የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w06 1/1 ገጽ 30
  • የአንባቢያን ጥያቄዎች

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • የአንባቢያን ጥያቄዎች
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2006
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • አዎንታዊ አመለካከት ይዘን መቀጠል የምንችለው እንዴት ነው?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2014
  • ምድራችን ትጠፋ ይሆን?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2008
  • ይሖዋ ዕድሜያችንን እንዴት እንደምንቆጥር ያስተምረናል
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2001
  • ለዘላለም መኖር እንችላለን
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2022
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2006
w06 1/1 ገጽ 30

የአንባቢያን ጥያቄዎች

መዝሙር 102:​26 ምድርና ሰማይ “ይጠፋሉ” ይላል። ይህ ሲባል ፕላኔቷ ምድር ትጠፋለች ማለት ነው?

መዝሙራዊው ለይሖዋ ባቀረበው ጸሎት ላይ እንደሚከተለው ብሏል:- “አንተ ከጥንት ምድርን መሠረትህ፤ ሰማያትም የእጆችህ ሥራ ናቸው። እነርሱ ይጠፋሉ፤ አንተ ግን ጸንተህ ትኖራለህ፤ ሁላቸው እንደ ልብስ ያረጃሉ፤ እንደ መጐናጸፊያም ትለውጣቸዋለህ፤ እነርሱም ወዲያ ይጣላሉ።” (መዝሙር 102:25, 26) በጥቅሱ ዙሪያ ያለው ሐሳብ እንደሚያሳየው እነዚህ ቁጥሮች የሚናገሩት ስለ ምድር መጥፋት ሳይሆን ስለ አምላክ ዘላለማዊነት ነው። ከዚህ በተጨማሪ በጥቅሱ ዙሪያ ያለው ሐሳብ ይሖዋ ዘላለማዊ የመሆኑ መሠረታዊ ሐቅ ለአምላክ አገልጋዮች ማጽናኛ የሚሆናቸው ለምን እንደሆነ ይገልጻል።

ምናልባት በባቢሎን በግዞት ሥር ይኖር የነበረው ይህ መዝሙራዊ የደረሰበትን ሥቃይ በመናገር ይጀምራል። ሕይወቱ “እንደ ጢስ” እንደበነነ በምሬት ተናግሯል። ባለበት ከፍተኛ ጭንቀት ሳቢያ አካሉ መንምኗል፣ አጥንቶቹም “እንደ ማንደጃ ግለዋል።” እጅግ ከመዛሉ የተነሳ “ዋግ እንደመታው ሣር ደርቆአል” እንዲሁም ብቸኝነቱ ‘በቤቱ ጉልላት ላይ ያለ ብቸኛ ወፍ’ እንደሆነ ያህል ሆኖ እንዲሰማው አድርጎታል። የምግብ ፍላጎቱን አጥቷል፤ መላው ሕይወቱም በሐዘን ተሞልቷል። (መዝሙር 102:3-11) ያም ሆኖ ግን መዝሙራዊው ተስፋ አልቆረጠም። ለምን? ይሖዋ ለጽዮን ወይም ለኢየሩሳሌም የገባውን ቃል ስለሚያውቅ ነው።

በጊዜው ጽዮን ጠፍታ የነበረች ቢሆንም ተመልሳ እንደምትታደስ ይሖዋ ቃል ገብቷል። (ኢሳይያስ 66:8) በመሆኑም መዝሙራዊው “ጽዮንንም በርኅራኄ ዐይን ታያለህ፤ እግዚአብሔር ጽዮንን መልሶ ይሠራታል” ሲል ወደ ይሖዋ በልበ ሙሉነት ጸልዮአል። (መዝሙር 102:13, 16) ከዚያም መዝሙራዊው በራሱ ላይ ስለደረሰበት መከራ መናገሩን ይቀጥላል። ባድማ የነበረችው ኢየሩሳሌም በአምላክ ኃይል ዳግም የምትታደስ ከሆነ ካለበት አስከፊ ሁኔታም በእርግጥ ይሖዋ ሊታደገው እንደሚችል ገልጿል። (መዝሙር 102:17, 20, 23) መዝሙራዊው በይሖዋ ላይ ሙሉ በሙሉ እንዲታመን ያደረገው ሌላም ምክንያት አለ። ይህ ምን ይሆን? አምላክ ዘላለማዊ የመሆኑ ሐቅ ነው።

ከመዝሙራዊው አጭር ሕይወት ጋር ሲወዳደር የይሖዋ ዘላለማዊነት ይበልጥ ጎልቶ ይታያል። መዝሙራዊው ይሖዋን “ዘመናትህ ከትውልድ እስከ ትውልድ ይኖራሉ” ብሎታል። (መዝሙር 102:24) በመቀጠልም “አንተ ከጥንት ምድርን መሠረትህ፤ ሰማያትም የእጆችህ ሥራ ናቸው” ሲል ተናግሯል።​—⁠መዝሙር 102:25

ሆኖም ረጅም ዘመን የኖሩት ምድርና ሰማይ እንኳ ከይሖዋ ዘላለማዊነት ጋር ሊወዳደሩ አይችሉም። ስለሆነም መዝሙራዊው በመቀጠል “እነርሱ [ምድርና ሰማይ] ይጠፋሉ፤ አንት ግን ጸንተህ ትኖራለህ” ብሏል። (መዝሙር 102:26) ግዑዝ የሆኑት ምድርና ሰማይ ሊጠፉ ይችላሉ። እውነት ነው፣ ይሖዋ እነዚህ አካላት ዘላለማዊ እንደሆኑ የተናገረባቸው ቦታዎች አሉ። (መዝሙር 119:90፤ መክብብ 1:4) ሆኖም የአምላክ ዓላማ ቢሆን ኖሮ እነዚህ ነገሮች ሊጠፉ ይችሉ ነበር። በአንጻሩ ግን አምላክ ሊሞት አይችልም። እነዚህ ግዑዝ ፍጥረታት ‘ከዘላለም እስከ ዘላለም ሊጸኑ’ የሚችሉት ይሖዋ ስለሚጠብቃቸው ነው። (መዝሙር 148:6) ይሖዋ እነዚህን ግዑዝ ፍጥረታት በየጊዜው ማደሱን ቢያቆም ኖሮ ‘ሁላቸው እንደ ልብስ ባረጁ’ ነበር። (መዝሙር 102:26) አንድ ሰው ከልብሶቹ ይበልጥ ረጅም ዕድሜ መኖር እንደሚችል ሁሉ ይሖዋም ፍጥረታቱ ሲያልፉ እርሱ መኖሩን ይቀጥላል። ይሁንና በሌሎች ጥቅሶች ላይ እንደምናነበው ይሖዋ ምድርና ሰማይ እንዲያልፉ ፈቃዱ አይደለም። ይሖዋ ግዑዙ ምድርና ሰማይ ለዘላለም እንዲኖሩ መወሰኑን የአምላክ ቃል ያረጋግጥልናል።​—⁠መዝሙር 104:5

ይሖዋ ምንጊዜም ቃሉን የሚፈጽም አምላክ መሆኑን ማወቅ ያጽናናል። የቱንም ያህል ፈተና ይድረስብን ወደ እርሱ በምንጮኽበት ጊዜ ‘የችግረኞችን ጸሎት እንደሚመለከትና ልመናቸውንም እንደማይንቅ’ እርግጠኞች መሆን እንችላለን። (መዝሙር 102:17) አዎን፣ በመዝሙር 102 ላይ ይሖዋ እንደሚደግፈን የሚገልጹት ቃላት ከቆምንባት ምድር ይልቅ ጽኑ ናቸው።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ