የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w00 2/15 ገጽ 20-25
  • እንደ ኢየሱስ ለማድረግ ትገፋፋለህን?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • እንደ ኢየሱስ ለማድረግ ትገፋፋለህን?
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2000
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • የጎደላቸውን መንፈሳዊ ምግብ ለማሟላት መገፋፋት
  • ሌሎችም እንዲመሰክሩ አበረታቷል
  • ዛሬም የክርስቶስን አስተሳሰብ አዳብሩ
  • “በጣም አዘነላቸው”
    “ተከታዬ ሁን”
  • ‘የክርስቶስን ፍቅር ማወቅ’
    ወደ ይሖዋ ቅረብ
  • ይሖዋ የሚገዛው በርኅራኄ ነው
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1997
  • እንደ ይሖዋ ሩኅሩኅ ሁኑ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2017
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2000
w00 2/15 ገጽ 20-25

እንደ ኢየሱስ ለማድረግ ትገፋፋለህን?

“ብዙ ሕዝብ አየና እረኛ እንደሌላቸው በጎች ስለ ነበሩ አዘነላቸው፣ ብዙም ነገር ያስተምራቸው ጀመር።”​—⁠ማርቆስ 6:​34

1. ሰዎች የሚደነቁ ባሕርያትን ማንጸባረቅ መቻላቸው ብዙም ሊያስገርመን የማይገባው ለምንድን ነው?

በታሪክ ዘመናት ሁሉ በርካታ ሰዎች ድንቅ ባሕርያትን አንጸባርቀዋል። ይህ የሆነው ለምን እንደሆነ ሊገባህ ይችላል። ይሖዋ አምላክ እንደ ፍቅር፣ ደግነት፣ ለጋስነትና ሌሎች ከፍተኛ ግምት የምንሰጣቸው ባሕርያት ያሉት ሲሆን እነዚህንም ባሕርያት አሳይቷል። ሰዎች የተፈጠሩት በአምላክ አምሳል ነው። ስለዚህ ብዙ ሰዎች በተወሰነ ደረጃ ፍቅርን፣ ደግነትን፣ ርኅራኄንና ሌሎች መለኮታዊ ባሕርያትን ለምን እንደሚያሳዩ በቀላሉ ሊገባን ይችላል። እንዲያውም ብዙዎች በሕሊናቸው በመመራት ብቻ እነዚህን ባሕርያት ያሳያሉ። (ዘፍጥረት 1:​26፤ ሮሜ 2:​14, 15) ሆኖም አንዳንዶች እነዚህን ባሕርያት ከሌሎች በተሻለ መንገድ እንደሚያንጸባርቁ ተገንዝበህ ሊሆን ይችላል።

2. ሰዎች የክርስቶስን አርዓያ እየኮረጁ እንዳሉ በማሰብ የሚያከናውኗቸው አንዳንድ በጎ ተግባራት ምንድን ናቸው?

2 የታመሙ ሰዎችን የሚጠይቁ ወይም የሚያስታምሙ፣ ለአካል ጉዳተኞች የበጎ አድራጎት ተግባር የሚያከናውኑ ወይም ድሆችን የሚረዱ ሰዎችን ታውቅ ይሆናል። በተጨማሪም ውስጣዊ የርኅራኄ ስሜት ገፋፍቷቸው መላ ሕይወታቸውን ለሥጋ ደዌ በሽተኞች ወይም ለሙት ልጆች እንክብካቤ በሚደረግበት ቦታ ያሳለፉ በሐኪም ቤት ወይም በሌሎች የሕክምና ተቋማት በፈቃደኝነት የሚሠሩ ወይም መኖሪያ ቤት የሌላቸውን ወይም ስደተኞችን ለመርዳት ደፋ ቀና የሚሉ ሰዎችንም አስብ። ከእነዚህ ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ ለክርስቲያኖች ምሳሌ የተወውን ኢየሱስን እየኮረጁ እንዳሉ ይሰማቸው ይሆናል። ክርስቶስ የታመሙትን እንደፈወሰና የተራቡትን እንደመገበ በወንጌሎች ውስጥ እናነባለን። (ማርቆስ 1:​34፤ 8:​1-9፤ ሉቃስ 4:​40) ኢየሱስ ያሳየው የፍቅር፣ የርኅራኄና የአዘኔታ ስሜት “የክርስቶስ አስተሳሰብ” ነጸብራቅ ሲሆን እርሱም የሰማዩ አባቱን ምሳሌ በመኮረጅ ያገኛቸው ባሕርያት ናቸው።​—⁠1 ቆሮንቶስ 2:​16 NW

3. ኢየሱስ ስላከናወናቸው መልካም ሥራዎች ሚዛናዊ የሆነ አመለካከት ለመያዝ ምን ነገር መመርመር ይኖርብናል?

3 በኢየሱስ ፍቅርና ርኅራኄ ልባቸው የተነካ በዛሬው ጊዜ ያሉ ብዙ ሰዎች የክርስቶስን አስተሳሰብ ዋነኛ ገጽታ የዘነጉ መሆናቸውን አስተውለሃል? ማርቆስ ምዕራፍ 6ን በጥንቃቄ መመርመራችን ይህን ጉዳይ በተመለከተ ጥልቅ ማስተዋል እንድናገኝ ይረዳናል። እዚህም ላይ ኢየሱስ እንዲፈውስላቸው ሕዝቡ የታመሙ ሰዎችን ወደ ኢየሱስ እንዳመጡ እናነባለን። ከዚህም በተጨማሪ ኢየሱስ ከርሱ ጋር የነበሩት በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች በተራቡ ጊዜ በተአምር እንደመገባቸው በጥቅሱ ዙሪያ ካሉት ሐሳቦች መገንዘብ እንችላለን። (ማርቆስ 6:​35-44, 54-56) የታመሙትን መፈወስና የተራቡትን መመገብ አስደናቂ የፍቅራዊ ርኅራኄ መግለጫ ቢሆንም ኢየሱስ ሌሎችን የረዳበት ዋነኛ መንገድ ይህ ነውን? ኢየሱስ ይሖዋን እንደመሰለ ሁሉ እኛም የኢየሱስን ፍጹም የሆነ የፍቅር፣ የደግነትና የርኅራኄ ባሕርይ መኮረጅ የምንችለው እንዴት ነው?

የጎደላቸውን መንፈሳዊ ምግብ ለማሟላት መገፋፋት

4. በ⁠ማርቆስ 6:​30-34 ላይ የሚገኘው ዘገባ መቼት ምን ይመስል ነበር?

4 ኢየሱስ አብረውት ለነበሩት ሰዎች በአንደኛ ደረጃ ያዘነው ለጎደላቸው መንፈሳዊ ምግብ ነበር። እነዚህ ምግቦች ከአካላዊ ምግብ እንኳ ሳይቀር የበለጡ የግድ አስፈላጊ የሆኑ ነገሮች ናቸው። በ⁠ማርቆስ 6:​30-34 ላይ የሚገኘውን ዘገባ ተመልከት። ሁኔታው የተፈጸመው በገሊላ ባሕር ዳርቻ ሲሆን በ32 እዘአ የሚከበረው የማለፍ በዓል ተቃርቦ በነበረበት ወቅት ነበር። ሐዋርያቱ ደስ ብሏቸው የነበረ ሲሆን ለዚህም በቂ ምክንያት ነበራቸው። ረጅም ጉዞ ካደረጉ በኋላ ወደ ኢየሱስ ገና መመለሳቸው ነበር። ያገኟቸውን ተሞክሮዎች ሁሉ ሊነግሩት ጓጉተው እንደነበር ጥርጥር የለውም። ሆኖም ብዙ ሰዎች ተሰበሰቡ። የተሰበሰበው ሕዝብ በጣም ብዙ ስለነበረ ኢየሱስና ሐዋርያቱ መብላትም ሆነ ማረፍ አልቻሉም። ኢየሱስ ለሐዋርያቱ “እናንት ራሳችሁ ብቻችሁን ወደ ምድረ በዳ ኑና ጥቂት ዕረፉ አላቸው።” (ማርቆስ 6:​31) ቦታው ቅፍርናሆም ሳይሆን አይቀርም በአንድ ጀልባ ተሳፈሩና የገሊላን ባሕር አቋርጠው ጸጥ ወዳለ ቦታ መጓዝ ጀመሩ። ይሁን እንጂ ሕዝቡ የባሕሩን ዳርቻ ተከትለው ሮጠው ከጀልባው በፊት ቀድመው ደረሱ። ኢየሱስ ምን ተሰማው? ማረፍ ባለመቻሉ ተበሳጭቶ ይሆን? በፍጹም!

5. ኢየሱስ ወደ እሱ ስለ ተሰበሰበው ሕዝብ ምን ተሰማው? ከዚህስ የተነሳ ምን አደረገ?

5 ኢየሱስ የታመሙትን ጨምሮ በጉጉት ይጠባበቁት የነበሩትን በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች በተመለከተ ጊዜ ልቡ በጣም ተነካ። (ማቴዎስ 14:​14፤ ማርቆስ 6:​44) ከልቡ እንዲያዝን ያደረገው ነገር ምን እንደሆነና ምን እርምጃ እንደወሰደ ማርቆስ እንዲህ በማለት ጽፏል:- “ብዙ ሕዝብ አየና እረኛ እንደሌላቸው በጎች ስለ ነበሩ አዘነላቸው፣ ብዙም ነገር ያስተምራቸው ጀመር።” (ማርቆስ 6:​34) ኢየሱስ ያየው እንዲሁ ዝም ብሎ የተከማቸ ሕዝብ አልነበረም። መንፈሳዊ ነገር የሚያስፈልጋቸውን ግለሰቦች ተመልክቷል። ኢየሱስ ሕዝቡን የተመለከታቸው የለመለመ መስክ ወዳለበት ቦታ የሚያሰማራቸው ወይም ከአደጋ የሚጠብቃቸው እረኛ አጥተው እንደባዘኑ በጎች ነበር። በጎቹን በእንክብካቤ መጠበቅ ይገባቸው የነበሩት ጨካኞቹ የሃይማኖት መሪዎች ተራውን ሕዝብ እንደሚንቁና መንፈሳዊ ፍላጎቶቻቸውን ችላ እንዳሉ ኢየሱስ ተገንዝቧል። (ሕዝቅኤል 34:​2-4፤ ዮሐንስ 7:​47-49) ኢየሱስ አቅሙ የፈቀደለትን ያህል ጥሩ ነገር በማድረግ ሕዝቡን በተለየ መንገድ ለመያዝ አስቧል። ስለ አምላክ መንግሥት ያስተምራቸው ጀመር።

6, 7. (ሀ) በወንጌሎች ዘገባ መሠረት ኢየሱስ ቅድሚያ ሰጥቶ ለሕዝቡ ምን ነገር አደረገ? (ለ) ኢየሱስ እንዲሰብክና እንዲያስተምር ያነሳሳው ውስጣዊ ግፊት ምንድን ነው?

6 በሌላ ተመሳሳይ ዘገባ ውስጥ ያለውን የታሪኩን ቅደም ተከተል እንዲሁም ቅድሚያ ትኩረት የተሰጠው ነገር ምን መሆኑን ልብ በል። ይህን ታሪክ የጻፈው ሐኪምና የሌሎች አካላዊ ጤንነት ያሳስበው የነበረው ሉቃስ ነው። “ሕዝቡም . . . [ኢየሱስን] ተከተሉት፤ ተቀብሎአቸውም ስለ እግዚአብሔር መንግሥት ይነግራቸው ነበር፣ መፈወስ ያስፈለጋቸውንም ፈወሳቸው።” (ሉቃስ 9:​11፣ በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን፤ ቆላስይስ 4:​14) ተዓምር ስለመፈጸሙ የሚናገሩት ዘገባዎች በሙሉ ይህን የመሰለ አቀማመጥ አላቸው ማለት ባይሆንም ሉቃስ በመንፈስ አነሳሽነት ባሰፈረው በዚህኛው ዘገባ ላይ ቅድሚያ የተሰጠው ነገር ምንድን ነው? ኢየሱስ ሕዝቡን ማስተማሩን ነው።

7 ይህም ማርቆስ 6:​34 ላይ ተመዝግቦ በምናገኘው ታሪክ ላይ ጠበቅ ተደርጎ ከተገለጸው ታሪክ ጋር በትክክል የሚስማማ ነው። እዚያ ላይ ኢየሱስን ከልብ እንዲያዝን ያደረገው ነገር ምን እንደሆነ በግልጽ ያሳያል። መንፈሳዊ ፍላጎታቸውን በማስተዋል ሕዝቡን አስተምሯል። ኢየሱስ በአገልግሎቱ መጀመሪያ ላይ “ስለዚህ ተልኬአለሁና ለሌሎቹ ከተማዎች ደግሞ የእግዚአብሔርን መንግሥት ወንጌል እሰብክ ዘንድ ይገባኛል” ብሎ ተናግሯል። (ሉቃስ 4:​43) ሆኖም ኢየሱስ የመንግሥቱን መልእክት ያወጀው የስብከቱን ሥራ እንደ ግዴታ አድርጎ በመቁጠር እንዲያው በዘልማድ ነው ብለን አስበን ከሆነ ተሳስተናል። ምሥራቹን ለሕዝቡ እንዲያካፍል የገፋፋው ቁልፍ ነገር ለሕዝቡ የነበረው ፍቅራዊ ርኅራኄው ነው። ኢየሱስ ለታመሙ፣ በአጋንንት ለተያዙ፣ ለድሆች ወይም ለተራቡ ሰዎች ሳይቀር ሊያደርግ የሚችለው ከሁሉ የላቀ ጥሩ ነገር ስለ አምላክ መንግሥት የሚገልጸውን እውነት እንዲያውቁ፣ እንዲቀበሉና እንዲወዱ መርዳት ነበር። የይሖዋ ሉዓላዊነት የሚረጋገጠውና ለሰው ልጆች ዘላቂ የሆኑ በረከቶች የሚመጡት በዚህ መንግሥት አማካኝነት በመሆኑ ስለዚህ መንግሥት የሚናገረው እውነት በጣም አስፈላጊ ነው።

8. ኢየሱስ ለስብከቱና ለማስተማሩ ሥራ የነበረው ስሜት ምን ነበር?

8 ኢየሱስ ወደ ምድር የመጣበት ዋነኛ ምክንያት መንግሥቱን በቅንዓት መስበክ ነው። ኢየሱስ ምድራዊ ሕይወቱን ሊያጠናቅቅ በተቃረበበት ወቅት ለጲላጦስ እንዲህ አለው:- “እኔ ለእውነት ልመሰክር ስለዚህ ተወልጃለሁ ስለዚህም ወደ ዓለም መጥቻለሁ፤ ከእውነት የሆነ ሁሉ ድምፄን ይሰማል አለው።” (ዮሐንስ 18:​37) ኢየሱስ ከአንጀት የመራራት ስሜት የነበረው ማለትም ለሰዎች የሚያስብ፣ በቀላሉ የሚቀረብ፣ በሌሎች ላይ እምነት የሚጥልና ከሁሉም በላይ ደግሞ አፍቃሪ እንደነበር ቀደም ባሉት ሁለት ርዕሶች ተመልክተናል። የክርስቶስን አስተሳሰብ በትክክል ለመረዳት ከፈለግን እነዚህን የባሕርያቱን ገጽታዎች በሚገባ ማወቅም ይኖርብናል። የክርስቶስ አስተሳሰብ ኢየሱስ በሰበከበትና ባስተማረበት ወቅት ለምን ነገር ቅድሚያ እንደሰጠ ማወቅንም የሚያካትት ነው።

ሌሎችም እንዲመሰክሩ አበረታቷል

9.የስብከቱንና የማስተማሩን ሥራ እነማንም ጭምር ማስቀደም ነበረባቸው?

9 የፍቅርና የርኅራኄ ስሜት መግለጫ ለሆኑት ለስብከቱና ለማስተማሩ ሥራ ቅድሚያ መስጠት ያለበት ኢየሱስ ብቻ አይደለም። ተከታዮቹ የእርሱን ዓይነት ውስጣዊ ግፊት እንዲኖራቸው፣ እርሱ ያስቀደማቸውን ነገሮች እንዲያስቀድሙና ተግባሩን እንዲኮርጁ አጥብቆ አሳስቧቸዋል። ለምሳሌ ያህል ኢየሱስ አሥራ ሁለቱን ሐዋርያት የመረጠው ምን እንዲያደርጉ ነበር? ማርቆስ 3:​14, 15 እንዲህ በማለት ይነግረናል:- “ከእርሱ ጋር እንዲሆኑ፣ ለማስተማርም [“ለመስበክ፣” NW ] እንዲልካቸው ዐሥራ ሁለቱን መርጦ ‘ሐዋርያት’ ብሎ ሰየማቸው። አጋንንትን እንዲያወጡም ሥልጣን ሰጣቸው።” (በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን) ሐዋርያቱ ለየትኛው ሥራ ቅድሚያ መስጠት እንደነበረባቸው አስተዋልክ?

10, 11. (ሀ) ኢየሱስ ሐዋርያቱን በላከ ጊዜ ምን እንዲያደርጉ ነገራቸው? (ለ) ሐዋርያቱ የተላኩበት ዋነኛ ዓላማ ምን ነበር?

10 ከጊዜ በኋላ ኢየሱስ ለአሥራ ሁለቱ የመፈወስና አጋንንትን የማውጣት ሥልጣን ሰጥቷቸዋል። (ማቴዎስ 10:​1፤ ሉቃስ 9:​1) ከዚያም “የእስራኤል ቤት ወደሚሆኑ ወደ ጠፉት በጎች” እንዲሄዱ ላካቸው። ምን እንዲያደርጉ? ኢየሱስ የሚከተለውን መመሪያ ሰጣቸው:- “ሄዳችሁም:- መንግሥተ ሰማያት ቀርባለች ብላችሁ ስበኩ። ድውዮችን ፈውሱ፤ ሙታንን አስነሡ፤ ለምጻሞችን አንጹ፤ አጋንንትን አውጡ።” (ማቴዎስ 10:​5-8፤ ሉቃስ 9:​2) በእርግጥ ያደረጉት ምን ነበር? “ወጥተውም [1] ንስሐ እንዲገቡ ሰበኩ፣ [2] ብዙ አጋንንትንም አወጡ፣ ብዙ ድውዮችንም ዘይት እየቀቡ ፈወሱአቸው።”​—⁠ማርቆስ 6:​12, 13

11 ማስተማር በሁሉም ጥቅሶች ላይ በአንደኛ ደረጃ አለመጠቀሱ እሙን ነው። ታዲያ ቅድሚያ የተሰጠውን ወይም ሥራው የተከናወነበትን ውስጣዊ ግፊት ለማስረዳት ከላይ የተገለጸውን ቅደም ተከተል እንደ ማስረጃ አድርጎ መጥቀስ አጉል መመራመር አይሆንምን? (ሉቃስ 10:​1-8) እንደዚያ ብለህ ታስብ ይሆናል። ነገር ግን ማስተማር ከፈውስ ቀድሞ የተጠቀሰባቸው ቦታዎች ተደጋጋሚ መሆናቸው ልብ ሊባል የሚገባው ነገር ነው። በዚህ ረገድ በጥቅሱ ዙሪያ ያለውን ሐሳብ ተመልከት። ኢየሱስ አሥራ ሁለቱን ሐዋርያት ከመላኩ በፊት በሕዝቡ ሁኔታ ልቡ በጣም ተነክቶ ነበር። እንዲህ እናነባለን:- “ኢየሱስም በምኵራቦቻቸው እያስተማረ፣ የመንግሥትንም ወንጌል እየሰበከ፣ በሕዝብም ያለውን ደዌና ሕማም ሁሉ እየፈወሰ፣ በከተማዎችና በመንደሮች ሁሉ ይዞር ነበር። ብዙ ሕዝብም ባየ ጊዜ፣ እረኛ እንደ ሌላቸው በጎች ተጨንቀው ተጥለውም ነበርና አዘነላቸው። በዚያን ጊዜ ደቀ መዛሙርቱን:- መከሩስ ብዙ ነው፣ ሠራተኞች ግን ጥቂቶች ናቸው፤ እንግዲህ የመከሩን ጌታ ወደ መከሩ ሠራተኞች እንዲልክ ለምኑት አላቸው።”​—⁠ማቴዎስ 9:​35-38

12. ኢየሱስና ሐዋርያቱ የፈጸሙት ተአምር ምን ተጨማሪ ዓላማ አከናውኗል?

12 ሐዋርያቱ ከኢየሱስ ጋር ስለነበሩ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን የኢየሱስን አስተሳሰብ ቀስመው ሊሆን ይችላል። ለሰዎች እውነተኛ ፍቅርና ርኅራኄ እንዳላቸው የሚያሳዩበት አንደኛው መንገድ ስለ መንግሥቱ መስበክንና ማስተማርን የሚጨምር መሆኑን መገንዘብ ይችላሉ። ይህም ከሚያከናውኗቸው መልካም ሥራዎች መካከል ዋነኛው ነው። ከዚህ ጋር በመስማማት በሽተኞችን መፈወስን የመሰሉት ለሰብዓዊ ደህንነት የሚጠቅሙ መልካም ተግባራት ተጨማሪ ዓላማዎችን አከናውነዋል። አንዳንድ ሰዎች የመጡት በተመለከቱት ፈውስና በተአምር በቀረበው ምግብ ተስበው እንደሆነ ልትገምት ትችላለህ። (ማቴዎስ 4:​24, 25፤ 8:​16፤ 9:​32, 33፤ 14:​35, 36፤ ዮሐንስ 6:​26) ሆኖም እነዚያ ሥራዎች አካላዊ ጥቅም ከማስገኘትም ባሻገር ሁኔታውን ያስተዋሉ ሰዎች ኢየሱስ የአምላክ ልጅ እንደሆነና ሙሴ አስቀድሞ የተናገረለት “ነቢይ” መሆኑን እንዲገነዘቡ አድርጓቸዋል።​—⁠ዮሐንስ 6:​14፤ ዘዳግም 18:​15

13. በ⁠ዘዳግም 18:​18 ላይ የሚገኘው ትንቢት “ነቢዩ” ምን ሚና እንደሚጫወት ጠበቅ አድርጎ ገልጿል?

13 ኢየሱስ “ነቢይ” መሆኑ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ለምንድን ነው? በትንቢት የተነገረው የዚህ “ነቢይ” ቁልፍ ሚና ምንድን ነው? ተአምራዊ ፈውስ በመፈጸም ወይም ለተራቡ ሰዎች በማዘንና በተአምር በመመገብ ዝነኛ መሆን ነውን? ዘዳግም 18:​18 እንዲህ በማለት ተንብዮአል:- “ከወንድሞቻችሁ መካከል እንደ አንተ [ሙሴ] ያለ ነቢይ አስነሣላቸዋለሁ፤ ቃሌንም በአፉ አደርጋለሁ፣ ያዘዝሁትንም ቃል ሁሉ ይነግራቸዋል።” ሐዋርያቱ ከአንጀት የመራራት ስሜት ማዳበርንና ማንጸባረቅን ቢማሩም የክርስቶስ አስተሳሰብ የሚንጸባረቀው በስብከትና በማስተማር ሥራቸው ጭምር መሆኑን ሊገነዘቡ ይችላሉ። ለሰዎች ሊያደርጉት የሚችሉት ከሁሉ የላቀ ነገር ደግሞ ይህ ነው። በዚህ መንገድ ሕመምተኞችም ሆኑ ድሆች በሕይወት በቆዩባቸው አጭር ዕድሜ ወይም ጥቂት ምግብ በመመገብ ላገኙት ጊዜያዊ ጥቅም ሳይሆን ከዚያ የሚበልጥ ዘላቂ ጥቅሞችን ሊያገኙ ይችላሉ።​—⁠ዮሐንስ 6:​26-30

ዛሬም የክርስቶስን አስተሳሰብ አዳብሩ

14. የክርስቶስን አስተሳሰብ ማዳበርና የስብከቱ ሥራ የተያያዙ ነገሮች የሆኑት እንዴት ነው?

14 የክርስቶስን አስተሳሰብ ማንጸባረቅ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ይኖሩ ለነበሩት ለኢየሱስና ሐዋርያው ጳውሎስ “እኛ ግን የክርስቶስ ልብ [“አስተሳሰብ፣” NW ] አለን” ብሎ ለጻፈላቸው ለመጀመሪያዎቹ ደቀ መዛሙርት ብቻ የተተወ ነገር አይደለም። (1 ቆ⁠ሮ​ንቶስ 2:​16) ምሥራቹን የመስበክና ደቀ መዛሙርት የማድረግ ግዴታ እንዳለብን ያለ አንዳች ማቅማማት እንቀበላለን። (ማቴዎስ 24:​14፤ 28:​19, 20) ሆኖም ይህን ሥራ ለማከናወን ያነሳሳኝ ውስጣዊ ግፊት ምንድን ነው? እያልን ራሳችንን መመርመራችን ጠቃሚ ነው። ግዴታ እንደሆነ ተሰምቶን ብቻ የምናከናውነው ነገር መሆን የለበትም። በአገልግሎቱ እንድንካፈል የሚያነሳሳን ዋነኛው ምክንያት ለአምላክ ያለን ፍቅር ነው። ደግሞም በትክክል ኢየሱስን መምሰል በርኅራኄ ተነሳስቶ መስበክንና ማስተማርን ይጨምራል።​—⁠ማቴዎስ 22:​37-39

15. ርኅራኄ የሕዝባዊ አገልግሎታችን ክፍል መሆኑ ተገቢ የሆነው ለምንድን ነው?

15 እምነታችንን ለማይጋሩን በተለይ ደግሞ ግዴለሽ ለሆኑ፣ ፍላጎት ለሌላቸው ወይም ለተቃዋሚዎች የርኅራኄ ስሜት ማሳየት ሁልጊዜ ቀላል እንዳይደለ የታወቀ ነው። ሆኖም ለሰዎች ያለን ፍቅርና የርኅራኄ ስሜት ከውስጣችን ከጠፋ በክርስቲያናዊ አገልግሎት እንድንካፈል የሚያነሳሳንን ውስጣዊ ግፊት ልናጣ እንችላለን። ታዲያ የርኅራኄን ስሜት ማዳበር የምንችለው እንዴት ነው? ኢየሱስ ለሰዎች የነበረው ዓይነት አመለካከት እኛም እንዲኖረን ጥረት ማድረግ እንችላለን። ኢየሱስ “እረኛ እንደ ሌላቸው በጎች ተጨንቀው ተጥለውም” ተመልክቷቸዋል። (ማቴዎስ 9:​36) በዛሬው ጊዜ ያሉ የብዙ ሰዎች ሁኔታ እንደዚህ አይደለምን? በሐሰት ሃይማኖታዊ እረኞች ተጥለውና በመንፈሳዊ ታውረው ይገኛሉ። በዚህም የተነሳ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን ትክክለኛ መመሪያም ሆነ የአምላክ መንግሥት በቅርቡ በምድር ላይ የሚያመጣውን ገነታዊ ሁኔታ አያውቁም። የመንግሥቱን ተስፋ ስለማያውቁ በዕለታዊ ሕይወታቸው የሚገጥሟቸውን እንደ ድህነት፣ የቤተሰብ ብጥብጥ፣ ሕመምና ሞት ያሉትን ችግሮች የሚጋፈጡት ብቻቸውን ነው። እኛ ግን እነዚህ ሰዎች የግድ ሊያውቁት የሚገባ በሰማይ ተቋቁሞ ስለሚገኘው ስለ አምላክ መንግሥት የሚናገረው ሕይወት አድን ምሥራች አለን!

16. ምሥራቹን ለሌሎች ሰዎች ለማካፈል መፈለግ ያለብን ለምንድን ነው?

16 በአካባቢህ የሚገኙ ሰዎች ስለሚያስፈልጋቸው መንፈሳዊ ነገር ስታሰላስል ስለ አምላክ ፍቅራዊ ዓላማ ለእነርሱ ለመንገር የቻልከውን ሁሉ እንድታደርግ ልብህ አያነሳሳህም? አዎን፣ ሥራችን የርኅራኄ ስሜት ማንጸባረቅን የሚጠይቅ ነው። ኢየሱስ ለሰዎች ያሳየው ዓይነት የሐዘኔታ ስሜት ካለን በፊታችን ላይ ይነበባል፣ በድምፃችን ቃናና በምናስተምርበት ሁኔታ ግልጽ ሆኖ ይታያል። እነዚህ ሁሉ ነገሮች መልእክታችን ‘ለዘላለም ሕይወት ትክክለኛ ዝንባሌ’ ላላቸው ሰዎች ይበልጥ ማራኪ እንዲሆን ያደርጋሉ።​—⁠ሥራ 13:​48 NW

17. (ሀ) ለሌሎች ሰዎች ያለንን ፍቅርና ርኅራኄ ልናሳይ የምንችልባቸው አንዳንድ መንገዶች ምንድን ናቸው? (ለ) ጉዳዩ መልካም ሥራዎችን ከመሥራትና በሕዝብ በሚደረገው አገልግሎት ከመካፈል አንዱን የመምረጥ ጉዳይ ያልሆነው ለምንድን ነው?

17 እርግጥ ነው፣ ፍቅራችንና ርኅራኄያችን በመላ አኗኗራችን መንጸባረቅ ይኖርበታል። ይህም አቅማችን የፈቀደውን ያህል የተቸገሩትን፣ የታመሙትንና ድሆችን በመርዳት ደግነት ማሳየትን ይጨምራል። የሚወዱትን ሰው በሞት ያጡ ሰዎችን በቃላችንም ሆነ በድርጊታችን ማጽናናትንም ያካትታል። (ሉቃስ 7:​11-15፤ ዮሐንስ 11:​33-35) ሆኖም እነዚህ የፍቅር፣ የደግነትና የርኅራኄ መግለጫዎች እንደ አንዳንድ በጎ አድራጊዎች የመልካም ሥራችን ዋነኛ ግቦች መሆን የለባቸውም። ሆኖም ይበልጥ ዘላቂ ጠቀሜታ ያለው በእነዚሁ መለኮታዊ ባሕርያት ተገፋፍተን በክርስቲያናዊ የስብከትና የማስተማር ሥራ የምናደርገው እንቅስቃሴ ነው። ኢየሱስ የአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪዎችን በማስመልከት “ከአዝሙድና ከእንስላል ከከሙንም አሥራት ስለምታወጡ፣ ፍርድንና ምሕረትን ታማኝነትንም፣ በሕግ ያለውን ዋና ነገር ስለምትተዉ” በማለት የተናገረውን አስታውስ። (ማቴዎስ 23:​23) ኢየሱስ አካላዊ ጉዳት የነበረባቸውን ሰዎች ፈውሷል እንዲሁም ሕይወት አድን የሆነውን መንፈሳዊ ጉዳይ አስተምሯል። ኢየሱስ ሁለቱንም አድርጓል። ሆኖም ቅድሚያ የሰጠው ለማስተማሩ ሥራ ነበር። ምክንያቱም ዘላቂ ጥቅም ሊያስገኝ የሚችለው በማስተማሩ ሥራ አማካኝነት የሚያከናውነው መልካም ተግባር ነው።​—⁠ዮሐንስ 20:​16

18. የክርስቶስን አስተሳሰብ መመርመራችን ምን እንድናደርግ ይገፋፋናል?

18 ይሖዋ የክርስቶስን አስተሳሰብ ማወቅ የምንችልበትን አጋጣሚ ስለሰጠን ምንኛ አመስጋኞች ነን! በወንጌሎች አማካኝነት እስከ ዛሬ ከኖሩት ሁሉ የሚበልጠው ታላቅ ሰው የነበረውን አስተሳሰብ፣ ስሜት፣ ባሕርይ እንዲሁም ያከናወናቸውን ተግባራትና ቅድሚያ ይሰጣቸው የነበሩትን ነገሮች በተሻለ መንገድ ለማወቅ እንችላለን። ስለ ኢየሱስ የሚገልጹትን መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ ዘገባዎች ማንበብ፣ በእነርሱ ላይ ማሰላሰልና ተግባራዊ ማድረግ የእኛ ፈንታ ነው። ኢየሱስን መምሰል የምንፈልግ ከሆነ በመጀመሪያ ፍጹማን ባለመሆናችን አቅማችን የፈቀደልንን ያህል እንደ እርሱ ማሰብን፣ የእሱ ዓይነት ስሜት ማንጸባረቅንና እርሱ ነገሮችን ይመዝን በነበረበት መንገድ መመዘንን መማር እንዳለብን አስታውስ። ስለዚህ የክርስቶስን አስተሳሰብ ለማዳበርና ለማንጸባረቅ ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ። ከዚህ ጋር የሚተካከል አንድም የሕይወት መንገድ የለም። ለሰዎች ጥሩ አያያዝ ለማሳየትና እኛም ሆንን ሌሎች ኢየሱስ ፍጹም በሆነ መንገድ ያንጸባረቀውን ሩኅሩኅ አምላክ ይሖዋን ለመቅረብ የሚያስችል ከዚህ የተሻለ መንገድ የለም።​—⁠2 ቆሮንቶስ 1:​3፤ ዕብራውያን 1:​3

እንዴት ብለህ ትመልሳለህ?

• ኢየሱስ ችግር ላይ ወድቀው ለነበሩ ሰዎች በአብዛኛው ምላሽ የሰጠበትን መንገድ በተመለከተ መጽሐፍ ቅዱስ ምን ጥልቅ ማስተዋል ይሰጣል?

• ኢየሱስ ለተከታዮቹ መመሪያ ሲሰጥ ጠበቅ አድርጎ የገለጸው ምንን ነው?

• “የክርስቶስን አስተሳሰብ” በመላው አኗኗራችን ማንጸባረቅ የምንችለው እንዴት ነው?

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ባለ ሙሉ ገጽ ሥዕል]

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ክርስቲያኖች ለሌሎች ሊያደርጉ የሚችሉት ከሁሉ የተሻለው ነገር ምንድን ነው?

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ