የመንፈስ ፍሬ መኮትኮታቸውን መቀጠል አለባቸው። በተጨማሪም ሰዎችንና እንዲያከናውኑ የተላኩትን ሥራ መውደድ ያስፈልጋቸዋል። በጊልያድ ቆይታቸው ወቅት ደጋግሜ ለተማሪዎቹ ማስገንዘብ የምፈልገው እነዚህን ነገሮች ነው።

እርግጥ ምን ያህል ተማሪዎች እንዳስተማርኩ በትክክል አላውቀውም። ሆኖም ለእነርሱ የሚሰማኝን ስሜት አውቀዋለሁ። ክፍል ውስጥ አብሬአቸው አምስት ወር ካሳለፍኩ በኋላ ለእነርሱ ከፍተኛ ፍቅር ያድርብኛል። ከዚያም በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ቀን መድረክ ላይ ወጥተው ዲፕሎማቸውን ሲቀበሉ ስመለከት ትምህርቱን በተሳካ ሁኔታ እንዳጠናቀቁና ብዙም ሳይቆይ ትምህርት ቤቱን ለቀው እንደሚሄዱ ይገባኛል። የተወሰነ የቤተሰቤ ክፍል የሄደ ያህል ይሰማኛል። ራሳቸውን ለማቅረብና እነዚህ ወጣቶች ሊያከናውኑ ያሉትን ሥራ ለመሥራት ፈቃደኛ የሆኑ ሰዎችን ከማፍቀር እንዴት መቆጠብ ትችላላችሁ?

ከዓመታት በኋላ ለእረፍት ተመልሰው መጥተው በአገልግሎት ያገኙትን ደስታ ሲናገሩ በምሰማበት ጊዜ አሁንም ሥልጠና የቀሰሙበትን ሥራ እየሠሩና ምድብ ቦታቸው ላይ እንዳሉ እረዳለሁ። ይህን ማወቄ ምን ስሜት ያሳድርብኛል? ደስታዬን የምገልጽበት ቃላት ያጥረኛል።

የወደፊቱን ጊዜ በጉጉት መጠባበቅ

በአሁኑ ጊዜ ዓይኔ እየደከመ ሲሆን ይህም አቅሜን ውስን አድርጎታል። የሚያስከትለው ስጋትም ይሰማኛል። ከተወሰነ ጊዜ አንስቶ በጊልያድ ትምህርት ቤት ማስተማር አቁሜአለሁ። መጀመሪያ ላይ ሁኔታውን መቀበል ከብዶኝ ነበር። ሆኖም በሕይወቴ ዘመን ሁሉ አዳዲስ ሁኔታዎችን መቀበልና ከእነርሱም ጋር ተስማምቶ መኖርን ተምሬአለሁ። አብዛኛውን ጊዜ ሐዋርያው ጳውሎስ የነበረበት ‘የሥጋ መውጊያ’ ትዝ ይለኛል። ጳውሎስ ከነበረበት ሥቃይ ለመገላገል ሦስት ጊዜ የጸለየ ቢሆንም ጌታ “ጸጋዬ ይበቃሃል፣ ኃይሌ በድካም ይፈጸማልና” ብሎታል። (2 ቆሮንቶስ 12:​7-10) ጳውሎስ ሥቃዩን ችሎ ኖሯል። እርሱ ከቻለ እኔ ደግሞ መሞከር አለብኝ። ምንም እንኳ ማስተማር ባቆምም አሁንም ተማሪዎቹ በየቀኑ ሲወጡና ሲገቡ የማየት አጋጣሚ ስላለኝ ደስተኛ ነኝ። አንዳንድ ጊዜ ከተማሪዎቹ ጋር የመነጋገር አጋጣሚ አገኛለሁ፤ እንዲሁም ስለሚያሳዩት መልካም ዝንባሌ ሳስብ ልቤ በደስታ ይሞላል።

የወደፊቱ ጊዜ በያዘው ተስፋ ላይ ማሰላሰል በጣም አስደሳች ነው። አሁን ለዚያ የሚሆን መሠረት በመጣል ላይ ነው። በዚህ ረገድ ጊልያድ የጎላ ድርሻ አበርክቷል። ከታላቁ መከራ በኋላ ራእይ 20:​12 ላይ የተጠቀሱት ጥቅልሎች ሲፈቱ የይሖዋን መንገዶች በተመለከተ ለአንድ ሺህ ዓመት የሚዘልቅ ተጨማሪ ሰፊ ትምህርት ይኖራል። (ኢሳይያስ 11:​9) ይሁን እንጂ ይህም ቢሆን የመጨረሻ አይሆንም። ይህ የነገሩ መጀመሪያ ብቻ እንደሆነ የታወቀ ነው። በዘመናት ሁሉ ስለ ይሖዋ የምንማረውም ሆነ የእርሱ ዓላማ መገለጡን እያየን ስንሄድ የምንሠራው ተጨማሪ ነገር ይኖራል። ይሖዋ የሰጣቸውን ታላላቅ ተስፋዎች በሙሉ እንደሚፈጽም ሙሉ ትምክህት አለኝ። እንዲሁም በዚያን ጊዜ ይሖዋ ለእኛ የሚያወጣውን መመሪያ ለመቀበል በዚያ መገኘት እፈልጋለሁ።

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ1953 በኒው ዮርክ ያንኪ ስታዲዮም የተካሄደው የጊልያድ የምረቃ ሥነ ሥርዓት

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ገርትሩድ፣ እኔ፣ ካተሪን እና ራስል

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የአውራጃ ስብሰባ ለማደራጀት ከኤን ኤች ኖር (በስተ ግራ ጥግ) እና ከኤም ጂ ሄንሸል ጋር ስሠራ

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በደብሊው ቢ ቢ አር የራዲዮ ማሰራጫ ጣቢያ

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በጊልያድ ትምህርት ቤት መማሪያ ክፍል ውስጥ

[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከጥቂት ጊዜያት በፊት ከአን ጋር

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ