ከክፉ መናፍስት ጥቃት ራስህን ጠብቅ
ጄምስ ያደገው በሰለሞን ደሴቶች ውስጥ በምትካተተው በማሌይታ ደሴት ራቅ ብሎ በሚገኝ አካባቢ ነው። ከልጅነቱ ጀምሮ፣ መናፍስትን እንዲያከብር ትምህርት ይሰጠው ነበር። ጄምስ እንዲህ ብሏል፦ “መናፍስት በሰዎች ላይ ጉዳት እንዲያደርሱ መጠየቅ ፈጽሞ የማላስበው ነገር ነበር፤ ይሁንና ከክፉ ነገር ጥበቃ ለማግኘት በራራፎኖ [ከመናፍስት እርዳታ ለመጠየቅ የሚከናወን ድርጊት] ካልተካፈልኩ ደስተኛ ሕይወት መምራት እንደማልችል ይሰማኝ ነበር።”
በሌሎች በርካታ የዓለም ክፍሎች እንደሚኖሩ ሰዎች ሁሉ የሰለሞን ደሴት ነዋሪዎችም፣ መናፍስት ሰዎችን ሊጠቅሙ አሊያም ሊጎዱ እንደሚችሉ ያምናሉ። እንዲያውም በማሌይታ ደሴት የሚኖሩ በርካታ ሰዎች ጥሩ የሚባሉትን መናፍስት ከመፍራት ይልቅ ይወዷቸዋል።
ሰዎች መናፍስት በሚያደርጓቸው ነገሮች እንደሚያምኑ በተለያዩ መንገዶች ይታያል። ለምሳሌ ያህል፣ ጄምስ ልጅ እያለ እናቶች ኮሮኮሮ የተባለው ወፍ ሲጮህ ከሰሙ ልጆቻቸውን በፍጥነት ወደ ቤት ያስገቧቸዋል። እንዲህ የሚያደርጉት ለምንድን ነው? የወፉ ጩኸት አንድ ሰው ጉዳት ሊደርስበት እንደሆነ የሚጠቁም ነው ብለው ስለሚያምኑ ነው።
ጄምስ ባደገበት መንደር የሚኖሩ አንዳንድ ሰዎች ከበራቸው በላይ ለየት ያለ ነጭ ድንጋይ ያስቀምጣሉ። ጄምስም ይህ ድንጋይ ከክፉ መናፍስት እንደሚጠብቀው በማመን ተመሳሳይ ነገር ያደርግ ነበር። ከዚህም በላይ በሥራ ቦታው ምሳውን ከበላ በኋላ ትርፍራፊውን ልቅም አድርጎ ያስቀምጠውና በኋላ ላይ ይጥለዋል። ትርፍራፊውን የሚለቅመው አንድ ጠንቋይ በፍርፋሪው ላይ ድግምት በማድረግ እንዳያሳምመው ይፈራ ስለነበር ነው።
በምትኖርበት ቦታ ሰዎች እንዲህ ያሉ ልማዶችን የማይፈጽሙ ቢሆንም እንኳ አንተም እንደ ጄምስ ክፉ መናፍስት ከሚሰነዝሩት ጥቃት ጥበቃ ለማግኘት በአካባቢህ የሚዘወተሩ ልማዶችን መከተል እንደሚያስፈልግህ ይሰማህ ይሆናል። እንደነዚህ ያሉትን ልማዶች ካልተከተልክ ጉዳት ሊደርስብህ እንደሚችል ታስብ ይሆናል።
ለመጽሐፍ ቅዱስ አክብሮት ካለህ የአምላክ ቃል ከዚህ ቀጥሎ ለቀረቡት ጥያቄዎች ምን መልስ እንደሚሰጥ ለማወቅ መፈለግህ አይቀርም፦ (1) ክፉ መናፍስት ሊጎዱህ የሚችሉት እንዴት ነው? (2) በአካባቢህ የተለመዱ አንዳንድ ልማዶችን መከተልህ ለክፉ መናፍስት ጥቃት ሊያጋልጥህ ይችላል? (3) ከክፉ መናፍስት እውነተኛ ጥበቃ ማግኘትና ደስተኛ ሕይወት መምራት የምትችለው እንዴት ነው?
ክፉ መናፍስት በሰዎች ላይ ጉዳት የሚያደርሱት እንዴት ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ ክፉ መናፍስት የሞቱ ሰዎች መንፈስ ሊሆኑ እንደማይችሉ ይናገራል። የአምላክ ቃል “ሕያዋን እንደሚሞቱ ያውቃሉና፤ ሙታን ግን ምንም አያውቁም” ይላል። (መክብብ 9:5) ክፉ መናፍስት፣ ከሰይጣን ጋር ተባብረው ሰዎችን ለማሳት የሚጥሩ ዓመፀኛ መላእክት ናቸው።—ራእይ 12:9
ቅዱሳን መጻሕፍት፣ ከክፉ መናፍስት ጥቃት ጥበቃ እንደሚያስፈልገን በግልጽ ይናገራሉ። ሐዋርያው ጳውሎስ በኤፌሶን ለነበሩት ክርስቲያኖች ሲጽፍ እንዲህ ብሏል፦ “ትግል የምንገጥመው ከደምና ከሥጋ ጋር ሳይሆን . . . በሰማያዊ ስፍራዎች ካሉ ከክፉ መንፈሳዊ ኃይሎች ጋር ነው።” ሐዋርያው ጴጥሮስም፣ የክፉ መናፍስት ሁሉ ገዢ የሆነው ሰይጣን ዲያብሎስ “የሚውጠውን በመፈለግ እንደሚያገሳ አንበሳ” መሆኑን ገልጿል።—ኤፌሶን 6:12፤ 1 ጴጥሮስ 5:8
ሰይጣን በዋነኝነት ጥቃት የሚሰነዝረው ሰዎችን በማሳሳት ይኸውም አምላክን የሚያሳዝን ድርጊት እንዲፈጽሙ በማታለል አሊያም ፈተና በማቅረብ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ፣ ሰይጣን “የብርሃን መልአክ ለመምሰል ዘወትር ራሱን ይለዋውጣል” ይላል። (2 ቆሮንቶስ 11:14) ሰይጣን ክፉ ሆኖ ሳለ ሰዎችን ከመጥፎ ነገር የሚጠብቅ ጥሩ መንፈስ መስሎ ለመቅረብ ይሞክራል። ሰዎች ስለ እሱም ሆነ ስለ አምላክ እውነቱን እንዳያውቁ አእምሯቸውን አሳውሮታል። (2 ቆሮንቶስ 4:4) ሰይጣን ሰዎችን የሚያሳስትበት ዓላማ ምንድን ነው?
ሰይጣን የመመለክ ከፍተኛ ፍላጎት አለው፤ ሰዎች አውቀውም ይሁን ሳያውቁ እንዲያመልኩት ይፈልጋል። ሰይጣን፣ የአምላክ ልጅ የሆነው ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ወቅት ‘አንድ ጊዜ ተደፍቶ እንዲያመልከው’ ፈልጎ ነበር። ኢየሱስ ግን “አንተ ሰይጣን፣ ከፊቴ ራቅ! ‘ይሖዋ አምላክህን ብቻ አምልክ . . .’ ተብሎ ተጽፏል” አለው። (ማቴዎስ 4:9, 10) ኢየሱስ ለሰይጣን አምልኮ እንዳቀረበ የሚያስመስል አንድም ነገር ለማድረግ ፈቃደኛ አልነበረም።
ይሖዋ ከማንኛውም መንፈሳዊ አካል የበለጠ ኃያል ነው፤ በመሆኑም እሱን የሚታዘዙት ሰዎች ምንም ዓይነት ዘላቂ ጉዳት እንዲደርስባቸው አይፈቅድም። (መዝሙር 83:18፤ ሮም 16:20) ይሁን እንጂ ኢየሱስ እንዳደረገው እኛም ይሖዋ አምላክን ለማስደሰት ከፈለግን ለሰይጣንም ሆነ ለአጋንንቱ እንድንገዛ የሚያደርገንን ማንኛውንም ድርጊት ከመፈጸም መቆጠብ ይኖርብናል። ይህንንም ለማድረግ ለክፉ መናፍስት አምልኮ አከል ክብር እንድንሰጥ የሚያደርጉ ልማዶችን ለይተን ማወቅ ያስፈልገናል። እነዚህን ልማዶች ማወቅ የምትችለው እንዴት ነው?
አምላክን የማያስደስቱ ልማዶችን ለይተህ እወቅ
ይሖዋ አምላክ፣ በጥንት ጊዜ ሕዝቦቹ የነበሩት እስራኤላውያን በአቅራቢያቸው ያሉት ብሔራት የሚከተሏቸውን አንዳንድ ልማዶች እንዳይኮርጁ አስጠንቅቋቸው ነበር። እንዲህ ብሏቸዋል፦ “ሟርተኛ፣ ወይም መተተኛ፣ ሞራ ገላጭ፣ ጠንቋይ ወይም በድግምት የሚጠነቍል . . . በመካከልህ ከቶ አይገኝ።” መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው “እነዚህን የሚያደርግ ሁሉ በእግዚአብሔር ዘንድ አስጸያፊ ነው።”—ዘዳግም 18:10-12
እንግዲያው አንተ በምትኖርበት አካባቢ ሰዎች በአብዛኛው ከሚከተሏቸው ልማዶች ጋር በተያያዘ ቀጥሎ የቀረቡትን ጥያቄዎች አስብባቸው፦ እነዚህ ልማዶች በገድ ማመንን ያበረታታሉ? ግዑዝ የሆኑ ነገሮች አስማታዊ ኃይል አላቸው እንዲሁም ከክፉ ነገር ይጠብቃሉ የሚል እምነት ያንጸባርቃሉ? በአካባቢህ የሚፈጸሙት ልማዶች መተት ማድረግን ወይም ድግምትን ለመከላከል የሚከናወኑ ነገሮችን ይጨምራሉ? አሊያም ደግሞ ለይሖዋ ወይም እሱ ለሾመው ለኢየሱስ ሳይሆን ለሌላ መንፈሳዊ አካል መገዛትን የሚያሳይ ድርጊት መፈጸምን ያካትታሉ?—ሮም 14:11, 12፤ ፊልጵስዩስ 2:9-11
እንዲህ ያሉትን ድርጊቶች ከሚያበረታታ ከማንኛውም ዓይነት ልማድ መራቅህ በጣም አስፈላጊ ነው። ለምን? ሐዋርያው ጳውሎስ፣ “‘ከይሖዋ ማዕድ’ እና ከአጋንንት ማዕድ መካፈል አትችሉም” በማለት በመንፈስ ተመርቶ ጽፏል። ጳውሎስ፣ አምላክንም ሆነ ሌሎች መንፈሳዊ አካላትን ለማስደሰት የሚጥሩ ሰዎች ‘ይሖዋን እያስቀኑት’ እንደሆነ ተናግሯል። (1 ቆሮንቶስ 10:20-22) ይሖዋ አምላክ እሱን ብቻ እንድናመልከው የሚፈልግ ሲሆን እንዲህ ዓይነት አምልኮ ሊሰጠውም ይገባል።—ዘፀአት 20:4, 5
የሚከተለውን ጥያቄም አስብበት፦ በአካባቢህ ያሉት ልማዶች አንድ ሰው ለሚፈጽመው ድርጊት ተጠያቂ እንዳልሆነ የሚገልጸውን አመለካከት ይደግፋሉ? ለምሳሌ ያህል፣ ምንዝርና ከጋብቻ በፊት የሚፈጸም የጾታ ግንኙነት በብዙ ማኅበረሰቦች ዘንድ የተጠላ ድርጊት ሲሆን መጽሐፍ ቅዱስም እንዲህ ያለውን ድርጊት ያወግዛል። (1 ቆሮንቶስ 6:9, 10) ይሁን እንጂ በፓስፊክ ውቅያኖስ ላይ በሚገኙ አንዳንድ ደሴቶች ላይ አንዲት ልጃገረድ የጾታ ብልግና እንድትፈጽም የገፋፋት ‘በቅጠል የተደረገባት መተት’a እንደሆነ ከተናገረች ምንዝር በመፈጸሟ ላትወገዝ ትችላለች።
ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ ለምናደርጋቸው ነገሮች ተጠያቂ እንደሆንን ያስተምራል። (ሮም 14:12፤ ገላትያ 6:7) ለአብነት ያህል፣ የመጀመሪያዋ ሴት ሔዋን አምላክን ያልታዘዘችው ሰይጣን ስላሳሳታት እንደሆነ ስትገልጽ “እባብ አሳሳተኝና በላሁ” ብላ ነበር። ይሖዋ ግን ከተጠያቂነት ነፃ አላደረጋትም። (ዘፍጥረት 3:13, 16, 19) እኛም ለምናደርጋቸው ነገሮች በፊቱ ተጠያቂዎች ነን።—ዕብራውያን 4:13
ምን ማድረግ ይኖርብሃል?
አምላክን ማስደሰትና የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያዎች እየተከተልክ መኖር ከፈለግህ ጠንከር ያለ እርምጃ መውሰድ ይኖርብሃል። በመጀመሪያው መቶ ዘመን በኤፌሶን ይኖሩ የነበሩ ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች በዚህ ረገድ ጥሩ አርዓያ ይሆናሉ። እነዚህ ሰዎች ክፉ መናፍስት ከሚያሳድሩት ተጽዕኖ ለመላቀቅ ሲሉ ከመናፍስታዊ ድርጊቶች ጋር ንክኪ ያላቸውን መጻሕፍቶቻቸውን በሙሉ ሰብስበው “በሁሉ ሰው ፊት አቃጠሉ።”—የሐዋርያት ሥራ 19:19
እነዚህ ሰዎች መጻሕፍቶቻቸውን ከማቃጠላቸው በፊት “ያደረጉትን ይናዘዙና በግልጽ ይናገሩ ነበር።” (የሐዋርያት ሥራ 19:18) ሰዎቹ፣ ጳውሎስ ስለ ክርስቶስ ያስተማራቸው ነገር ልባቸውን ስለነካው ከመናፍስታዊ ድርጊቶች ጋር ንክኪ ያላቸውን መጻሕፍቶቻቸውን አስወገዱ፤ ከዚህም በላይ ለመናፍስታዊ ልማዶች ያላቸውን አመለካከት አስተካከሉ።
እንዲህ ባሉ ልማዶች ከመካፈል መራቅ ቀላል እንዳልሆነ ግልጽ ነው። ቀደም ሲል የተጠቀሰው ጄምስ ይህን ማድረግ ፈተና ሆኖበት ነበር። ጄምስ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ሲያጠና የተማረው ነገር አስደስቶት ነበር። ይሁንና ራራፎኖ በሚባለው ድርጊት መካፈሉን ቀጥሎ ነበር። ጄምስ ስለ እነዚህ ልማዶች ቆም ብሎ ሲያስብ፣ ይሖዋ ስለወደፊቱ ጊዜ በሰጠው ተስፋ ቢያምንም በአሁኑ ጊዜ ከክፉ ነገር ጥበቃ ለማግኘት በእነዚህ ልማዶች መካፈል እንዳለበት እንደሚሰማው አስተዋለ።
ታዲያ ጄምስ አመለካከቱን ለማስተካከል የረዳው ምንድን ነው? እንዲህ ብሏል፦ “ይሖዋ ጥበቃ እንዲያደርግልኝና በእሱ እንድታመን እንዲረዳኝ ጸለይኩ። እንዲሁም ከመናፍስታዊ ድርጊት ጋር በተያያዙ ልማዶች መካፈሌን እርግፍ አድርጌ ተውኩ።” እንዲህ በማድረጉ ክፉ ነገር ገጥሞት ይሆን? ጄምስ “በፍጹም አልገጠመኝም” በማለት ከተናገረ በኋላ አክሎ እንዲህ ብሏል፦ “እንዲያውም በይሖዋ መታመንን ተምሬያለሁ። ይሖዋ የቅርብ ወዳጅ ሊሆንልን እንደሚችል ተመልክቻለሁ።” ላለፉት ሰባት ዓመታት ጄምስ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርት እንዲያውቁ በመርዳት በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ሲካፈል ቆይቷል።
አንተስ ለምን የጄምስን ምሳሌ አትከተልም? ‘በማሰብ ችሎታህ’ በመጠቀም፣ በምትኖርበት ማኅበረሰብ ውስጥ ያሉት ልማዶች ‘ከአምላክ ፈቃድ’ ጋር ይስማሙ እንደሆነና እንዳልሆነ መርምር። (ሮም 12:1, 2) መናፍስታዊ ድርጊቶችን ከመፈጸም ለመራቅ ድፍረት ይኑርህ። ይህንን ካደረግህ ይሖዋ ‘እንደሚቀበልህ’ እንዲሁም ጥበቃ እንደሚያደርግልህ እርግጠኛ መሆን ትችላለህ። (2 ቆሮንቶስ 6:16-18) “የእግዚአብሔር [“የይሖዋ፣” NW] ስም ጽኑ ግንብ ነው፤ ጻድቅ ወደ እርሱ በመሮጥ ተገን ያገኝበታል” የሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳብ እውነተኛ መሆኑን አንተም እንደ ጄምስ በሕይወትህ ውስጥ መመልከት ትችላለህ።—ምሳሌ 18:10
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ይህ አገላለጽ በአንድ ለየት ያለ ቅጠል ወይም ምግብ ላይ ድግምት የማድረግን ልማድ ያመለክታል። ከዚያም ድግምት የተደረገበት ነገር ለልጅቷ ይሰጣታል። ቅጠሉ ወይም ምግቡ ልጅቷ በአንድ ወንድ እንድትማረክ ያደርጋታል ተብሎ ይታመናል። ይህ ልማድ ለአንዲት ልጃገረድ ሳታውቅ የሚያደነዝዝ መድኃኒት በመስጠት አስገድዶ ከመድፈር የተለየ ነው። እንዲህ ዓይነት ድርጊት የተፈጸመባት ሴት በፈቃዷ በድርጊቱ እንደተካፈለች ሊገለጽ አይችልም።
[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
“ኮሮኮሮ”
[የሥዕል ምንጭ]
Courtesy of Dr. Bakshi Jehangir
[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አንዲት ልጅ መሬት ላይ የወደቀውን ምግብ ድግምት እንዳይደረግበት ስትለቅም