አሳዛኝ ሁኔታዎች ቢደርሱብኝም አመስጋኝ ነኝ—መጽሐፍ ቅዱስ እንድቋቋመው ረድቶኛል
ኤንሪኬ ካራባካ አኮስታእንደ ተናገረው
ዕለቱ ሚያዝያ 15 ቀን 1971 ሲሆን በግብርና ሥራ የሚተዳደሩትን ቤተሰቦቼን ለመጠየቅ እየሄድኩ ነበር። ለተወሰነ ጊዜ ከቤተሰቦቼ ርቄ ስለቆየሁ ሁሉንም እስካያቸው በጣም ቸኩያለሁ። ‘ሁሉም ቤት ይኖሩ ይሆን? መጀመሪያ የማገኘውስ ማንን ይሆን?’ እያልኩ አሰብኩ። ቤት እንደደረስኩ የገጠመኝ ሁኔታ ግን ዘግናኝ ነበር፤ እናቴን ጨምሮ አራት ሰዎች መገደላቸውን ስመለከት ክው ብዬ ቀረሁ!
ምን ያህል እንደደነገጥኩ በቃላት መግለጽ አልችልም። ምንድን ነው ጉዱ? ምን ባደርግ ይሻለኛል? ቤት ውስጥ ማንም ሰው ስላልነበር የምይዘው የምጨብጠው ጠፋኝ። በዚያን ዕለት ያጋጠመኝን ሁኔታ መተረኬን እዚህ ላይ ላቋርጥና ስለ ራሴ በመጠኑ ልንገራችሁ። ይህን ማወቃችሁ፣ በዚህ ጊዜም ሆነ ከዚያ በኋላ በሕይወቴ የደረሱብኝ አሳዛኝ ሁኔታዎች ምን እንዲሰማኝ እንዳደረጉ የበለጠ ለመረዳት ያስችላችኋል።
እውነትን አገኘን
የተወለድኩት በኮስታ ሪካ፣ ኒኮያ ከተማ አቅራቢያ በሚገኘው በኪሪማን ነው። በ1953 ከወላጆቼ ጋር በቤተሰባችን እርሻ ቦታ እኖር ነበር፤ በዚህ ወቅት 37 ዓመቴ ነበር። የካቶሊክ እምነት ተከታዮች ብንሆንም የማንስማማባቸው አንዳንድ ትምህርቶች የነበሩ ከመሆኑም ሌላ መልስ ያላገኘንላቸው በርካታ ጥያቄዎች ነበሩን።
አንድ ቀን ማለዳ ላይ አናቶልዮ አልፋሮ የተባለ ሰው ቤታችን መጥቶ መጽሐፍ ቅዱስን እንድናጠና አበረታታን። ጥቅሶችን እየጠቀሰ ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ብዙ ነገሮችን አወያየን። እኔ፣ አባቴ፣ እናቴ፣ አንድ ወንድሜ፣ እህቴና አብራን ትኖር የነበረች ጓደኛዋ ቁጭ ብለን አዳመጥነው። ብዙ ጥያቄዎች ስለነበሩን ጠዋት ላይ የጀመርነው ውይይት እስከ ሌሊት ድረስ ዘለቀ።
አናቶልዮ ያን ቀን ከእኛ ጋር ያደረ ሲሆን የሚቀጥለውንም ቀን አብሮን አሳለፈ። የሰማነው ነገር በጣም አስደሰተን፤ ይበልጥ እንድንደሰት ያደረገን ግን ለጥያቄዎቻችን በቀጥታ ከመጽሐፍ ቅዱስ መልስ ማግኘታችን ነበር። በዚያን ቀን ያደረግነው ውይይት ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድሮብናል። ስለተማርነው ነገር በደንብ ካሰብንበት በኋላ እውነትን እንዳገኘን እርግጠኛ ሆንን። አናቶልዮ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ አንዳንድ መጽሔቶችንና መጽሐፎችን ትቶልን ሄደ። ማታ ማታ በቤተሰብ አንድ ላይ ሆነን እነዚህን ጽሑፎች እናነባቸውና እናጠናቸው ነበር። ቤታችን መብራት ስላልነበረው ይህን ማድረግ ቀላል አልነበረም። ማጥናት ከመጀመራችን በፊት ትንኞች እንዳይነክሱን ሁላችንም በትላልቅ የድንች ጆንያዎች እግሮቻችንን እንሸፍን ነበር።
ከስድስት ወራት በኋላ እኔንና ወላጆቼን ጨምሮ አምስት የቤተሰባችን አባላት ተጠመቅን። ከቤት ወደ ቤት በመሄድ የተማርነውን ነገር በታላቅ ጉጉት ለሌሎች ማካፈል ጀመርን። ካሪዮ በተባለችው ከተማ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ለመሰብሰብ ሁለት ሰዓት ገደማ የሚፈጅ የእግር መንገድ እንሄድ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ በፈረስ እንጓዝ ነበር። አናቶልዮም ቤታችን እየመጣ እኛን መጽሐፍ ቅዱስን ማስጠናቱን አላቆመም። ከዚያም እኛ ቤት ስብሰባ ለማድረግ ዝግጅት የተደረገ ሲሆን በስብሰባው ላይ ስምንት የሚሆኑ ሰዎች ይገኙ ነበር። ከጊዜ በኋላ ስምንቱም ተጠመቁ። ብዙም ሳይቆይ ይህ ቡድን 20 አባላት ያሉት አነስተኛ ጉባኤ ሆነ።
የአምላክን ሥራ ለመሥራት ሙሉ ጊዜዬን ሰጠሁ
ከጊዜ በኋላ በኮስታ ሪካ የሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ፣ ሙሉ ጊዜያቸውን በወንጌላዊነቱ ሥራ ማሳለፍ የሚችሉ ሁሉ በዚህ መስክ እንዲሰማሩ ግብዣ አቀረበ። እኔም በ1957 ይህን ግብዣ ተቀብዬ የሙሉ ጊዜ አገልግሎትን ጀመርኩ። ሥራው እጅግ አስደሳች ነበር። በገጠራማ አካባቢ ለሚኖሩ ሰዎች ምሥራቹን ለመስበክ በአብዛኛው ብቻዬን ለሰዓታት እጓዝ ነበር። አንዳንድ ጊዜ ሰዎች ወደ መንደራቸው መሄዴ አያስደስታቸውም። ቢያንስ ሦስት ጊዜ ቆንጨራ የያዙ ሰዎች ማንነቴንና ምን እየሠራሁ እንዳለሁ በመጠየቅ ሊያስፈራሩኝ ሞክረዋል።
በ1950ዎቹ ዓመታት ወደተለያዩ ቦታዎች የሚያደርሱ በደንብ የወጡ መንገዶች ስላልነበሩ ምሥራቹን ለሰዎች ማድረስ ቀላል አልነበረም። አንዳንድ ቦታዎች ለመድረስ በፈረስ መጓዝ ነበረብን። ወንዞችን በእግራችን እናቋርጥ የነበረ ከመሆኑም ሌላ ሜዳ ላይ ያደርንባቸው ጊዜያትም ነበሩ። እንዲሁም በአካባቢው ትንኞች በብዛት ስለሚገኙ እንቸገር ነበር። ከዚህም ሌላ እባቦችና አዞዎች ስለነበሩ እንዳይጎዱን ነቅተን መጠበቅ ነበረብን። ይህ ሁሉ አስቸጋሪ ሁኔታ ቢኖርም ሰዎች ስለ ይሖዋ አምላክ እንዲያውቁ መርዳት በጣም ያስደስተኝ ነበር። አገልግሎቴን ጨርሼ ቤቴ ስመለስ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነቶች ለሰዎች ማካፈል በመቻሌ የደስታና የእርካታ ስሜት ይሰማኝ ነበር። በየዕለቱ መስበኬና መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናቴ ለይሖዋ አምላክ ያለኝ ፍቅር እያደገ እንዲሄድና ወደ እሱ ይበልጥ እንደቀረብኩ እንዲሰማኝ አድርጎኛል።
ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ተጨማሪ ኃላፊነቶች ተሰጡኝ። ከአሥር ለሚበልጡ ዓመታት ተጓዥ የበላይ ተመልካች ሆኜ ያገለገልኩ ሲሆን በዚህ ወቅት በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ መንፈሳዊ ወንድሞችን ለማበረታታት በየሳምንቱ አንድ ጉባኤ እጎበኝ ነበር። የጤንነቴ ሁኔታ በዚህ የአገልግሎት ዘርፍ እንድቀጥል ባይፈቅድልኝም በአምላክ አገልግሎት ሙሉ ጊዜዬን በማሳለፍ በስብከቱ ሥራ ደስታ ማግኘት ችያለሁ።
አሳዛኝ ሁኔታዎች አጋጠሙኝ
በ1971 በኒኮያ በነበርኩበት ጊዜ ቤተሰቦቼን ለመጠየቅ ሄድኩ። ቤት ስገባ 80 ዓመት የሆናት እናቴ ወለሉ ላይ ተዘርራ አገኘኋት። በጥይት ተመትታለች እንዲሁም በስለት ተወግታለች። ቀና ላደርጋት ጎንበስ ስል እስትንፋሷ እንዳለ አስተዋልኩ። ይሁንና ብዙም ሳይቆይ በእጄ ላይ እንዳለች ሕይወቷ አለፈ። ዞር ዞር ብዬ ስመለከት ደግሞ የስምንት ወር ነፍሰ ጡር የነበረችው የቤት ሠራተኛ ወጥ ቤቱ ወለል ላይ ተዘርራ አየኋት፤ እሷም ሞታለች። ይህ አልበቃ ብሎ የቤተሰቦቼ ጉባኤ አባል የሆነችን አንዲት ሴት ኮሪደሩ ላይ ሞታ አየኋት፤ የቤት ሠራተኛዋን ወንድ ልጅ ደግሞ መታጠቢያ ቤት ውስጥ ሞቶ አገኘሁት። ሁሉም በአሰቃቂ ሁኔታ በስለት ተወግተዋል እንዲሁም በጥይት ተመትተዋል። እንዲህ ያለውን ዘግናኝ ወንጀል ሊፈጽም የሚችለው ማን ነው? ለምንስ?
ወደ ውጭ ስወጣ ደግሞ አባቴን አገኘሁት። ጭንቅላቱ ላይ በጥይት የተመታ ቢሆንም አልሞተም ነበር! ከቤታችን የ15 ደቂቃ የእግር መንገድ ርቆ ወደሚገኘው የወንድሜ ቤት እየሮጥኩ ሄድኩ፤ እዚያ ስደርስም አንዲት ሴትና ወንድ ልጇ መገደላቸውን ሰማሁ። ገዳዩ 17 ዓመት የሆነው የእህቴ ልጅ መሆኑን ሳውቅ ምን ያህል እንደደነገጥኩ ልነግራችሁ አልችልም! ይህ ልጅ የአእምሮ ሕመምተኛ ሲሆን የይሖዋ ምሥክርም አልነበረም። አካባቢውን ጥሎ ስለጠፋም እሱን ለማግኘት በኮስታ ሪካ ታሪክ ታይቶም ሆነ ተሰምቶ የማይታወቅ ከፍተኛ አሰሳ ተካሄደ።
የተፈጸመው ወንጀል በመላው አገሪቱ በዜና ተሰራጨ። ከሰባት ቀናት አሰሳ በኋላ ፖሊሶች ገዳዩን ያገኙት ሲሆን ትልቅ ቢላዋና ከአንድ ሰው የገዛውን ሽጉጥ ይዞ ነበር፤ ሰውየው ሽጉጡን የሸጠለት የአእምሮ ሕመምተኛ መሆኑን እያወቀ ነበር። ፖሊሶች የእህቴን ልጅ በቁጥጥር ሥር ሊያውሉት በሚሞክሩበት ጊዜ በጥይት ተመትቶ ሞተ።
ፖሊሶች ገዳዩን እያፈላለጉ በነበሩበት ወቅት ብዙዎች የእህቴ ልጅ ተመልሶ በመምጣት እኔንም እንዳይገድለኝ ስለሰጉ አካባቢውን ለቅቄ እንድሄድ አበረታተውኝ ነበር። ይሁንና በሕይወት ከተረፉት የቤተሰቤ አባላትና ከጉባኤው ጋር መሆን እንዳለብኝ ስለተሰማኝ በጉዳዩ ላይ ከጸለይኩ በኋላ እዚያው ለመቆየት ወሰንኩ።
መከራ ተደራረበብኝ
የሚያሳዝነው ነገር አባቴ ከአንድ ዓመት በኋላ ሞተ። በቀጣዩ ዓመት ደግሞ ታማኝ የይሖዋ አምላክ አገልጋይ የነበረችው እህቴ ከዚህ ጋር ምንም ግንኙነት በሌለው በሌላ አጋጣሚ ተገደለች። በዚህ ጊዜም ዘመዶቼ በሙሉ ሌላ የቤተሰብ አባል በሞት በማጣታቸው በጣም አዘኑ። በወቅቱ እኛም ሆንን ጓደኞቻችን የተሰማንን የሐዘን ስሜት በቃላት መግለጽ ይከብደኛል። በእነዚህ የመከራ ጊዜያት ሁሉ በይሖዋ ላይ በእጅጉ የታመንኩ ሲሆን ጥንካሬ እንዲሰጠኝም አዘውትሬ እማጸነው ነበር።
በ1985 በኮስታ ሪካ ዋና ከተማ በሳን ሆሴ፣ ለክርስቲያን ሽማግሌዎች የተሰጠውን የሦስት ቀናት ሥልጠና ወሰድኩ። ሥልጠናው ካበቃ በኋላ በመንፈሳዊ እንደተበረታታሁ ሆኖ ተሰማኝ። ሰኞ ዕለት ማለዳ ላይ ወደ ቤት ለመሄድ ተነሳሁ። ወደ አውቶቡስ መናኸሪያው እየተጓዝኩ ሳለም ወሮበሎች ጉሮሮዬን አንቀው ዘረፉኝ። ሁሉም ነገር በፍጥነት ስለተፈጸመ ፊታቸውን ማየት አልቻልኩም። በዚህ አጋጣሚ የደረሰብኝ ጉዳት በተለመደው የኮስታ ሪካ ባሕል መሠረት ሰላምታ መለዋወጥ አስቸጋሪ እንዲሆንብኝ አድርጓል። በዚህ የግዋናካስቴ ክልል ወንዶች ሲገናኙ ሰላምታ የሚለዋወጡት ወይም መምጣታቸውን የሚያሳውቁት ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ነው። ይህ ወንጀል እስከተፈጸመብኝ ጊዜ ድረስ እኔም ጥሩ አድርጌ መጮኽ እችል ነበር፤ ከዚያ በኋላ ግን እንደዚህ ማድረግ አልቻልኩም።
በ1979 በጎረቤት ጉባኤ የምታገለግል ሲልየ የተባለች የይሖዋ ምሥክር አገባሁ። ሲልየ ለመጽሐፍ ቅዱስ ፍቅር ነበራት። መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ አብረን እናነብና እናጠና ነበር። የሚያሳዝነው ግን ሲልየ በካንሰር ምክንያት ሐምሌ 2001 በሞት ተለየችኝ። አልፎ አልፎ የብቸኝነት ስሜት የሚሰማኝ ቢሆንም የትንሣኤ ተስፋ የብርታት ምንጭ ሆኖልኛል።—ዮሐንስ 5:28, 29
ፈተናዎች ቢኖሩም ደስተኛ ነኝ
ብዙ ሰዎች ከደረሰባቸው የበለጠ በርካታ አሳዛኝ ሁኔታዎችን በሕይወቴ ያስተናገድኩ ቢሆንም፣ እነዚህ ፈተናዎች በይሖዋ ላይ ያለኝን እምነትና ለእሱ ታማኝ መሆኔን ለማሳየት የሚያስችሉኝ አጋጣሚዎች እንደሆኑ አድርጌ እመለከታቸዋለሁ። (ያዕቆብ 1:13) የደረሱብኝን መከራዎች በተመለከተ ሚዛናዊ አመለካከት እንዲኖረኝ፣ ሁላችንም “መጥፎ ጊዜና ያልተጠበቁ ክስተቶች” ሊያጋጥሙን እንደሚችሉ ሁልጊዜ ለማሰብ እሞክራለሁ። (መክብብ 9:11 NW) ከዚህም በተጨማሪ የምንኖረው “ለመቋቋም የሚያስቸግር በዓይነቱ ልዩ የሆነ ዘመን” ውስጥ በመሆኑ ሰዎች ጨካኞች፣ ዓመጸኞችና ራሳቸውን የማይገዙ እንደሆኑ ለማስታወስ እጥራለሁ። (2 ጢሞቴዎስ 3:1-5) የኢዮብን ምሳሌም ቢሆን ከአእምሮዬ አላወጣውም። ኢዮብ ብዙ መከራ ቢደርስበትም ይኸውም ቤተሰቡን፣ ጤናውንና መተዳደሪያውን ቢያጣም ‘የይሖዋ ስም ቡሩክ ይሁን’ በማለት መጽናቱን አሳይቷል። ይሖዋም ኢዮብ ላሳየው ንጹሕ አቋም አትረፍርፎ ባርኮታል። (ኢዮብ 1:13-22፤ 42:12-15) ከመጽሐፍ ቅዱስ ያገኘኋቸው እነዚህን የመሳሰሉ ሐሳቦች በርካታ ፈተናዎች ቢደርሱብኝም ደስተኛ ሆኜ እንድቀጥል ረድተውኛል።
ይሖዋ በሕይወቴ ውስጥ ለእሱ የመጀመሪያውን ቦታ መስጠት እንድችል ረድቶኛል። መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ ማንበቤ የመጽናናት ምንጭ የሆነልኝ ሲሆን ችግሮችን ለመቋቋም የሚያስችለኝን ጥንካሬም ሰጥቶኛል። ወደ ይሖዋ በመጸለይ ‘ከማሰብ ችሎታ ሁሉ በላይ የሆነውን የአምላክ ሰላም’ ማግኘት ችያለሁ። (ፊልጵስዩስ 4:6, 7) ይህ ደግሞ አእምሮዬ እንዲረጋጋ አድርጎልኛል። በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መገኘቴና ተሳትፎ ማድረጌም እምነቴን አጠናክሮልኛል።—ዕብራውያን 10:24, 25
አሁን ዕድሜዬ ገፍቷል፤ ያም ሆኖ አሁንም ድረስ ከክርስቲያን ባልንጀሮቼ ጋር አብሬ ለመሥራት፣ ሰዎችን መጽሐፍ ቅዱስ ለማስጠናትና በአገልግሎት ለመካፈል የሚያስችለኝ ጥንካሬ ስላለኝ ይሖዋን አመሰግነዋለሁ። ሌሎችን በእነዚህ መንገዶች ማገልገሌ የተስፋ መቁረጥን ስሜት እንድቋቋም ኃይል ይሰጠኛል። በሕይወቴ ውስጥ በርካታ አሳዛኝ መከራዎች ቢያጋጥሙኝም ይሖዋን ከልቤ አመሰግነዋለሁ።a
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ወንድም ኤንሪኬ ካራባካ አኮስታ ይህን የሕይወት ታሪካቸውን ከሰጡ ከሁለት ዓመት በኋላ በ90 ዓመታቸው አርፈዋል።
[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ ማንበቤ የመጽናናት ምንጭ የሆነልኝ ሲሆን ችግሮችን ለመቋቋም የሚያስችለኝን ጥንካሬም ሰጥቶኛል
[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የመጽሐፍ ቅዱስ ንግግር ማቅረብ በጀመርኩበት ወቅት
[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በወጣትነቴ በመስክ አገልግሎት ላይ እያለሁ