የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w01 12/1 ገጽ 14-18
  • ይሖዋን የሚፈራ ልብ ይኑርህ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ይሖዋን የሚፈራ ልብ ይኑርህ
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2001
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • መደመም፣ ጥልቅ አክብሮትና ፍርሃት
  • “ከእርሱ ጋር ተጣበቁ”
  • አምላክን መፍራት ለእሱ ያለን ፍቅር መግለጫ ነው
  • ይሖዋን መፍራትን መማር
  • ይሖዋን የሚፈራ ሁሉ ደስተኛ ነው
  • ይሖዋን በመፍራት ደስታ ማግኘትን መማር
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1995
  • ይሖዋን ፍራ ትእዛዙንም ጠብቅ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2001
  • ይሖዋን ፍሩ ቅዱስ ስሙንም አክብሩ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1992
  • እውነተኛውን አምላክ መፍራት የሚያስገኛቸው ጥቅሞች
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1995
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2001
w01 12/1 ገጽ 14-18

ይሖዋን የሚፈራ ልብ ይኑርህ

“እንዲፈሩኝ ሁልጊዜም ትእዛዜን ሁሉ እንዲጠብቁ እንዲህ ያለ ልብ ምነው በሆነላቸው!”​—⁠ዘዳግም 5:​29

1. ሰዎች ከፍርሃት የሚላቀቁበት ጊዜ እንደሚመጣ እርግጠኞች መሆን የምንችለው እንዴት ነው?

ፍርሃት ለብዙ መቶ ዘመናት የሰውን ዘር ሲያሰቃይ ኖሯል። የረሀብ፣ የበሽታ፣ የወንጀል ወይም የጦርነት ፍርሃት በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ዘወትር በጭንቀት እንዲኖሩ አድርጓቸዋል። የዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብቶች ድንጋጌ የመግቢያ ሐሳብ የሰው ልጆች ሁሉ ከፍርሃት ነፃ የሚሆኑበት ዓለም ለማምጣት ፍላጎት እንዳለው የሚገልጽ መሆኑ አለ ምክንያት አይደለም።a ምንም እንኳ ይህ በሰብአዊ ጥረት የሚመጣ ባይሆንም ደስ የሚለው አምላክ ራሱ እንዲህ ዓይነት ዓለም እንደሚያመጣ ዋስትና ሰጥቶናል። ይሖዋ እሱ በሚያመጣው ጽድቅ በሰፈነበት አዲስ ዓለም ውስጥ ‘ሕዝቦቹን የሚያስፈራ ነገር እንደማይኖር’ በነቢዩ ሚክያስ አማካኝነት ቃል ገብቶልናል።​—⁠ሚክያስ 4:​4

2. (ሀ) ቅዱሳን ጽሑፎች አምላክን እንድንፈራ የሚያሳስቡን እንዴት ነው? (ለ) አምላክን በመፍራት ረገድ ስላለብን ግዴታ ስንመረምር ምን ጥያቄዎች ሊነሱ ይችላሉ?

2 በሌላ በኩል ደግሞ ፍርሃት ለበጎ ተግባር የሚያነሳሳ ኃይል ሊሆንም ይችላል። የአምላክ አገልጋዮች ይሖዋን እንዲፈሩ በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ በተደጋጋሚ ማሳሰቢያ ተሰጥቷቸዋል። ሙሴ እስራኤላውያንን “አምላክህን እግዚአብሔርን ፍራ፤ እርሱንም አምልክ” ብሏቸው ነበር። (ዘዳግም 6:13) ከብዙ መቶ ዘመን በኋላ ሰሎሞን “ይህ የሰው ሁለንተናው ነውና፤ እግዚአብሔርን ፍራ፣ ትእዛዙንም ጠብቅ” ሲል ጽፏል። (መክብብ 12:13) እኛም በተመሳሳይ በመላእክት መሪነት በምናከናውነው የምሥክርነቱ ሥራ “እግዚአብሔርን ፍሩ” እያልን ሰዎችን እናሳስባለን። (ራእይ 14:6, 7) ክርስቲያኖች ይሖዋን መፍራት ብቻ ሳይሆን በሙሉ ነፍሳቸው ሊወድዱት ይገባቸዋል። (ማቴዎስ 22:37, 38) አምላክን ልንወደው እንዲሁም ልንፈራው የምንችለው እንዴት ነው? አፍቃሪ የሆነውን አምላክ መፍራት ለምን አስፈለገ? አምላካዊ ፍርሃትን በማዳበር ምን ጥቅሞችን እናገኛለን? ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ከመስጠታችን በፊት አምላክን መፍራት ሲባል ምን ማለት እንደሆነና ይህ ዓይነቱ ፍርሃት ከይሖዋ ጋር ባለን ዝምድና ረገድ ምን ቁልፍ ቦታ እንዳለው ማስተዋል ይገባናል።

መደመም፣ ጥልቅ አክብሮትና ፍርሃት

3. አምላክን መፍራት ሲባል ምን ማለት ነው?

3 አምላክን መፍራት ክርስቲያኖች ለፈጣሪያቸው ሊኖራቸው የሚገባ ስሜት ነው። የዚህ ዓይነቱ ፍርሃት አንዱ ፍቺ “ለፈጣሪ የመደመም ስሜት እንዲያድርብን ማድረግና የጠለቀ አክብሮት ማሳየት፤ እሱን ላለማሳዘን ጤናማ ፍርሃት ማሳደር” የሚል ነው። ስለዚህ አምላክን መፍራት በሁለት ዋና ዋና አቅጣጫዎች ሕይወታችንን ይነካዋል። እነዚህም ለራሱ ለአምላክና አምላክ ለሚጠላቸው ነገሮች ያሉን ዝንባሌዎች ናቸው። ሁለቱም አቅጣጫዎች ወሳኝና በጥንቃቄ ልንመረምራቸው የሚገቡ እንደሆኑ ግልጽ ነው። የቫይን ኤክስፖዚተሪ ዲክሽነሪ ኦፍ ኒው ቴስታመንት ዎርድስ መዝገበ ቃላት እንዳስቀመጠው ይህ ዓይነቱ አክብሮታዊ ፍርሃት ለክርስቲያኖች ‘በመንፈሳዊም ሆነ በሥነ ምግባራዊ ጉዳዮች ረገድ ሕይወትን የሚቆጣጠር ውስጣዊ ግፊት ነው።’

4. ለፈጣሪያችን የመደመም ስሜትና አክብሮታዊ ፍርሃት እንዲያድርብን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?

4 ለፈጣሪያችን ጥልቅ አክብሮትና የመደመም ስሜት እንዲያድርብን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? ውብ የሆነ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ፣ ማራኪ ዕይታ ያለው ፏፏቴ ወይም አስደናቂ የሆነ የፀሐይ መጥለቅ ስንመለከት በከፍተኛ የአድናቆት ስሜት መደመማችን የማይቀር ነው። ከእነዚህ የፍጥረት ሥራዎች በስተጀርባ የአምላክ እጅ እንዳለ በእምነት ዓይን ስንመለከት ይህ የአድናቆት ስሜታችን ከምንጊዜውም ይበልጥ ከፍ ይላል። ከዚህም በተጨማሪ እንደ ንጉሥ ዳዊት እኛም አስገራሚ ከሆነው የይሖዋ የፍጥረት ሥራ አንጻር ስንታይ እዚህ ግቡ የማንባል ፍጥረታት መሆናችንን እንገነዘባለን። “የጣቶችህን ሥራ ሰማ​ዮችን ባየሁ ጊዜ፣ ጨረቃንና ከዋክብትን አንተ የሠራሃቸውን፣ ታስበው ዘንድ ሰው ምንድር ነው? ትጐበኘውም ዘንድ የሰው ልጅ ምንድር ነው?” (መዝሙር 8:3, 4) እንዲህ ዓይነቱ የመደመም ስሜት አክብሮታዊ ፍርሃት የሚያሳድርብን ሲሆን ይህም ላደረገልን ነገሮች ሁሉ ይሖዋን እንድናወድሰውና እንድናመሰግነው ያነሳሳናል። በተጨማሪም ዳዊት እንደሚከተለው ሲል ጽፏል:- “ግሩምና ድንቅ ሆኜ ተፈጥሬአለሁና አመሰግንሃለሁ፤ ሥራህ ድንቅ ነው፣ ነፍሴም እጅግ ታውቀዋለች።”​—⁠መዝሙር 139:14

5. ይሖዋን መፍራት የሚኖርብን ለምንድን ነው? በዚህ ረገድስ እነማን ግሩም ምሳሌ ይሆኑናል?

5 የመደመም ስሜትና አክብሮታዊ ፍርሃት ስለ አምላክ የፈጣሪነት ኃይል እና ስለ ትክክለኛ የአጽናፈ ዓለም ሉዓላዊ ገዥነቱ ከአክብሮት የመነጨ ጤናማ ፍርሃት እንዲያድርብን ያደርጋል። ሐዋርያው ዮሐንስ ‘በአውሬውና በምስሉ ላይ ድል ነስተው’ በሰማይ የሚገኙት ቅቡዓን የክርስቶስ ተከታዮች “ሁሉን የምትገዛ ጌታ አምላክ ሆይ፣ ሥራህ ታላቅና ድንቅ ነው፤ የአሕዛብ ንጉሥ ሆይ፣ መንገድህ ጻድቅና እውነተኛ ነው፤ ጌታ ሆይ፣ የማይፈራህና ስምህን የማያከብር ማን ነው?” እያሉ ውዳሴ ሲያሰሙ በራእይ ተመልክቷል። (ራእይ 15:​2-4) ለግርማው ካላቸው ጥልቅ አክብሮት የሚመነጨው አምላካዊ ፍርሃት በሰማያዊው መንግሥት ከክርስቶስ ጋር የሚነግሡትን እነዚህን ተባባሪ ገዥዎች አምላክን የመጨረሻው ከፍተኛ ባለሥልጣን አድርገው እንዲያከብሩት ይገፋፋቸዋል። ይሖዋ ያከናወናቸውን ነገሮችና አጽናፈ ዓለሙን የሚያስተዳድርበትን የጽድቅ መንገድ ስናስብ እኛስ ለእርሱ ፍርሃት እንዲያድርብን የሚያደርግ በቂ ምክንያት አናገኝም?​—⁠መዝሙር 2:11፤ ኤርምያስ 10:7

6. ይሖዋን እንዳናሳዝን የሚያደርገንን ጤናማ ፍርሃት ማዳበር የሚኖርብን ለምንድን ነው?

6 ሆኖም አምላክን መፍራት እንዲያው በመደመምና ጥልቅ አክብሮት በማሳየት ብቻ አያበቃም፤ እሱን ከማሳዘንም ሆነ በእሱ ላይ ከማመፅ እንድንርቅ የሚያደርገንን ጤናማ ፍርሃትም የሚጨምር መሆን አለበት። ለምን? ምንም እንኳ ይሖዋ ‘ለቁጣ የዘገየና ፍቅራዊ ደግነቱ የበዛ’ ቢሆንም ‘በደለኛውን ሳይቀጣ እንደማይተው’ ማስታወስ ይገባናል። (ዘጸአት 34:6, 7) ይሖዋ አፍቃሪና መሐሪ ቢሆንም ዓመፅንና ሆን ተብሎ የሚሠራ ኃጢአትን ዝም ብሎ አይመለከትም። (መዝሙር 5:4, 5፤ ዕንባቆም 1:13) ንስሐ ለመግባት እምቢተኛ በመሆን ሆን ብለው በይሖዋ ፊት መጥፎ የሆነውን ማድረጋቸውን የሚቀጥሉና እሱን የሚቃወሙ ሁሉ ፈጽሞ ከቅጣት ሊያመልጡ አይችሉም። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዳለው “በሕያው እግዚአብሔር እጅ መውደቅ የሚያስፈራ ነው።” እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ላለመውደቅ ጤናማ ፍርሃት ማዳበራችን ትልቅ ጥበቃ ይሆንልናል።​—⁠ዕብራውያን 10:31

“ከእርሱ ጋር ተጣበቁ”

7. በይሖዋ የማዳን ኃይል እንድንታመን የሚያደርጉን ምን ማስረጃዎች አሉን?

7 በይሖዋ ላይ ልንታመንና ትምክህት ልንጥል የምንችለው አክብሮታዊ ፍርሃት ሲያድርብንና ታላቅ ኃይል እንዳለው በሚገባ ስንገነዘብ ነው። አንድ ሕፃን ልጅ ከአባቱ ጋር ሲሆን የመረጋጋት ስሜት እንደሚሰማው ሁሉ እኛም የይሖዋን እጅ ይዘን ስንጓዝ ምንም ዓይነት ፍርሃትና ስጋት አያድርብንም። እስራኤላውያን ይሖዋ ከግብፅ ባርነት ነፃ ካወጣቸው በኋላ ምን እንደተሰማቸው ልብ በል። “እስራኤልም እግዚአብሔር በግብፃውያን ላይ ያደረጋትን ታላቂቱን እጅ አዩ፣ ሕዝቡም እግዚአብሔርን ፈሩ፣ በእግዚአብሔርም በባሪያውም በሙሴ አመኑ።” (ዘጸአት 14:31) በተጨማሪም ኤልሳዕ ያጋጠመው ሁኔታ “የእግዚአብሔር መልአክ በሚፈሩት ሰዎች ዙሪያ ይሰፍራል” የሚለውን አባባል የሚያረጋግጥ ነው። (መዝሙር 34:7፤ 2 ነገሥት 6:15-17) ዘመናዊ የይሖዋ ምሥክሮች ታሪክም ሆነ ምናልባትም በእኛ በራሳችን ሕይወት ያጋጠመን ተሞክሮ አምላክ ለአገልጋዮቹ ሲል ኃይሉን እንደሚጠቀም ማረጋገጫ ይሰጠናል። (2 ዜና መዋዕል 16:9) በዚህ መንገድ “እግዚአብሔርን ለሚፈራ ጠንካራ መታመን” እንዳለው እንገነዘባለን።​—⁠ምሳሌ 14:26

8. (ሀ) አምላክን መፍራት በመንገዶቹ እንድንሄድ የሚገፋፋን ለምንድን ነው? (ለ) ከይሖዋ ጋር ‘መጣበቅ’ ያለብን እንዴት እንደሆነ አብራራ።

8 አምላክን በተመለከተ የሚኖረን ጤናማ ፍርሃት በእርሱ ላይ እንድንታመንና ትምክህት እንድንጥል ብቻ ሳይሆን በመንገዶቹ እንድንጓዝ ይገፋፋናል። ሰሎሞን ቤተ መቅደሱን መርቆ በከፈተበት ወቅት “ለአባቶቻችን በሰጠኸው ምድር ላይ በሚኖሩበት ዘመን ሁሉ [የእስራኤል ሕዝቦች] ይፈሩህ ዘንድ በመንገዶችህም ይሄዱ ዘንድ” ሲል ወደ ይሖዋ ጸልዮአል። (2 ዜና መዋዕል 6:31) ቀደም ሲል ሙሴ እስራኤላውያንን “አምላካችሁን እግዚአብሔርን ተከተሉ፣ እርሱንም ፍሩ፣ ትእዛዙንም ጠብቁ፣ ቃሉንም ስሙ፣ እርሱንም አምልኩ፣ ከእርሱም ጋር ተጣበቁ” ሲል አጥብቆ አሳስቧቸው ነበር። (ዘዳግም 13:4) አንድ ሰው በይሖዋ መንገዶች የመሄድና ከእርሱ ጋር ‘የመጣበቅ’ ፍላጎት የሚያድርበት በአምላክ ላይ የመታመንና ትምክህት የመጣል ዝንባሌ ሲያዳብር መሆኑን እነዚህ ጥቅሶች በግልጽ ያሳያሉ። አዎን፣ አምላካዊ ፍርሃት ይሖዋን እንድንታዘዝ፣ እንድናገለግለው እንዲሁም ሙሉ በሙሉ እምነትና ትምክህት የሚጥልበት አባቱን እጅ ሙጭጭ አድርጎ እንደሚይዝ ሕፃን ልጅ እኛም እሱን የሙጥኝ እንድንል ያደርገናል።​—⁠መዝሙር 63:8፤ ኢሳይያስ 41:13

አምላክን መፍራት ለእሱ ያለን ፍቅር መግለጫ ነው

9. አምላክን በመውደድና አምላክን በመፍራት መካከል ያለው ግንኙነት ምንድን ነው?

9 ከቅዱስ ጽሑፉ አንጻር አምላክን እንፈራዋለን ማለት አንወደውም ማለት አይደለም። እንዲያውም እስራኤላውያን ‘ይሖዋን ይፈሩ ዘንድ፣ በመንገዶቹም ይሄዱና ይወድዱት ዘንድ’ ታዝዘዋል። (ዘዳግም 10:12, 13) ስለዚህ አምላክን መፍራትና አምላክን መውደድ እርስ በርስ የሚዛመዱ ባሕርያት ናቸው። አምላክን መፍራት በመንገዶቹ እንድንሄድ የሚያነሳሳን ሲሆን ይህ ደግሞ ለእሱ ፍቅር እንዳለን የሚያረጋግጥ ማስረጃ ነው። (1 ዮሐንስ 5:3) ይህ ምክንያታዊ ነው። አንድን ሰው ከወደድነው እንዳናሳዝነው መፍራታችን ያለ ነገር ነው። እስራኤላውያን በምድረ በዳ ሳሉ በተከተሉት የዓመፀኝነት ጎዳና ይሖዋን አሳዝነውታል። እኛ ሰማያዊ አባታችንን የሚያሳዝን ምንም ነገር ማድረግ እንደማንፈልግ የተረጋገጠ ነው። (መዝሙር 78:40, 41) በሌላ በኩል ደግሞ ይሖዋ ‘በሚፈሩት ስለሚደሰት’ ታዛዥና ታማኝ መሆናችን ልቡን ደስ ያሰኘዋል። (መዝሙር 147:11፤ ምሳሌ 27:11) ለአምላክ ያለን ፍቅር እሱን ደስ እንድናሰኘው የሚገፋፋን ሲሆን ለአምላክ ያለን ፍርሃት ደግሞ እሱን የሚያሳዝን ነገር ከማድረግ እንድንታቀብ ያደርገናል። ስለዚህ ፍርሃትና ፍቅር እርስ በርስ የሚደጋገፉ እንጂ የሚቃረኑ ባሕርያት አይደሉም።

10. ኢየሱስ ይሖዋን በመፍራት እንደሚደሰት ያሳየው እንዴት ነው?

10 የኢየሱስ ክርስቶስ ሕይወት አምላክን ልንወደው እንዲሁም ልንፈራው የምንችለው እንዴት እንደሆነ ጥሩ አድርጎ የሚያሳይ ምሳሌ ነው። ነቢዩ ኢሳይያስ ስለ ኢየሱስ እንደሚከተለው ሲል ጽፏል:- “የእግዚአብሔር መንፈስ፣ የጥበብና የማስተዋል መንፈስ፣ የምክርና የኃይል መንፈስ፣ የእውቀትና እግዚአብሔርን የመፍራት መንፈስ ያርፍበታል። እግዚአብሔርን በመፍራት ደስታውን ያያል።” (ኢሳይያስ 11:2, 3) በዚህ ትንቢት መሠረት የአምላክ መንፈስ ኢየሱስ ሰማያዊ አባቱን እንዲፈራ አነሳስቶታል። ከዚህም በላይ ይህ ፍርሃት ሸክም ሳይሆን የሚያስደስት ነው። ኢየሱስ እጅግ አስቸጋሪ በሆነ ሁኔታ ውስጥም እንኳ ሳይቀር የአምላክን ፈቃድ በማድረግና እሱን ደስ በማሰኘት ከፍተኛ ደስታ አግኝቷል። በመከራ እንጨት ላይ ተሰቅሎ ሊገደል ተቃርቦ በነበረበት ወቅት ለይሖዋ “አንተ እንደምትወድ ይሁን እንጂ እኔ እንደምወድ አይሁን” ብሎት ነበር። (ማቴዎስ 26:39) ባሳየው አምላካዊ ፍርሃት የተነሳ ይሖዋ ልጁ ያቀረበውን ምልጃ አዳምጦ ያበረታው ሲሆን ከሞት እስራትም አውጥቶታል።​—⁠ዕብራውያን 5:7

ይሖዋን መፍራትን መማር

11, 12. (ሀ) አምላክን መፍራት መማር ያለብን ለምንድን ነው? (ለ) ኢየሱስ ይሖዋን መፍራት የሚያስተምረን እንዴት ነው?

11 በተፈጥሮ ላይ ተንጸባርቆ የምንመለከተው ኃይልና ግርማ የመደመም ስሜት ሊፈጥርብን ቢችልም አምላካዊ ፍርሃት ግን እንዲሁ በራሱ የሚመጣ አይደለም። ታላቁ ዳዊት ኢየሱስ ክርስቶስ “ልጆቼ ኑ፣ ስሙኝ፤ እግዚአብሔርን መፍራት አስተምራችኋለሁ” በማለት ትንቢታዊ ግብዣ ያቀረበልን ለዚህ ነው። (መዝሙር 34:11) ይሖዋን መፍራት ከኢየሱስ መማር የምንችለው እንዴት ነው?

12 ኢየሱስ የሰማያዊ አባታችንን ድንቅ ባሕርያት እንድናስተውል በማድረግ ይሖዋን መፍራት ያስተምረናል። (ዮሐንስ 1:18) ኢየሱስ የአባቱ ፍጹም ነጸብራቅ እንደመሆኑ መጠን እሱ የተወልን ምሳሌ የአምላክ ሐሳብ ምን እንደሆነና ሌሎችን በምን መንገድ እንደሚይዝ ያሳያል። (ዮሐንስ 14:9, 10) ከዚህም በተጨማሪ ኃጢአታችን ይቅር እንዲባልልን በምንጸልይበት ጊዜ በኢየሱስ መሥዋዕት አማካኝነት ወደ ይሖዋ መቅረብ እንችላለን። ይህ ታላቅ የአምላክ ምሕረት መግለጫ ራሱ አምላክን እንድንፈራ የሚገፋፋን ከፍተኛ ኃይል ነው። መዝሙራዊው “በአንተ ዘንድ ይቅርታ አለ፤ ስለዚህም ልትፈራ ይገባሃል” ሲል ጽፏል።​—⁠መዝሙር 130:4 አ.መ.ት 

13. በምሳሌ መጽሐፍ ውስጥ ይሖዋን እንድንፈራ የሚረዱን ምን እርምጃዎች ተዘርዝረዋል?

13 የምሳሌ መጽሐፍ አምላካዊ ፍርሃት ማዳበር የምንችልባቸውን እርምጃዎች በቅደም ተከተል ያስቀምጥልናል። “ልጄ ሆይ፣ ቃሌን ብትቀበል፣ ትእዛዜንም በአንተ ዘንድ ሸሽገህ ብትይዛት፣ ጆሮህ ጥበብን እንዲያደምጥ ታደርጋለህ፣ ልብህንም ወደ ማስተዋል ታዘነብላለህ። ረቂቅ እውቀትን ብትጠራት፣ ለማስተዋልም ድምፅህን ብታነሣ፣ . . . የዚያን ጊዜ እግዚአብሔርን መፍራት ታውቃለህ፣ የአምላክንም እውቀት ታገኛለህ።” (ምሳሌ 2:1-5) ስለዚህ አምላክን ለመፍራት ቃሉን ማጥናት፣ መመሪያዎቹን ለመረዳት ልባዊ ጥረት ማድረግና ምክሮቹን ልብ ማለት ያስፈልገናል።

14. ለእስራኤል ነገሥታት የተሰጠውን ምክር ተግባራዊ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?

14 እያንዳንዱ የጥንት እስራኤል ንጉሥ የሕጉ ቅጂ በእጁ እንዲኖረውና ‘አምላኩን እግዚአብሔርን መፍራት ይማር ዘንድ፣ የዚህን ሕግ ቃል ሁሉ ያደርግ ዘንድ ዕድሜውን ሁሉ እንዲያነብበው’ መመሪያ ተሰጥቶ ነበር። (ዘዳግም 17:18-20) እኛም ይሖዋን መፍራት መማር ከፈለግን መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብና ማጥናት አለብን። የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በሕይወታችን ላይ ተግባራዊ ባደረግን መጠን ቀስ በቀስ መለኮታዊ ጥበብና እውቀት እያገኘን እንሄዳለን። በሕይወታችን ላይ የሚኖረውን መልካም ውጤት ስለምንመለከት ‘እግዚአብሔርን መፍራት እናውቃለን’ እንዲሁም ከአምላክ ጋር ያለንን ዝምድና ከፍ አድርገን እንመለከተዋለን። ከዚህም በተጨማሪ ከእምነት አጋሮቻችን ጋር ዘወትር በመሰብሰብ ወጣት አረጋዊ ሳንል መለኮታዊውን ትምህርት ማዳመጥ፣ አምላክን መፍራት መማርና በመንገዶቹ መሄድ እንችላለን።​—⁠ዘዳግም 31:​12

ይሖዋን የሚፈራ ሁሉ ደስተኛ ነው

15. አምላክን መፍራት ለእርሱ ከምናቀርበው አምልኮ ጋር የሚዛመደው በምን መንገድ ነው?

15 ለይሖዋ በምናቀርበው አምልኮ ውስጥ ቁልፍ ቦታ ያለው በመሆኑ አምላክን መፍራት ሁላችንም ልናዳብረው የሚገባ ጤናማ ዝንባሌ መሆኑን ከላይ ስንመለከት መጥተናል። ሙሉ በሙሉ በይሖዋ እንድንታመን፣ በመንገዶቹ እንድንሄድና ከእርሱ ጋር እንድንጣበቅ ያደርገናል። በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ እንደታየው ሁሉ አምላክን መፍራት ራሳችንን ስንወስን የገባነውን ቃል አሁንና ለዘላለም ጠብቀን እንድንመላለስ ሊያንቀሳቅሰን ይችላል።

16. ይሖዋ እንድንፈራው የሚያበረታታን ለምንድን ነው?

16 አምላካዊ ፍርሃት የሚያርበደብድ ወይም መፈናፈኛ የሚያሳጣ አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ “እግዚአብሔርን የሚፈሩት ሁሉ፣ በመንገዶቹም የሚሄዱ ምስጉኖች [“ደስተኞች፣” NW ] ናቸው” በማለት ማረጋገጫ ይሰጠናል። (መዝሙር 128:1) ይሖዋ ይህ ባሕርይ ጥበቃ እንደሚሆንልን ስለሚያውቅ እሱን እንድንፈራው ያበረታታናል። ለሙሴ ከተናገራቸው ከሚከተሉት ቃላት ፍቅራዊ አሳቢነቱን ማስተዋል እንችላለን:- “ለእነርሱ [ለእስራኤላውያን] ለዘላለምም ለልጆቻቸው መልካም ይሆንላቸው ዘንድ፣ እንዲፈሩኝ ሁልጊዜም ትእዛዜን ሁሉ እንዲጠብቁ እንዲህ ያለ ልብ ምነው በሆነላቸው!”​—⁠ዘዳግም 5:29

17. (ሀ) አምላክን በመፍራታችን ምን ጥቅሞችን እናገኛለን? (ለ) በሚቀጥለው ርዕሰ ትምህርት ላይ የአምላካዊ ፍርሃት የትኛው ገጽታ ይብራራል?

17 እኛም ልባችን ይሖዋን መፍራት እንዲማር ብናደርግ በእጅጉ እንጠቀማለን። በምን መንገድ? በመጀመሪያ ደረጃ ይህ ዓይነቱ ባሕርይ አምላክን ደስ የሚያሰኝ ሲሆን ወደ እርሱ እንድንቀርብም ያደርገናል። ዳዊት ከራሱ ተሞክሮ በመነሳት “ለሚፈሩት ምኞታቸውን ያደርጋል፣ ልመናቸውንም ይሰማል ያድናቸዋልም” ለማለት ችሏል። (መዝሙር 145:19) በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ አምላካዊ ፍርሃት መጥፎ ለሆነው ነገር ያለንን ዝንባሌ ስለሚነካው በዚህም ይጠቅመናል። (ምሳሌ 3:7) የሚቀጥለው ርዕሰ ትምህርት ይህ ፍርሃት ከመንፈሳዊ አደጋ እንዴት እንደሚጠብቀን የሚያብራራ ሲሆን በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ የሚገኙ አምላክን የፈሩና ከክፋት የራቁ አንዳንድ ምሳሌ የሚሆኑ ሰዎችንም ይጠቅሳል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ ታኅሣሥ 10, 1948 ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ድንጋጌን አጽድቋል።

የሚከተሉትን ጥያቄዎች መመለስ ትችላለህ?

• አምላክን መፍራት ማለት ምን ማለት ነው? እኛን የሚነካንስ እንዴት ነው?

• አምላክን በመፍራትና ከአምላክ ጋር በመመላለስ መካከል ምን ዝምድና አለ?

• ኢየሱስ የተወው ምሳሌ አምላክን መፍራትና አምላክን መውደድ ተዛማጅ ነገሮች መሆናቸውን የሚያሳየው እንዴት ነው?

• ልባችን ይሖዋን መፍራት እንዲያዳብር ልናደርገው የምንችለው እንዴት ነው?

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የእስራኤል ነገሥታት የሕጉ የግል ቅጂ እንዲኖራቸውና በየዕለቱ እንዲያነቡት ታዝዘው ነበር

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አንድ ሕፃን ልጅ በአባቱ እንደሚታመን ሁሉ ይሖዋን መፍራትም በእሱ እንድንታመን ያደርገናል

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

ከዋክብት:- Photo by Malin, © IAC/RGO 1991

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ