የአንባብያን ጥያቄዎች
ሦስቱ ዕብራውያን ናቡከደነፆር በዱራ ሜዳ ባቆመው ግዙፍ ምስል ፊት እንዲሰግዱ በተፈተኑ ጊዜ ዳንኤል የት ነበር?
መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ጉዳይ ምንም ስለማይናገር በዛሬውም ጊዜ ዳንኤል በፈተናው ወቅት የት እንደነበር አስረግጦ ሊናገር የሚችል ማንም ሰው የለም።
አንዳንዶች ዳንኤል የነበረው የመንግሥት ሥልጣን ወይም በናቡከደነፆር ፊት ያገኘው የተለየ ሞገስ ከሲድራቅ፣ ከሚሳቅና ከአብደናጎ ይበልጥ ስለነበር ወደ ዱራ ሜዳ ለመሄድ አልተገደደም የሚል አስተያየት ሰጥተዋል። ዳንኤል 2:49 ዳንኤል በአንድ ወቅት ከሦስቱ ጓደኞቹ የሚበልጥ ሥልጣን እንደነበረው ይጠቁማል። ሆኖም ይህ ከሌሎች ጋር በምስሉ ፊት ከመገኘት ነፃ ያደርገዋል ብለን ማረጋገጥ አንችልም።
ሌሎች ደግሞ ለመንግሥት ሥራ ጉዳይ ወደ ሌላ ቦታ ሄዶ ወይም በሕመም ምክንያት መገኘት አልቻለ ይሆናል በማለት ዳንኤል በወቅቱ ያልተገኘበትን ምክንያት ለማብራራት ሞክረዋል። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ እንደዚህ አይልም። ያም ሆነ ይህ ዳንኤል የወሰደው እርምጃ ለነቀፋ መንገድ የሚከፍት አልነበረም። እንደዚያ ቢሆን ኖሮ በቅንዓት የበገኑት የባቢሎን ባለ ሥልጣናት እርሱን ለመክሰስ ይጠቀሙበት ነበር። (ዳንኤል 3:8) ዳንኤል ከዚህ አጋጣሚ በፊትም ሆነ በኋላ ምንም ዓይነት ፈተና ቢገጥመው ለአምላክ ታማኝ በመሆን ፍጹም አቋም ጠባቂ መሆኑን አረጋግጧል። (ዳንኤል 1:8፤ 5:17፤ 6:4, 10, 11) ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ ዳንኤል በዱራ ሜዳ ያልነበረበትን ምክንያት ባይናገርም ዳንኤል ያለማወላወል ለይሖዋ አምላክ ታማኝ እንደነበር እርግጠኞች መሆን እንችላለን።—ሕዝቅኤል 14:14፤ ዕብራውያን 11:33