“ይሖዋ ጥበብን ይሰጣል”
ጊዜህንና ጉልበትህን የሚያሟጥጥብህ ሥራ የትኛው ነው? ለራስህ ጥሩ ስም ማትረፍ ትልቅ ቦታ የምትሰጠው ጉዳይ ነውን? መላ ሕይወትህ ያተኮረው ሀብት በማካበት ላይ ነውን? ከፍተኛ ጥረት በሚጠይቅ አንድ ዓይነት የሥራ መስክ መሰማራትን በሚመለከትስ? ወይም በአንድ ወይም ከዚያ በላይ በሆኑ የትምህርት መስኮች ኤክስፐርት ለመሆን መጣር ነውን? ከሌሎች ጋር ጥሩ ወዳጅነት መመሥረት ትልቅ ቦታ የምትሰጠው ነገር ነውን? በጣም የሚያሳስብህ ጥሩ ጤና አግኝቶ የመኖር ጉዳይ ነውን?
ከላይ የተዘረዘሩት ሁሉ አስፈላጊ ነገሮች ሊመስሉ ይችላሉ። ይሁን እንጂ የመጀመሪያውን ቦታ የሚይዘው የትኛው ነው? መጽሐፍ ቅዱስ “ጥበብ ዓይነተኛ ነገር ናትና ጥበብን አግኝ” በማለት መልሱን ይሰጠናል። (ምሳሌ 4:7) ታዲያ ጥበብን እንዴት ማግኘት እንችላለን? ምን ጥቅሞችንስ ያስገኝልናል? የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነው የምሳሌ መጽሐፍ ሁለተኛ ምዕራፍ መልሱን ይሰጠናል።
‘ጥበብን አድምጥ’
በጥንቷ እስራኤል ይኖር የነበረው ጠቢቡ ንጉሥ ሰሎሞን የሚከተለውን በፍቅር ላይ የተመሠረተ አባታዊ ቃላት ሰንዝሯል:- “ልጄ ሆይ፣ ቃሌን ብትቀበል፣ ትእዛዜንም በአንተ ዘንድ ሸሽገህ ብትይዛት፣ ጆሮህ ጥበብን እንዲያደምጥ ታደርጋለህ፣ ልብህንም ወደ ማስተዋል ታዘነብላለህ። ረቂቅ እውቀትን ብትጠራት፣ ለማስተዋልም ድምፅህን ብታነሣ፣ እርስዋንም እንደ ብር ብትፈላልጋት፣ እርስዋንም እንደ ተቀበረ ገንዘብ ብትሻት፤ የዚያን ጊዜ እግዚአብሔርን መፍራት ታውቃለህ፣ የአምላክንም እውቀት ታገኛለህ።”—ምሳሌ 2:1-5
ጥበብን በማግኘት ረገድ ኃላፊነቱ የወደቀው በማን ላይ እንደሆነ ትመለከታለህ? በእነዚህ ቁጥሮች ውስጥ ‘እንዲህ ብታደርግ’ የሚሉ አባባሎች ሰፍረው እናገኛለን። በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ጥበብንም ሆነ ከጥበብ ጋር ተዛምዶ ያላቸውን ማስተዋልንና እውቀትን ለማግኘት መጣጣር የሚኖርብን እኛው ነን። በመጀመሪያ ግን በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ የሚገኙትን የጥበብ ቃላት ‘ተቀብለን’ በአእምሯችን ውስጥ ‘መሸሸግ’ አለብን። ለዚህም መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ይኖርብናል።
ጥበብ ከአምላክ ያገኘነውን እውቀት ተገቢ በሆነ መንገድ የመጠቀም ችሎታ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ጥበብን ግሩም በሆነ መንገድ ይገልጽልናል። አዎን፣ የጥበብ ቃላት ምሳሌን እና መክብብን በመሰሉ መጻሕፍት ውስጥ ሰፍረው ይገኛሉ። እኛም እነዚህን ቃላት በትኩረት መከታተል ይኖርብናል። በተጨማሪም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የአምላክን መሠረታዊ ሥርዓቶች በሥራ ላይ ማዋል ያለውን ዋጋማነት ጎላ አድርገው የሚያሳዩ በርካታ ምሳሌዎችን እናገኛለን። (ሮሜ 15:4፤ 1 ቆሮንቶስ 10:11) ለምሳሌ ያህል የነቢዩ ኤልሳዕ አገልጋይ ስለነበረው ስለ ስግብግቡ ግያዝ የሚናገረውን ታሪክ ተመልከት። (2 ነገሥት 5:20-27) ይህ ታሪክ ስግብግብ ከመሆን መራቅ ጥበብ መሆኑን አያስተምረንም? መጀመሪያ ላይ ምንም ዓይነት ጉዳት የሚያመጣ የማይመስለውን የያዕቆብ ሴት ልጅ ዲና የከነዓን “አገር ሴቶች ልጆች”ን ለማየት መሄዷ ያስከተለው አሳዛኝ ውጤትስ? (ዘፍጥረት 34:1-31) መጥፎ ጓደኝነት የሚያስከትለውን ጉዳት ከወዲሁ እንድንገነዘብ አያደርገንም?—ምሳሌ 13:20፤ 1 ቆሮንቶስ 15:33
ጥበብን በትኩረት ለመከታተል ማስተዋልና እውቀት መቅሰም ይኖርብናል። ዌብስተርስ ሪቫይዝድ አንብሪጅድ ዲክሽነሪ እንደሚለው ማስተዋል “አንድን ነገር ከሌላው ለመለየት የሚያስችል የአእምሮ ኃይል ወይም ችሎታ ነው።” አምላካዊ ማስተዋል ትክክል የሆነውን ነገርና ስህተት የሆነውን ነገር ለይቶ የማወቅና ከዚያም ትክክለኛውን ጎዳና የመምረጥ ችሎታ ነው። ‘ልባችንን ወደ ማስተዋል’ ካላዘነበልን ወይም ማስተዋልን ለመቅሰም ጉጉቱ ከሌለን ‘ወደ ሕይወት በሚወስደው መንገድ’ ላይ መጓዛችንን እንዴት ልንቀጥል እንችላለን? (ማቴዎስ 7:14፤ ከዘዳግም 30:19, 20 ጋር አወዳድር።) የአምላክን ቃል ማጥናትና በሥራ ላይ ማዋል ማስተዋልን ያስገኛል።
አንድ ትምህርት በውስጡ የያዛቸው ዘርፎች እርስ በርሳቸውና ከዋናው ትምህርት ጋር ያላቸውን ተዛማጅነት ለማየት የሚያስችል ‘እውቀት መጥራት’ የምንችለው እንዴት ነው? እርግጥ ነው፣ በዕድሜና በተሞክሮ ከፍተኛ እውቀት ማግኘት የሚቻል ቢሆንም ሁልጊዜ ግን በዚህ መንገድ ማግኘት ይቻላል ማለት አይደለም። (ኢዮብ 12:12፤ 32:6-12) “ትእዛዝህን ፈልጌአለሁና ከሽማግሌዎች ይልቅ አስተዋልሁ” በማለት መዝሙራዊው ተናግሯል። ጨምሮም “የቃልህ ፍቺ ያበራል፣ ሕፃናትንም [“ተሞክሮ የሚጎድላቸውንም፣” NW] አስተዋዮች ያደርጋል” በማለት ተናግሯል። (መዝሙር 119:100, 130) ይሖዋ ‘በዘመናት የሸመገለ’ ከመሆኑም በላይ ከሁሉም የሰው ዘር የሚበልጥ እውቀት አለው። (ዳንኤል 7:13) አምላክ ተሞክሮ ለሚጎድለው ሰው እውቀትን በመስጠት በዕድሜ ከሚበልጡት ሰዎች የተሻለ እንዲሆን ሊያደርገው ይችላል። ስለዚህ የአምላክን ቃል መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናትና በሥራ ላይ ለማዋል ትጉዎች መሆን ይኖርብናል።
የምሳሌ መጽሐፍ ሁለተኛ ምዕራፍ “ብትቀበል፣” “ብትይዛት፣” “ብትጠራት፣” “ብትፈላልጋት፣” “ብትሻት” በሚሉ አገላለጾች ምንባቡን ይጀምራል። ጸሐፊው እነዚህን አባባሎች በመድገም ጠበቅ አድርጎ ሊገልጽ የፈለገው ነገር ምንድን ነው? አንድ የማመሳከሪያ መጽሐፍ እንዲህ ይላል:- “እዚህ ላይ ብልሁ ሰው ጥበብን በጥብቅ የመፈለግን አስፈላጊነት ጎላ አድርጎ ገልጿል።” አዎን፣ ጥበብንና የእርሱ ተዛማጅ ባሕርይ የሆኑትን ማስተዋልንና እውቀትን በትጋት መከታተል ይገባናል።
አስፈላጊውን ጥረት ታደርጋለህን?
ትጋት የተሞላበት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ጥበብን በመፈለግ ረገድ ትልቅ ሚና ይጫወታል። ሆኖም ይህ ዓይነቱ ጥናት መረጃ ለማግኘት ብቻ ተብሎ ከሚደረገው ንባብ የላቀ መሆን ይኖርበታል። ባነበብነው ነገር ላይ በዓላማ ማሰላሰል ቅዱሳን ጽሑፎችን ለማጥናት የግድ አስፈላጊ የሆነ ክፍል ነው። ጥበብንና ማስተዋልን ማግኘት ማለት ችግሮችን ለመፍታትና ውሳኔ ለማድረግ የተማርናቸውን ነገሮች እንዴት ልንሠራባቸው እንደምንችል ማሰላሰልን ይጠይቃል። እውቀትን መቅሰም፣ ያገኘናቸውን አዳዲስ ትምህርቶች ከዚህ ቀደም ከምናውቃቸው ነገሮች ጋር እንዴት እንደሚስማሙ ቆም ብሎ ማሰብን ይጠይቃል። እንዲህ ያለው ጥልቀት የተሞላበት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ጊዜና ብርቱ ጥረት ማድረግን የሚጠይቅ መሆኑን ማን ሊክድ ይችላል? ለዚህ የሚውለው ጊዜና ጉልበት ‘ብርና የተደበቀ ሀብት ለመፈለግ’ ከሚወጣው ጊዜና ጉልበት ጋር የሚመሳሰል ነው። ታዲያ አስፈላጊውን ጥረት ለማድረግ ፈቃደኛ ነህ? ለዚህስ ‘ጊዜ ትዋጃለህ?’—ኤፌሶን 5:15, 16
በቅን ልቦና ተነሳስተን መጽሐፍ ቅዱስን በጥልቀት መቆፈራችን ሊያስገኝልን የሚችለውን ውድ ሀብት አስብ። ‘የአምላክን እውቀት’፤ አዎን፣ ጤናማና ሕይወት ሰጪ የሆነውን የፈጣሪያችንን እውቀት እንድናገኝ ያደርገናል! (ዮሐንስ 17:3) ልናገኝ ከምንችለው ውድ ሀብት መካከል አንዱ ‘ይሖዋን መፍራት’ ነው። እንዲህ ያለው በአክብሮት ላይ የተመሠረተ ፍርሃት ዋጋማነቱ ምንኛ ከፍ ያለ ነው! እርሱን ላለማሳዘን የምናሳየው ጤናማ ፍርሃት እያንዳንዱን የኑሯችንን ዘርፍ የሚመራና በምናደርገው ነገር ሁሉ መንፈሳዊ አድማሳችንን የሚያሰፋ መሆን አለበት።—መክብብ 12:13
መንፈሳዊ ውድ ሀብት ለማግኘት የመቆፈርና የመፈለግ ከፍተኛ ምኞት በውስጣችን መቀጣጠል ይኖርበታል። ይሖዋ ፍለጋችንን ለማቀላጠፍ የሚረዱ ግሩም የሆኑ የቁፋሮ መሣሪያዎችን አቅርቦልናል። እነርሱም ጊዜያቸውን ጠብቀው የሚወጡ የእውነት መጽሔቶች መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! እንዲሁም ሌሎች በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎች ናቸው። (ማቴዎስ 24:45-47) ይሖዋ ቃሉንና መንገዶቹን እንድንማር ክርስቲያናዊ ስብሰባዎችንም አዘጋጅቶልናል። በእነዚህ ስብሰባዎች ላይ አዘውትረን መገኘት፣ የሚሰጡትን ትምህርቶች በጥሞና ማዳመጥ፣ ቁልፍ ነጥቦችን በትኩረት መከታተልና የራሳችን ማድረግ እንዲሁም ከይሖዋ ጋር ስላለን ዝምድና በጥልቀት ማሰብ ይኖርብናል።—ዕብራውያን 10:24, 25
ጥረትህ ከንቱ ሆኖ አይቀርም
ሰዎች የተቀበሩ የከበሩ ድንጋዮችን፣ ወርቅ ወይም ብር ለማግኘት የሚያደርጉት ጥረት ሁሉ መና ሆኖ የሚቀርበት ጊዜ አለ። መንፈሳዊ ውድ ሀብት ለማግኘት በሚደረገው ጥረት ግን እንዲህ ያለ ሁኔታ አያጋጥምም። ለምን? “እግዚአብሔር ጥበብን ይሰጣልና፤ ከአፉም እውቀትና ማስተዋል ይወጣሉ” በማለት ሰሎሞን ማረጋገጫ ይሰጠናል።—ምሳሌ 2:6
ንጉሥ ሰሎሞን ባካበተው ጥበብ በሰፊው የሚታወቅ ነበር። (1 ነገሥት 4:30-32) ዕፅዋትን፣ እንስሳትን፣ ሰብዓዊ አፈጣጠርንና የአምላክን ቃል ጨምሮ ስለ ተለያዩ ጉዳዮች እውቀት እንደነበረው ቅዱሳን ጽሑፎች ያሳያሉ። ገና ወጣት ንጉሥ ሳለ ሁለት ሴቶች የእኔ ነው የእኔ ነው በሚል በአንድ ሕፃን በተጣሉበት ጊዜ ጉዳዩ ለመፍታት የተጠቀመበት ማስተዋል ዓለም አቀፍ እውቅና እንዲያገኝ አስችሎታል። (1 ነገሥት 3:16-28) ይህን ሁሉ ከፍተኛ እውቀት ያገኘው ከየት ነው? ሰሎሞን “ጥበብና እውቀት” እንዲሁም “መልካሙንና ክፉውን” የመለየት ችሎታ እንዲሰጠው ይሖዋን በጸሎት ጠይቆ ነበር። ይሖዋም የለመነውን ሰጥቶታል።—2 ዜና መዋዕል 1:10-12፤ 1 ነገሥት 3:9
እኛም ቃሉን በትጋት ስናጠና ይሖዋ እንዲረዳን መጸለይ ይኖርብናል። መዝሙራዊው “አቤቱ፣ መንገድህን ምራኝ፣ በእውነትህም እሄዳለሁ፤ ስምህን ለመፍራት ልቤ ደስ ይለዋል [“ልቤን አንድ አድርግልኝ፣” NW]” በማለት ጸልዮአል። (መዝሙር 86:11) ይሖዋ ይህን ጸሎት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንዲመዘገብ ማድረጉ ጸሎቱን መቀበሉን የሚያሳይ ነው። እኛም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙትን መንፈሳዊ ውድ ሀብቶች ለማግኘት ስንል የምናቀርበው ተደጋጋሚና ትጋት የተሞላበት ጸሎት መልስ ሳያገኝ እንደማይቀር ትምክህት ሊኖረን ይችላል።—ሉቃስ 18:1-8
ሰሎሞን እንዲህ በማለት ገልጿል:- “እርሱ ለቅኖች ደኅንነትን ያከማቻል፤ ያለ ነውር ለሚሄዱትም ጋሻ ነው፤ የፍርድን ጎዳና ይጠብቃል፤ የቅዱሳኑንም መንገድ ያጸናል። የዚያን ጊዜ ጽድቅንና ፍርድን ቅንነትንና መልካም መንገድን ሁሉ ታስተውላለህ።” (ምሳሌ 2:7-9) እነዚህ እንዴት ያሉ የማረጋገጫ ቃላት ናቸው! ይሖዋ በቅን ልቦና ተነሳስተው ጥበብን ለማግኘት ለሚፈልጉ ቅን ሰዎች ጥበብ ከመስጠቱም በላይ ካወጣው የጽድቅ የአቋም ደረጃ ጋር ተስማምተው ለመኖር እውነተኛ ጥበብና ታማኝነት ስለሚያሳዩ መከላከያ ጋሻም ይሆንላቸዋል። ይሖዋ “መልካም መንገድን ሁሉ” እንዲያስተውሉ ከሚረዳቸው ሰዎች መካከል ያድርገን።
‘ደስ የሚያሰኝ እውቀት’
ጥበብን ለማግኘት የግድ አስፈላጊ የሆነው የግል የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለብዙ ሰዎች አስደሳች ሥራ አይደለም። ለምሳሌ ያህል ሎውሬንስ የተባለ አንድ የ58 ዓመት ሰው እንዲህ በማለት ተናግሯል:- “ወዲያ ወዲህ እያልኩ መሥራት ስለለመድኩ ቁጭ ብሎ አርፎ ማጥናት ለእኔ አስቸጋሪ ነው።” ተማሪ በነበረበት ወቅት ማጥናት የማይወደው ማይክል የተባለ አንድ የ24 ዓመት ወጣት “ቁጭ ብዬ ለማጥናት ራሴን ማስገደድ ነበረብኝ” ብሏል። ሆኖም ለጥናት ፍላጎት ማዳበር ይቻላል።
ማይክል ያደረገውን ነገር ተመልከት። እንዲህ ይላል:- “ራሴን እየገሠጽሁ በየቀኑ ለግማሽ ሰዓት ለማጥናት ወሰንኩ። ወዲያውም በዝንባሌዬ፣ ክርስቲያን ጉባኤ ላይ በምሰጠው ሐሳብና ከሌሎች ጋር በማደርገው ጭውውት በራሴ ላይ ለውጥ መመልከት ጀመርኩ። አሁን የማጠናበትን ሰዓት በጉጉት የምጠባበቅ ሲሆን ምንም ነገር እንዲያስተጓጉልብኝም አልፈቅድም።” አዎን፣ የምናደርገውን እድገት እየተመለከትን ስንሄድ የግል ጥናት አስደሳች ይሆንልናል። ሎውሬንስም የግል ጥናት ማድረግን ሥራዬ ብሎ በመያዙ ከጊዜ በኋላ በይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ ውስጥ ሽማግሌ ሆኖ ለማገልገል በቅቷል።
ከግል ጥናት አስደሳች ተሞክሮ ለማግኘት ያልተቋረጠ ጥረት ማድረግ ይጠይቃል። የሚያስገኘው ጥቅምም ቢሆን ከፍተኛ ነው። “ጥበብ ወደ ልብህ ትገባለችና፣ እውቀትም ነፍስህን ደስ ታሰኛለችና፤ ጥንቃቄ ይጠብቅሃል፣ ማስተዋልም ይጋርድሃል።”—ምሳሌ 2:10, 11
“ከክፉ ነገር አንተን ለማዳን”
ጥበብ፣ እውቀት፣ የማሰብ ችሎታና ማስተዋል ጥበቃ ሊሆን የሚችለው በምን መንገድ ነው? ሰሎሞን እንዲህ በማለት ተናግሯል:- “ከክፉ መንገድ አንተን ለማዳን፣ ጠማማ ነገርን ከሚናገሩም ሰዎች፤ እነርሱም በጨለማ መንገድ ይሄዱ ዘንድ የቀናውን ጎዳና የሚተዉ፣ ክፉ በመሥራት ደስ የሚላቸው በጠማማነትም ደስታን የሚያደርጉ፣ መንገዳቸውን የሚጠመዝዙ አካሄዳቸውንም የሚያጣምሙ ናቸው።”—ምሳሌ 2:12-15
አዎን፣ እውነተኛ ጥበብን ከፍ አድርገው የሚመለከቱ ‘ጠማማ ነገርን ከሚናገሩ’ ማለትም እውነትንና ትክክል የሆኑ ነገሮችን ከሚቃረኑ ሰዎች ይርቃሉ። የማሰብ ችሎታና ማስተዋል በጨለማ ጎዳና ለመጓዝ ሲሉ እውነትን ከናቁ እንዲሁም በጠማማና በክፉ ሥራ ከሚደሰቱ ሰዎች ይጠብቀናል።—ምሳሌ 3:32
በተጨማሪም እውነተኛ ጥበብና የእርሱ ተዛማጅ የሆኑት ባሕርያት ሥነ ምግባር የጎደላቸው ወንዶችና ሴቶች ከሚከተሉት መጥፎ አካሄድ የሚጠብቁን በመሆናቸው ምንኛ አመስጋኞች ነን! ሰሎሞን ከእነዚህ ባሕርያት የምናገኘውን ጥቅም ሲናገር እንዲህ ብሏል:- “ከጋለሞታ [“ከእንግዳ፣” NW] ሴት አንተን ለመታደግ፣ ቃልዋን ከምታለዝብ ከሌላዪቱም ሴት፤ የሕፃንነት ወዳጅዋን የምትተው የአምላክዋንም ቃል ኪዳን የምትረሳ፤ ቤትዋ ወደ ሞት ያዘነበለ ነው፣ አካሄድዋም ወደ ሙታን ጥላ። ወደ እርስዋ የሚገቡ ሁሉ አይመለሱም፣ የሕይወትንም ጎዳና አያገኙም።”—ምሳሌ 2:16-19
‘ጋለሞታይቱ [“እንግዳዋ፣” NW] ሴት’ በልጅነቷ ያገባችውን ባሏን ሳይሆን አይቀርም “የሕፃንነት ወዳጅዋን” እንደተወች ተደርጋ ተገልጻለች።a (ከሚልክያስ 2:14 ጋር አወዳድር።) ምንዝር መፈጸም የሚከለክለውን በሕጉ ቃል ኪዳን ውስጥ ተካቶ የሚገኘውን ሕግ ረስታለች። (ዘጸአት 20:14) መንገዷ ወደ ሞት የሚያደርስ ነው። ከእርሷ ጋር ወዳጅነት የመሠረቱ ሁሉ ፈጥኖም ይሁን ዘግይቶ ተመልሰው ሊወጡ ወደማይችሉበት ቃል በቃል መመለስ ወደማይችሉበት ወደ ሞት አፋፍ ስለሚሄዱ “የሕይወትንም ጎዳና አያገኙም።” ማስተዋልና የማሰብ ችሎታ ያለው ሰው ወደ ፆታ ብልግና የሚመሩ ነገሮችን ጠንቅቆ የሚያውቅ ሲሆን በዚህ ዓይነቱ ወጥመድ ውስጥ ላለመያዝ በጥበብ ይርቃል።
‘ቅኖች በምድር ላይ ይኖራሉ’
ሰሎሞን ጥበብን በተመለከተ የሰጠውን ምክር ሲያጠቃልል “አንተም በደጋግ ሰዎች መንገድ እንድትሄድ የጻድቃንንም ጎዳና እንድትጠብቅ” በማለት ተናግሯል። (ምሳሌ 2:20) ጥበብ እንዴት ግሩም የሆነ ዓላማ ያከናውናል! በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያለው ደስተኛና አርኪ የሆነ ሕይወት እንድንመራ ይረዳናል።
በተጨማሪም ‘በደጋግ ሰዎች መንገድ የሚሄዱ’ ሁሉ ወደፊት የሚጠብቃቸውን ታላላቅ በረከቶች አስብ። “ቅኖች በምድር ላይ ይቀመጣሉና፣ ፍጹማንም በእርስዋ ይኖራሉና፤ ኀጥአን ግን ከምድር ይጠፋሉ፣ ዓመፀኞችም ከእርስዋ ይነጠቃሉ።” (ምሳሌ 2:21, 22) ጽድቅ በሰፈነበት በአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ ለዘላለም ከሚኖሩት ቅን ሰዎች መካከል ያድርጋችሁ።—2 ጴጥሮስ 3:13
[የግርጌ ማስታወሻ]
a “እንግዳ” [NW] የሚለው ቃል የሚያመለክተው ከሕጉ ጋር የሚስማማ ነገር ከማድረግ ዘወር በማለታቸው ከይሖዋ የራቁ ሴቶችን ነው። ስለዚህ ጋለሞታይቱ የሌላ አገር ሴት ባትሆንም “እንግዳ” [NW] ተብላ ተጠርታለች።
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሰሎሞን ጥበብ ለማግኘት ጸልዮአል። እኛም መጸለይ ይኖርብናል