አምላክ አካል አለው?
የተለመዱት መልሶች፦
◼ “ልክ እንደ አየር፣ እሱ በየትኛውም ስፍራ፤ በማንኛውም ነገር ውስጥ ይገኛል።”
◼ “እንዲህ ነው ተብሎ ሊገለጽ የማይችል የማሰብ ችሎታ ያለው ነገር ወይም ኃይል ነው።”
ኢየሱስ ምን ብሏል?
◼ “በአባቴ ቤት ብዙ መኖሪያ አለ።” (ዮሐንስ 14:2) ኢየሱስ በምሳሌያዊ አነጋገር አምላክ ቤት ወይም መኖሪያ ስፍራ እንዳለው ገልጿል።
◼ “እኔ ከአብ ወጥቼ ወደ ዓለም መጥቻለሁ። አሁን ደግሞ ዓለምን ትቼ ወደ አብ ልሄድ ነው።” (ዮሐንስ 16:28) ኢየሱስ፣ አምላክ በተወሰነ ቦታ እንደሚኖርና ቃል በቃል አካል እንዳለው ያምን ነበር።
ኢየሱስ፣ አምላክ ይህ ነው ተብሎ ሊገለጽ የማይችል አንድ ዓይነት ኃይል እንደሆነ አድርጎ ተናግሮ አያውቅም። እንዲያውም አምላክን ያነጋግርና ወደ እሱ ይጸልይ ነበር። አብዛኛውን ጊዜ ይሖዋን በሰማይ የሚኖር አባቱ እንደሆነ አድርጎ ይጠራው የነበረ ሲሆን ይህም ከእሱ ጋር የጠበቀ ዝምድና እንዳለው የሚያሳይ አባባል ነው።—ዮሐንስ 8:19, 38, 54
እርግጥ “አምላክን ያየው አንድም ሰው የለም፤” ደግሞም “አምላክ መንፈስ ነው።” (ዮሐንስ 1:18፤ 4:24) እንዲህ ሲባል ግን አምላክ አካል ወይም ቅርጽ የለውም ማለት አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ “ሥጋዊ አካል ካለ መንፈሳዊ አካልም አለ” በማለት ይናገራል። (1 ቆሮንቶስ 15:44) ታዲያ ይሖዋ መንፈሳዊ አካል አለው ማለት ነው?
አዎ። ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ በኋላ “ስለ እኛ በአምላክ ፊት ይታይ ዘንድ በቀጥታ ወደ ሰማይ ገብቷል።” (ዕብራውያን 9:24) ይህ ሁኔታ ስለ አምላክ ሁለት ቁም ነገሮች ያስተምረናል። በመጀመሪያ ደረጃ አምላክ መኖሪያ ቦታ እንዳለው እንገነዘባለን። በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ አምላክ በየትም ስፍራ የሚገኝ ሊገለጽ የማይችል ኃይል ሳይሆን የተወሰነ አካል እንዳለው እንረዳለን።
እንዲህ ከሆነ ታዲያ አምላክ ሁሉንም ነገር እንዴት መቆጣጠር ይችላል? አምላክ ቅዱስ መንፈሱን ወይም በእንቅስቃሴ ላይ የሚገኘውን ኃይሉን በአጽናፈ ዓለም ውስጥ ወደየትኛውም ቦታ መላክ ይችላል። አንድ አባት ልጆቹን ለማበረታታት ወይም ለመደገፍ እጁን እንደሚዘረጋ ሁሉ አምላክም ዓላማውን ለመፈጸም ቅዱስ መንፈሱን ይልካል።—መዝሙር 104:30፤ 139:7
አምላክ የራሱ የሆነ ባሕርይ ያለው አካል በመሆኑ የሚወዳቸውና የሚጠላቸው ነገሮች አልፎ ተርፎም የተለያዩ ስሜቶች አሉት። መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ ሕዝቦቹን እንደሚወድ፣ በሥራው እንደሚደሰት፣ የጣዖት አምልኮን እንደሚጠላ እንዲሁም ሰዎች የሚሠሩት ክፋት እንደሚያሳዝነው ይገልጻል። (ዘፍጥረት 6:6፤ ዘዳግም 16:22፤ 1 ነገሥት 10:9፤ መዝሙር 104:31) አንደኛ ጢሞቴዎስ 1:11 ላይ ‘ደስተኛ የሆነ አምላክ’ ተብሎ ተጠርቷል። ኢየሱስ ይህን አምላክ በሙሉ ልባችን መውደድን መማር እንደምንችል መናገሩ ምንም አያስደንቅም!—ማርቆስ 12:30a
[የግርጌ ማስታወሻ]
a በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች ከተዘጋጀው ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? ከተባለው መጽሐፍ ላይ ምዕራፍ 1ን ተመልከት።
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
አንድ አባት ለልጆቹ እጁን እንደሚዘረጋላቸው ሁሉ አምላክም ዓላማውን ለመፈጸም ቅዱስ መንፈሱን ይልካል