ሰዎች ለመንፈሳዊ እሴቶች ያላቸው አመለካከት እየተለወጠ መጥቷል
“አሥራ አምስት እጮኛሞች [የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ] ከጋብቻ በፊት የምትሰጠውን ትምህርት ለማዳመጥ ተገኝተዋል። በዚያ ከተገኙት 30 ሰዎች መካከል እምነት እንዳላቸው የተናገሩት 3 ብቻ ናቸው።”ላ ክሩዋ፣ ዕለታዊ የፈረንሳይ ካቶሊክ ጋዜጣ
በዛሬው ጊዜ ሰዎች ለሃይማኖታዊ እሴቶች ያላቸው አመለካከት በእጅጉ ተለውጧል። ዓለም አቀፋዊ ስርጭት ያለው ኒውስዊክ መጽሔት በሐምሌ 12, 1999 እትሙ “አምላክ ሞቶ ይሆን?” የሚል የሽፋን ርዕስ ይዞ ወጥቶ ነበር። መጽሔቱ ምዕራብ አውሮፓን አስመልክቶ ካቀረበው መረጃ አንጻር ሲታይ ሁኔታው እንደዚያ ይመስላል። በዚያው ዓመት ጥቅምት ላይ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ሲኖዶስ ሮም ውስጥ ያደረገውን ስብሰባ በተመለከተ ለ ሞንድ የተባለው የፈረንሳይ ጋዜጣ እንዲህ ሲል ዘግቧል:- “ቤተ ክርስቲያኒቱ ‘በጥላቻ ዓይን’ ለሚያያት ኅብረተሰብ የምታቀርበው ትምህርት ተቀባይነት እያጣ ነው። . . . ኢጣሊያ ውስጥ የካቶሊክ እምነት ተከታዮች ሃይማኖታዊ ትምህርቶችንና ተግባሮችን በተመለከተ ያላቸው አመለካከት የተለያየ ነው። . . . ጀርመን ውስጥ የቅድመ ውርጃ ምክር መስጫ ማዕከላትን በተመለከተ የተፈጠረው ውዝግብ በጳጳሱና አምባገነናዊ መመሪያዎችን ለመቀበል እምቢተኛ በሆነው ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት መካከል ያለውን ልዩነት ይበልጥ አስፍቶታል። [ኔዘርላንድ] ሥነ ምግባርንና የምሕረት ግድያን በተመለከተ የወሰደችው ከባድ አቋም አገሪቱ በአስደንጋጭ ሁኔታ ከክርስትና እምነት እየራቀች መሆኑን ያመላክታል ሲሉ አንዳንድ ታዛቢዎች ተናግረዋል።”
በሌሎች አገሮችም ተመሳሳይ ሁኔታ ይታያል። በ1999 የካንተርበሪ ሊቀ ጳጳስ ጆርጅ ኬሪ የእንግሊዝ ቤተ ክርስቲያን “ከሕልውና ውጪ ለመሆን የቀራት አንድ ትውልድ ብቻ ነው” በማለት አስጠንቅቀዋል። በፈረንሳይኛ የሚዘጋጀው ለ ፊጋሮ የተባለው ጋዜጣ “የክርስቲያኗ አውሮፓ ፍጻሜ” በሚል ርዕስ ባወጣው ጽሑፍ ላይ “በየትኛውም ቦታ ተመሳሳይ አዝማሚያ ይታያል። . . . ሰዎች በሥነ ምግባር አቋምና በሃይማኖታዊ መሠረተ ትምህርቶች ላይ ያደረባቸውን ጥርጣሬ ማሰማት ጀምረዋል” ብሏል።
ሰዎች ከሃይማኖት እየራቁ ነው
በአውሮፓ ቤተ ክርስቲያን የሚሄዱ ሰዎች ቁጥር በእጅጉ አሽቆልቁሏል። ፓሪስ ውስጥ ከሚኖሩ ካቶሊኮች መካከል በየሳምንቱ እሁድ ቅዳሴ ላይ የሚገኙት 10 በመቶ የማይሞሉ ሲሆን አዘውትረው ቤተ ክርስቲያን የሚሄዱት ደግሞ 3 ወይም 4 በመቶ ብቻ ናቸው። በዩናይትድ ኪንግደም፣ በጀርመንና በስካንዲኔቪያን አገሮችም ቤተ ክርስቲያን የሚሄዱ ሰዎች ቁጥር ከዚህ የማይለይ አንዳንዴም አነስተኛ እንደሆነ ተስተውሏል።
በቅስና ለማገልገል ፈቃደኛ የሚሆኑ ሰዎች እየተመናመኑ መምጣታቸው ለሃይማኖት መሪዎች አሳሳቢ ጉዳይ ሆኖባቸዋል። አንድ መቶ ዓመት በማይሞላ ጊዜ ውስጥ በፈረንሳይ ያሉ ቄሶች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ በመውረዱ ምክንያት 14 ቄሶች ለ10, 000 ነዋሪዎች የነበረው አኃዝ በዛሬው ጊዜ 1 ቄስ ለ10, 000 ሰዎች ሆኗል። በመላው አውሮፓ የቄሶች አማካይ ዕድሜ እየጨመረ ሲሆን እንደ አየርላንድና ቤልጅየም በመሳሰሉ አገሮች እንኳ ሳይቀር የቄሶች እጥረት እያጋጠመ ነው። ከዚሁ ጋር በተያያዘ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በምትሰጠው የሃይማኖት ትምህርት ላይ የሚገኙ ልጆች ቁጥር እየተመናመነ መጥቷል። ይህም ቤተ ክርስቲያኒቱ ዳግም ለመጠናከር የምታደርገው ጥረት የመሳካቱን ጉዳይ በጣም አጠራጣሪ አድርጎታል።
ሰዎች በሃይማኖት ላይ የነበራቸው ትምክህት ጠፍቷል። “እውነት የሚገኘው በአንድ ሃይማኖት ውስጥ ብቻ ነው” የሚል እምነት የነበራቸው ፈረንሳውያን በ1952 50 በመቶ፣ በ1981 ደግሞ 15 በመቶ ሲሆኑ በአሁኑ ጊዜ ግን 6 በመቶ ብቻ ሆነዋል። ሰዎች ለሃይማኖት ግድየለሽ እየሆኑ መጥተዋል። የየትኛውም ሃይማኖት ተከታይ አለመሆናቸውን የሚናገሩ ሰዎች ቁጥር በ1980 26 በመቶ የነበረው በ2000 ወደ 42 በመቶ አሻቅቧል።—ሌ ቫለር ዴ ፍሮንሴ—ኤቮሉስዮን ደ 1980 አ 2000 (ፈረንሳይ ውስጥ ከ1980 እስከ 2000 በሥነ ምግባር አቋም ላይ የታየ ለውጥ)
በሥነ ምግባር እሴቶች ላይ የደረሰ ሥር ነቀል ለውጥ
በሃይማኖታዊ እሴቶች ላይ ብቻ ሳይሆን በሥነ ምግባር ረገድም ውድቀት ይታያል። ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው ብዙ ሰዎች ቤተ ክርስቲያናቸው ሥነ ምግባርን በተመለከተ የሚያወጣቸውን ደንቦች ለመቀበል ፈቃደኞች አይደሉም። የሃይማኖት መሪዎች የሥነ ምግባር ደንብ የማውጣት መብት አላቸው በሚለው ሐሳብ አይስማሙም። ጳጳሱ ስለ ሰብዓዊ መብት ያላቸውን አቋም የደገፉ ሰዎች የግል ሕይወታቸውን የሚነካ ነገር ሲያነሱ ግን የሚናገሩትን አይቀበሉም። ለምሳሌ ያህል፣ ጳጳሱ የወሊድ መቆጣጠሪያን በተመለከተ ያላቸው አቋም ሌላው ቀርቶ የካቶሊክ እምነት ተከታይ በሆኑ በርካታ ባልና ሚስቶች ዘንድ ተቀባይነት አላገኘም።
እንዲህ ያለው ዝንባሌ በኅብረተሰቡ ውስጥ የተለያየ የኑሮ ደረጃ ያላቸውን ሃይማኖተኛም ሆኑ ሃይማኖተኛ ያልሆኑ ሰዎችን በእኩል ደረጃ ይነካል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በግልጽ የተወገዙ ድርጊቶች በቸልታ ይታለፋሉ። ከሃያ ዓመታት በፊት 45 በመቶ የሚያህሉ ፈረንሳውያን ግብረ ሰዶማዊነትን ይቃወሙ ነበር። በዛሬው ጊዜ ግን 80 በመቶ የሚያህሉት ተቀባይነት እንዳለው ይሰማቸዋል። ምንም እንኳን አብዛኛው ሕዝብ ለትዳር ጓደኛ ታማኝ መሆንን ቢደግፍም ከጋብቻ ውጪ የሚደረጉ ግንኙነቶችን የሚያወግዙት 36 በመቶ ብቻ ናቸው።—ሮሜ 1:26, 27፤ 1 ቆሮንቶስ 6:9, 10፤ ዕብራውያን 13:4
ሃይማኖታዊ እምነቶችን መቀላቀል
በምዕራቡ ዓለም ሰዎች ከተለያዩ ሃይማኖቶች ውስጥ የሚቀበሏቸውን ትምህርቶች ወስደው የራሳቸውን ሃይማኖት መፍጠራቸው እየተለመደ መጥቷል። አንዳንድ መሠረተ ትምህርቶችን ተቀብለው ሌሎቹን ይተዋሉ። አንዳንዶች ክርስቲያን እንደሆኑ እየተናገሩም በሪኢንካርኔሽን ያምናሉ። ሌሎች ደግሞ የተለያዩ ሃይማኖቶች የሚያስተምሯቸውን ትምህርቶች ይቀበላሉ። (መክብብ 9:5, 10፤ ሕዝቅኤል 18:4, 20፤ ማቴዎስ 7:21፤ ኤፌሶን 4:5, 6) ሌ ቫለር ዴ ፍሮንሴ የተባለው መጽሐፍ ዛሬ ብዙ አማኞች ቤተ ክርስቲያን ከምትከተለው ጎዳና በመውጣት ባዝነው እንደሚቀሩ በግልጽ ተናግሯል።
ይሁን እንጂ እንዲህ ያለው ግለሰቦች የራሳቸውን ሃይማኖት የመፍጠር አዝማሚያ የራሱ አደጋ አለው። የሃይማኖት ታሪክ ምሁርና የኧንስቲቱ ደ ፍራንስ ባልደረባ የሆኑት ዦ ደሉሞ አንድ ሰው ከማንኛውም ድርጅት ተነጥሎ የራሱን ሃይማኖት ማቋቋሙ የማይቻል ነገር ነው የሚል ጽኑ እምነት አላቸው። “ማንኛውም እምነት በአንድ የሃይማኖት ድርጅት ውስጥ በጥብቅ ካልተመሠረተ በስተቀር ዕድሜ ሊኖረው አይችልም።” ትክክለኛ የሆኑ መንፈሳዊ እሴቶችና ሃይማኖታዊ ልማዶች አንድ ሰው በሚከተለው ሃይማኖት ውስጥ በሚገባ የታቀፉ መሆን አለባቸው። ታዲያ በለውጥ በሚናወጠው በዚህ ዓለም ውስጥ ትክክለኛ የሆኑ መንፈሳዊ እሴቶችን ከየት ማግኘት ይቻላል?
መጽሐፍ ቅዱስ ተቀባይነት ያላቸውን የባሕርይና የሥነ ምግባር ደንቦች የማውጣት መብት ያለው አምላክ መሆኑን ይናገራል። እርግጥ ይህንን መከተል አለመከተል ለሰዎች የተተወ ነው። በዓለም ዙሪያ የሚኖሩ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ይህ መጽሐፍ ዛሬም ተግባራዊ ጠቀሜታ ያለውና ‘ለእግራቸው መብራት፣ ለመንገዳቸው ብርሃን’ መሆኑን ይቀበላሉ። (መዝሙር 119:105) እዚህ መደምደሚያ ላይ ሊደርሱ የቻሉት እንዴት ነው? ይህ በሚቀጥለው ርዕስ ውስጥ ይብራራል።