የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w03 8/15 ገጽ 14-19
  • በይሖዋ ስም ለዘላለም እንሄዳለን!

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • በይሖዋ ስም ለዘላለም እንሄዳለን!
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2003
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ይሖዋ ፍትሐዊ እንድንሆን ይጠብቃል
  • ይሖዋ የሚሰማው የእነማንን ጸሎት ነው?
  • በአምላክ መንፈስ መሞላት
  • ይሖዋ ሁኔታዎችን ያስተካክላል
  • በይሖዋ ስም ለመሄድ ቆርጠናል
  • መንፈሳዊ እረፍት የሚያስገኝ መልእክት
  • የይሖዋ አገልጋዮች እውነተኛ ተስፋ አላቸው
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2003
  • ይሖዋ ከእኛ የሚፈልገው ምንድን ነው?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2003
  • ሚክያስ 6:8—“በአምላክህም ፊት በትሕትና ትራመድ ዘንድ”
    የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችና ማብራሪያቸው
  • ነቢያትን አርዓያ አድርጋችሁ ተመልከቷቸው—ሚክያስ
    የመንግሥት አገልግሎታችን—2014
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2003
w03 8/15 ገጽ 14-19

በይሖዋ ስም ለዘላለም እንሄዳለን!

“እኛም በአምላካችን በእግዚአብሔር ስም ለዘላለም እንሄዳለን።”—ሚክያስ 4:5

1. ከሚክያስ ምዕራፍ 3 እስከ 5 ድረስ የትኞቹ መልእክቶች በግልጽ ተቀምጠዋል?

ይሖዋ ለሕዝቡ የሚናገረው ነገር አለው። በነቢይነት የሚያገለግለውም ሚክያስ ነው። አምላክ በክፉ አድራጊዎች ላይ እርምጃ ለመውሰድ ዓላማ አለው። እስራኤል ከሃዲ በመሆኗ ይቀጣታል። በስሙ የሚሄዱትን ግን ይባርካቸዋል። እነዚህ መልእክቶች በሚክያስ ትንቢት ውስጥ ከምዕራፍ 3 እስከ 5 ድረስ በግልጽ ተቀምጠዋል።

2, 3. (ሀ) የእስራኤል አለቆች ምን ዓይነት ባሕርይ ማሳየት ይገባቸው ነበር? እነርሱ ግን ምን ያደርጉ ነበር? (ለ) በሚክያስ 3:2, 3 ላይ የተጠቀሰውን ምሳሌያዊ አባባል አብራራ።

2 የአምላክ ነቢይ እንዲህ ይላል፦ “የያዕቆብ አለቆችና የእስራኤል ቤት ገዦች ሆይ፣ እባካችሁ ስሙኝ፤ ፍርድን [“ፍትሕን፣” አ.መ.ት] ታውቁ ዘንድ አይገባችሁምን?” አዎን፣ ፍትሕን ማወቅ ይገባቸው ነበር። እነርሱ ግን ምን ያደርጉ ነበር? ሚክያስ እንዲህ አለ፦ “መልካሙን ጠልታችኋል፣ ክፉውንም ወድዳችኋል፤ ቁርበታቸውን ገፍፋችኋቸዋል፣ ሥጋቸውንም ከአጥንታቸው ለያይታችኋል፤ የሕዝቤን ሥጋ በልታችኋል፣ ቁርበታቸውንም ገፍፋችኋቸዋል፣ አጥንታቸውንም ሰብራችኋል፤ ለአፍላል እንደሚሆን ሥጋ ለድስትም እንደሚሆን ሙዳ ቆራረጣችኋቸው።”—ሚክያስ 3:1-3

3 አለቆቹ ድሆችንና አይዞህ ባይ የሌላቸውን ሰዎች ይጨቁናሉ! እዚህ ላይ የተሠራባቸው ምሳሌያዊ ቃላት ለሚክያስ አድማጮች ለመረዳት የሚያስቸግሩ አልነበሩም። አንድ በግ ከታረደ በኋላ ቆዳው ይገፈፍና በብልት በብልት ተቆራርጦ ለመቀቀል ይዘጋጃል። አንዳንድ ጊዜ መቅኒውን ለማውጣት ሲባል አጥንቶቹ ይሰበራሉ። ከዚያም ሥጋውና አጥንቱ አንድ ላይ ሆኖ ሚክያስ በተናገረው ዓይነት ድስት ወይም አፍላል ይቀቀላል። (ሕዝቅኤል 24:3-5, 10) በሚክያስ ዘመን የነበሩት ክፉዎቹ አለቆች በሕዝቡ ላይ ያደርሱ የነበረውን ግፍ የሚገልጽ እንዴት ያለ ተስማሚ ምሳሌ ነው!

ይሖዋ ፍትሐዊ እንድንሆን ይጠብቃል

4. በይሖዋና በእስራኤል አለቆች መካከል ምን ልዩነት ይታያል?

4 አፍቃሪ እረኛ በሆነው በይሖዋ አምላክና በእስራኤል አለቆች መካከል ያለው ልዩነት በጣም የተራራቀ ነው። እነዚህ አለቆች ፍትሕ ማስፈን ስላልቻሉ መንጋውን እንዲጠብቁ የተሰጣቸውን ኃላፊነት ሳይወጡ ቀርተዋል። ከዚህ ይልቅ ለጥቅማቸው ሲሉ ምሳሌያዊዎቹን በጎች ፍትሕ በመንፈግና ሚክያስ 3:10 እንደሚለው ‘ደም በማፋሰስ’ ግፍ ይፈጽሙባቸዋል። ከዚህ ምን ትምህርት ልናገኝ እንችላለን?

5. ይሖዋ በሕዝቦቹ መካከል ግንባር ቀደም ሆነው ከሚያገለግሉት ምን ይጠብቃል?

5 አምላክ በሕዝቦቹ መካከል ግንባር ቀደም ሆነው እያገለገሉ ያሉት ሰዎች ፍትሐዊ እንዲሆኑ ይጠብቅባቸዋል። ይህ በዘመናችን በይሖዋ አገልጋዮች መካከል ተፈጽሞ እናገኛለን። እንዲያውም ይህ ሁኔታ በኢሳይያስ 32:1 ላይ ከተገለጸው ጋር ይስማማል። “እነሆ፣ ንጉሥ በጽድቅ ይነግሣል፣ መሳፍንትም በፍርድ [“በፍትሕ፣” አ.መ.ት] ይገዛሉ” ይላል። ሆኖም በሚክያስ ዘመን የነበረው ሁኔታ ምን ይመስል ነበር? ‘መልካሙን የሚጠሉና ክፉውን የሚወድዱ’ በመሆን ፍርድ በማጣመም ጸንተዋል።

ይሖዋ የሚሰማው የእነማንን ጸሎት ነው?

6, 7. ሚክያስ 3:4 ምን አስፈላጊ ነጥብ ያስገነዝበናል?

6 በሚክያስ ዘመን የነበሩት ክፉ ሰዎች የይሖዋን ሞገስ እናገኛለን ብለው ሊጠብቁ ይችላሉ? እንደማይችሉ የታወቀ ነው! ሚክያስ 3:4 እንዲህ ይላል፦ “የዚያን ጊዜ ወደ እግዚአብሔር ይጮኻሉ፣ እርሱም አይሰማቸውም፤ ሥራቸውንም ክፉ አድርገዋልና በዚያን ጊዜ ፊቱን ከእነርሱ ይሰውራል።” ይህ በጣም አስፈላጊ የሆነ ነጥብ ያስገነዝበናል።

7 ኃጢአት መሥራትን ልማድ ካደረግን ይሖዋ ጸሎታችንን አይሰማም። በተለይ አምላክን በታማኝነት የምናገለግል እየመሰልን ክፉ ድርጊታችንን ደብቀን ሁለት ዓይነት ኑሮ የምንኖር ከሆነ አምላክ ፈጽሞ አይሰማንም። በመዝሙር 26:4 ላይ ዳዊት “በከንቱ ሸንጎ አልተቀመጥሁም፣ ከዓመፀኞችም ጋር አልገባሁም” በማለት ዘምሯል። ታዲያ ይሖዋ ቃሉን ሆነ ብለው የሚተላለፉ ሰዎችን ጸሎት ይሰማል ብሎ መጠበቅ እንዴት ይቻላል?

በአምላክ መንፈስ መሞላት

8. በሚክያስ ዘመን የነበሩት ሐሰተኛ ነቢያት ምን እንደሚመጣባቸው ተነግሯቸዋል?

8 የእስራኤል መንፈሳዊ አለቆች በጣም አስከፊ የሆኑ ኃጢአቶችን ይፈጽሙ ነበር። ሐሰተኛ ነቢያት የአምላክ ሕዝቦች በመንፈሳዊ እንዲባዝኑ አድርገዋል። ስግብግብ አለቆች ‘ሰላም ነው!’ ብለው ይጮሃሉ። የሚበላ ነገር በማይሰጣቸው ሰው ላይ ግን ጦርነት ያውጁበታል። “ስለዚህ” ይላል ይሖዋ፣ “ሌሊት ይሆንባችኋል እንጂ ራእይ አይሆንላችሁም፤ ጨለማም ይሆንባችኋል እንጂ አታምዋርቱም፤ ፀሐይም በነቢያት ላይ ትገባለች፣ ቀኑም ይጠቁርባቸዋል። . . . ባለ ራእዮቹ ያፍራሉ፣ ምዋርተኞችም ይዋረዳሉ፤ ሁሉም ከንፈራቸውን [“ጢማቸውን፣” NW] ይሸፍናሉ።”—ሚክያስ 3:5-7

9, 10. ‘ጢማቸውን ይሸፍናሉ’ ሲባል ምን ማለት ነው? ሚክያስ ግን ‘ጢሙን መሸፈን’ የማያስፈልገው ለምንድን ነው?

9 ‘ጢማቸውን የሚሸፍኑት’ ለምንድን ነው? በሚክያስ ዘመን ይኖሩ የነበሩ ሰዎች ይህን የሚያደርጉት ስለሚያፍሩ ነው። በእርግጥም እነዚህ ክፉ ሰዎች ማፈር ይገባቸዋል። ‘ከእግዚአብሔር ዘንድ የሚያገኙት መልስ የለምና።’ (ሚክያስ 3:7) ይሖዋ ትዕቢተኞችና ክፉ ሰዎች ለሚያቀርቡት ጸሎት ጆሮውን አይሰጥም።

10 ሚክያስ ግን ‘ጢሙን የሚሸፍንበት’ ምንም ምክንያት የለም። ምንም የሚያፍርበት ነገር የለም። ይሖዋ ጸሎቱን ይመልስለታል። ይህ ታማኝ ነቢይ በሚክያስ 3:8 ላይ የተናገረውን ልብ በል፦ “እኔ ግን . . . በእግዚአብሔር መንፈስ ኃይልንና ፍርድን ብርታትንም ተሞልቻለሁ።” ሚክያስ ይሖዋን በታማኝነት ባገለገለባቸው በርካታ ዓመታት በሙሉ ‘በይሖዋ መንፈስ በመሞላቱ’ ምንኛ አመስጋኝ ነበር! ይህም ‘ለያዕቆብ በደሉን፣ ለእስራኤልም ኃጢአቱን’ እንዲናገር የሚያስችለውን ብርታት ሰጥቶታል።

11. የአምላክን መልእክት ለማወጅ ኃይል ማግኘት የሚቻለው ከየት ነው?

11 ሚክያስ የአምላክን የቅጣት ፍርድ ለማወጅ ከሰው አቅም የበለጠ ኃይል ይኸውም የይሖዋ መንፈስ ወይም ኃይል ያስፈልገው ነበር። እኛስ? የስብከት ሥራችንን ልናከናውን የምንችለው ይሖዋ በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት ኃይል ከሰጠን ብቻ ነው። ሆነ ብለን ኃጢአት የምንሠራ ከሆነ ለመስበክ የምናደርገው ሙከራ ሁሉ ፍሬ ቢስ መሆኑ የማይቀር ነው። በዚህ ሁኔታ ላይ እያለን ሥራውን እንድናከናውን የሚያስፈልገንን ኃይል እንዲሰጠን አምላክን ብንለምን አይሰማንም። ‘የይሖዋ መንፈስ’ ከሌለን የሰማዩ አባታችንን የፍርድ መልእክት ልናውጅ አንችልም። ተሰሚነት ያለው ጸሎት ካቀረብንና የመንፈስ ቅዱስን እገዛ ካገኘን ልክ እንደ ሚክያስ የአምላክን ቃል በድፍረት እንናገራለን።

12. በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት የአምላክን ቃል በድፍረት መናገር የቻሉት ለምንድን ነው?

12 በሥራ 4:23-31 ላይ ያለውን ታሪክ ታስታውስ ይሆናል። ከመጀመሪያው መቶ ዘመን የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት አንዱ እንደሆንክ አድርገህ አስብ። አክራሪ አሳዳጆች የክርስቶስን ተከታዮች አፍ ለመዝጋት ፈልገዋል። እነዚህ ታማኝ ሰዎች ግን ለልዑሉ ጌታቸው “ጌታ ሆይ፣ ወደ ዛቻቸው ተመልከት፤ . . . ባሪያዎችህ በፍጹም ግልጥነት ቃልህን እንዲናገሩ ስጣቸው” በማለት ጸለዩ። ታዲያ ውጤቱ ምን ሆነ? ከጸለዩ በኋላ ተሰብስበው የነበሩበት ስፍራ ተናወጠ፣ በሁሉም መንፈስ ቅዱስ ሞላባቸው፣ የአምላክንም ቃል በድፍረት ተናገሩ። ስለዚህ እኛም አገልግሎታችንን በምናከናውንበት ጊዜ ወደ ይሖዋ እንጸልይ፣ እንዲሁም በቅዱስ መንፈሱ አማካኝነት በሚሰጠን እርዳታ እንታመን።

13. ኢየሩሳሌምና ሰማርያ ምን ይደርስባቸዋል? ለምንስ?

13 አሁንም እንደገና ወደ ሚክያስ ዘመን መለስ እንበል። ሚክያስ 3:9-12 እንደሚለው ደም አፍሳሽ ገዥዎች በጉቦ ይፈርዳሉ፣ ካህናቱ በዋጋ ያስተምራሉ፣ ሐሰተኛ ነቢያትም ለገንዘብ ሲሉ ያሟርታሉ። አምላክ የይሁዳ ዋና ከተማ የሆነችው ኢየሩሳሌም “የድንጋይ ክምር ትሆናለች” ማለቱ ምንም አያስገርምም። የሥነ ምግባር ዝቅጠትና የሐሰት አምልኮ በእስራኤልም በጣም ተስፋፍቶ ስለነበር ሚክያስ በመንፈስ ተነሳስቶ ሰማርያ “የድንጋይ ክምር” ትሆናለች ሲል አስጠንቅቋል። (ሚክያስ 1:6) እንዲያውም ሰማርያ በ740 ከዘአበ በአሦራውያን ጭፍሮች ስትወድም በዓይኑ ተመልክቷል። (2 ነገሥት 17:5, 6፤ 25:1-21) በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ሚክያስ በኢየሩሳሌምና በሰማርያ ላይ እነዚህን ኃይለኛ መልእክቶች መናገር የቻለው ከይሖዋ ባገኘው ጥንካሬ ብቻ ነው።

14. በሚክያስ 3:12 ላይ የተመዘገበው ትንቢት ፍጻሜውን ያገኘው እንዴት ነው? ይህስ እኛን የሚነካን እንዴት ነው?

14 ይሁዳም ብትሆን ከይሖዋ የጥፋት ፍርድ አታመልጥም። በሚክያስ 3:12 ትንቢት ፍጻሜ መሠረት ጽዮን “እንደ እርሻ ትታረሳለች።” በዚህ 21ኛ መቶ ዘመን ላይ ሆነን ወደኋላ ስንመለከት እነዚህ ትንቢቶች ባቢሎናውያን በ607 ከዘአበ ይሁዳንና ኢየሩሳሌምን ባወደሙ ጊዜ እንደተፈጸሙ እናውቃለን። ይህ የተፈጸመው ሚክያስ ትንቢት ከተናገረ ከብዙ ዓመታት በኋላ ነበር። ቢሆንም መፈጸሙ እንደማይቀር እርግጠኛ ነበር። እኛም ይህ የአሁኑ ክፉ ሥርዓት በትንቢት በተነገረው መሠረት ‘በእግዚአብሔር ቀን’ መጥፋቱ እንደማይቀር ልክ እንደ ሚክያስ እርግጠኞች መሆን ይኖርብናል።—2 ጴጥሮስ 3:11, 12

ይሖዋ ሁኔታዎችን ያስተካክላል

15. በሚክያስ 4:1-4 ላይ ያለውን ትንቢት በራስህ አባባል ግለጽ።

15 ሚክያስ በመቀጠል አስደሳች ተስፋ ያዘለ መልእክት እንደሚያስተላልፍ እንመለከታለን። በሚክያስ 4:1-4 ላይ የሚገኙት ቃላት ምንኛ የሚያጽናኑ ናቸው! ጥቅሱ በከፊል እንዲህ ይላል፦ “በመጨረሻውም ዘመን የእግዚአብሔር ቤት ተራራ በተራሮች ራስ ላይ ጸንቶ ይቆማል፣ ከኮረብቶችም በላይ ከፍ ከፍ ይላል፤ አሕዛብም ወደ እርሱ ይጎርፋሉ። . . . በብዙዎችም አሕዛብ መካከል ይፈርዳል፣ በሩቅም ባሉ በብርቱዎች አሕዛብ ላይ ይበይናል፤ ሰይፋቸውንም ማረሻ፣ ጦራቸውንም ማጭድ ለማድረግ ይቀጠቅጣሉ፤ ሕዝብም በሕዝብ ላይ ሰይፍ አያነሣም ከእንግዲህም ወዲህ ሰልፍ አይማሩም። የሠራዊት ጌታ የእግዚአብሔር አፍም ተናግሮአልና ሰው እያንዳንዱ ከወይኑና ከበለሱ በታች ይቀመጣል፣ የሚያስፈራውም የለም።”

16, 17. ሚክያስ 4:1-4 በዘመናችን ፍጻሜውን እያገኘ ያለው እንዴት ነው?

16 እዚህ ላይ ‘ብዙዎች አሕዛብ’ እና ‘ብርቱዎች አሕዛብ’ የተባሉት እነማን ናቸው? የዚህ ዓለም ብሔራትና መንግሥታት አይደሉም። ከዚያ ይልቅ ትንቢቱ እውነተኛ አምልኮ በሚገኝበት በይሖዋ ተራራ ላይ አንድ ሆነው ቅዱስ አገልግሎት የሚያቀርቡትን ከአሕዛብ ሁሉ የተውጣጡ ግለሰቦች ያመለክታል።

17 በሚክያስ ትንቢት መሠረት ከንጹሑ የይሖዋ አምልኮ በስተቀር በምድር ላይ ምንም ዓይነት ሌላ አምልኮ የማይኖርበት ጊዜ ይመጣል። አሁንም እንኳን “ለዘላለም ሕይወት የተዘጋጁ” ሰዎች የይሖዋን መንገዶች እየተማሩ ነው። (ሥራ 13:48) ይሖዋ ከመንግሥቱ ጎን ለሚሰለፉ አማኞች ሁሉ እየፈረደና በመንፈሳዊ ሁኔታ ነገሮችን እያስተካከለ ነው። እነዚህ ሰዎች ‘የእጅግ ብዙ ሰዎች’ ክፍል በመሆን ‘ታላቁን መከራ’ በሕይወት ያልፋሉ። (ራእይ 7:9, 14) ሰይፋቸውን ቀጥቅጠው ማረሻ ስላደረጉ ባልንጀሮቻቸው ከሆኑት የይሖዋ ምሥክሮችና ከሌሎች ሰዎች ጋር በሰላም ይኖራሉ። ከእነርሱ እንደ አንዱ መሆን እንዴት ያለ መታደል ነው!

በይሖዋ ስም ለመሄድ ቆርጠናል

18. ‘በወይንና በለስ ሥር መቀመጥ’ ምን ያመለክታል?

18 ፍርሃት በመላው ምድር ላይ እንደ ጥቁር ዳመና ባጠላበት በዚህ ዘመን ብዙ ሰዎች የይሖዋን መንገዶች እየተማሩ መሆናቸው በጣም ያስደስተናል። እንደነዚህ ያሉት አምላክን የሚወድዱ ሰዎች ጦርነት የማይማሩበትንና ከወይናቸውና ከበለሳቸው በታች የሚቀመጡበትን ጊዜ በናፍቆት እንጠባበቃለን። የበለስ ዛፎች አብዛኛውን ጊዜ የሚተከሉት በወይን የአትክልት ቦታዎች ነው። (ሉቃስ 13:6) በራስ ወይንና በለስ ሥር መቀመጥ ሰላምና ብልጽግና የሰፈነበት እንዲሁም ሥጋት የሌለበት ሁኔታ መኖሩን ያመለክታል። በአሁኑ ጊዜም እንኳ ከይሖዋ ጋር የመሠረትነው ዝምድና የአእምሮ ሰላምና መንፈሳዊ ደህንነት ያስገኝልናል። እነዚህ ሁኔታዎች በአምላክ መንግሥት አገዛዝ ሥር ሲሰፍኑ ከፍርሃትና ከስጋት ሙሉ በሙሉ ነጻ እንሆናለን።

19. በይሖዋ ስም መሄድ ሲባል ምን ማለት ነው?

19 መለኮታዊ ሞገስና በረከት ለማግኘት ከፈለግን በይሖዋ ስም መሄድ ይኖርብናል። ይህም በሚክያስ 4:5 ላይ ግሩም በሆነ ሁኔታ ተገልጿል። “ሕዝብም ሁሉ እያንዳንዱ በየአምላኩ ስም ይሄዳል፣ እኛም በአምላካችን በእግዚአብሔር ስም ለዘላለም እንሄዳለን።” በይሖዋ ስም መሄድ ሲባል እርሱ አምላካችን ነው ብሎ መናገር ብቻ አይደለም። በክርስቲያን ስብሰባዎች ላይ ከመገኘትና በመንግሥቱ የስብከት ሥራ ከመካፈል የበለጡ ነገሮችን ማድረግንም ይጠይቃል። በይሖዋ ስም የምንሄድ ከሆነ ራሳችንን ለእርሱ እንወስናለን እንዲሁም ከልብ በመነጨ ፍቅር እርሱን በታማኝነት እናገለግላለን። (ማቴዎስ 22:37) አገልጋዮቹ እንደመሆናችን መጠን በአምላካችን በይሖዋ ስም ለዘላለም ለመሄድ ቆርጠናል።

20. በሚክያስ 4:6-13 ላይ ምን ትንቢት ተነግሯል?

20 አሁን ደግሞ በሚክያስ 4:6-13 ላይ የሚገኙትን ትንቢታዊ ቃላት እንመልከት። “የጽዮን ሴት ልጅ” ተግዛ ‘እስከ ባቢሎን ትደርሳለች።’ በሰባተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ በኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ላይ የደረሰው ይህ ነበር። ሆኖም ወደ ይሁዳ የሚመለሱ ቀሪዎች እንደሚኖሩና ጽዮን ዳግመኛ በምትቋቋምበት ጊዜ ይሖዋ ጠላቶቿን እንደሚያደቅ የሚክያስ ትንቢት ያመለክታል።

21, 22. ሚክያስ 5:2 ፍጻሜውን ያገኘው እንዴት ነው?

21 በሚክያስ ምዕራፍ 5 ላይ ደግሞ ሌሎች አስደናቂ ክንውኖች ተተንብየዋል። ለምሳሌ ሚክያስ 5:2-4 ምን እንደሚል ተመልከት። ሚክያስ “አወጣጡ ከቀድሞ ጀምሮ ከዘላለም የሆነ” በአምላክ የተሾመ ገዥ ከቤተ ልሔም እንደሚወጣ ይተነብያል። “በእግዚአብሔርም ኃይል” መንጋውን ይጠብቃል። በተጨማሪም ይህ ገዥ በእስራኤል ምድር ላይ ብቻ ሳይሆን ‘እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ታላቅ ይሆናል።’ የዚህ ገዥ ማንነት ለዓለም እንቆቅልሽ ይሁን እንጂ ለእኛ ምሥጢር አይደለም።

22 በቤተ ልሔም ከተወለዱት ሁሉ በጣም ታላቅ የሆነው ማን ነው? “እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ታላቅ” የሚሆነውስ ማን ነው? ከመሲሑ ከኢየሱስ ክርስቶስ ሌላ ማንም ሊሆን አይችልም! ታላቁ ሄሮድስ የካህናት አለቆችንና ጸሐፊዎችን መሲሑ የት እንደሚወለድ በጠየቀ ጊዜ “በይሁዳ ቤተ ልሔም” የሚል መልስ ሰጥተውታል። በሚክያስ 5:2 ላይ የሚገኘውንም ትንቢት ጠቅሰውለታል። (ማቴዎስ 2:3-6) ተራ ሰዎችም በዮሐንስ 7:42 ላይ “ክርስቶስ ከዳዊት ዘር ዳዊትም ከነበረባት መንደር ከቤተ ልሔም እንዲመጣ መጽሐፍ አላለምን?” እንዳሉ ስለተጠቀሰ እነርሱም መሲሑ በቤተ ልሔም እንደሚወለድ ያውቁ ነበር።

መንፈሳዊ እረፍት የሚያስገኝ መልእክት

23. ሚክያስ 5:7 በዘመናችን እየተፈጸመ ያለው እንዴት ነው?

23 ሚክያስ 5:5-15 ጊዜያዊ ድል ስለሚያስገኘው የአሦራውያን ወረራና አምላክ ታዛዥ ባልሆኑ ብሔራት ላይ ስለሚያስፈጽመው የቅጣት ፍርድ ይናገራል። ሚክያስ 5:7 ንሥሐ የገቡት አይሁዳውያን ቀሪዎች ወደ አገራቸው እንደሚመለሱ ተስፋ የሚሰጥ ሲሆን ይህ ትንቢት በጊዜያችንም ፍጻሜውን ያገኛል። ጥቅሱ እንዲህ ይላል፦ “የያዕቆብም ቅሬታ በብዙ አሕዛብ መካከል ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደሚወርድ ጠል፣ በሣር ላይ እንደሚወርድ ካፊያ፤ . . . ይሆናል።” ይህ አስደሳች ምሳሌያዊ አነጋገር የመንፈሳዊ ያዕቆብ ወይም እስራኤል ቀሪዎች ለሰው ልጆች ከአምላክ የተላኩ በረከቶች እንደሚሆኑ ያሳያል። ምድራዊ ተስፋ ያላቸው የኢየሱስ “ሌሎች በጎች” ከዘመናችን ‘የአምላክ እስራኤል’ ቀሪዎች ጋር እጅ ለእጅ ተያይዘው መንፈሳዊ እረፍት የሚያስገኘውን መልእክት ለሌሎች ማዳረሳቸውን እንደ ትልቅ መብት ይቆጥሩታል። (ዮሐንስ 10:16፤ ገላትያ 6:16፤ ሶፎንያስ 3:9) በዚህ ረገድ ልብ ልንለው የሚገባ ሌላ ነጥብም አለ። የአምላክ መንግሥት አዋጅ ነጋሪዎች እንደመሆናችን ሁላችንም እውነተኛ እፎይታ የሚያስገኘውን መልእክት ለሌሎች የማዳረስ መብታችንን እንደ ውድ ሀብት ልንመለከተው ይገባናል።

24. ከሚክያስ ምዕራፍ 3 እስከ 5 ድረስ አንተን በግል የነኩህ ነጥቦች የትኞቹ ናቸው?

24 ከሚክያስ ምዕራፍ 3 እስከ 5 ምን ቁምነገሮች ቃርመናል? የሚከተሉትን ነጥቦች ተገንዝበን ይሆናል። (1) አምላክ በሕዝቡ መካከል ግንባር ቀደም ሆነው የሚያገለግሉት ሰዎች ፍትሕን እንዲያስከብሩ ይጠብቅባቸዋል። (2) ሆን ብሎ ኃጢአት የመሥራት ልማድ ካለብን ይሖዋ ጸሎታችንን አይሰማም። (3) የስብከት ሥራችንን ልናከናውን የምንችለው አምላክ በቅዱስ መንፈሱ አማካኝነት ኃይል ከሰጠን ብቻ ነው። (4) መለኮታዊ ሞገስ ማግኘት ከፈለግን በይሖዋ ስም መሄድ ይኖርብናል። (5) የአምላክ መንግሥት አዋጅ ነጋሪዎች እንደመሆናችን እውነተኛ እፎይታ የሚያስገኘውን መልእክት ለሰዎች የማዳረስ መብታችንን ከፍ አድርገን መመልከት ይኖርብናል። በግልህ የነኩህ ሌሎች ነጥቦችም ይኖሩ ይሆናል። ከዚህ ትንቢታዊ መጽሐፍ ምን ሌሎች ትምህርቶችን ልናገኝ እንችላለን? በሚቀጥለው ርዕስ ላይ እምነት ከሚያጠነክሩት ከመጨረሻዎቹ ሁለት የሚክያስ ምዕራፎች ጠቃሚ ትምህርት እናገኛለን።

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

• አምላክ በሕዝቡ መካከል ግንባር ቀደም ሆነው ከሚያገለግሉት ምን ይጠብቅባቸዋል?

• ለይሖዋ ከምናቀርበው አገልግሎት ጋር በተያያዘ ጸሎትና ከመንፈስ ቅዱስ የሚገኘው እርዳታ አስፈላጊ የሆኑት እንዴት ነው?

• ሰዎች ‘በይሖዋ ስም የሚሄዱት’ እንዴት ነው?

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሚክያስ ስለ ድስት የተናገረውን ምሳሌ ልታብራራ ትችላለህ?

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ልክ እንደ ሚክያስ እኛም አገልግሎታችንን በድፍረት እንፈጽም

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ