ከሚያምኑት ወገን ነን
በፊጂ ደሴቶች የአምላክን መንግሥት ማስታወቅ
ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ሁለት መንገዶች ተናግሮ ነበር። አንደኛው ሰፊና ወደ ሞት የሚወስድ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ጠባብና ወደ ሕይወት የሚያደርስ ነው። (ማቴዎስ 7:13, 14) ይሖዋ አምላክ ሰዎች ትክክለኛውን ምርጫ እንዲያደርጉ ለመርዳት ሲል የመንግሥቱ ምሥራች በዓለም ሁሉ እንዲሰበክ አድርጓል። (ማቴዎስ 24:14) በዚህም ምክንያት በሁሉም ቦታዎች የሚገኙ ሰዎች የመንግሥቱን መልእክት በማዳመጥ ላይ ሲሆኑ ከእነዚህም መካከል አንዳንዶቹ “ነፍሳቸውን ሊያድኑ ከሚያምኑቱ” ወገን በመሆን ሕይወትን በመምረጥ ላይ ናቸው። (ዕብራውያን 10:39) በፊጂና በአካባቢው በሚገኙት የደቡባዊ ፓስፊክ ሌሎች ደሴቶች ላይ የሚኖሩ አንዳንድ ሰዎች ለሕይወት ያደረጉትን ምርጫ በሚመለከት እንድታነብ እንጋብዝሃለን።
በይሖዋ ታምነዋል
ሜሬ የመንግሥቱን መልእክት የሰማችው በ1964 ገና ተማሪ ሳለች ነው። የምትኖረው ራቅ ባለ ደሴት ላይ ከመሆኑ የተነሣ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር የምትገናኝበት አጋጣሚ አልነበረም ለማለት ይቻላል። ይሁን እንጂ ሜሬ ውሎ አድሮ የመጽሐፍ ቅዱስን ትክክለኛ እውቀት አገኘች። በዚህ ጊዜ የመንደሩ የጎሳ አለቃ የሆነ አንድ ሰው አግብታ ነበር። ሜሬ ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር ተስማምታ ለመኖር በመምረጧ ባሏና የእርሱ ዘመዶች ጭካኔ የተሞላበት ስደት አደረሱባት። የመንደሩ ነዋሪዎችም በንቀት ይመለከቷት ነበር። ሜሬ ይህ ሁሉ ነገር ቢደርስባትም በ1991 ተጠመቀች።
ከጥቂት ጊዜ በኋላ ቾሱዋ የተባለው ባሏ አመለካከቱን እያስተካከለ መጣ። እንዲያውም ሜሬ ከልጆቹ ጋር የመጽሐፍ ቅዱስ ውይይት በምታደርግበት ጊዜ ቁጭ ብሎ ማዳመጥ ጀመረ። ወደ ሜቶዲስት ቤተ ክርስቲያን መሄዱን አቆመ። ሆኖም አለቃ እንደመሆኑ መጠን የመንደሩ ነዋሪዎች በየሳምንቱ በሚያደርጓቸው ስብሰባዎች ላይ ሊቀ መንበር ሆኖ ማገልገሉን ቀጥሎ ነበር። የሜቶዲስት ቤተ ክርስቲያንና የፊጂ መንደር ሕይወት የማይነጣጠሉ በመሆናቸው ቾሱዋ ያደረገው ነገር በመንደርተኞቹ አመለካከት ታማኝነት የጎደለው ድርጊት ነበር። በዚህም ምክንያት ቾሱዋ ወደ ቀድሞ ሃይማኖቱ እንዲመለስ የመንደሩ ቄስ አጥብቆ ለመነው።
ቾሱዋ እርሱና ቤተሰቡ የራሳቸውን ምርጫ እንዳደረጉና ይሖዋን “በመንፈስና በእውነት” ለማምለክ እንደቆረጡ በድፍረት ተናገረ። (ዮሐንስ 4:24) በቀጣዩ ስብሰባ ላይ የመንደሩ ዋና አለቃ ቾሱዋንና ቤተሰቡን በማግለል መንደሩን ለቅቀው እንዲሄዱ ውሳኔ አስተላለፈ። ቤታቸውን መሬታቸውንና እርሻቸውን እንኳ ሳይቀር በመተው ደሴቱን ለቅቀው እንዲሄዱ ሰባት ቀን ተሰጣቸው። አዎን፣ ይህ ቤተሰብ መተዳደሪያውን በሙሉ አጥቷል።
በሌላ ደሴት የሚኖሩ መንፈሳዊ ወንድሞች ለቾሱዋና ለቤተሰቡ የመኖሪያ ቤትና የእርሻ መሬት በመስጠት በችግራቸው ደረሱላቸው። በአሁኑ ጊዜ ቾሱዋና የመጀመሪያ ወንድ ልጁ የተጠመቁ ሲሆን ሌላኛው ልጁ ደግሞ ያልተጠመቀ የምሥራቹ አስፋፊ በመሆን ያገለግላል። ሜሬ በቅርቡ የዘወትር አቅኚ (የሙሉ ጊዜ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪ) በመሆን ማገልገል ጀምራለች። ይሖዋን ለማገልገል መምረጣቸው ከፍ ያለ ቦታቸውንና ንብረታቸውን ቢያሳጣቸውም ልክ እንደ ሐዋርያው ጳውሎስ እነርሱም የደረሰባቸው መከራ ካገኙት ነገር ጋር ሲወዳደር ከቁጥር እንደማይገባ ሆኖ ይሰማቸዋል።—ፊልጵስዩስ 3:8
ሕሊናን የሚመለከት ምርጫ
በመጽሐፍ ቅዱስ የሠለጠነ ሕሊናን መታዘዝ እምነትና ድፍረት ይጠይቃል። ይህ ሁኔታ ከኪሪባቲ ደሴቶች መካከል ታራዋ በተባለው ደሴት ላይ በምትኖረውና በቅርቡ በተጠመቀችው በወጣቷ ሱራንግ ላይ ደርሶ ነበር። ሱራንግ ነርስ ስትሆን ከሆስፒታል ሥራዋ መካከል መሥራት የማትፈልገው ነገር እንዳለ አሳወቀች። ሆኖም ይህ ጥያቄዋ ተቀባይነት አላገኘም። እንዲያውም በዚሁ ምክንያት ገለልተኛ ደሴት ላይ በሚገኝ አንድ አነስተኛ የሕክምና ማዕከል ውስጥ እንድትሠራ ተመደበች። ይህም ከእምነት አጋሮቿ እንድትለይ አደረጋት።
ወደዚህ ደሴት ለመጀመሪያ ጊዜ የሚመጡ እንግዶች አካባቢውን ለሚቆጣጠረው “መንፈስ” መሥዋዕት ማቅረባቸው የተለመደ ነው። የደሴቲቱ ነዋሪዎች ይህንን አለማድረግ ሞት እንደሚያስከትል ያምናሉ። ሱራንግ ይህ የጣዖት አምልኮ ድርጊት ለእርሷም ሆነ ለሥራ ባልደረቦቿ እንዲከናወን ፈቃደኛ ባለመሆኗ መንደርተኞቹ የተቆጣው መንፈስ አንቆ ሲገድላት ለማየት ይጠባበቁ ነበር። ሆኖም በሱራንግም ሆነ በባልደረቦቿ ላይ ምንም ዓይነት ጉዳት ባለመድረሱ ሁኔታው ጥሩ ምሥክርነት ለመስጠት የሚያስችሉ ብዙ አጋጣሚዎች ከፍቶላታል።
ይሁን እንጂ የሱራንግ ፈተና በዚህ ብቻ አላበቃም። በደሴቲቱ የሚኖሩ አንዳንድ ወጣቶች ለጉብኝት የመጡትን ሴቶች የፆታ ብልግና እንዲፈጽሙ ማባበልን ልክ እንደ ጀብዱ ይቆጥሩታል። ሆኖም ሱራንግ የወጣቶቹን ተጽዕኖ ተቋቁማ ለአምላክ ያላትን ጽኑ አቋም ጠብቃለች። እንዲያውም ነርስ እንደመሆኗ መጠን በቀኑ 24 ሰዓታት ውስጥ በማንኛውም ጊዜ ለሥራ የምትጠራበት አጋጣሚ ቢኖርም የዘወትር አቅኚ ሆና ማገልገል ችላለች።
ሱራንግ ደሴቱን ለቅቃ ልትሄድ ስትል ለእርሷ ክብር ከተዘጋጀው ግብዣ ትንሽ ቀደም ብሎ የመንደሩ ሽማግሌዎች እነርሱን ለመጎብኘት የመጣች የመጀመሪያዋ እውነተኛ ሚስዮናዊት እንደሆነች ተናግረዋል። ሱራንግ ለመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች በነበራት ጽኑ አቋም ምክንያት ሌሎች የደሴቲቱ ነዋሪዎች ለመንግሥቱ መልእክት ጥሩ ምላሽ ሰጥተዋል።
ሌሎች ፈታኝ ሁኔታዎች
የአንዳንድ መንደሮች መራራቅ የይሖዋ ሕዝቦች በአገልግሎቱ ለመካፈልና በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ለመገኘት ከፍተኛ ጥረት እንዲያደርጉ ጠይቆባቸዋል። ለምሳሌ፣ ወደ ስብሰባዎች በመሄድና በመምጣት ብዙ ሰዓታት የሚያሳልፉትን የአንድ ወንድምና የሦስት እህቶች ሁኔታ ተመልከት። ወደ ስብሰባዎች ለመሄድ ብቻ ሦስት ጊዜ ወንዝ ማቋረጥ ይኖርባቸዋል። ወንዙ በሚሞላበት ወቅት ወንድም ቦርሳቸውን፣ መጽሐፋቸውንና የስብሰባ ልብሳቸውን የያዘውን አንድ ትልቅ ድስት ይዞ አስቀድሞ በዋና ካቋረጠ በኋላ ተመልሶ በመምጣት ሦስቱ እህቶች እንዲሻገሩ ይረዳቸው ነበር።
ኪሪባቲ ውስጥ ኖኖቲ በተባለች አንድ ገለልተኛ ደሴት ላይ በሚደረገው ስብሰባ ላይ የሚገኝ አንድ ቡድን ደግሞ ለየት ያለ ፈተና ገጥሞታል። ስብሰባ የሚያደርጉበት ቤት መያዝ የሚችለው ሰባት ወይም ስምንት ሰዎችን ብቻ ስለሆነ የተቀሩት ውጪ ተቀምጠው ከሽቦ በተሠራው ግድግዳ ቀዳዳ አሾልቀው በመመልከት ስብሰባውን ይከታተላሉ። ይህ የስብሰባ ቦታ በአስደናቂ ሁኔታ ወደተገነቡ ቤተ ክርስቲያኖቻቸው ለሚሄዱትና ከዚያ ለሚመጡት የመንደሩ ነዋሪዎች እይታ የተጋለጠ ነው። እርግጥ ነው፣ በአምላክ ፊት ዋጋ ያላቸው ሰዎች እንጂ ሕንጻዎች እንዳልሆኑ የይሖዋ አገልጋዮች ይገነዘባሉ። (ሐጌ 2:7) በዚህ ደሴት የሚኖሩ አንዲት እህት በጣም ከማርጀታቸው የተነሣ ረዘም ያለ ጉዞ ማድረግ አይችሉም። ሆኖም አንዲት ያልተጠመቀች ወጣት አስፋፊ በጋሪ እየገፋች ወደ አገልግሎት በመውሰድ ትረዳቸዋለች። ለእውነት ያላቸው አድናቆት እንዴት የሚያስገርም ነው!
ከ2,100 በላይ የሚሆኑት በፊጂ የሚገኙ አስፋፊዎች ስለ አምላክ መንግሥት የሚናገረውን ምሥራች ማወጃቸውን ለመቀጠል ቁርጥ ውሳኔ አድርገዋል። ገና ብዙ ሰዎች “ነፍሳቸውን ሊያድኑ ከሚያምኑቱ” ወገን እንደሚሆኑም እርግጠኞች ናቸው።
[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ካርታ]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
አውስትራሊያ
ፊጂ