ንጹሕ አቋም ይዘህ መኖርህ የይሖዋን ልብ ደስ ያሰኛል
“ልጄ ሆይ፣ ጠቢብ ሁን፣ ልቤንም ደስ አሰኘው፣ ለሚሰድበኝ መልስ መስጠት ይቻለኝ ዘንድ።”—ምሳሌ 27:11 የ1954 ትርጉም
1, 2. (ሀ) የኢዮብ መጽሐፍ ሰይጣን ምን ክስ እንደሰነዘረ ይገልጻል? (ለ) ሰይጣን ከኢዮብ ዘመን በኋላም ይሖዋን መገዳደሩን እንዳላቆመ የሚጠቁመው ምንድን ነው?
ሰይጣን፣ የአምላክ ታማኝ አገልጋይ የሆነውን የኢዮብን ንጹሕ አቋም ለመፈተን ያቀረበውን ጥያቄ ይሖዋ ተቀብሎት ነበር። በዚህም የተነሳ ኢዮብ ከብቶቹንና ልጆቹን ያጣ ሲሆን ጤንነቱም ተቃውሶ ነበር። ሆኖም ሰይጣን የኢዮብን ንጹሕ አቋም ለመፈተን የተነሳው እሱን ብቻ አስቦ አልነበረም። ሰይጣን “‘ቍርበት ስለ ቍርበት ነው’ እንዲሉ ሰው ለሕይወቱ ሲል ያለውን ሁሉ ይሰጣል” ብሏል። ሰይጣን እንዲህ ብሎ መናገሩ ኢዮብን ብቻ ሳይሆን ሌሎች ሰዎችንም የሚመለከት ለብዙ ዘመናት የዘለቀ አከራካሪ ጉዳይ አስነስቷል።—ኢዮብ 2:4
2 ኢዮብ ፈተና ከደረሰበት ከ600 ዓመታት ገደማ በኋላ ሰለሞን በመንፈስ መሪነት “ልጄ ሆይ፣ ጠቢብ ሁን፣ ልቤንም ደስ አሰኘው፣ ለሚሰድበኝ መልስ መስጠት ይቻለኝ ዘንድ” በማለት ጽፏል። (ምሳሌ 27:11 የ1954 ትርጉም) ከዚህ በግልጽ መረዳት እንደሚቻለው ሰይጣን በዚያም ወቅት ቢሆን ይሖዋን መገዳደሩን አላቆመም ነበር። ከዚህም በላይ ሐዋርያው ዮሐንስ ባየው ራእይ ላይ የአምላክ መንግሥት በ1914 ከተቋቋመ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ከሰማይ የተባረረው ሰይጣን፣ የአምላክን አገልጋዮች ይከስ እንደነበር ተገልጿል። አዎን፣ የዚህ ክፉ ሥርዓት ፍጻሜ በጣም በተቃረበበት በዚህ ጊዜም ቢሆን ሰይጣን የአምላክ አገልጋዮችን ንጹሕ አቋም በመፈተን ላይ ይገኛል!—ራእይ 12:10
3. ከኢዮብ መጽሐፍ ምን ጠቃሚ ትምህርት ማግኘት እንችላለን?
3 ከኢዮብ መጽሐፍ የምናገኛቸውን ሦስት ጠቃሚ ትምህርቶች እስቲ እንመልከት። በመጀመሪያ ደረጃ በኢዮብ ላይ የደረሰው ፈተና፣ በአምላክ ሕዝቦች ላይ ተቃውሞ የሚያስነሳውና የሰው ልጆች ቀንደኛ ጠላት የሆነው ማን እንደሆነ በግልጽ ያሳያል። ይህ ጠላት ሰይጣን ዲያብሎስ ነው። በሁለተኛ ደረጃ ምንም ዓይነት ፈተና ቢደርስብን ከአምላክ ጋር የጠበቀ ዝምድና ካለን ንጹሕ አቋማችንን መጠበቅ እንችላለን። በሦስተኛ ደረጃ ደግሞ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙንና በሆነ መንገድ ፈተና ሲደርስብን አምላክ ኢዮብን እንደረዳው ሁሉ እኛንም ይረዳናል። በዛሬው ጊዜ ይሖዋ እንዲህ የሚያደርገው በቃሉ፣ በድርጅቱና በቅዱስ መንፈሱ አማካኝነት ነው።
ቀንደኛ ጠላታችን ማን እንደሆነ ምንጊዜም አስታውስ
4. በአሁኑ ጊዜ በዓለም ላይ ለሚታየው ሁኔታ ተጠያቂው ማነው?
4 ብዙ ሰዎች ሰይጣን መኖሩን አያምኑም። በመሆኑም የዓለም ሁኔታ ሊያስጨንቃቸው ቢችልም እንኳ የችግሮቹ ዋነኛ መንስኤ ሰይጣን ዲያብሎስ መሆኑን አያስተውሉም። እውነት ነው፣ በሰዎች ላይ እየደረሰ ላለው መከራ በአብዛኛው ተጠያቂ የሚሆኑት ራሳቸው የሰው ልጆች ናቸው። የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን አዳምና ሔዋን ከፈጣሪያቸው አፈንግጠው በራሳቸው ለመመራት ወሰኑ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የተነሱት ትውልዶች በሙሉ ጥበብ የጎደለው ጎዳና ተከትለዋል። ያም ሆኖ ሔዋንን በማታለል በአምላክ ላይ እንድታምጽ ያደረጋት ዲያብሎስ ነው። ፍጽምና የጎደላቸውና ሟች የሆኑ የሰው ልጆች የሚኖሩበትን በእሱ ቁጥጥር ሥር ያለ ሥርዓት ያቋቋመው ሰይጣን ነው። ሰይጣን “የዚህ ሥርዓት አምላክ” በመሆኑ ሰብዓዊው ኅብረተሰብ የእሱ መለያ የሆኑትን ባሕርያት ይኸውም ኩራትን፣ ምቀኝነትን፣ ቅናትን፣ ስግብግብነትን፣ አታላይነትንና ዓመጽን ያንጸባርቃል። (2 ቆሮ. 4:4፤ 1 ጢሞ. 2:14፤ 3:6፤ ያዕቆብ 3:14, 15ን አንብብ።) እንዲህ ያሉ ባሕርያት ፖለቲካዊና ሃይማኖታዊ ግጭቶች እንዲቀሰቀሱ እንዲሁም ጥላቻ፣ ሙስናና ሥርዓት አልበኝነት እንዲስፋፋ ያደረጉ ሲሆን ይህም በሰው ልጆች ላይ የተለያዩ ችግሮች እንዲደርሱ ምክንያት ሆኗል።
5. ያገኘነው ውድ እውቀት ምን እንድናደርግ ያነሳሳናል?
5 የይሖዋ አገልጋዮች በመሆናችን በጣም ጠቃሚ የሆነ እውቀት አግኝተናል። አዎን፣ የዓለም ሁኔታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሽቆለቆለ እንዲሄድ ምክንያት የሆነው ማን እንደሆነ እናውቃለን። ይህን ማወቃችን በመስክ አገልግሎት በመሳተፍ፣ ዋነኛው ችግር ፈጣሪ ማን እንደሆነ ለሰዎች እንድናሳውቅ አያነሳሳንም? በተጨማሪም እውነተኛ አምላክ ከሆነው ከይሖዋ ጎን የመሰለፍና ይሖዋ፣ ሰይጣንን እንዴት እንደሚያጠፋ ብሎም በሰዎች ላይ የሚደርሰውን መከራ እንዴት እንደሚያስወግድ ለሌሎች የመናገር መብት በማግኘታችን ልንደሰት አይገባም?
6, 7. (ሀ) በእውነተኛ የአምላክ አገልጋዮች ላይ ለሚደርሰው ተቃውሞ ተጠያቂው ማን ነው? (ለ) የኤሊሁን ምሳሌ መኮረጅ የምንችለው እንዴት ነው?
6 ሰይጣን በዓለም ላይ ለሚከሰቱት በርካታ አሳዛኝ ሁኔታዎች ብቻ ሳይሆን በአምላክ ሕዝቦች ላይ ለሚደርሰው ተቃውሞም ጭምር ተጠያቂ ነው። ዲያብሎስ እኛን ለመፈተን ቆርጦ ተነስቷል። ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ሐዋርያው ጴጥሮስን “ስምዖን፣ ስምዖን፣ ሰይጣን እንደ ስንዴ ያበጥራችሁ ዘንድ ጥያቄ አቅርቧል” ብሎት ነበር። (ሉቃስ 22:31) በተመሳሳይ እኛም የኢየሱስን ፈለግ የምንከተል እንደመሆናችን መጠን ሁላችንም በሆነ መንገድ ፈተና ይደርስብናል። ጴጥሮስ፣ ዲያብሎስን ‘የሚውጠውን በመፈለግ ከሚያገሳ አንበሳ’ ጋር አመሳስሎታል። ጳውሎስ ደግሞ “ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር በመሆን ለአምላክ ያደሩ ሆነው መኖር የሚፈልጉ ሁሉ ስደት ይደርስባቸዋል” በማለት ተናግሯል።—1 ጴጥ. 5:8፤ 2 ጢሞ. 3:12
7 አንድ ወንድም ወይም አንዲት እህት አሳዛኝ ሁኔታ ሲያጋጥማቸው ቀንደኛ ጠላታችን ማን እንደሆነ ምንጊዜም እንደምናስታውስ ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? ችግር ላይ ከወደቀው ወንድማችን ከመራቅ ይልቅ የኢዮብ እውነተኛ ወዳጅ እንደነበረው እንደ ኤሊሁ ሆነን ለመገኘት ጥረት እናደርጋለን። ወንድማችን የሁላችንም ጠላት ከሆነው ከሰይጣን ጋር በሚያደርገው ትግል ከጎኑ እንሆናለን። (ምሳሌ 3:27፤ 1 ተሰ. 5:25) ዋናው ግባችን፣ የተቻለንን ሁሉ ጥረት በማድረግ የእምነት አጋራችን ንጹሕ አቋሙን ጠብቆ እንዲኖርና የይሖዋን ልብ ደስ እንዲያሰኝ መርዳት ነው።
8. ሰይጣን፣ ኢዮብ ይሖዋን ማክበሩን እንዲያቆም በማድረግ ረገድ ያልተሳካለት ለምንድን ነው?
8 ሰይጣን ከኢዮብ ንብረቶች መካከል በመጀመሪያ ያጠፋው ከብቶቹን ነበር። እነዚህ ከብቶች ለኢዮብ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደነበራቸው ጥርጥር የለውም፤ እንዲያውም ዋነኛ የገቢ ምንጮቹ ሳይሆኑ አይቀሩም። ሆኖም ኢዮብ ከብቶቹን ለአምላክ መሥዋዕት አድርጎም ያቀርባቸው ነበር። ኢዮብ “‘ምናልባት ልጆቼ ኀጢአት ሠርተው እግዚአብሔርንም በልባቸው ረግመው ይሆናል’ በማለት ጠዋት በማለዳ ስለ እያንዳንዳቸው የሚቃጠል መሥዋዕት በማቅረብ ያነጻቸው ነበር፤ ኢዮብ ይህን ዘወትር ያደርግ ነበር።” (ኢዮብ 1:4, 5) በመሆኑም ኢዮብ ዘወትር ለይሖዋ እንስሳትን መሥዋዕት አድርጎ ያቀርብ ነበር። መፈተን በጀመረበት ወቅት ግን ይህን ማድረግ አልቻለም። በዚህ ጊዜ ይሖዋን ለማክበር የሚያስችል ምንም “ሀብት” አልነበረውም። (ምሳሌ 3:9) ይሁንና ኢዮብ ይሖዋን በከንፈሮቹ ማክበር ይችል ነበር፤ ደግሞም እንደዚያ ከማድረግ ወደኋላ አላለም!
ከይሖዋ ጋር የቅርብ ዝምድና ይኑርህ
9. ከምንም በላይ ውድ የሆነው ሀብታችን ምንድን ነው?
9 ሀብታምም ሆን ድሃ፣ ወጣትም ሆን አረጋዊ፣ ጥሩ ጤንነት ያለንም ሆን የጤና ችግር ያለብን ከይሖዋ ጋር ጥሩ ዝምድና እንዲኖረን ማድረግ እንችላለን። ማንኛውም ዓይነት ፈተና ቢደርስብን ከአምላክ ጋር የቅርብ ዝምድና መመሥረታችን፣ ንጹሕ አቋማችንን ጠብቀን መኖርና የይሖዋን ልብ ደስ ማሰኘት እንድንችል ይረዳናል። ሌላው ቀርቶ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ እውነት የተወሰነ እውቀት ያላቸው ሰዎችም እንኳ ድፍረት የተሞላበት አቋም መያዝና ንጹሕ አቋማቸውን ጠብቀው መኖር ችለዋል።
10, 11. (ሀ) አንዲት እህት ንጹሕ አቋምን ከመጠበቅ ጋር በተያያዘ ያጋጠማቸውን ፈተና የተቋቋሙት እንዴት ነበር? (ለ) እኚህ እህት ለሰይጣን ምን አጥጋቢ መልስ ሰጥተዋል?
10 ከባድ ፈተናዎች ቢደርሱባቸውም በጥንት ዘመን እንደኖረው እንደ ታማኙ ኢዮብ ንጹሕ አቋማቸውን ጠብቀው ከኖሩት በርካታ ሩሲያውያን የይሖዋ ምሥክሮች መካከል አንዷ የሆኑትን የእህት ቫለንቲና ጋርኖፍስከየ ታሪክ እንደ ምሳሌ እንመልከት። በ1945 የሃያ ዓመት ወጣት ሳሉ አንድ ወንድም መሠከረላቸው። ይህ ወንድም ሁለት ጊዜ ተመልሶ በመምጣት ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ አንዳንድ ሐሳቦችን ያካፈላቸው ሲሆን ከዚያ በኋላ ግን ዳግመኛ አላዩትም። ያም ሆኖ ቫለንቲና ለሰዎች መስበክ ጀመሩ። በዚህም የተነሳ ተያዙና የስምንት ዓመት እስራት ተፈርዶባቸው ወደ አንድ ካምፕ ተላኩ። በ1953 ከእስር ሲፈቱ ወዲያውኑ መስበካቸውን ቀጠሉ። በዚህ ጊዜም እንደገና ተያዙና አሥር ዓመት ተፈረደባቸው። በአንድ ካምፕ ውስጥ ለበርካታ ዓመታት ታስረው ከቆዩ በኋላ ወደ ሌላ ካምፕ ተዛወሩ። በዚህ ካምፕ ውስጥ መጽሐፍ ቅዱስ የነበራቸው ጥቂት እህቶች ነበሩ። አንድ ቀን አንዲት እህት መጽሐፍ ቅዱሱን ለቫለንቲና አሳየቻቸው። ምን ያህል ተደስተው ሊሆን እንደሚችል መገመት አያዳግትም! ቫለንቲና በ1945 የመሠከረላቸው ወንድም ይዞት ከነበረው መጽሐፍ ቅዱስ ሌላ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ሲያዩ ይህ የመጀመሪያ ጊዜያቸው ነበር!
11 በ1967 ቫለንቲና ከእስር የተለቀቁ ሲሆን በመጨረሻም ራሳቸውን ለይሖዋ መወሰናቸውን በውኃ ጥምቀት ማሳየት ቻሉ። ባገኙት ነፃነት ተጠቅመው እስከ 1969 ድረስ በአገልግሎት በቅንዓት ሲካፈሉ ቆይተዋል። ይሁንና በዚህ ዓመት እንደገና ተይዘው የሦስት ዓመት እስር ተፈረደባቸው። ያም ሆኖ ቫለንቲና መስበካቸውን አላቆሙም። በ2001 ከመሞታቸው በፊት 44 ሰዎች እውነትን እንዲያውቁ መርዳት ችለዋል። እኚህ እህት በእስር ቤቶችና በካምፖች ውስጥ 21 ዓመታት አሳልፈዋል። ንጹሕ አቋማቸውን ለመጠበቅ ሲሉ ነፃነታቸውን ጨምሮ ማንኛውንም ነገር መሥዋዕት ለማድረግ ፈቃደኛ ሆነዋል። እህት ቫለንቲና በሕይወታቸው ማብቂያ ላይ እንዲህ ብለው ነበር፦ “የእኔ ነው የምለው ቤት ኖሮኝ አያውቅም። ያለኝ ንብረት ሁሉ ከአንድ ሻንጣ አይበልጥም ነበር፤ ሆኖም ይሖዋን በማገልገሌ ደስታና እርካታ አግኝቻለሁ።” እህት ቫለንቲና፣ የሰው ልጆች ፈተና ቢደርስባቸው ለአምላክ ታማኝ አይሆኑም በማለት ለሚከራከረው ለሰይጣን አጥጋቢ መልስ ሰጥተዋል። (ኢዮብ 1:9-11) እኚህ እህት የይሖዋን ልብ ደስ እንዳሰኙ እንዲሁም ይሖዋ እሳቸውን ጨምሮ ታማኝነታቸውን ጠብቀው የሞቱ ሌሎች ሰዎችን በትንሣኤ የሚያስነሳበትን ጊዜ በጉጉት እንደሚጠባበቅ እርግጠኞች መሆን እንችላለን።—ኢዮብ 14:15
12. ከይሖዋ ጋር ከመሠረትነው ወዳጅነት ጋር በተያያዘ ፍቅር ምን ሚና ይጫወታል?
12 ከይሖዋ ጋር ያለን ወዳጅነት የተመሠረተው ለእሱ ባለን ፍቅር ላይ ነው። የአምላክን ባሕርያት የምናደንቅ ከመሆኑም ሌላ ከእሱ ዓላማ ጋር ተስማምተን ለመኖር የምንችለውን ሁሉ እናደርጋለን። ዲያብሎስ ከሰነዘረው ክስ በተቃራኒ ለይሖዋ ባለን ፍቅር ተነሳስተን ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ በፈቃደኝነት እንገዛለታለን። እንዲህ ያለው ከልብ የመነጨ ፍቅር፣ ፈተና ሲያጋጥመን ንጹሕ አቋማችንን ጠብቀን ለመኖር የሚያስችል ጥንካሬ ይሰጠናል። ይሖዋ ደግሞ በበኩሉ ‘በታማኝነት የሚያገለግሉትን ይጠብቃል።’—ምሳሌ 2:8 የ1980 ትርጉም፤ መዝ. 97:10
13. ይሖዋ ለእሱ የምናደርገውን ነገር የሚመለከተው እንዴት ነው?
13 ለይሖዋ ያለን ፍቅር አቅማችን እንደተገደበ በሚሰማን ጊዜም እንኳ ስሙን እንድናከብር ይገፋፋናል። ይሖዋ በውስጣችን ያለውን ጥሩ ዝንባሌ የሚያይ ከመሆኑም ሌላ ማድረግ የምንፈልገውን ሁሉ ማድረግ ሳንችል ብንቀር አይኮንነንም። ትልቅ ግምት የሚሰጠው፣ የምናከናውነው ነገር ብቻ ሳይሆን ያንን ነገር ለማድረግ የተነሳሳንበት ምክንያት ጭምር ነው። ኢዮብ ብዙ መከራና ከባድ ሐዘን የደረሰበት ቢሆንም ይወነጅሉት ለነበሩት ሰዎች ለይሖዋ መንገዶች ያለውን ፍቅር ገልጿል። (ኢዮብ 10:12፤ 28:28ን አንብብ።) በኢዮብ መጽሐፍ የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ አምላክ ሐሰተኛ አጽናኞች የሆኑት ኤልፋዝ፣ በልዳዶስና ሶፋር እውነት የሆነውን ነገር ባለመናገራቸው ቁጣውን ገልጿል። ከዚህም በተጨማሪ ይሖዋ ኢዮብን አራት ጊዜ “አገልጋዬ” ብሎ መጥራቱ እንዲሁም እነዚህ ሐሰተኛ አጽናኞች ምሕረት እንዲያገኙ እንዲለምንላቸው መመሪያ መስጠቱ ኢዮብ በአምላክ ፊት ሞገስ እንዳገኘ ይጠቁማል። (ኢዮብ 42:7-9) እኛም የይሖዋን ሞገስ በሚያስገኝ መንገድ ለመመላለስ የተቻለንን ጥረት እናድርግ።
ይሖዋ ታማኝ አገልጋዮቹን ይረዳል
14. ይሖዋ፣ ኢዮብ አስተሳሰቡን እንዲያስተካክል የረዳው እንዴት ነው?
14 ኢዮብ ፍጹም ባይሆንም እንኳ ንጹሕ አቋሙን ጠብቆ መኖር ችሏል። እርግጥ ነው፣ በደረሰበት ከባድ ተጽዕኖ የተነሳ አንዳንድ ነገሮችን በተመለከተ የተሳሳተ አመለካከት አድሮበት ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ ይሖዋን “ወደ አንተ ጮኽሁ፤ ነገር ግን አልመለስህልኝም፤ . . . በክንድህም ብርታት አስጨነቅኸኝ” ብሎታል። ከዚህም በላይ ኢዮብ ‘እኔ በደለኛ አይደለሁም’ እንዲሁም “በእጄ ዐመፅ አይገኝም፤ ጸሎቴም ንጹሕ ነው” ብሎ መናገሩ ከበደል ነፃ መሆኑን ለማሳየት ከልክ ያለፈ ትኩረት ሰጥቶ እንደነበር ይጠቁማል። (ኢዮብ 10:7፤ 16:17፤ 30:20, 21) ይሁንና ይሖዋ ለኢዮብ የተለያዩ ጥያቄዎችን በማቅረብ ኢዮብ ለራሱ ከልክ ያለፈ ትኩረት መስጠቱ ተገቢ እንዳልሆነ እንዲገነዘብ በደግነት ረድቶታል። ከዚህም በተጨማሪ እነዚህ ጥያቄዎች አምላክ ታላቅ እንደሆነና የሰው ልጅ እዚህ ግባ የሚባል ፍጡር እንዳልሆነ በሚገባ እንዲያስተውል አድርገውታል። ኢዮብ የተሰጠውን መመሪያ የተቀበለ ከመሆኑም ሌላ አስፈላጊውን ማስተካከያ አድርጓል።—ኢዮብ 40:8፤ 42:2, 6ን አንብብ።
15, 16. ይሖዋ በዛሬው ጊዜ ለሚገኙ አገልጋዮቹ እርዳታ የሚሰጠው በምን መንገዶች ነው?
15 ይሖዋ በዛሬው ጊዜ ለሚገኙት አገልጋዮቹም ደግነት የሚንጸባረቅበት መመሪያና ምክር ይሰጣል፤ እኛም ከእነዚህ በእጅጉ እንጠቀማለን። ለምሳሌ ያህል፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ሕይወቱን ቤዛዊ መሥዋዕት አድርጎ በመስጠት የኃጢአት ይቅርታ ማግኘት የምንችልበትን መሠረት ጥሏል። ፍጹም ባንሆንም እንኳ በዚህ መሥዋዕት አማካኝነት ከአምላክ ጋር የቅርብ ዝምድና መመሥረት እንችላለን። (ያዕ. 4:8፤ 1 ዮሐ. 2:1) ፈተናዎች በሚያጋጥሙን ጊዜ ደግሞ አምላክ በቅዱስ መንፈሱ እንዲያበረታንና እንዲያጠነክረን መጸለይ እንችላለን። በተጨማሪም ሙሉው መጽሐፍ ቅዱስ ያለን ሲሆን ይህን መጽሐፍ የምናነብና ባነበብነው ነገር ላይ የምናሰላስል ከሆነ የሚያጋጥሙንን የእምነት ፈተናዎች ለመቋቋም ከወዲሁ ዝግጁዎች እንሆናለን። የአምላክን ቃል ማጥናታችን ከአጽናፈ ዓለም ሉዓላዊነትና ከሰው ልጅ ንጹሕ አቋም ጋር በተያያዘ የተነሱትን አከራካሪ ጉዳዮች እንድንገነዘብ ይረዳናል።
16 ከዚህም በላይ ይሖዋ ‘በታማኝና ልባም ባሪያ’ አማካኝነት በመንፈሳዊ በሚመግበው ዓለም አቀፍ የወንድማማች ማኅበር ውስጥ በመታቀፋችን በእጅጉ እንጠቀማለን። (ማቴ. 24:45-47) ወደ 100,000 በሚጠጉት የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች ውስጥ በሚካሄዱት ስብሰባዎች ላይ በሕይወታችን ውስጥ ሊያጋጥሙን የሚችሉ የእምነት ፈተናዎችን ለመቋቋም የሚያስችል ትምህርትና ማበረታቻ ይሰጣል። በጀርመን የምትኖረውና በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ የምትገኘው የሺላ ተሞክሮ ለዚህ ጥሩ ማስረጃ ይሆናል።
17. በዛሬው ጊዜ የይሖዋ ድርጅት የሚሰጠውን መመሪያ በጥብቅ መከተል ያለውን ጥቅም የሚያሳይ ተሞክሮ ተናገር።
17 በአንድ ወቅት ሺላ በምትማርበት ክፍል ውስጥ አስተማሪ አልነበረም። በክፍሏ ውስጥ ያሉ ተማሪዎች ለመናፍስታዊ ድርጊት በሚያገለግል አንድ ሰሌዳ በመጠቀም ስለ ወደፊቱ ጊዜ ለማወቅ ፈለጉ። በዚህ ጊዜ ሺላ ወዲያውኑ ክፍሉን ለቃ ወጣች፤ በኋላ የሰማችው ነገር እንዲህ ማድረጓ ትክክል እንደነበር እንድትገነዘብ አድርጓታል። ተማሪዎቹ በሰሌዳው እየተጠቀሙ ሳሉ አንዳንዶቹ ተማሪዎች አጋንንት ስለታዩአቸው በጣም ደንግጠው እግሬ አውጪኝ አሉ። ሺላ ክፍሉን ወዲያውኑ ለቃ እንድትወጣ ያነሳሳት ምንድን ነው? እንዲህ ስትል ገልጻለች፦ “ይህ ከመሆኑ ከጥቂት ጊዜ በፊት በመንግሥት አዳራሽ ውስጥ ባደረግነው አንድ ስብሰባ ላይ ለመናፍስታዊ ድርጊት በሚያገለግለው በዚህ ሰሌዳ መጠቀም ስለሚያስከትለው ችግር ትምህርት ተሰጥቶ ነበር። በመሆኑም በዚህ ጊዜ ምን እርምጃ መውሰድ እንዳለብኝ አውቅ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ በምሳሌ 27:11 ላይ የሚሰጠውን ምክር በመከተል ይሖዋን ደስ ማሰኘት ፈልጌ ነበር።” ሺላ በስብሰባው ላይ በመገኘቷና ፕሮግራሙን በጥሞና በማዳመጧ በእጅጉ ተጠቅማለች!
18. አንተ በግለሰብ ደረጃ ምን ለማድረግ ቁርጥ ውሳኔ አድርገሃል?
18 ሁላችንም የአምላክ ድርጅት የሚሰጠንን መመሪያ በጥብቅ ለመከተል ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ። በስብሰባ ላይ አዘውትረን በመገኘት፣ መጽሐፍ ቅዱስን በማንበብ፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎችን በማጥናት፣ በመጸለይና ከጎለመሱ ክርስቲያኖች ጋር በመቀራረብ የሚያስፈልገንን መመሪያና ድጋፍ ማግኘት እንችላለን። ይሖዋ ንጹሕ አቋማችንን ይዘን እንድንኖር የሚፈልግ ሲሆን እስከ መጨረሻው በታማኝነት እንደምንጸና ይተማመናል። የይሖዋን ስም የማወደስ፣ ንጹሕ አቋማችንን ጠብቀን የመኖርና የይሖዋን ልብ ደስ የማሰኘት ታላቅ መብት አለን!
ታስታውሳለህ?
• ሰይጣን ለየትኞቹ ሁኔታዎችና ፈተናዎች ተጠያቂ ነው?
• ከምንም በላይ ውድ የሆነው ሀብታችን ምንድን ነው?
• ከይሖዋ ጋር ያለን ወዳጅነት በምን ላይ የተመሠረተ ነው?
• ይሖዋ በዛሬው ጊዜ እኛን ከሚረዳበት መንገድ መካከል አንዳንዶቹ የትኞቹ ናቸው?
[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ያገኘኸውን ውድ እውቀት ለሰዎች ለማካፈል አትነሳሳም?
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የእምነት አጋሮቻችን ንጹሕ አቋማቸውን ጠብቀው እንዲኖሩ መርዳት እንችላለን
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ቫለንቲና ንጹሕ አቋማቸውን ጠብቀው ለመኖር ሲሉ ማንኛውንም ነገር መሥዋዕት ለማድረግ ፈቃደኛ ሆነዋል