መንፈሳዊ የልብ ድካም እንዳይዝህ መከላከል ትችላለህ
ከፍተኛ ብቃት የነበረውና ከላይ ለሚያየው ጠንካራ የሰውነት አቋም ያለው የሚመስል አንድ ታዋቂ አትሌት በልምምድ ላይ ሳለ ምን ነካው ሳይባል ተዝለፍልፎ ወደቀና ሞተ። ይህ አትሌት በበረዶ ላይ ሸርተቴ ሁለት ጊዜ የኦሎምፒክ የወርቅ ሜዳልያ ተሸላሚ የሆነውና በስፖርቱ ዓለም ገና ታዋቂነትን በማትረፍ ላይ ሳለ በ28 ዓመት ዕድሜው የተቀጨው ሰርጊዬ ግሪንኮፍ ነው። ምንኛ ያሳዝናል! የሞቱ መንስኤ ምን ነበር? የልብ ድካም። ሰርጊዬ አንዳችም የልብ ሕመም ምልክት ስላልታየበት ሞቱ ድንገተኛ እንደነበረ ተነግሯል። ይሁን እንጂ ሐኪሞች ባደረጉት ምርመራ ሰርጊዬ የልብ ችግር እንደነበረበትና ልብ ደም ወሳጅ ቧንቧው ሙሉ ለሙሉ ማለት ይቻላል ተደፍኖ እንደነበረ ደርሰውበታል።
አብዛኛውን ጊዜ የልብ ድካም የሚከሰተው ድንገት ቢመስልም የሕክምና ባለሙያዎች ብዙውን ጊዜ ሁኔታው ከዚያ የተለየ እንደሆነ ይናገራሉ። እውነታው እንደሚያሳየው የትንፋሽ ቁርጥ ቁርጥ ማለት፣ የክብደት መጨመር፣ የደረት ሕመምና የመሳሰሉት የማስጠንቀቂያ ምልክቶች አብዛኛውን ጊዜ ችላ ይባላሉ። ከዚህም የተነሣ በሽታው ለሞት ባያደርሳቸው እንኳ ብዙዎች ቀሪ ሕይወታቸውን ከባድ የአካል ጉዳተኛ ሆነው ለማሳለፍ ይገደዳሉ።
የልብ ድካምን ለመከላከል በአመጋገብና በአኗኗር ረገድ ያልተቋረጠ ጥንቃቄ ማድረግን ጨምሮ በየጊዜው የሕክምና ክትትል ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን የሕክምና ባለሙያዎች ይስማሙበታል።a አንድ ሰው እነዚህን እርምጃዎች ከወሰደና አስፈላጊ ሲሆን ለውጥ ለማድረግ ልባዊ ፈቃደኝነት ካሳየ ልብ ድካም የሚያስከትላቸውን አስከፊ መዘዞች ማስቀረት የሚችልበት አጋጣሚ ሰፊ ይሆናል።
ይሁን እንጂ ይበልጥ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ሌላ የልባችን ዘርፍም አለ። መጽሐፍ ቅዱስ “አጥብቀህ ልብህን ጠብቅ” በማለት ያስጠነቅቃል። “የሕይወት መውጫ ከእርሱ ነውና።” (ምሳሌ 4:23) እርግጥ ይህ ጥቅስ በዋነኛነት የሚናገረው ስለ ምሳሌያዊው ልብ ነው። ሥጋዊ ልባችንን ለመጠበቅ ንቁ መሆን አስፈላጊ ነው። ይሁን እንጂ ምሳሌያዊ ልባችንንም ሞት ከሚያስከትሉ አደጋዎች ለመጠበቅ ከፈለግን ይበልጥ ንቁ መሆን ይኖርብናል።
የምሳሌያዊ ልብ ድካም የተለያዩ ገጽታዎች
ሥጋዊ የልብ ድካምን ለመከላከል የሚያስችሉ አንዳንድ መንገዶች እንዳሉ ሁሉ በመንፈሳዊ ሁኔታ የሚያጋጥመውን የልብ ድካም ለመከላከል ከሚያስችሉት አስተማማኝ መንገዶች መካከል አንደኛው የበሽታውን መንስኤ መገንዘብና ተስማሚ እርምጃ መውሰድ ነው። በሥጋዊም ሆነ በምሳሌያዊ ልብ ላይ ችግር የሚያስከትሉትን አንዳንድ መሠረታዊ ነገሮች እስቲ እንመልከት።
አመጋገብ። ምንም ገንቢነት የሌለው ምግብ ሲበሉት ቢጣፍጥም ለሰውነት አስፈላጊውን ጥቅም እንደማይሰጥ የታወቀ ነው። በተመሳሳይም አሸር ባሸር የሆነና ስሜትን የሚማርክ የአእምሮ ምግብ በቀላሉ ማግኘት የሚቻል ቢሆንም እንዲህ ዓይነቱ ምግብ ለአንድ ሰው መንፈሳዊ ጤንነት ጎጂ ነው። በጥንቃቄ ታስቦባቸው የተዘጋጁና ልቅ ወሲብን፣ አደገኛ ዕፆች መውሰድን፣ ዓመፅንና መናፍስታዊ ድርጊቶችን የሚያስፋፉ መዝናኛዎች በመገናኛ ብዙኃን በገፍ ይቀርባሉ። አንድ ሰው አእምሮውን እንዲህ ባሉት ነገሮች የሚመግብ ከሆነ ለምሳሌያዊው ልብ እጅግ አደገኛ ነው። የአምላክ ቃል የሚከተለውን በማለት ያስጠነቅቃል:- “በዓለም ያለው ሁሉ እርሱም የሥጋ ምኞትና የዓይን አምሮት ስለ ገንዘብም መመካት ከዓለም ስለ ሆነ . . . ከአባት [አይደለም።] . . . ዓለሙም ምኞቱም ያልፋሉ፤ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ ግን ለዘላለም ይኖራል።”—1 ዮሐንስ 2:15-17
አትክልትና አረንጓዴ ቅጠላ ቅጠሎችን የመሳሰሉ ለጤና ተስማሚ የሆኑ ምግቦች ምንም ገንቢነት የሌላቸውን ጣፋጭ ምግቦች የመመገብ ልማድ የተጠናወተውን ሰው እምብዛም ላይማርኩት ይችላሉ። በተመሳሳይም ጤናማና ጠንከር ያሉ መንፈሳዊ ምግቦች አእምሮውንና ልቡን ዓለማዊ ነገሮችን መመገብ ለለመደ ሰው እምብዛም አይማርኩት ይሆናል። እንዲህ ዓይነቱ ሰው የአምላክን ቃል “ወተት” እየተመገበ ለተወሰነ ጊዜ ይቆይ ይሆናል። (ዕብራውያን 5:13) ሆኖም ከጊዜ በኋላ በክርስቲያን ጉባኤና በአገልግሎት ረገድ ያሉበትን መሠረታዊ የሆኑ መንፈሳዊ ኃላፊነቶች ለመወጣት የሚያስችለውን መንፈሳዊ ጉልምስና ሳያዳብር ይቀራል። (ማቴዎስ 24:14፤ 28:19፤ ዕብራውያን 10:24, 25) እንዲህ ባለ ሁኔታ ውስጥ የገቡ አንዳንዶች መንፈሳዊ ጥንካሬያቸው እጅግ ከመዳከሙ የተነሣ እስከ መቀዝቀዝና እምነታቸውን እስከ መተው ደርሰዋል!
ሌላው አደጋ ደግሞ ውጫዊ መልክ ሊያሳስት መቻሉ ነው። በቁሳዊ ነገሮች ላይ የተመሠረቱ ፍልስፍናዎች ወይም የጾታ ብልግናን፣ ዓመፅንና መናፍስታዊ ድርጊቶችን በሚያሳዩ መዝናኛዎች የመጠመድ ስውር ልማድ በሚያሳድረው ተጽእኖ እየተባባሰ የሚሄድ ሕመም ያለበት ልብ እውነተኛ ገጽታ በዘልማድ በሚከናወኑ ውጫዊ ክርስቲያናዊ ተግባራት ሊሸፈን ይችላል። እንዲህ ያለው መጥፎ መንፈሳዊ የአመጋገብ ልማድ በአንድ ሰው መንፈሳዊነት ላይ የሚያሳድረው ተጽእኖ ቀላል ሊመስል ይችላል። ሆኖም ጤናማ ያልሆነ የአመጋገብ ልማድ የደም ወሳጅ ግድግዳዎችን በማደንደን በሥጋዊው ልብ ላይ ጉዳት እንደሚያደርስ ሁሉ ይህ ዓይነቱ ደካማ መንፈሳዊ የአመጋገብ ልማድም ምሳሌያዊውን ልብ ሊያዳክመው ይችላል። ኢየሱስ፣ አንድ ሰው በልቡ ውስጥ ተገቢ ያልሆኑ ፍላጎቶች እንዲቀሰቀሱ መፍቀዱ የሚያስከትለውን አደጋ በተመለከተ ሲያስጠነቅቅ የሚከተለውን ብሏል:- “ወደ ሴት ያየ ሁሉ የተመኛትም ያን ጊዜ በልቡ ከእርስዋ ጋር አመንዝሮአል።” (ማቴዎስ 5:28) አዎን፣ ደካማ መንፈሳዊ የአመጋገብ ልማድ መንፈሳዊ የልብ ድካም ሊያስከትል ይችላል። ሆኖም ሊታሰብባቸው የሚገቡ ሌሎች ነገሮችም አሉ።
የሰውነት እንቅስቃሴ። ብዙ እንቅስቃሴ የማይጠይቅ አኗኗር ሥጋዊ የልብ ድካም ሊያስከትል እንደሚችል የታወቀ ነው። በተመሳሳይም በመንፈሳዊ ሁኔታ እንቅስቃሴ አልባ ሕይወት መምራት አደገኛ ሁኔታዎችን ሊያስከትል ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ሰው በክርስቲያናዊ አገልግሎት የተወሰነ ተሳትፎ ያደርግ ይሆናል። ነገር ግን ምቾቱ እንዳይነካ በማሰብ ‘የእውነትን ቃል በቅንነት የሚናገር የማያሳፍርም ሠራተኛ በመሆን፣ የተፈተነውን ራሱን ለእግዚአብሔር ለማቅረብ’ አይተጋ አሊያም ከናካቴው ምንም ዓይነት ጥረት አያደርግ ይሆናል። (2 ጢሞቴዎስ 2:15) ወይም አንድ ሰው በአንዳንድ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ይገኝ ይሆናል። ሆኖም ለስብሰባዎቹ ለመዘጋጀትም ሆነ ተሳትፎ ለማድረግ አይጥር ይሆናል። መንፈሳዊ ግብም ሆነ መንፈሳዊ ነገሮችን የማንበብ ፍላጎትና ጉጉት አይኖረው ይሆናል። መንፈሳዊ እንቅስቃሴ አለማድረጉ በአንድ ወቅት የነበረውን እምነት እንኳ ሳይቀር ሊያዳክምበት ብሎም ጨርሶ ሊያጠፋበት ይችላል። (ያዕቆብ 2:26) ሐዋርያው ጳውሎስ ለዕብራውያን ክርስቲያኖች ሲጽፍ እንዲህ ያለውን አደጋ አስተውሎ ነበር። ከእነዚህ ክርስቲያኖች መካከል አንዳንዶቹ በመንፈሳዊ አነጋገር እንቅስቃሴ አልባ ሕይወት በመምራት ወጥመድ ተይዘው ነበር። ጳውሎስ እንዲህ ዓይነቱ አኗኗር በመንፈሳዊነታቸው ላይ ሊያስከትል የሚችለውን የማደንደን አደጋ አስመልክቶ የሰጠውን ማስጠንቀቂያ ልብ በል:- “ወንድሞች ሆይ፣ ምናልባት ሕያው እግዚአብሔርን የሚያስክዳችሁ ክፉና የማያምን ልብ ከእናንተ በአንዳችሁ እንዳይኖር ተጠንቀቁ፤ ነገር ግን ከእናንተ ማንም በኃጢአት መታለል እልከኛ እንዳይሆን፣ ዛሬ ተብሎ ሲጠራ ሳለ፣ በእያንዳንዱ ቀን እርስ በርሳችሁ ተመካከሩ።”—ዕብራውያን 3:12, 13
ውጥረት። ሌላው የሥጋዊ ልብ ድካም ዋነኛ መንስኤ ደግሞ ከልክ በላይ መጨነቅ ነው። በተመሳሳይም ውጥረት ወይም ‘የኑሮ ጭንቀቶች’ ለምሳሌያዊው ልብ ጤንነት አደገኛ ሊሆኑ ይችላሉ። እንዲያውም እነዚህ ነገሮች ግለሰቡ ሙሉ በሙሉ አምላክን ማገልገሉን እንዲያቆም ሊያደርጉት ይችላሉ። በዚህ ረገድ ኢየሱስ የሰጠው ማስጠንቀቂያ ወቅታዊ ነው:- “ነገር ግን ልባችሁ በመጠጥ ብዛትና በስካር ስለ ትዳርም በማሰብ [“ስለ ኑሮ በመጨነቅ፣” አ.መ.ት ] እንዳይከብድ፣ ያ ቀንም በድንገት እንዳይመጣባችሁ ለራሳችሁ ተጠንቀቁ፤ በምድር ሁሉ ላይ በሚቀመጡ ሁሉ እንደ ወጥመድ ይደርስባቸዋልና።” (ሉቃስ 21:34, 35) የሠራነውን ኃጢአት ሰውረን ለረዥም ጊዜ ከያዝነው ውጥረት በምሳሌያዊው ልባችን ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል። ንጉሥ ዳዊት እንዲህ ካለው ጎጂ ውጥረት ጋር ተያይዞ የሚመጣውን ስቃይ ከተሞክሮ አይቷል። እንዲህ ብሏል:- “ከኃጢአቴም የተነሣ ለአጥንቶቼ ሰላም የላቸውም። ኃጢአቴ በራሴ ላይ ከፍ ከፍ ብሎአልና፣ እንደ ከባድ ሸክምም በላዬ ከብዶአልና።”—መዝሙር 38:3, 4
ከልክ በላይ በራስ መተማመን። አብዛኞቹ የልብ ድካም በሽታ ሰለባዎች ሕመሙ እንዳለባቸው ከመገንዘባቸው በፊት ስለ ጤንነታቸው በጣም እርግጠኞች ነበሩ። አብዛኛውን ጊዜ የጤና ምርመራ ማድረግ ችላ ይባላል አሊያም አላስፈላጊ እንደሆነ ተደርጎ ይወሰዳል። በተመሳሳይም አንዳንዶች በክርስትና ጎዳና የተወሰነ ጊዜ በማሳለፋቸው ምክንያት ምንም ነገር እንደማይደርስባቸው ሆኖ ይሰማቸዋል። አንድ ዓይነት አደጋ እስኪደርስባቸው ድረስ መንፈሳዊ ምርመራም ሆነ በራሳቸው ላይ ፍተሻ ማድረጋቸውን ችላ ይሉ ይሆናል። ሐዋርያው ጳውሎስ ከመጠን በላይ በራስ የመተማመንን አደጋ አስመልክቶ የሰጠውን ጥሩ ምክር ልብ ማለቱ በጣም አስፈላጊ ነው። “እንደ ቆመ የሚመስለው እንዳይወድቅ ይጠንቀቅ።” ስለዚህ ፍጽምና የሌለን መሆናችንን አምኖ መቀበልና በራሳችን ላይ ዘወትር መንፈሳዊ ምርመራ ማድረግ ጥበብ ነው።—1 ቆሮንቶስ 10:12፤ ምሳሌ 28:14
የማስጠንቀቂያ ምልክቶቹን ችላ አትበሉ
ቅዱሳን ጽሑፎች ምሳሌያዊው ልብ ለሚገኝበት ሁኔታ የበለጠ ትኩረት መስጠታቸው የተገባ ነው። በኤርምያስ 17:9, 10 ላይ እንዲህ የሚል እናነባለን:- “የሰው ልብ ከሁሉ ይልቅ ተንኰለኛ እጅግም ክፉ ነው፤ ማንስ ያውቀዋል? እኔ እግዚአብሔር ለሰው ሁሉ እንደ መንገዱ፣ እንደ ሥራው ፍሬ እሰጥ ዘንድ ልብን እመረምራለሁ ኩላሊትንም እፈትናለሁ።” ይሁን እንጂ ይሖዋ ልባችንን ከመፈተንም በተጨማሪ ራሳችንን እንድንመረምር የሚያስችሉ ፍቅራዊ ዝግጅቶችም አድርጎልናል።
‘በታማኝና ልባም ባሪያ’ በኩል ወቅታዊ ማሳሰቢያዎች ይቀርቡልናል። (ማቴዎስ 24:45) ለምሳሌ ያህል፣ ምሳሌያዊው ልባችን ሊያታልለን ከሚችልባቸው ዋና ዋና መንገዶች መካከል አንዱ በዓለማዊ ቅዠቶች እንድንዋጥ ማድረግ ነው። ይህም ከእውነታው ውጪ በሆኑ ሐሳቦች፣ በቀን ቅዠቶችና አእምሮአችን በሚፈጥራቸው ሐሳቦች መዋጥን ይጨምራል። እነዚህ ነገሮች በተለይ በአእምሮአችን ንጹህ ያልሆኑ ሐሳቦች እንዲጸነሱ የሚያደርጉ ከሆነ በጣም አደገኛ ሊሆኑ ይችላሉ። ስለዚህ እንዲህ ዓይነቶቹን ቅዠቶች ሙሉ በሙሉ ማስወገድ ይኖርብናል። ኢየሱስ እንዳደረገው ዓመፅን የምንጠላ ከሆነ ዓለማዊ ቅዠቶች በልባችን ውስጥ ሥር እንዳይሰዱ መከላከል እንችላለን።—ዕብራውያን 1:8, 9
ከዚህም በተጨማሪ የክርስቲያን ጉባኤ ሽማግሌዎች ፍቅራዊ እርዳታም አለልን። የሌሎች አሳቢነት የሚደነቅ ቢሆንም ለምሳሌያዊ ልባችን እንክብካቤ የማድረጉ ኃላፊነት በእያንዳንዳችን ላይ የወደቀ ነው። ‘ሁሉንም ነገር መፈተኑ’ እንዲሁም ‘በሃይማኖት ብንኖር ራሳችንን መመርመሩና መፈተኑ’ የእኛው ኃላፊነት ነው።—1 ተሰሎንቄ 5:20, 21፤ 2 ቆሮንቶስ 13:5
ልብህን ጠብቅ
“ሰው የሚዘራውን ሁሉ ያንኑ ደግሞ ያጭዳልና” የሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት የምሳሌያዊውን ልባችንን ጤንነት በተመለከተም ይሠራል። (ገላትያ 6:7) አብዛኛውን ጊዜ ድንገተኛ መንፈሳዊ አደጋ መስሎ የሚታየው ነገር ወሲባዊ ሥዕሎች መመልከትን፣ ለቁሳዊ ነገሮች ከመጠን በላይ መጨነቅን አለዚያም ሥልጣን ወይም ክብር ለማግኘት መጣርን የመሳሰሉ በመንፈሳዊ ሊጎዱ የሚችሉ የረጅም ጊዜ ድብቅ ልማዶች ያስከተሉት ውጤት ሆኖ ይገኛል።
እንግዲያው ልቡን መጠበቅ የሚፈልግ ማንኛውም ሰው መንፈሳዊ የአመጋገብ ልማዱን ዘወትር መመርመር ይኖርበታል። የአምላክን ቃል በማንበብ አእምሮህንና ልብህን መግብ። በየቦታው ተስፋፍቶ ከሚገኘውና ለሥጋ በጣም ማራኪ መስሎ ከሚታየው በውጤቱ ግን ምሳሌያዊውን ልብ የማደንደን ባሕርይ ካለው አሸር ባሸር የሆነ የአእምሮ ምግብ ራቅ። መዝሙራዊው “ልባቸው የሰባና የደነደነ ነው” በማለት ተገቢና በሕክምናውም ዘንድ እውነተኝነቱ የተረጋገጠ ምሳሌያዊ አባባል በመጠቀም አስጠንቅቋል።—መዝሙር 119:70 አ.መ.ት
ለረዥም ጊዜ የቆዩ ስውር ድክመቶች ካሉብህ ድክመቶቹ ምሳሌያዊ ደም ወሳጅ ቧንቧዎችህን ከመዝጋታቸው በፊት እነርሱን ለማስወገድ ከፍተኛ ጥረት አድርግ። ዓለም ደስታና እርካታ የሚያስገኙ ብዙ ጥሩ አጋጣሚዎች እንደሚሰጥ ሆኖ ይታይህ ከጀመረ ሐዋርያው ጳውሎስ በሰጠው ጥበብ የተሞላበት ምክር ላይ አሰላስል:- “ዳሩ ግን፣ ወንድሞች ሆይ፣ ይህን እናገራለሁ፤ ዘመኑ አጭር ሆኖአል . . . በዚችም ዓለም የሚጠቀሙ በሙሉ እንደማይጠቀሙባት ይሁኑ፤ የዚች ዓለም መልክ አላፊ [“ተለዋዋጭ፣” NW ] ነውና።” (1 ቆሮንቶስ 7:29-31) እንዲሁም ቁሳዊ ሀብት ሊያማልልህ ከጀመረ ኢዮብ የሰጠውን ምክር ተግባራዊ አድርግ:- “ወርቅን ተስፋ አድርጌ፣ ጥሩውንም ወርቅ:- በአንተ እታመናለሁ ብዬ እንደ ሆነ፤ . . . ልዑል እግዚአብሔርን በካድሁ ነበርና ይህ ደግሞ ፈራጆች የሚቀጡበት በደል በሆነ ነበር።”—ኢዮብ 31:24, 28፤ መዝሙር 62:10፤ 1 ጢሞቴዎስ 6:9, 10
መጽሐፍ ቅዱሳዊ ምክሮችን ሆን ብሎ የመጣስን ልማድ አደገኛነት በምሳሌያዊ ሁኔታ ሲያስጠነቅቅ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል:- “ብዙ ጊዜ ተዘልፎ አንገቱን ያደነደነ ድንገት ይሰበራል፣ ፈውስም የለውም።” (ምሳሌ 29:1) ከዚህ በተቃራኒ ምሳሌያዊ ልባችንን በጥሩ ሁኔታ ከተንከባከብን ቀላልና ሥርዓታማ ሕይወት ከመምራት የሚገኘውን ደስታና የአእምሮ ሰላም ማጨድ እንችላለን። ይህ ሌላ አማራጭ የማይገኝለት የእውነተኛው ክርስትና ጎዳና ሆኖ ቆይቷል። ሐዋርያው ጳውሎስ በመንፈስ ተገፋፍቶ የሚከተለውን ጽፏል:- “ኑሮዬ ይበቃኛል ለሚለው ግን እግዚአብሔርን መምሰል እጅግ ማትረፊያ ነው፤ ወደ ዓለም ምንም እንኳ አላመጣንምና፣ አንዳችንም ልንወስድ አይቻለንም፤ ምግብና ልብስ ከኖረን ግን፣ እርሱ ይበቃናል።”—1 ጢሞቴዎስ 6:6-8
አዎን፣ ራሳችንን ለአምላክ ያደሩ በመሆን ጎዳና ማሰልጠናችንና ማስለመዳችን ጤናማና ጠንካራ ምሳሌያዊ ልብ እንዲኖረን ያደርጋል። መንፈሳዊ የአመጋገብ ልማዳችንን በትኩረት በመከታተል የዚህ ዓለም አታላይ መደለያዎችና አስተሳሰቦች በመንፈሳዊነታችን ላይ ጉዳት ወይም አደጋ እንዳያደርሱ እንጠነቀቃለን። ከሁሉም በላይ ደግሞ ይሖዋ በድርጅቱ በኩል ካደረገልን ዝግጅቶች ሙሉ በሙሉ በመጠቀም ዘወትር ምሳሌያዊ ልባችንን እንመርምር። ሳናሰልስ እንዲህ ማድረጋችን መንፈሳዊ የልብ ድካም የሚያስከትለውን አስከፊ መዘዝ በማስቀረት ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት “የልብ ድካም—ምን ማድረግ ይቻላል?” በሚል ርዕስ በታኅሣሥ 8, 1996 ንቁ! (እንግሊዝኛ) ላይ የወጣውን ተመልከት።
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
ጤናማ ያልሆነ የአመጋገብ ልማድ ደም ወሳጅ ግድግዳዎችን በማደንደን በሥጋዊው ልብ ላይ ጉዳት እንደሚያደርስ ሁሉ ደካማ መንፈሳዊ የአመጋገብ ልማድም ምሳሌያዊውን ልብ ሊያዳክመው ይችላል
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
በመንፈሳዊ እንቅስቃሴ አልባ ሕይወት መምራት አስከፊ መዘዞች ሊያስከትል ይችላል
[በገጽ 11ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
“የኑሮ ጭንቀቶች” ምሳሌያዊውን ልብ በቀላሉ ሊጎዱት ይችላሉ
[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
መንፈሳዊ ጤንነታችንን ችላ ማለት ከባድ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል
[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ጥሩ መንፈሳዊ ልማዶች ማዳበር ምሳሌያዊውን ልብ ለመጠበቅ ይረዳል
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
AP Photo/David Longstreath