ኢየሱስ ክርስቶስ—መልእክቱ ለአንተ ምን ትርጉም አለው?
“እኔ የመጣሁት ሕይወት እንዲኖራቸውና እንዲትረፈረፍላቸው ነው።”—ዮሐንስ 10:10
ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ምድር የመጣበት ዋነኛ ዓላማ መስጠት እንጂ መቀበል አይደለም። በስብከቱ ሥራ አማካኝነት ለሰው ልጆች በዋጋ የማይገመት ስጦታ ይኸውም ስለ አምላክና ስለ ፈቃዱ እውነቱን የሚገልጥ መልእክት ሰጥቷቸዋል። በሚሊዮን ከሚቆጠሩ እውነተኛ ክርስቲያኖች ሕይወት መመልከት እንደሚቻለው ይህንን መልእክት የሚቀበሉ ሰዎች በአሁኑ ጊዜ የተሻለ ሕይወት ያገኛሉ።a ኢየሱስ የሰበከው መልእክት ካሉት ዋነኛ ገጽታዎች አንዱ ከሁሉ ስለሚበልጠው ስጦታ የሚገልጽ ሲሆን ይህም ለእኛ ሲል መሥዋዕት ያደረገው ፍጹም ሕይወቱ ነው። ዘላለማዊ ደኅንነታችን የተመካው ወሳኝ ለሆነው ለዚህ የመልእክቱ ገጽታ በምንሰጠው ምላሽ ላይ ነው።
አምላክና ክርስቶስ የሰጡን ስጦታ። ኢየሱስ በጠላቶቹ እጅ ተሠቃይቶ እንደሚገደል ያውቅ ነበር። (ማቴዎስ 20:17-19) ያም ቢሆን ዮሐንስ 3:16 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘውን በብዙዎች ዘንድ የሚታወቀውን የሚከተለውን ሐሳብ ተናግሯል፦ “አምላክ ዓለምን እጅግ ከመውደዱ የተነሳ በልጁ እንደሚያምን በተግባር የሚያሳይ ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ ሲል አንድያ ልጁን ሰጥቷል።” በተጨማሪም ኢየሱስ የመጣው “በብዙዎች ምትክ ነፍሱን [ወይም ሕይወቱን] ቤዛ አድርጎ ለመስጠት” እንደሆነ ተናግሯል። (ማቴዎስ 20:28) ኢየሱስ ሕይወቱን እንደሚያጣ ከመናገር ይልቅ እንደሚሰጥ የገለጸው ለምንድን ነው?
አምላክ ተወዳዳሪ በሌለው ፍቅሩ ተገፋፍቶ የሰው ልጆችን ከወረሱት ኃጢአትና ካስከተላቸው መዘዞች ማለትም ከአለፍጽምናና ከሞት ለማዳን የሚያስችል ዝግጅት አደረገ። አምላክ ይህን ያደረገው አንድያ ልጁን ወደ ምድር በመላክ መሥዋዕት ሆኖ እንዲሞት በማድረግ ነው። ኢየሱስ ፍጹም የሆነውን ሰብዓዊ ሕይወቱን ስለ እኛ በፈቃደኝነት ሰጥቷል። ቤዛ ተብሎ የሚጠራው ይህ ዝግጅት አምላክ ለሰው ልጆች ከሰጣቸው ስጦታዎች ሁሉ የላቀ ነው።b ይህ ስጦታ የዘላለም ሕይወት ያስገኛል።
ማድረግ የሚኖርብህ ነገር። ቤዛው በግልህ እንደተሰጠህ ስጦታ ሆኖ ይሰማሃል? ይህ በአንተ ላይ የተመካ ነው። ነጥቡን በምሳሌ ለማስረዳት፦ አንድ ሰው የተጠቀለለ ስጦታ ሊሰጥህ ተዘጋጅቷል እንበል። እጅህን ዘርግተህ ስጦታውን እስካልተቀበልከው ድረስ ስጦታው የአንተ ሊሆን አይችልም። በተመሳሳይም ይሖዋ ከቤዛው ዝግጅት ተጠቃሚ እንድትሆን ግብዣ አቅርቦልሃል፤ ይሁንና ይህን ስጦታ እጅህን ዘርግተህ ካልተቀበልከው የአንተ ሊሆን አይችልም። ይህን ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው?
ኢየሱስ የዘላለም ሕይወት የሚያገኙት በእሱ ‘እንደሚያምኑ በተግባር የሚያሳዩ’ ሰዎች እንደሆኑ ተናግሯል። እምነት እንዳለህ በአኗኗርህ ሊታይ ይገባል። (ያዕቆብ 2:26) በኢየሱስ ላይ እምነት እንዳለህ በተግባር ማሳየት ሲባል እሱ ከተናገራቸውና ካደረጋቸው ነገሮች ጋር በሚስማማ መንገድ ሕይወትህን መምራት ማለት ነው። ይህን ለማድረግ ደግሞ ኢየሱስንና አባቱን በሚገባ ልታውቃቸው ይገባል። ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “የዘላለም ሕይወት ማግኘት እንዲችሉ ብቸኛው እውነተኛ አምላክ ስለሆንከው ስለ አንተና ስለላክኸው ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ እውቀት መቅሰማቸውን መቀጠል አለባቸው።”—ዮሐንስ 17:3
ከ2,000 ዓመታት ገደማ በፊት ኢየሱስ ክርስቶስ የተናገረው መልእክት በዓለም ዙሪያ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት ለውጧል። ስለዚህ መልእክት ተጨማሪ እውቀት ማግኘት እንዲሁም አንተም ሆንክ የምትወዳቸው ሰዎች አሁን ብቻ ሳይሆን ለዘላለም ከዚህ መልእክት እንዴት ጥቅም ማግኘት እንደምትችሉ መማር ትፈልጋለህ? የይሖዋ ምሥክሮች በዚህ ረገድ ሊረዱህ ፈቃደኞች ናቸው።
ከዚህ ቀጥሎ ያሉት ርዕሶች ሕይወትህን ለዘላለም ሊለውጥ የሚችል መልእክት ስለሰበከው ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ የበለጠ ማወቅ እንድትችል ይረዱሃል።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a ክርስቲያን ነኝ የሚል ሁሉ የክርስቶስ እውነተኛ ተከታይ አይደለም። የኢየሱስ እውነተኛ ተከታዮች፣ ኢየሱስ ስለ አምላክና ስለ ፈቃዱ ካስተማራቸው እውነቶች ጋር በሚስማማ መንገድ የሚኖሩ ሰዎች ናቸው።—ማቴዎስ 7:21-23
b በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ስለሚገኘው የቤዛው ትምህርት ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች በተዘጋጀው ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? በተባለው መጽሐፍ ላይ “ቤዛው—ከሁሉ የላቀ የአምላክ ስጦታ” የሚለውን ምዕራፍ 5ን ተመልከት።