ያለሌሎች ድጋፍ መኖር የማንችለው ለምንድን ነው?
“አንድ ብቻ ከመሆን ሁለት መሆን ይሻላል። ቢወድቁ አንዱ ሁለተኛውን ያነሣዋልና።”—ንጉሥ ሰሎሞን
የጥንት እስራኤል ንጉሥ የነበረው ሰሎሞን እንዲህ ብሎ ነበር:- “ድካማቸው መልካም ዋጋ አለውና አንድ ብቻ ከመሆን ሁለት መሆን ይሻላል። ቢወድቁ አንዱ ሁለተኛውን ያነሣዋልና፤ አንዱ ብቻውን ሆኖ በወደቀ ጊዜ ግን የሚያነሣው ሁለተኛ የለውምና ወዮለት።” (መክብብ 4:9, 10) የሰዎችን ባሕርይ በጥልቀት ያስተዋለው ይህ ጠቢብ ንጉሥ የሌሎች ድጋፍ እንደሚያስፈልገንና ራሳችንን አለማግለላችን ጠቃሚ እንደሆነ ጎላ አድርጎ ገልጿል። ይህ ግን ሰብዓዊ አእምሮ ያመነጨው ሐሳብ አይደለም። ሰሎሞን ይህንን የተናገረው አምላክ በመንፈሱ አማካኝነት በገለጠለት ጥበብ ተመርቶ ነው።
ራስን ከሰዎች ማግለል ጥሩ አይደለም። የሰው መድኃኒቱ ሰው ነው። ሁላችንም ብንሆን የሌሎች ማበረታቻና ድጋፍ ያስፈልገናል። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ “መለየት የሚወድድ ምኞቱን ይከተላል፣ መልካሙንም ጥበብ ሁሉ ይቃወማል” ይላል። (ምሳሌ 18:1) በመሆኑም የማኅበራዊ ኑሮ ጠበብት ሰዎች የአንድ ማኅበራዊ ቡድን አባል እንዲሆኑና ለሌሎች በግል አሳቢነት እንዲያሳዩ ማበረታታታቸው የሚያስገርም አይደለም።
ሮበርት ፑትናም የተባሉ አንድ ፕሮፌሰር በማኅበራዊ ኑሮ ላይ ዳግም ሕይወት ለመዝራት ያስችላሉ ብለው ከጠቀሷቸው ነገሮች መካከል አንዱ “ሃይማኖት ያለውን ተጽዕኖ ማጠናከር” ነው። በዚህ ረገድ የይሖዋ ምሥክሮች ዓይነተኛ ምሳሌ ይሆናሉ። ምክንያቱም በዓለም ዙሪያ እንደ ቤተሰብ ባሉ ጉባኤዎች ውስጥ ጥበቃ ያገኛሉ። ከሐዋርያው ጴጥሮስ ቃላት ጋር በሚስማማ መንገድ ለአምላክ አክብሮታዊ ፍርሃት ያላቸውን በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ‘ወንድሞቻቸውን ይወዳሉ።’ (1 ጴጥሮስ 2:17) እንዲሁም የይሖዋ ምሥክሮች ከእውነተኛው አምልኮ ጋር የተያያዙት እንቅስቃሴዎች የአምላክ ቃል በሆነው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን እውነት ለጎረቤቶቻቸው ማስተማርን ስለሚጠይቅባቸው ራሳቸውን ከሌሎች አያገልሉም፤ ይህም መገለል ከሚያስከትለው ጎጂ ውጤት ይጠብቃቸዋል።—2 ጢሞቴዎስ 2:15
ፍቅርና ወዳጅነት ሕይወታቸውን ለወጠው
የይሖዋ ምሥክሮች እያንዳንዱ አባል ጠቃሚ ሚና የሚጫወትበት አንድነት ያለው ኅብረተሰብ ፈጥረዋል። ለምሳሌ ያህል በላቲን አሜሪካ የሚኖሩ ሚጌል፣ ፍሮይላን እና አልማ ሩት የተባሉ የአንድ ቤተሰብ አባላት ታሪክ ተመልከት። በዘር በወረሱት የአጥንት በሽታ የተነሳ ሦስቱም ድንክዬዎች በመሆናቸው ያለ ተሽከርካሪ ወንበር መንቀሳቀስ አይችሉም ነበር። ታዲያ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መቀራረባቸው ሕይወታቸውን የለወጠው እንዴት ነው?
ሚጌል እንዲህ ይላል:- “በጣም ብዙ ችግሮች ተፈራርቀውብኛል፤ ከይሖዋ ሕዝቦች ጋር ከተገናኘሁ በኋላ ግን ሕይወቴ ተለውጧል። ራስን ከሌሎች ማግለል በጣም አደገኛ ነው። በየሳምንቱ ከእምነት አጋሮቼ ጋር በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መገኘት ደስታና እርካታ እንዳገኝ በእጅጉ ረድቶኛል።”
አልማ ሩት ደግሞ እንዲህ ትላለች:- “በከፍተኛ የመንፈስ ጭንቀት የተዋጥኩባቸው ጊዜያት ነበሩ፤ በጣም አዝን ነበር። ስለ ይሖዋ ከተማርኩ በኋላ ግን ከእርሱ ጋር የቀረበ ወዳጅነት መመሥረት እንደምችል ተሰማኝ። ይህ በሕይወቴ ውስጥ ትልቁን ቦታ የምሰጠው ነገር ሆነ። የቤተሰቤም ድጋፍ ያልተለየን ሲሆን ይህም ይበልጥ አቀራርቦናል።”
ሚጌል አባቱ ማንበብና መጻፍ አስተምሮት ነበር። እርሱም በበኩሉ ፍሮይላንና አልማ ሩትን ማንበብና መጻፍ አስተማራቸው። ይህ መንፈሳዊነታቸውን ለመጠበቅ በጣም አስፈላጊ ነበር። አልማ ሩት “ማንበብ መቻላችን በእጅጉ ጠቅሞናል፤ ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስንና በቅዱሳን ጽሑፎች ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎችን በማንበብ ራሳችንን በመንፈሳዊ መገንባት እንችላለን” በማለት ተናግራለች።
በአሁኑ ጊዜ ሚጌል በጉባኤ ውስጥ ሽማግሌ ሆኖ በማገልገል ላይ ነው። ፍሮይላን መጽሐፍ ቅዱስን ከዳር እስከ ዳር ዘጠኝ ጊዜ አንብባዋለች። አልማ ሩትም ከ1996 ጀምሮ አቅኚ ወይም የሙሉ ጊዜ ሰባኪ በመሆን ለይሖዋ የምታቀርበውን አገልግሎት ከፍ አድርጋለች። እንዲህ ትላለች:- “የይሖዋ በረከት ታክሎበት እዚህ ደረጃ መድረስ ችያለሁ፤ ክርስቲያን እህቶቼም በስብከቱ ሥራ ብቻ ሳይሆን በማስተማሩ ሥራም ተሳትፎ እንዳደርግ 11 የሚያህሉትን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቼን በማስጠናበት ወቅት ይረዱኛል።”
ሌላዋ ግሩም ምሳሌ ኤሚሊያ ስትሆን በእግሮቿና በአከርካሪዋ ላይ በደረሰባት አደጋ የተነሳ ያለ ተሽከርካሪ ወንበር መንቀሳቀስ አትችልም ነበር። በሜክሲኮ ሲቲ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱስ አስጠንተዋት በ1996 ተጠመቀች። እንዲህ ትላለች:- “እውነትን ከማወቄ በፊት ራሴን ማጥፋት እፈልግ ነበር። በሕይወት መኖር አስጠልቶኝ ነበር። የባዶነት ስሜት ይሰማኝ ስለነበር ቀን ከሌት አለቅስ ነበር። ከይሖዋ ሕዝቦች ጋር ከተገናኘሁ በኋላ ግን በአንድ የወንድማማች ማኅበር ፍቅር ውስጥ እንደታቀፍኩ ተሰማኝ። በግለሰብ ደረጃ የሚያሳዩኝ አሳቢነት የብርታት ምንጭ ሆኖልኛል። በተለይ አንድ የጉባኤ ሽማግሌ የወንድም እና የአባት ያህል ይንከባከበኝ ነበር። እርሱና አንዳንድ የጉባኤ አገልጋዮች ተሽከርካሪ ወንበሬን እየገፉ ወደ አገልግሎትና ወደ ስብሰባ ይወስዱኛል።”
በ1992 ተጠምቀው የይሖዋ ምሥክር የሆኑት ሆሴ የሚኖሩት ብቻቸውን ነው። አሁን የ70 ዓመት አረጋዊ ሲሆኑ ጡረታ የወጡት በ1990 ነበር። ሆሴ የመንፈስ ጭንቀት ይሰማቸው የነበረ ሲሆን አንድ የይሖዋ ምሥክር ምሥራቹን ከሰበከላቸው በኋላ ግን በስብሰባዎች ላይ መገኘት ጀመሩ። በዚያ የሰሙትና የተመለከቱት ነገር አስደሰታቸው። ለምሳሌ ወንድሞች በጣም እንደሚቀራረቡና ለእሳቸውም በግለሰብ ደረጃ እንደሚያስቡላቸው አስተዋሉ። አሁን ያሉበት ጉባኤ ሽማግሌዎችና አገልጋዮች እንክብካቤ ያደርጉላቸዋል። (ፊልጵስዩስ 1:1፤ 1 ጴጥሮስ 5:2) እንደዚህ ያሉት የእምነት ባልንጀሮቻቸው ‘አጽናንተዋቸዋል።’ (ቆላስይስ 4:10, 11) ሲታመሙ ሐኪም ቤት ይወስዷቸዋል፣ እቤት መጥተው ይጠይቋቸዋል እንዲሁም ቀዶ ሕክምና ባደረጉባቸው አራት ጊዜያት ከጎናቸው አልተለዩም። እንዲህ ብለዋል:- “በጣም ያስቡልኛል፣ ለእኔ እንደ ቤተሰብ ናቸው፤ ከእነርሱ ጋር ስሆን ደስ ይለኛል።”
መስጠት እውነተኛ ደስታ ያስገኛል
ንጉሥ ሰሎሞን “አንድ ብቻ ከመሆን ሁለት መሆን ይሻላል” ያለው ጊዜንና ጉልበትን ቁሳዊ ሀብትን በማሳደድ ላይ ማዋል ከንቱ መሆኑን ከተናገረ በኋላ ነበር። (መክብብ 4:7-9) በዛሬው ጊዜ ግን ብዙዎች በቤተሰብ ውስጥም ሆነ ከቤተሰብ ውጪ ከሰዎች ጋር ያላቸውን ግንኙነት አደጋ ላይ ጥለው ሀብትን ሲያሳድዱ ይታያሉ።
ይህ የስግብግብነትና የራስ ወዳድነት መንፈስ ብዙዎች ራሳቸውን ከሌሎች እንዲያገልሉ አድርጓቸዋል። እንዲህ ዓይነቱ አኗኗር ግን ደስታም ሆነ እርካታ አያስገኝም፤ ምክንያቱም ለእንዲህ ዓይነቱ የስግብግብነት መንፈስ የሚሸነፉ ሁሉ መጨረሻቸው ተስፋ መቁረጥና ብስጭት ነው። በአንጻሩ ግን ከላይ ያየናቸው ተሞክሮዎች ይሖዋን ከሚያገለግሉና ለአምላክም ሆነ ለጎረቤቶቻቸው ፍቅር ካላቸው ሰዎች ጋር መቀራረብ ምን ያህል ጠቃሚ እንደሆነ ያሳያሉ። እነዚህ ግለሰቦች ራስን ማግለል የሚያስከትለውን ጎጂ ተጽዕኖ እንዲያሸንፉ የረዳቸው በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ አዘውትሮ መገኘት፣ በክርስቲያናዊው አገልግሎት በቅንዓት መካፈል እንዲሁም ክርስቲያን ወንድሞች የሚያሳዩአቸው አሳቢነትና ድጋፍ ነው።—ምሳሌ 17:17፤ ዕብራውያን 10:24, 25
ሌሎችን መርዳት እርካታ እንደሚሰጥ የታወቀ ነው፤ ምክንያቱም ማናችንም ብንሆን የሌሎች ድጋፍ ያስፈልገናል። ለሰው ዘር ጠቃሚ ሥራ ያበረከተው አልበርት አንስታይን “የአንድ ሰው ዋጋማነት የሚለካው ከሌሎች በሚያገኘው ነገር ሳይሆን ለሌሎች ሊሰጥ በሚችለው ነው” በማለት ተናግሯል። ይህ አባባል ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ ብፁዕ ነው” በማለት ከተናገረው ሐሳብ ጋር ይስማማል። (ሥራ 20:35) ስለዚህ በሌሎች መፈቀር የሚያስደስት ቢሆንም ለሌሎች ፍቅር ማሳየትም ያለው ጠቀሜታ ይህ ነው የሚባል አይደለም።
ጉባኤዎችን እየጎበኘ በመንፈሳዊ በማበረታታትና ዝቅተኛ ኢኮኖሚ ባላቸው አገሮች ለሚኖሩ ክርስቲያኖች የስብሰባ አዳራሾችን በመገንባት በርካታ ዓመታት ያሳለፈ አንድ ተጓዥ የበላይ ተመልካች እንዲህ ይላል:- “ወንድሞችን ሳገለግልና ፊታቸው በአድናቆት ሲፈካ ስመለከት በጣም ደስ ስለሚለኝ ሌሎችን መርዳት የምችልበትን ተጨማሪ መንገድ እንድፈልግ ይገፋፋኛል። ለደስታ ቁልፉ ለሌሎች በግል አሳቢነት ማሳየት እንደሆነ ከራሴ ተሞክሮ ተምሬያለሁ። እንዲሁም ሽማግሌዎች እንደመሆናችን መጠን ‘ከነፋስ እንደ መሸሸጊያ . . .፣ በጥም ቦታም እንደ ወንዝ ፈሳሽ፣ በበረሀም አገር እንደ ትልቅ ድንጋይ ጥላ’ መሆን እንዳለብን ተገንዝቤያለሁ።”—ኢሳይያስ 32:2
ወንድሞች በአንድነት ሲኖሩ ምንኛ መልካም ነው!
በእርግጥም ሌሎችን መርዳትና ይሖዋን ከሚያገለግሉ ሰዎች ጋር መወዳጀት በርካታ ጥቅሞች ያሉት ሲሆን እውነተኛ ደስታም ያስገኛል። መዝሙራዊው “ወንድሞች በኅብረት ቢቀመጡ፣ እነሆ፣ መልካም ነው፣ እነሆም፣ ያማረ ነው” በማለት ተናግሮ ነበር። (መዝሙር 133:1) የሚጌል፣ የፍሮይላንና የአልማ ሩት ተሞክሮ እንደሚያሳየው የቤተሰብ አንድነት እርስ በርስ በመደጋገፍ ረገድ ቁልፍ ሚና ይጫወታል። ደግሞም በአንድነት በእውነተኛው አምልኮ የሚካፈል ቤተሰብ ማግኘት እንዴት መታደል ነው! ሐዋርያው ጴጥሮስ ለክርስቲያን ባሎችና ሚስቶች ምክር ከሰጠ በኋላ “በመጨረሻው ሁላችሁ በአንድ ልብ ሁኑ፣ የሌላው መከራ ለእናንተ እንደሚሆን አድርጉ፣ እንደ ወንድሞች ተዋደዱ፣ ርኅሩኆችና ትሑታን ሁኑ” በማለት ጽፏል።—1 ጴጥሮስ 3:8
እውነተኛ ጓደኝነት መንፈሳዊም ሆነ ስሜታዊ ጥቅሞች አሉት። ሐዋርያው ጳውሎስ የእምነት ባልንጀሮቹን እንዲህ በማለት አሳስቧቸዋል:- “ድፍረት የሌላቸውን አጽኑአቸው፤ ለደካሞች ትጉላቸው፤ ሰውን ሁሉ ታገሡ። . . . ነገር ግን ሁልጊዜ እርስ በርሳችሁ ለሁሉም መልካሙን ለማድረግ ትጉ።”—1 ተሰሎንቄ 5:14, 15
ስለዚህ ለሌሎች መልካም ለማድረግ የሚያስችሏችሁን አጋጣሚዎች ተጠቀሙባቸው። ሐዋርያው ጳውሎስ “ለሰው ሁሉ ይልቁንም ለሃይማኖት ቤተ ሰዎች መልካም እናድርግ” የሚል ምክር ሰጥቷል። (ገላትያ 6:9, 10) እንዲህ ማድረግህ ሕይወትህ ትርጉም ያለው እንዲሆን ከማስቻሉም በላይ ደስታና እርካታ ያስገኝልሃል። የኢየሱስ ደቀ መዝሙር የነበረው ያዕቆብ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ወንድም ወይም እኅት ራቁታቸውን ቢሆኑ የዕለት ምግብንም ቢያጡ፣ ከእናንተ አንዱም:- በደኅና ሂዱ፣ እሳት ሙቁ፣ ጥገቡም ቢላቸው ለሰውነት ግን የሚያስፈልጉትን ባትሰጡአቸው ምን ይጠቅማቸዋል?” (ያዕቆብ 2:15, 16) የዚህ ጥያቄ መልስ ሳይታለም የተፈታ ነው። ‘እያንዳንዳችን ሌሎችን የሚጠቅመውን እንጂ ራሳችንን የሚጠቅመንን ብቻ’ መመልከት አይኖርብንም።—ፊልጵስዩስ 2:4
የይሖዋ ምሥክሮች አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ ወይም አንድ ዓይነት አደጋ በሚከሰትበት ጊዜ ለሰዎች ቁሳዊ እርዳታ ከማቅረብ በተጨማሪ የአምላክን መንግሥት ምሥራች በትጋት በመስበክ ለሰው ልጆች ጠቃሚ አገልግሎት ያበረክታሉ። (ማቴዎስ 24:14) ይህን አጽናኝና ተስፋ ሰጪ መልእክት በማወጁ ሥራ ከ6,000,000 የሚበልጡ የይሖዋ ምሥክሮች የሚካፈሉ መሆናቸው ለሌሎች ያላቸውን ከልብ የመነጨ አሳቢነት የሚያሳይ ማስረጃ ነው። ይሁን እንጂ በቅዱሳን ጽሑፎች አማካኝነት ሌሎችን መርዳት የሚያሟላው ሌላም መሠረታዊ ፍላጎት አለ። ይህ ፍላጎት ምንድን ነው?
መሠረታዊ ፍላጎት ማሟላት
እውነተኛ ደስታ ለማግኘት የምንፈልግ ከሆነ ከአምላክ ጋር የተቀራረበ ዝምድና መመሥረት ይኖርብናል። ክሬሲ ሞሪሰን ማን ዳዝ ኖት ስታንድ አሎን በተባለው መጽሐፋቸው ላይ እንዲህ ብለዋል:- “ከጥንት ጀምሮ እስከዛሬ ድረስ የሰው ልጅ ከእርሱ እንደሚበልጥና ኃያል እንደሆነ አድርጎ የሚያስበውን አካል ለማምለክ ያለው ፍላጎት ሃይማኖት ተፈጥሯዊ መሆኑንና ሳይንሳዊ እውቅና ሊሰጠው እንደሚገባ ያሳያል። . . . የሰው ልጅ ከእርሱ ይበልጥ ኃያል የሆነን አንድ አካል ለማግኘትና በእርሱ ለማመን ያደረገው ጥረት ዓለም አቀፋዊ መሆኑን ስንመለከት በአድናቆት ልንደመምና አክብሮታዊ ፍርሃት ሊያድርብን ይገባል።”
ኢየሱስ ክርስቶስ “ለመንፈሳዊ ፍላጎታቸው ንቁ የሆኑ ደስተኞች ናቸው” በማለት ተናግሯል። (ማቴዎስ 5:3 NW) ሰዎች ከሌሎች ተገልለው ብቻቸውን ለረጅም ጊዜ መኖር አይችሉም። ከፈጣሪ ተለይቶ ለመኖር መሞከር ደግሞ ከዚህ ይበልጥ የከፋ ነው። (ራእይ 4:10, 11) “የአምላክን እውቀት” ማግኘትና በሥራ ላይ ማዋል በሕይወታችን ትልቁን ቦታ ልንሰጠው ይገባል። (ምሳሌ 2:1-5) አዎን፣ ከአምላክ ተለይተን ብቻችንን መኖር ስለማንችል መንፈሳዊ ፍላጎታችንን ለማርካት ቁርጥ ውሳኔ ማድረግ አለብን። ሕይወታችን አስደሳችና የሚክስ እንዲሆን ‘በምድር ሁሉ ላይ ልዑል ከሆነው’ ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ዝምድና መመሥረት አለብን።—መዝሙር 83:18
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
“በጣም ብዙ ችግሮች ተፈራርቀውብኛል፤ ከይሖዋ ሕዝቦች ጋር ከተገናኘሁ በኋላ ግን ሕይወቴ ተለውጧል።”—ሚጌል
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
“ስለ ይሖዋ ከተማርኩ በኋላ ግን ከእርሱ ጋር የቀረበ ወዳጅነት መመሥረት እንደምችል ተሰማኝ።”—አልማ ሩት
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
‘እውነትን ከማወቄ በፊት የባዶነት ስሜት ይሰማኝ ነበር።’—ኤሚሊያ
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከእውነተኛ አምላኪዎች ጋር መሰብሰባችን መንፈሳዊ ፍላጎታችንን ለማርካት ያስችለናል