የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w99 11/1 ገጽ 30-31
  • የይሖዋን ፈቃድ ፈጽመዋል

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • የይሖዋን ፈቃድ ፈጽመዋል
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1999
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • በቁሳቁስና በችሎታ የተደረገ አስተዋጽኦ
  • ለእኛ የሚሆን ትምህርት
  • ‘በዓመፃ ገንዘብ ወዳጆችን አብጁ’
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1994
  • የይሖዋን መንገድ መማር
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2005
  • አምላክን ለማወደስ በአንድነት መገንባት
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2006
  • የዘፀአት መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2004
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1999
w99 11/1 ገጽ 30-31

የይሖዋን ፈቃድ ፈጽመዋል

ንጹሕ አምልኮን ለማስፋፋት በፈቃደኛነት የተደረገ ልግስና

እስራኤላውያን የይሖዋን የማዳን ኃይል በዓይናቸው ተመልክተዋል። በደረቅ ምድር እንዲሻገሩና ከግብጻውያን ሠራዊት እንዲያመልጡ የቀይ ባሕር ውኃ በተዓምራዊ መንገድ ሲከፈል ተመልክተዋል። በማዶ አስተማማኝ ርቀት ላይ ቆመው ያው ውኃ በአሳዳጆቻቸው ላይ ሲከነበል ተመልክተዋል። ይሖዋ ከሞት አድኗቸዋል!​—⁠ዘጸአት 14:​21-31

የሚያሳዝነው ግን አንዳንድ እስራኤላውያን አምላክ የዋለላቸውን ውለታ ረሱ። ሙሴ በሲና ተራራ ላይ በነበረበት ጊዜ የወርቅ ጌጣ ጌጦቻቸውን ወደ አሮን አምጥተው የሚያመልኩት ጣዖት እንዲሠራላቸው ጠየቁት። ሙሴ ተመልሶ ሲመጣ እነዚህ ዓመፀኞች ተሰብስበው ሲበሉ፣ ሲጠጡ፣ ሲዘፍኑና ለወርቅ ጥጃው ሲሰግዱ አገኛቸው! ከዚያም በይሖዋ ትእዛዝ ዋነኛዎቹ የዓመፁ ጠንሳሾች ሳይሆኑ አይቀሩም 3,000 የሚያክሉ ሰዎች ተገደሉ። በዚያ ዕለት የአምላክ ሕዝብ ለይሖዋ ብቻ የተለየ አምልኮ መስጠት ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ትልቅ ትምህርት አግኝቷል።​—⁠ዘጸአት 32:​1-6, 19-29

ይህ ሁኔታ ከደረሰ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ሙሴ የመገናኛ ድንኳን ማለትም ከቦታ ወደ ቦታ የሚንቀሳቀስ የአምልኮ ድንኳን እንዲሠራ አምላክ የሰጠውን ትእዛዝ ለመፈጸም ተነሣ። ይህ የግንባታ ፕሮጄክት ውድ የሆኑ ቁሳቁሶችንና ችሎታ ያላቸው ሠራተኞችን የሚጠይቅ ነበር። ይህን ሁሉ ከየት ማግኘት ይቻላል? እኛስ ከዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ምን ልንማር እንችላለን?

በቁሳቁስና በችሎታ የተደረገ አስተዋጽኦ

ይሖዋ በሙሴ አማካኝነት “ለይሖዋ መዋጮ አቅርቡ፤ ፈቃደኛ ልብ ያለው ሁሉ ለይሖዋ መዋጮ ያምጣ” የሚል ትእዛዝ ሰጣቸው። ይህ ምን ዓይነት መዋጮ ነበር? ሙሴ ከዘረዘራቸው ነገሮች መካከል ወርቅ፣ ብር፣ ናስ፣ ሱፍ ክር፣ ጨርቆች፣ ቁርበትና እንጨት እንዲሁም የከበሩ ድንጋዮች ይገኙበት ነበር።​—⁠ዘጸአት 35:​5-9NW

እስራኤላውያኑ በልግስና እንዲህ ያለውን መዋጮ ለማድረግ የሚያስችል አቅም ነበራቸው። ግብጽን ለቅቀው በወጡበት ጊዜ ብዙ የወርቅና የብር ዕቃ እንዲሁም ልብስ ይዘው እንደወጡ አስታውስ። በእርግጥም ‘ግብጻውያንን በዝብዘዋቸው ነበር።’a (ዘጸአት 12:​35, 36) ቀደም ሲል እስራኤላውያን ለሐሰት አምልኮ ጣዖት ለመሥራት ጌጣቸውን በፈቃደኛነት አቅርበው ነበር። አሁንስ እውነተኛውን አምልኮ ለማስፋፋት እንደዚያ ባለ በጉጉት ስጦታ ያመጡ ይሆን?

ሙሴ እያንዳንዱ ሰው ምን ያህል መስጠት እንዳለበት እንዳልወሰነ ወይም እንዲሰጡ ለማነሳሳት የጥፋተኛነት ወይም የሐፍረት ስሜት እንዲሰማቸው እንዳላደረገ ልብ በል። ከዚህ ይልቅ ‘ፈቃደኛ ልብ ላለው ሁሉ’ ጥሪ አቀረበ። ሙሴ የአምላክን ሕዝብ ማስገደድ እንዳለበት ሆኖ አልተሰማውም። እያንዳንዱ የቻለውን ያህል እንደሚሰጥ ትምክህት ነበረው።​—⁠ከ2 ቆሮንቶስ 8:​10-12 ጋር አወዳድር።

ይሁን እንጂ ለግንባታው ፕሮጄክት የሚያስፈልገው የቁሳቁስ ስጦታ ብቻ አልነበረም። በተጨማሪም ይሖዋ ለእስራኤላውያን እንዲህ ብሏቸዋል:- “በእናንተም ዘንድ ያሉ በልባቸው ጥበበኞች ሁሉ መጥተው እግዚአብሔር ያዘዘውን ሁሉ ያድርጉ።” አዎን፣ ይህ የግንባታ ፕሮጄክት ባለሙያዎችም ያስፈልጉት ነበር። በእርግጥም ይህንን ፕሮጄክት ለማጠናቀቅ የእንጨት፣ የብረትና የጌጣ ጌጥ ሥራን ጨምሮ ‘ሁሉንም ዓይነት የእጅ ጥበብ ሥራ’ የሚችሉ ሰዎች መኖር ነበረባቸው። እርግጥ ይሖዋ ሠራተኞቹ ያላቸውን ተሰጥዖ እንዲጠቀሙበት ስለሚረዳቸው ለፕሮጄክቱ ስኬት የሚመሰገነው እርሱ መሆኑ ተገቢ ነበር።​—⁠ዘጸአት 35:​10, 30-35፤ 36:​1, 2

እስራኤላውያኑ ንብረታቸውንም ሆነ ችሎታቸውን እንዲሰጡ የቀረበላቸውን ግብዣ በደስታ ተቀበሉ። የመጽሐፍ ቅዱሱ ዘገባ እንዲህ ይላል:- “ከእነርሱም ሰው ሁሉ ልቡ እንዳነሣሣው መንፈሱም እሺ እንዳሰኘው ለመገናኛውም ድንኳን ሥራ ለማገልገያውም ሁሉ ለተቀደሰውም ልብስ ለእግዚአብሔር ስጦታ አመጡ። ወንዶችና ሴቶች ልባቸው እንደፈቀደ . . . አመጡ።”​—⁠ዘጸአት 35:​21, 22

ለእኛ የሚሆን ትምህርት

በዛሬው ጊዜ እየተከናወነ ያለው ትልቁ የአምላክ መንግሥት ምሥራች ስብከት ሥራ የሚካሄደው በፈቃደኝነት በሚደረጉ መዋጮዎች ነው። ብዙውን ጊዜ እነዚህ መዋጮዎች በገንዘብ መልክ የሚሰጡ ናቸው። በሌላ በኩል ግን ክርስቲያን ወንድሞችና እህቶች ያካበቱትን እውቀት የመንግሥት አዳራሾችን፣ የትላልቅ ስብሰባ አዳራሾችንና የቅርንጫፍ ቢሮዎችን ለመገንባት ይጠቀሙበታል። ከዚህም ሌላ በዓለም ዙሪያ ከአንድ መቶ በሚበልጡት የቤቴል ቤቶች ውስጥ የሚከናወነው ሥራ የተለያየ ችሎታ የሚጠይቅ ነው። እንዲህ ያለውን ስጦታ በማቅረብ ላይ ያሉት ፈቃደኛ ልብ ያላቸው ሰዎች ሁሉ ይሖዋ ድካማቸውን እንደማይረሳ እርግጠኞች ሊሆኑ ይችላሉ!​—⁠ዕብራውያን 6:​10

እያንዳንዳችን በክርስቲያናዊ አገልግሎት የምናደርገውም ተሳትፎ ቢሆን ከዚያ የተለየ አይደለም። ሁላችንም በአገልግሎቱ በቅንዓት መካፈል እንችል ዘንድ ጊዜያችንን እንድንዋጅ ማበረታቻ ተሰጥቶናል። (ማቴዎስ 24:​14፤ ኤፌሶን 5:​15-17) አንዳንዶች ይህንን ማበረታቻ በመቀበል የሙሉ ጊዜ ወንጌላውያን ወይም አቅኚዎች ይሆናሉ። ሌሎች ደግሞ ካለባቸው ሁኔታ አንጻር በአገልግሎት የአቅኚዎችን ያህል ሰዓት ማሳለፍ አይችሉም። ሆኖም እነርሱም የይሖዋን ልብ ደስ እያሰኙ ነው። በመገናኛው ድንኳን ግንባታ ወቅት እንደሆነው ሁሉ ዛሬም ይሖዋ እያንዳንዱ ሰው ምን ያህል መሥራት እንዳለበት አልወሰነም። የሚፈልግብን ነገር ቢኖር እያንዳንዳችን በፍጹም ልባችን፣ ነፍሳችን፣ ሐሳባችንና ኃይላችን እንድናገለግለው ነው። (ማርቆስ 12:​30) ይህንን እያደረግን ከሆነ ንጹሕ አምልኮን ለማስፋፋት ለምናደርገው አስተዋጽኦ ብድራት እንደሚከፍለን እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን።​—⁠ዕብራውያን 11:​6

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ይህ ድርጊት ስርቆት አልነበረም። እስራኤላውያን ከግብፃውያን የጠየቁት መዋጮ ሲሆን ይህንንም በነፃ ሰጥተዋቸዋል። ከዚህም ሌላ ግብጻውያን መጀመሪያውኑም እስራኤላውያንን በባርነት የመግዛት አንዳችም መብት ያልነበራቸው በመሆኑ የአምላክ ሕዝቦች ለብዙ ዓመታት ላከናወኑት ከባድ ሥራ ምንዳቸውን ሊሰጧቸው ይገባ ነበር።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ