የአንባቢያን ጥያቄዎች
ስለ ሙታን መጠመቅ ምንድን ነው?
ሐዋርያው ጳውሎስ በሰማይ ለመኖር ትንሣኤ ስለማግኘት ሲጽፍ ትኩረት የሚስብ አንድ ሐሳብ አስፍሯል። ጥቅሱ እንዲህ ይላል:- “እንዲያማ ካልሆነ፣ ስለ ሙታን የሚጠመቁ ምን ያደርጋሉ? ሙታንስ ከቶ የማይነሡ ከሆነ፣ ስለ እነርሱ የሚጠመቁ ስለ ምንድር ነው?” የ1980 ትርጉም ደግሞ ይህንን ጥቅስ እንዲህ በማለት አስቀምጦታል:- “የሞቱ ሰዎች የማይነሱ ከሆነማ፣ ስለ ሞቱ ሰዎች የሚጠመቁ ሁሉ ትርፋቸው ምንድን ነው? የሞቱ ሰዎች ከቶ የማይነሡ ከሆነማ፣ ሰዎች በእነርሱ ምትክ ስለምን ይጠመቃሉ?”—1 ቆሮንቶስ 15:29
እዚህ ላይ ጳውሎስ በሕይወት ያሉ ሰዎች፣ ሳይጠመቁ በሞቱ ሰዎች ምትክ እንደሚጠመቁ መናገሩ ነበር? ከእነዚህና ከአንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች አንጻር እንዲህ ብሎ መደምደሙ ትክክል ይመስል ይሆናል። ይሁን እንጂ ሌሎች ጥቅሶችንና ጳውሎስ የተጠቀመበትን የመጀመሪያውን የግሪክኛ ቃል ጠለቅ ብለን ስንመረምር ሌላ መደምደሚያ ላይ እንደርሳለን። ጳውሎስ እንዲህ ብሎ ሲናገር በመንፈስ የተቀቡ ክርስቲያኖች ከተጠመቁ በኋላ የሚከተሉት የሕይወት ጎዳና እንደ ክርስቶስ እስከ ሞት ድረስ ታማኝ መሆን እንደሚጠይቅባቸው ማመልከቱ ነበር። ከዚያም ልክ እንደ ክርስቶስ ትንሣኤ አግኝተው መንፈሳዊ ሕይወት ይሰጣቸዋል።
መጽሐፍ ቅዱስ ይህንን ሐሳብ ይደግፋል። ጳውሎስ ለሮሜ ክርስቲያኖች በላከው ደብዳቤ ላይ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ የተጠመቅን ሁላችን ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ እንደ ተጠመቅን አታውቁምን?” (ሮሜ 6:3) ጳውሎስ ለፊልጵስዩስ ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ “[በክርስቶስ መከራ] እንድካፈል፣ ወደ ሙታንም ትንሣኤ ልደርስ ቢሆንልኝ፣ በሞቱ እንድመስለው እመኛለሁ” በማለት ስለ ራሱ ተናግሯል። (ፊልጵስዩስ 3:10, 11) ጳውሎስ በመንፈስ የተቀባ አንድ የክርስቶስ ደቀ መዝሙር የሚከተለው የሕይወት ጎዳና በፈተና ወቅት አቋም መጠበቅን፣ በየዕለቱ ሞትን መጋፈጥንና በመጨረሻም ትንሣኤ አግኝቶ ወደ ሰማይ የመሄድ ተስፋ በመያዝ በታማኝነት መሞትን እንደሚያካትት መናገሩ ነበር።
ሞትን ከተጠመቁ ሰዎች ጋር በቀጥታ አያይዘው የሚናገሩት እነዚህም ሆኑ ሌሎች ጥቅሶች የሚያመለክቱት በሕይወት ያሉ የተጠመቁ ግለሰቦችን እንጂ የሞቱ ሰዎችን ጥምቀት አለመሆኑ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው። በተጨማሪም ጳውሎስ በመንፈስ የተቀቡ ክርስቲያን ባልንጀሮቹን እንዲህ ብሏቸዋል:- “በጥምቀትም ከእርሱ ጋር ተቀብራችሁ፣ በጥምቀት ደግሞ፣ ከሙታን ባስነሣው በእግዚአብሔር አሠራር በማመናችሁ፣ ከእርሱ ጋር ተነሣችሁ።”—ቆላስይስ 2:12
የተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች “ስለ” ወይም “በ . . . ምትክ” በማለት የተረጎሙት በ1 ቆሮንቶስ 15:29 ላይ ያለው የግሪክኛ መስተዋድድ ሃይፐር ሲሆን ይህ ቃል “ለ . . . ሲሉ” ማለትም ሊሆን ይችላል። በዚህም ምክንያት የአዲሲቱ ዓለም የቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉም ከሌሎች ጥቅሶች ጋር በሚስማማ መልኩ ይህንን ጥቅስ እንዲህ ሲል በትክክል ተርጉሞታል:- “እንደ ሙታን ለመሆን ሲሉ የሚጠመቁ ምን ያደርጋሉ? ሙታንስ ከቶ የማይነሡ ከሆነ፣ እንደ እነርሱ ለመሆን ሲሉ የሚጠመቁት ለምንድን ነው?”