በጊዜያችን ልጆችን ማሰልጠን ያለው ችግር
ምሽቱ ገፍቷል። አንድ የምግብ ቤት ባለቤት ምግብ ቤቱን ዘጋግቶ ወደ ቤቱ ለመሄድ እየተዘጋጀ ሳለ ትንሽ ልጅ የያዙ ሁለት ሴቶች ገቡና ምግብ አዘዙ። በቀኑ ውሎው በጣም የተዳከመው የምግብ ቤቱ ባለቤት ዘግተናል ብሎ ሊመልሳቸው አስቦ ነበር። ሆኖም ሐሳቡን ቀየረና ሊያስተናግዳቸው ወሰነ። ሁለቱ ሴቶች የቀረበላቸውን ምግብ እየተመገቡ ሲጫወቱ ትንሹ ልጅ ግን በምግብ ቤቱ ውስጥ ወዲያና ወዲህ እየተሯሯጠ የያዘውን ብስኩት እዚህም እዚያም ያንጠባጥብና በእግሩ እየረጋገጠ መሬቱን ያበላሽ ነበር። እናቱም እንደ መከልከል ዝም ብላ እያየችው ትስቃለች። በመጨረሻ ሴቶቹ ሲሄዱ ቀኑን ሙሉ ሲለፋ የዋለው የምግብ ቤቱ ባለቤት በብስኩት ፍርፋሪ የቆሸሸውን መሬት ለማጽዳት ተገደደ።
ይህ እውነተኛ ታሪክ እንደሚያሳየው አብዛኞቹ ወላጆች ልጆችን በማሰልጠን ረገድ ብዙም እየተሳካላቸው እንዳልሆነ ሳታስተውል አትቀርም። ለዚህ የሚቀርቡት ምክንያቶች የተለያዩ ናቸው። አንዳንድ ወላጆች ልጆች ነጻነት አግኝተው ማደግ አለባቸው ብለው ስለሚያስቡ እንዳሻቸው እንዲሆኑ ይፈቅዱላቸዋል። ወይም ሕይወታቸው በጥድፊያ የተሞላ በመሆኑ ለልጆቻቸው የሚያስፈልጋቸውን ሥልጠናና ትኩረት ለመስጠት ጊዜ አይኖራቸውም። ሌሎች ወላጆች ደግሞ ዋናው ነገር ልጃቸው ትምህርት ቤት ገብቶ መማሩ ነው ብለው ስለሚያስቡ ጥሩ ውጤት አምጥቶ ታዋቂ ኮሌጅ መግባት እስከቻለ ድረስ እንደፈለገ እንዲሆን ይፈቅዱለታል።
አንዳንዶች ደግሞ ወላጆች ብሎም አጠቃላዩ ኅብረተሰብ የሚመሩባቸው የሥነ ምግባር እሴቶች መስተካከል አለባቸው ይላሉ። ለዚህም ልጆች አሉ በተባሉ የወንጀል ዓይነቶች በሙሉ የሚካፈሉ መሆናቸውንና በትምህርት ቤት የሚፈጸመው ዓመጽ ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ መሆኑን እንደ ማስረጃ ይጠቅሳሉ። በመሆኑም በኮሪያ ሪፑብሊክ፣ ሴኡል የሚገኝ የአንድ መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር “በቅድሚያ ጥሩ ስብዕና ከገነባህ በኋላ ነው እውቀት ማስጨበጥ ያለብህ” ብለዋል።
ልጆቻቸው ከኮሌጅ ተመርቀው ስኬታማ ሕይወት እንዲመሩ የሚመኙ በርካታ ወላጆች እንዲህ ላሉ ማሳሰቢያዎች እምብዛም ጆሮ አይሰጡም። ወላጅ ከሆንክ ልጅህ ምን ዓይነት ሰው እንዲወጣው ትፈልጋለህ? ጥሩ ሥነ ምግባር ያለው፣ ኃላፊነት የሚሰማው፣ ለሌሎች አሳቢ፣ ከሁኔታዎች ጋር ራሱን የሚያስማማና ብሩህ አስተሳሰብ ያለው ሆኖ እንዲያድግ ትፈልጋለህ? እንግዲያው የሚቀጥለውን ርዕስ እንድታነብ እንጋብዝሃለን።