የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w99 11/1 ገጽ 28-29
  • የአንባብያን ጥያቄዎች

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • የአንባብያን ጥያቄዎች
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1999
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ለባንዲራ ሰላምታ መስጠት፣ ድምፅ መስጠትና የሲቪል አገልግሎት
    ‘ከአምላክ ፍቅር አትውጡ’
  • የይሖዋ ምሥክሮች ከፖለቲካ ጉዳዮች ገለልተኛ የሆኑት ለምንድን ነው?
    ስለ ይሖዋ ምሥክሮች ብዙ ጊዜ የሚነሱ ጥያቄዎች
  • “ከዓለም አይደሉም”
    እውነተኛውን አንድ አምላክ አምልክ
  • “የዓለም ክፍል አይደሉም”
    እውነተኛው አንድ አምላክ ያስገኘው የአምልኮ አንድነት
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1999
w99 11/1 ገጽ 28-29

የአንባብያን ጥያቄዎች

የይሖዋ ምሥክሮች ድምፅ ስለ መስጠት ያላቸው አመለካከት ምንድን ነው?

የአምላክ አገልጋዮች ስለዚህ ጉዳይ ተገቢው አመለካከት እንዲኖራቸው የሚያስችሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተዘረዘሩ ግልጽ የሆኑ መሠረታዊ ሥርዓቶች አሉ። ይሁንና ድምፅ መስጠትን በቀጥታ የሚቃወም መሠረታዊ ሥርዓት የለም። ለምሳሌ ያህል አንድ የዲሬክተሮች ቦርድ ድርጅቱን በሚመለከት ጉዳይ ላይ ድምፅ በመስጠት ውሳኔ ሊያሳልፍ ይችላል። የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች አብዛኛውን ጊዜ የስብሰባ ሰዓትንና የጉባኤ መዋጮዎች አጠቃቀምን በሚመለከት እጅ አውጥቶ ድምፅ በመስጠት ውሳኔዎችን ያሳልፋሉ።

ይሁንና በፖለቲካዊ ምርጫዎች ላይ ድምፅ መስጠትን በተመለከተ ምን ለማለት ይቻላል? እርግጥ ነው፣ በአንዳንድ ዲሞክራሲያዊ አገሮች ውስጥ ከሕዝቡ መካከል 50 በመቶ የሚሆነው በምርጫ ቀናት ድምፅ ለመስጠት አይወጣም። የይሖዋ ምሥክሮች ሌሎች ሰዎች ያላቸውን ድምፅ የመስጠት መብት አይጋፉም፤ ወይም ፖለቲካዊ ምርጫዎችን በተመለከተ ምንም ዓይነት የተቃውሞ ዘመቻ አያደርጉም። እነዚህን በመሳሰሉ ምርጫዎች አግባብ ባለው መንገድ የሚመረጡ ባለ ሥልጣናትን ያከብራሉ፣ ይተባበራሉም። (ሮሜ 13:​1-7) ለምርጫ የሚወዳደርን ሰው መምረጥ አለመምረጥን በተመለከተ ግን እያንዳንዱ የይሖዋ ምሥክር በመጽሐፍ ቅዱስ የሰለጠነ ሕሊናውን ተጠቅሞ እንዲሁም ለአምላክና ለመንግሥት ያለበትን ኃላፊነት ከግምት ውስጥ በማስገባት ውሳኔ ያደርጋል። (ማቴዎስ 22:​21፤ 1 ጴጥሮስ 3:​16) የይሖዋ ምሥክሮች ይህን የግል ውሳኔ በሚያደርጉበት ጊዜ በርካታ ጉዳዮችን ግምት ውስጥ ያስገባሉ።

አንደኛ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ተከታዮቹ “እኔ ከዓለም እንዳይደለሁ እነሱም ከዓለም አይደሉም” ብሏል። (ዮሐንስ 17:​14) የይሖዋ ምሥክሮች ይህን መሠረታዊ ሥርዓት በቁም ነገር ይመለከቱታል። ‘የዓለም ክፍል ባለመሆናቸው’ ከዚህ ዓለም ፖለቲካዊ ጉዳዮች ገለልተኛ ናቸው።​—⁠ዮሐንስ 18:​36

ሁለተኛ፣ ሐዋርያው ጳውሎስ በዘመኑ ለነበሩ ሰዎች እሱ የክርስቶስ ‘አምባሳደር’ መሆኑን ገልጾ ነበር። (ኤፌሶን 6:​20፤ 2 ቆሮንቶስ 5:​20 የ1980 ትርጉም) የይሖዋ ምሥክሮች፣ ክርስቶስ ኢየሱስ በአሁኑ ጊዜ የአምላክ ሰማያዊ መንግሥት ንጉሥ እንደሆነና እንደ አምባሳደሮች እነሱም ይህን ለብሔራት ማሳወቅ እንዳለባቸው ያምናሉ። (ማቴዎስ 24:​14፤ ራእይ 11:​15) አምባሳደሮች ገለልተኞች እንዲሆኑና በተላኩበት አገር የውስጥ ጉዳይ እጃቸውን ከማስገባት እንዲቆጠቡ ይጠበቅባቸዋል። የይሖዋ ምሥክሮችም በተመሳሳይ የአምላክ ሰማያዊ መንግሥት ተወካዮች እንደመሆናቸው መጠን በሚኖሩባቸው አገሮች ውስጥ ካለው ፖለቲካዊ ሥርዓት ገለልተኛ ለመሆን ይፈልጋሉ።

ሊታሰብበት የሚገባው ሦስተኛው ነጥብ ደግሞ አንድን ሰው ለተወሰነ የኃላፊነት ቦታ እንዲበቃ ድምፅ የሚሰጡ ሰዎች ሰውየው በሚያደርገው ነገር በኃላፊነት የሚጠየቁ መሆናቸው ነው። (ከ1 ጢሞቴዎስ 5:​22 የ1980 ትርጉም ጋር አወዳድር።) ክርስቲያኖች ይህን ኃላፊነት ለመሸከም ይፈልጉ እንደሆነና እንዳልሆነ በጥንቃቄ መመርመር ይገባቸዋል።

አራተኛ፣ የይሖዋ ምሥክሮች ለክርስቲያናዊ አንድነታቸው የላቀ ግምት ይሰጣሉ። (ቆላስይስ 3:​14) ሃይማኖቶች በፖለቲካ ጉዳዮች ውስጥ ጣልቃ ሲገቡ አብዛኛውን ጊዜ በአባላቱ መካከል መከፋፈል ይፈጠራል። የይሖዋ ምሥክሮች የኢየሱስ ክርስቶስን ምሳሌ በመከተል በፖለቲካ ጉዳዮች ውስጥ እጃቸውን ስለማያስገቡ ክርስቲያናዊ አንድነታቸው ይጠበቃል።​—⁠ማቴዎስ 12:​25፤ ዮሐንስ 6:​15፤ 18:​36, 37

አምስተኛውና የመጨረሻው፣ የይሖዋ ምሥክሮች በፖለቲካ ጉዳዮች ውስጥ እጃቸውን አለማስገባታቸው በሁሉም ፖለቲካዊ ሥርዓቶች ውስጥ ለሚገኙ ሰዎች አስፈላጊውን የመንግሥት መልእክት በልበ ሙሉነት ለማቅረብ ያስችላቸዋል።​—⁠ዕብራውያን 10:​35

ከላይ የተዘረዘሩትን ቅዱስ ጽሑፋዊ መሠረታዊ ሥርዓቶች ከግምት ውስጥ በማስገባት በብዙ አገሮች የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች በፖለቲካዊ ምርጫዎች ላለመካፈል የግል ውሳኔ ያደርጋሉ፤ ይህን ውሳኔ የማድረግ ነፃነታቸውም ያሉበት አገር ሕግ ድጋፍ አለው። ይሁንና የአንድ አገር ሕግ ዜጎቹ ድምፅ እንዲሰጡ የሚያስገድድ ከሆነስ? እንዲህ ባለ ሁኔታ ላይ እያንዳንዱ ምሥክር በሕሊናው ተመርቶ ሁኔታውን የሚመለከት ቅዱስ ጽሑፋዊ ውሳኔ የማድረግ ኃላፊነት አለበት። አንድ ሰው ወደ ምርጫ ጣቢያው ለመሄድ ከወሰነ ይህ የራሱ ውሳኔ ነው። በምሥጢር ድምፅ መስጫው ውስጥ የሚያደርገውን ነገር የሚያውቁት እሱና ፈጣሪ ብቻ ናቸው።

የኅዳር 15, 1950 መጠበቂያ ግንብ እትም በገጽ 445ና 446 ላይ እንዲህ ብሎ ነበር:- “ቄሣር ዜጎቹ ድምፅ እንዲሰጡ የሚያስገድድ ከሆነ . . . [የይሖዋ ምሥክሮች] ወደ ምርጫ ጣቢያዎች ሊሄዱና በምሥጢር ድምፅ ወደሚሰጥባቸው ክፍሎች ሊገቡ ይችላሉ። የቆሙለትን ዓላማ በሚያሳውቅ መልኩ በምርጫው ካርድ ላይ ምልክት ማድረግ ወይም መጻፍ ያለባቸው በዚህ ጊዜ ነው። መራጮቹ በምርጫ ካርዶቻቸው ላይ የፈለጉትን ሊያደርጉ ይችላሉ። ስለዚህ ምሥክሮቹ ከአምላክ ትእዛዛትና ከእምነታቸው ጋር በሚስማማ መንገድ እርምጃ መውሰድ ያለባቸው በዚህ አምላክ ብቻ በሚያያቸው ወቅት ነው። በምርጫ ካርዱ ላይ ምን ማድረግ እንዳለባቸው መመሪያ መስጠት የእኛ ኃላፊነት አይደለም።”

አንዲት ክርስቲያን ሴት የማያምን ባልዋ ወደ ምርጫ ጣቢያው እንድትሄድና እንድትመርጥ ቢያስገድዳትስ? ክርስቲያኖች ለበላይ ባለ ሥልጣኖች እንደሚገዙ ሁሉ እሷም ለባሏ ትገዛለች። (ኤፌሶን 5:​22፤ 1 ጴጥሮስ 2:​13-17) ባሏን በመታዘዝ ወደ ምርጫ ጣቢያው ከሄደች ይህ የራሷ ውሳኔ ነው። ማንም ሊነቅፋት አይገባም።​—⁠ከሮሜ 14:​4 ጋር አወዳድር።

ሰዎች በምርጫ እንዲካፈሉ ሕግ በማያስገድድባቸው አገሮች የሚኖሩና ሆኖም በምርጫ ጣቢያዎች በማይገኙ ሰዎች ላይ ጥላቻ የሚቀሰቀስ ምናልባትም ለአካላዊ ጥቃት የሚያጋልጥ ከሆነስ? ወይም ግለሰቦች ድምፅ እንዲሰጡ በሕግ ባይገደዱም በምርጫ ጣቢያ በማይገኙት ላይ ግን በሆነ መንገድ ከባድ ቅጣት የሚደርስባቸው ከሆነስ? እነዚህንና እነዚህን በመሳሰሉ ሌሎች ሁኔታዎች አንድ ክርስቲያን የራሱን ውሳኔ ማድረግ አለበት። “እያንዳንዱ የገዛ ራሱን ሸክም ሊሸከም ነውና።”​—⁠ገላትያ 6:​5

በአገራቸው ምርጫ በሚደረግበት ጊዜ አንዳንድ የይሖዋ ምሥክሮች ወደ ምርጫ ጣቢያው ሲሄዱ ሌሎቹ አለመሄዳቸውን በመመልከት የተደናቀፉ ሰዎች ይኖሩ ይሆናል። ‘የይሖዋ ምሥክሮች ወጥ የሆነ ሥርዓት የላቸውም’ ይሉ ይሆናል። ይሁንና እነዚህን በመሳሰሉ ለግለሰቡ ሕሊና በሚተዉ ጉዳዮች ረገድ እያንዳንዱ ክርስቲያን በይሖዋ አምላክ ፊት የራሱን ውሳኔ ማድረግ እንዳለበት ሰዎች መገንዘብ አለባቸው።​—⁠ሮሜ 14:​12

የይሖዋ ምሥክሮች የሚያጋጥሟቸውን የተለያዩ ሁኔታዎች ተንተርሰው ማንኛውንም ዓይነት የግል ውሳኔ ሲያደርጉ ክርስቲያናዊ ገለልተኝነታቸውንና የመናገር ነፃነታቸውን ጠብቀው ለመቆየት ጥረት ያደርጋሉ። እንዲያጠነክራቸው፣ ጥበብ እንዲሰጣቸውና እምነታቸውን የሚያስጥስ ነገር ከማድረግ እንዲቆጠቡ እንዲረዳቸው ሙሉ በሙሉ በይሖዋ አምላክ ይታመናሉ። እንዲህ በማድረግም በሚከተሉት የመዝሙራዊው ቃላት እንደሚታመኑ ያሳያሉ:- “አምባዬና መጠጊያዬ አንተ ነህና ስለ ስምህ መንገዴን አቅና ምራኝም።”​—⁠መዝሙር 31:​3

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ