አዳምና ሔዋን እንደሚሳሳቱ አምላክ ያውቅ ነበር?
ብዙ ሰዎች የዚህን ጥያቄ መልስ ለማወቅ ይፈልጋሉ። ‘አምላክ ክፋት እንዲኖር የፈቀደው ለምንድን ነው?’ የሚለው ጥያቄ ሲነሳ የመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት በኤደን የአትክልት ስፍራ የፈጸሙት ኃጢአት ዋነኛ የውይይት አጀንዳ መሆኑ አይቀርም። አምላክ ሁሉን ነገር ያውቃል የሚለው አመለካከት ብዙ ጊዜ ሰዎች ‘አምላክ አዳምና ሔዋን ኃጢአት እንደሚሠሩ አስቀድሞ ያውቅ ነበር’ ወደሚለው መደምደሚያ እንዲደርሱ ሊያደርጋቸው ይችላል።
አምላክ ፍጹም የሆኑት እነዚህ ባልና ሚስት ኃጢአት እንደሚሠሩ ያውቃል ብሎ መናገር ምን ትርጉም ያስተላልፋል? ይህ ዓይነቱ አመለካከት በተለያየ መንገድ ለአምላክ መጥፎ ስም ሊያሰጠው ይችላል። ለምሳሌ ፍቅር የሌለው፣ ኢፍትሐዊና አስመሳይ እንደሆነ ሊያስቆጥረው ይችላል። አንዳንዶች ደግሞ አምላክ የመጀመሪያዎቹ ሰዎች መጨረሻቸው እንደማያምር እያወቀ ሆን ብሎ ወደ ሕልውና አምጥቷቸዋል በሚል እንደ ጨካኝ ያዩታል። በተጨማሪም አምላክ አዳምና ሔዋን ኃጢአት እንደሚሠሩ አስቀድሞ የሚያውቅ ከሆነ በታሪክ ዘመናት ሁሉ ለተከሰተው ክፋትና መከራ ቢያንስ በከፊል ተጠያቂ ይሆናል። እንዲያውም አንዳንዶች አምላክን እንደ ሞኝ ያዩታል።
ታዲያ በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ለተጠቀሰው ለይሖዋ አምላክ እንዲህ ያለ ስም መሰጠቱ ትክክል ነው? የዚህን ጥያቄ መልስ ለማወቅ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ይሖዋ የፍጥረት ሥራዎችና ስለ ባሕርያቱ ምን እንደሚል እንመርምር።
“እጅግ መልካም ነበረ”
የዘፍጥረት መጽሐፍ የመጀመሪያዎቹን የሰው ልጆች ጨምሮ አምላክ የፈጠራቸውን ነገሮች አስመልክቶ ሲናገር “እግዚአብሔርም ያደረገውን ሁሉ አየ፤ እነሆም፣ እጅግ መልካም ነበረ” ይላል። (ዘፍጥረት 1:31) አዳምና ሔዋን የተፈጠሩት ፍጹም ተደርገው ሲሆን ምድራዊ መኖሪያቸውም ለእነሱ እጅግ ተስማሚ ነበር። አፈጣጠራቸው ምንም ጉድለት አልነበረውም። “እጅግ መልካም” ተደርገው ስለተፈጠሩ ከእነሱ የሚጠበቀውን ተገቢ ምግባር የማሳየት ብቃት እንደነበራቸው ምንም ጥርጥር የለውም። የተፈጠሩት “በእግዚአብሔር መልክ” ነው። (ዘፍጥረት 1:27) በመሆኑም እንደ ጥበብ፣ ጽኑ ፍቅር፣ ፍትሕና ጥሩነት ያሉ አምላካዊ ባሕርያትን በተወሰነ መጠን ማሳየት ይችሉ ነበር። እነዚህን ባሕርያት ቢያንጸባርቁ ኖሮ ራሳቸውን የሚጠቅምና ሰማያዊ አባታቸውን የሚያስደስት ውሳኔ ማድረግ ይችሉ ነበር።
ይሖዋ ለእነዚህ ፍጹማን የሆኑ የማሰብ ችሎታ ያላቸው ፍጥረታት ነፃ ምርጫ ሰጥቷቸዋል። በመሆኑም አስቀድመው ፕሮግራም እንደሚደረጉ ሮቦቶች በደመ ነፍስ አምላክን እንዲያስደስቱ ተደርገው አልተፈጠሩም። እስቲ ቆም ብለህ ለማሰብ ሞክር። ይበልጥ የሚያስደስትህ ምን ዓይነት ስጦታ ነው? እንዲያው ለይስሙላ የሚደረግ ነው ወይስ ከልብ ታስቦበት የሚሰጥ? መልሱ ግልጽ ነው። በተመሳሳይም አምላክ ይበልጥ የሚደሰተው አዳምና ሔዋን በራሳቸው ፍላጎት እሱን ለመታዘዝ ቢመርጡ ነበር። የመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት የመምረጥ ነፃነት የነበራቸው መሆኑ አምላክን በፍቅር ተነሳስተው እንዲታዘዙት ያስችላቸው ነበር።—ዘዳግም 30:19, 20
ጽድቅ፣ ፍትሕና ጥሩነት
መጽሐፍ ቅዱስ የይሖዋን ባሕርያት ይገልጽልናል። ይሖዋ ያሉት ባሕርያት ከኃጢአት ጋር የተያያዘ ምንም ነገር ከመፈጸም እንዲርቅ ያደርጉታል። መዝሙር 33:5 ይሖዋ “ጽድቅንና ፍትሕን ይወዳል” በማለት ይናገራል። በመሆኑም ያዕቆብ 1:13 እንደሚገልጸው “አምላክ በክፉ ነገሮች ሊፈተን አይችልም፤ እሱ ራሱም ማንንም አይፈትንም።” አምላክ ምክንያታዊና አሳቢ በመሆኑ አዳምን “በአትክልት ስፍራው ውስጥ ከሚገኝ ከማንኛውም ዛፍ ፍሬ ትበላለህ። ነገር ግን መልካምና ክፉን ከሚያሳውቀው ዛፍ አትብላ፤ ምክንያቱም ከእርሱ በበላህ ቀን በእርግጥ ትሞታለህ” በማለት አስጠንቅቆታል። (ዘፍጥረት 2:16, 17) የመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት የዘላለም ሕይወትን አሊያም ሞትን እንዲመርጡ አጋጣሚ ተሰጥቷቸው ነበር። አምላክ ከኃጢአት እንዲርቁ ያስጠነቀቃቸው መጨረሻቸው እንደማያምር እያወቀ ከሆነ እንደ አስመሳይ አያስቆጥረውም ነበር? ይሖዋ ‘ጽድቅንና ፍትሕን የሚወድ’ አምላክ እንደመሆኑ መጠን የማያገኙትን ነገር ለምርጫ አያቀርብላቸውም።
በተጨማሪም የይሖዋ በጎነት ወይም ጥሩነት እጅግ ብዙ ነው። (መዝሙር 31:19) ኢየሱስ የአምላክን ጥሩነት አስመልክቶ እንዲህ ብሏል፦ “ከመካከላችሁ ልጁ ዳቦ ቢለምነው ድንጋይ የሚሰጠው አለ? ወይስ ዓሣ ቢለምነው እባብ ይሰጠዋል? ታዲያ እናንተ ክፉዎች ሆናችሁ ሳላችሁ ለልጆቻችሁ መልካም ስጦታ መስጠት ካወቃችሁ በሰማያት ያለው አባታችሁ ለሚለምኑት እንዴት መልካም ነገር አብልጦ አይሰጣቸውም!” (ማቴዎስ 7:9-11) አምላክ ለፍጡራኑ ‘መልካም ነገሮችን’ ይሰጣል። የሰዎች አፈጣጠርና ለእነሱ መኖሪያ እንድትሆን የተሰጠቻቸው ገነት የተዘጋጀችበት መንገድ የአምላክን ጥሩነት በግልጽ ያሳያሉ። ለጥሩነቱ ወደር የማይገኝለት እንዲህ ያለው ሉዓላዊ ገዥ፣ እንደሚነጥቃቸው እያወቀ ለሰዎች ውብ መኖሪያ የሚሰጥ ጨካኝ አምላክ ሊሆን ይችላል? በጭራሽ! ጻድቅና ጥሩ የሆነው ፈጣሪያችን የሰው ልጆች ለፈጸሙት ዓመፅ በፍጹም ተወቃሽ ሊሆን አይችልም።
“እሱ ብቻ ጥበበኛ” ነው
ቅዱሳን መጻሕፍት ይሖዋ “ብቻ ጥበበኛ” እንደሆነም ይናገራሉ። (ሮም 16:27) በሰማይ ያሉት መላእክት ይሖዋ ወደር የሌለው ጥበቡን በብዙ መንገዶች ሲገልጥ የመመልከት አጋጣሚ አግኝተዋል። አምላክ በምድር ላይ ያሉ ፍጥረታትን ወደ ሕልውና ሲያመጣ መላእክት “እልል” ብለው ነበር። (ኢዮብ 38:4-7) እነዚህ የማሰብ ችሎታ ያላቸው መንፈሳዊ ፍጥረታት በኤደን ገነት ውስጥ የተከናወኑትን ሁኔታዎች በታላቅ ጉጉት ተከታትለው እንደነበር ምንም ጥርጥር የለውም። እንዲህ ያለው ጥበበኛ አምላክ ዕጹብ ድንቅ የሆነውን አጽናፈ ዓለምና በምድር ላይ ያሉ ስፍር ቁጥር የሌላቸውን ነገሮች ከፈጠረ በኋላ መጨረሻቸው እንደማያምር እያወቀ ሁለት ልዩ ፍጥረታትን በመላእክቱ ፊት ወደ ሕልውና ያመጣል ብሎ ማሰብ ስሜት ይሰጣል? እንዲህ ዓይነት ጥፋት ለማምጣት ማቀድ ምክንያታዊ እንደማይሆን ግልጽ ነው።
ያም ሆኖ አንድ ሰው፣ ‘ለጥበቡ ወደር የማይገኝለት አምላክ እንዴት አስቀድሞ ማወቅ አይችልም?’ የሚል ጥያቄ ያነሳ ይሆናል። እርግጥ ነው፣ “የመጨረሻውን ከመጀመሪያው” ማወቅ የይሖዋ ጥበብ አንዱ ገጽታ ነው። (ኢሳይያስ 46:9, 10) ይሁን እንጂ አምላክ ገደብ የለሽ ኃይሉን ሁልጊዜ ሙሉ በሙሉ መጠቀም እንደማያስፈልገው ሁሉ አስቀድሞ የማወቅ ችሎታውንም ሁልጊዜ መጠቀም አያስፈልገውም። ይሖዋ ይህንን ችሎታውን መቼ መጠቀም እንዳለበት በጥበብ ይወስናል። ይህንን ችሎታውን የሚጠቀመው ምክንያታዊ ብሎም ከሁኔታዎች አንጻር ተገቢ እንደሆነ በሚሰማው ጊዜ ነው።
የወደፊቱን ሁኔታ ከማወቅ የመቆጠብ ችሎታን አንድ ዘመናዊ የኤሌክትሮኒክ መሣሪያ ካለው ችሎታ ጋር ልናመሳስለው እንችላለን። በቪዲዮ የተቀዳ የስፖርት ውድድር የሚመለከት አንድ ሰው ከፈለገ ፊልሙን ወደፊት በማስኬድ የጨዋታውን የመጨረሻ ውጤት ማየት ይችላል። ይሁንና ይህ ሰው ጨዋታውን ለማየት የግድ በዚህ መንገድ መጀመር የለበትም። ይህ ሰው ጨዋታውን ከመጀመሪያው አንስቶ ለማየት ቢፈልግ ማን ሊወቅሰው ይችላል? በተመሳሳይም ፈጣሪ “የመጨረሻውን ውጤት” ላለመመልከት እንደመረጠ ከሁኔታው መረዳት ይቻላል። ከዚህ ይልቅ ምድራዊ ልጆቹ የሚያሳዩትን ምግባር በጊዜ ሂደት ለመመልከት መርጦ ነበር።
ቀደም ሲል እንደተገለጸው ይሖዋ ጥበቡን ተጠቅሞ የመጀመሪያዎቹን ሰዎች የፈጠረው አንድን ሥራ እንዲያከናውን አስቀድሞ ፕሮግራም ከሚደረግ ሮቦት ጋር በሚመሳሰል መልኩ አይደለም። ከዚህ ይልቅ በፍቅር ተነሳስቶ ነፃ ምርጫ ሰጥቷቸዋል። የመጀመሪያዎቹ ሰዎች ትክክለኛውን መንገድ በመምረጥ ፍቅራቸውን፣ አመስጋኝነታቸውንና ታዛዥነታቸውን ማሳየት ይችሉ ነበር፤ ይህ ደግሞ ለራሳቸውም ሆነ ለሰማዩ አባታቸው ተጨማሪ ደስታ ያመጣ ነበር።—ምሳሌ 27:11፤ ኢሳይያስ 48:18
አምላክ አስቀድሞ የማወቅ ችሎታውን ያልተጠቀመባቸው ጊዜያት እንዳሉ የሚጠቁሙ በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች ይገኛሉ። ለምሳሌ ያህል፣ ታማኙ አብርሃም ልክ ልጁን መሥዋዕት ሊያደርግ ሲል ይሖዋ “አንድ ልጅህን ለእኔ አልከለከልህምና እግዚአብሔርን የምትፈራ እንደ ሆንህ አሁን አውቄአለሁ” ብሎት ነበር። (ዘፍጥረት 22:12 የ1954 ትርጉም) በሌላ በኩል ደግሞ አንዳንድ ሰዎች በፈጸሙት መጥፎ ተግባር ‘ያዘነባቸው’ ጊዜያት ነበሩ። እነዚህ ግለሰቦች የሚያደርጉትን ነገር አስቀድሞ የሚያውቅ ቢሆን ኖሮ እንዲህ ዓይነት ስሜት ሊሰማው ይችል ነበር?—መዝሙር 78:40, 41፤ 1 ነገሥት 11:9, 10
ከዚህ በመነሳት በጥበቡ ተወዳዳሪ የሌለው አምላክ የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን ኃጢአት እንደሚሠሩ ለማወቅ ሲል አስቀድሞ የማወቅ ችሎታውን አልተጠቀመም ብሎ መደምደም ምክንያታዊ ነው። ይሖዋ አስቀድሞ በማወቅ ችሎታው ተጠቅሞ አዳምና ሔዋን ምን እንደሚያጋጥማቸው ያውቅ ነበር ብሎ ማሰብ የሰው ልጆች ትርጉም የለሽ ሕይወት እንደሚመሩ እያወቀ እነሱን ወደ ሕልውና አምጥቷቸዋል ማለት ይሆናል፤ እሱ ግን እንዲህ ዓይነት ሞኝ አምላክ አይደለም።
“አምላክ ፍቅር ነው”
ኃጢአትንና ሞትን ጨምሮ መጥፎ ውጤቶችን ያስከተለው ዓመፅ በኤደን እንዲቀሰቀስ ያደረገው የአምላክ ጠላት የሆነው ሰይጣን ነው። በዚህ መንገድ ሰይጣን “ነፍሰ ገዳይ” ሆኗል። በተጨማሪም “ውሸታምና የውሸት አባት” መሆኑ ተረጋግጧል። (ዮሐንስ 8:44) መጥፎ ዝንባሌ ያለው እሱ ሆኖ ሳለ ሰዎች ለአፍቃሪው ፈጣሪያችን እንዲህ ያለ ስም እንዲሰጡት ለማድረግ ይጥራል። የሰው ልጆች ኃጢአት ላይ ለመውደቃቸው ምክንያቱ እሱ መሆኑ እንዳይታወቅበት ጥፋቱን በይሖዋ ላይ ያላክካል።
ይሖዋ አዳምና ሔዋን ኃጢአት እንደሚሠሩ አስቀድሞ ላለማወቅ እንዲመርጥ ያደረገው ትልቁ ምክንያት ለእነሱ ያለው ፍቅር ነው። የአምላክ ዋነኛ ባሕርይ ፍቅር ነው። አንደኛ ዮሐንስ 4:8 “አምላክ ፍቅር ነው” ይላል። ፍቅር መልካሙን እንጂ መጥፎ የሆነውን ነገር አያስብም። እንዲሁም በሌሎች ውስጥ ያለውን ጥሩ ነገር ለማየት ይጥራል። አዎን፣ ይሖዋ አምላክ ፍቅር ስለሆነ የመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት ከሁሉ የተሻለውን ነገር እንዲያገኙ ይፈልግ ነበር።
የአምላክ ምድራዊ ልጆች ጥበብ የጎደለው ውሳኔ የማድረግ ምርጫ ቢኖራቸውም አፍቃሪው አምላካችን ፍጹም ለሆኑት ፍጥረታቱ አፍራሽ አመለካከት የመያዝ ወይም እነሱን በጥርጣሬ ዓይን የመመልከት ዝንባሌ አልነበረውም። ለሕይወታቸው የሚያስፈልጋቸውን ነገር አሟልቶ የሰጣቸው ከመሆኑም ሌላ ማወቅ የሚገባቸውን አንድም ሳያስቀር ነግሯቸው ነበር። እንግዲያው አምላክ፣ ሰዎች ከዓመፅ ይልቅ በፍቅር ተነሳስተው እሱን እንዲታዘዙት መጠበቁ ተገቢ ነው። አምላክ አዳምና ሔዋን ለእሱ ታማኝ መሆን እንደሚችሉ ያውቅ ነበር፤ በኋላ ላይ እንደታየው እንደ አብርሃም፣ ኢዮብና ዳንኤል ያሉ ፍጽምና የጎደላቸው ሰዎች እንኳ ለአምላክ ታማኝ መሆን እንደሚቻል አስመሥክረዋል።
ኢየሱስ “በአምላክ ዘንድ . . . ሁሉ ነገር ይቻላል” ብሏል። (ማቴዎስ 19:26) ይህ የሚያጽናና ሐሳብ ነው። ይሖዋ ከፍቅር በተጨማሪ ሌሎች ዋና ዋና ባሕርያት ማለትም ፍትሕ፣ ጥበብና ኃይል ያሉት መሆኑ የኃጢአትና የሞት ውጤቶችን በሙሉ በተገቢው ጊዜ የማጥፋት አቅሙም ሆነ ፍላጎቱ እዳለው ማረጋገጫ ይሰጠናል።—ራእይ 21:3-5
እስካሁን እንደተመለከትነው ይሖዋ የመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት ኃጢአት እንደሚሠሩ አስቀድሞ አያውቅም ነበር። አምላክ፣ ሰዎች ዓመፀኞች መሆናቸውና በዚህም ምክንያት ለመከራ መዳረጋቸው ቢያሳዝነውም ይህ ጊዜያዊ ሁኔታ ለምድርና በውስጧ ለሚኖሩት የሰው ልጆች ያለውን ዘላለማዊ ዓላማ ዳር ከማድረስ ሊያግደው እንደማይችል ያውቃል። ይህ ዓላማ ምን እንደሆነና ክብራማ ፍጻሜውን ማግኘቱ አንተን የሚጠቅምህ እንዴት እንደሆነ ይበልጥ ለማወቅ ጥረት እንድታደርግ እናበረታታሃለን።a
[የግርጌ ማስታወሻ]
a አምላክ ለምድር ስላለው ዓላማ የበለጠ መረጃ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 3 ተመልከት።
[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
ይሖዋ የመጀመሪያዎቹን ሰዎች የፈጠረው አንድን ሥራ እንዲያከናውን አስቀድሞ ፕሮግራም ከሚደረግ ሮቦት ጋር በሚመሳሰል መልኩ አይደለም
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳበ]
አምላክ አዳምና ሔዋን ለእሱ ታማኝ መሆን እንደሚችሉ ያውቅ ነበር