የሕይወት ታሪክ
‘የልቤን መሻት’ አግኝቻለሁ
ዶሚኒክ ሞርጉ እንደተናገረችው
በመጨረሻ ተሳክቶልኝ በታኅሣሥ 1998 ወደ አፍሪካ ሄድኩ! የልጅነት ሕልሜ እውን ሆነ። ስለ አፍሪካ ሰፋፊ መስኮችና ማራኪ የዱር እንስሳት ሳስብ ደስ ይለኝ ነበር። ከጊዜ በኋላ በአካል በቦታው ተገኘሁ። በዚህ ጊዜ ሌላው ሕልሜም እውን ሆነልኝ። በውጭ አገር የሙሉ ጊዜ ወንጌላዊ ሆኜ እያገለገልኩ ነበር። ምናልባት ብዙዎች ይህ የማይቻል ነገር ይመስላቸው ይሆናል። ዓይኔ በጣም ደካማ ሲሆን ለአውሮፓ አውራ ጎዳናዎች በሠለጠነችው ውሻዬ እየተመራሁ በአፍሪካ አሸዋማ መንገዶች ላይ እጓዝ ነበር። በአፍሪካ ማገልገል የቻልኩት እንዴት እንደሆነና ይሖዋ ‘የልቤን መሻት’ የሰጠኝ በምን መልኩ እንደሆነ እስቲ ላውጋችሁ።—መዝሙር 37:4
ሰኔ 9, 1966 በደቡባዊ ፈረንሳይ ተወለድኩ። ከሁለት ወንዶችና አምስት ሴቶች ልጆች መካከል እኔ የመጨረሻዋ ነበርኩ፤ ማናችንም ብንሆን አፍቃሪ ወላጆቻችን የሚያደርጉልን እንክብካቤ ተጓድሎብን አያውቅም። ይሁንና ገና በወጣትነቴ በሕይወቴ ላይ ያጠላ አንድ ጥቁር ነጥብ ተከሰተ። ልክ እንደ ሴት አያቴ፣ እናቴና አንዲት እህቴ እኔም ቀስ በቀስ ዓይን በሚያሳውር በዘር የሚተላለፍ በሽታ ተይዤ ነበር።
በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ ሳለሁ ይፈጸምብን የነበረው የዘር መድሎ፣ ጭፍን ጥላቻና የግብዝነት ተግባር በማኅበረሰቡ ላይ እንዳምጽ አደረገኝ። በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ላይ ነበር ወደ ኤሮ ክፍለ ግዛት የተዛወርነው። በዚያም አንድ አስገራሚ ሁኔታ ተከሰተ።
አንድ እሁድ ጠዋት ሁለት የይሖዋ ምሥክሮች ወደ ቤታችን መጡ። እናቴ ማንነታቸውን ስላወቀች ወደ ውስጥ እንዲገቡ ጋበዘቻቸው። ከመጡት ሴቶች አንደኛዋ እናቴን መጽሐፍ ቅዱስ እንድታጠና የቀረበላትን ግብዣ አንድ ቀን እንደምትቀበል ቃል መግባቷን ታስታውስ እንደሆነ ጠየቀቻት። እናቴም ሁኔታው ትዝ ብሏት “ታዲያ መቼ እንጀምር?” ስትል መልሳ ጠየቀቻቸው። ከዚያም ዘወትር እሁድ ጠዋት ተገናኝተው ለማጥናት ተስማሙ፤ በዚህ መንገድ ‘የወንጌልን እውነት’ መማር ጀመረች።—ገላትያ 2:14
ማስተዋል አገኘሁ
እናቴ የምትማራቸውን ነገሮች ለመገንዘብና ያወቀችውንም ላለመርሳት የተቻላትን ሁሉ ትጥር ነበር። ማየት ስለማትችል ሁሉንም በቃሏ ማስታወስ ነበረባት። የሚያስጠኗት የይሖዋ ምሥክሮችም በትዕግሥት ይይዟት ነበር። እኔ ግን፣ በመጡ ቁጥር ክፍሌ እደበቃለሁ፤ እስኪሄዱም ድረስ ከዚያ አልወጣም። ሆኖም አንድ ቀን ጠዋት ዩጌኒ የተባለች የይሖዋ ምሥክር አግኝታ አነጋገረችኝ። የአምላክ መንግሥት ማንኛውንም ዓይነት ግብዝነት፣ ጥላቻና መድሎ ከምድር እንደሚያስወግድ ገለጸችልኝ። “የሁሉም ችግር መፍትሄ ያለው በአምላክ እጅ ነው” ካለች በኋላ ስለዚህ ጉዳይ ይበልጥ ማወቅ እፈልግ እንደሆነ ጠየቀችኝ። በቀጣዩ ቀን መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመርኩ።
የምማረው ሁሉ ለኔ እንግዳ ነበር። አምላክ ክፋት ለጊዜው እንዲኖር የፈቀደበት አጥጋቢ ምክንያት እንዳለው ተረዳሁ። (ዘፍጥረት 3:15፤ ዮሐንስ 3:16፤ ሮሜ 9:17) ይሖዋ አለምንም ተስፋ እንዳልተወን፣ በምድር ላይ በገነት ለዘላለም ሊያኖረን ቃል እንደገባና ይህንንም አጋጣሚ ከፊታችን እንደዘረጋልን ተገነዘብኩ። (መዝሙር 37:29፤ 96:11, 12፤ ኢሳይያስ 35:1, 2፤ 45:18) በዚህች ገነት ውስጥ ቀስ በቀስ እየደከመ የሄደው የማየት ችሎታዬን መልሼ አገኛለሁ።—ኢሳይያስ 35:5
የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ጀመርኩ
እህቴ ማርያ-ክሌር ከእኔ ትንሽ ቀደም ብላ ስትጠመቅ እኔ ደግሞ በታኅሣሥ 12, 1985 ራሴን ለይሖዋ መወሰኔን በጥምቀት አሳየሁ። ብዙም ሳይቆይ ዣን-ፔር የተባለው ወንድሜና እናቴ ራሳቸውን ወስነው ተጠመቁ።
በጉባኤያችን ውስጥ ብዛት ያላቸው የዘወትር አቅኚዎች ማለትም የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች ነበሩ። በፊታቸው ላይ የሚነበበው ደስታና ያላቸው የአገልግሎት ቅንዓት እኔም እንደ እነርሱ እንድሆን አነሳሳኝ። የዓይን ሕመምና እንደ ልብ የማያንቀሳቅስ የእግር ችግር ያለባት ማርያ-ክሌር እንኳ የሙሉ ጊዜ አገልጋይ መሆን ችላ ነበር፤ ምሳሌነቷ አሁንም ድረስ ግሩም ማበረታቻ ሆኖልኛል። በጉባኤም ሆነ በቤተሰብ አካባቢ በአቅኚዎች መከበቤ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት የመካፈል ከፍተኛ ጉጉት እንዲያድርብኝ አድርጓል። በመሆኑም በኅዳር 1990 በቤዚየ ከተማ ውስጥ አቅኚ ሆኜ ማገልገል ጀመርኩ።—መዝሙር 94:17-19
የተስፋ መቁረጥ ስሜትን መቋቋም
በአገልግሎት የሌሎች አቅኚዎች እርዳታ ያልተለየኝ ቢሆንም እንኳ ያለብኝ የአቅም ውስንነትና የበለጠ ለማድረግ የነበረኝ ጉጉት ከጊዜ ወደ ጊዜ ተስፋዬን እያሟጠጠው ሄደ። ያም ሆኖ በእነዚህ ወቅቶች የይሖዋ ድጋፍ አልተለየኝም። የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ጽሑፎች ማውጫን በመጠቀም እንደ እኔው የዓይን ችግር ያለባቸውን የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች የሕይወት ታሪኮችን አነብ ነበር። ብዙ መሆናቸውን ስረዳ እጅግ ተገረምኩ! እነዚህ ጠቃሚና አበረታች ተሞክሮዎች የማደርገውን ጥረት ማድነቅ እንደሚኖርብኝ እንዲሁም ያለብኝን የአቅም ገደብ አምኜ እንድቀበል አድርገውኛል።
የሚያስፈልጉኝን ነገሮች ለማሟላት ስል ከሌሎች የይሖዋ ምሥክሮች ጋር በመሆን አንድ የገበያ ማዕከል አጸዳ ጀመር። አንድ ቀን የሥራ ባልደረቦቼ አጽድቼ ያለፍኩትን ሥፍራ ደግመው ሲያጸዱ ተመለከትኩ። በእርግጥም ሳላጸዳ ያለፍኩት ብዙ ቆሻሻ ነበር። በመሆኑም የጽዳት ቡድኑ ኃላፊ ወደ ሆነችው ቫሌሪ የተባለች አቅኚ እህት ሄድኩና በሌሎች ላይ ችግር እየፈጠርኩ መሆኑንና አለመሆኑን ምንም ሳትደብቅ እንድትነግረኝ ጠየቅኳት። ሥራውን መሥራት እንደማልችል ተሰምቶኝ ራሴ ማቆም እንዳለብኝ እስከምወስን ድረስ መቀጠል እንደምችል በደግነት ነገረችኝ። የጽዳት ሥራውን በመጋቢት 1994 አቆምኩ።
አሁንም የዋጋ ቢስነት ስሜት ያስቸግረኝ ጀመር። ይሁንና ለይሖዋ ከልብ የመነጨ ጸሎት አቀርባለሁ፤ ልመናዬን እንደሚሰማም አውቅ ነበር። በዚህ ጊዜም ቢሆን መጽሐፍ ቅዱስንና ሌሎች መንፈሳዊ ጽሑፎችን ማጥናቴ ትልቅ ድጋፍ ሆኖልኛል። ዓይኔ እየደከመ ቢሄድም ይሖዋን ለማገልገል ያለኝ ጉጉት ግን ከመቼውም ይበልጥ ጨምሮ ነበር። ምን ማድረግ እችል ይሆን?
መጀመሪያ ተመዘገብኩ፣ ከዚያም ፈጣን ውሳኔ አደረግሁ
ኒም በሚገኘው የማየት ችግር ያለባቸውና ማየት የተሳናቸው ተሃድሶ ማዕከል ለመግባት አመለከትኩና ለሦስት ወር ያህል እንድሠለጥን ተፈቀደልኝ። እነዚህን ጊዜያት በአግባቡ ተጠቅሜባቸዋለሁ። ያለብኝ የአካል ጉድለት ምን ያህል ከባድ እንደሆነ የተረዳሁ ከመሆኑም በላይ እንዴት ከሁኔታዎቹ ጋር ራሴን ማስማማት እንዳለብኝ ተማርኩ። በተለያየ የአካል ጉዳት ከሚሠቃዩ ሰዎች ጋር አብሬ መሆኔ ያለኝ ክርስቲያናዊ ተስፋ ምን ያህል ውድ መሆኑን እንድገነዘብ ረዳኝ። ቢያንስ ቢያንስ እኔ ግብ አለኝ፤ ጠቃሚ የሆነ ተግባር ማከናወንም እችላለሁ። በተጨማሪም ፈረንሳይኛ ብሬይል ተማርኩ።
ወደ ቤት ስመለስ ቤተሰቦቼ የወሰድኩት ሥልጠና ምን ያህል እንደረዳኝ ማስተዋል ቻሉ። ይሁንና በጣም የጠላሁት ነገር ማየት የተሳናቸው ሰዎች የሚጠቀሙበትን ነጭ ዘንግ መያዝ ነበር። ይህን ዘንግ መያዝ እንዳለብኝ አምኜ ለመቀበል ተቸገርኩ። በመሆኑም ምናልባት የሚመራኝ የሠለጠነ ውሻ ወይም ሌላ ዓይነት እርዳታ ባገኝ የተሻለ እንደሆነ ተሰማኝ።
የሠለጠነ ውሻ ለማግኘት ለአንድ ድርጅት ያመለከትኩ ቢሆንም ተራዬ እስኪደርስ መጠበቅ እንዳለብኝ ተነገረኝ። ከዚህም በላይ ድርጅቱ ሁኔታዎችን አጣርቶ እንጂ እንዲሁ ለማንም የሠለጠነ ውሻ አይሰጥም። አንድ ቀን፣ ማየት ለተሳናቸው ሰዎች የተቋቋመን ማኅበር በገንዘብ የምትደጉም አንዲት ሴት በሠፈራችን ያለው የቴኒስ ክበብ በአካባቢያችን ለሚገኝ ማየት ለተሳነው ወይም አጥርቶ የማየት ችግር ላለበት አንድ ሰው ለመምራት የሠለጠነ ውሻ ለመለገስ እንዳሰበ ነገረችኝ። በጊዜው ትዝ ያልኳት እኔ እንደሆንኩ ገለጸችልኝ። እሺ ብዬ መቀበል ይኖርብኝ ይሆን? በጉዳዩ ውስጥ የይሖዋ እጅ እንዳለበት ስላስተዋልኩ በደግነት የቀረበልኝን ግብዣ ተቀበልኩ። ይሁንና ውሻው እስኪደርሰኝ መጠበቅ ነበረብኝ።
ስለ አፍሪካ ማሰቤን አልተውኩም
በዚህ ጊዜ የትኩረት አቅጣጫዬ ተቀየረ። ቀደም ሲል እንደጠቀስኩት ከልጅነቴ ጀምሮ ስለ አፍሪካ አስብ ነበር። ዓይኔ ከቀን ወደ ቀን እየደከመ ቢሄድም፣ በተለይ በአፍሪካ መጽሐፍ ቅዱስን ለማወቅና ይሖዋን ለማገልገል ከፍተኛ ፍላጎት ያላቸው ብዙ ሰዎች እንዳሉ ማወቄ ወደዚህ አህጉር ለመሄድ ያለኝን ጉጉት ከፍ አደረገው። ከጥቂት ጊዜ በፊት አፍሪካን መጎብኘት እንደምፈልግ ለቫሌሪ አጫውቻት ነበር። አብራኝ መሄድ ትፈልግ እንደሆነ ጠየቅኳት። ቫሌሪም በጉዳዩ ተስማማች፤ በአፍሪካ ለሚገኙ ፈረንሳይኛ ተናጋሪ የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮዎች ደብዳቤ ጻፍን።
ከቶጎ ቅርንጫፍ ቢሮ መልስ አገኘን። እኔም እጅግ በመደሰት ደብዳቤውን እንድታነብልኝ ቫሌሪን ጠየቅኳት። ደብዳቤው የሚያበረታታ ስለነበር ቫሌሪ “ጥሩ ነዋ፣ ታዲያ ለምን አንሄድም?” አለችኝ። በቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ ከሚገኙት ወንድሞች ጋር ከተጻጻፍን በኋላ በዋና ከተማው በሎሜ ከምትገኝ ሳንድራ የተባለች አቅኚ እህት ጋር አስተዋወቁኝ። የመነሻ ቀናችን ታኅሣሥ 1, 1998 እንዲሆን ተቆረጠ።
የገጠመን ነገር ከለመድነው ፍጹም የተለየ ቢሆንም በጣም አስደሳች ነበር። ሎሜ ደርሰን ከአውሮፕላን ስንወርድ የአፍሪካ ሞቃት አየር ልክ እንደ ብርድ ልብስ ሲያለብሰን ተሰማን። እዚያም ከሳንድራ ጋር ተገናኘን ። ከዚህ ቀደም ተያይተን የማናውቅ ብንሆንም እንኳ ከትንሽ ጊዜ በኋላ የረጅም ጊዜ ወዳጆች የሆንን ያህል ተሰማን። ሳንድራና ጓደኛዋ ከመምጣታችን ጥቂት ቀደም ብሎ በመካከለኛው የአገሪቱ ክፍል በምትገኝ ታብሊግቦ ተብላ በምትጠራ ትንሽ ከተማ ውስጥ ልዩ አቅኚ ሆነው እንዲያገለግሉ ተሹመው ነበር። በመሆኑም እኛም ወደተሰጣቸው አዲስ ምድብ የመሄድ መብት አገኘን። ከሁለት ወራት ቆይታ በኋላ ስንሰነባበት ተመልሼ እንደምመጣ እርግጠኛ ነበርኩ።
ወደ ቶጎ ተመልሼ በመሄዴ ተደሰትኩ
ብዙም ሳይቆይ ከፈረንሳይ ወደ ቶጎ ለማደርገው ሁለተኛ ጉዞ ዝግጅት ማድረግ ጀመርኩ። የቤተሰቦቼ እርዳታ ታክሎበት ስድስት ወር ለመቆየት የሚያስችለኝን ዝግጅት አደረግሁ። በመሆኑም በመስከረም 1999 ወደ ቶጎ በሚበር አውሮፕላን ተሳፈርኩ። ይሁንና በዚህ ወቅት ብቻዬን ነበርኩ። የአካል ጉዳተኛ ሆኜ ያላንዳች ረዳት ብቻዬን ስሄድ ሲያዩ ቤተሰቦቼ ምን እንደተሰማቸው አስቡ! ሆኖም ያንን ያህል መጨነቅ አልነበረባቸውም። እንደ ቤተሰብ የሆኑት ጓደኞቼ ሎሜ እንደሚጠብቁኝ ለወላጆቼ አስረድቻቸው ነበር።
ለመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ፍላጎት ያላቸው ብዙ ሰዎች ወደሚገኙበት ወደዚህ ሥፍራ ዳግመኛ መመለስ ምንኛ አስደሳች ነው! በየመንገዱ መጽሐፍ ቅዱስ የሚያነብቡ ሰዎችን መመልከት እንግዳ ነገር አይደለም። በታብሊግቦ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ውይይት ለማድረግ ሲሉ ብቻ ሰዎቹ ራሳቸው ይጠሯችኋል። መጠነኛ ኑሮ ካላቸው ከሁለቱ ልዩ አቅኚዎች ጋር አንድ ላይ መኖር እንዴት ያለ ታላቅ መብት ነበር! ሌላ ዓይነት ባሕል አወቅሁ፤ እንዲሁም ነገሮችን በተለየ መንገድ የመመልከት ችሎታ አዳበርኩ። በመጀመሪያ በአፍሪካ የሚኖሩት ክርስቲያን ወንድሞቻችን ከመንግሥቱ ጋር ለተያያዙ ጉዳዮች በሕይወታቸው ውስጥ ቀዳሚ ሥፍራ እንደሚሰጡ መገንዘብ ቻልኩ። ለምሳሌ ያህል፣ መንግሥት አዳራሻቸው ለመድረስ ብዙ ኪሎ ሜትሮችን በእግር መጓዝ የሚጠይቅባቸው መሆኑ ስብሰባዎች ላይ ከመገኘት አያግዳቸውም። ከዚህም በላይ ያላቸው ፍቅርና የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ ብዙ አስተምሮኛል።
አንድ ቀን ከመስክ አገልግሎት እየተመለስን እያለ ወደ ፈረንሳይ መሄድ እንዳስፈራኝ ለሳንድራ አጫወትኳት። የማየት ችሎታዬ ይበልጥ ተዳክሟል። በሰው ስለተጨናነቁትና ጫጫታ ስለሚበዛባቸው የቤዚዬ አውራ ጎዳናዎች፣ ስለ አፓርታማ ደረጃዎች እንዲሁም ውስን የማየት ችሎታ ላለው ሰው አስቸጋሪ ስለሆኑት የተለያዩ ነገሮች አብሰለስል ነበር። በአንጻሩ ግን የታብሊግቦ መንገዶች ያን ያህል የተስተካከሉ ባይሆኑም ጸጥታ የነገሰባቸውና ሰውም ሆነ መኪና የማይበዛባቸው ነበሩ። ታዲያ በታብሊግቦ ይህን ለምጄ ፈረንሳይ ውስጥ እንዴት መኖር እችላለሁ?
ከሁለት ቀናት በኋላ እናቴ የውሾች ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት የእኔን መምጣት በመጠባበቅ ላይ እንደሆነ ደውላ ነገረችኝ። ኦሴኦን የተባለች ቡችላ “ዓይኔ” እንድትሆን ተዘጋጅታልኝ ነበር። በዚህ ጊዜም የሚያስፈልገኝ ነገር ተሟላልኝ፤ ስጋቴም ጠፋ። በታብሊግቦ ስድስት አስደሳች ወራት በአገልግሎት ካሳለፍኩ በኋላ ኦሴኦንን ለመውሰድ ወደ ፈረንሳይ ተመለስኩ።
ከበርካታ ወራት ልምምድ በኋላ ኦሴኦንን በኃላፊነት ተረከብኩ። መጀመሪያ ላይ ሁኔታው አስቸጋሪ ሆኖብኝ ነበር። እርስ በርሳችን መግባባትን መማር ነበረብን። ይሁንና ቀስ በቀስ ኦሴኦን ምን ያህል እንደምታስፈልገኝ ተገነዘብኩ። እንደ እውነቱ ከሆነ አሁን ይህቺ ውሻ የሕይወቴ ክፍል ሆናለች። የቤዚዬ ነዋሪዎች ውሻ ይዤ ቤታቸው በር ላይ ሲያዩኝ ምን ይሰማቸው ይሆን? በጥልቅ አክብሮትና በደግነት ይመለከቱኝ ነበር። የሰፈራችን ሰዎች ኦሴኦንን በጣም ወደዷት። ብዙ ሰዎች አካል ጉዳተኛ ከሆነ ሰው ጋር ሲሆኑ ስለሚከብዳቸው የውሻዋ መኖር ስለ ሁኔታዬ በቀላሉ ለማስረዳት አስችሎኛል። ሰዎቹም ዘና ብለው ያዳምጡኛል። በእርግጥም ኦሴኦን ጥሩ የውይይት መክፈቻ ሆናልኛለች።
ከኦሴኦን ጋር በአፍሪካ
አሁንም ስለ አፍሪካ ማሰቤን ስላልተውኩ ለሦስተኛ ጉዞዬ መዘጋጀት ጀመርኩ። በዚህ ጊዜ ግን ኦሴኦን ከጎኔ ነበረች። ከዚህም በላይ እንደ እኔው አቅኚ የሆኑት አንቶኒና ኦሮሮ የተባሉ ወጣት ባልና ሚስቶች እንዲሁም ጓደኛዬ ካሮሊን አብረውኝ ነበሩ። በዚህ ሁኔታ መስከረም 10, 2000 ሎሜ ደረስን።
መጀመሪያ ላይ ብዙዎቹ ኦሴኦንን ፈርተዋት ነበር። በሎሜ የሚገኙት ውሾች ትንንሾች በመሆናቸው አብዛኞቹ ሰዎች እንዲህ ዓይነት ትልቅ ውሻ አይተው አያውቁም ነበር። አንዳንዶች አንገቷ ላይ የታሰረውን ቀበቶ ሲመለከቱ መታሰር ያለባት ተናካሽ ውሻ እንደሆነች አድርገው ያስቡ ነበር። ኦሴኦንም በበኩሏ እኔ ላይ ጉዳት የሚያስከትል መስሎ የተሰማትን ነገር ሁሉ ለመከላከል ትሞክር ጀመር። ያም ሆኖ አካባቢውን ለመላመድ ብዙ ጊዜ አልፈጀባትም። የአንገቷ ቀበቶ ሲታሰርላት በሥራ ላይ እንዳለች ስለምታውቅ አደብ ገዝታ በታማኝነት ከጎኔ ትቆማለች። ስትፈታ ደግሞ ተጫዋች አንዳንዴም ተንኮለኛ ናት። በርካታ አስደሳች ጊዜያት አብረን አሳልፈናል።
በታብሊግቦ የሚኖሩት ሳንድራና ክርስቲና ሁላችንም እነርሱ ቤት እንድናርፍ ጋበዙን። በአካባቢው የሚኖሩት ወንድሞችና እህቶች ከኦሴኦን ጋር እንዲላመዱ በማሰብ ወደ ማረፊያችን እየጋበዝን የውሻዋ ሥራ ምን እንደሆነ፣ ለምን እንዳስፈለገችኝና ያላትን ባሕርይ እንገልጽላቸው ነበር። የጉባኤ ሽማግሌዎች ኦሴኦንን ወደ መንግሥት አዳራሹ ይዣት እንድመጣ ተስማሙ። ይሁንና በቶጎ ውስጥ ይህ ዓይነቱ ዝግጅት ሲደረግ የመጀመሪያ ስለነበር ሁኔታውን የሚገልጽ ማስታወቂያ በጉባኤ ተነገረ። አገልግሎት ስወጣ ኦሴኦንን ይዤ የምሄደው ተመላልሶ መጠይቅ የማደርግ ወይም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የምመራ ከሆነ ነው፤ ምክንያቱም በእነዚህ ወቅቶች ሰዎቹ ለምን ይዣት እንደምሄድ ስለሚገነዘቡ ነበር።
በዚህ ክልል ውስጥ ማገልገል ሁልጊዜ አስደሳች ነው። የምቀመጥበት ወንበር ለማምጣት ያላቸውን ጉጉት ጨምሮ ቅን የሆኑ ሰዎች የሚያሳዩኝ የአሳቢነት መንፈስ ዘወትር ልቤን ይነካዋል። ጥቅምት 2001 ወደ ቶጎ ባደረግኩት አራተኛ ጉዞ ላይ እናቴ አብራኝ ነበረች። ለሦስት ሳምንታት አብራኝ ከቆየች በኋላ ደኅንነቴን አረጋግጣና ደስ ብሏት ወደ ፈረንሳይ ተመለሰች።
ቶጎ ውስጥ ማገልገል በመቻሌ ይሖዋን አመሰግነዋለሁ። ይሖዋ እሱን ለማገልገል የተቻለኝን ጥረት እስካደረግሁ ድረስ ዘወትር ‘የልቤን መሻት እንደሚሰጠኝ’ እተማመናለሁ።a
[የግርጌ ማስታወሻ]
a እህት ሞርጉ ወደ ፈረንሳይ ከተመለሰች በኋላ ለአምስተኛ ጊዜ ወደ ቶጎ የተጓዘች ሲሆን በዚህ ወቅት ከጥቅምት 6, 2003 እስከ የካቲት 6, 2004 ቆይታለች። የሚያሳዝነው ግን፣ ይህ ጉዞ በአንዳንድ ውስብስብ የጤና እክሎች የተነሳ በዚህ ሥርዓት ወደ ቶጎ ያደረገችው የመጨረሻ ጉዞ ሳይሆን አይቀርም። ይሁንና አሁንም ይሖዋን ለማገልገል ከፍተኛ ጉጉት አላት።
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ስለ አፍሪካ ሰፋፊ መስኮችና ማራኪ የዱር እንስሳት ሳስብ ደስ ይለኝ ነበር
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኦሴኦን ተመላልሶ መጠየቅ ሳደርግ አብራኝ ትሄዳለች
[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የጉባኤ ሽማግሌዎች ኦሴኦንን ወደ መንግሥት አዳራሹ ይዣት እንድመጣ ተስማሙ