ጢሞቴዎስ ‘በእምነት እውነተኛ ልጅ የሆነ’
ክርስቲያኑ ሐዋርያው ጳውሎስ የጉዞ ጓደኛ አድርጎ ሲመርጠው ጢሞቴዎስ ገና ወጣት ነበር። ይህም ለ15 ዓመታት የዘለቀ ወዳጅነት እንዲመሠርቱ አድርጓል። በሁለቱ ሰዎች መካከል የነበረው ወዳጅነት ጠንካራ ስለነበረ ጳውሎስ ጢሞቴዎስን ‘የምወደው፣ የታመነውና በጌታ ልጄ የሆነው’ እና ‘በእምነት እውነተኛ ልጄ የሆነ’ በማለት ሊጠራው ችሏል።—1 ቆሮንቶስ 4:17፤ 1 ጢሞቴዎስ 1:2
ጳውሎስ ይህን ያክል እንዲወድደው ያደረገው ጢሞቴዎስ ምን ባህርይ ቢኖረው ነው? ጢሞቴዎስ ጠቃሚ ባልደረባ ሊሆን የበቃው እንዴት ነው? በመንፈስ አነሣሽነት ከተጻፈው ስለ ጢሞቴዎስ እንቅስቃሴዎች ከሚገልጸው ዘገባስ ምን ትምህርቶች ልናገኝ እንችላለን?
በጳውሎስ የተመረጠ
ጳውሎስ ወጣቱን ደቀ መዝሙር ጢሞቴዎስን ያገኘው ሐዋርያው በ50 እዘአ ገደማ ሁለተኛ ሚስዮናዊ ጉዞውን በሚያደርግበት ጊዜ ልስጥራንን (በዘመናዊቷ ቱርክ የምትገኝ) በጎበኘበት ወቅት ነበር። ምናልባት በአሥራዎቹ የዕድሜ ክልል መገባደጃ ወይም በ20ዎቹ መጀመሪያ ላይ የሚገኘው ጢሞቴዎስ በልስጥራንና በኢቆንዮን በሚገኙ ክርስቲያኖች ዘንድ በመልካም የተመሰከረለት ሰው ነበር። (ሥራ 16:1-3) “አምላክን የሚያከብር ሰው” ከሚለው የስሙ ትርጉም ጋር በሚስማማ መንገድ ኖሯል። ጢሞቴዎስ ከልጅነቱ አንስቶ ቅዱሳን ጽሑፎችን ከአያቱ ከሎይድና ከእናቱ ከኤውንቄ ተምሯል። (2 ጢሞቴዎስ 1:5፤ 3:14, 15) አያቱና እናቱ ክርስትናን የተቀበሉት ጳውሎስ ከሁለት ዓመታት ገደማ በፊት ለመጀመሪያ ጊዜ የሚኖሩባትን ከተማ በጎበኘበት ወቅት ሳይሆን አይቀርም። አሁን በመንፈስ ቅዱስ አሠራር አማካኝነት አንድ ትንቢታዊ መግለጫ የጢሞቴዎስ የወደፊት ዕጣ ምን እንደሚሆን አመልክቷል። (1 ጢሞቴዎስ 1:18) ከዚህ መመሪያ ጋር በሚስማማ መንገድ ጳውሎስና በጉባኤው ውስጥ የሚገኙ ሽማግሌዎች በዚህ ወጣት ላይ እጃቸውን በመጫን ለአንድ የተለየ አገልግሎት ያጩት ሲሆን ሐዋርያው ደግሞ ሚስዮናዊ ጓደኛ አድርጎ መረጠው።—1 ጢሞቴዎስ 4:14፤ 2 ጢሞቴዎስ 1:6
አባቱ የማያምን ግሪካዊ ሰው ስለነበር ጢሞቴዎስ አልተገረዘም። እርግጥ መገረዝ ከአንድ ክርስቲያን የሚፈለግ ብቃት ነው ማለት አልነበረም። ይሁን እንጂ የሚጎበኟቸውን አይሁዶች ላለማሰናከል ጢሞቴዎስ ሥቃይ ቢያስከትልበትም ለመገረዝ ፈቃደኛ ሆኗል።—ሥራ 16:3
ጢሞቴዎስ ቀደም ሲልም እንደ አይሁዳዊ ይቆጠር ነበርን? በረቢ ባለ ሥልጣናት አባባል መሠረት “ከባዕዳን ሕዝቦች ጋር ከሚፈጸም ጋብቻ የሚወለዱ ልጆች ዜግነታቸው የሚወሰነው በአባታቸው ሳይሆን በእናታቸው ነው” በማለት አንዳንድ ምሁራን ይከራከራሉ። ይህም ደግሞ “አንዲት አይሁዳዊት ሴት አይሁዳውያን ልጆችን ትወልዳለች” ማለት ነው። ይሁንና ደራሲው ሼ ኮኸን ይህን የመሰለ “ሰዎችን የሚመለከት የረቢ ሕግ በመጀመሪያው መቶ ዘመን በሥራ ላይ መዋሉ” እና በትንሿ እስያ ውስጥ የሚኖሩ አይሁዳውያን ይመሩበት የነበረ መሆኑ አጠያያቂ ነው ይላሉ። ታሪካዊ ማረጋገጫዎችን ከመረመሩ በኋላ አንድ ከአሕዛብ መካከል የሆነ ወንድ እስራኤላዊት ሴት ካገባ “ከዚህ ጋብቻ የሚወለዱ ልጆች እስራኤላውያን ተደርገው የሚቆጠሩት ቤተሰቡ በእስራኤላውያን መካከል የሚኖር ከሆነ ብቻ ነው። በእናቲቱ አገር ውስጥ የሚኖሩ ከሆነ የእናትየውን የትውልድ መሥመር ይይዛሉ። እስራኤላዊቷ ሴት ከአሕዛብ ባሏ ጋር አብራ ለመኖር ወደ ሌላ አገር ከተዛወረች ልጆቿ አሕዛብ ተደርገው ይቆጠራሉ።” በዚያም ሆነ በዚህ ጢሞቴዎስ የተለያየ ዘር ያላቸው ወላጆች ያሉት መሆኑ ለስብከቱ ሥራ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል። ለአይሁዳውያንም ሆነ ለአሕዛብ ለመናገር የማይቸገር ሲሆን በሁለቱ መካከል ያለውን ልዩነትም ለማስወገድ ሳያስችለው አልቀረም።
ጳውሎስ ልስጥራንን መጎብኘቱ የጢሞቴዎስ ሕይወት አዲስ አቅጣጫ እንዲይዝ አድርጓል። ይህ ወጣት የመንፈስ ቅዱስን አመራር ለመከተል የነበረው ፈቃደኝነትና ከክርስቲያን ሽማግሌዎች ጋር በትሕትና መተባበሩ ታላላቅ በረከቶችንና የአገልግሎት መብቶችን አስገኝቶለታል። ጢሞቴዎስ በወቅቱ ይህን ይገንዘበው አይገንዘበው በጳውሎስ አመራር ሥር በመሆን ከጊዜ በኋላ የግዛቱ ዋና ከተማ እስከሆነው እስከ ሮም ድረስ የሚወስደውን አስፈላጊ የሆነ ቲኦክራሲያዊ ሥራ ሊያከናውን ነበር።
ጢሞቴዎስ የመንግሥቱን ፍላጎቶች አስፋፍቷል
ጢሞቴዎስ የመንግሥቱን ፍላጎቶች ለማስፋፋት ወደ ብዙ ቦታዎች የተጓዘ ቢሆንም ስለ እንቅስቃሴዎቹ የሚናገር የተሟላ ዘገባ የለንም። ጢሞቴዎስ ከጳውሎስና ሲላስ ጋር በ50 እዘአ ያደረገው የመጀመሪያው ጉዞ ከትንሿ እስያ አንስቶ እስከ አውሮፓ ድረስ ወስዶታል። በዚያም በፊልጵስዩስ፣ በተሰሎንቄና በቤሪያ በተካሄዱ የስብከት ዘመቻዎች ተካፍሏል። በተቃውሞ ምክንያት ጳውሎስ ወደ አቴና ለመሄድ ሲገደድ ጢሞቴዎስና ሲላስ በቤሪያ የሚገኘውን የደቀ መዛሙርት ቡድን ለመርዳት በዚያው ቆዩ። (ሥራ 16:6-17:14) ከጊዜ በኋላ ጳውሎስ በተሰሎንቄ የተቋቋመውን አዲስ ጉባኤ እንዲያጠነክር ጢሞቴዎስን ወደዚያ ልኮት ነበር። ጢሞቴዎስ ጳውሎስን በቆሮንቶስ ሲያገኘው ስለ እነሱ ጥሩ ዜና አምጥቶለታል።—ሥራ 18:5፤ 1 ተሰሎንቄ 3:1-7
ጢዎቴዎስ ከቆሮንቶስ ሰዎች ጋር ለምን ያህል ጊዜ እንደቆየ ቅዱሳን ጽሑፎች የሚናገሩት ነገር የለም። (2 ቆሮንቶስ 1:19) ይሁን እንጂ በ55 እዘአ ገደማ ሳይሆን አይቀርም ጳውሎስ የቆሮንቶስ ሰዎች ስላሉበት አሳሳቢ ሁኔታ በደረሰው ዜና ምክንያት ጢሞቴዎስን መልሶ ሊልከው እያሰበ ነበር። (1 ቆሮንቶስ 4:17፤ 16:10) ከጊዜ በኋላ ጢሞቴዎስ ከኤርስጦን ጋር ከኤፌሶን ወደ መቄዶንያ ተልኳል። ጳውሎስ በቆሮንቶስ ሆኖ ለሮሜ ሰዎች በጻፈ ጊዜ ጢሞቴዎስ እንደገና ከእርሱ ጋር ነበረ።—ሥራ 19:22፤ ሮሜ 16:21
ጳውሎስ ቆሮንቶስን ለቅቆ ወደ ኢየሩሳሌም ለመሄድ ሲነሳ ጢሞቴዎስና ሌሎችም አብረውት የተጓዙ ሲሆን ሐዋርያውን ቢያንስ እስከ ጢሮአዳ ድረስ ሸኝተውታል። ጢሞቴዎስ ጉዞውን በመቀጠል ወደ ኢየሩሳሌም ይሂድ አይሂድ ምንም የሚታወቅ ነገር የለም። ሆኖም ጳውሎስ ከ60-61 እዘአ ገደማ በሮም በእስር ላይ በነበረበት ጊዜ በጻፋቸው ሦስት ደብዳቤዎች መግቢያ ላይ ስሙ ተጠቅሶ ይገኛል።a (ሥራ 20:4፤ ፊልጵስዩስ 1:1፤ ቆላስይስ 1:1፤ ፊልሞና 1) ጳውሎስ ጢሞቴዎስን ከሮም ወደ ፊልጵስዩስ ሊልከው እያሰበ ነበር። (ፊልጵስዩስ 2:19) ጳውሎስ ከእስር ከተለቀቀ በኋላ ግን ጢሞቴዎስ በሐዋርያው ትእዛዝ መሠረት በኤፌሶን ቆየ።—1 ጢሞቴዎስ 1:3
በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበረው ጉዞ አድካሚና አስቸጋሪ ስለነበረ ጢሞቴዎስ ጉባኤዎችን ለመጎብኘት ሲል በርካታ ጉዞዎችን ለማድረግ ፈቃደኛ መሆኑ በእርግጥም የሚያስመሰግነው ነበር። (በነሐሴ 15, 1996 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 29 ላይ የሚገኘውን ሣጥን ተመልከት።) ካደረጋቸው ጉዞዎች መካከል አንደኛውን መርምርና ስለ ጢሞቴዎስ ምን እንደሚነግረን ተመልከት።
ስለ ጢሞቴዎስ ባሕርይ እንድናውቅ የሚረዳ አጋጣሚ
በእስር ላይ የነበረው ሐዋርያ በመከራ ሥር ለነበሩት የፊልጵስዩስ ክርስቲያኖች የሚከተለውን ሲጽፍ ጢሞቴዎስ ከእርሱ ጋር ነበረ:- “እኔ ደግሞ ደስ እንዲለኝ ፈጥኜ ጢሞቴዎስን ልልክላችሁ በጌታ በኢየሱስ ተስፋ አደርጋለሁ። እንደ እርሱ ያለ፣ ስለ ኑሮአችሁ በቅንነት የሚጨነቅ፣ ማንም የለኝምና፤ ሁሉ የራሳቸውን ይፈልጋሉና፣ የክርስቶስ ኢየሱስን አይደለም። ነገር ግን ልጅ ለአባቱ እንደሚያገለግል ከእኔ ጋር ሆኖ ለወንጌል እንደ አገለገለ መፈተኑን ታውቃላችሁ።”—ፊልጵስዩስ 1:1, 13, 28-30፤ 2:19-22
እነዚህ ቃላት ጢሞቴዎስ ለመሰል አማኞች የነበረውን አሳቢነት ጎላ አድርገው ያሳያሉ። የሄደው በጀልባ ካልሆነ እንዲህ ያለው ጉዞ ከሮም እስከ ፊልጵስዩስ ድረስ ለ40 ቀናት ያህል በእግር መሄድንና በአድሪአቲክ ባሕር ላይ ጥቂት መጓዝን ከዚያም ለሌላ 40 ቀናት የመልስ ጉዞ ማድረግን የሚጠይቅ ነበር። ጢሞቴዎስ ወንድሞቹንና እህቶቹን ለማገልገል የሚችለውን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ ነበር።
ጢሞቴዎስ ረዥም ርቀት ቢጓዝም አንዳንድ ጊዜ የጤና መቃወስ ያጋጥመው ነበር። ‘በተደጋጋሚ የሚያሰቃየው’ አንድ ዓይነት የሆድ ሕመም እንደነበረበት የታወቀ ነው። (1 ጢሞቴዎስ 5:23 NW) ይሁንና ለምሥራቹ ሲል ብዙ ደክሟል። ጳውሎስ ከእሱ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት ቢኖረው ምንም አያስደንቅም!
በሐዋርያው አስተማሪነትና አብረው ባሳለፏቸው ተሞክሮዎች ምክንያት ጢሞቴዎስ የጳውሎስን የመሰለ ባህርይ ይዟል። በመሆኑም ጳውሎስ እንዲህ ሊለው ችሏል:- “አንተ ግን ትምህርቴንና አካሄዴን አሳቤንም እምነቴንም ትዕግሥቴንም ፍቅሬንም መጽናቴንም ስደቴንም መከራዬንም ተከተልህ፤ በአንጾኪያና በኢቆንዮን በልስጥራንም የሆነብኝን የታገሥሁትንም ስደት ታውቃለህ።” ጢሞቴዎስ ከጳውሎስ ጋር እንባውን ያፈሰሰባቸው ጊዜያት ነበሩ። ጳውሎስ በጸሎቱ ያስበው የነበረው ጢሞቴዎስ ከጳውሎስ ጎን በመቆም የመንግሥቱን ፍላጎቶች ለማስፋፋት ብዙ ደክሟል።—2 ጢሞቴዎስ 1:3, 4፤ 3:10, 11
ጳውሎስ ‘ማንም ሰው ታናሽነትህን አይናቀው’ በማለት ጢሞቴዎስን አበረታቶታል። ይህ ምናልባት ጢሞቴዎስ ዓይነ አፋርና በሥልጣኑ ለመጠቀም ያመነታ እንደነበር የሚጠቁም ሊሆን ይችላል። (1 ጢሞቴዎስ 4:12፤ 1 ቆሮንቶስ 16:10, 11) ይሁን እንጂ ራሱን ችሎ የመሥራት ብቃት የነበረው ሲሆን ጳውሎስም ሥራውን በአግባቡ እንደሚፈጽም ትምክህት ስለነበረው ኃላፊነት አሸክሞ ሊልከው ችሏል። (1 ተሰሎንቄ 3:1, 2) ጳውሎስ በኤፌሶን የሚገኘው ጉባኤ ጠንከር ያለ ቲኦክራሲያዊ አመራር እንደሚያስፈልገው በተገነዘበ ጊዜ ጢሞቴዎስ በዚያ ቆይቶ ‘አንዳንዶች ልዩ ትምህርትን እንዳያስተምሩ እንዲያዛቸው’ አሳስቦት ነበር። (1 ጢሞቴዎስ 1:3) ይሁን እንጂ ጢሞቴዎስ ብዙ ኃላፊነቶችን ቢሸከምም ትሑት ነበር። ዓይነ አፋርነት ሊኖርበት ቢችልም ደፋር ነበር። ለምሳሌ ያህል ጳውሎስ በእምነቱ ምክንያት ለፍርድ በቀረበ ጊዜ እሱን ለመርዳት ወደ ሮም ተጉዟል። እንዲያውም ጢሞቴዎስ ራሱ በዚሁ ምክንያት ለተወሰነ ጊዜ ሳይታሰር አይቀርም።—ዕብራውያን 13:23
ጢሞቴዎስ ከጳውሎስ ብዙ ነገር እንደ ተማረ ምንም አያጠራጥርም። ሐዋርያው ለሥራ ባልደረባው የነበረው ላቅ ያለ ግምት በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ የተካተቱ በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፉ ሁለት ደብዳቤዎችን የጻፈለት በመሆኑ በሚገባ ተመስክሯል። በ65 እዘአ ገደማ ጳውሎስ ሰማዕት የሚሆንበት ጊዜ እንደቀረበ ሲገነዘብ ጢሞቴዎስን ወደ እርሱ እንዲመጣ ጠርቶት ነበር። (2 ጢሞቴዎስ 4:6, 9) ሐዋርያው ከመገደሉ በፊት ጢሞቴዎስ ሊያገኘው ስለ መቻሉ ቅዱሳን ጽሑፎች ምንም የሚገልጹት ነገር የለም።
ራስህን አቅርብ!
ከጢሞቴዎስ ግሩም ምሳሌ ብዙ ለመማር ይቻላል። ከጳውሎስ ጋር በመወዳጀቱ በእጅጉ የተጠቀመ ሲሆን ዓይነ አፋር የነበረ ወጣት የበላይ ተመልካች ሊሆን ችሏል። ዛሬም ወጣት ክርስቲያን ወንዶችና ሴቶች ተመሳሳይ የሆነ ወዳጅነት በመመሥረት ብዙ ሊጠቀሙ ይችላሉ። የይሖዋን አገልግሎት ቋሚ ሥራቸው ካደረጉት ደግሞ ጠቃሚ የሆነ ሥራ ሊበዛላቸው ይችላል። (1 ቆሮንቶስ 15:58) በራሳቸው ጉባኤ ውስጥ አቅኚዎች ወይም የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች ሊሆኑ ይችላሉ፤ ወይም የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት ቦታ ሄደው ማገልገል ይችሉ ይሆናል። በሌሎች አገሮች ውስጥ ሚስዮናዊ ሆኖ መሥራት ወይም በመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ዋና መሥሪያ ቤት ወይም ከቅርንጫፍ ቢሮዎች በአንዱ ውስጥ ማገልገል አንዳንዶቹ አማራጮች ናቸው። በእርግጥም ሁሉም ክርስቲያኖች ይሖዋን በሙሉ ነፍሳቸው በማገልገል የጢሞቴዎስን የመሰለ መንፈስ ሊያንጸባርቁ ይችላሉ።
የይሖዋ ድርጅት ጠቃሚ ነው በሚለው በማንኛውም ቦታ ተመድበህ ለመሥራት እንድትችል በመንፈሳዊ ማደግህን ለመቀጠል ትፈልጋለህን? እንግዲያው ጢሞቴዎስ እንዳደረገው አድርግ። አቅምና ሁኔታህ በፈቀደ መጠን ራስህን አቅርብ። ወደፊት ምን ዓይነት የአገልግሎት መብቶች እንደሚከፈቱልህ ማን ያውቃል?
[የግርጌ ማስታወሻ]
a በተጨማሪም ጢሞቴዎስ በሌሎች አራት የጳውሎስ ደብዳቤዎች ላይ ተጠቅሷል።—ሮሜ 16:21፤ 2 ቆሮንቶስ 1:1፤ 1 ተሰሎንቄ 1:1፤ 2 ተሰሎንቄ 1:1
[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
‘እንደ እርሱ ያለ ማንም የለኝም’