የአምላክ ቃል አስተማሪዎች ተልዕኳቸውን እንዲወጡ ማበረታቻ አግኝተዋል
ባለፉት ጥቂት ወራት በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ አስተማሪዎች ትምህርት ለመቅሰም ተሰብስበው ነበር። እነዚህ አስተማሪዎች ካለፈው ግንቦት ጀምሮ በዓለም ዙሪያ በተካሄዱ በመቶዎች በሚቆጠሩ “የአምላክ ቃል አስተማሪዎች” የይሖዋ ምሥክሮች የአውራጃ ስብሰባዎች ላይ ተገኝተዋል። የስብሰባው ተካፋዮች የተሻለ ብቃት አግኝተው የማስተማር ተልዕኳቸውን መወጣት እንዲችሉ ራሳቸውን ማስተማር እንዳለባቸው ማበረታቻ ተሰጥቷቸዋል።
አንተስ ከእነዚህ የአውራጃ ስብሰባዎች በአንዱ ላይ ተገኝተህ ነበር? ተገኝተህ ከነበረ እውነተኛ አምላክ የሆነውን ይሖዋን ለማምለክ በተዘጋጁት በእነዚህ ስብሰባዎች ላይ በቀረበው ግሩም መንፈሳዊ ምግብ እንደተደሰትክ ምንም ጥርጥር የለውም። ትምህርት ሰጪ የሆነውን የአውራጃ ስብሰባውን ፕሮግራም ለምን አብረን አንከልስም?
የመጀመሪያው ቀን —በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት የተጻፉት ቅዱሳን ጽሑፎች ለትምህርት ይጠቅማሉ
የአውራጃ ስብሰባው ሊቀመንበር “እናንት የአምላክ ቃል አስተማሪዎች ከይሖዋ ተማሩ” የሚል ንግግር በማቅረብ ለስብሰባው ተካፋዮች ሞቅ ያለ አቀባበል አደረገላቸው። ኢየሱስ ክርስቶስ ‘ከሁሉ የላቀ አስተማሪ’ ከሆነው ከይሖዋ በመማር ታላቅ አስተማሪ ለመሆን በቅቷል። (ኢሳይያስ 30:20 NW ፤ ማቴዎስ 19:16) እኛም በአምላክ ቃል አስተማሪነታችን እድገት ማድረግ ከፈለግን ከይሖዋ መማር ይኖርብናል።
ቀጥሎ “የመንግሥቱ ትምህርት መልካም ፍሬ ያፈራል” የሚለው ክፍል ቀረበ። ተሞክሮ ካላቸው የአምላክ ቃል አስተማሪዎች ጋር በተደረገው ቃለ ምልልስ አማካኝነት ደቀ መዝሙር የማድረጉ ሥራ የሚያስገኘው ደስታና በረከት ጎላ ተደርጎ ተገልጿል።
ቀጥሎ “‘የአምላክ ታላቅ ሥራ’ ሰዎችን ለተግባር ያንቀሳቅሳል” የሚል ርዕስ ያለው ቀስቃሽ ንግግር ቀረበ። በመጀመሪያው መቶ ዘመን ከአምላክ መንግሥት ጋር ግንኙነት ያላቸው ‘ታላላቅ ሥራዎች’ ሰዎችን ለተግባር አንቀሳቅሰዋቸው ነበር። (ሥራ 2:11) እኛም ስለ ቤዛ፣ ስለ ትንሣኤና ስለ አዲሱ ቃል ኪዳን የሚናገሩ ቅዱስ ጽሑፋዊ ትምህርቶችን የመሳሰሉ ‘ታላላቅ ሥራዎች’ ለሌሎች በመንገር ሰዎችን ለተግባር ማንቀሳቀስ እንችላለን።
ቀጥሎ የቀረበው ንግግር “በይሖዋ ጽድቅ ደስ ይበላችሁ” ሲል ሁሉንም አበረታቷል። (መዝሙር 35:27) ጽድቅን መውደድ እና ክፋትን መጥላት በመማር፣ መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናት፣ በመንፈሳዊ ጎጂ የሆኑ ተጽዕኖዎችን በጽናት በመቃወም ብሎም ትህትናን በማዳበር ጽድቅን እንድንከታተል ተመክረናል። እነዚህ እርምጃዎች ከመጥፎ ባልንጀርነት፣ ዓለም ለቁሳዊ ነገሮች ካለው አመለካከት እንዲሁም በሥነ ምግባር ካዘቀጠውና በዓመፅ ከተሞላው መዝናኛ ራሳችንን እንድንጠብቅ ይረዱናል።
“የአምላክን ቃል ለማስተማር በሚገባ የታጠቁ” የሚል ርዕስ ያለው የጭብጡ ቁልፍ ንግግር ይሖዋ በቃሉ፣ በቅዱስ መንፈሱና በምድራዊ ድርጅቱ አማካኝነት ብቃቱን የምናሟላ አገልጋዮቹ እንዳደረገን ቆም ብለን እንድናስብ አድርጎናል። ተናጋሪው በመጽሐፍ ቅዱስ መጠቀምን አስመልክቶ ሲናገር “ግባችን የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት ከተጻፈበት ወረቀት አንስተን በሰዎች ልብ ውስጥ ጠልቆ እንዲገባ ማድረግ ነው” በማለት በጥብቅ አሳስቦናል።
የአውራጃ ስብሰባው የመጀመሪያ ሲምፖዚየም “ሌሎችን እያስተማርን ራሳችንንም ማስተማር” የሚል ርዕስ ነበረው። የመክፈቻው ንግግር ለሌሎች ሰዎች የምናስተምረውን የላቀ ክርስቲያናዊ የሥነ ምግባር ደረጃ እኛም ራሳችን መጠበቅ እንደሚገባን በጥብቅ አሳስቦናል። ቀጣዩ ክፍል ‘የእውነትን ቃል በትክክል እንድንጠቀም’ አበረታቶናል። (2 ጢሞቴዎስ 2:15) የቱንም ያህል ረጅም ዓመት አምላክን ያገለገልን ብንሆን ራሳችንን ለማስተማር ዘወትር ትጋት የተሞላበት የግል የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ማድረጋችን አስፈላጊ ነው። የሲምፖዚየሙ የመጨረሻ ክፍል ዲያብሎስ ኩራት፣ በራስ የመመራት መንፈስ፣ ራስን የማዋደድ ስሜት፣ ቅናት፣ ምቀኝነት፣ ጥላቻ፣ ቂመኛነትና ስህተት ለቃቃሚነት የመሳሰሉ ባሕርያት ያጠቁን እንደሆነ ለማየት ሲል እንደሚከታተለን ገልጿል። ይሁን እንጂ ዲያብሎስን ጸንተን ከተቃወምነው ከእኛ ይሸሻል። እርሱን ለመቃወም ደግሞ ወደ አምላክ መቅረብ ይኖርብናል።—ያዕቆብ 4:7, 8
“በዓለም ላይ እንደ ወረርሽኝ የተስፋፉትን ወሲባዊ ሥዕሎች መጸየፍ” የሚለው ወቅታዊ ንግግር መንፈሳዊነታችንን ለአደጋ ሊያጋልጥ የሚችለውን ይህን አቋምን ዝቅ የሚያደርግ ሁኔታ እንዴት መቋቋም እንደምንችል ግልጽ አድርጎልናል። ነቢዩ ዕንባቆም ስለ ይሖዋ ሲናገር “ዓይኖችህ ክፉ እንዳያዩ ንጹሐን ናቸው፣ ጠማምነትንም ትመለከት ዘንድ አትችልም” ብሎ ነበር። (ዕንባቆም 1:13) እኛም ‘ክፉውን ነገር መጸየፍ’ ይገባናል። (ሮሜ 12:9) ወላጆች ልጆቻቸው በኢንተርኔትና በቴሌቪዥን ምን እንደሚያዩ እንዲከታተሉ በጥብቅ ተመክረዋል። ተናጋሪው ወሲባዊ ሥዕሎችን ለማየት የሚፈተኑ ሰዎች በመንፈሳዊ ከጎለመሱ ወዳጆቻቸው እርዳታ ማግኘት እንደሚገባቸው ተናግሯል። እንዲሁም መዝሙር 97:10፤ ማቴዎስ 5:28፤ 1 ቆሮንቶስ 9:27፣ ኤፌሶን 5:3, 12፣ ቆላስይስ 3:5 እና 1 ተሰሎንቄ 4:4, 5 የመሳሰሉ ጥቅሶችን በማሰላሰል በአእምሮ መያዙ ይረዳል።
“የአምላክ ሰላም ይጠብቃችሁ” የሚለው ቀጣዩ ንግግር በጭንቀት በምንዋጥበት ጊዜ ሸክማችንን በይሖዋ ላይ መጣል እንደምንችል በማረጋገጥ አጽናንቶናል። (መዝሙር 55:22) በጸሎት አማካኝነት የልባችንን ግልጥልጥ አድርገን የምንናገር ከሆነ ይሖዋ ‘የአምላክን ሰላም’ ይሰጠናል። ይህ ሰላም ደግሞ ከእርሱ ጋር ካለን ውድ ዝምድና የሚመነጭ መረጋጋትና ውስጣዊ እረፍት ነው።—ፊልጵስዩስ 4:6, 7
የመጀመሪያው ቀን የተደመደመው የኢሳይያስ ምዕራፍ 60 ፍጻሜን በሚያብራራው “ይሖዋ ሕዝቡን በብርሃን ያስጌጣል” በሚለው አስደሳች ንግግር ነበር። ዓለም በጨለማ በሚዳክርበት በዚህ ጊዜ “የባዕድ አገር ሰዎች” ማለትም ቁጥራቸው እየጨመረ ያለው በበግ የተመሰሉት እጅግ ብዙ ሰዎች ከቅቡዓን ክርስቲያኖች ጋር በመሆን የይሖዋን ብርሃን አግኝተዋል። ተናጋሪው ቁጥር 19 እና 20ን ሲያብራራ “ይሖዋ እንደ ፀሐይ ‘አይጠልቅም’ ወይም እንደ ጨረቃ ‘አይቋረጥም።’ ይሖዋ ብርሃኑን በማብራት ሕዝቡን ማስጌጡን ይቀጥላል። ጨለማ በዋጠው በዚህ ዓለም ውስጥ ስንኖር ይህ ለእኛ እንዴት ግሩም ዋስትና ነው!” ብሎ ነበር። በንግግሩ መደምደሚያ ላይ ተናጋሪው የኢሳይያስ ትንቢት—ለመላው የሰው ዘር የፈነጠቀ ብርሃን (እንግሊዝኛ) የተባለው መጽሐፍ ጥራዝ ሁለት መውጣቱን አስታውቆ ነበር። ይህን አዲስ ጽሑፍ አንብበህ ጨርሰሃል?
ሁለተኛው ቀን—ሌሎችን ለማስተማር ብቁ ሆኖ መገኘት
በሁለተኛው ቀን በዕለቱ ጥቅስ ላይ ማብራሪያ ከተሰጠ በኋላ “ሌሎች አማኝ እንዲሆኑ የረዱ አገልጋዮች” በሚል ርዕስ የአውራጃ ስብሰባውን ሁለተኛ ሲምፖዚየም በከፍተኛ ጉጉት አዳመጥን። የዚህን ሲምፖዚየም ሦስት ንግግሮች ያቀረቡት ተናጋሪዎች ሌሎች ሰዎች አማኝ እንዲሆኑ መርዳት የሚቻልባቸውን ሦስት ደረጃዎች ጎላ አድርገው ገልጸዋል። እነዚህም የመንግሥቱን መልእክት ማዳረስ፣ የሰዎችን ፍላጎት መኮትኮት፣ ፍላጎት ያላቸው ሰዎች ክርስቶስ ያዘዘውን እንዲጠብቁ ማስተማር ናቸው። በቀረቡት ቃለ ምልልሶችና በሠርቶ ማሳያዎች በቀረቡት ተሞክሮዎች አማካኝነት ሌሎች ደቀ መዛሙርት እንዲሆኑ እንዴት ማስተማር እንደምንችል ተምረናል።
ቀጥሎ የቀረበው ንግግር “በጽናትም ላይ ለአምላክ ማደርን ጨምሩ” የሚል ጭብጥ ነበረው። ተናጋሪው ዋናው ነገር ‘እስከ መጨረሻው ድረስ መጽናታችን’ መሆኑን አመልክቷል። (ማቴዎስ 24:13) ለአምላክ የማደር ባሕርያችንን ለማዳበር በሁሉም የአምላክ ዝግጅቶች ይኸውም በጸሎት፣ በግል ጥናት፣ በስብሰባዎችና በአገልግሎት መጠቀም ይገባናል። ዓለማዊ ምኞቶችና እንቅስቃሴዎች ለአምላክ የማደር ባሕርያችንን እንዳያበላሹብን ወይም እንዳያጠፉብን መከላከል ያስፈልገናል።
ዛሬ ሸክም የከበደባቸውና የደከሙ ሰዎች እረፍት ማግኘት የሚችሉት እንዴት ነው? “የክርስቶስን ቀንበር በመሸከም እረፍት ማግኘት” የሚለው ንግግር ለዚህ ጥያቄ መልስ ሰጥቷል። ኢየሱስ ተከታዮቹ ቀንበሩን እንዲሸከሙና ከእርሱ እንዲማሩ በደግነት ጋብዟቸዋል። (ማቴዎስ 11:28-30) የኢየሱስን ምሳሌ በመኮረጅ ቀላልና ሚዛናዊ ኑሮ በመኖር ቀንበሩን መሸከም እንችላለን። የዚህ ክፍል ዋና ዋና ነጥቦች አኗኗራቸውን ቀላል ካደረጉ ወንድሞችና እህቶች ጋር በተደረጉ ቃለ ምልልሶች ይበልጥ ግልጽ ሆነዋል።
የይሖዋ ምሥክሮች በሚያደርጓቸው ትላልቅ ስብሰባዎች ላይ ጉልህ ሥፍራ ከሚሰጣቸው ነገሮች መካከል አንዱ በቅርብ ጊዜ ራሳቸውን የወሰኑ የአምላክ አገልጋዮች ጥምቀት ነው። “ጥምቀት ለበለጡ የማስተማር መብቶች በር ይከፍታል” የሚለውን ንግግር ያቀረበው ወንድም ለጥምቀት ዕጩዎቹ ሞቅ ያለ አቀባበል ካደረገላቸው በኋላ በበለጡ የአገልግሎት መብቶች እንዲካፈሉ ጋበዛቸው። ቅዱስ ጽሑፋዊ ብቃቶችን የሚያሟሉ አዲስ ተጠማቂ የአምላክ ቃል አስተማሪዎች በጉባኤ ውስጥ የተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ ለመድረስ መጣጣር ይችላሉ።
በዚያን ዕለት ከሰዓት በኋላ የቀረበው የመጀመሪያ ንግግር “የታላቁን አስተማሪ ምሳሌ ኮርጁ” የሚል ነበር። ኢየሱስ ሕልቆ መሳፍርት ለሌለው ዘመን በሰማይ በኖረበት ጊዜ አባቱን በቅርብ ተመልክቶ በመኮረጅ ታላቅ አስተማሪ ለመሆን በቅቷል። በምድር በነበረበት ወቅት ስሜት ቀስቃሽ ጥያቄዎችንና ቀላል ሆኖም ሕያው የሆኑ ምሳሌዎችን የመሳሰሉ ውጤታማ የማስተማሪያ ዘዴዎችን ተጠቅሟል። የኢየሱስ ትምህርቶች በአምላክ ቃል ላይ የተመሠረቱ ሲሆን በግለት፣ በፍቅራዊ ስሜትና በሥልጣን ይናገር ነበር። ታላቁ አስተማሪ የተወውን ምሳሌ ለመኮረጅ አልተገፋፋንም?
“ሌሎችን ለማገልገል ፈቃደኛ ናችሁ?” የሚል ርዕስ ያለው ሌላው ቀስቃሽ ንግግር ሌሎችን በማገልገል ረገድ የኢየሱስን ምሳሌ እንድንኮርጅ አበረታቶናል። (ዮሐንስ 13:12-15) ተናጋሪው ሌሎችን በመርዳት ረገድ የሚያገኙትን አጋጣሚ በመጠቀም የጢሞቴዎስን ምሳሌ እንዲኮርጁ ብቃት ያላቸው ወንዶችን በቀጥታ አበረታቷል። (ፊልጵስዩስ 2:20, 21) ወላጆች ልጆቻቸው የሙሉ ጊዜ አገልግሎትን ግብ እንዲከታተሉ በመርዳት በኩል የሕልቃናን እና የሐናን ምሳሌ እንዲኮርጁ ማበረታቻ ተሰጥቷቸዋል። እንዲሁም ወጣቶች ራሳቸውን በፈቃደኝነት በማቅረብ የኢየሱስ ክርስቶስንና የወጣቱን የጢሞቴዎስን ምሳሌ እንዲኮርጁ በጥብቅ ተመክረዋል። (1 ጴጥሮስ 2:21) በተጨማሪ ሌሎችን ለመርዳት ያገኟቸውን አጋጣሚዎች የተጠቀሙ ሰዎች ከተናገሩት ቃል ማበረታቻ አግኝተናል።
የሦስተኛው ሲምፖዚየም ጭብጥ “ከቲኦክራሲያዊው ትምህርት ሙሉ በሙሉ ተጠቀሙ” የሚል ነበር። የመጀመሪያው ተናጋሪ ረዘም ላለ ጊዜ በትኩረት የመከታተልን ልማድ ማዳበር አስፈላጊ መሆኑን ጎላ አድርጎ ገልጾልናል። እዚያ ግብ ላይ ለመድረስ መጀመሪያ ላይ የግል ጥናት የምናደርግበትን ክፍለ ጊዜ አጭር ማድረግና ቀስ በቀስ ማስረዘም እንችላለን። በተጨማሪም በስብሰባዎች ላይ ጥቅሶችን አውጥተው እንዲከታተሉና ማስታወሻ እንዲይዙ አድማጮቹን አበረታቷል። ሁለተኛው ተናጋሪ ‘የጤናማውን ቃል ምሳሌ’ አጥብቆ የመያዝን አስፈላጊነት በጥብቅ አሳስቦናል። (2 ጢሞቴዎስ 1:13, 14) በመገናኛ ብዙኃን ላይ ከሚቀርቡት ሥነ ምግባር የጎደላቸው ፕሮግራሞች፣ ከሰብዓዊ ፍልስፍናዎች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ተቺዎች ከሚሰነዝሩት ሐሳብና ከከሃዲዎች ትምህርት ራሳችንን መጠበቅ እንችል ዘንድ ለግል ጥናትና ለጉባኤ ስብሰባዎች ጊዜ መዋጀት ይገባናል። (ኤፌሶን 5:15, 16) የሲምፖዚየሙ የመጨረሻ ተናጋሪ ከቲኦክራሲያዊው ትምህርት ሙሉ በሙሉ ለመጠቀም የተማርናቸውን ነገሮች በሥራ ላይ የማዋልን አስፈላጊነት ጎላ አድርጎ ገልጿል።—ፊልጵስዩስ 4:9
“ለመንፈሳዊ እድገታችን የሚረዱ አዲስ ዝግጅቶች” የሚለውን ንግግር በማዳመጣችን ምንኛ ተደስተን ነበር! በቅርቡ “በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ከሚሰጠው ትምህርት ተጠቀሙ” የሚል ርዕስ ያለው አዲስ መጽሐፍ እንደሚዘጋጅ በማወቃችን በጣም ተደስተናል። ተናጋሪው ስለ መጽሐፉ ይዘት ሲናገር መጽሐፉን የማግኘት ጉጉታችን ከፍ ብሎ ነበር። በመጽሐፉ ውስጥ ስለተካተቱት የተለያዩ የንግግር ምክር መስጫ ነጥቦች ሲናገር “ይህ አዲስ መማሪያ መጽሐፍ ጥሩ ንባብን፣ ንግግርንና ማስተማርን በተመለከተ ስላቀረባቸው 53 የምክር መስጫ ነጥቦች የሚሰጠው ማብራሪያ በዓለማዊ መማሪያ መጻሕፍት ላይ የሚገኘውን ዓይነት አይደለም። ማብራሪያዎቹ በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ላይ የተመሠረቱ ናቸው” ብሎ ነበር። መጽሐፉ የነቢያትን፣ የኢየሱስንና የደቀ መዛሙርቱን ጥሩ የማስተማር ዘዴ ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ይሆናል። አዎን፣ ይህ መማሪያ መጽሐፍና ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት የሚኖረው አዲስ ገጽታ የተሻልን የአምላክ ቃል አስተማሪዎች እንድንሆን እንደሚረዳን ምንም ጥርጥር የለውም።
ሦስተኛው ቀን—ከጊዜው የተነሳ አስተማሪዎች ሁኑ
በመጨረሻው ዕለት በዕለቱ ጥቅስ ላይ ውይይት ከተደረገ በኋላ ሁሉም “የሚልክያስ ትንቢት ለይሖዋ ቀን ያዘጋጀናል” የሚለውን የአውራጃ ስብሰባው የመጨረሻ ሲምፖዚየም በጥሞና ይከታተል ጀመር። ሚልክያስ ትንቢቱን የተናገረው አይሁዳውያን ከባቢሎን ከተመለሱ በግምት ከአንድ መቶ ዓመት በኋላ ነበር። የጽድቅ ሕጎቹን ችላ በማለት እንዲሁም ዕውር፣ አንካሳና የታመሙ እንስሳትን መሥዋዕት አድርገው በማቅረብ የይሖዋን ስም በማቃለል ዳግም ወደ ክህደትና ወደ ክፉ ድርጊት ተመልሰዋል። ከዚህም በተጨማሪ የባዕድ አገር ሴቶችን ለማግባት ሲሉ ሳይሆን አይቀርም፣ የልጅነት ሚስቶቻቸውን ይፈቱ ነበር።
የሚልክያስ ትንቢት የመጀመሪያ ምዕራፍ ይሖዋ ሕዝቡን እንደሚወድ ይናገራል። ለአምላክ አክብሮታዊ ፍርሃት ማዳበር እንዲሁም ቅዱስ ለሆኑ ነገሮች አድናቆት ማሳየት አስፈላጊ መሆኑን ጎላ አድርጎ ይገልጻል። ይሖዋ ከራስ ወዳድነት ነጻ በሆነ ፍቅር ተነሳስተን እንድናመልከውና ምርጣችንን እንድንሰጠው ይፈልጋል። የምናቀርበው ቅዱስ አገልግሎት እንዲያው ለደንቡ ያህል የሚደረግ መሆን የለበትም። ለምናደርገው ነገር ለአምላክ መልስ መስጠት ይገባናል።
የሲምፖዚየሙ ሁለተኛ ተናጋሪ ሚልክያስ ምዕራፍ ሁለት በዘመናችን እንዴት እንደሚሠራ በማብራራት “‘በከንፈራችን ውስጥ በደል እንዳይገኝ’ እንጠነቀቃለን?” የሚል ጥያቄ አንስቷል። (ሚልክያስ 2:6) በማስተማሩ ሥራ ግንባር ቀደም ሆነው የሚያገለግሉ ወንድሞች ትምህርታቸው በሙሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ መሆን አለበት። ፍትሐዊ ባልሆነ ምክንያት የትዳር ጓደኛን በመፍታት የሚፈጸመውን ክህደት መጥላት ይገባናል።—ሚልክያስ 2:14-16
“ከይሖዋ ቀን በሕይወት የሚተርፈው ማን ነው?” በሚል ጭብጥ የሲምፖዚየሙን የመጨረሻ ንግግር ያቀረበው ተናጋሪ ለይሖዋ ቀን እንድንዘጋጅ አበረታትቶናል። ተናጋሪው “ሚልክያስ ምዕራፍ 3 ቁጥር 17 ዋነኛ ፍጻሜውን በእነርሱ ላይ በማግኘት ላይ መሆኑን ማወቃቸው ለይሖዋ አገልጋዮች ምንኛ የሚያጽናና ነው!” ብሏል። “ጥቅሱ እንዲህ ይላል:- ‘እኔ በምሠራበት ቀን እነርሱ የእኔ ገንዘብ ይሆናሉ፣ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፤ ሰውም የሚያገለግለውን ልጁን እንደሚምር፣ እንዲሁ እምራቸዋለሁ።’”
የአውራጃ ስብሰባ ሌላው ጉልህ ገጽታ ስለ ቆሬ ልጆች የሚተርከው “የይሖዋን ሥልጣን አክብሩ” የሚለው ሙሉ በሙሉ ጥንታዊ አለባበስ የተንጸባረቀበት ድራማ ነበር። አባታቸው በሙሴና በአሮን ላይ ቢያምፅም እነርሱ ለይሖዋ እና እርሱ ሥልጣን ላይ ላስቀመጣቸው ሰዎች ታማኝነታቸውን አሳይተዋል። ቆሬ እና ተከታዮቹ ሲጠፉ የቆሬ ልጆች ከጥፋቱ ተርፈዋል። ቀጥሎ የቀረበው “ለአምላክ ሥልጣን በታማኝነት ተገዙ” የሚለው ንግግር ድራማው በእያንዳንዳችን ላይ እንዴት እንደሚሠራ አብራርቷል። ተናጋሪው ቆሬና ተከታዮቹ የወደቁባቸውን ስድስት አቅጣጫዎች በመጥቀስ እኛንም አስጠንቅቋል። ስድስቱ አቅጣጫዎች የይሖዋን ሥልጣን በታማኝነት አለመደገፍ፣ ኩራት፣ የሥልጣን ጥምና ቅናት እንዲጠናወታቸው መፍቀድ፣ ይሖዋ በሾማቸው ሰዎች አለፍጽምና ላይ ትኩረት ማድረግ፣ የማማረር ዝንባሌ ማሳየት፣ ባገኙት የአገልግሎት መብት አለመርካት፣ ለይሖዋ ታማኝ ሆኖ ከመገኘት ይልቅ ለወዳጅነት ወይም ለቤተሰብ ትስስር ቅድሚያ መስጠት ናቸው።
የሕዝብ ንግግሩ ጭብጥ “ለአሕዛብ ሁሉ እውነትን እያስተማሩ ያሉት እነማን ናቸው?” የሚል ነበር። በዚህ ንግግር አማካኝነት ማብራሪያ የተሰጠው ስለ አጠቃላይ እውነት ሳይሆን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ መሠከረለት ስለ ይሖዋ ዓላማ ስለሚናገረው እውነት ነበር። ተናጋሪው ከምናምንባቸው ነገሮች ጋር ተዛምዶ ስላለው እውነት፣ የአምልኮ ሥርዓትን ስለሚመለከተው እውነት እንዲሁም ከግል አኗኗር ጋር ስለሚዛመደው እውነት ማብራሪያ ሰጥቷል። የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖችን ከዛሬዎቹ የይሖዋ ምሥክሮች ጋር በማነጻጸር በተሰጠው በዚህ ማብራሪያ ‘አምላክ በእርግጥ በመካከላችን እንዳለ’ ያለን እምነት ይበልጥ ተጠናክሯል።—1 ቆሮንቶስ 14:25
የሳምንቱ የመጠበቂያ ግንብ ጥናት ፍሬ ሐሳቦች ከቀረቡ በኋላ በስብሰባው ላይ የተገኙት የአምላክ ቃል አስተማሪዎች በሙሉ “ሌሎችን እንድናስተምር የተሰጠንን ተልዕኮ በጥድፊያ ስሜት መፈጸም” የሚል ጭብጥ ባለው የመደምደሚያ ንግግር አማካኝነት ለተግባር የሚያንቀሳቅስ ማበረታቻ ተሰጥቷቸዋል። በአጭሩ የቀረበው ክለሳ በማስተማሩ ሥራ ጥቅሶችን የመጠቀምን አስፈላጊነት፣ ብቃቱን ያሟላን አስተማሪዎች መሆን የምንችልባቸውን መንገዶች እንዲሁም ለሌሎች በምናስተምረው እውነት ላይ እምነት ማዳበራችን አስፈላጊ መሆኑን ያጎላ ነበር። ተናጋሪው ‘እድገታችን ግልጥ ሆኖ እንዲታይ’ እንዲሁም ‘ለራሳችንና ለትምህርታችን ጥንቃቄ እንድናደርግ’ በጥብቅ አሳስቦናል።—1 ጢሞቴዎስ 4:15, 16
“የአምላክ ቃል አስተማሪዎች” በተባለው የአውራጃ ስብሰባ ያገኘነው መንፈሳዊ ምግብ ምንኛ የተትረፈረፈ ነው! የአምላክን ቃል በማስተማር ረገድ ከሁሉ የላቀውን አስተማሪ ይሖዋንና ታላቁን አስተማሪ ኢየሱስ ክርስቶስን እንምሰል።
[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
አንዳንዶች የሚያስፈልጋቸውን ከግምት ውስጥ በማስገባት የተዘጋጁ አዳዲስ ጽሑፎች
“የአምላክ ቃል አስተማሪዎች” የአውራጃ ስብሰባ ተካፋዮች በአንዳንድ የምድር ክፍሎች ላይ ለሚኖሩ ሕዝቦች ቅዱስ ጽሑፋዊ እውነትን ለማስተማር የሚረዱ ሁለት ጽሑፎችን በማግኘታቸው በጣም ተደስተዋል። የማይሞት መንፈስ አለህን? (እንግሊዝኛ) የሚል ርዕስ ያለው ትራክት የአገሬው ቋንቋዎች “ነፍስ” እና “መንፈስ” ለሚሉት ቃላት የተለያየ ቃል በሌላቸው አገሮች ውስጥ የሚኖሩ ሰዎችን ውይይት ለማስጀመር የሚረዳ ጠቃሚ መሣሪያ ነው። አዲሱ ትራክት የመንፈስ ኃይል እና መንፈሳዊ ፍጥረት የተለያዩ ነገሮች እንደሆኑና ሰዎች በሚሞቱበት ጊዜ መንፈሳዊ ፍጥረት እንደማይሆኑ በግልጽ ያሳያል።
በአውራጃ ስብሰባው ሁለተኛ ቀን መደምደሚያ ላይ “እርካታ ያለው ሕይወት—እንዴት ማግኘት ይቻላል?” (እንግሊዝኛ) የሚል ብሮሹር መውጣቱ ተነገረ። ይህ ብሮሹር የራሱ የሆነ ስብዕና ያለው ፈጣሪ እንዲሁም በመለኮታዊ መንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ መጽሐፍ ስለመኖሩ ምንም የማያውቁ ሰዎችን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማስጀመር ተብሎ የተዘጋጀ ነው። እነዚህን አዳዲስ ጽሑፎች እስከ አሁን በአገልግሎትህ ተጠቅመህባቸዋል?
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በኢጣሊያ ሚላን እና በዓለም ዙሪያ በተደረጉ የአውራጃ ስብሰባዎች ላይ በመቶዎች የሚቆጠሩ ተጠምቀዋል
[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አድማጮች “የይሖዋን ሥልጣን አክብሩ” በተባለው ድራማ በእጅጉ ተነክተዋል