በአምላክ መንፈስ በሚመራው ንጉሥ አማካኝነት የሚገኘውን በረከት እጨዱ!
“[ይሖዋን] የመፍራት መንፈስ ያርፍበታል።”—ኢሳ. 11:2
1. አንዳንዶች በዓለም ላይ ያሉ ችግሮችን በተመለከተ ያላቸውን ስጋት የገለጹት እንዴት ነው?
“በፖለቲካ፣ በማኅበራዊ ሕይወትና በከባቢያዊ ሁኔታ በችግር እየታመሰ ባለው ዓለም ውስጥ የሰው ዘር ከአሁን በኋላ ለሌላ 100 ዓመት እንዴት መዝለቅ ይችላል?” በ2006 ይህን ጥያቄ የጠየቁት ስቴፈን ሃውኪንግ የተባሉ ሳይንቲስት ናቸው። ኒው ስቴትስማን በተሰኘ መጽሔት ላይ የወጣ አንድ ጽሑፍ የሚከተለውን ሐሳብ አስፍሮ ነበር፦ “ድህነትን ማጥፋትም ሆነ በዓለም ላይ ሰላም ማስፈን አልቻልንም። እንዲያውም ፍጹም ተቃራኒ ውጤት ያገኘን ይመስላል። ይህ ሲባል ግን ምንም ጥረት አላደረግንም ማለት አይደለም። ድህነትን ለማጥፋት ከኮሚኒዝም እስከ ነፃ ገበያ ድረስ ሁሉንም ሞክረናል፤ ጦርነትን ለማስቀረት ደግሞ የመንግሥታት ቃል ኪዳን ማኅበርን ከማቋቋም አንስቶ ብሔራት ተፈራርተው እንዲኖሩ የኑክሌር ጦር መሣሪያዎችን እስከ ማከማቸት ድረስ ያልሞከርነው ነገር የለም። ጦርነትን እንዴት ማስቆም እንደምንችል እናውቃለን በሚል ስሜት ስንትና ስንት ጦርነቶች ውስጥ ገብተናል።”
2. ይሖዋ በቅርቡ ሉዓላዊ ገዥነቱን በምድር ላይ የሚያረጋግጠው እንዴት ነው?
2 የይሖዋ አገልጋዮች እንዲህ ያሉ አስተያየቶችን ሲሰሙ አይደነቁም። የሰው ልጅ ራሱን የመግዛት ችሎታ ኖሮት እንዳልተፈጠረ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ኤር. 10:23) ሰዎችን የመግዛት መብት ያለው ይሖዋ ብቻ ነው። በመሆኑም ልንመራባቸው የሚገቡ ደንቦችን የማውጣት፣ ሕይወታችን ምን ዓላማ ሊኖረው እንደሚገባ የመወሰንና እዚያ ዓላማ ላይ እንድንደርስ የመምራት መብት ያለው እሱ ብቻ ነው። በተጨማሪም ይሖዋ ሥልጣኑን በመጠቀም የሰው ልጅ ራሱን ለማስተዳደር ላደረገው ፍሬ ቢስ ጥረት መቋጫ ያበጃል። በዚያን ጊዜ የይሖዋን ሉዓላዊ ገዥነት በመቃወም የሰው ልጆች የኃጢአት፣ የአለፍጽምናና “የዚህ ሥርዓት አምላክ” የሆነው የሰይጣን ዲያብሎስ ባሪያዎች ሆነው እንዲቀጥሉ የሚፈልጉትን ሁሉ ድምጥማጣቸውን ያጠፋል።—2 ቆሮ. 4:4
3. ኢሳይያስ ስለ መሲሑ ምን ትንቢት ተናግሯል?
3 ገነት በምትሆነው አዲስ ምድር ላይ ፍቅራዊ የሆነው የይሖዋ ሉዓላዊነት ለሰው ልጆች የሚገለጸው በመሲሐዊው መንግሥት አማካኝነት ነው። (ዳን. 7:13, 14) የዚህን መንግሥት ንጉሥ በተመለከተ ኢሳይያስ እንዲህ የሚል ትንቢት ተናግሯል፦ “ከእሴይ ግንድ ቍጥቋጥ ይወጣል፤ ከሥሮቹም አንዱ ቅርንጫፍ ፍሬ ያፈራል። የእግዚአብሔር መንፈስ፣ የጥበብና የማስተዋል መንፈስ፣ የምክርና የኀይል መንፈስ፣ የዕውቀትና እግዚአብሔርን የመፍራት መንፈስ ያርፍበታል።” (ኢሳ. 11:1, 2) የአምላክ ቅዱስ መንፈስ ‘ከእሴይ ግንድ የሚወጣው ቍጥቋጥ’ ማለትም ኢየሱስ ክርስቶስ የሰው ልጆችን የመግዛት ብቃት እንዲኖረው ያስቻለው በየትኞቹ መንገዶች ነው? የእሱ አገዛዝ ምን በረከት ያመጣል? እነዚህን በረከቶች ለማጨድስ ምን ማድረግ አለብን?
ለመግዛት የሚያስችል መለኮታዊ ብቃት አለው
4-6. ኢየሱስ ጥበበኛና ሩኅሩኅ ንጉሥ፣ ሊቀ ካህናትና ፈራጅ የመሆን ብቃት ሊኖረው የቻለው የትኛው አስፈላጊ እውቀት ስላለው ነው?
4 ይሖዋ ሰብዓዊ ተገዥዎቹ ጥበበኛና ሩኅሩኅ በሆነ ንጉሥ፣ ሊቀ ካህናትና ፈራጅ አማካኝነት እየተመሩ ወደ ፍጽምና እንዲደርሱ ይፈልጋል። አምላክ፣ በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት እነዚህን ወሳኝ ኃላፊነቶች ለመወጣት የሚያስችለውን ብቃት ያገኘውን ኢየሱስ ክርስቶስን የመረጠው ለዚህ ነው። ኢየሱስ፣ አምላክ የሰጠውን ኃላፊነት ፍጹም በሆነ መንገድ ይወጣል እንድንል የሚያደርጉንን አንዳንድ ምክንያቶች እስቲ እንመልከት።
5 ኢየሱስ ስለ ይሖዋ ከሁሉ የላቀ ጥልቅ እውቀት አለው። የአምላክ አንድያ ልጅ ለብዙ ዘመናት ምናልባትም ለብዙ ቢሊዮን ዓመታት ከአባቱ ጋር ስለኖረ ከማንም በላይ አባቱን ያውቀዋል። ኢየሱስ በእነዚህ ሁሉ ዓመታት ስለ ይሖዋ ጥልቅ የሆነ እውቀት ስላዳበረ “የማይታየው አምላክ አምሳል” ተብሎ ሊጠራ ችሏል። (ቆላ. 1:15) ኢየሱስ ራሱ “እኔን ያየ አብንም አይቷል” ብሏል።—ዮሐ. 14:9
6 ኢየሱስ፣ ከይሖዋ ቀጥሎ ስለ ሰው ልጆችም ሆነ ስለ ሁሉም ፍጥረታት ጥልቅ እውቀት አለው። ቆላስይስ 1:16, 17 እንዲህ ይላል፦ “በሰማያትና በምድር ያሉ ሌሎች ነገሮች በሙሉ፣ የሚታዩትና የማይታዩት ነገሮች፣ . . . የተፈጠሩት በእሱ [በአምላክ ልጅ] አማካኝነት ነው። . . . በተጨማሪም እሱ ከሌሎች ነገሮች ሁሉ በፊት ነው፤ ሌሎች ነገሮች ሁሉ ወደ ሕልውና የመጡትም በእሱ አማካኝነት ነው።” እስቲ ሁኔታውን ለማሰብ ሞክር! የአምላክ “ዋና ባለሙያ” የሆነው ኢየሱስ በሌሎች የፍጥረት ሥራዎች በሙሉ ተካፍሏል። በመሆኑም ኢምንት ከሆኑት የአቶሚክ ቅንጣቶች አንስቶ ድንቅ እስከሆነው የሰው አንጎል ድረስ በጽንፈ ዓለም ውስጥ ስላለው ስለ እያንዳንዱ ነገር ዝርዝር እውቀት አለው። በእርግጥም፣ ክርስቶስ በጥበብ መመሰሉ የተገባ ነው!—ምሳሌ 8:12, 22, 30, 31
7, 8. ኢየሱስ አገልግሎቱን ሲያከናውን የአምላክ መንፈስ የረዳው እንዴት ነው?
7 ኢየሱስ በአምላክ ቅዱስ መንፈስ ተቀብቶ ነበር። ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “የይሖዋ መንፈስ በእኔ ላይ ነው፤ ለድሆች ምሥራች እንዳውጅ ቀብቶኛል፤ ለተማረኩት ነፃነትን፣ ለታወሩትም ማየትን እንድሰብክ፣ የተጨቆኑትን ነፃ እንዳወጣ እንዲሁም በይሖዋ ዘንድ የተወደደውን ዓመት እንድሰብክ ልኮኛል።” (ሉቃስ 4:18, 19) ኢየሱስ ሲጠመቅ መሲሕ በመሆን በምድር ላይ እንዲያከናውን የተሰጠውን ኃላፊነት ጨምሮ ሰው ሆኖ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት የተማራቸውን ነገሮች መንፈስ ቅዱስ እንዲያስታውስ ያደረገው ይመስላል።—ኢሳይያስ 42:1ን፤ ሉቃስ 3:21, 22ን እና ዮሐንስ 12:50ን አንብብ።
8 ኢየሱስ በመንፈስ ቅዱስ መሞላቱና በአካልም ሆነ በአእምሮ ፍጹም መሆኑ እስከ ዛሬ ከኖሩት ሁሉ የሚበልጥ ታላቅ ሰው ብቻ ሳይሆን ታላቅ አስተማሪም እንዲሆን አድርጎታል። እንዲያውም አድማጮቹ “በትምህርት አሰጣጡ እጅግ [ተደንቀው]” ነበር። (ማቴ. 7:28) በመጀመሪያ ደረጃ ኢየሱስ ለሰው ልጆች ችግሮች ዋነኛ መንስኤ ለሆኑት ነገሮች ይኸውም ለኃጢአት፣ ለአለፍጽምና እንዲሁም ለመንፈሳዊ ድርንቁርና መፍትሔ ማግኘት ችሎ ነበር። በተጨማሪም የሰዎችን ልብ ማንበብ ስለሚችል እንደማንነታቸው ይይዛቸው ነበር።—ማቴ. 9:4፤ ዮሐ. 1:47
9. ኢየሱስ ምድር ሳለ ባሳለፈው ሕይወት ላይ ማሰላሰልህ ብቃት ያለው ገዥ ስለመሆኑ ይበልጥ እንድትተማመን የሚያደርግህ እንዴት ነው?
9 ኢየሱስ ሰው ሆኖ ምድር ላይ ኖሯል። ሰው ሆኖ ያሳለፈው ሕይወትና ፍጽምና ከሌላቸው ሰዎች ጋር መቀራረቡ ንጉሥ ለመሆን ብቃት እንዲኖረው በእጅጉ ረድቶታል። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “[ኢየሱስ] ለሕዝቡ ኃጢአት የማስተሰረያ መሥዋዕት ለማቅረብ በአምላክ አገልግሎት መሐሪና ታማኝ ሊቀ ካህናት ይሆን ዘንድ በሁሉ ረገድ የግድ እንደ ወንድሞቹ መሆን አስፈለገው። በተፈተነበት ጊዜ እሱ ራሱ መከራ ስለደረሰበት በመፈተን ላይ ላሉት ሊደርስላቸው ይችላል።” (ዕብ. 2:17, 18) ኢየሱስ እሱ ራሱ ‘ስለተፈተነ’ መከራ ለሚደርስባቸው ሰዎች ይራራላቸዋል። ኢየሱስ ምድራዊ አገልግሎቱን ባከናወነባቸው ዓመታት ሩኅሩኅ መሆኑ በግልጽ ታይቷል። የታመሙ፣ የአካል ጉዳት ያለባቸውና የተጨቆኑ ሰዎች አልፎ ተርፎም ሕፃናት እንኳ ወደ እሱ መቅረብ አይከብዳቸውም ነበር። (ማር. 5:22-24, 38-42፤ 10:14-16) በተጨማሪም ገሮችና በመንፈሳዊ የተራቡ ሰዎች ወደ እሱ ይቀርቡ ነበር። በሌላ በኩል ግን ኩሩ፣ ትዕቢተኛና ‘የአምላክ ፍቅር የሌላቸው’ ሰዎች ያልተቀበሉት ከመሆኑም በላይ ይጠሉትና ይቃወሙት ነበር።—ዮሐ. 5:40-42፤ 11:47-53
10. ኢየሱስ ለእኛ ያለውን ፍቅር የገለጸበት ከሁሉ የላቀው መንገድ የትኛው ነው?
10 ኢየሱስ ለእኛ ሲል ሕይወቱን አሳልፎ ሰጥቷል። ኢየሱስ ብቃት ያለው ገዥ ነው እንድንል የሚያደርገን ከሁሉ የላቀው ማስረጃ ሕይወቱን ለእኛ ለመስጠት ፈቃደኛ መሆኑ ሳይሆን አይቀርም። (መዝሙር 40:6-10ን አንብብ።) ክርስቶስ “ነፍሱን ለወዳጆቹ ሲል አሳልፎ ከሚሰጥ ሰው የበለጠ ፍቅር ያለው ማንም የለም” በማለት ተናግሯል። (ዮሐ. 15:13) በተገዥዎቻቸው ገንዘብ የተንደላቀቀ ሕይወት ከሚመሩት ፍጽምና የጎደላቸው ሰብዓዊ ገዥዎች በተቃራኒ ኢየሱስ ለሰው ልጆች ሕይወቱን አሳልፎ ሰጥቷል።—ማቴ. 20:28
ቤዛውን ጥቅም ላይ እንዲያውል አምላክ ኃይል ሰጥቶታል
11. ኢየሱስ በቤዛዊ መሥዋዕቱ አማካኝነት በሚያደርግልን ነገር ሙሉ በሙሉ መተማመን የምንችለው ለምንድን ነው?
11 ኢየሱስ ሊቀ ካህናት እንደመሆኑ መጠን የከፈለልን ቤዛዊ መሥዋዕት ጥቅም ላይ እንዲውል ቁልፍ ሚና የሚጫወተው እሱ መሆኑ የተገባ ነው! እንዲያውም በምድራዊ አገልግሎቱ ወቅት አንዳንድ ተአምራትን በማከናወን፣ ታማኝ ሆነን ወደ ሺህ ዓመት ግዛቱ ከገባን በቤዛዊ መሥዋዕቱ አማካኝነት የሚያደርግልንን ነገር በናሙና መልክ አሳይቷል። የታመሙትንና የአካል ጉዳት የነበረባቸውን ፈውሷል፣ ብዙ ሰዎችን መግቧል፣ ሌላው ቀርቶ የተፈጥሮ ኃይላትን እንኳ ተቆጣጥሯል። (ማቴ. 8:26፤ 14:14-21፤ ሉቃስ 7:14, 15) እነዚህን ነገሮች ያደረገው ሥልጣኑንና ኃይሉን ለማሳየት ሳይሆን ለሰዎች ያለውን ርኅራኄና ፍቅር ለመግለጽ ነበር። በሥጋ ደዌ የተያዘ አንድ ሰው እንዲፈውሰው በለመነው ጊዜ “እፈልጋለሁ፣ ንጻ” ብሎታል። (ማር. 1:40, 41) ኢየሱስ በሺህ ዓመት ግዛቱ ወቅት በዓለም ዙሪያ ላሉ ሰዎች ተመሳሳይ የርኅራኄ ስሜት ያሳያል።
12. ኢሳይያስ 11:9 ፍጻሜውን የሚያገኘው እንዴት ነው?
12 ክርስቶስና ተባባሪ ገዥዎቹ እሱ የዛሬ 2,000 ዓመት ገደማ የጀመረውን መንፈሳዊ ትምህርት የማስተማሩን ሥራ ይቀጥላሉ። በዚያን ጊዜ በኢሳይያስ 11:9 ላይ የሚገኘው “ውኃ ባሕርን እንደሚከድን ምድር እግዚአብሔርን በማወቅ ትሞላለች” የሚለው ትንቢት ፍጻሜውን ያገኛል። ይህ መለኮታዊ ትምህርት መጀመሪያ ላይ ለአዳም ተሰጥቶት የነበረውን ምድርንና በእሷ ላይ የሚኖሩትን ስፍር ቁጥር የሌላቸውን ፍጥረታት የመንከባከቡን ሥራ እንዴት መወጣት እንደሚቻል የሚገልጸውን መመሪያ እንደሚጨምር ምንም ጥርጥር የለውም። በዘፍጥረት 1:28 ላይ የተገለጸው የአምላክ የመጀመሪያ ዓላማ በአንድ ሺው ዓመት መጨረሻ ላይ ፍጻሜውን ያገኛል፤ እንዲሁም ቤዛዊ መሥዋዕቱ ሙሉ በሙሉ ጥቅም ላይ ይውላል።
ፈራጅ እንዲሆን አምላክ ኃይል ሰጥቶታል
13. ኢየሱስ ለጽድቅ ፍቅር እንዳለው ያሳየው እንዴት ነበር?
13 ክርስቶስ ‘በሕያዋንና በሙታን ላይ ፈራጅ እንዲሆን በአምላክ ተሹሟል።’ (ሥራ 10:42) ኢየሱስ በጥቅም የማይደለል እንደሆነ ብሎም ጽድቅንና ታማኝነትን የወገቡ መታጠቂያ እንዳደረገ ማወቃችን እንዴት የሚያጽናና ነው! (ኢሳ. 11:5) ኢየሱስ ስስትን፣ ግብዝነትንና ሌሎች መጥፎ ድርጊቶችን እንደሚጠላ ያሳየ ከመሆኑም በላይ የሌሎች ሥቃይ የማይሰማቸው ሰዎችን አውግዟል። (ማቴ. 23:1-8, 25-28፤ ማር. 3:5) በተጨማሪም “እሱ ራሱ በሰው ውስጥ ያለውን ያውቅ ስለነበር” በሌሎች ውጫዊ ገጽታ አይታለልም ነበር።—ዮሐ. 2:25
14. ኢየሱስ ለጽድቅና ለፍትሕ ያለውን ፍቅር እያንጸባረቀ ያለው እንዴት ነው? ራሳችንን ምን ብለን መጠየቅ ይኖርብናል?
14 ኢየሱስ በታሪክ ውስጥ ተወዳዳሪ የሌለውን የስብከት እንዲሁም የማስተማር ዘመቻ በበላይነት በመቆጣጠር ለጽድቅና ለፍትሕ ያለውን ፍቅር ማሳየቱን ቀጥሏል። ማንኛውም ሰውም ሆነ ሰብዓዊ መንግሥት አሊያም ርኩስ መንፈስ ይህ ሥራ አምላክ እስከሚፈልገው ደረጃ ድረስ እንዳይከናወን ማገድ አይችልም። በመሆኑም ከአርማጌዶን በኋላ መለኮታዊ ፍትሕ እንደሚሰፍን ሙሉ በሙሉ እርግጠኞች መሆን እንችላለን። (ኢሳይያስ 11:4ን እና ማቴዎስ 16:27ን አንብብ።) እስቲ ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ፦ ‘በአገልግሎት ላይ ኢየሱስ ለሰዎች የነበረውን አመለካከት እያንጸባረቅሁ ነው? ጤንነቴ ወይም ያለሁበት ሁኔታ አቅሜን የሚገድብብኝ ቢሆንም እንኳ ለይሖዋ ምርጤን እየሰጠሁ ነው?’
15. ለይሖዋ ምርጣችንን እንድንሰጥ ምን ሊረዳን ይችላል?
15 የስብከቱ ሥራ የአምላክ ሥራ መሆኑን ምንጊዜም ማስታወሳችን እሱን በሙሉ ነፍስ ለማገልገል ይረዳናል። ሥራው እንዲሠራ ያዘዘው አምላክ ነው፤ በተጨማሪም በልጁ በኩል ሥራውን እየመራ ከመሆኑም ሌላ በዚህ ሥራ ለሚካፈሉ ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት ኃይል ይሰጣቸዋል። በመንፈስ ከሚመራው የአምላክ ልጅ ጋር በማገልገል ከአምላክ ጋር የመሥራት መብትህን ከፍ አድርገህ ትመለከተዋለህ? በአብዛኛው “ያልተማሩ ተራ ሰዎች” ተደርገው የሚቆጠሩትን ከሰባት ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎች የመንግሥቱን መልእክት በ236 አገሮች ለሚገኙ ሕዝቦች ለማዳረስ እንዲነሳሱ ያደረጋቸው ከይሖዋ ውጪ ማን ሊሆን ይችላል?—ሥራ 4:13
በክርስቶስ አማካኝነት ራስህን ባርክ!
16. ዘፍጥረት 22:18 ከአምላክ ስለሚገኘው በረከት ምን ይጠቁማል?
16 ይሖዋ ለአብርሃም “ቃሌን ስለ ሰማህ የምድር ሕዝቦች ሁሉ በዘርህ ይባረካሉ” ብሎት ነበር። (ዘፍ. 22:18) ይህ ተስፋ፣ አምላክንና ልጁን የማገልገል መብታቸውን ከፍ አድርገው የሚመለከቱ ሰዎች በመሲሐዊው ዘር በኩል የሚመጣውን በረከት በእርግጠኝነት መጠባበቅ እንደሚችሉ ይጠቁማል። በመሆኑም እነዚህ ሰዎች ይህን ተስፋ ከሚጠባበቁ ሌሎች ሰዎች ጋር በመሆን አምላክን በንቃት ያገለግላሉ።
17, 18. ይሖዋ በዘዳግም 28:2 ላይ ምን ተስፋ ሰጥቷል? ይህ ተስፋስ ለእኛ ምን ትርጉም አለው?
17 በአንድ ወቅት አምላክ የአብርሃም ዘር ለሆነው የእስራኤል ብሔር “የአምላክህን የይሖዋን ድምፅ ከሰማህ እነዚህ ሁሉ በረከቶች ይወርዱልሃል፤ በሄድክበትም ይከተሉሃል” ብሎት ነበር። (ዘዳ. 28:2 NW) ይህ ጥቅስ በዛሬው ጊዜ በሚገኙ የአምላክ ሕዝቦች ላይም ይሠራል። የይሖዋን በረከት ማግኘት ከፈለግህ ድምፁን ‘መስማትህን’ መቀጠል ይኖርብሃል። እንዲህ ካደረግህ የይሖዋ “በረከቶች ይወርዱልሃል፤ በሄድክበትም ይከተሉሃል።” ታዲያ ‘መስማት’ ምንን ይጨምራል?
18 አምላክን መስማት፣ ቃሉ ውስጥ በሰፈሩት ነገሮች ላይ በጥሞና ማሰብንና እሱ ያዘጋጃቸውን መንፈሳዊ ምግቦች በሚገባ መመገብን እንደሚያካትት ግልጽ ነው። (ማቴ. 24:45) እንዲሁም አምላክንና ልጁን መታዘዝን ይጨምራል። ኢየሱስ “‘ጌታ ሆይ፣ ጌታ ሆይ’ የሚለኝ ሁሉ ወደ መንግሥተ ሰማያት አይገባም፤ ወደ መንግሥተ ሰማያት የሚገባው በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ ነው” ብሏል። (ማቴ. 7:21) በተጨማሪም አምላክን መስማት ሲባል እሱ ላደረገው ዝግጅት ይኸውም ‘ስጦታ የሆኑ ወንዶች’ በተባሉት ሽማግሌዎች አማካኝነት ላቋቋመው የክርስቲያን ጉባኤ በፈቃደኝነት መገዛት ማለት ነው።—ኤፌ. 4:8
19. የአምላክን በረከት እንድናጭድ የሚረዳን አንዱ መንገድ ምንድን ነው?
19 ‘ስጦታ ከሆኑት ወንዶች’ መካከል የመላው ክርስቲያን ጉባኤ ወኪል ሆነው የሚያገለግሉት የበላይ አካል አባላት ይገኙበታል። (ሥራ 15:2, 6) እንዲያውም በመጪው ታላቅ መከራ ወቅት የምናገኘው ፍርድ ለክርስቶስ መንፈሳዊ ወንድሞች ባለን አመለካከት ላይ በእጅጉ የተመካ ነው። (ማቴ. 25:34-40) በመሆኑም የአምላክን በረከት ለማጨድ የሚያስችለን አንደኛው መንገድ እሱ የቀባቸውን ክርስቲያኖች በታማኝነት መደገፍ ነው።
20. (ሀ) ‘ስጦታ የሆኑት ወንዶች’ ተቀዳሚ ኃላፊነት ምንድን ነው? (ለ) እነዚህን ወንድሞች እንደምናደንቃቸው ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?
20 ‘ስጦታ ከሆኑት ወንዶች’ መካከል የቅርንጫፍ ኮሚቴ አባላት፣ ተጓዥ የበላይ ተመልካቾችና የጉባኤ ሽማግሌዎችም ይገኙበታል፤ ሁሉም በመንፈስ ቅዱስ የተሾሙ ናቸው። (ሥራ 20:28) የእነዚህ ወንድሞች ተቀዳሚ ኃላፊነት ሁሉም የአምላክ ሕዝቦች “በእምነትና ስለ አምላክ ልጅ ትክክለኛ እውቀት በመቅሰም ወደሚገኘው አንድነት እንዲሁም ሙሉ ሰው ወደ መሆንና ክርስቶስ ወዳለበት የሙላት ደረጃ [እንዲደርሱ]” እነሱን መገንባት ነው። (ኤፌ. 4:13) እነዚህ ወንዶች ልክ እንደ እኛ ፍጽምና እንደሚጎድላቸው የታወቀ ነው። ያም ሆኖ የሚያደርጉልንን ፍቅራዊ እረኝነት የምናደንቅና በጎ ምላሽ የምንሰጥ ከሆነ በረከት እናገኛለን።—ዕብ. 13:7, 17
21. የአምላክን ልጅ መታዘዛችን አጣዳፊ የሆነው ለምንድን ነው?
21 በቅርቡ ክርስቶስ በሰይጣን ክፉ ሥርዓት ላይ እርምጃ ይወስዳል። ኢየሱስ ትንቢት የተነገረላቸውን ‘እጅግ ብዙ ሕዝቦች’ “ወደ ሕይወት ውኃ ምንጭ” እንዲመራ ሥልጣን ስለተሰጠው በዚያን ጊዜ በሕይወት መትረፋችን የተመካው በእሱ ላይ ነው። (ራእይ 7:9, 16, 17) በመሆኑም በመንፈስ ለሚመራው የይሖዋ ንጉሥ በፈቃደኝነትና በአድናቆት ለመገዛት የተቻለንን ሁሉ እናድርግ።
ከሚከተሉት ጥቅሶች ምን ትምህርት አግኝተሃል?
• ከኢሳይያስ 11:1-5
• ከማርቆስ 1:40, 41
• ከሐዋርያት ሥራ 10:42
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢየሱስ የኢያኢሮስን ልጅ ከሞት ባስነሳበት ጊዜ ሩኅሩኅ መሆኑ በግልጽ ታይቷል
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢየሱስ ክርስቶስ በታሪክ ውስጥ ተወዳዳሪ የሌለውን የስብከት ዘመቻ በበላይነት እየተቆጣጠረ ነው