በአምላክ እንድናምን ሊያነሳሳን የሚገባ ትክክለኛ ምክንያት
በኮሪያ ቋንቋ የተዘጋጀው 31 ሪዝንስ ዋይ ያንግ ፒፕል ሊቭ ዘ ቸርች (ወጣቶች ቤተ ክርስቲያንን ትተው እንዲወጡ የሚያደርጓቸው 31 ምክንያቶች) የተባለው መጽሐፍ ብዙዎች ወደ ቤተ ክርስቲያን መሄድ የሚያቆሙት ለጥያቄዎቻቸው አጥጋቢ መልሶች ማግኘት ስላልቻሉ እንደሆነ ገልጿል። ለአብነት ያህል፣ ‘በአምላክ የሚያምኑ ሰዎች ሥቃይ የሚደርስባቸው ለምንድን ነው?’ እንዲሁም ‘አብያተ ክርስቲያናት የሚያስተምሩት አብዛኛው ነገር ግራ የሚያጋባና እርስ በርሱ የሚጋጭ ሆኖ እያለ ትምህርቱን በሙሉ አምነን መቀበል ያለብን ለምንድን ነው?’ እንደሚሉት ያሉ ጥያቄዎች ያነሳሉ።
ብዙዎች ቀሳውስት የሚሰጧቸው መልሶች ስለማያረኳቸው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለጥያቄዎቻቸው መልስ እንደሌለ ያስባሉ። ቀሳውስት ሙሉ በሙሉ በራሳቸው አመለካከት ላይ የተመሠረተ መልስ በሚሰጡበት ጊዜ በአብዛኛው ሰዎች ግራ እንዲጋቡና አልፎ ተርፎም አምላክንና መጽሐፍ ቅዱስን እንዳይቀበሉ ያደርጓቸዋል።
በደቡብ አፍሪካ የሉተራን ሃይማኖት ተከታይ ሆኖ ያደገው አቤል ያጋጠመው ሁኔታ ከዚህ ጋር ይመሳሰላል። እንዲህ ይላል:- “ቤተ ክርስቲያን የሞቱ ሰዎችን ሁሉ አምላክ ‘እንደወሰዳቸው’ ታስተምራለች። ሆኖም አፍቃሪ የሆነ አምላክ ወላጆችን ከልጆቻቸው ነጥሎ ለምን ‘እንደሚወስዳቸው’ ሊገባኝ አልቻለም። እኔ ባደግሁበት ገጠራማ የአፍሪካ ክፍል አንዲት ዶሮ ጫጩቶቿ እስኪያድጉ ድረስ አናርዳትም። አንዲት ላም እርጉዝ መሆኗን ካወቅን ወልዳ ጥጃው መጥባት እስኪያቆም ድረስ አትታረድም። አፍቃሪ የሆነ አምላክ ለሰው ልጆች ተመሳሳይ አሳቢነት ለምን እንደማያሳይ ሊገባኝ አልቻለም።”
ካናዳዊው አራምም ተመሳሳይ ጥርጣሬዎች ነበሩት። እንዲህ ይላል:- “አባቴ የሞተው የ13 ዓመት ልጅ እያለሁ ነበር። በቀብር ሥነ ሥርዓቱ ላይ አንድ ታዋቂ ቄስ፣ አምላክ አባቴ እንዲሞት ያደረገው ወደ ሰማይ ሄዶ ከእርሱ አጠገብ እንዲሆን ስለፈለገ መሆኑን ተናገሩ። ‘አምላክ ጻድቃንን ስለሚወድድ ጥሩ ሰዎችን ይወስዳቸዋል’ አሉ። አምላክ እንዴት ይህን ያህል ራስ ወዳድ ሊሆን እንደሚችል አልገባኝም።”
ከጊዜ በኋላ አቤልና አራም ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ተገናኝተው መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናታቸው ለጥያቄዎቻቸው መልስ አገኙ። ለአምላክ ፍቅር ከማዳበራቸውም በላይ በእርሱ ላይ ጠንካራ እምነት ገነቡ። በመጨረሻም ሕይወታቸውን ለይሖዋ ወስነው ታማኝ አገልጋዮቹ ሆኑ።
ትክክለኛ እውቀት —በአምላክ ለማመን የግድ አስፈላጊ ነው
ከእነዚህ ተሞክሮዎች ምን ትምህርት እናገኛለን? በአምላክ ለማመን ትክክለኛ የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት አስፈላጊ እንደሆነ ያሳዩናል። ሐዋርያው ጳውሎስ በጥንቷ የፊልጵስዩስ ከተማ የነበሩትን ክርስቲያኖች “ፍቅራችሁ በእውቀትና በማስተዋል ሁሉ ከፊት ይልቅ እያደገ እንዲበዛ ይህን እጸልያለሁ” ብሏቸዋል። (ፊልጵስዩስ 1:9-11) እዚህ ላይ ጳውሎስ ለአምላክና ለእምነት ባልንጀሮቻችን ፍቅር ማዳበርን ስለ አምላክ ትክክለኛ እውቀት ከማግኘትና ፈቃዱን ከማስተዋል ጋር አያይዞ ገልጾታል።
በአንድ ሰው ላይ እምነትና ትምክህት ለመጣል የሚያስፈልገው የመጀመሪያው ነገር ግለሰቡን ማወቅ በመሆኑ ጳውሎስ ይህንን ማለቱ ተገቢ ነው። ስለ ግለሰቡ ይበልጥ የተሟላና ትክክለኛ የሆነ እውቀት ስናገኝ በዚያው መጠን እንተማመንበታለን። በተመሳሳይ አንተም በአምላክ ለማመን እንድትነሳሳ ትክክለኛ እውቀት ማግኘት ያስፈልግሃል። ጳውሎስ “እምነትም ተስፋ ስለ ምናደርገው ነገር የሚያስረግጥ፣ የማናየውንም ነገር የሚያስረዳ ነው” ብሏል። (ዕብራውያን 11:1) በትክክለኛ የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት ላይ ያልተመሠረተ እምነት እንደ እንቧይ ካብ ነው።
መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናትህ አቤልንና አራምን ግራ አጋብቷቸው እንደነበረው ሰዎች የሚሞቱት ለምንድን ነው? እንደሚለው ለመሳሰሉ ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት ያስችልሃል። መጽሐፍ ቅዱስ “ኃጢአት በአንድ ሰው ወደ ዓለም ገባ በኃጢአትም ሞት፣ እንደዚሁም ሁሉ ኃጢአትን ስላደረጉ ሞት ለሰው ሁሉ ደረሰ” ይላል። (ሮሜ 5:12) ሰዎች የሚያረጁትና የሚሞቱት አምላክ ወደ ራሱ ስለሚወስዳቸው ሳይሆን አዳም በሠራው ኃጢአት ምክንያት ነው። (ዘፍጥረት 2:16, 17፤ 3:6, 17-19) ከዚህም በላይ መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ አምላክ የሰጠውን እውነተኛ ተስፋ ይገልጻል። በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት ኃጢአተኛው የሰው ዘር ትንሣኤ የሚያገኝበትን ዝግጅት አድርጓል።—ዮሐንስ 5:28, 29፤ የሐዋርያት ሥራ 24:15
ስለ ትንሣኤ ተስፋ እውነቱን መረዳት እንድንችል መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ ከሞት ያስነሳቸውን ሰዎች በተመለከተ በርካታ ማስረጃዎች ይዟል። (ሉቃስ 7:11-17፤ 8:40-56፤ ዮሐንስ 11:17-45) እነዚህን የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች በምታነብበት ጊዜ ትንሣኤ ያገኙት ሰዎች ወዳጆችና ቤተሰቦቻቸው ምን ያህል ተደስተውና ፈንጥዘው ሊሆን እንደሚችል አስብ። እነዚህ ሰዎች አምላክን ለማመስገንና በኢየሱስ ላይ እምነት ለማሳደር እንደተገፋፉም ልብ በል።
ዛሬም ሰዎች ስለ አምላክና ስለ ዓላማዎቹ ትክክለኛ እውቀት ማግኘታቸው ተመሳሳይ ምላሽ እንዲሰጡ ሊያነሳሳቸው ይችላል። ብዙዎች አንገብጋቢ ለሆኑ ጥያቄዎቻቸው አጥጋቢ መልስ ማግኘት ባለመቻላቸው በአንድ ወቅት ግራ ተጋብተው፣ ተጨንቀውና አልፎ ተርፎም እምነት አጥተው ነበር። መጽሐፍ ቅዱስን ሲያጠኑ ግን ለጥያቄዎቻቸው መልስ ስላገኙ ሕይወታቸው ሙሉ በሙሉ ተለወጠ።
አምላክን መውደድ —እርሱን ለማገልገል የሚያነሳሳ ዋነኛ ምክንያት
በአምላክ ለማመን ትክክለኛ እውቀት አስፈላጊ ቢሆንም አንድ ሰው እርሱን ለመታዘዝና ለማገልገል እንዲነሳሳ ከዚህ የበለጠ ምክንያት ያስፈልገዋል። ኢየሱስ አምላክ ከሰጣቸው ትእዛዛት ሁሉ የላቀው የትኛው እንደሆነ ተጠይቆ ሲመልስ “አንተም በፍጹም ልብህ በፍጹምም ነፍስህ በፍጹምም አሳብህ በፍጹምም ኃይልህ ጌታ አምላክህን ውደድ” ብሏል። (ማርቆስ 12:30) አንድ ሰው ኢየሱስ በገለጸው መሠረት አምላክን ከወደደው እርሱን ለመታዘዝና ለማገልገል ሙሉ በሙሉ ፈቃደኛ ይሆናል። አንተስ ለአምላክ ያለህ ፍቅር እንዲህ እንድታደርግ ይገፋፋሃል?
ለበርካታ አሥርተ ዓመታት በኮሪያ ሚስዮናዊ ሆና ያገለገለችው ሬቸል በአምላክ እንድታምን ያደረጋት ምን እንደሆነ ስትናገር እንዲህ ትላለች:- “ይሖዋ ለፍጡሮቹ ያሳየውን ለጋስነት፣ ከሕዝቦቹ ጋር ባለው ግንኙነት የታየውን ይቅር ባይነት እንዲሁም እርሱ ምን እንደሚፈልግብን በማወቅ ራሳችንን እንድንጠቅም ያለውን ፍላጎት አስባለሁ። እነዚህ ሁሉ ነገሮች ለአምላክ ያለኝ ፍቅር እንዲያድግ አድርገዋል። ይህ ፍቅር ደግሞ እንዳገለግለው አነሳስቶኛል።”
በጀርመን የምትኖር ማርታ የተባለች አንዲት መበለት ይሖዋን ለ48 ዓመታት አገልግላዋለች። እንዲህ ትላለች:- “ይሖዋን የማገለግለው ለምንድን ነው? ስለምወድደው ነው። ሁልጊዜ ማታ ማታ ይሖዋን በጸሎት የማነጋግረው ሲሆን ለስጦታዎቹ በተለይም ለቤዛዊው መሥዋዕት በጥልቅ እንደማመሰግነው እነግረዋለሁ።”
አዎን፣ ለአምላክ ፍቅር ማዳበራችን ከልብ ተነሳስተን እርሱን የማገልገል ፍላጎት እንዲያድርብን ያደርገናል። ይሁን እንጂ አንድ ሰው እንዲህ ያለ ፍቅር ማዳበር የሚችለው እንዴት ነው? ለአምላክ ፍቅር እንድናዳብር የሚገፋፋን ከሁሉ የላቀው ጠንካራ ምክንያት እርሱ ላሳየን ፍቅር ያለን ጥልቅ አድናቆት ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግቦ የሚገኘውን የሚከተለውን አስደሳች ሐሳብ ተመልከት:- “ፍቅር የሌለው እግዚአብሔርን አያውቅም፣ እግዚአብሔር ፍቅር ነውና። በዚህ የእግዚአብሔር ፍቅር በእኛ ዘንድ ተገለጠ፣ በእርሱ በኩል በሕይወት እንኖር ዘንድ እግዚአብሔር አንድ ልጁን ወደ ዓለም ልኮታልና። ፍቅርም እንደዚህ ነው፤ እግዚአብሔር እርሱ ራሱ እንደ ወደደን ስለ ኃጢአታችንም ማስተስሪያ ይሆን ዘንድ ልጁን እንደ ላከ እንጂ እኛ እግዚአብሔርን እንደ ወደድነው አይደለም።”—1 ዮሐንስ 4:8-10
ይህ ፍቅር ምን ያህል ታላቅ እንደሆነ ተገንዝበሃል? በኃይለኛ ወራጅ ወንዝ እየተወሰድክ እያለ አንድ ሰው የራሱን ሕይወት አደጋ ላይ ጥሎ ሕይወትህን አተረፈልህ። ይህንን ሰው ትረሳዋለህ? ላደረገልህ ነገር እጅግ በጣም አታመሰግነውም? ለዚህ ሰው አቅምህ የፈቀደውን ማንኛውንም ነገር ለማድረግ ፈቃደኛ አትሆንም? አምላክ ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት እንዲሆን በመስጠት ያሳየው ታላቅ ፍቅር ከማንኛውም ነገር ጋር ሊወዳደር አይችልም። (ዮሐንስ 3:16፤ ሮሜ 8:38, 39) ልብህ በአምላክ ፍቅር ሲነካ እርሱን ከልብ ለማፍቀርና ለማገልገል ትነሳሳለህ።
አሁንና ወደፊት የምናገኛቸው በረከቶች
የአምላክን ፈቃድ እንድናደርግ ሊገፋፋን የሚገባው ዋነኛ ምክንያት ለእርሱ ያለን ፍቅር ቢሆንም አምላክ ለአገልጋዮቹ ወሮታ እንደሚከፍል ማወቁም ያስደስታል። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ብሏል:- “ያለ እምነትም ደስ ማሰኘት አይቻልም፤ ወደ እግዚአብሔር የሚደርስ እግዚአብሔር እንዳለ ለሚፈልጉትም ዋጋ እንዲሰጥ ያምን ዘንድ ያስፈልገዋልና።”—ዕብራውያን 11:6
አምላክን የሚወድዱና የሚታዘዙ ሰዎች በእርግጥም ይባረካሉ። ብዙዎች የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ተግባራዊ በማድረጋቸው የተሻለ ጤንነት አግኝተዋል። (ምሳሌ 23:20, 21፤ 2 ቆሮንቶስ 7:1) መጽሐፍ ቅዱስ ሐቀኝነትንና ትጋትን አስመልክቶ የሚሰጠውን መመሪያ ተግባራዊ የሚያደርጉ ሰዎች በአጠቃላይ ሲታይ በአሠሪዎቻቸው ዘንድ አመኔታን ያተረፉ በመሆኑ በሥራ ገበታቸው የመቆየት የተሻለ አጋጣሚ አላቸው። (ቆላስይስ 3:23) የአምላክ አገልጋዮች በይሖዋ ስለሚታመኑ በአስቸጋሪ ጊዜያትም እንኳ የአእምሮ ሰላም አላቸው። (ምሳሌ 28:25፤ ፊልጵስዩስ 4:6, 7) ከሁሉ በላይ ደግሞ ወደፊት ገነት በምትሆነው ምድር ላይ የዘላለም ሕይወት በማግኘት እንደሚባረኩ እርግጠኞች ናቸው።—መዝሙር 37:11, 29
እነዚህን የመሰሉ በረከቶች ከይሖዋ ያገኙ ሰዎች ስለ እርሱ ምን ይሰማቸዋል? በካናዳ የምትኖር ጃክለን የተባለች አንዲት ክርስቲያን ለአምላክ ያላትን አድናቆት ስትገልጽ “ሁልጊዜ ድንቅ የሆኑ ስጦታዎች የሚሰጠን ከመሆኑም በላይ የዘላለም ሕይወት የማግኘት የተረጋገጠ ተስፋ ዘርግቶልናል” ብላለች። ቀደም ሲል የተጠቀሰው አቤልም እንዲህ ሲል ስሜቱን ገልጿል:- “ገነት በሆነች ምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ ለእኔ አዲስ ነገር ሲሆን ይህንንም በጉጉት እየተጠባበቅሁ ነው። ሆኖም የገነት ተስፋ ባይኖርም እንኳ አምላክን በማገልገል ለእርሱ ያለኝን ፍቅር መግለጽ በራሱ ያስደስተኛል።”
አንተም እውነተኛ እምነት ሊኖርህ ይችላል
መጽሐፍ ቅዱስ “ኩላሊትንና ልብን የምትፈትን በቅንም የምትፈርድ አቤቱ የሠራዊት ጌታ ሆይ” በማለት ይናገራል። (ኤርምያስ 11:20) አዎን፣ ይሖዋ ውስጣዊ ማንነታችንን ይመረምራል። እያንዳንዱ ሰው በአምላክ እንዲያምን የሚገፋፋውን ምክንያት ሊመረምር ይገባል። ከዚህ ቀደም ስለ አምላክ የነበረን ትክክል ያልሆነ እምነትና አመለካከት የተሳሳተ እርምጃ እንድንወስድ አድርጎን ይሆናል። ሆኖም ትክክለኛ የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት ማግኘት ከፈጣሪያችን ከይሖዋ አምላክ ጋር ጤናማ ዝምድና ለመመሥረት ያስችለናል።—1 ጢሞቴዎስ 2:3, 4
የይሖዋ ምሥክሮች ሰዎችን በነፃ መጽሐፍ ቅዱስ በማስጠናት ስለ አምላክ ትክክለኛ እውቀት እንዲያገኙ እየረዷቸው ነው። (ማቴዎስ 28:19, 20) እንደዚህ ዓይነት እርዳታ ያገኙ በርካታ ሰዎች አምላክን መውደድና በእርሱ ላይ እውነተኛ እምነት ማሳደር ችለዋል። መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናት “መልካም ጥበብንና ጥንቃቄን” ማግኘት ችለዋል፤ ይህም በዚህ አስቸጋሪ ጊዜ ‘ተማምነው ለመሄድ’ አስችሏቸዋል። (ምሳሌ 3:21-23) ከሁሉ በላይ ደግሞ ስለ ወደፊቱ ጊዜ “እርግጥና ጽኑ የሆነ” ተስፋ አላቸው። (ዕብራውያን 6:19) አንተም እውነተኛ እምነት በማዳበር እነዚህን በረከቶች ልታገኝ ትችላለህ።
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
መልስ ያሻቸው የነበሩ ግራ የሚያጋቡ ጥያቄዎች
“በሆስፒታል ውስጥ የሕክምና ተማሪ ሆኜ በምሠለጥንበት ወቅት ጥሩ ሰዎች በበሽታና በአደጋ ምክንያት በሥቃይ ሲያቃስቱ እመለከት ነበር። አምላክ ካለ እነዚህ ነገሮች የሚደርሱት ለምንድን ነው? ሃይማኖት የአእምሮ ሰላም እንድናገኝ ከመርዳት ሌላ ጥቅም የለውም ማለት ነው?”—በደቡብ ኮሪያ የሚኖር የቀድሞ የፕሪስባይቴሪያን ሃይማኖት ተከታይ
“የአልኮል ሱሰኛ የነበረው አባቴ ወደ ሲኦል ወርዶ ይሆን ወይስ ወደ ሰማይ ሄዷል ብዬ ብዙ ጊዜ አስባለሁ። ሙታንና የመቃጠያ ሲኦል ትምህርት በጣም ያስፈሩኛል። አፍቃሪ የሆነ አምላክ አንድን ሰው በሲኦል ውስጥ ለዘላለም እንዴት ያሠቃያል?”—በብራዚል የምትኖር የቀድሞ ካቶሊክ
“ወደፊት ምድርም ሆነች የሰው ልጆች ምን ይጠብቃቸዋል? የሰው ዘር ለዘላለም መኖር የሚችለው እንዴት ነው? የሰው ልጅ እውነተኛ ሰላም እንዴት ማግኘት ይችላል?”—በጀርመን የሚኖር የቀድሞ ካቶሊክ
“አንድ ሰው ከሞተ በኋላ ነፍሱ ሌላ ፍጥረት ሆና እንደገና ትወለዳለች የሚለው ትምህርት ትርጉም አይሰጠኝም ነበር። እንስሳት አምላክን ማምለክ አይችሉም፤ እንግዲያው እንደገና በምትወለድበት ጊዜ ቀደም ሲል በሠራኸው ኃጢአት ምክንያት እንስሳ ሆነህ ብትፈጠር አቋምህን አስተካክለህ ከዚህ ሁኔታ መውጣት የምትችለው እንዴት ነው?”—በደቡብ አፍሪካ የሚኖር የቀድሞ የሂንዱ እምነት ተከታይ
“ያደግሁት የኮንፊሽየስ እምነት ተከታይ በሆነ ቤተሰብ ውስጥ ሲሆን የቀድሞ አባቶቻችን በሰላም እንዲያንቀላፉ ሲባል በሚካሄዱ የአምልኮ ሥርዓቶች እካፈል ነበር። መሥዋዕት የሚቀርብበትን ጠረጴዛ በምናዘጋጅበትና በምንሰግድበት ወቅት ሞተው ያሉት የቀድሞ አባቶቻችን ምግቡን ለመብላት ይመጡ እንደሆነና ስንሰግድላቸው ያዩን እንደሆነ አስብ ነበር።”—በደቡብ ኮሪያ የሚኖር የቀድሞ የኮንፊሽየስ እምነት ተከታይ
እነዚህ ሰዎች ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ተገናኝተው መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናታቸው ለጥያቄዎቻቸው መልስ አግኝተዋል።