የተትረፈረፈ ልግስና
ለአንድ ንጉሥ ስጦታ የመስጠት አጋጣሚ ብታገኝ ምን ነገር ትሰጥ ነበር? ንጉሡ በሀብቱና በጥበቡ በዓለም አቻ የማይገኝለት ቢሆንስ? እርሱን ደስ የሚያሰኝ ስጦታ ማግኘት የምትችል ይመስልሃል? ከሦስት ሺህ ዓመታት ገደማ ቀደም ብሎ የሳባ ንግሥት በሀብቱና በጥበቡ አቻ ያልነበረውን የእስራኤሉን ንጉሥ ሰሎሞንን ለመጎብኘት ስትዘጋጅ በእነዚህ ጥያቄዎች ላይ ማውጠንጠን አስፈልጓት ነበር።
የወሰደችው ስጦታ 120 መክሊት ወርቅን ጨምሮ “እጅግም ብዙ ሽቱ [“የባልሳም ዘይት፣” NW] የከበረም ዕንቁ” እንደነበር መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል። ዛሬ ባለው ዋጋ ሲተመን ወርቁ ብቻ እስከ 40,000,000 የአሜሪካ ዶላር የሚያወጣ ነበር። የባልሳም ዘይት ግሩም መዓዛና መድኃኒትነት ያለው ዘይት ሲሆን ከወርቅ ተርታ የሚመደብ ውድ ሸቀጥ ነበር። ንግሥቲቱ ለሰሎሞን የሰጠችው የዘይት መጠን ምን ያህል እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ባይነግረንም ያመጣችው ስጦታ አቻ የሌለው እንደነበር ይገልጻል።—1 ነገሥት 10:10
የሳባ ንግሥት ሃብታምና ለጋስ ሴት እንደነበረች ግልጽ ነው። ደግሞም ያሳየችው ልግስና መልሶ ክሷታል። መጽሐፍ ቅዱስ “የሳባ ንግሥት ወደ ንጉሡ ካመጣችው ይበልጥ፣ ንጉሥ ሰሎሞን የወደደችውን ሁሉ የለመነችውን ሁሉ ሰጣት” ይላል። (2 ዜና መዋዕል 9:12 በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።) ነገሥታት ስጦታ መለዋወጣቸው የተለመደ ነገር ሊሆን ቢችልም መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሰሎሞን ‘ልግስና’ በግልጽ ይናገራል። (1 ነገሥት 10:13 የ1980 ትርጉም) ሰሎሞን ራሱ “ለጋስ ነፍስ መልሳ ራስዋ ትጠግባለች፣ በነፃ ውኃ የሚያጠጣም ራሱ መልሶ በነፃ ይጠጣል” ሲል ጽፏል።—ምሳሌ 11:25 NW
እርግጥ ነው፣ የሳባ ንግሥት ሰሎሞንን ለመጎብኘት ስትል በጊዜም ሆነ በድካም በኩል የከፈለችው መሥዋዕትነት ቀላል አልነበረም። ሳባ ትገኝ የነበረው በዛሬው ደቡብ የመን አካባቢ ስለሆነ ንግሥቲቱ ካስከተለችው የግመል ቅፍለት ጋር ኢየሩሳሌም ለመድረስ ከ1,600 የሚበልጡ ኪሎ ሜትሮችን ተጉዛለች። ኢየሱስ እንደተናገረው የመጣችው “ከምድር ዳር” ነበር። የሳባ ንግሥት ይህን ያህል ከፍተኛ ጥረት ያደረገችው ለምንድን ነው? የመጣችበት ዋነኛ ዓላማ ‘የሰሎሞንን ጥበብ ለመስማት’ ነበር።—ሉቃስ 11:31
አንደኛ ነገሥት 10:1, 2 የሳባ ንግሥት “[ሰሎሞንን] በእንቆቅልሽ ትፈትነው ዘንድ መጣች። . . . በልብዋ ያለውን ሁሉ አጫወተችው” ይላል። ሰሎሞንስ ምን ምላሽ ሰጠ? “ሰሎሞንም የጠየቀችውን ሁሉ ፈታላት፤ ሊፈታላት ያልቻለውና ከንጉሡ የተሰወረ ነገር አልነበረም።”—1 ነገሥት 10:3
ንግሥቲቱ በሰማችውና ባየችው ነገር እጅግ ተደንቃ በትህትና እንዲህ ስትል መለሰች:- “በፊትህ ሁል ጊዜ የሚቆሙ ጥበብህንም የሚሰሙ ሰዎችና እነዚህ ባሪያዎችህ ምስጉኖች [“ደስተኛ፣” NW] ናቸው።” (1 ነገሥት 10:4-8) የሰሎሞን አገልጋዮች በሃብት የታጠሩ ቢሆኑም እንኳ ደስተኛ ያለቻቸው በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ በመገኘታቸው አልነበረም። ከዚህ ይልቅ የሰሎሞን አገልጋዮች አምላክ ለንጉሡ የሰጠውን ጥበብ ዘወትር የመስማት አጋጣሚ ስለነበራቸው የተባረኩ ነበሩ። የሳባ ንግሥት ዛሬ በፈጣሪና በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ጥበብ ለሚደሰቱት የይሖዋ ሕዝቦች እንዴት ግሩም ምሳሌ ናት!
ንግሥቲቱ “አምላክህ እግዚአብሔር የተባረከ ይሁን” ስትል ለሰሎሞን የተናገረችው ነገርም ልብ ሊባል የሚገባው ነው። (1 ነገሥት 10:9) ከሁኔታው ለመረዳት እንደሚቻለው የሰሎሞን ጥበብና ብልጽግና ከይሖዋ የተገኘ መሆኑን ተገንዝባለች። ይህም ቀደም ሲል ይሖዋ ለእስራኤል ከገባው ቃል ጋር የሚስማማ ነው። ‘ትእዛዜን ብትጠብቁ’ “በእውነት ይህ ታላቅ ሕዝብ ጠቢብና አስተዋይ ሕዝብ ነው በሚሉ በአሕዛብ ፊት ጥበባችሁና ማስተዋላችሁ ይህ ነውና” ብሏቸው ነበር።—ዘዳግም 4:5-7
ጥበብ ወደሚሰጠው አምላክ መቅረብ
በዘመናችን በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ‘የአምላክ እስራኤል’ ‘ጠቢብና አስተዋይ ሕዝብ’ መሆናቸውን በማስተዋል ወደ ይሖዋ ድርጅት ተስበዋል። ይሁንና የአምላክ እስራኤል ይህን ጥበብና ማስተዋል ያገኙት በተፈጥሮ ችሎታቸው ሳይሆን በአምላክ ፍጹም ሕግጋትና መሠረታዊ ሥርዓቶች በመመራታቸው ነው። (ገላትያ 6:16) የተጠማቂዎች ቁጥር እንደሚያሳየው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በየዓመቱ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ አዳዲስ ደቀ መዛሙርት መንፈሳዊ እስራኤልን “እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር እንዳለ ሰምተናልና ከእናንተ ጋር እንሂድ” እያሉአቸው ነው። (ዘካርያስ 8:23) እነዚህ አዲሶች ይሖዋ ለአገልጋዮቹ የዘረጋውን ታላቅ መንፈሳዊ ዝግጅት ሲመለከቱ እንዴት ይገረማሉ! ቀደም ሲል በነበሩበት ሃይማኖት ውስጥ ይህን የመሰለ ነገር ፈጽሞ አይተው አያውቁም።—ኢሳይያስ 25:6
ለታላቁ ሰጭ መስጠት
አድናቆት ያላቸው ሰዎች የተቀበሉት ነገር በጣም ብዙ ከመሆኑ የተነሣ እነርሱ በተራቸው ለታላቁ ንጉሥና ሰጪ ለይሖዋ አምላክ ምን ሊሰጡት እንደሚችሉ ግራ ይገባቸዋል። መጽሐፍ ቅዱስ ለይሖዋ ልንሰጠው የምንችለው ከሁሉ የተሻለ ስጦታ ‘የምሥጋና መሥዋዕት’ እንደሆነ ይናገራል። (ዕብራውያን 13:15) ለምን? ይህ መሥዋዕት የሰዎችን ሕይወት ከማዳን ጋር በቀጥታ የተያያዘ በመሆኑና ይሖዋም በዚህ የፍጻሜ ዘመን እንዲሠራ የሚፈልገው ትልቅ ሥራ በመሆኑ ነው። (ሕዝቅኤል 18:23) በተጨማሪም አንድ ሰው የታመሙትን፣ የተጨነቁትንና ሌሎችንም ለመርዳት የሚያውለው ጉልበትና ጊዜ ተቀባይነት ያለው መሥዋዕት ነው።—1 ተሰሎንቄ 5:14፤ ዕብራውያን 13:16፤ ያዕቆብ 1:27
በገንዘብ የሚደረጉ መዋጮዎችም ቁልፍ ሚና ይጫወታሉ። መጽሐፍ ቅዱስና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች ለማዘጋጀት እንዲሁም ክርስቲያኖች የሚሰበሰቡባቸውን ቦታዎች ለማግኘት ያስችላል። (ዕብራውያን 10:24, 25) መዋጮ በጦርነትና በተፈጥሮ አደጋዎች የተጎዱ ሰዎችንም ለመርዳት የሚያስችል ገንዘብ ያስገኛል።
የአምላክ ቃል መስጠትን በተመለከተ መምሪያ ይሆኑን ዘንድ አንዳንድ ግሩም መሠረታዊ ሥርዓቶችን ይጠቅሳል። ለምሳሌ ያህል ክርስቲያኖች የሚሰጡት የተወሰነ መጠን ተመድቦላቸው ሳይሆን ከደስተኛ ልብ በመነሳሳት አቅማቸው የሚፈቅድላቸውን ያህል እንደሆነ ያስተምራል። (2 ቆሮንቶስ 9:7) አንዳንዶች ብዙ መስጠት ይችላሉ፤ ሌሎች ደግሞ በኢየሱስ ዘመን እንደነበረችው ድሃ መበለት መስጠት የሚችሉት ትንሽ ነገር ይሆናል። (ሉቃስ 21:2-4) የመላው ጽንፈ ዓለም ባለቤት የሆነው ይሖዋ አምላክ፣ ሰዎች በቀና ልብ ተገፋፍተው በስሙ ለሚያመጡት ስጦታና ለሚያቀርቡት መሥዋዕት ሁሉ ትልቅ ግምት የሚሰጥ መሆኑ አያስገርምም?—ዕብራውያን 6:10
የይሖዋ ሕዝቦች በደስታ መስጠት ይችሉ ዘንድ ድጋፍ መስጠት የሚያስፈልግባቸው ዘርፎች ምን እንደሆኑና ይህን ለማድረግ የሚያስችለው ውጤታማ መንገድ ምን እንደሆነ ሁልጊዜ እንዲያውቁ ይደረጋል። የይሖዋ መንፈስም ፈቃደኛ ልብ ያላቸውን ሰዎች ያነሳሳል። በጥንቷ እስራኤል በመገናኛው ድንኳንና በኋላም በቤተ መቅደሱ ግንባታ ወቅት ይህ ዓይነት አሠራር ተግባራዊ ሆኖ ነበር። (ዘጸአት 25:2፤ 35:5, 21, 29፤ 36:5-7፤ 39:32፤ 1 ዜና መዋዕል 29:1-19) በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንደ ዘመናችን አቆጣጠርም ክርስቲያኖች የመንግሥቱን ምሥራች ለአሕዛብ ለማድረስና በእስራኤልም ረሀብ በተነሳ ጊዜ በዚያ ያሉትን ወንድሞች ለመደገፍ የሚያስችል ገንዘብ ለማሰባሰብ የተጠቀሙት ይህንኑ አሠራር ነው።—1 ቆሮንቶስ 16:2-4፤ 2 ቆሮንቶስ 8:4, 15፤ ቆላስይስ 1:23
ዛሬም በተመሳሳይ ሕዝቦቹ በዓለም ላይ ታይቶ በማያውቅ መጠን የሚያካሂዱትን ሰፊ የስብከትና የማስተማር ዘመቻ ከዳር ለማድረስ ይችሉ ዘንድ ይሖዋ የሚያስፈልጋቸውን ሁሉ በመስጠት እየባረካቸው ሲሆን ወደፊትም መባረኩን ይቀጥላል።—ማቴዎስ 24:14፤ 28:19, 20
ዛሬ መሟላት ያለባቸው ነገሮች ምንድን ናቸው?
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የይሖዋ ምሥክሮች ሥራቸው እገዳ ተደርጎበት በቆዩባቸው ብዙ አገሮች ውስጥ ሕጋዊ እውቅና አግኝተው ተመዝግበዋል። ከዚህም የተነሣ ከእነዚህ አገሮች መካከል ብዙዎቹ በአስፋፊዎች ቁጥር ረገድ እጅግ ከፍተኛ ጭማሪ አግኝተዋል። የመጽሐፍ ቅዱስና የመጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች ፍላጎት እንደሚጨምር ግልጽ ነው።
የመንግሥት አዳራሾችም እንዲሁ። በአሁኑ ወቅት በዓለም ዙሪያ 9,000 አዳዲስ የመንግሥት አዳራሾች ያስፈልጋሉ። በየቀኑ አንድ የመንግሥት አዳራሽ ቢገነባ እንኳ በአሁኑ ጊዜ ያለውን ፍላጎት ለማሟላት ከ24 የሚበልጥ ዓመት ይፈጃል! በዚህ መሃል ደግሞ በየቀኑ ሰባት የሚያክሉ አዳዲስ ጉባኤዎች ይቋቋማሉ። ከእነዚህ መካከል ብዙዎቹ የገንዘብ አቅሙ ውስን በሆነበት የዓለም ክፍል የሚገኙ ናቸው። በሌላ በኩል ደግሞ ከእነዚህ መካከል በብዙዎቹ ቦታዎች የሚከናወነው የግንባታ ሥራ ብዙ ወጪ የሚጠይቅ አይደለም። በአንዳንድ አካባቢዎች ችግሩን ለማቃለልም ሆነ ለማኅበረሰቡም ጥሩ ምሥክርነት ለመስጠት የሚያስችል የመንግሥት አዳራሽ ሠርቶ ለማጠናቀቅ የሚያስፈልገው ወጪ 6,000 የአሜሪካ ዶላር ብቻ ነው።
በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ አንዳንድ ክርስቲያኖች በገንዘብ አቅማቸው ረገድ ከሌሎች የተሻሉ በመሆናቸው ሐዋርያው ጳውሎስ እንደሚከተለው ሲል ጽፏል:- “የእነርሱ ትርፍ ደግሞ የእናንተን ጒድለት እንዲሞላ በአሁኑ ጊዜ የእናንተ ትርፍ የእነርሱን ጕድለት ይሙላ፤ በትክክል እንዲሆን።” (2 ቆሮንቶስ 8:14) ዛሬም ቢሆን እንዲህ ያለው ‘መተካከል’ መጽሐፍ ቅዱስንና፣ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ለማዳረስ እንዲሁም የመንግሥት አዳራሾችን ለማሠራት፣ በአደጋ ጊዜ እርዳታ ለማቅረብ እንዲሁም ሌሎች ነገሮችን ለማከናወን የሚያስፈልገውን ገንዘብ ለማግኘት አስችሏል። እንዲህ ያለው ስጦታ ለሰጪውም ሆነ ለተቀባዩ እንዴት ያለ በረከት ነው!—ሥራ 20:35
ለጋስ ልብ ያላቸው ሰዎች ለማኅበሩ ከሚልኩት ደብዳቤ መረዳት እንደሚቻለው የዚህ መጽሔት አንባቢ የሆኑ ብዙ ሰዎች መርዳት ይፈልጋሉ፤ ነገር ግን በምን በምን መልኩ መዋጮ ማድረግ እንደሚችሉ እርግጠኛ አይደሉም። ከዚህ ጋር ተያይዞ የቀረበው ሣጥን ለጥያቄዎቻቸው መልስ እንደሚሰጣቸው ምንም ጥርጥር የለውም።
በሰሎሞን ክብራማ ግዛት ወቅት ስለ እርሱ የሰሙ “የምድር ነገሥታት ሁሉ” ወደ እርሱ ሄደው ነበር። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ ለይቶ የሚጠቅሰው የሳባ ንግሥትን ብቻ ነው። (2 ዜና መዋዕል 9:23) የከፈለችው መሥዋዕትነት ምንኛ ከፍተኛ ነበር! ይሁን እንጂ በጉብኝቷ መጨረሻ ‘ትንፋሽ እስኪያጥራት ድረስ ተገርማ’ ስለነበር በእጅጉ ተባርካበት ነበር ለማለት ይቻላል።—2 ዜና መዋዕል 9:4 ቶዴይስ ኢንግሊሽ ቨርሽን
ወደፊት ታላቁ ንጉሥና ሰጭ የሆነው ይሖዋ ለእርሱ መሥዋዕት ለሚያቀርቡለት ሁሉ ከሰሎሞን እጅግ የበለጠ ታላቅ ነገር ያደርግላቸዋል። ይሖዋ አስፈሪ ከሆነው የፍርድ ቀኑ በሕይወት ማዳን ብቻ ሳይሆን ከዚያ በኋላ ‘እጁን ከፍቶ ከመልካም ነገሮች ሁሉ ስለሚያጠግባቸው’ እነዚህ ሰዎች ‘ትንፋሽ እስኪያጥራቸው ድረስ በመገረም’ ከማየት በቀር የሚያደርጉት ነገር አይኖርም።—መዝሙር 145:16
[ገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
አንዳንዶች ለዓለም አቀፉ ሥራ
መዋጮ የሚያደርጉባቸው መንገዶች
ብዙዎች “ለማኅበሩ ዓለም አቀፍ ሥራ የሚደረግ መዋጮ—ማቴዎስ 24:14” ተብሎ የተለጠፈባቸው ሣጥኖች ውስጥ የሚጨምሩትን የተወሰነ የገንዘብ መጠን ይመድባሉ ወይም ወጪ ያደርጋሉ። ጉባኤዎች ይህን ገንዘብ በየወሩ በብሩክሊን ኒው ዮርክ ወዳለው ዋና መሥሪያ ቤት ወይም በአካባቢው ወደሚገኝ ቅርንጫፍ ቢሮ ይልካሉ።
በፈቃደኛነት የሚደረጉ የገንዘብ እርዳታዎችን በቀጥታ Treasurer’s Office, Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania, 25 Col-umbia Heights, Brooklyn, New York 11201-2483 በሚለው አድራሻ ወይም በአገርህ ወደሚገኝ የማኅበሩ ቅርንጫፍ ቢሮ መላክ ይቻላል። ጌጣጌጦችን ወይም ሌሎች ውድ ዕቃዎችንም በእርዳታ መስጠት ይቻላል። የተላከው ነገር ስጦታ መሆኑን የሚገልጽ አጭር ደብዳቤ አብሮ መላክ ይኖርበታል።
ተመላሽ ሊሆን የሚችል ገንዘብ ለመስጠት የሚያስችል ዝግጅት
አንድ ሰው ለመጠበቂያ ግንብ ማኅበር የሰጠውን ገንዘብ ሊጠቀምበት በሚፈልግበት ጊዜ ሊመለስለት የሚያስችል ልዩ ዝግጅት በማድረግ ለማኅበሩ ሊሰጥ ይችላል። ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ከላይ በተገለጸው አድራሻ የማኅበሩን የንብረት ክፍል መጠየቅ ይቻላል።
በእቅድ የሚደረግ ስጦታ
ለማኅበሩ በቀጥታ የገንዘብ ስጦታ ከመለገስና ተመላሽ ሊሆን የሚችል ገንዘብ ከመስጠት በተጨማሪ በመላው ዓለም የሚካሄደውን የመንግሥት አገልግሎት ለመደጎም መስጠት የሚቻልባቸው ሌሎች መንገዶችም አሉ። ከእነዚህ አንዳንዶቹ፦
ኢንሹራንስ፦ የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር የአንድ የሕይወት ዋስትና ኢንሹራንስ ፖሊሲ ወይም የጡረታ ክፍያ ተጠቃሚ እንዲሆን ስም ሊዛወርለት ይችላል።
የባንክ ሒሳብ፦ የአገሩ ባንክ በሚፈቅደው መሠረት የባንክ ሒሳቦች፣ ገንዘብ መቀመጡን የሚገልጽ የምሥክር ወረቀት ወይም የግል ጡረታ ሒሳቦች በአደራ ወይም በሞት ጊዜ የሚከፈል መሆኑ ተገልጾ ለመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ሊሰጥ ይችላል።
አክሲዮኖችና ቦንዶች፦ አክሲዮኖችና ቦንዶች እንዳለ በስጦታ መልክም ሆነ ገቢው ለሰጪው ያለ ማቋረጥ የሚከፈልበት ዝግጅት ተደርጎ ለመጠበቂያ ግንብ ማኅበር በእርዳታ መልክ መስጠት ይቻላል።
የማይንቀሳቀሱ ንብረቶች፦ ሊሸጡ የሚችሉ የማይንቀሳቀሱ ንብረቶች እንዳለ በስጦታነት ወይም ሰጪው በሕይወት እስካለ ድረስ በንብረቱ በመተዳደር እንዲቀጥል መብቱን በማስጠበቅ ለማኅበሩ በእርዳታ መስጠት ይቻላል። አንድ ሰው ማንኛውንም የማይንቀሳቀስ ንብረት ለማኅበሩ ከማስተላለፉ በፊት ከማኅበሩ ጋር መገናኘት ይኖርበታል።
ኑዛዜዎችና አደራዎች፦ ንብረት ወይም ገንዘብ በሕግ ፊት ተፈጻሚነት ባለው ኑዛዜ አማካኝነት ለመጠበቂያ ግንብ ማኅበር በውርሻ ሊሰጥ ወይም ማኅበሩ በአደራ የተሰጠው ንብረት ተጠቃሚ ተደርጎ ስሙ ሊዘዋወር ይችላል። አንድ የሃይማኖት ድርጅት እንዲጠቀምበት በአደራ የተሰጠ ንብረት በቀረጥ ረገድ አንዳንድ ጥቅሞች አሉት።
“በእቅድ የሚደረግ ስጦታ” የሚለው ሐረግ እንደሚያመለክተው እነዚህን የመሳሰሉ መዋጮዎች በሰጪው በኩል በትንሹም ቢሆን እቅድ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ያሳያሉ። ማኅበሩን በእቅድ በሚደረግ ስጦታ ለመደጎም ለሚፈልጉ ግለሰቦች የዓለም አቀፉን የመንግሥት አገልግሎት ለመደጎም በእቅድ የሚደረግ ስጦታ የሚል ብሮሹር አዘጋጅቷል። ይህ ብሮሹር የተዘጋጀው ስጦታዎችን፣ ኑዛዜዎችንና አደራዎችን በተመለከተ ማኅበሩ ለቀረቡለት ብዛት ያላቸው ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት ነው። ብሮሹሩ ንብረትን፣ የገንዘብ አጠቃቀምንና የቀረጥ ምጣኔን አስመልክቶ ጠቃሚ የሆኑ ተጨማሪ መረጃዎችን የያዘ ከመሆኑም በተጨማሪ በዩናይትድ ስቴትስ ለሚኖሩና በዓለም ዙሪያ የሚካሄደውን የመንግሥቱን ፍላጎት አሁንም ሆነ ከሞቱ በኋላ ውርስ በመስጠት ለመደጎም ፍላጎት ያላቸውን ግለሰቦች የቤተሰባቸውና የግል ሁኔታቸው የሚፈቅድላቸውን ጠቃሚና ውጤታማ ዘዴ ለመምረጥ እንዲችሉ ታስቦ የተዘጋጀ ነው። በእቅድ የሚደረግ ስጦታ ዴስክን በመጠየቅ ይህን ብሮሹር ማግኘት ይቻላል።
ይህን ብሮሹር በማንበብና በእቅድ የሚደረግ ስጦታ ዴስክ ላይ ከሚሠሩት ወንድሞች ምክር በመጠየቅ ብዙዎች ማኅበሩን ለመርዳት ከመቻላቸውም በላይ ከቀረጥ ቅናሽ የሚገኘውን ጥቅም ከፍ ለማድረግ ችለዋል። በእቅድ የሚደረግ ስጦታ ዴስክ እነዚህን ዝግጅቶች የሚመለከት ማንኛውንም ሰነድ ማግኘትና ስለ ጉዳዩ እንዲነገረው ያስፈልጋል። ከእነዚህ በእቅድ የሚደረጉ ስጦታዎች በአንዱ ለመካፈል የምትፈልጉ ከሆነ ከታች ያለውን አድራሻ ተጠቅማችሁ ወይም በአገራችሁ ወዳለው የማኅበሩ ቢሮ በመጻፍ ወይም በመደወል ማሳወቅ ይኖርባችኋል።
CHARITABLE PLANNING OFFICE
Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
100 Watchtower Drive, Patterson, New York 12563-9204
Telephone: (914) 306-1000
[በገጽ 23 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
የይሖዋ ምሥክሮች እንቅስቃሴ በፈቃደኛነት በሚደረጉ መዋጮዎች የተደገፈ ነው