የአንባቢያን ጥያቄዎች
አንድ ሰው አጋንንት ከሚያደርሱበት ጥቃት ለመላቀቅ ምን ማድረግ ይችላል?
የአምላክ ቃል የአጋንንት ጥቃት የሚደርስባቸው ሰዎች ከችግሩ መላቀቅ እንደሚችሉ ያሳያል። ለዚህም ጸሎት ትልቁን ሚና ይጫወታል። (ማርቆስ 9:25-29) ይሁንና አጋንንት እያስቸገሩት ያለ አንድ ሰው ተጨማሪ እርምጃዎችን መውሰድም ይኖርበት ይሆናል። የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች ያከናወኗቸው አንዳንድ ነገሮች እንዲህ ያለው ሰው ምን ማድረግ እንደሚጠበቅበት ይጠቁማሉ።
በጥንቷ ኤፌሶን ከተማ ይኖሩ የነበሩ አንዳንድ ሰዎች የክርስቶስ ተከታዮች ከመሆናቸው በፊት በአጋንንታዊ ድርጊቶች ይካፈሉ ነበር። ሆኖም አምላክን ለማገልገል ከወሰኑ በኋላ “ሲጠነቁሉ ከነበሩትም መካከል ብዙዎች መጽሐፋቸውን ሰብስበው በማምጣት በሕዝብ ፊት አቃጠሉ።” (የሐዋርያት ሥራ 19:19) በኤፌሶን ይኖሩ የነበሩት እነዚህ አዳዲስ አማኞች ለመናፍስታዊ ድርጊቶች ሲገለገሉባቸው የነበሩትን መጻሕፍት በማቃጠል ከአጋንንት ጥቃት ነጻ ለመውጣት የሚፈልግ ማንኛውም ሰው ሊከተለው የሚገባ ምሳሌ ትተዋል። እንደዚህ ያሉት ሰዎች ከመናፍስታዊ ሥራዎች ጋር ንክኪ ያላቸውን ዕቃዎች ምንም ሳያስቀሩ ማስወገዳቸው እጅግ አስፈላጊ ነው። ይህም መጻሕፍትን፣ መጽሔቶችን፣ ፊልሞችን፣ ኢንተርኔትን ጨምሮ ከኤሌክትሮኒክ ምንጮች የተገኙ መረጃዎችን፣ መናፍስታዊ ይዘት ያላቸው ዘፈኖችን፣ ክታቦችን እንዲሁም “ጥበቃ ያስገኛሉ” ተብለው የሚታሰቡ ከመናፍስታዊ ድርጊቶች ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ዕቃዎችና አልባሳትን ያካትታል።—ዘዳግም 7:25, 26፤ 1 ቆሮንቶስ 10:21
በኤፌሶን ይኖሩ የነበሩት ክርስቲያኖች የጥንቆላ መጽሐፎቻቸውን ካቃጠሉ ከጥቂት ዓመታት በኋላ ሐዋርያው ጳውሎስ “ተጋድሎአችን . . . ከርኩሳን መናፍስት ሰራዊት ጋር ነው” ሲል ጽፏል። (ኤፌሶን 6:12) ጳውሎስ “የዲያብሎስን የተንኰል ሥራ መቋቋም ትችሉ ዘንድ፣ የእግዚአብሔርን ሙሉ የጦር ዕቃ ልበሱ” በማለት ክርስቲያኖችን አሳስቧቸዋል። (ኤፌሶን 6:11) ይህ ምክር ዛሬም ቢሆን ይሠራል። ክርስቲያኖች ክፉ መናፍስት የሚያደርሱባቸውን ጥቃት ለመመከት መንፈሳዊ ትጥቃቸውን ማጠናከር ይኖርባቸዋል። ጳውሎስ “ከእነዚህም ሁሉ ጋር፣ የሚንበለበሉትን የክፉውን ፍላጻዎች ሁሉ ልታጠፉ የምትችሉበትን የእምነትን ጋሻ አንሡ” ሲል ጠበቅ አድርጎ ገልጿል። (ኤፌሶን 6:16) አንድ ሰው መጽሐፍ ቅዱስን በማንበብ እምነቱን ማጠናከር ይችላል። (ሮሜ 10:17፤ ቈላስይስ 2:6, 7) በመሆኑም አዘውትሮ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ክፉ መናፍስት የሚያደርሱብንን ተጽዕኖ ለመመከት የሚያስችል የእምነት ጋሻ እንዲኖረን ይረዳናል።—መዝሙር 91:4፤ 1 ዮሐንስ 5:5
በኤፌሶን ይኖሩ የነበሩት ክርስቲያኖች ሊወስዱት የሚገባ ሌላም እርምጃ ነበር። ጳውሎስ “በሁሉ ዐይነት ጸሎትና ልመና፣ በማንኛውም ሁኔታ በመንፈስ ጸልዩ” በማለት ነግሯቸዋል። (ኤፌሶን 6:18) በእርግጥም ከአጋንንት ጥቃት መላቀቅ የሚፈልጉ ሁሉ የይሖዋን ጥበቃ ለማግኘት አጥብቀው መጸለያቸው እጅግ አስፈላጊ ነው። (ምሳሌ 18:10፤ ማቴዎስ 6:13፤ 1 ዮሐንስ 5:18, 19) ከዚህ ጋር በሚስማማ መንገድ መጽሐፍ ቅዱስ “እንግዲህ ራሳችሁን ለእግዚአብሔር አስገዙ፤ ዲያብሎስን ተቃወሙት፤ ከእናንተም ይሸሻል” በማለት ይናገራል።—ያዕቆብ 4:7
የአጋንንት ጥቃት የሚደርስበት ሰው ነጻ ለመውጣት አጥብቆ መጸለይ ይኖርበታል፤ ይሁንና ሌሎች ክርስቲያኖችም ይሖዋን ከልብ ለማገልገል የሚፈልገውንና ክፉ መናፍስትን ለመቋቋም የሚታገለውን ግለሰብ አስመልክተው መጸለይ ይችላሉ። በአጋንንት ጥቃት የሚደርስበት ሰው ጥቃቱን ለመቋቋም የሚያስችል መንፈሳዊ ጥንካሬ እንዲያገኝ ወደ አምላክ ሊጸልዩለት ይችላሉ። የአምላክ ቃል “የጻድቅ ሰው ጸሎት ኀይል አለው፤ ታላቅ ነገርም ያደርጋል” በማለት ስለሚናገር የአምላክ አገልጋዮች የሚያቀርቡት ጸሎት ‘ዲያብሎስን ለመቃወም’ ከልቡ የሚጥረውን ሰው እንደሚጠቅመው አያጠራጥርም።—ያዕቆብ 5:16
[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በኤፌሶን የነበሩት በክርስቶስ ያመኑ ሰዎች የጥንቆላ መጽሐፎቻቸውን አስወግደዋል