መጽሐፍ ቅዱስ በዘመናችን ለሚነሱ አንገብጋቢ ጥያቄዎች መልስ ይሰጣል
መጽሐፍ ቅዱስ በዛሬው ጊዜ አስፈላጊ ነውን? አዎን፣ የሚል መልስ መስጠት የሚቻለው ይህ ዘመናት ያስቆጠረ መጽሐፍ ለአንባቢዎቹ ወቅታዊና አንገብጋቢ ለሆኑ ጥያቄዎች መልስ የሚሰጥ ከሆነ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ በዛሬው ዓለም ውስጥ በጣም አስፈላጊ በሆኑ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ጠቃሚ ምክር ይሰጣልን?
እስቲ ሁለት አንገብጋቢ ጥያቄዎችን እንመልከት። እንዲህ በማድረግ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ እነዚህ ጉዳዮች ምን እንደሚል እንመረምራለን።
አምላክ መከራ እንዲኖር የፈቀደው ለምንድን ነው?
በዛሬው ጊዜ በዓለም ላይ ካሉት ሁኔታዎች በመነሳት ብዙዎች እንደሚከተለው ብለው ይጠይቃሉ:- አምላክ ንጹሐን ሰዎች እንዲሰቃዩ የሚፈቅደው ለምንድን ነው? ከዕለት ወደ ዕለት ቁጥራቸው እየጨመረ የሚሄድ በርካታ ሰዎች በወንጀል፣ በሙስና፣ በዘር ማጥፋት፣ በግል ሕይወት በሚያጋጥም አሳዛኝ ሁኔታና በመሳሰሉት ችግሮች ሥቃይ የሚደርስባቸው በመሆኑ ይህ ጥያቄ ተገቢ ነው።
ለምሳሌ ያህል በሰሜናዊ ጀርመን ሰኔ 1998 አንድ ፈጣን ባቡር ድልድይ ጥሶ በመግባቱ ከመቶ በላይ ለሚሆኑ ሰዎች መሞት ምክንያት ሆኗል። የቆሰሉትንና የሞቱትን ለማንሳት በቦታው የተገኙ የብዙ ዓመት ተሞክሮ ያላቸው የሕክምና ባለሙያዎችና የእሳት አደጋ ሠራተኞች እንኳ አደጋው ከመጠን በላይ ዘግናኝ መሆኑን ተናግረዋል። አንድ የወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን ጳጳስ “አቤቱ አምላክ፣ እንዲህ ያለው ነገር እንዲደርስ የፈቀድከው ለምንድን ነው?” ሲሉ ጠይቀዋል። ጳጳሱ ራሳቸውም ቢሆኑ መልሱን አያውቁትም።
ከተሞክሮ እንደታየው ንጹሐን ሰዎች ምንም በማያውቁት ምክንያት መከራ ሲደርስባቸው አንዳንዴ በጣም ይመረራሉ። መጽሐፍ ቅዱስ ጠቃሚ የሆነበት አንደኛው ምክንያት ንጹሐን ሰዎች ለክፋትና ለመከራ የሚዳረጉበትን ምክንያት የሚያብራራልን መሆኑ ነው።
ይሖዋ አምላክ ምድርንና በምድር ላይ ያሉትን ነገሮች ሲፈጥር የሰው ልጆች በክፋትና በመከራ እንዲሰቃዩ ፈጽሞ ዓላማው አልነበረም። እንዴት እርግጠኞች መሆን እንችላለን? ምክንያቱም አምላክ የፍጥረት ሥራውን ሲጨርስ “ያደረገውን ሁሉ አየ፣ እነሆም እጅግ መልካም ነበረ።” (ዘፍጥረት 1:31) ‘እኔ አንድ መጥፎ የሆነ ነገር እየተመለከትኩ “እጅግ መልካም” በማለት እናገራለሁ?’ ብለህ ራስህን ጠይቅ። እንደዚያ እንደማትል የታወቀ ነው! በተመሳሳይም አምላክ ሁሉ ነገር “እጅግ መልካም” ብሎ ሲናገር በምድር ላይ ምንም ዓይነት ክፋት አልነበረም ማለት ነው። ታዲያ ክፋት የጀመረው እንዴትና መቼ ነው?
የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን አዳምና ሔዋን ከተፈጠሩ በኋላ ብዙም ሳይቆይ አንድ ኃይለኛ መንፈሳዊ ፍጡር ወደ ሴቲቱ በመቅረብ የይሖዋን እውነተኝነትና የሉዓላዊነቱን ትክክለኝነት አጠያያቂ አደረገ። (ዘፍጥረት 3:1-5) ሰይጣን ዲያብሎስ የተባለው ይህ ፍጡር ቆየት ብሎም ሰዎች መከራ ቢደርስባቸው ለአምላክ ታማኝ ሆነው አይቀጥሉም ሲል ተከራከረ። (ኢዮብ 2:1-5) ይሖዋ ይህን ጉዳይ በተመለከተ ምን ምላሽ ሰጠ? ሰዎች ከእሱ አመራር ውጭ በመሆን በተሳካ ሁኔታ አካሄዳቸውን ማቅናት የማይችሉ መሆናቸው በጊዜ ሂደት እንዲረጋገጥ ፈቀደ። (ኤርምያስ 10:23) ፍጥረታት ከአምላክ ሕጎችና መሠረታዊ ሥርዓቶች በሚቃረን መንገድ ከሄዱ ውጤቱ ኃጢአት ነው፤ ኃጢአት ደግሞ ጎጂ ነገሮችን ያስከትላል። (መክብብ 8:9፤ 1 ዮሐንስ 3:4) ይሁን እንጂ እነዚህ መጥፎ ሁኔታዎች ቢኖሩም ለእሱ ያላቸውን የጸና አቋም እንደያዙ የሚቀጥሉ ሰዎች እንደሚኖሩ ይሖዋ ያውቅ ነበር።
በኤደን ገነት ከተፈጸመው ከዚያ አሳዛኝ ዓመፅ ወዲህ 6,000 የሚያክሉ ዓመታት አልፈዋል። ይህ በጣም ረጅም ጊዜ ነውን? ይሖዋ ሰይጣንንና አጫፋሪዎቹን ከብዙ መቶ ዘመናት በፊት ሊያጠፋቸው ይችል ነበር። ሆኖም የይሖዋ ሉዓላዊነት ትክክል መሆኑንና ሰዎች ከእሱ ጎን በመቆም ረገድ ያላቸውን የጸና አቋም በተመለከተ ሊነሳ የሚችል ማንኛውም ጥርጣሬ እስኪወገድ ድረስ በትዕግሥት መጠበቅ የተሻለ አይደለምን? ዛሬ ያለው የፍትህ አሠራር አንዳንድ ጊዜ ማን ንጹህ ማን ደግሞ ጥፋተኛ እንደሆነ ለማረጋገጥ ጉዳዩ በፍርድ ቤት ሲታይ ዓመታት ይፈጅ የለምን?
የይሖዋን አጽናፈ ዓለማዊ ሉዓላዊነትና የሰዎችን የአቋም ጽናት በተመለከተ በይሖዋም ሆነ በሰው ልጆች ፊት ከተደቀኑት ጥያቄዎች አስፈላጊነት አንጻር ሲታይ አምላክ በቂ ጊዜ እንዲያልፍ መፍቀዱ ምንኛ ጥበብ ነው! ሰዎች የአምላክን ሕጎች ችላ ሲሉና ራሳቸውን በራሳቸው መምራት ሲጀምሩ ውጤቱ ምን እንደሚሆን በግልጽ ተመልክተናል። በዚህም ምክንያት ክፋት በእጅጉ ተስፋፍቷል። በዛሬው ጊዜ ንጹሐን ሰዎች መከራ የሚደርስባቸውም ለዚህ ነው።
ደስ የሚለው ግን ክፋት ለዘላለም እንደማይቀጥል የአምላክ ቃል ይናገራል። እንዲያውም ይሖዋ በቅርቡ ክፋትንና የክፋት ምንጭ የሆኑትን ያስወግዳቸዋል። ምሳሌ 2:22 “ኀጥአን ግን ከምድር ይጠፋሉ፣ ዓመፀኞችም ከእርስዋ ይነጠቃሉ” ይላል። በአንጻሩ ግን ለአምላክ ታማኝ የሆኑ ሰዎች በአሁኑ ጊዜ በደጅ ቀርቦ ያለውን ‘ሞት፣ ኀዘን፣ ጩኸትና ሥቃይ የማይኖርበትን’ ጊዜ በጉጉት ሊጠባበቁ ይችላሉ።—ራእይ 21:4
ስለዚህ ንጹሐን ሰዎች ለምን መከራ እንደሚደርስባቸው መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ያብራራል። በተጨማሪም ክፋትና መከራ በቅርቡ እንደሚወገዱ ማረጋገጫ ይሰጠናል። ሆኖም አሁን ካለው የሕይወት ውጣ ውረድ ጋር በምንታገልበት ጊዜ ለአንድ ሌላ አንገብጋቢ ጥያቄ መልስ ማግኘት እንፈልጋለን።
የሕይወት ዓላማ ምንድን ነው?
በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ከምንጊዜውም ይበልጥ ዛሬ ሰዎች የሕይወትን ዓላማ ለማወቅ በመጣር ላይ ናቸው። ብዙዎች ‘የእኔ መኖር ትርጉሙ ምንድን ነው? ሕይወቴ ትርጉም ያለው ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው?’ እያሉ ይጠይቃሉ። እንዲህ ብለው እንዲጠይቁ የሚያደርጓቸው በርካታ ምክንያቶች አሉ።
አንድ ግለሰብ በሚያጋጥመው አደጋ ሕይወቱ ድንገት ሊቀጭ ይችላል። ለምሳሌ ያህል በ1998 መጀመሪያ አካባቢ በጀርመን ባቫሪያ የምትኖር አንዲት የ12 ዓመት ልጃገረድ ታፍና ከተወሰደች በኋላ ተገደለች። የልጅቷ እናት ከዚያ በኋላ በነበረው ዓመት ሕይወት ጨርሶ ትርጉም የለሽ ሆኖባት እንደነበር ተናግራለች። አንዳንድ ወጣቶች የሕይወት ትርጉም ምንድን ነው የሚለው ጉዳይ በጣም ያሳስባቸዋል። የተረጋጋና አስተማማኝ ሕይወት መምራት እንዲሁም በሕይወታቸው እርካታና እውነተኛ ወዳጅ ማግኘት ይፈልጋሉ። ይሁንና በዚህ ግብዝነት በተስፋፋበትና ጥሩ ሥነ ምግባር በጠፋበት ዓለም ውስጥ ይህ የማይታሰብ ነገር ነው። ሌሎች ግለሰቦች ደግሞ መላ ሕይወታቸውን በአንድ ዓይነት ሙያ እንዲጠመድ ያደርጋሉ። ይሁን እንጂ ሥልጣን፣ ክብርና ሀብት ስለ ሕይወት ትርጉም ለማወቅ ያላቸውን ከፍተኛ ጉጉት ሳያረካላቸው ይቀራል።
አንድ ሰው ስለ ሕይወት ዓላማ እንዲጠይቅ የሚያነሳሳው ምክንያት ምንም ይሁን ምን ይህ ጥያቄ ትክክለኛና አርኪ መልስ የሚያሻው ነው። በዚህ ረገድም ቢሆን መጽሐፍ ቅዱስ ከፍተኛ እርዳታ ሊያበረክት ይችላል። ይሖዋ ለሚያደርገው ለእያንዳንዱ ነገር በቂ ምክንያት ያለው የዓላማ አምላክ መሆኑን ይገልጻል። ምንም ምክንያት ሳይኖርህ እንዲያው ዝም ብለህ ቤት መሥራት ትጀምራለህን? ቤት መሥራት ብዙ ወጪ የሚጠይቅ ከመሆኑም በላይ ወራት ምናልባትም ዓመታት ሊፈጅ የሚችል በመሆኑ እንዲህ እንደማታደርግ የታወቀ ነው። ቤት የምትሠራው አንተ ራስህ ልትኖርበት አሊያም ሌላ ሰው እንዲኖርበት ነው። ይህ ምክንያታዊ መደምደሚያ ለይሖዋም ሊሠራ ይችላል። ምክንያት ወይም ዓላማ ባይኖረው ኖሮ ምድርንም ሆነ በምድር ላይ ያሉትን ነገሮች አይፈጥርም ነበር። (ከዕብራውያን 3:4 ጋር አወዳድር።) ለምድር ያለው ዓላማ ምንድን ነው?
የኢሳይያስ ትንቢት ይሖዋ ‘ምድርን የሠራና ያደረገ እውነተኛው አምላክ’ እንደሆነ ይገልጻል። በእርግጥም ‘ለከንቱ ሳይሆን መኖሪያ እንድትሆን ምድርን ያጸናት እርሱ ነው።’ (ኢሳይያስ 45:18) አዎን፣ ምድር ከተፈጠረችበት ጊዜ ጀምሮ ይሖዋ ለምድር ያለው ዓላማ መኖሪያ እንድትሆን ነው። መዝሙር 115:16 “የሰማያት ሰማይ ለእግዚአብሔር ነው፤ ምድርን ግን ለሰው ልጆች ሰጣት” ይላል። ስለሆነም ይሖዋ ምድርን የፈጠራት በሚንከባከቧት ታዛዥ ሰዎች እንድትሞላ መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጻል።—ዘፍጥረት 1:27, 28
የአዳምና የሔዋን ማመፅ ይሖዋ ዓላማውን እንዲለውጥ አድርጎታልን? በፍጹም። እንዴት እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን? ይህን ነጥብ ልብ በል:- መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈው በኤደን ዓመፅ ከተፈጸመ በሺ ከሚቆጠሩ ዓመታት በኋላ ነው። አምላክ የመጀመሪያ ዓላማውን ትቶት ቢሆን ኖሮ ለምን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አይጠቀስም ነበር? ስለዚህ ግልጽ የሆነው መደምደሚያ አምላክ ምድርንም ሆነ የሰው ልጆችን በተመለከተ ያለው ዓላማ አልተለወጠም።
ከዚህም በላይ ደግሞ የይሖዋ ዓላማ በፍጹም ሳይፈጸም አይቀርም። አምላክ በነቢዩ ኢሳይያስ አማካኝነት የሚከተለውን ዋስትና ይሰጠናል:- “ዝናብና በረዶ ከሰማይ እንደሚወርድ፣ ምድርን እንደሚያረካት፣ ታበቅልና ታፈራም ዘንድ እንደሚያደርጋት፣ ዘርንም ለሚዘራ እንጀራንም ለሚበላ እንደሚሰጥ እንጂ ወደ ሰማይ እንደማይመለስ፣ ከአፌ የሚወጣ ቃሌ እንዲሁ ይሆናል፤ የምሻውን ያደርጋል የላክሁትንም ይፈጽማል እንጂ ወደ እኔ በከንቱ አይመለስም።”—ኢሳይያስ 55:10, 11
አምላክ የሚፈልግብን ነገር
ስለዚህ ምድር ታዛዥ በሆኑ ሰዎች እንድትሞላ አምላክ ያለው ዓላማ እንደሚፈጸም ትምክህት ሊኖረን ይችላል። በምድር ላይ ለዘላለም የመኖር መብት ከሚሰጣቸው ሰዎች መካከል ለመሆን ከፈለግን ጠቢቡ ንጉሥ ሰሎሞን የተናገረውን ማድረግ አለብን። “ይህ የሰው ሁለንተናው ነውና፤ እግዚአብሔርን ፍራ፣ ትእዛዙንም ጠብቅ።”—መክብብ 12:13፤ ዮሐንስ 17:3
ይሖዋ ለሰው ዘር ካለው ዓላማ ጋር በሚስማማ መንገድ መኖር ማለት እውነተኛውን አምላክ ማወቅና በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ሰፍረው ከሚገኙት መስፈርቶች ጋር መስማማት ማለት ነው። በአሁኑ ጊዜ እንዲህ ካደረግን ገነት በሆነች ምድር ላይ የዘላለም ሕይወት የማግኘት ተስፋ ሊኖረን ይችላል። በዚያም ስለ አምላክና አስደናቂ ስለሆኑት የፍጥረት ሥራዎቹ በየጊዜው አዳዲስ ነገር እየተማርን እንቀጥላለን። (ሉቃስ 23:43) እንዴት የሚያስደስት ተስፋ ነው!
የሕይወትን ዓላማ ለማወቅ የሚፈልጉ ብዙ ሰዎች ወደ መጽሐፍ ቅዱስ ዞር በማለታቸው በአሁኑ ጊዜም ከፍተኛ ደስታ አግኝተዋል። ለምሳሌ ያህል አልፍሬት የተባለው ወጣት የሕይወት ትርጉም ጠፍቶበት ነበር። ሃይማኖት በጦርነት ውስጥ የሚያደርገው ጣልቃ ገብነት እጅግ አንገሸገሸው፤ እንዲሁም በፖለቲካ ውስጥ የሚታየው ግብዝነትና የሥነ ምግባር ብልግና ያናድደው ነበር። አልፍሬት ስለ ሕይወት ዓላማ የማወቅ አጋጣሚ ባገኝ ብሎ ተስፋ በማድረግ ወደ ሰሜን አሜሪካ ሕንዳውያን ዘንድ ሄዶ ነበር። ሆኖም ያሰበው ሳይሳካለት ወደ አውሮፓ ተመለሰ። ከዚያም ተስፋ ቆርጦ አደገኛ ዕፆችን ወደ መውሰድና መረን የለቀቀ ሙዚቃ ወደ ማዳመጥ ዘወር አለ። ይሁን እንጂ በመጨረሻ መጽሐፍ ቅዱስን ዘወትር በጥንቃቄ መመርመሩ ትክክለኛው የሕይወት ዓላማ ምን እንደሆነ እንዲገነዘብና ደስታ እንዲያገኝ ረዳው።
ለመንገዳችን አስተማማኝ የሆነ ብርሃን
ታዲያ አሁን ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ምን ብለን መደምደም እንችላለን? ለጊዜያችን አስፈላጊ ነውን? ወቅታዊ ለሆኑ ጉዳዮች መመሪያ ስለሚሰጥ በእርግጥም አስፈላጊ ነው። ክፋት አምላክ ያመጣው ነገር አለመሆኑን የሚያብራራ ከመሆኑም በላይ ሕይወታችን ትርጉም ያለው እንዲሆንልን በማድረግ እርካታ እንድናገኝ ይረዳናል። ከዚህም በተጨማሪ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሌሎች አንገብጋቢ ጉዳዮች ብዙ የሚናገረው ነገር አለው። ስለ ትዳር፣ ልጆችን ስለማሳደግ፣ በሰዎች መካከል ስለሚኖር ግንኙነትና ሙታን ስላላቸው ተስፋ በአምላክ ቃል ውስጥ ተብራርቷል።
እስከ አሁን አላደረግክ ከሆነ እባክህ መጽሐፍ ቅዱስን ቀረብ ብለህ መርምረው። ሕይወትን በተመለከተ የሚሰጣቸው መመሪያዎች ምን ያህል ጠቃሚ እንደሆኑ አንዴ ከተገነዘብክ ከይሖዋ አምላክ መመሪያ ይጠይቅ እንደነበረውና “ሕግህ ለእግሬ መብራት፣ ለመንገዴ ብርሃን ነው” ብሎ እንደዘመረው መዝሙራዊ ሊሰማህ ይችላል።—መዝሙር 119:105
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አምላክ ንጹሐን ሰዎች መከራ እንዲደርስባቸው የሚፈቅደው ለምን እንደሆነ ታውቃለህ?
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሕይወትህ ትርጉም ያለው ሊሆንልህ ይችላል