አንባቢያን የሚያነሱት ጥያቄ
የሁሉም ተአምራዊ ፈውስ ምንጭ አምላክ ነው?
ይሖዋ አምላክ የመፈወስ ኃይል እንዳለው ምንም ጥርጥር የለውም። ይህንን ኃይሉን ለአምላኪዎቹ መስጠት እንደሚችልም የታወቀ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ በሐዋርያት ዘመን ለክርስቲያኖች ከተሰጡት ለየት ያሉ የአምላክ መንፈስ ስጦታዎች አንዱ ተአምራዊ ፈውስ የመፈጸም ችሎታ ነበር። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “መንፈስ በእያንዳንዱ ሰው አማካኝነት ጠቃሚ ለሆነ ዓላማ ይገለጣል። ለምሳሌ ያህል፣ ለአንዱ በመንፈስ አማካኝነት በጥበብ የመናገር ችሎታ ይሰጠዋል፤ . . . ለሌላው ደግሞ በዚያው መንፈስ የመፈወስ ስጦታ ይሰጠዋል፤ . . . ለሌላው ትንቢት የመናገር፣ . . . ለሌላው በተለያዩ ልሳኖች የመናገር፣ . . . ችሎታ ይሰጠዋል።”—1 ቆሮንቶስ 12:4-11
ይሁን እንጂ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በጻፈው በዚያው ደብዳቤ ላይ ከአምላክ ቅዱስ መንፈስ ስጦታዎች መካከል አንዳንዶቹ የሚቀሩበት ጊዜ እንደሚመጣም ገልጿል። እንዲህ ብሏል፦ “የመተንበይ ስጦታም ቢሆን ይቀራል፤ በልሳን መናገርም ቢሆን ያበቃል፣ እውቀትም ቢሆን ይቀራል።”—1 ቆሮንቶስ 13:8
በመጀመሪያው መቶ ዘመን ኢየሱስ ክርስቶስም ሆነ ሐዋርያቱ ተአምራዊ ፈውስ ፈጽመው ነበር። የክርስቲያን ጉባኤ አዲስ በነበረበት በዚያ ወቅት የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች (የመፈወስ ችሎታንም ይጨምራል) ለሐዋርያት የተሰጧቸው፣ ለአምላክ ክብር ለማምጣት እንዲሁም ይሖዋ አዲስ የተቋቋመውን የክርስቲያን ጉባኤ እንደተቀበለው ብሎም እንደባረከው ለማሳየት ነበር። የክርስቲያን ጉባኤ ከጎለመሰ ወይም ከተጠናከረ በኋላ ግን ጉባኤው በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት እንዳገኘ ማረጋገጫ ሆኖ የሚያገለግለው አባላቱ የሚያገኙት ልዩ የሆነ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ ሳይሆን የሚያሳዩት የማይናወጥ እምነት፣ ተስፋና ፍቅር ነበር። (ዮሐንስ 13:35፤ 1 ቆሮንቶስ 13:13) በዚህም ምክንያት ከ100 ዓ.ም. ገደማ ጀምሮ ተአምራዊ ፈውሶች ጉባኤው በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘቱ ማረጋገጫ ሆነው ማገልገላቸው ቀርቷል።a
‘ታዲያ ተአምራዊ ፈውስ እንደተፈጸመ ስለሚገልጹ ዘገባዎች በዛሬው ጊዜም የምሰማው ለምንድን ነው?’ ብለህ ትጠይቅ ይሆናል። ለምሳሌ ያህል፣ ካንሰር ይዞት እንደነበር ስለሚናገር ሰው የሚገልጽ ዘገባ በአንድ ጋዜጣ ላይ ወጥቶ ነበር። ይህ ሰው በጭንቅላቱና በኩላሊቶቹ ሌላው ቀርቶ በአጥንቶቹ ውስጥ ጭምር ዕጢ እንደተገኘበት ተናግሯል። አምላክ “እስካነጋገረው” ዕለት ድረስ የመኖር ተስፋው የመነመነ ነበር። ይህ ከሆነ ከጥቂት ቀናት በኋላ ካንሰሩ ከሰውነቱ ውስጥ እንደጠፋ ዘገባው ገልጿል።
እንዲህ ዓይነት ታሪክ ስትሰማ እንደሚከተለው እያልክ ራስህን ብትጠይቅ ጥሩ ይሆናል፦ ‘ይህ ዘገባ በእውነታ ላይ የተመሠረተ ነው? በሕክምና ማስረጃስ የተደገፈ ነው? በእርግጥ ፈውስ የተፈጸመ ቢመስልም እንኳ ተአምራዊ ፈውስ የሚመስሉ ክስተቶች ሁሉ ምንጭ አምላክ እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምራል?’
በተለይ ለመጨረሻው ጥያቄ ለምናገኘው መልስ ትኩረት ልንሰጠው ይገባል። ኢየሱስ ተከታዮቹን እንደሚከተለው በማለት አስጠንቅቋቸዋል፦ “ወደ እናንተ ከሚመጡ ሐሰተኛ ነቢያት ተጠንቀቁ። . . . በዚያ ቀን ብዙዎች ‘ጌታ ሆይ፣ ጌታ ሆይ፣ በስምህ ትንቢት አልተናገርንም? በስምህ አጋንንትን አላወጣንም? በስምህስ ብዙ ተአምራት አላደረግንም?’ ይሉኛል። እኔም በዚያ ጊዜ ‘ቀድሞውንም አላውቃችሁም! እናንተ ዓመፀኞች፣ ከእኔ ራቁ’ እላቸዋለሁ።”—ማቴዎስ 7:15, 21-23
ከዚህ ለመረዳት እንደምንችለው በተአምር ተፈጽመዋል የሚባሉ ፈውሶች ምንጭ አምላክ ብቻ አይደለም። በአምላክ ስም ተአምር እንደሚፈጽሙ የሚናገሩ ሰዎች እንዳያታልሉን ስለ አምላክ ትክክለኛ እውቀት ማግኘት፣ አምላክ የሰጠንን የማሰብ ችሎታ መጠቀም እንዲሁም የእሱን ፈቃድ የሚያደርጉ ሰዎችን እንዴት መለየት እንደምንችል ትምህርት መቅሰም ያስፈልገናል።—ማቴዎስ 7:16-19፤ ዮሐንስ 17:3፤ ሮም 12:1, 2
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ሐዋርያት ሲሞቱ ተአምራዊ ስጦታዎችን ለሌሎች የማስተላለፍ ችሎታም ያበቃ ይመስላል። ተአምራዊ ስጦታ የተሰጣቸው ሰዎች በሙሉ ሲሞቱ ደግሞ ተአምራዊ የሆኑት የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች ሙሉ በሙሉ ቀርተዋል።