‘የመዳን ተስፋችሁ’ ብሩህ ሆኖ እንዲቀጥል አድርጉ!
“የመዳንንም ተስፋ እንደ ራስ ቁር [ልበሱ]።”—1 ተሰሎንቄ 5:8
1. ‘የመዳን ተስፋ’ ለመጽናት የሚረዳው እንዴት ነው?
እድናለሁ የሚለው ተስፋ በጣም አደገኛ ሁኔታ ውስጥ የወደቀን ሰው እንኳ ሳይቀር ተስፋ ቆርጦ እጁን እንዳይሰጥ ሊረዳው ይችላል። ከደረሰበት የመርከብ መሰበር አደጋ ተርፎ ሕይወት አድን ጀልባ ላይ በመንሳፈፍ ላይ የሚገኝ አንድ ሰው እርዳታ እየመጣለት እንዳለ ማወቁ ይበልጥ እንዲጸና ሊረዳው ይችላል። በተመሳሳይም ባለፉት በርካታ ሺህ ዓመታት እምነት የነበራቸው ወንዶችና ሴቶች ‘የእግዚአብሔርን ማዳን’ ተስፋ ማድረጋቸው በመከራ ጊዜ ጠብቋቸዋል። ይህም ተስፋ አላሳፈራቸውም። (ዘጸአት 14:13፤ መዝሙር 3:8፤ ሮሜ 5:5፤ 9:32, 33) ሐዋርያው ጳውሎስ ‘የመዳንን ተስፋ’ ከክርስቲያኖች መንፈሳዊ የጦር ትጥቅ አንዱ ከሆነው ‘ከራስ ቁር’ ጋር አመሳስሎታል። (1 ተሰሎንቄ 5:8፤ ኤፌሶን 6:17) አዎን፣ አምላክ እንደሚያድነን ያለን ትምክህት የማሰብ ችሎታችንን ይጠብቅልናል እንዲሁም መከራ፣ ተቃውሞና ፈተና በሚገጥመን ጊዜ የማስተዋል ስሜታችንን እንድንጠብቅ ይረዳናል።
2. ‘የመዳን ተስፋ’ ለእውነተኛ አምልኮ መሠረት የሆነው በምን መንገዶች ነው?
2 በመጀመሪያው መቶ ዘመን በነበሩት ክርስቲያኖች ዙሪያ የነበረው “የአረማውያን ዓለም የወደፊቱን ጊዜ በተስፋ የሚጠባበቅ አልነበረም” በማለት ዚ ኢንተርናሽናል ስታንዳርድ ባይብል ኢንሳይክሎፔዲያ ይገልጻል። (ኤፌሶን 2:12፤ 1 ተሰሎንቄ 4:13) በአንጻሩ ደግሞ ‘የመዳን ተስፋ’ የእውነተኛ አምልኮ መሠረታዊ አካል ነው። እንዴት? በመጀመሪያ ደረጃ፣ የይሖዋ አገልጋዮች መዳን ከራሱ ከይሖዋ ስም ጋር የተያያዘ በመሆኑ ነው። መዝሙራዊው አሳፍ “አምላካችንና መድኃኒታችን ሆይ፣ እርዳን፤ ስለ ስምህ ክብር፣ አቤቱ፣ ታደገን” በማለት ዘምሯል። (መዝሙር 79:9፤ ሕዝቅኤል 20:9) ከዚህም በላይ ይሖዋ ቃል በገባቸው በረከቶች ማመን ከይሖዋ ጋር ጥሩ ዝምድና ለመመሥረት የግድ አስፈላጊ የሆነ ነገር ነው። ጳውሎስ ሁኔታውን እንዲህ በማለት አስቀምጦታል:- “ያለ እምነትም ደስ ማሰኘት አይቻልም፤ ወደ እግዚአብሔር የሚደርስ እግዚአብሔር እንዳለ ለሚፈልጉትም ዋጋ እንዲሰጥ ያምን ዘንድ ያስፈልገዋልና።” (ዕብራውያን 11:6) በተጨማሪም ጳውሎስ ኢየሱስ ወደ ምድር የመጣበት አንዱ ዋና ምክንያት ንስሐ የሚገቡ ሰዎች መዳን ይችሉ ዘንድ እንደሆነ ገልጿል። ጳውሎስ “ኃጢአተኞችን ሊያድን ክርስቶስ ኢየሱስ ወደ ዓለም መጣ የሚለው ቃል የታመነና ሁሉ እንዲቀበሉት የተገባ ነው” በማለት ገልጿል። (1 ጢሞቴዎስ 1:15) እንዲሁም ሐዋርያው ጴጥሮስ መዳንን ‘የእምነታችን ፍጻሜ [የመጨረሻ ውጤት]’ በማለት ገልጾታል። (1 ጴጥሮስ 1:9) ስለዚህ ለመዳን ተስፋ ማድረግ ተገቢ ነው። ይሁን እንጂ መዳን ሲባል ምን ማለት ነው? ለመዳንስ ምን ብቃት ማሟላት ያስፈልጋል?
መዳን ምንድን ነው?
3. በጥንት ጊዜ የነበሩ የይሖዋ አገልጋዮች ያገኙት ምን ዓይነት መዳን ነው?
3 በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ “መዳን” የሚለው ቃል ብዙውን ጊዜ ከጭቆና ወይም ያለ ዕድሜ ከሚቀጭ ድንገተኛ ሞት መትረፍ ወይም ነፃ መውጣት የሚል ትርጉም አለው። ለምሳሌ ያህል ዳዊት “መድኃኒቴ” በማለት ይሖዋን ከጠራው በኋላ “እግዚአብሔር ጠባቂዬ ነው፣ . . . መሸሸጊያዬ፣ መድኃኒቴ ሆይ፣ ከግፍ ሥራ ታድነኛለህ። ምስጋና የሚገባውን እግዚአብሔርን እጠራለሁ፤ ከጠላቶቼም እድናለሁ” በማለት ተናግሯል። (2 ሳሙኤል 22:2-4) ይሖዋ ታማኝ አገልጋዮቹ ለእርዳታ የሚያሰሙትን ጩኸት እንደሚሰማ ዳዊት ተገንዝቦ ነበር።—መዝሙር 31:22, 23፤ 145:19
4. በቅድመ ክርስትና ዘመን የነበሩ የይሖዋ አገልጋዮች የወደፊቱን ሕይወት በተመለከተ ምን ተስፋ ያደርጉ ነበር?
4 በቅድመ ክርስትና ዘመን የነበሩ የይሖዋ አገልጋዮችም ወደፊት የሚመጣውን ሕይወት ተስፋ ያደርጉ ነበር። (ኢዮብ 14:13-15፤ ኢሳይያስ 25:8፤ ዳንኤል 12:13) እንዲያውም በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ የሚገኙት ስለ መዳን የሚናገሩት ብዙዎቹ ተስፋዎች ወደ ዘላለም ሕይወት ስለሚመራው ታላቅ የመዳን ዝግጅት የሚናገሩ ትንቢቶች ናቸው። (ኢሳይያስ 49:6, 8፤ ሥራ 13:47፤ 2 ቆሮንቶስ 6:2) በኢየሱስ ዘመን የነበሩ በርካታ አይሁዳውያን የዘላለም ሕይወትን ተስፋ ያደርጉ የነበረ ቢሆንም ይህንን ተስፋቸውን እውን የሚያደርግላቸውን ኢየሱስን ለመቀበል ግን አሻፈረን ብለዋል። ኢየሱስ በዘመኑ ለነበሩት የሃይማኖት መሪዎች “እናንተ በመጻሕፍት የዘላለም ሕይወት እንዳላችሁ ይመስላችኋልና እነርሱን ትመረምራላችሁ፤ እነርሱም ስለ እኔ የሚመሰክሩ ናቸው” ብሏቸዋል።—ዮሐንስ 5:39
5. በመጨረሻ መዳን የሚያስገኘው ነገር ምንድን ነው?
5 አምላክ በኢየሱስ አማካኝነት የመዳን ትርጉም የሚያካትታቸውን ነገሮች ግልጽ አድርጓል። ከኃጢአት አገዛዝ፣ ከሃሰት ሃይማኖት ባርነት፣ ሰይጣን ከሚቆጣጠረው ዓለም፣ ከሰውና ሌላው ቀርቶ ከሞት ፍርሃት ነፃ መውጣትን ያጠቃልላል። (ዮሐንስ 17:16፤ ሮሜ 8:2፤ ቆላስይስ 1:13፤ ራእይ 18:2, 4) በመጨረሻም አምላክ የሚያስገኘው መዳን የአምላክን ታማኝ አገልጋዮች ከጭቆናና ከመከራ ነፃ እንዲወጡ ማድረግ ብቻ ሳይሆን የዘላለም ሕይወት የማግኘት አጋጣሚንም የሚጨምር ይሆናል። (ዮሐንስ 6:40፤ 17:3) ‘ለታናሹ መንጋ’ መዳን ማለት ለሰማያዊ ሕይወት ትንሣኤ አግኝቶ በመንግሥቱ አገዛዝ ከክርስቶስ ጋር ተካፋይ መሆን ማለት እንደሆነ ኢየሱስ አስተምሯል። (ሉቃስ 12:32) ለተቀሩት የሰው ዘሮች ደግሞ መዳን ማለት አዳምና ሔዋን ኃጢአት ከመሥራታቸው በፊት በኤደን ገነት ውስጥ የነበራቸው ዓይነት ፍጹም ሕይወት ማግኘትና በዚያን ጊዜ ከነበረው ሁኔታ ጋር በሚመሳሰል መንገድ ከአምላክ ጋር መወዳጀት ዝምድና መመሥረት ማለት ይሆናል። (ሥራ 3:21፤ ኤፌሶን 1:10) መጀመሪያም ቢሆን አምላክ ዓላማው የሰው ልጆች እንዲህ በመሰለው ገነታዊ ሁኔታ ውስጥ ለዘላለም እንዲኖሩ ነበር። (ዘፍጥረት 1:28፤ ማርቆስ 10:30) ታዲያ እንዲህ የመሰለው ሁኔታ ተመልሶ ሊመጣ የሚችለው እንዴት ነው?
ቤዛው የመዳን መሠረት ነው
6, 7. ኢየሱስ በእኛ መዳን ረገድ የሚጫወተው ሚና ምንድን ነው?
6 የዘላለም መዳን የሚገኘው በክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት አማካኝነት ብቻ ነው። ለምን? መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚገልጸው አዳም ኃጢአት ሲሠራ ራሱንም ሆነ እኛን ጨምሮ የወደፊት ልጆቹን ለኃጢአት አሳልፎ ‘ሸጧል።’ ስለዚህ የሰው ልጆች የተረጋገጠ ተስፋ እንዲኖራቸው ቤዛ አስፈለጋቸው። (ሮሜ 5:14, 15፤ 7:14) በሙሴ ሕግ ሥር ይቀርብ የነበረው የእንስሳ መሥዋዕት አምላክ ለሰው ዘር ቤዛ እንደሚያዘጋጅ የሚጠቁም ነበር። (ዕብራውያን 10:1-10፤ 1 ዮሐንስ 2:2) እነዚህን ትንቢታዊ አምሳያዎች ፍጻሜያቸውን እንዲያገኙ ያደረገው ኢየሱስ ያቀረበው መሥዋዕት ነው። ኢየሱስ ከመወለዱ በፊት “እርሱም ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ያድናቸዋል” በማለት የይሖዋ መልአክ አውጆአል።—ማቴዎስ 1:21፤ ዕብራውያን 2:10
7 ኢየሱስ ድንግል በነበረችው ማርያም በኩል ተዓምራዊ በሆነ መንገድ የተወለደ ሲሆን የአምላክ ልጅ እንደመሆኑ መጠን ሞትን ከአዳም አልወረሰም። የተከተለውን ፍጹም የታማኝነት አካሄድ ጨምሮ ይህ እውነታ የሰውን ዘር ከኃጢአትና ከሞት ለመቤዠት የሚያስችለውን ዋጋ ለመክፈል ብቁ አድርጎታል። (ዮሐንስ 8:36፤ 1 ቆሮንቶስ 15:22) ኢየሱስ ከሌሎች ሰዎች በተለየ መንገድ የኃጢአት ኩነኔ አልነበረበትም። ወደ ምድር የመጣው ‘ነፍሱን ለብዙዎች ቤዛ ሊሰጥ’ ነው። (ማቴዎስ 20:28) አሁን ከሞት የተነሳውና ዙፋን ላይ የተቀመጠው ኢየሱስ ይህን በማድረጉ አምላክ ያወጣቸውን ብቃቶች የሚያሟሉትን ሁሉ የማዳን ሥልጣን ተሰጥቶታል።—ራእይ 12:10
ለመዳን ምን ነገር ማድረግ ይጠይቃል?
8, 9. (ሀ) ኢየሱስ ባለጠጋ የነበረ አንድ ወጣት ባለ ሥልጣን መዳንን አስመልክቶ ላቀረበለት ጥያቄ መልስ የሰጠው እንዴት ነው? (ለ) ኢየሱስ ይህን አጋጣሚ ደቀ መዛሙርቱን ለማስተማር የተጠቀመበት እንዴት ነበር?
8 በአንድ ወቅት ባለጠጋ የነበረ አንድ እስራኤላዊ ወጣት ባለ ሥልጣን “የዘላለም ሕይወትን እወርስ ዘንድ ምን ላድርግ?” በማለት ኢየሱስን ጠይቆት ነበር። (ማርቆስ 10:17) ይህ ወጣት ያቀረበው ጥያቄ አምላክ የተወሰኑ መልካም ሥራዎችን ከሰዎች የሚጠብቅ በመሆኑ አንድ ሰው እነዚያን መልካም ሥራዎች ከፈጸመ ከአምላክ መዳንን ሊያገኝ ይችላል የሚለውን በጊዜው ተስፋፍቶ የነበረውን የአይሁዳውያን አስተሳሰብ የሚያንጸባርቅ ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ እንዲህ የመሰለው ልማዳዊ አምልኮ ራስ ወዳድ ከሆነ ውስጣዊ ግፊት ሊመነጭ ይችላል። ፍጹም ካልሆኑ ሰዎች መካከል አምላክ ያወጣቸውን ብቃቶች ሙሉ በሙሉ ሊያሟላ የሚችል አንድም ሰው ስለማይገኝ እንደነዚህ ያሉት ሥራዎች የተረጋገጠ የመዳን ተስፋ ሊያስገኙ አይችሉም።
9 ኢየሱስ ሰውዬው ላቀረበው ጥያቄ መልስ ሲሰጥ ባጭሩ የአምላክን ትእዛዛት እንዲጠብቅ አሳሰበው። ወዲያውም ወጣቱ ባለ ሥልጣን ከልጅነቱ ጀምሮ ትእዛዛቱን እንደጠበቀ ገለጸለት። የሰጠው መልስ ኢየሱስ ለእርሱ ፍቅር እንዲያድርበት አደረገው። ከዚያም ኢየሱስ “አንድ ነገር ጐደለህ፤ ሂድ፣ ያለህን ሁሉ ሽጠህ ለድሆች ስጥ፣ በሰማይም መዝገብ ታገኛለህ፣ . . . ና፣ ተከተለኝ አለው።” ይሁን እንጂ ወጣቱ ሰው “ብዙ ንብረት ነበረውና እያዘነ” ሄደ። ከዚያም ኢየሱስ ይህ ዓለም ከሚያቀርባቸው ቁሳዊ ነገሮች ጋር ከመጠን በላይ የሚቆራኝ ሰው መዳን እንዳይችል እንቅፋት እንደሚሆንበት ለደቀ መዛሙርቱ ጠበቅ አድርጎ ገለጸላቸው። አክሎም በራሱ ጥረት መዳንን ሊያገኝ የሚችል ማንም ሰው እንደሌለ ነገራቸው። ይሁን እንጂ ኢየሱስ በመቀጠል “በእግዚአብሔር ዘንድ እንጂ በሰው ዘንድ አይቻልም በእግዚአብሔር ዘንድ ሁሉ ይቻላልና” በማለት ማረጋገጫ ሰጣቸው። (ማርቆስ 10:18-27፤ ሉቃስ 18:18-23) ታዲያ መዳን ሊገኝ የሚችለው እንዴት ነው?
10. መዳን እንድናገኝ ምን ሁኔታ ማሟላት አለብን?
10 መዳን ከአምላክ የሚገኝ ስጦታ ነው፤ ሆኖም እንዲሁ የሚገኝ ነገር አይደለም። (ሮሜ 6:23) ይህን ስጦታ ለማግኘት እያንዳንዱ ግለሰብ ሊያሟላቸው የሚገቡ የተወሰኑ መሠረታዊ ሁኔታዎች አሉ። ኢየሱስ “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና” በማለት ተናግሯል። እንዲሁም ሐዋርያው ዮሐንስ “በልጁ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፤ በልጁ የማያምን ግን . . . ሕይወትን አያይም” በማለት ጨምሮ ተናግሯል። (ዮሐንስ 3:16, 36) ከዚህ ለማየት እንደሚቻለው አምላክ የዘላለም መዳን ለማግኘት ከሚፈልግ ከእያንዳንዱ ግለሰብ እምነትንና ታዛዥነትን ይጠብቃል። እያንዳንዱ ግለሰብ ቤዛውን ለመቀበልና የኢየሱስን ፈለግ ለመከተል ውሳኔ ማድረግ ይገባዋል።
11. ፍጽምና የጎደለው አንድ ሰው የይሖዋን ሞገስ ሊያገኝ የሚችለው እንዴት ነው?
11 ፍጽምና የጎደለን ሰዎች እንደመሆናችን መጠን በተፈጥሯችን የታዛዥነት ዝንባሌ የሌለን ከመሆኑም በላይ ፍጹም በሆነ መንገድ መታዘዝ ያቅተናል። ይሖዋ ኃጢአታችንን ለመሸፈን ቤዛ ያዘጋጀውም ለዚህ ነው። የሆነ ሆኖ፣ ከአምላክ መንገዶች ጋር ተስማምተን ለመኖር የማያቋርጥ ጥረት ማድረግ ይገባናል። ኢየሱስ ባለጠጋ ለነበረው ወጣት ባለ ሥልጣን እንደተናገረው የአምላክን ትእዛዛት መጠበቅ አለብን። እንዲህ ማድረጋችን የአምላክን ሞገስ የሚያስገኝልን ከመሆኑም በላይ ከፍተኛ ደስታ ያመጣልናል። ምክንያቱም “ትእዛዛቱም ከባዶች አይደሉም።” ከዚህ ይልቅ ‘የሚያጠነክሩ’ ናቸው። (1 ዮሐንስ 5:3፤ ምሳሌ 3:1, 8 የ1980 ትርጉም ) እንዲህም ሆኖ የመዳንን ተስፋ አጥብቆ መያዝ ቀላል አይደለም።
“ለእምነት ተጋደሉ”
12. አንድ ክርስቲያን ለብልሹ ሥነ ምግባር የሚጋብዙ ፈተናዎችን እንዲቋቋም የመዳን ተስፋ ሊያጠነክረው የሚችለው እንዴት ነው?
12 ደቀ መዝሙሩ ይሁዳ ለጥንቶቹ ክርስቲያኖች ‘በጋራ ስለሚካፈሉት መዳን’ ሊጽፍላቸው ፈልጎ ነበር። ይሁን እንጂ ተስፋፍቶ የነበረው መጥፎ ሥነ ምግባር ወንድሞቹን ‘ለእምነት እንዲጋደሉ’ እንዲመክር አስገድዶታል። አዎን፣ መዳን ለማግኘት ማመን፣ እውነተኛውን የክርስትና እምነት የሙጥኝ ብሎ መያዝና አስቸጋሪ ሁኔታ በሌለበት ጊዜ ታዛዥ መሆን ብቻውን በቂ አይደለም። ለይሖዋ ያለን አምልኮታዊ ፍቅር ፈተናዎችንና መጥፎ የሥነ ምግባር ተጽዕኖዎችን መቋቋም እንድንችል የሚረዳን ዓይነት መሆን አለበት። ሆኖም መረን የለቀቀ የጾታ ስሜት፣ ለሥልጣን አክብሮት አለማሳየት፣ መከፋፈልና ጥርጣሬ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበረውን ጉባኤ በክለውት ነበር። ይሁዳ ክርስቲያን ባልደረቦቹ እነዚህን ዝንባሌዎች ተዋግተው ማሸነፍ እንዲችሉ ለመርዳት ሲል ዋነኛ ዓላማቸው ሁልጊዜ በአእምሯቸው ውስጥ ቁልጭ ብሎ እንዲታያቸው አሳሰባቸው:- “ወዳጆች ሆይ፣ ከሁሉ ይልቅ በተቀደሰ ሃይማኖታችሁ ራሳችሁን ለማነጽ እየተጋችሁ በመንፈስ ቅዱስም እየጸለያችሁ፣ ወደ ዘላለም ሕይወት የሚወስደውን የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ምሕረት ስትጠባበቁ በእግዚአብሔር ፍቅር ራሳችሁን ጠብቁ።” (ይሁዳ 3, 4, 8, 19-21) የመዳን ተስፋ በሥነ ምግባር ንጹሕ ሆነው ለመኖር በሚያደርጉት ውጊያ ጥንካሬ ሊሰጣቸው ይችላል።
13. ይገባናል የማንለውን የአምላክን ደግነት ዓላማ እንዳልሳትን ልናሳይ የምንችለው እንዴት ነው?
13 ይሖዋ አምላክ የሚያድናቸው ሰዎች ምሳሌ የሚሆን ጥሩ ሥነ ምግባር እንዲኖራቸው ይጠብቅባቸዋል። (1 ቆሮንቶስ 6:9, 10) ይሁን እንጂ አምላክ ያወጣቸውን የሥነ ምግባር መስፈርቶች መጠበቅ በሌሎች ላይ ፈራጅ መሆን ማለት አይደለም። የሰዎችን ዘላለማዊ ዕጣ የመወሰን መብት አልተሰጠንም። ጳውሎስ አቴንስ ለሚኖሩ ግሪካውያን እንደተናገረው ይህንን የሚያደርገው አምላክ ነው:- “ቀን ቀጥሮአልና፣ በዚያም ቀን ባዘጋጀው ሰው እጅ [በኢየሱስ ክርስቶስ] በዓለሙ ላይ በጽድቅ ሊፈርድ አለው።” (ሥራ 17:31፤ ዮሐንስ 5:22) በኢየሱስ ቤዛ ላይ በማመን የምንመላለስ ከሆነ መጪውን የፍርድ ቀን የምንፈራበት ምንም ምክንያት አይኖርም። (ዕብራውያን 10:38, 39) ዋናው ነገር በተሳሳተ አስተሳሰብና ድርጊት እንድንፈተን በመፍቀድ “ይገባናል የማንለውን የአምላክ ደግነት [በቤዛው በኩል ከእርሱ ጋር የፈጠርነውን እርቅ] ተቀብለን ዓላማውን መሳት” አይገባንም። (2 ቆሮንቶስ 6:1 NW ) በተጨማሪም ሌሎች መዳን እንዲያገኙ በመርዳት የአምላክን ምሕረት ዓላማ እንዳልሳትን እናሳያለን። እንዴት ልንረዳቸው እንችላለን?
የመዳንን ተስፋ ማካፈል
14, 15. ኢየሱስ የመዳንን ምሥራች የማወጁን ሥራ የሰጠው ለእነማን ነው?
14 ጳውሎስ ነቢዩ ኢዩኤል የተናገረውን በመጥቀስ “የጌታን [“የይሖዋን፣” NW ] ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናል” በማለት ጽፏል። ከዚያም በማከል “እንግዲህ ያላመኑበትን እንዴት አድርገው ይጠሩታል? ባልሰሙትስ እንዴት ያምናሉ? ያለ ሰባኪስ እንዴት ይሰማሉ?” በማለት ተናገረ። ከዚያም ጥቂት ቁጥሮች ዝቅ ብሎ ጳውሎስ እምነት የሚገኘው “ከመስማት” ማለትም “በእግዚአብሔር [“ስለ ክርስቶስ ከሚናገረው፣” NW ] ቃል” እንጂ እንዲሁ የሚገኝ ነገር እንዳልሆነ አመልክቷል።—ሮሜ 10:13, 14, 17፤ ኢዩኤል 2:32
15 “ስለ ክርስቶስ የሚናገረውን ቃል” ለአሕዛብ የሚያደርሰው ማን ነው? ኢየሱስ ቀደም ሲል ይህንን “ቃል” ተምረው ለነበሩት ደቀ መዛሙርቱ ይህን ሥራ ሰጥቷቸዋል። (ማቴዎስ 24:14፤ 28:19, 20፤ ዮሐንስ 17:20) በመንግሥቱ ስብከትና ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ ስንካፈል ሐዋርያው ጳውሎስ ከኢሳይያስ መጽሐፍ በመጥቀስ “መልካሙን የምሥራች የሚያወሩ እግሮቻቸው እንዴት ያማሩ ናቸው” በማለት የጻፈውን ነገር ማድረጋችን ነው። ይዘነው የምንሄደውን ምሥራች ብዙ ሰዎች ባይቀበሉ እንኳ እግሮቻችን በይሖዋ ፊት “ያማሩ” ናቸው።—ሮሜ 10:15፤ ኢሳይያስ 52:7
16, 17. የስብከቱ ሥራችን የትኞቹን ሁለት ዓላማዎች ለማከናወን ያገለግላል?
16 ይህን ተልእኮ መፈጸም አስፈላጊ ለሆኑ ለሁለት ዓላማዎች ያገለግላል። በመጀመሪያ ደረጃ የአምላክን ስም ከፍ ከፍ ለማድረግና መዳን የሚፈልጉ ሰዎች ፊታቸውን ወደ ማን ማዞር እንዳለባቸው እንዲያውቁ ለመርዳት ምሥራቹ መሰበክ አለበት። ጳውሎስ ይህን የተልዕኮውን ገጽታ ተገንዝቦ ነበር። “እንዲሁ ጌታ:- እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ለማዳን ትሆን ዘንድ ለአሕዛብ ብርሃን አድርጌሃለሁ ብሎ አዞናልና” ሲል ገልጿል። በመሆኑም የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት እንደመሆናችን መጠን እያንዳንዳችን የመዳንን መልእክት ለሰዎች በማድረሱ ተግባር መካፈል አለብን።—ሥራ 13:47፤ ኢሳይያስ 49:6
17 ሁለተኛ፣ የምሥራቹ ስብከት አምላክ ለሚያስፈጽመው የጽድቅ ፍርድ መሠረት ይጥላል። ኢየሱስ ይህን ፍርድ በማስመልከት እንዲህ በማለት ተናግሯል:- “የሰው ልጅ በክብሩ በሚመጣበት ጊዜ ከእርሱም ጋር ቅዱሳን መላእክቱ ሁሉ፣ በዚያን ጊዜ በክብሩ ዙፋን ይቀመጣል አሕዛብም ሁሉ በፊቱ ይሰበሰባሉ፤ እረኛም በጎቹን ከፍየሎች እንደሚለይ እርስ በርሳቸው ይለያቸዋል።” የመፍረዱና የመለየቱ ሥራ የሚከናወነው “የሰው ልጅ በክብሩ በሚመጣበት ጊዜ” ቢሆንም የስብከቱ ሥራ በዛሬው ጊዜ ያሉት ሰዎች የክርስቶስን መንፈሳዊ ወንድሞች ለይተው እንዲያውቁና ለራሳቸው ዘላለማዊ መዳን ከነርሱ ጋር ተባብረው እንዲሠሩ አጋጣሚ ይሰጣቸዋል።—ማቴዎስ 25:31-46
“ተስፋ እስኪሞላ ድረስ” በጽናት ቀጥሉ
18. ‘የመዳን ተስፋችን’ ብሩህ ሆኖ እንዲቀጥል ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?
18 በስብከቱ ሥራ በንቃት መካፈላችን ተስፋችን ብሩህ ሆኖ እንዲቀጥል ለማድረግም ይረዳናል። ጳውሎስ እንዲህ በማለት ጽፏል:- “ተስፋ እስኪሞላ ድረስ እያንዳንዳችሁ ያን ትጋት እስከ መጨረሻ እንድታሳዩ እንመኛለን።” (ዕብራውያን 6:11) ስለዚህ ሁላችንም “እግዚአብሔር ለቁጣ አልመረጠንምና፣ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ መዳንን ለማግኘት ነው እንጂ” የሚለውን እያስታወስን ‘የመዳንን ተስፋ እንደ ራስ ቁር እንልበስ።’ (1 ተሰሎንቄ 5:8, 9) ጴጥሮስ የሰጠውንም ምክር ልብ እንበል:- “የልቡናችሁን ወገብ ታጥቃችሁና በመጠን ኖራችሁ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ሲገለጥ የምታገኙትን ጸጋ ፈጽማችሁ ተስፋ አድርጉ።” (1 ጴጥሮስ 1:13) እንዲህ የሚያደርጉ ሁሉ ‘የመዳናቸው ተስፋ’ ሙሉ በሙሉ ፍጻሜውን ሲያገኝ ይመለከታሉ!
19. በሚቀጥለው ርዕስ ምን ነገር እንመረምራለን?
19 እስከዚያው ድረስ ግን ይህ ሥርዓት ስለቀረው ጊዜ ምን ዓይነት አመለካከት ሊኖረን ይገባል? እኛም ሆንን ሌሎች ሰዎች መዳንን እንድናገኝ ይህን ጊዜ እንዴት ልንጠቀምበት እንችላለን? በሚቀጥለው ርዕስ እነዚህን ጥያቄዎች እንመረምራለን።
ልታብራራ ትችላለህ?
• ‘የመዳን ተስፋችን’ ብሩህ ሆኖ እንዲቀጥል ማድረግ ያለብን ለምንድን ነው?
• መዳን ምን ነገሮችን ያጠቃልላል?
• የመዳንን ስጦታ ለማግኘት ምን ማድረግ አለብን?
• የስብከት ሥራችን ከአምላክ ዓላማ ጋር በተያያዘ ምን ነገር ያከናውናል?
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
መዳን ከጥፋት መትረፍ ማለት ብቻ አይደለም