የሰይጣን አገዛዝ የገነነበት ዘመን ነበርን?
ዘኒው ዮርክ ታይምስ የተባለው ጋዜጣ በናዚ የማጎሪያ ካምፖች ታስረው የነበሩ ንጹሐን ሰዎች ነጻ የወጡበትን 50ኛ ዓመት በዓል አስመልክቶ ጥር 26, 1995 ባወጣው ዘገባ ላይ እንዲህ ብሎ ነበር:- “የምንኖረው የሰይጣን አገዛዝ በገነነበት መቶ ዘመን ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም። ሰዎች በዘር፣ በሃይማኖት ወይም በመደብ ልዩነት የተነሳ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሌሎች ሰዎችን ለመጨፍጨፍ እንዲህ ያለ ከፍተኛ ዝንባሌና ፍላጎት ያሳዩበት ሌላ ዘመን የለም።”
በታሪክ ውስጥ ከተፈጸሙት የዘር ማጥፋት ዘመቻዎች ሁሉ በሰፊው የሚታወቀው የናዚ እልቂት ስድስት ሚልዮን የሚያህሉ አይሁዳውያንን ጨርሷል። ወደ ሦስት ሚልዮን የሚጠጉ የአይሁድ ዝርያ የሌላቸው ፖላንዳውያንም “ፎርጎትን ሆሎኮስት” ተብሎ በተሰየመው የጅምላ ጭፍጨፋ ተገድለዋል።
ጆናታን ግሎቨር ሂውማኒቲ —ኤ ሞራል ሂስትሪ ኦቭ ዘ ትዌንቲዝ ሴንቸሪ በተባለው መጽሐፋቸው ላይ “ከ1900 እስከ 1989 ባሉት ዓመታት ውስጥ 86 ሚልዮን የሚያህሉ ሰዎች በጦርነት አልቀዋል” ሲሉ ጽፈዋል። አክለውም እንዲህ ብለዋል:- “በ20ኛው መቶ ዘመን በተካሄዱት ጦርነቶች የተገደሉትን ሰዎች ብዛት ለመገመት ያዳግታል። ከእነዚህ ሰዎች መካከል ሁለት ሦስተኛ የሚሆኑት (58 ሚልዮን) ያለቁት በሁለቱ የዓለም ጦርነቶች በመሆኑ በአማካይ ይህን ያህል ሰው በጦርነት ሞቷል ብሎ መናገር እውነታውን ለማገናዘብ አይረዳም። ሆኖም በእነዚህ ጦርነቶች የሞቱትን ሰዎች ቁጥር በክፍለ ዘመኑ ውስጥ እኩል እንከፋፍል ብንል በየቀኑ 2, 500 የሚያህሉ ሰዎች በጦርነት ይገደሉ ነበር ማለት ነው፤ ይህም ለ90 ዓመታት ያህል በየሰዓቱ ከ100 በላይ ሰዎች ሞተዋል ማለት ነው።”
በዚህም ምክንያት 20ኛው መቶ ዘመን በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ በደም አፍሳሽነቱ አቻ የማይገኝለት ዘመን ተብሎ ተጠርቷል። ናዲዬዥዳ ማንዲልሽታም የተባሉ አንዲት ሴት ሆፕ አጌይንስት ሆፕ በተባለው መጽሐፋቸው ላይ “የሰብዓዊነት መሥፈርቶች ጎድፈውና ተረግጠው ክፋት ድል ሲያደርግ ተመልክተናል” ሲሉ ጽፈዋል። ጥሩነት ከክፋት ጋር በሚያደርገው ትግል በእርግጥ ክፋት ድል አድርጓልን?
[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
COVER: Mother and daughter: J.R. Ripper/Social Photos
[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
U.S. Department of Energy photograph