ልጆቻችሁን አስተምሩ
ሳሙኤል ዘወትር ትክክል የሆነውን ያደርግ ነበር
ሰዎች መጥፎ ነገር ሲሠሩ አይተህ ታውቃለህ?—a ሳሙኤል እንዲህ ያለውን ሁኔታ አይቶ ያውቃል። ሳሙኤል ይኖር የነበረው ሰዎች መጥፎ ነገር ይሠራሉ ተብሎ በማይጠብቅበት ስፍራ ነበር። ይህም ስፍራ በሴሎ ይገኝ የነበረው የአምላክ ቤተ መቅደስ ወይም አምላክ የሚመለክበት ቦታ ነበር። ከዛሬ 3,000 ዓመት በፊት ሳሙኤል በዚህ ስፍራ መኖር የጀመረው እንዴት እንደነበር እንመልከት።
ሳሙኤል ከመወለዱ በፊት እናቱ ሐና ልጅ እንዲኖራት በጣም ትፈልግ ነበር። ወደ ቤተ መቅደስ በሄደችበት ጊዜ ይህን ፍላጎቷን ለአምላክ በጸሎት ነገረችው። ሐና ከልብ በመነጨ ስሜት ትጸልይ ስለነበር ከንፈሯ ይንቀሳቀስ ነበር። ይህን የተመለከተው ሊቀ ካህኑ ዔሊ የሰከረች መሰለው። ይሁንና ዔሊ፣ ሐና እንደዚያ ያደረገችው ሰክራ ሳይሆን በጣም ተጨንቃ መሆኑን ሲረዳ “የእስራኤል አምላክ የለመንሺውን ይስጥሽ” በማለት ባረካት።—1 ሳሙኤል 1:17
ከጊዜ በኋላ ሳሙኤል ተወለደ፤ ሐናም በጣም ከመደሰቷ የተነሳ ለባሏ ለሕልቃና ‘ሳሙኤል ጡት እንደጣለ አምላክን እንዲያገለግል ወደ ቤተ መቅደስ እወስደዋለሁ’ በማለት ነገረችው። ሐናም የተናገረችውን ፈጸመች! ሳሙኤል በዚያን ጊዜ አራት ወይም አምስት ዓመት ሳይሆነው አይቀርም።
በወቅቱ ዔሊ ዕድሜው ገፍቶ የነበረ ሲሆን ልጆቹ አፍኒንና ፊንሐስ ይሖዋን በትክክለኛው መንገድ ማምለክ ትተው ነበር። ወደ ቤተ መቅደሱ ከሚመጡ ሴቶች ጋር ሳይቀር የጾታ ብልግና ይፈጽሙ ነበር! አባታቸው ምን ማድረግ የነበረበት ይመስልሃል?— አዎ፣ ተግሣጽ ሊሰጣቸውና መጥፎ ድርጊቶችን ከመፈጸም እንዲቆጠቡ ሊያደርጋቸው ይገባ ነበር።
ወጣቱ ሳሙኤል ያደገው በቤተ መቅደሱ ውስጥ በመሆኑ የዔሊ ልጆች መጥፎ ሥነ ምግባር እንዳላቸው ሳያውቅ አልቀረም። ሳሙኤል የእነሱን መጥፎ ምሳሌ ተከትሎ ይሆን?— በፍጹም፣ ከዚህ ይልቅ ልክ ወላጆቹ እንዳስተማሩት ትክክል የሆነውን ነገር ማድረጉን ቀጥሎ ነበር። ይሖዋም በዔሊ መቆጣቱ ምንም አያስገርምም። እንዲያውም ይሖዋ፣ የዔሊን ቤተሰብ በተለይም መጥፎ ልጆቹን እንደሚቀጣቸው እንዲናገር አንድ ነቢይ ልኮ ነበር።—1 ሳሙኤል 2:22-36
ሳሙኤል ከዔሊ ጋር ሆኖ በቤተ መቅደሱ ውስጥ ያገለግል ነበር። ከዕለታት አንድ ቀን ሳሙኤል ተኝቶ ሳለ ስሙ ሲጠራ ሰማ። ሳሙኤልም ወደ ዔሊ ሮጦ ሄደ። ዔሊ ግን እሱ እንዳልጠራው ነገረው። ቆይቶም ሳሙኤል በድጋሚ የተጠራ መሰለው። ሁኔታው ለሦስተኛ ጊዜ ሲከሰት፣ ዔሊ ሳሙኤልን ስትጠራ “እግዚአብሔር ሆይ፤ ባሪያህ ይሰማልና ተናገር” በል አለው። ሳሙኤል እንደተባለው ሲያደርግ ይሖዋ አነጋገረው። ይሖዋ ለሳሙኤል ምን እንደነገረው ታውቃለህ?—
አምላክ፣ በዔሊ ቤተሰብ ላይ ምን ቅጣት እንደሚያመጣ ለሳሙኤል ነገረው። በማግስቱ ጠዋት፣ ሳሙኤል ይሖዋ ያለውን ነገር ለዔሊ ለመንገር ፈራ። ይሁን እንጂ ዔሊ አምላክ የነገረህን “አትደብቀኝ” ሲል ለመነው። በመጨረሻም፣ ሳሙኤል ከዚያ ቀደም የአምላክ ነቢይ እንዳደረገው ሁሉ ይሖዋ ያለውን አንድም ሳያስቀር ነገረው። ዔሊም “[ይሖዋ] መልካም መስሎ የታየውን ያድርግ” አለ። ከጊዜ በኋላ አፍኒንና ፊንሐስ የተገደሉ ሲሆን ዔሊም ሞተ።—1 ሳሙኤል 3:1-18
ሳሙኤል ግን ‘እያደገ ሄደ፤ ይሖዋም ከእርሱ ጋር ነበር።’ በዚህ ወቅት ሳሙኤል፣ በወጣቶች ሕይወት ውስጥ ትልቅ ቦታ በሚሰጠው በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ ይገኝ ነበር። ሳሙኤል ሌሎች ሰዎች መጥፎ ነገር በሚያደርጉበት ጊዜም እንኳ ትክክለኛውን ነገር ማድረግ መቀጠሉን ቀላል ሆኖ ያገኘው ይመስልሃል?— ቀላል ባይሆንም እንኳ ሳሙኤል ዕድሜውን ሙሉ ይሖዋን በታማኝነት አገልግሏል።—1 ሳሙኤል 3:19-21
አንተስ? እያደግክ ስትሄድ የሳሙኤልን ምሳሌ ትከተላለህ? ዘወትር ትክክል የሆነውን ለማድረግ ትጥራለህ? የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶችንና ወላጆችህ ያስተማሩህን ነገሮች ተግባራዊ ማድረግህን ትቀጥላለህ? እንደዚህ የምታደርግ ከሆነ ይሖዋንም ሆነ ወላጆችህን ታስደስታለህ።
a ይህን ርዕስ የምታነበው ከልጆች ጋር ከሆነ፣ ይህ ሰረዝ ጥያቄውን ቆም ብለህ እንድትጠይቃቸው ለማስታወስ ተብሎ የተደረገ ነው።