ወንጌሎች—ክርክሩ አሁንም እንደቀጠለ ነው
በወንጌሎች ውስጥ የሚገኙት ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ መወለድ የሚናገሩት ታሪኮች እውነተኛ ዘገባዎች ናቸውን?
ኢየሱስ የተራራውን ስብከት ሰጥቷልን?
በእርግጥ ኢየሱስ ከሞት ተነስቷል?
በእርግጥ “እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ” በማለት ተናግሯል?—ዮሐንስ 14:6
ከ1985 ጀምሮ በዓመት ሁለት ጊዜ ሲካሄድ በቆየው የኢየሱስ ሴሚናር ተብሎ በሚታወቀው ስብሰባ ላይ የተገኙ 80 የሚያክሉ ምሁራን እነዚህን በመሰሉ ጉዳዮች ላይ ውይይት አድርገው ነበር። ይህ የምሁራን ቡድን እነዚህን ለመሰሉ ጥያቄዎች መልስ የሰጠው ለየት ባለ መንገድ ነበር። የሴሚናሩ ተካፋዮች በወንጌል ውስጥ ለሚገኘው ኢየሱስ እንደተናገረው ለሚታሰበው ለእያንዳንዱ ንግግር የድምፅ መስጫ ወረቀቶች አዘጋጁ። ቀይ ቀለም ያለው ወረቀት ኢየሱስ ተናግሯቸዋል የሚባሉትን ቃላት ያመለክታል። ሐምራዊ ቀለም ያለው ወረቀት ኢየሱስ የተናገረው የሚመስል ሐሳብን ያመለክታል። ግራጫ ቀለም ያለው ወረቀት ደግሞ ኢየሱስ በቀጥታ የተናገረው ባይሆንም እንኳ እሱ ከተናገረው ነገር ጋር የሚቀራረብ ሐሳብን ያመለክታል። ጥቁር ቀለም ያለው ወረቀት ግን ፈጽሞ አሉታዊ የሆነ መልእክት የሚያስተላልፍ ሲሆን ሐሳቦቹ ከጊዜ በኋላ ከመጣ ወግና ልማድ የመነጩ እንደሆኑ ያመለክታል።
የኢየሱስ ሴሚናር ተካፋዮች ይህንን ዘዴ በመጠቀም በመግቢያው ላይ በጥያቄ መልክ የቀረቡትን አራቱን ነጥቦች ውድቅ አድርገዋቸዋል። እንዲያውም በወንጌል ውስጥ ኢየሱስ ተናግሯቸዋል ከሚባልላቸው ቃላት መካከል 82 በመቶ ለሚሆኑት ድምፅ የሰጡት በጥቁሩ ወረቀት ነው። እንደነርሱ አባባል ከሆነ በወንጌሎችም ሆነ በሌሎች ጽሑፎች ውስጥ ስለ ኢየሱስ ከሚናገረው ታሪክ መካከል ትክክለኛ ዘገባ እንደሆነ ተደርጎ የሚታሰበው 16 በመቶው ብቻ ነው።
በወንጌሎች ላይ እንዲህ የመሰለ ትችት መሰንዘር የጀመረው አሁን አይደለም። በወንጌሎች ላይ ጥቃት መሰንዘር የጀመረው በሃምቡርግ ጀርመን የምሥራቅ አገሮች ቋንቋዎች ፕሮፌሰር የነበሩት ሄርማን ራይማሩስ ያዘጋጁት 1, 400 ገጽ ያለው ጽሑፍ ከእሳቸው ሞት በኋላ በ1774 ታትሞ በወጣበት ጊዜ ነው። ራይማሩስ በዚህ ጽሑፋቸው ላይ ወንጌሎች እውነተኛ ታሪክ መሆናቸውን ጥርጣሬ ላይ የሚጥል ዘገባ አስፍረዋል። እዚህ መደምደሚያ ላይ የደረሱት በቋንቋ ላይ የተመሠረተ ጥናት ካካሄዱና ስለ ኢየሱስ ሕይወት በሚተርኩት በአራቱ ወንጌሎች ውስጥ እርስ በርሳቸው የሚጋጩ የሚመስሉ ሐሳቦችን ካገኙ በኋላ ነው። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ተቺዎች የወንጌሎችን ትክክለኛነት በሚመለከት የጥርጣሬ አስተያየቶችን በተደጋጋሚ የሰነዘሩ ሲሆን ይህም ብዙሓኑ በእነዚህ ጽሑፎች የነበራቸው እምነት በተወሰነ መጠን እንዲሸረሸር አድርጓል።
እነዚህን ምሁራን አንድ የሚያደርጋቸው ነገር በወንጌል ውስጥ የሚገኙት ዘገባዎች የተለያዩ ግለሰቦች ያስተላለፏቸው ሃይማኖታዊ ልብ ወለዶች ናቸው የሚል የጋራ የሆነ እምነት ያላቸው መሆኑ ነው። ጥርጣሬ ያላቸው ምሁራን ከሚያነሷቸው የተለመዱ ጥያቄዎች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል:- አራቱ የወንጌል ጸሐፊዎች እምነታቸው ሃቁን አሰማምረው እንዲጽፉ አድርጓቸው ይሆን? የጥንቱ የክርስቲያን ማኅበረሰብ ፖለቲካ ስለ ኢየሱስ በሚናገረው ታሪክ ውስጥ ተጨማሪ ሐሳብ እንዲያክሉ ወይም በታሪኩ ላይ አንዳንድ ማስተካከያ እንዲያደርጉ ተጽዕኖ አድርጎባቸው ይሆን? ከፈጠራ ሐሳብ ነፃ በሆነ መንገድ በቀጥታ የተጻፈው የወንጌሎች ክፍል የትኛው ነው?
በአምላክ መኖር በማያምን ወይም ከሃይማኖታዊ ተጽዕኖ ነፃ በሆነ ኅብረተሰብ ውስጥ ያደጉ ሰዎች ወንጌሎችን ጨምሮ መጽሐፍ ቅዱስን የሚመለከቱት በአፈ ታሪኮችና በተረት እንደተሞላ መጽሐፍ አድርገው ነው። ሌሎች ደግሞ እንደ ደም መፋሰስ፣ ጭቆና፣ መከፋፈልና አምላካዊ ያልሆነ ምግባር ባሉ ድርጊቶች የተሞላው የሕዝበ ክርስትና ታሪክ ያስደነግጣቸዋል። እነዚህ ሰዎች ሕዝበ ክርስትና እንደ ቅዱስ አድርጋ የምትመለከታቸውን ጽሑፎች በትኩረት የሚከታተሉበት ምንም ምክንያት አይታያቸውም። በግብዝነቱ የሚታወቅ ሃይማኖት ያፈራው የሥነ ጽሑፍ ሥራ ከአፈ ታሪክነት ያለፈ ምን ዋጋ ሊኖረው ይችላል ብለው ያስባሉ።
አንተስ ምን ይሰማሃል? በወንጌሎች ታሪካዊ ትክክለኛነት ላይ ጥያቄ ያስነሱ አንዳንድ ምሁራን በአእምሮህ ውስጥ የጥርጣሬ ዘር እንዲዘሩ መፍቀድ ይኖርብሃል? የወንጌል ጸሐፊዎች ዘገባ የፈጠራ ሐሳብ ነው ስለተባለ ብቻ በጽሑፎቻቸው ላይ ያለህ እምነት እንዲናጋ መፍቀድ ይኖርብሃል? ሕዝበ ክርስትና ያስመዘገበችው መጥፎ ምግባር የወንጌሎችን ትክክለኛነት እንድትጠራጠር ሊያደርግህ ይገባልን? አንዳንዶቹን እውነታዎች እንድትመረምር እንጋብዝሃለን።
[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ወንጌሎች የያዙት አፈ ታሪክ ነው ወይስ እውነተኛ ታሪክ?
[ምንጭ]
Jesus Walking on the Sea/The Doré Bible Illustrations/Dover Publications
[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
Background, pages 3-5 and 8: Courtesy of the Freer Gallery of Art, Smithsonian Institution, Washington, D.C.