በቅርቡ ተስፋ መቁረጥ የሌለበት ዓለም ይመጣል
ሕይወት ከጊዜ ወደ ጊዜ ከፍተኛ ጥሮሽ የሚጠይቅ እየሆነ የመጣ ሲሆን ለተስፋ መቁረጥ ምክንያት የሚሆኑ ብዙ ነገሮች አሉ። ተስፋ ስንቆርጥ ስሜታችንን መቆጣጠር ይከብደን ይሆናል። ሕይወትን የሚወዱ ሰዎች እንኳ ከልክ በላይ ሊያዝኑ ይችላሉ! ጥቂት ምሳሌዎችን ተመልከቱ።
ጥንት ይኖር የነበረው ሙሴ በጣም ተስፋ ከመቁረጡ የተነሳ “በፊትህ ሞገስ አግኝቼ እንደ ሆነ፣ በእኔ ላይ የሚሆነውን መከራ እንዳላይ፣ እባክህ ፈጽሞ ግደለኝ” በማለት ለአምላክ ተናግሮ ነበር። (ዘኁልቊ 11:15) ከጠላቶቹ በመሸሽ ላይ የነበረው ነቢዩ ኤልያስ “ይበቃኛል፤ አሁንም . . . ነፍሴን [ሕይወቴን] ውሰድ” ሲል በምሬት ተናግሯል። (1 ነገሥት 19:4) ነቢዩ ዮናስም “አቤቱ፣ ከሕይወት ሞት ይሻለኛልና እባክህ፣ ነፍሴን ከእኔ ውሰድ” ብሎ ነበር። (ዮናስ 4:3) ይሁን እንጂ ሙሴም ሆነ ኤልያስ ወይም ዮናስ ራሳቸውን አልገደሉም። ሁሉም “አትግደል” የሚለውን የአምላክ ትእዛዝ ያውቁ ነበር። (ዘጸአት 20:13) በአምላክ ላይ ጠንካራ እምነት ስለነበራቸው የትኛውም ዓይነት ሁኔታ መፍትሔ እንደሚኖረውና ሕይወት የአምላክ ስጦታ እንደሆነ ተገንዝበው ነበር።
በአሁኑ ጊዜ በእኛ ላይ እየደረሱብን ስላሉት ችግሮችስ ምን ለማለት ይቻላል? ከሚደርስብን የስሜት ውጥረት ወይም የአካል ጉዳት በተጨማሪ አንዳንድ ጊዜ በቤተሰባችን አባላት፣ በጎረቤቶቻችን፣ ወይም በሥራ ባልደረቦቻችን የሚፈጸምብንን በደል መቋቋም ያስፈልገን ይሆናል። መጽሐፍ ቅዱስ በመጥፎ ባሕርያት ስለተሞሉ ሰዎች ሲናገር እንዲህ ይላል:- “ዓመፃ ሁሉ፣ ግፍ፣ መመኘት፣ ክፋት ሞላባቸው፤ ቅናትን፣ ነፍስ መግደልን፣ ክርክርን፣ ተንኰልን፣ ክፉ ጠባይን ተሞሉ፤ የሚያሾከሹኩ፣ ሐሜተኞች፣ አምላክን የሚጠሉ፣ የሚያንገላቱ፣ ትዕቢተኞች፣ ትምክህተኞች፣ ክፋትን የሚፈላ[ል]ጉ፣ ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፣ የማያስተውሉ፣ ውል የሚያፈርሱ፣ ፍቅር የሌላቸው፣ ምሕረት ያጡ ናቸው።” (ሮሜ 1:28-31) በየዕለቱ እንደዚህ ዓይነት ባሕርይ ባላቸው ሰዎች ተከቦ መኖር ሕይወት ሸክም መስሎ እንዲታየን ሊያደርግ ይችላል። ታዲያ ማጽናኛና እፎይታ ማግኘት የሚያስፈልጋቸውን ሰዎች መርዳት የምንችለው እንዴት ነው?
ለማዳመጥ ፈቃደኛ መሆን
መከራና ችግር የአንድን ሰው የአስተሳሰብ ሚዛን ሊያዛቡ ይችላሉ። ጠቢቡ ሰው ሰሎሞን “ግፍ ጠቢቡን ያሳብደዋል” ሲል ተናግሯል። (መክብብ 7:7) በመሆኑም ራስን ስለመግደል የሚያወራ ግለሰብ ሁኔታ በቸልታ ሊታለፍ አይገባም። የግለሰቡ ስሜታዊም ሆነ አካላዊ፣ አእምሮአዊም ሆነ መንፈሳዊ ችግር አፋጣኝ ትኩረት የሚሻ ሊሆን ይችላል። እርግጥ፣ ባለሞያዎች የሚሰጡት እርዳታና የሕክምና ዓይነት ይለያያል። ግለሰቡ በሚወስደው ሕክምና ረገድ የራሱን ውሳኔ ማድረግ ይኖርበታል።—ገላትያ 6:5
አንድ ሰው ራስን የመግደል ስሜት እንዲሰማው ያደረገው ምክንያት ምንም ይሁን ምን ግለሰቡ ሊተማመንበት የሚችል አስተዋይ፣ ርኅሩኅና ትዕግሥተኛ ሰው ማግኘቱ ሁኔታውን ሙሉ በሙሉ ሊለውጠው ይችላል። ለማዳመጥ ፈቃደኛ የሆኑ የቤተሰብ አባላትና ጓደኞች በዚህ ረገድ እርዳታ መስጠት ይችሉ ይሆናል። ችግሩን እንደራስ አድርጎ ከመመልከትና ደግነት ከማሳየት በተጨማሪ በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኙት የሚያንጹ ሐሳቦች ተስፋ ለቆረጡት ሰዎች ከፍተኛ እርዳታ ሊያደርጉላቸው ይችላሉ።
ለተጨነቁ የሚሆን መንፈሳዊ እርዳታ
መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ምን ያህል ሊያበረታታ እንደሚችል ስታውቁ ትገረሙ ይሆናል። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አእምሮ ጤና መመሪያ የሚሰጥ መጽሐፍ ባይሆንም ሕይወትን ከፍ አድርገን እንድንመለከት ሊረዳን ይችላል። ንጉሥ ሰሎሞን እንዲህ ብሏል:- “ሰው ደስ ከሚለውና በሕይወቱ ሳለ መልካምን ነገር ከሚያደርግ በቀር መልካም ነገር እንደሌለ አወቅሁ። ደግሞም ሰው ሁሉ ይበላና ይጠጣ ዘንድ በድካሙም ሁሉ ደስ ይለው ዘንድ የእግዚአብሔር ስጦታ ነው።” (መክብብ 3:12, 13) ሕይወት ትርጉም እንዲኖረው ከሚያደርግ አርኪ ሥራ በተጨማሪ ንጹህ አየር፣ የፀሐይ ብርሃን፣ አበቦች፣ ዛፎችና ወፎችን የመሳሰሉት ቀላል ነገሮች ለመደሰት የሚያስችሉን ከአምላክ የተገኙ ስጦታዎች ናቸው።
መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ አምላክና ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሚያስቡልን የሚሰጠው ማረጋገጫ ደግሞ ይበልጥ መንፈስን የሚያነቃቃ ነው። (ዮሐንስ 3:16፤ 1 ጴጥሮስ 5:6, 7) መዝሙራዊው “እግዚአብሔር አምላክ ብሩክ ነው፤ እግዚአብሔር በየዕለቱ ብሩክ ነው [“ሸክማችንን በየዕለቱ ይሸከምልናል፣” NW ]፤ የመድኃኒታችን አምላክ ይረዳናል” ብሎ መናገሩ ተገቢ ነበር። (መዝሙር 68:19) የማንረባና ዋጋ ቢስ እንደሆንን ቢሰማን እንኳ አምላክ ወደ እርሱ እንድንጸልይ ጋብዞናል። በትህትናና ከልብ በመነጨ ስሜት የእርሱን እርዳታ የሚጠይቅን ማንኛውንም ሰው እንደማይንቅ ማረጋገጫ ተሰጥቶናል።
በአሁኑ ጊዜ ማንኛውም ሰው ከችግር ነጻ የሆነ ሕይወት እመራለሁ ብሎ መጠበቅ አይኖርበትም። (ኢዮብ 14:1) ሆኖም በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘው እውነት ራስን መግደል ለችግራቸው ትክክለኛ መፍትሔ እንደማይሆን ብዘዎችን አስገንዝቧል። እስቲ ሐዋርያው ጳውሎስ አንድን ተስፋ የቆረጠ የወኀኒ ቤት ጠባቂ እንዴት እንደረዳው ተመልከት። “የወኅኒውም ጠባቂ ከእንቅልፉ ነቅቶ የወኅኒው ደጆች ተከፍተው ባየ ጊዜ፣ እስረኞቹ ያመለጡ መስሎት ራሱን ይገድል ዘንድ አስቦ ሰይፉን መዘዘ።” በዚች ቅጽበት ይህ ጠባቂ ሥራውን በሚገባ ባለመወጣቱ ምክንያት ከሚደርስበት ውርደትና ምናልባትም ከሚጠብቀው የስቃይ ሞት ይልቅ ራሱን መግደል እንደሚሻል ተሰምቶት ነበር። ሐዋርያው “በታላቅ ድምፅ:- ሁላችን ከዚህ አለንና በራስህ ክፉ ነገር አታድርግ ብሎ ጮኸ”! ጳውሎስ ይህንን ብቻ ብሎ አላበቃም። እርሱና ሲላስ ጠባቂውን ከማጽናናታቸውም በላይ “ጌቶች ሆይ፣ እድን ዘንድ ምን ማድረግ ይገባኛል?” በማለት ለጠየቃቸው ጥያቄ “በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ እመን አንተና ቤተ ሰዎችህም ትድናላችሁ” የሚል መልስ ሰጥተውታል። ከዚያም የይሖዋን ቃል ለእርሱና ለቤተሰቡ ካስተማሯቸው በኋላ ወዲያው “እርሱ ከቤተ ሰዎቹ ሁሉ ጋር ተጠመቀ።” ይህ የወኅኒ ጠባቂና ቤተሰቡ በጣም ከመደሰታቸውም በላይ ሕይወታቸው ትርጉም ያለው ሆኗል።—ሥራ 16:27-35
በዘመናችንም አምላክ በምድር ላይ ላለው ክፋት ተጠያቂ እንዳልሆነ ማወቁ እንዴት ያጽናናል! “ዓለሙንም ሁሉ የሚያስተው፣ ዲያብሎስና ሰይጣን” የተባለው ክፉ መንፈስ እንደሆነ ቃሉ ያረጋግጥልናል። ሆኖም ጊዜው እያለቀበት ነው። (ራእይ 12:9, 12) ሰይጣንና አጋንንቱ በምድር ነዋሪዎች ላይ ያመጡት መከራና ስቃይ ሁሉ በቅርቡ በመለኮታዊ ጣልቃ ገብነት ያከትማል። ከዚያ በኋላ አምላክ ቃል በገባው ጽድቅ የሰፈነበት አዲስ ዓለም ውስጥ ለተስፋ መቁረጥና ራስን ለመግደል ምክንያት የሚሆኑት ችግሮች በሙሉ ዘላቂ መፍትሄ ያገኛሉ።—2 ጴጥሮስ 3:13
የእርዳታ ጥሪ ለሚያሰሙ የሚሆን ማጽናኛ
ተስፋ የቆረጡ ሰዎች በዛሬው ጊዜም ቢሆን ከቅዱሳን ጽሑፎች ማጽናኛ ማግኘት ይችላሉ። (ሮሜ 15:4) መዝሙራዊው “የተሰበ[ረ]ውንና የተዋረደውን ልብ እግዚአብሔር አይንቅም” ሲል ዘምሯል። (መዝሙር 51:17) እርግጥ ነው፣ ሁላችንም ከአንዳንድ ፈተናዎችና አለፍጽምና ከሚያስከትላቸው መጥፎ ውጤቶች ማምለጥ አንችልም። ሆኖም ደግ፣ አፍቃሪና ምክንያታዊ ስለሆነው ሰማያዊ አባታችን ትክክለኛ እውቀት ማግኘታችን በእርሱ ፊት ውድ እንደሆንን ማረጋገጫ ይሰጠናል። አምላክ ከማንም በላይ የቅርብ ወዳጃችንና አስተማሪያችን ሊሆን ይችላል። ከይሖዋ አምላክ ጋር የተቀራረበ ዝምድና ከመሠረትን ፈጽሞ አያሳፍረንም። ፈጣሪያችን እንዲህ ይላል:- “እኔ የሚረባህን ነገር የማስተምርህ በምትሄድባትም መንገድ የምመራህ አምላክህ እግዚአብሔር ነኝ።”—ኢሳይያስ 48:17
ብዙዎች በአምላክ መመካታቸው ጠቅሟቸዋል። ለምሳሌ፣ ማራ አንድ ልጅዋን በመኪና አደጋ ያጣችው ለረዥም ጊዜ የቆየ የመንፈስ ጭንቀት አዳክሟት እያለ ነበር።a የምትይዘው የምትጨብጠው ስለጠፋት ራሷን ለመግደል ሞከረች። አሁን ግን ማራ ሁልጊዜ ጠዋት ተነስታ የቤት ውስጥ ሥራዎቿን ታከናውናለች። ሙዚቃ ማዳመጥና ሌሎችን መርዳት ያስደስታታል። “ጻድቃንም ዓመፀኞችም ከሙታን” እንደሚነሱ የሚናገረው የመጽሐፍ ቅዱስ ተስፋ የምትወደው ልጅዋ አሳዛኝ ሞት ያስከተለባትን መሪር ሐዘን እንድትቋቋም ከማድረጉም በላይ በአምላክ ላይ ያላትን እምነት አጠንክሮላታል። (ሥራ 24:15) ማራ በሰማይ እንዳሉት መላእክት የመሆን ፍላጎት ስላልነበራት መዝሙር 37:11 ላይ የሚገኙት ቃላት ልቧን ነክተዋታል። “ገሮች ግን ምድርን ይወርሳሉ፣ በብዙም ሰላም ደስ ይላቸዋል።”
ሳንድራ የተባለች ሌላ ብራዚላዊት ሴት ደግሞ ለሦስት ልጆቿ ጥሩ እናት ለመሆን ከፍተኛ ጥረት አድርጋለች። እንዲህ ስትል ሳትሸሽግ ተናግራለች:- “የአባቴ ድንገተኛ ሞት ከፍተኛ ውጥረት አስከትሎብኝ እያለ ባለቤቴ ከሌላ ሴት ጋር እንደሚማግጥ ተገነዘብኩ። በዚህ ወቅት አምላክ እንዲረዳኝ እንኳ ስለመጸለይ አላሰብኩም።” ሳንድራ ተስፋ ስለቆረጠች ራሷን የመግደል ሙከራ አደረገች። ሳንድራ የደረሰባትን መከራ እንድትቋቋም የረዳት ምን ነበር? ለመንፈሳዊ ነገሮች የነበራት አድናቆት ነው። “በእያንዳንዱ ምሽት ከመተኛቴ በፊት መጽሐፍ ቅዱስ አነብባለሁ እንዲሁም ታሪካቸውን በማነበው ሰዎች ቦታ ራሴን ለማስቀመጥ እሞክራለሁ። በተጨማሪም መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶችን አነባለሁ። በተለይ በእነዚህ መጽሔቶች ላይ የሚወጡትን የሕይወት ታሪኮች ማንበብ በጣም ያስደስተኛል። እነዚህ ተሞክሮዎች በሕይወቴ ረክቼ እንድኖር ትልቅ እርዳታ አበርክተውልኛል።” ሳንድራ ይሖዋ የቅርብ ጓደኛዋ እንደሆነ በመገንዘብ በምትጸልይበት ጊዜ የምትፈልገውን ነገር ለይታ መጥቀስን ተምራለች።
ተስፋ መቁረጥ የማይኖርበት ጊዜ
በሰው ልጆች ላይ የሚደርሰው መከራ ጊዜያዊ መሆኑን ማወቁ እንዴት ያጽናናል! በአሁኑ ጊዜ የወንጀል፣ የግፍ ወይም የጭፍን ጥላቻ ሰለባ የሆኑት ልጆችና አዋቂዎች በአምላክ መንግሥት ሥር ደስ ይላቸዋል። ትንቢታዊ ይዘት ባለው አንድ መዝሙር ላይ አስቀድሞ እንደተነገረው ይሖዋ የሾመው ንጉሡ ኢየሱስ ክርስቶስ “ችግረኛውን [“የእርዳታ ጥሪ የሚያሰማውን፣” NW ] ከቀማኛው እጅ፣ ረዳት የሌለውንም ምስኪን ያድነዋልና።” ከዚህም በላይ “ለችግረኛና ለምስኪን ይራራል፣ የችግረኞችንም ነፍስ ያድናል።” በእርግጥም “ከግፍና ከጭንቀት ነፍሳቸውን ያድናል፤ ስማቸው በፊቱ ክቡር ነው።”—መዝሙር 72:12-14
የእነዚህ ትንቢታዊ ቃላት ፍጻሜ ቀርቧል። እንዲህ በመሰሉት ሁኔታዎች ሥር በምድር ላይ የዘላለም ሕይወት አግኝቶ በደስታ የመኖሩ ሐሳብ ያስደስትሃል? ከሆነ ደስተኛ የምትሆንበትና ሕይወትን ከአምላክ የተገኘ ስጦታ አድርገህ በመቁጠር የምትንከባከብበት ጥሩ ምክንያት አለህ። እነዚህን አጽናኝ የሆኑ ቅዱስ ጽሑፋዊ ተስፋዎች በዚህ ስሜት አልባና ፍቅር በጎደለው ዓለም ውስጥ የእርዳታ ጥሪ በማሰማት ላይ ላሉት ሰዎች በማካፈል ሕይወታቸው አስደሳች እንዲሆን ማድረግ ትችል ይሆናል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በዛሬው ጊዜ ለመደሰት የሚያስችሉ ብዙ አጋጣሚዎች አሉ
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ተስፋ መቁረጥ የሌለበትን ዓለም ትናፍቃለህ?