ድሆች ይበልጥ እየደኸዩ ናቸው
“አብዛኛው የኅብረተሰቡ ክፍል በድህነት እየማቀቀ ሳለ በደስታና በብልጽግና ሊኖር የሚችል ማኅበረሰብ የለም።”
ይህንን የተናገሩት በ18ኛው መቶ ዘመን ይኖሩ የነበሩት አዳም ስሚዝ የተባሉ የምጣኔ ሃብት ባለሞያ ናቸው። ይህ አባባል እውነት መሆኑ ዛሬ ይበልጥ በገሃድ እየታየ እንዳለ ብዙዎች ይሰማቸዋል። በሀብታሞችና በድሆች መካከል ያለው የኑሮ ልዩነት ይበልጥ እየሰፋ በመሄድ ላይ ነው። በፊሊፒንስ አንድ ሦስተኛ የሚሆነው ሕዝብ ኑሮውን የሚገፋው በቀን ከአንድ የአሜሪካ ዶላር ባነሰ ገቢ ነው። በበለጸጉ አገሮች ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ግን በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ ይህንን ያህል ገንዘብ ማግኘት ይችላሉ። የተባበሩት መንግሥታት የ2002 ሂውማን ዴቨሎፕመንት ሪፖርት እንደገለጸው “በዓለም ላይ በጣም ሀብታም ከሚባሉት ሰዎች መካከል 5 በመቶ የሚሆኑት የሚያገኙት ገቢ የመጨረሻ ድሃ ከሚባሉት ሰዎች መካከል 5 በመቶ የሚሆኑት ከሚያገኙት ገቢ 114 እጥፍ ይበልጣል።”
አንዳንዶች በአንጻራዊ ሁኔታ የተደላደለ ኑሮ ሲኖሩ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሌሎች ሰዎች ግን ባገኙት ቦታ ደሳሳ ጎጆ ቀልሰው ያልተረጋጋ ሕይወት ይመራሉ። የዚህንም ያህል ያልታደሉ ሌሎች ደግሞ ካርቶን አንጥፈው ወይም ላስቲክ ዘርግተው በየጎዳናው ይኖራሉ። አብዛኞቹ በቆሻሻ መጣያ ውስጥ ያገኙትን በመለቃቀም፣ ከባድ ሸክም በመሸከም ወይም አሮጌ ቆርቆሮና ጠርሙስ ሰብስበው በመሸጥ ሕይወታቸውን ለማቆየት ሲጥሩ ይታያሉ።
በሀብታሞችና በድሆች መካከል ከፍተኛ የኑሮ ልዩነት የሚታየው በታዳጊ አገሮች ውስጥ ብቻ አይደለም። የዓለም ባንክ “‘ድሃ ኅብረተሰብ’ የማይገኝበት አገር እንደሌለ” ገልጿል። በመላው ዓለም በጣም ባለጸጋ የሆኑ የተወሰኑ ሰዎች ቢኖሩም የዚያኑ ያህል ደግሞ የሚላስ የሚቀመስ ወይም አንገታቸውን የሚያስገቡበት ጎጆ ለማግኘት የሚዋትቱ ሰዎች አሉ። ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ የዩናይትድ ስቴትስ የሕዝብ ቆጠራ መሥሪያ ቤት በ2001 ያቀረበውን ሪፖርት ጠቅሶ እንደዘገበው በአሜሪካ ውስጥ በሀብታሞችና በድሆች መካከል ያለው የኑሮ ልዩነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሰፋ በመሄድ ላይ ነው። ሪፖርቱ እንዲህ ይላል:- “ባለፈው ዓመት ከአጠቃላዩ የአገሪቱ የቤተሰብ ገቢ ግማሽ ያህሉን ያገኘው ከአገሪቱ ሕዝብ መካከል 20 በመቶ የሚሆነው ባለጸጋ ኅብረተሰብ ነው። . . . 20 በመቶ የሚሆነው የመጨረሻው ድሃ ኅብረተሰብ ግን ያገኘው 3.5 በመቶ ብቻ ነው።” በሌሎች በርካታ አገሮች ያለው ሁኔታም ተመሳሳይ አሊያም የከፋ ነው። ከዓለማችን ሕዝብ መካከል 57 በመቶ የሚሆነው የቀን ገቢው ከ2 ዶላር ያነሰ እንደሆነ አንድ ከዓለም ባንክ የተገኘ ሪፖርት አመልክቷል።
በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ፣ አጠያያቂ በሆነ መንገድ ሃብት ስለሚያጋብሱ ባለ ሥልጣናት የሚገልጹ ዘገባዎች በ2002 ወጥተው ነበር፤ ይህም በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን አሳዝኗቸዋል። ምንም እንኳ በግልጽ የሚታይ ሕገወጥ ድርጊት ባይፈጸምም እነዚህ ባለ ሥልጣናት “ስለ ሌሎች ደንታ ቢስ በመሆን ሃብት በሃብት ላይ እያካበቱ እንደሆነ” ብዙዎች እንደሚሰማቸው ፎርቹን የተባለው መጽሔት ዘግቧል። አንዳንዶች በዓለም ላይ ያለውን ሁኔታ በመመልከት በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በድህነት እየማቀቁ እያሉ ሌሎች በመቶ ሚልዮን የሚቆጠር ገንዘብ ማጋበሳቸው ተገቢ ነውን የሚለው ጉዳይ በጣም ያሳስባቸዋል።
ድህነት እስከ ወዲያኛው መፍትሔ የለውም ማለት ነው?
ይህ ማለት ግን የድሆችን ሰቆቃ ለማስወገድ የሚፍጨረጨሩ ወገኖች የሉም ማለት አይደለም። ቀና አስተሳሰብ ያላቸው የመንግሥት ባለ ሥልጣናትና እርዳታ ሰጪ ድርጅቶች ለውጥ ለማምጣት ብዙ ሙከራዎች ያደርጋሉ። እውነታው ሲታይ ግን ተስፋ አስቆራጭ ነው። ለውጥ ለማምጣት የቱንም ያህል በጎ ጥረቶች ቢደረጉም የ2002 ሂውማን ዴቨሎፕመንት ሪፖርት እንደገለጸው “በርካታ አገሮች ከዛሬ 10፣ 20 ወይም 30 ዓመት በፊት ከነበሩበት በከፋ ድህነት ውስጥ ይገኛሉ።”
ታዲያ ድሆች ምንም ተስፋ የላቸውም ማለት ነው? የሚቀጥለው ርዕስ በአሁኑ ጊዜ ሊረዱህ የሚችሉ ምክሮችንና ምናልባትም ከዚህ ቀደም አስበኸው የማታውቀውን መፍትሔ ስለሚጠቁምህ እንድታነብበው እንጋብዝሃለን።