የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w02 4/1 ገጽ 21-24
  • አምላክ አሕዛብን ሁሉ ይቀበላል

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • አምላክ አሕዛብን ሁሉ ይቀበላል
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2002
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ጥንታዊ ምሳሌ
  • ሳምራውያንንና አይሁዳዊ ያልሆኑትን መቀበል
  • ጳውሎስ​—⁠ለአሕዛብ የተመረጠ ዕቃ
  • የምድር አሕዛብን ሁሉ መርዳት
  • ምሕረት ስለ ማሳየት ትምህርት አግኝቷል
    በእምነታቸው ምሰሏቸው
  • ምሕረት ስለ ማሳየት ትምህርት አግኝቷል
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2009
  • ሌሎችን በይሖዋ ዓይን ለማየት ጣሩ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2003
  • ዮናስ ስለ ይሖዋ ምሕረት ትምህርት አገኘ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1996
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2002
w02 4/1 ገጽ 21-24

አምላክ አሕዛብን ሁሉ ይቀበላል

ጆን ለመጀመሪያ ጊዜ ማሊ ሄዶ በነበረበት ወቅት ማማዱ እና ቤተሰቡ ባደረጉለት ሞቅ ያለ የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ ልቡ ተነክቶ ነበር። ጆን መሬት ላይ ተቀምጦ ለሁሉም በአንድ ገበታ ላይ ከቀረበው ምግብ ባልለመደው መንገድ እየተመገበ ሳለ ለጋባዡ ውድ ስጦታ የሆነውን የመንግሥቱን ምሥራች ከአምላክ ቃል ከመጽሐፍ ቅዱስ እንዴት ሊያካፍለው እንደሚችል ያስብ ነበር። ጆን በማሊ ውስጥ መግባቢያ ቋንቋ የሆነውን ፈረንሳይኛን የሚያውቅ ቢሆንም ከእሱ ፍጹም የተለየ ሃይማኖትና አስተሳሰብ ካለው ቤተሰብ ጋር እንዴት ሊግባባ እንደሚችል ግራ ገብቶት ነበር።

ጆን ስለ ባቤል ከተማ የሚናገረውን የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ አስታወሰ። አምላክ የዓመፀኞቹን ሕዝቦች ቋንቋ የደባለቀው እዚያ ነበር። (ዘፍጥረት 11:1-9) በዚህም የተነሳ የተለያየ ቋንቋ፣ ሃይማኖትና አስተሳሰብ ያላቸው ሕዝቦች በልዩ ልዩ የምድር ክፍሎች ብቅ አሉ። ከቦታ ወደ ቦታ የሚደረገው ጉዞና ፍልሰት የተለመዱ ነገሮች እየሆኑ በመጡበት በአሁኑ ጊዜ ብዙዎች ጆን እንዳጋጠመው ያለ ችግር በሚኖሩበት አካባቢ እንኳን ሳይቀር ያጋጥማቸዋል። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተውን ተስፋቸውን ከእነርሱ የተለየ አስተዳደግ ላላቸው ሰዎች እንዴት ማካፈል እንደሚችሉ ይቸግራቸዋል።

ጥንታዊ ምሳሌ

ዮናስ በእስራኤል ውስጥ እንደነበሩት ሌሎች ነቢያት ሁሉ የነቢይነት ተግባሩን በዋነኛነት ያከናውን የነበረው በእስራኤላውያን መካከል ነበር። ከዳተኛው የአሥሩ ነገድ መንግሥት አምላክን በማያስከብሩ ድርጊቶች ይካፈል በነበረበት ወቅት ትንቢት ተናግሯል። (2 ነገሥት 14:23-25) ዮናስ የትውልድ አገሩን ለቆ ወደ አሦር በመሄድ የተለየ ሃይማኖትና ባሕል ላላቸው ለነነዌ ነዋሪዎች እንዲሰብክ ልዩ ተልዕኮ ሲሰጠው ምን እንደተሰማው ገምት። ዮናስ የነነዌ ሰዎች የሚናገሩትን ቋንቋ አያውቅ ይሆናል፣ ቢያውቅም እንኳን አቀላጥፎ ላይናገር ይችላል። ሁኔታው ምንም ይሁን ምን ዮናስ የተሰጠው ተልዕኮ ከባድ ሆኖ ስለተሰማው ወደ ሌላ አገር ኮበለለ።​—⁠ዮናስ 1:1-3

ዮናስ፣ ይሖዋ አምላክ ውጫዊ ገጽታን ከመመልከት አልፎ ልብን እንደሚመረምር መማር አስፈልጎት እንደነበር ግልጽ ነው። (1 ሳሙኤል 16:7) ይሖዋ ዮናስን ከመስጠም በተአምር ካዳነው በኋላ ለነነዌ ነዋሪዎች እንዲሰብክ ለሁለተኛ ጊዜ አዘዘው። ዮናስ ታዘዘ፤ በውጤቱም የነነዌ ነዋሪዎች በነቂስ ንስሐ ገቡ። ዮናስ ግን አሁንም አመለካከቱን አላስተካከለም። ይሖዋ የሚታይ ምሳሌ በመጠቀም አስተሳሰቡን መለወጥ እንደሚያስፈልገው አስተማረው። ይሖዋ እንዲህ ሲል ዮናስን ጠየቀው:- “ቀኛቸውንና ግራቸውን የማይለዩ ከመቶ ሀያ ሺህ የሚበልጡ ሰዎች . . . ላሉባት ለታላቂቱ ከተማ ለነነዌ አላዝንምን?” (ዮናስ 4:5-11) በዛሬው ጊዜ የምንገኝ እኛስ? ከእኛ የተለየ አስተዳደግ ያላቸውን ሰዎች እንዴት መርዳት እንችላለን?

ሳምራውያንንና አይሁዳዊ ያልሆኑትን መቀበል

በመጀመሪያው መቶ ዘመን ኢየሱስ ተከታዮቹን አሕዛብን ሁሉ ደቀ መዛሙርት እንዲያደርጉ አዝዟቸው ነበር። (ማቴዎስ 28:19) ይህን ማድረግ ለእነሱ ቀላል አልነበረም። የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት አይሁዳውያን ስለነበሩ እንደ ዮናስ ይነጋገሩ የነበረው የእነሱ ዓይነት አስተዳደግና ባሕል ካላቸው ሰዎች ጋር ብቻ ነበር። በጊዜው ተስፋፍቶ የነበረው ከወገናዊነት የመነጨ ጥላቻም ተጽዕኖ አሳድሮባቸው ሊሆን እንደሚችልም የሚጠበቅ ነው። ይሁን እንጂ ይሖዋ አገልጋዮቹ ፈቃዱን ደረጃ በደረጃ ለአሕዛብ እንዲገልጡላቸው ሁኔታዎችን አመቻቸ።

የመጀመሪያው እርምጃ በአይሁዳውያንና በሳምራውያን መካከል የነበረውን ጭፍን ጥላቻ ማስወገድ ነበር። አይሁዳውያን ከሳምራውያን ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት አልነበራቸውም። ሆኖም ኢየሱስ ሳምራውያን ወደፊት ምሥራቹን የሚቀበሉበትን መንገድ በተደጋጋሚ አመ​ቻችቷል። ሳምራዊት የሆነች ሴት በማነጋገር አድሎ እንደማያደርግ አሳየ። (ዮሐንስ 4:​7-26) በሌላ አጋጣሚ ስለ ደጉ ሳምራዊ የሚገልጽ ምሳሌ በመናገር አይሁዳዊ ያልሆኑ ሰዎች ጎረቤታቸውን ሊወዱ እንደሚችሉ ለአንድ ሃይማኖተኛ አይሁዳዊ ገለጸ። (ሉቃስ 10:​25-37) ይሖዋ ሳምራውያንን ወደ ክርስቲያን ጉባኤ የሚያመጣበት ጊዜ ሲደርስ አይሁዳውያን የነበሩት ፊልጶስ፣ ጴጥሮስና ዮሐንስ ለሰማሪያ ነዋሪዎች ሰበኩላቸው። መልእክታቸው በዚያች ከተማ ውስጥ ከፍተኛ ደስታ አስገኘ።​—⁠ሥራ 8:4-8, 14-17

አይሁዳውያን ክርስቲያኖች በርቀት ይዛመዷቸው የነበሩትን ሳምራውያንን መውደድ ከብዷቸው ከነበረ በአይሁዳውያን ይናቁና ይጠሉ ለነበሩት አይሁዳውያን ላልሆኑ ሰዎች ወይም ለአሕዛብ የጎረቤት ፍቅር ማሳየት ይበልጥ እንደሚያስቸግራቸው የታወቀ ነው። ይሁን እንጂ ከኢየሱስ ሞት በኋላ በአይሁዳውያን ክርስቲያኖችና በአሕዛብ መካከል የነበረው ግድግዳ ሊወገድ ይችላል። (ኤፌሶን 2:13, 14) ጴጥሮስ ይህን አዲስ ዝግጅት እንዲቀበል ለመርዳት ይሖዋ በራእይ እንዲህ አለው:- “እግዚአብሔር ያነጻውን አንተ አታርክሰው።” ከዚያም የይሖዋ መንፈስ ቆር​ኔሌዎስ ወደተባለ አንድ አሕዛብ መራው። ጴጥሮስ የአምላክን አመለካከት ማለትም ከአሕዛብ ወገን የሆነውን ይህን ሰው አምላክ ስላነጻው እሱ ርኩስ ብሎ ሊጠራው እንደማይገባ ሲረዳ በመንፈስ ቅዱስ ተገፋፍቶ እንዲህ አለ:- “እግዚአብሔር ለሰው ፊት እንዳያደላ ነገር ግን በአሕዛብ ሁሉ እርሱን የሚፈራና ጽድቅን የሚያደርግ በእርሱ የተወደደ እንደ ሆነ በእውነት አስተዋልሁ።” (ሥራ 10:9-35) አምላክ መንፈስ ቅዱስን በላያቸው ላይ በማፍሰስ ቆርኔሌዎስንና ቤተሰቡን እንደተቀበለ ሲያሳይ ጴጥሮስ ምንኛ ተደንቆ ይሆን!

ጳውሎስ​—⁠ለአሕዛብ የተመረጠ ዕቃ

የጳውሎስ አገልግሎት ይሖዋ አገልጋዮቹ ሁሉንም ዓይነት ሰዎች እንዲወዱና እንዲረዱ እንዴት ደረጃ በደረጃ እንደሚያሰለጥናቸው የሚያሳይ ግሩም ምሳሌ ነው። ጳውሎስ ወደ ክርስትና በተለወጠበት ወቅት በአሕዛብ ፊት ስሙን ለመሸከም የተመረጠ ዕቃ ሆኖ እንደሚያገለግለው ኢየሱስ ተናግሯል። (ሥራ 9:15) ከዚያ በኋላ ጳውሎስ ምሥራቹን ለአሕዛብ ለማወጅ አምላክ በእሱ ለመጠቀም ስላለው ዓላማ ለማሰላሰል ሳይሆን አይቀርም ወደ ዓረብ ምድር ሄደ።​—⁠ገላትያ 1:15-17

ጳውሎስ በመጀመሪያ የሚስዮናዊ ጉዞው ወቅት አይሁዳውያን ላልሆኑ ሰዎች በመስበክ ረገድ ቅንዓት አሳይቷል። (ሥራ 13:46-48) ይሖዋ የጳውሎስን እንቅስቃሴ መባረኩ ሐዋርያው ነገሮችን በይሖዋ ዝግጅት መሠረት እየሠራ እንደነበረ የሚያሳይ ማረጋገጫ ነው። ጳውሎስ አይሁዳውያን ካልሆኑ ወንድሞቹ ጋር ከመቀራረብ በመቆጠብ አድልዎ ያሳየውን ጴጥሮስን በድፍረት ሲገስጸው የይሖዋን አመለካከት በደንብ እንደተገነዘበ አሳይቷል።​—⁠ገላትያ 2:11-14

ጳውሎስ በሁለተኛው የሚስዮናዊ ጉዞው ወቅት የሮማ አውራጃ በነበረችው በቢታንያ እንዳይሰብክ በመንፈስ ቅዱስ መከልከሉ ይሖዋ የጳውሎስን እንቅስቃሴ ይመራ እንደነበር የሚያሳይ ተጨማሪ ማስረጃ ነው። (ሥራ 16:7) ጳውሎስ ወደ ቢታንያ እንዳይሄድ የተከለከለው ጊዜው ገና ስላልደረሰ ይመስላል። ከጊዜ በኋላ ግን አንዳንድ የቢታንያ ሰዎች ክርስቲያን ሆነዋል። (1 ጴጥሮስ 1:1) በራእይ አንድ የመቄዶንያ ሰው “ወደ መቄዶንያ ተሻገርና እርዳን” በማለት ለመነው። ጳውሎስ በዚያ የሮማ አውራጃ ምሥራቹን ለማወጅ መንገዱን መቀየር እንዳለበት ተገነዘበ።​—⁠ሥራ 16:9, 10

ጳውሎስ ለአቴና ሰዎች በሚሰብክበት ወቅት አቀራረቡን ከሁኔታዎች ጋር የማስማማት ችሎታው ክፉኛ ተፈትኖ ነበር። የግሪክና የሮም ሕግ ባዕድ አማልክትንና አዳዲስ ሃይማኖታዊ ልማዶችን ለሕዝብ ማስተዋወቅን ይከለክል ነበር። ጳውሎስ ለሰዎች የነበረው ፍቅር ሃይማኖታዊ ልማዶቻቸውን በጥንቃቄ እንዲመረምር ገፋፍቶታል። በአቴንስ እያለ “ለማይታወቅ አምላክ” የሚል ጽሑፍ የተቀረጸበት መሠዊያ ተመለከተ። በምሥክርነት ሥራው ይህን ሐሳብ ጠቅሶታል። (ሥራ 17:22, 23) መልእክቱን በደግነትና አክብሮት በተሞላበት መንገድ ለማስተዋወቅ እንዴት ያለ ግሩም ዘዴ ነው!

ጳውሎስ ለአሕዛብ ሐዋርያ በመሆን ያከናወነው ሥራ ያስገኘውን ውጤት መለስ ብሎ ሲያስብ ምንኛ ተደስቶ ይሆን! በቆሮንቶስ፣ በፊልጵስዩስ፣ በተሰሎንቄና በገላትያ በሚገኙ ከተሞች አይሁዳዊ ያልሆኑ አያሌ ክርስቲያኖችን ያቀፉ ጉባኤዎች እንዲቋቋሙ ረድቷል። እንደ ደማሪስ፣ ዲዮናስዮስ፣ ሰርግዮስ ጳውሎስና ቲቶ ያሉ የእምነት ወንዶችና ሴቶችን ረድቷል። ስለ ይሖዋም ሆነ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ምንም እውቀት ያልነበራቸው ሰዎች የክርስትናን እውነት ሲቀበሉ መመልከት ምንኛ ልዩ መብት ነው! ጳውሎስ አይሁዳውያን ያልሆኑ ሰዎች እውነትን እንዲያውቁ በመርዳት ስለተጫወተው ሚና ሲናገር እንዲህ ብሏል:- “ክርስቶስ ባልተጠራበት ስፍራ ወንጌልን መስበክ የዘወትር ምኞቴ ነበር። ይልቁንም፣ ‘ስለ እርሱ ያልተነገራቸው ያያሉ፤ ያልሰሙም ያስተውላሉ’ ተብሎ እንደ ተጻፈ ነው።” (ሮሜ 15:20, 21 አ.መ.ት ) ከእኛ የተለየ ባሕል ላላቸው ሰዎች ምሥራቹን በማወጁ ሥራ ልንካፈል እንችላለን?

የምድር አሕዛብን ሁሉ መርዳት

ሰሎሞን ኢየሩሳሌም በሚገኘው ቤተ መቅደስ ለማምለክ የሚመጡትን እስራኤላውያን ያልሆኑ ሰዎችን አስመልክቶ ለይሖዋ ጸልዮአል። “አንተ በማደሪያህ በሰማይ ስማ፤ የምድርም አሕዛብ ሁሉ ስምህን ያውቁ ዘንድ እንደ ሕዝብህም እንደ እስራኤል ይፈሩህ ዘንድ፣ በዚህም በሠራሁት ቤት ስምህ እንደ ተጠራ ያውቁ ዘንድ፣ እንግዳው የሚለምንህን ሁሉ አድርግ” በማለት ልመና አቅርቧል። (1 ነገሥት 8:41-43 በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።) በዛሬው ጊዜ በብዙ አገሮች የሚገኙ በሺህ የሚቆጠሩ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ተመሳሳይ ስሜት ያንጸባርቃሉ። እንደ ነነዌ ሰዎች በመንፈሳዊ ‘ቀኛቸውንና ግራቸውን የማይለዩ’ ሰዎች ያጋጥሟቸዋል። የመንግሥቱ ሰባኪዎች ከተለያዩ ሕዝቦች እውነተኛ አምላኪዎች እንደሚሰበሰቡ የሚናገሩት ትንቢቶች ፍጻሜያቸውን እንዲያገኙ በመርዳቱ ተግባር ተካፋይ ለመሆን ይጓጓሉ።​—⁠ኢሳይያስ 2:2, 3፤ ሚክያስ 4:1-3

በሕዝበ ክርስትና ውስጥ የሚገኙ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን የተስፋ መልእክት እንደሚቀበሉ ሁሉ በሌሎች ሃይማኖቶች ውስጥ ያሉ ሰዎችም ይህንን መልእክት በመቀበል ላይ ናቸው። ይህ አንተን በግልህ እንዴት ሊነካህ ይገባል? ራስህን በሐቀኝነት መርምር። በውስጥህ ሥር የሰደደ ጭፍን ጥላቻ እንዳለብህ ከተሰማህ የፍቅር ባሕርይን በመኮትኮት አሸንፈው።a አምላክ የሚቀበላቸውን ሰዎች ለመቀበል እምቢተኛ አትሁን።​—⁠ዮሐንስ 3:16

የተለየ አስተዳደግ ያላቸውን ሰዎች ከማነጋገርህ በፊት ስለ እነርሱ በቂ መረጃ ለማግኘት ምርምር አድርግ። ከእምነታቸው፣ ከሚያሳስባቸው ጉዳይና ከአስተሳሰባቸው ጋር ራስህን አስተዋውቅ፤ ከዚያም ሁለታችሁም የምትስማሙበትን የጋራ ነጥብ ፈልግ። ለሌሎች ደግነትና ርኅራኄ አሳይ። ከመከራከር ተቆጠብ፣ ግትር አትሁን ከዚያ ይልቅ አዎንታዊ አመለካከት ይኑርህ። (ሉቃስ 9:52-56) እንዲህ ማድረግህ “ሰዎች ሁሉ እንዲድኑና እውነትን ወደ ማወቅ እንዲደርሱ” ፈቃዱ የሆነውን ይሖዋን ደስ ታሰኛለህ።​—⁠1 ጢሞቴዎስ 2:4 አ.መ.ት

በጉባኤያችን ውስጥ የተለያየ ዓይነት አስተዳደግ ያላቸው ሰዎች በመኖራቸው ምንኛ ደስተኞች ነን! (ኢሳይያስ 56:6, 7) በዛሬው ጊዜ እንደ ሜሪ፣ ዮሐንስ፣ እስጢፋኖስ እና ቶማስ ያሉ ስሞችን ብቻ ሳይሆን እንደ ማማዱ፣ ሐዋ፣ ኡጁሉ እና ጀማል ያሉ ስሞችንም መስማት ምንኛ አስደሳች ነው! በእርግጥም ‘ሥራ የሞላበት ትልቅ በር ተከፍቶልናል።’ (1 ቆሮንቶስ 16:9) የማያዳላው አምላክ ይሖዋ ከአሕዛብ ሁሉ የተውጣጡ ሰዎችን ለመቀበል ያቀረበውን ግብዣ ለሰዎች ለማድረስ ባገኘነው አጋጣሚ ሁሉ እንጠቀም!

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ሐምሌ 8, 1996 ንቁ! (እንግሊዝኛ) ገጽ 5-7 ላይ “ለሐሳብ ልውውጥ እንቅፋት የሚሆኑ ግድግዳዎች” የሚለውን ተመልከት።

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጳውሎስ አቀራረቡን ከሁኔታዎች ጋር በማስማማት ላገኛቸው ሰዎች ሁሉ ምሥራቹን አካፍሏል

. . . በአቴንስ

. . . በፊልጵስዩስ

. . . በጉዞ ላይ

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ