የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w99 8/15 ገጽ 19-24
  • ይሖዋ መንገዱን ያዘጋጃል

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ይሖዋ መንገዱን ያዘጋጃል
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1999
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ከባድ ሥራ
  • ሃይማኖታዊ ሁኔታ
  • የሕግ ከለላ
  • ሰላምና መቻቻል የሰፈነባቸው ወቅቶች
  • ቴክኖሎጂ የተጫወተው ሚና
  • ‘የይሖዋን ትምህርት’ እንዲቀበሉ ብሔራትን ማዘጋጀት
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2015
  • ይሖዋ ዓለም አቀፉን የማስተማር ሥራችንን ይመራል
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2015
  • “ሂዱና ከሁሉም ብሔራት ሰዎችን ደቀ መዛሙርት አድርጉ”
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2016
  • ‘ለሕዝብ ሁሉ የሚሰጥ ምስክርነት’
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2006
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1999
w99 8/15 ገጽ 19-24

ይሖዋ መንገዱን ያዘጋጃል

“ይህ የመንግሥት ወንጌል . . . ይሰበካል።”​—ማቴዎስ 24:14

1. በመጀመሪያውም ሆነ በ20ኛው መቶ ዘመን በተሠራው የስብከት ሥራ አማካኝነት ምን ነገር ተከናውኗል?

ይሖዋ የፍቅር አምላክ በመሆኑ ‘ሰዎች ሁሉ እንዲድኑና እውነቱን ወደ ማወቅ እንዲደርሱ’ ይፈልጋል። (1 ጢሞቴዎስ 2:​4) ይህ ደግሞ ዓለም አቀፍ የስብከትና የማስተማር ዘመቻ እንዲካሄድ የሚጠይቅ ሆኗል። በመጀመሪያው መቶ ዘመን የተካሄደው ይህ ስብከት የክርስቲያን ጉባኤ ‘የእውነት አምድና መሠረት’ እንዲሆን አድርጎት ነበር። (1 ጢሞቴዎስ 3:​15) ከዚያ በኋላ የእውነት ብርሃን ደብዝዞ የቆየበት ረጅም የክህደት ዘመን ጀመረ። በቅርብ ዓመታት ማለትም ‘በፍጻሜው ዘመን’ ደግሞ ‘እውነተኛ እውቀት’ እንደገና በመስፋፋቱ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ የዘላለም መዳን ተስፋ አግኝተዋል።​—⁠ዳንኤል 12:​4

2. ይሖዋ ከስብከቱ እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ ምን አድርጓል?

2 ሰይጣን የአምላክን ዓላማ ለማጨናገፍ የቻለውን ያህል ጥረት ቢያደርግም በአንደኛው መቶ ዘመንም ሆነ በ20ኛው መቶ ዘመን የተከናወነው የስብከት ሥራ አስገራሚ ውጤት አስገኝቷል። ይህም የኢሳይያስን ትንቢት ያስታውሰናል። ኢሳይያስ አይሁዳውያን ምርኮኞች በስድስተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ ወደ አገራቸው መመለሳቸውን አስመልክቶ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ሸለቆው ሁሉ ከፍ ይላል፣ ተራራውና ኮረብታውም ሁሉ ዝቅ ይላል፤ ጠማማውም ይቃናል፣ ስርጓጉጡም ሜዳ ይሆናል።” (ኢሳይያስ 40:​4) ከዚህም በተጨማሪ ይሖዋ በመጀመሪያውም ሆነ በ20ኛው መቶ ዘመን ለተከናወነው ታላቅ የስብከት ዘመቻ መንገዱን አዘጋጅቶ ነበር።

3. ይሖዋ በምን መንገዶች ዓላማውን ለማስፈጸም ይችላል?

3 ይህ ማለት ግን ይሖዋ የምሥራቹ ስብከት ሥራ እንዲስፋፋ ሲል በምድር ላይ የሚከናወነውን እያንዳንዱን ነገር በቀጥታ ይቆጣጠር ነበር ወይም የሚፈጸመውን እያንዳንዱን ነገር በዝርዝር ለመከታተል ወደፊት ስለሚሆነው ነገር የማወቅ ችሎታውን ተጠቅሞበታል ማለት አይደለም። ወደፊት የሚሆኑትን ነገሮች አስቀድሞ ለማወቅም ሆነ መልክ ለማስያዝ እንደሚችል የሚክድ አይኖርም። (ኢሳይያስ 46:​9-11) ይሁንና አዳዲስ ነገሮች ሲከሰቱ ለእነዚያ ሁኔታዎች ምላሽ መስጠትም ይችላል። አንድ ጥሩ ተሞክሮ ያለው እረኛ መንጋውን መምራትና መጠበቅ እንደሚያውቅ ሁሉ ይሖዋም በተመሳሳይ መንገድ ሕዝቡን ይመራል። መንፈሳዊነታቸውን በመጠበቅና በዓለም ዙሪያ በተሳካ መንገድ በመከናወን ላይ ያለውን የምሥራች ስብከት የሚያግዙ ሁኔታዎች ሲፈጠሩ በእነዚህ አጋጣሚዎች እንዲጠቀሙ በማንቀሳቀስ ወደ መዳን ይመራቸዋል።​—⁠መዝሙር 23:​1-4

ከባድ ሥራ

4, 5. ምሥራቹን መስበክ ተፈታታኝ ሥራ የሆነው ለምንድን ነው?

4 በኖኅ ዘመን እንደተከናወነው የመርከብ ግንባታ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የተሠራውም ሆነ በዘመናችን የተከናወነው የመንግሥቱ ስብከት ሥራ ትልቅ ፕሮጄክት ነው። ማንኛውንም መልእክት ቢሆን ለሰዎች ሁሉ ማዳረስ ቀላል ሥራ አይደለም። በተለይ ደግሞ የመንግሥቱን መልእክት ማዳረስ ይበልጥ ተፈታታኝ ነበር። በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት ደቀ መዛሙርት ቁጥር በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ ጥቂት ነበር። መሪያቸው ኢየሱስ በመንግሥት ላይ ዓመፅ ያነሳሳል በሚል ውንጀላ ተገድሏል። የአይሁድ ሃይማኖትም ተደላድሎ የኖረ ነበር። በኢየሩሳሌምም ዕጹብ ድንቅ ቤተ መቅደስ ነበር። ከአይሁድ ውጭ ያሉት የሜድትራንያን አካባቢ ሃይማኖቶችም ቢሆኑ ቤተ መቅደስና የክህነት ሥርዓት ያላቸው ሥር የሰደዱ ሃይማኖቶች ነበሩ። ‘የፍጻሜው ዘመን’ በ1914 ሲጀምርም ቅቡዓን ክርስቲያኖች በጣም ጥቂት የነበሩ ሲሆን አምላክን እናገለግላለን በሚሉት ሌሎች ሃይማኖቶች ውስጥ የነበሩት ሰዎች ግን ብዙ ነበሩ።​—⁠ዳንኤል 12:​9

5 ኢየሱስ ስደት እንደሚደርስባቸው ተከታዮቹን አስጠንቅቋቸው ነበር። “ለመከራ አሳልፈው ይሰጡአችኋል ይገድሉአችሁማል፣ ስለ ስሜም በአሕዛብ ሁሉ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ” ብሏል። (ማቴዎስ 24:​9) እንደዚህ ያሉት ችግሮች እንዳይበቁ፣ በተለይ ‘በመጨረሻው ዘመን’ ለሚኖሩት ክርስቲያኖች ጊዜው ጭምር ‘አስጨናቂ’ ይሆንባቸዋል። (2 ጢሞቴዎስ 3:​1) የሥራው ስፋት፣ ስደት መምጣቱ የማይቀር መሆኑና የጊዜው አስጨናቂነት የስብከቱን ሥራ ፈታኝና አስቸጋሪ አድርጎታል። ይህም ትልቅ እምነት ጠይቋል።

6. ይሖዋ ሕዝቦቹ እንደሚሳካላቸው ምን ማረጋገጫ ሰጥቷል?

6 ይሖዋ ችግሮች እንደሚኖሩ ቢያውቅም ሥራውን የሚገታው ምንም ነገር እንደማይኖርም ያውቅ ነበር። በመጀመሪያውም ሆነ በ20ኛው መቶ ዘመን አስገራሚ ፍጻሜውን ባገኘ በሰፊው የሚታወቅ አንድ ትንቢት ውስጥ ሥራው ከዳር እንደሚደርስ አስቀድሞ ተነግሯል:- “ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል።” ​—⁠ማቴዎስ 24:​14 በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።

7. በመጀመሪያው መቶ ዘመን የስብከቱ ሥራ ምን ያህል ስፋት ነበረው?

7 በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት የአምላክ አገልጋዮች እምነትና መንፈስ ቅዱስን ተሞልተው የተሰጣቸውን ተልዕኮ ለመፈጸም ወደ ፊት ገፍተዋል። ይሖዋም ከእነርሱ ጋር ስለነበር ከጠበቁት እጅግ የሚልቅ ስኬት አግኝተዋል። ኢየሱስ ከሞተ ከ27 ዓመት በኋላ ጳውሎስ ለቆላስይስ ሰዎች ሲጽፍላቸው ምሥራቹ “ከሰማይ በታች ባለው ፍጥረት ሁሉ ዘንድ፤ ተሰብኳል” ለማለት ችሎ ነበር። (ቆላስይስ 1:​23) በተመሳሳይም በ20ኛው መቶ ዘመን ማብቂያ ላይ ይህ ምሥራች በ233 አገሮች ውስጥ በመሰበክ ላይ ይገኛል።

8. ብዙዎች ምሥራቹን የተቀበሉት ምን ዓይነት ሁኔታዎች ውስጥ እያሉ ነው? ምሳሌ ስጥ።

8 በቅርብ አሥርተ ዓመታት በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ምሥራቹን የተቀበሉ ሲሆን ብዙዎቹ ይህንን ያደረጉት እንደ ጦርነት፣ እገዳና ጠንካራ ስደት ያሉት አስቸጋሪ ሁኔታዎች እያሉ ነው። በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበረው ሁኔታም ተመሳሳይ ነው። በአንድ ወቅት ጳውሎስና ሲላስ በበትር በጭካኔ ተደብድበው እሥር ቤት ተጥለው ነበር። በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ደቀ መዛሙርት ማፍራት ይቻላል ብሎ የሚያስብ ማን ይኖራል? ይሁንና ይሖዋ ይህን ሁኔታ ደቀ መዛሙርት ለማፍራት ተጠቅሞበታል። ጳውሎስና ሲላስ ከእሥር ተፈቱ፤ የወኅኒ ቤቱም ጠባቂ ከነቤተሰቡ አመነ። (ሥራ 16:​19-33) እንዲህ ያለው ተሞክሮ እንደሚያሳየው ተቃዋሚዎች የምሥራቹን ስብከት ሊያፍኑት አይችሉም። (ኢሳይያስ 54:​17) ሆኖም የክርስትና ታሪክ በመከራና ስደት ብቻ የተሞላ ነበር ማለት አይደለም። እስቲ አሁን ደግሞ በመጀመሪያውም ሆነ በ20ኛው መቶ ዘመን የምሥራቹ ስብከት በተሳካ መንገድ እንዲከናወን መንገድ በመጥረግ ረገድ ጠቃሚ ድርሻ ስለነበራቸው ክንውኖች እንመልከት።

ሃይማኖታዊ ሁኔታ

9, 10. ይሖዋ በመጀመሪያው መቶ ዘመንም ሆነ በ20ኛው መቶ ዘመን ሰዎች የምሥራቹን ስብከት በጉጉት እንዲጠብቁ ያደረገው እንዴት ነው?

9 ምድር አቀፉ የስብከት ዘመቻ የተካሄደበትን ጊዜም ልብ በል። በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበረውን መቼት የተመለከትን እንደሆነ በዳንኤል 9:​24-27 ላይ ተጠቅሶ የሚገኘው ስለ 70 የዓመታት ሳምንታት የሚገልጸው ትንቢት መሲሑ የሚገለጥበት ዓመት 29 እዘአ እንደሚሆን ይጠቁማል። በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት አይሁዶች ነገሮቹ የሚከናወኑበትን ትክክለኛ ጊዜ ባይገነዘቡም መሲሑን ይጠብቁ ነበር። (ሉቃስ 3:​15) የፈረንሳዩ ማኑዌል ቢብሊክ እንዲህ ይላል:- “ሕዝቡ ዳንኤል የተናገረላቸው ሰባ የዓመታት ሳምንታት የሚያበቁበት ጊዜ ተቃርቦ እንደነበር ተገንዝቧል። የአምላክ መንግሥት ቀርባለች የሚለው የዮሐንስ አዋጅ እንግዳ የሆነበት ሰው አልነበረም።”

10 በዘመናችን ስለነበረውስ መቼት ምን ማለት ይቻላል? በዚህ ጊዜ የነበረው ታላቅ ክንውን ደግሞ ኢየሱስ በሰማይ ሥልጣን መያዙ ሲሆን ይህም በመንግሥት ሥልጣኑ የሚገኝበት ጊዜ መጀመሩን የሚያመለክት ነበር። የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት እንደሚያሳየው ይህ የሆነው በ1914 ነበር። (ዳንኤል 4:​13-17) በዛሬ ጊዜ ያሉ አንዳንድ ሃይማኖታዊ ሰዎች ይህን ክንውን ለማየት መናፈቃቸው በጉጉት እንዲጠባበቁ አድርጓቸዋል። የክርስቶስ መገኘት አዋጅ ነጋሪ የሆነው የጽዮን መጠበቂያ ግንብ በሚል ስም በ1879 ይህን መጽሔት ማዘጋጀት የጀመሩት ቅን ልብ ያላቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎችም ተመሳሳይ ጉጉት አንጸባርቀዋል። በዚህ መንገድ እንዲህ ያለው ሃይማኖታዊ ጉጉት በመጀመሪያው መቶ ዘመንም ሆነ በዘመናችን ለምሥራቹ ስብከት ሁኔታውን አመቻችቷል።a

11. ለምሥራቹ ስብከት የሚጠቅሙ ምን ሃይማኖታዊ መሠረቶች ተጥለው ነበር?

11 በሁለቱም ዘመን የነበሩት ክርስቲያኖች ላከናወኑት ሥራ አጋዥ ሆኖ የተገኘው ሌላው ነገር ደግሞ ብዙ ሰዎች ከቅዱሳን ጽሑፎች ጋር ትውውቅ የነበራቸው መሆኑ ነው። በመጀመሪያው መቶ ዘመን የአይሁድ መንደሮች በአካባቢው ባሉት የአሕዛብ ብሔራት ዘንድ ተሰበጣጥረው ይገኙ ነበር። እነዚህ መንደሮች ደግሞ ሰዎች ቅዱሳን ጽሑፎች ሲነበቡና ሲብራሩ ለመስማት የሚሰባሰቡባቸው ምኩራቦች ነበሯቸው። በዚህ መንገድ የጥንቶቹ ክርስቲያኖች ሰዎች ቀደም ሲል የነበራቸውን ሃይማኖታዊ እውቀት መሠረት በማድረግ መገንባት ችለው ነበር። (ሥራ 8:​28-36፤ 17:​1, 2) በዚህ በእኛ ዘመን መጀመሪያ ላይም የይሖዋ ሕዝቦች በብዙ አገሮች የገጠማቸው ሁኔታ ከዚህ ጋር የሚመሳሰል ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ በሕዝበ ክርስትና ግዛቶች በተለይ ደግሞ በፕሮቴስታንት አገሮች ውስጥ በሰፊው ተሠራጭቶ ነበር። በብዙ አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ ይነበብ የነበረ ሲሆን በሚልዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችም የየራሳቸው ቅጂ ነበራቸው። መጽሐፍ ቅዱስ በሰዎች እጅ ገብቶ የነበረ ቢሆንም ይህን በእጃቸው ያለውን መጽሐፍ እንዲያስተውሉት የሚረዳቸው ያስፈልግ ነበር።

የሕግ ከለላ

12. የሮማ ሕግ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ከለላ ሆኖ ያገለገለው እንዴት ነው?

12 መንግሥታት የሚያወጡት ሕግ ለክርስቲያናዊው ስብከት ከለላ የሆነባቸው ጊዜያት በርካታ ናቸው። የሮማ ንጉሠ ነገሥታዊ ግዛት በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበረውን ዓለም በበላይነት ተቆጣጥሮት የነበረ ሲሆን በጽሑፍ የሰፈሩት ሕግጋቱም በሰዎች ዕለታዊ ሕይወት ላይ በቀላሉ የማይገመት ተጽዕኖ አሳድረዋል። እነዚህ ሕጎች የደህንነት ከለላ ያስገኙ ሲሆን የጥንቶቹ ክርስቲያኖችም ተጠቃሚ ሆነውባቸዋል። ለምሳሌ ያህል ጳውሎስ ለሮማ የሕግ አካል አቤት ማለቱ ከእስር ነፃ እንዲወጣና ከግርፋት እንዲድን ረድቶታል። (ሥራ 16:​37-39፤ 22:​25, 29) የሮማ ሕግ አስከባሪ በጉዳዩ ጣልቃ መግባቱ በኤፌሶን የተነሳውን የሕዝብ ዓመፅ ለማብረድ አስችሏል። (ሥራ 19:​35-41) ጳውሎስ የሮማ ዜጋ በመሆኑ ምክንያት በአንድ ወቅት በኢየሩሳሌም ከተነሣው ዓመፅ ማምለጥ ችሏል። (ሥራ 23:​27) ከጊዜ በኋላም የሮማ ሕግ በቄሳር ፊት ስለ እምነቱ ሕጋዊ መከላከያ እንዲያቀርብ ፈቅዶለታል። (ሥራ 25:​11) ምንም እንኳን ብዙዎቹ ቄሣሮች አምባገነን ገዥዎች የነበሩ ቢሆንም በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት ሕግጋት ባብዛኛው ‘ምሥራቹን በሕግ ለመከላከል’ የሚያስችሉ ነበሩ።​—⁠ፊልጵስዩስ 1:​7 NW

13. በጊዜያችን የስብከቱ ሥራ ከሕግ ከለላ ብዙ የተጠቀመው እንዴት ነው?

13 ዛሬም በብዙ አገሮች ያለው ሁኔታ ተመሳሳይ ነው። ‘ሕግን ተጠቅመው ችግር ለመፍጠር’ የሚሞክሩ ሰዎች ቢኖሩም በብዙ አገሮች የሚሠራባቸው በጽሑፍ የሰፈሩት ሕጎች የሃይማኖት ነፃነት መሠረታዊ መብት መሆኑን ይደነግጋሉ። (መዝሙር 94:​20) የይሖዋ ምሥክሮች በማኅበረሰቡ ላይ አንዳችም ስጋት የሚፈጥሩ ሰዎች አለመሆናቸውን በመገንዘብም ብዙ መንግሥታት ሕጋዊ እውቅና ሰጥተውናል። አብዛኛው የምሥክሮቹ የኅትመት ሥራ ሲከናወንባት በቆየችው በዩናይትድ ስቴትስ የመጠበቂያ ግንብ መጽሔት ያለማቋረጥ ለ120 ዓመታት እንዲታተምና በዓለም ዙሪያ ለንባብ እንዲበቃ የአገሪቱ ሕግ የተመቻቸ ሁኔታ ፈጥሯል።

ሰላምና መቻቻል የሰፈነባቸው ወቅቶች

14, 15. አንጻራዊ የሆነው ማኅበራዊ መረጋጋት በመጀመሪያው መቶ ዘመን ለተከናወነው የስብከት ሥራ ጠቃሚ የነበረው እንዴት ነው?

14 አንጻራዊ ሰላም የሰፈነባቸው ወቅቶችም ለስብከቱ ሥራ ጠቃሚ ድርሻ አበርክተዋል። ኢየሱስ በእነዚህ ሁለት ዘመናት ውስጥ ስለሚሆነው ነገር በትክክል ሲገልጽ ‘መንግሥት በመንግሥት ላይ እንደሚነሣ’ ቢተነብይም በመሀሉ የመንግሥቱን ስብከት በሰፊው ለማዳረስ የሚያስችሉ የተረጋጉ ወቅቶች ነበሩ። (ማቴዎስ 24:​7) የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች በፓክስ ሮማና ወይም በሮማ የሰላም ዘመን ኖረዋል። አንድ ታሪክ ጸሐፊ እንዲህ ብለዋል:- “ሮም በሜድትራንያኑ ዓለም የነበሩትን ሕዝቦች ሙሉ በሙሉ አስገዝታቸው ስለነበር የማያባራ ጦርነት ይካሄድበት የነበረው ዘመን መቋጫ እንዲያገኝ አድርጋለች።” ይህ መረጋጋት የሰፈነበት ሁኔታ የጥንቶቹ ክርስቲያኖች አንጻራዊ የሆነ ደህንነት ተሰምቷቸው በመላው የሮማውያኑ ዓለም እንዲዘዋወሩ አስችሏቸዋል።

15 የሮማ ንጉሠ ነገሥታዊ ግዛት ሕዝቡን በጠንካራ ክንዱ ሥር አንድ ለማድረግ ታግሏል። ይህ ፖሊሲ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላው መጓዝ፣ መቻቻል እንዲሁም የንድፈ ሐሳብ ልውውጥ ማድረግ እንዲለመድ ከማበረታታትም አልፎ የዓለም አቀፍ ወንድማማችነት ጽንሰ ሐሳብ እንዲሰፍን አድርጓል። ኦን ዘ ሮድ ቱ ሲቪላይዜሽን የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ይላል:- “የ[ሮማ] ንጉሠ ነገሥታዊ ግዛት መስኩን [ለክርስቲያናዊ ስብከት] አመቻችቶ ነበር። ብሔራዊ ወሰኖች ፈርሰው ነበር። የሮማ ዜጋ የሆነ ሰው የዓለምን ዜግነት ያገኘ ያህል ነበር። . . . ከዚህም በላይ አንድ ዜግነት የሚል ንድፈ ሐሳብ ባዳበረ መንግሥት ሥር ሆኖ የሰው ልጅ ወንድማማችነትን የሚያስተምር ሃይማኖትን መቀበል አስቸጋሪ አይሆንም።”​—⁠ከሥራ 10:​34, 35፤ 1 ጴጥሮስ 2:​17 ጋር አወዳድር።

16, 17. በጊዜያችን ለሰላም ጥረት እንዲደረግ የሚገፋፋ ኃይል የሆነው ነገር ምንድን ነው? ብዙ ሰዎችስ ምን መደምደሚያ ላይ ደርሰዋል?

16 ስለ ዘመናችንስ ምን ማለት ይቻላል? በዚህ በ20ኛው መቶ ዘመን ከዚህ በፊት በታሪክ ታይተው የማይታወቁ አውዳሚ ጦርነቶች የተካሄዱ ሲሆን አሁንም አካባቢያዊ ግጭቶች አንዳንድ አገሮችን ማመሳቸውን ቀጥለዋል። (ራእይ 6:​4) ይሁንና አንጻራዊ ሰላም የተገኘባቸውም ወቅቶች ነበሩ። የዓለማችን ታላላቅ መንግሥታት ለመጨረሻ ጊዜ እርስ በርሳቸው መጠነ ሰፊ ጦርነት ካካሄዱ ከ50 የሚበልጡ ዓመታት አልፈዋል። ይህ ሁኔታ በእነዚያ አገሮች ለሚካሄደው የምሥራቹ ስብከት ከፍተኛ እገዛ አድርጓል።

17 በ20ኛው መቶ ዘመን የተካሄዱት ጦርነቶች የፈጠሩት ታላቅ ድንጋጤ ብዙ ሰዎች ዓለም አቀፍ መስተዳድር አስፈላጊ መሆኑን እንዲገነዘቡ አድርጓቸዋል። ለመንግሥታት ቃል ኪዳን ማኅበርም ሆነ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መመሥረት ምክንያት የሆነው ነገር የዓለም ጦርነት ይነሣል የሚለው ፍርሃት ነው። (ራእይ 13:​14) በይፋ የተደነገገው የሁለቱም ድርጅቶች መሠረታዊ መርኅ ዓለም አቀፍ ትብብርና ሰላም ማስፈን ነው። ብዙውን ጊዜ የዚህን አስፈላጊነት የተገነዘቡ ሰዎች እውነተኛና ዘላቂ ሰላም ስለሚያሰፍነው ዓለም አቀፍ መስተዳድር ማለትም ስለ አምላክ መንግሥት ሲነገራቸው አዎንታዊ ምላሽ ይሰጣሉ።

18. ለስብከቱ ሥራ አመቺ ሁኔታ የፈጠረው ሃይማኖትን በሚመለከት የሰፈነው የትኛው አመለካከት ነው?

18 ክርስቲያኖች አስከፊ ስደት ለመቀበል የተገደዱባቸው ጊዜያት ቢኖሩም በመጀመሪያው መቶ ዘመንም ሆነ በ20ኛው መቶ ዘመን የነበሩት ክርስቲያኖች ሃይማኖታዊ መቻቻል የሰፈነባቸውንም ጊዜያት አሳልፈዋል። (ዮሐንስ 15:​20፤ ሥራ 9:​31) ሮማውያን ድል አድርገው የያዟቸውን ሕዝቦች ወንድና ሴት አማልክት እንደ ራሳቸው አማልክት ተቀብለው ያመልኩ ነበር። ፕሮፌሰር ሮድኔይ ስታርክ እንደሚከተለው ሲሉ ጽፈዋል:- “በብዙ ጎኑ ሲታይ ሮም እስከ አሜሪካው አብዮት ድረስ በሌላ ቦታ ያልታየ ከፍተኛ ደረጃ ያለው ሃይማኖታዊ ነፃነት እንዲሰፍን አድርጋ ነበር።” በጊዜያችን በብዙ አገሮች የሚገኙ ሰዎች ሌሎች አመለካከቶችን ለማስተናገድ ፈቃደኞች መሆናቸው የይሖዋ ምሥክሮች ለሚያዳርሱትም የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት ጆሮአቸውን እንዲሰጡ በር ከፍቷል።

ቴክኖሎጂ የተጫወተው ሚና

19. የጥንቶቹ ክርስቲያኖች ኮዴክስን የተጠቀሙበት እንዴት ነበር?

19 በመጨረሻም ይሖዋ፣ ሕዝቦቹ ከቴክኖሎጂ መሻሻሎች ጥቅም እንዲያገኙ እንዴት እንዳስቻላቸው ተመልከት። የጥንቶቹ ክርስቲያኖች የኖሩት ፈጣን የቴክኖሎጂ መሻሻል በነበረበት ዘመን ባይሆንም ከተጠቀሙባቸው የተሻሻሉ ነገሮች መካከል ኮዴክስ ወይም ብትን ገጾች ያሉት መጽሐፍ አንዱ ነበር። ለመያዝ የማይመቹት ጥቅልሎች በኮዴክስ ተተክተው ነበር። የኮዴክስ ልደት (እንግሊዝኛ) የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ብሏል:- “በዓለማዊ ጽሑፎች ረገድ ጥቅልሎች በኮዴክስ የተተኩበት ሂደት ዝግተኛና አዝጋሚ ሲሆን በክርስትና ውስጥ ግን ኮዴክስ ሥራ ላይ የዋለው በፍጥነትና ምድር አቀፍ ስፋት ባለው መጠን ይመስላል።” ይኸው የማመሳከሪያ ጽሑፍ እንዲህ ይላል:- “ኮዴክስ ከክርስቶስ ልደት በኋላ በሁለተኛው መቶ ዘመን በክርስትና ውስጥ እጅግ በሰፊው ጥቅም ላይ ውሎ ስለነበር የተጀመረው በ100 ከክርስቶስ ልደት በኋላ መሆን አለበት።” ከጥቅልሉ ይልቅ ለአጠቃቀም አመቺ የነበረው ኮዴክሱ ነበር። ጥቅሶችንም በቀላሉ ፈልጎ ማግኘት ይቻላል። ይህም እንደ ጳውሎስ ያሉት የጥንት ክርስቲያኖች ቅዱሳን ጽሑፎችን ማብራራት ብቻ ሳይሆን ስለሚያስተምሩት ነገር መጽሐፉን ገልጠው ‘ማስረጃ እንዲያቀርቡ’ እንደረዳቸው ምንም ጥርጥር የለውም።​—⁠ሥራ 17:​2, 3

20. የአምላክ ሕዝቦች ምድር አቀፉን የስብከት እንቅስቃሴ ለማገዝ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን ጥቅም ላይ ያዋሉት እንዴት ነው? ለምንስ?

20 በዚህ በእኛ መቶ ዘመን የታየው የቴክኖሎጂ መሻሻል ደግሞ እጅግ የላቀ ነው። ከፍተኛ ፍጥነት ያላቸው የማተሚያ መሣሪያዎች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች በበርካታ ቋንቋዎች በተመሳሳይ ጊዜ ታትመው እንዲወጡ አስችለዋል። ዘመናዊው ቴክኖሎጂ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ሥራ እንዲፋጠን አድርጓል። ከባድ መኪናዎች፣ ባቡሮች፣ መርከቦች እና አውሮፕላኖች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን በፍጥነት በምድር ዙሪያ ለማጓጓዝ አስችለዋል። የስልክና የፋክስ መሣሪያዎች ቅጽበታዊ የሆነ ግንኙነት ለማድረግ አስችለዋል። ይሖዋም በመንፈሱ አማካኝነት አገልጋዮቹ እንዲህ ያሉትን የቴክኖሎጂ ውጤቶች ምሥራቹን በዓለም ዙሪያ ለማስፋፋት በሚያስችል መንገድ እንዲጠቀሙባቸው አንቀሳቅሷቸዋል። እንዲህ ያሉትን የተሻሻሉ ውጤቶች የሚጠቀሙት በዓለም ውስጥ ያለውን አዲስ ነገር ሁሉ ለማወቅና ለመጠቀም ስለሚፈልጉ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ተቀዳሚው ዓላማቸው የስብከት ተልዕኳቸውን ይበልጥ ውጤታማ በሆነ መንገድ ለመፈጸም የሚረዳቸው ነገር ማግኘት ነው።

21. ስለ ምን ነገር እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን?

21 ኢየሱስ “ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል” ሲል ተንብዮአል። (ማቴዎስ 24:​14) የጥንቶቹ ክርስቲያኖች ይህ ትንቢት ፍጻሜውን ሲያገኝ እንደተመለከቱ ሁሉ እኛም ዛሬ ትንቢቱ በሰፊው ፍጻሜውን ሲያገኝ እያየን ነው። ሥራው ግዙፍና አስቸጋሪ ቢሆንም አመቺ በሆነበትም ወቅት ሆነ በአስቸጋሪ ጊዜ፣ ተለዋዋጭ ሕጎችና አመለካከቶች ባሉበት፣ ጦርነትና ሰላም በሚፈራረቁበት እንዲሁም የተለያዩ የቴክኖሎጂ መሻሻሎች በታዩበት ዘመን ሁሉ ምሥራቹ ሲሰበክ ቆይቷል አሁንም በመሰበክ ላይ ነው። ታዲያ ይህ የይሖዋ ጥበብና ድንቅ የሆነ አርቆ አሳቢነት በአድናቆት እንድትዋጥ አያደርግህምን? የስብከቱ ሥራ ልክ ይሖዋ በያዘለት የጊዜ ሰሌዳ መሠረት እንደሚጠናቀቅና ፍቅራዊ ዓላማው ተከናውኖ ለጻድቃን በረከት እንደሚያመጣ ፍጹም እርግጠኞች መሆን እንችላለን። ጻድቃን ምድርን ወርሰው ለዘላለም ይኖራሉ። (መዝሙር 37:​29፤ ዕንባቆም 2:​3) እኛም ሕይወታችንን ከአምላክ ዓላማ ጋር ካስማማን ከእነዚህ ሰዎች መካከል እንሆናለን።​—⁠1 ጢሞቴዎስ 4:​16

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ስለ እነዚህ ሁለት መሲሐዊ ትንቢቶች ዝርዝር ማብራሪያ ለማግኘት ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የተዘጋጀውን ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ እውቀት የተባለውን መጽሐፍ ገጽ 36, 97 እንዲሁም 98-107 ተመልከት።

ለክለሳ የቀረቡ ነጥቦች

◻ የምሥራቹ ስብከት ተፈታታኝ ሥራ ሆኖ የቆየው ለምንድን ነው?

◻ የመንግሥታት መዋቅርና አንጻራዊ የሆነው ማኅበራዊ መረጋጋት ክርስቲያኖች ለሚያከናውኑት ሥራ ጠቃሚ ሆኖ የተገኘው በምን መንገዶች ነው?

◻ ይሖዋ የስብከቱን ሥራ የሚባርክ መሆኑ ወደፊት ለሚፈጸም ምን ነገር ማረጋገጫ ይሆነናል?

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ