የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w11 3/15 ገጽ 12-16
  • መጨረሻው በቀረበ መጠን በይሖዋ ታመኑ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • መጨረሻው በቀረበ መጠን በይሖዋ ታመኑ
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2011
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • መጥፎ ነገር ለማድረግ ስትፈተኑ በአምላክ ታመኑ
  • ሰዎች ግዴለሽ ሲሆኑና ተቃውሞ ሲያጋጥማችሁ በአምላክ ታመኑ
  • የሚያስጨንቁ ነገሮች ሲያጋጥሟችሁ በአምላክ ታመኑ
  • “የአምላክ ሰላም” ልባችሁን ይጠብቅ
  • በይሖዋ ላይ ያለህን እምነት አጠናክር
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2001
  • ደስተኛ ሕይወት ለመምራት መተማመን አስፈላጊ ነው
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2003
  • ወንድሞቻችሁን ማመን ትችላላችሁ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2022
  • በፍጹም ልባችሁ በይሖዋ ታመኑ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2003
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2011
w11 3/15 ገጽ 12-16

መጨረሻው በቀረበ መጠን በይሖዋ ታመኑ

“በእግዚአብሔር [“በይሖዋ፣” NW] ለዘላለም ታመኑ።”​—ኢሳ. 26:4

1. በአምላክ አገልጋዮችና በዓለም ላይ ባሉ ሰዎች መካከል ምን ልዩነት ይታያል?

በምንኖርበት ዓለም ውስጥ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በማን ወይም በምን እንደሚታመኑ ግራ ተጋብተዋል፤ ይህም የሆነው በተደጋጋሚ ጊዜ በደል ስለደረሰባቸው ወይም የጠበቁት ነገር ሳይፈጸም በመቅረቱ ስሜታቸው ስለተጎዳ ሊሆን ይችላል። የይሖዋ አገልጋዮች ያሉበት ሁኔታ ግን ከዚህ ፍጹም የተለየ ነው! በአምላካዊ ጥበብ ስለሚመሩ በዚህ ዓለም ወይም በዓለም “ገዦች” መታመን ከንቱ እንደሆነ ያውቃሉ። (መዝ. 146:3) ከዚህ ይልቅ ይሖዋ እንደሚወዳቸውና ምንጊዜም ቃሉን እንደሚጠብቅ ስለሚያውቁ የአሁኑንም ሆነ የወደፊቱን ሕይወታቸውን ለይሖዋ በአደራ ይሰጣሉ።​—ሮም 3:4፤ 8:38, 39

2. ኢያሱ አምላክ እምነት የሚጣልበት መሆኑን የገለጸው እንዴት ነው?

2 በጥንት ዘመን የኖረው ኢያሱ፣ አምላክ እምነት የሚጣልበት መሆኑን አስረግጦ ተናግሯል። ኢያሱ በሕይወቱ መገባደጃ አካባቢ ለእስራኤላውያን እንዲህ ብሏቸው ነበር፦ “አምላካችሁ እግዚአብሔር ከሰጣችሁ መልካም ተስፋ ሁሉ አንዲቱን እንኳ እንዳላስቀረባችሁ፣ በፍጹም ልባችሁ በፍጹም ነፍሳችሁ ታውቃላችሁ፤ አንዱም ሳይቀር ሁሉም ተፈጽሞአል።”​—ኢያሱ 23:14

3. መለኮታዊው ስም ስለ አምላክ ምን ይገልጻል?

3 ይሖዋ ቃሉን የሚጠብቀው ሕዝቡን ስለሚወድ ብቻ ሳይሆን በተለይ ለስሙ ሲል ነው። (ዘፀ. 3:14፤ 1 ሳሙ. 12:22) በጆሴፍ ብርያንት ሮዘርሃም የተዘጋጀው ዚ ኢምፋሳይዝድ ባይብል የተባለው ትርጉም በመቅድሙ ላይ ስለ መለኮታዊው ስም የሚከተለውን ሐሳብ ሰጥቷል፦ መለኮታዊው ስም፣ አምላክ የገባውን ቃል ለመፈጸም ሲል ማንኛውንም ነገር መሆን እንደሚችል ያመለክታል። ስሙን ስንሰማ አምላክ የተናገረውን ነገር ምንጊዜም እንደሚፈጽም እናስባለን። አምላክ በማንኛውም ጊዜና በየትኛውም ቦታ ማድረግ ያለበትን ነገር ማድረግ እንደሚችልና ምንም የሚያቅተው ነገር እንደሌለ ያሳያል። ምንጊዜም ቢሆን ለስሙ ታማኝ ነው፤ በስሙ ፈጽሞ አያፍርም።

4. (ሀ) ኢሳይያስ 26:4 ምን እንድናደርግ ያሳስበናል? (ለ) በዚህ ርዕስ ውስጥ የትኞቹን ነጥቦች እንመለከታለን?

4 እስቲ ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ፦ ‘ስለ ይሖዋ ያለኝ እውቀት በእሱ ሙሉ በሙሉ ለመታመን የሚያስችለኝ ነው? ከአምላክ ቁጥጥር ውጭ የሆነ ነገር እንደሌለ በመገንዘብ የወደፊቱን ጊዜ በልበ ሙሉነት እጠባበቃለሁ?’ ኢሳይያስ 26:4 “በእግዚአብሔር ለዘላለም ታመኑ፤ ጌታ እግዚአብሔር የዘላለም ዐምባ ነውና” ይላል። አምላክ በጥንት ጊዜ እንዳደረገው በዛሬው ጊዜ ከሰው ልጆች ጋር በተያያዘ ተአምራዊ ነገሮችን እንደማይፈጽም የታወቀ ነው። ያም ሆኖ ይሖዋ “የዘላለም ዐምባ” በመሆኑ “ለዘላለም” ልንታመንበት እንችላለን። እምነት የሚጣልበት አምላካችን በዛሬው ጊዜ ታማኝ አምላኪዎቹን የሚደግፋቸው እንዴት ነው? ሦስት መንገዶችን እንመልከት፦ ፈተናን ለመቋቋም የእሱን እርዳታ በምንሻበት ጊዜ ያጠናክረናል፣ ሰዎች ግዴለሽ ሲሆኑ ወይም ቀጥተኛ ተቃውሞ ሲያጋጥመን ያበረታናል እንዲሁም የሚያስጨንቁ ነገሮች ሲደራረቡብን ደግፎ ያቆመናል። እነዚህን ነጥቦች ስንመረምር በይሖዋ ላይ ያለህን እምነት ማጠናከር የምትችለው እንዴት እንደሆነ ለማሰብ ሞክር።

መጥፎ ነገር ለማድረግ ስትፈተኑ በአምላክ ታመኑ

5. በአምላክ ላይ መታመን ከባድ የሚሆንብን መቼ ነው?

5 ገነትን ወይም ትንሣኤን የመሳሰሉ የምንጓጓላቸውን ነገሮች በተመለከተ ይሖዋ በሰጠን ተስፋ መታመን አንድ ነገር ነው። የሥነ ምግባር መሥፈርቶቹን በተመለከተ በይሖዋ መታመን ደግሞ ሌላ ነገር ነው፤ የይሖዋን መንገዶችና መሥፈርቶች መከተል ትክክለኛና የላቀ ደስታ የሚያስገኝ መሆኑን ከልባችን አምነን መቀበል ከባድ ሊሆንብን ይችላል። ንጉሥ ሰለሞን እንዲህ የሚል ምክር ሰጥቷል፦ “በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር ታመን፤ በራስህ ማስተዋል አትደገፍ፤ በመንገድህ ሁሉ እርሱን ዕወቅ፤ እርሱም ጐዳናህን ቀና ያደርገዋል።” (ምሳሌ 3:5, 6) “መንገድህ” እና “ጐዳናህ” የሚሉትን ቃላት ልብ በል። በእርግጥም ከክርስቲያናዊ ተስፋችን ጋር በተያያዘ ብቻ ሳይሆን በመላ ሕይወታችን በአምላክ እንደምንታመን ማሳየት ይኖርብናል። ፈተናዎች ሲያጋጥሙን በአምላክ ላይ እንደምንታመን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

6. መጥፎ ሐሳቦችን ከማውጠንጠን ለመራቅ ያደረግነውን ቁርጥ ውሳኔ ማጠናከር የምንችለው እንዴት ነው?

6 ከክፋት ድርጊቶች መራቅ የሚጀምረው ከአእምሯችን ነው። (ሮም 8:5⁠ን እና ኤፌሶን 2:3⁠ን አንብብ።) ታዲያ መጥፎ ሐሳቦችን ከማውጠንጠን ለመራቅ ያደረግከውን ቁርጥ ውሳኔ ማጠናከር የምትችለው እንዴት ነው? የሚከተሉትን አምስት መንገዶች ተመልከት፦ 1. በጸሎት አማካኝነት የአምላክን እርዳታ ጠይቅ። (ማቴ. 6:9, 13) 2. ይሖዋ የሚነግራቸውን ስላዳመጡና እሱን ከመስማት ዘወር ስላሉ ግለሰቦች በሚገልጹ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ላይ አሰላስል። ከዚያም እነዚህ ግለሰቦች መጨረሻቸው ምን እንደሆነ ለማሰብ ሞክር።a (1 ቆሮ. 10:8-11) 3. ኃጢአት መሥራት በአንተም ሆነ በምትወዳቸው ሰዎች ላይ የሚያስከትለውን ሥነ ልቦናዊና ስሜታዊ ቀውስ አስብ። 4. አምላክ አንድ አገልጋዩ ከባድ ኃጢአት ሲፈጽም ምን እንደሚሰማው ለማሰብ ሞክር። (መዝሙር 78:40, 41⁠ን አንብብ።) 5. ይሖዋ፣ አንድ ታማኝ አገልጋዩ ከሰዎች ጋርም ሆነ ብቻውን በሚሆንበት ጊዜ ከክፋት ርቆ ትክክል የሆነውን ነገር ሲያደርግ ሲመለከት ልቡ ምን ያህል በደስታ እንደሚሞላ በዓይነ ሕሊናህ ለመሳል ሞክር። (መዝ. 15:1, 2፤ ምሳሌ 27:11) አንተም በይሖዋ እንደምትታመን ማሳየት ትችላለህ።

ሰዎች ግዴለሽ ሲሆኑና ተቃውሞ ሲያጋጥማችሁ በአምላክ ታመኑ

7. ኤርምያስ ምን ዓይነት ፈተና አጋጥሞታል? ምን ተሰምቶትስ ያውቃል?

7 በርካታ ወንድሞቻችን የሚያገለግሉት ጽናት በሚጠይቁ በጣም አስቸጋሪ በሆኑ ክልሎች ውስጥ ነው። ነቢዩ ኤርምያስ ያገለገለው እንዲህ ባለ ክልል ውስጥ ነበር፤ በወቅቱ የይሁዳ መንግሥት የሚጠፋበት ጊዜ ተቃርቦ የነበረ ሲሆን በአገሪቱ ሁከት ሰፍኖ ነበር። ኤርምያስ የአምላክን የፍርድ መልእክት በታዛዥነት ያውጅ ስለነበር በአምላክ ላይ ያለው እምነት በየዕለቱ ይፈተን ነበር። ታማኝ የነበረው ጸሐፊው ባሮክ እንኳ በአንድ ወቅት እንደደከመ ገልጾ ነበር። (ኤር. 45:2, 3) ታዲያ ኤርምያስ በዚህ ጊዜ ተስፋ ቆርጦ ነበር? እርግጥ ነው፣ በጭንቀት የተዋጠባቸው ጊዜያት ነበሩ። “የተወለድሁባት ዕለት የተረገመች ትሁን፤ . . . ችግርና ሐዘንን ለማየት፣ ዘመኔንም በውርደት ለመፈጸም፣ ለምን ከማሕፀን ወጣሁ?” በማለት ተናግሮ ነበር።​—ኤር. 20:14, 15, 18

8, 9. ከ⁠ኤርምያስ 17:7, 8 እና ከ⁠መዝሙር 1:1-3 ጋር በሚስማማ መልኩ መልካም ፍሬ ማፍራታችንን ለመቀጠል ምን ማድረግ አለብን?

8 ይሁንና ኤርምያስ ተስፋ አልቆረጠም። በይሖዋ መታመኑን ቀጥሏል። በዚህም የተነሳ ይህ ታማኝ ነቢይ በኤርምያስ 17:7, 8 ላይ የሚገኘው ይሖዋ የገባው ቃል ሲፈጸም ተመልክቷል፦ “በእግዚአብሔር የሚታመን፣ መታመኛውም እግዚአብሔር የሆነ ሰው ቡሩክ ነው። በውሃ ዳር እንደ ተተከለ፣ ሥሩንም ወደ ወንዝ እንደ ሰደደ ዛፍ ነው፣ ሙቀት ሲመጣ አይፈራም፤ ቅጠሉም ዘወትር እንደለመለመ ነው፤ በድርቅ ዘመን አይሠጋም፤ ፍሬ ማፍራቱንም አያቋርጥም።”

9 “በውሃ ዳር እንደ ተተከለ” ወይም በመስኖ እንደሚለማ የለመለመ የፍራፍሬ ዛፍ ሁሉ ኤርምያስም ፈጽሞ ‘ፍሬ ማፍራቱን አላቋረጠም።’ በዙሪያው የነበሩ ፌዘኛ የሆኑ ክፉ ሰዎች ተጽዕኖ እንዲያደርጉበት አልፈቀደም። ከዚህ ይልቅ ሕይወት ሰጪ የሆነው “ውሃ” ምንጭ ከሆነው ከይሖዋ ጋር በመጣበቅ እሱ የነገረውን ነገር ሁሉ ተግባራዊ አድርጓል። (መዝሙር 1:1-3⁠ን አንብብ፤ ኤር. 20:9) ኤርምያስ ለሁላችን በተለይም በአስቸጋሪ ክልል ለምናገለግል ክርስቲያኖች እንዴት ያለ ግሩም ምሳሌ ነው! አንተም የአገልግሎት ክልልህ እንደዚህ ከሆነ በይሖዋ ሙሉ በሙሉ መታመንህን ቀጥል፤ እሱም ‘ስለ ስሙ በይፋ ስታውጅ’ እንድትጸና ይረዳሃል።​—ዕብ. 13:15

10. ምን በረከቶች አሉን? ራሳችንን ምን ብለን መጠየቅ ይኖርብናል?

10 በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት የሚያጋጥሙንን አስቸጋሪ ሁኔታዎች መቋቋም እንድንችል እኛን ለመርዳት ይሖዋ በርካታ ነገሮችን ሰጥቶናል። ከእነዚህም መካከል በየጊዜው በተለያዩ ቋንቋዎች በትክክል በመተርጎም ላይ ያለው ሙሉው የአምላክ ቃል ይገኝበታል። ይሖዋ በታማኝና ልባም ባሪያ አማካኝነት ወቅታዊ የሆነ መንፈሳዊ ምግብ አትረፍርፎ ሰጥቶናል። በጉባኤና በትላልቅ ስብሰባዎች ላይ የምናገኛቸውን ድጋፍ የሚሆኑ በርካታ የእምነት ባልንጀሮቻችንንም መጥቀስ ይቻላል። በእነዚህ ዝግጅቶች ሙሉ በሙሉ ትጠቀማለህ? እንዲህ የሚያደርጉ ሁሉ “ከልብ በመነጨ ደስታ ይዘምራሉ።” ይሁንና አምላክን የማይሰሙ ሁሉ ‘ልባቸው በማዘኑ ይጮኻሉ፤ መንፈሳቸው በመሰበሩም ወዮ ይላሉ።’​—ኢሳ. 65:13, 14

የሚያስጨንቁ ነገሮች ሲያጋጥሟችሁ በአምላክ ታመኑ

11, 12. የሚያጋጥሙንን ችግሮች የምንይዝበትን መንገድ በተመለከተ የጥበብ አካሄድ የሚሆነው ምንድን ነው?

11 በትንቢት እንደተነገረው መከራ የሰው ልጆችን እንደ ጎርፍ እያጥለቀለቃቸው ነው ማለት ይቻላል። (ማቴ. 24:6-8፤ ራእይ 12:12) ቃል በቃል ጎርፍ ሲከሰት ብዙውን ጊዜ ሰዎች የሚወስዱት እርምጃ ከፍ ወዳለ ቦታ መሄድ ለምሳሌ የቤት ጣሪያ ላይ መውጣት ሊሆን ይችላል። በተመሳሳይም ችግሮች ዓለምን እያጥለቀለቋት ሲሄዱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ከችግሩ ለማምለጥ ከፍ ተደርገው ወደሚታዩ የገንዘብ፣ የፖለቲካ ወይም የሃይማኖት ተቋማት ዘወር ይላሉ፤ እንዲሁም በሳይንስና ቴክኖሎጂ ይታመናሉ። ያም ሆኖ ከእነዚህ መካከል አንዳቸውም ቢሆኑ እውነተኛ ጥበቃ አያስገኙም። (ኤር. 17:5, 6) በሌላ በኩል ግን የይሖዋ አገልጋዮች “የዘላለም ዐምባ” የሆነ አስተማማኝ መጠጊያ አላቸው። (ኢሳ. 26:4) መዝሙራዊው ስለ ይሖዋ ሲናገር “ዐለቴና መድኀኒቴ እርሱ ብቻ ነው፤ መጠጊያዬም እርሱ ነው” ብሏል። (መዝሙር 62:6-9⁠ን አንብብ።) ይህ ዐለት መጠጊያችን እንዲሆን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?

12 አብዛኛውን ጊዜ ከሰብዓዊ ጥበብ ጋር የሚቃረነውን የአምላክን ቃል በተግባር ስናውል ከይሖዋ ጋር እንጣበቃለን። (መዝ. 73:23, 24) ለምሳሌ በሰብዓዊ ጥበብ የሚመሩ ሰዎች እንዲህ ይሉ ይሆናል፦ ‘ዘላለም አትኖር፤ ሕይወትህን በደንብ ብትጠቀምበት አይሻልህም?’ ‘ጥሩ ሥራ ለመያዝ መጣር አለብህ።’ ‘ገንዘብ በደንብ አጠራቅም።’ ‘ያማረህን ነገር ሁሉ ግዛ።’ ‘ዓለምን በመዞር አስደሳች ጊዜ አሳልፍ።’ በሌላ በኩል ግን መለኮታዊ ጥበብ፣ የሚከተለውን ምክር ተግባራዊ እንድናደርግ ያበረታታናል፦ “በዓለም የሚጠቀሙ ሙሉ በሙሉ እንደማይጠቀሙበት ይሁኑ፤ ምክንያቱም የዚህ ዓለም ትእይንት እየተለዋወጠ ነው።” (1 ቆሮ. 7:31) በተመሳሳይም ኢየሱስ ምንጊዜም ለይሖዋ የምናቀርበውን አምልኮ በማስቀደም ፍጹም አስተማማኝ በሆነ ስፍራ ይኸውም “በሰማይ . . . ሀብት” እንድናከማች መክሮናል።​—ማቴ. 6:19, 20

13. አንደኛ ዮሐንስ 2:15-17⁠ን በአእምሯችን በመያዝ ራሳችንን ምን ብለን መጠየቅ ይኖርብናል?

13 “ዓለምንም” ሆነ “በዓለም ውስጥ ያሉትን ነገሮች” በተመለከተ ያለህ አመለካከት በይሖዋ ሙሉ በሙሉ እንደምትታመን ያሳያል? (1 ዮሐ. 2:15-17) ዓለም ከሚያቀርባቸው ነገሮች የበለጠ ለመንፈሳዊ ሀብትና ለተለያዩ የአገልግሎት መብቶች ትልቅ ቦታ ትሰጣለህ? (ፊልጵ. 3:8) ምንጊዜም “ዓይንህ አጥርቶ የሚያይ” እንዲሆን ለማድረግ ትጥራለህ? (ማቴ. 6:22) እርግጥ ነው፣ በተለይ የምታስተዳድረው ቤተሰብ ካለህ ግዴለሽ ወይም ኃላፊነት የማይሰማህ ሰው እንድትሆን አምላክ አይፈልግም። (1 ጢሞ. 5:8) ያም ቢሆን ግን አገልጋዮቹ መጥፊያው በቀረበው የሰይጣን ዓለም ላይ ሳይሆን በእሱ ላይ ሙሉ በሙሉ እንዲታመኑ ይፈልጋል።​—ዕብ. 13:5

14-16. አንዳንዶች ‘ዓይናቸው አጥርቶ የሚያይ’ እንዲሆን በማድረጋቸውና ምንጊዜም ለይሖዋ የሚያቀርቡትን አምልኮ በማስቀደማቸው የተጠቀሙት እንዴት ነው?

14 ሦስት ትንንሽ ልጆች ያሏቸውን ሪቻርድን እና ሩትን እንደ ምሳሌ እንመልከት። ሪቻርድ እንዲህ ብሏል፦ “ለይሖዋ የበለጠ ማድረግ እንደምችል ውስጤ ይነግረኝ ነበር። የተመቻቸ ሕይወት ነበረኝ፤ ሆኖም ለአምላክ የምሰጠው ትርፌን እንደሆነ ይሰማኝ ነበር። በወቅቱ አገሪቱ የኢኮኖሚ ቀውስ ውስጥ የምትገኝ ቢሆንም እኔና ሩት ስለ ጉዳዩ ከጸለይንና ወጪያችንን ካሰላን በኋላ የምሠራባቸውን ቀናት በመቀነስ በሳምንት አራት ቀን ብቻ ለመሥራት እንዲፈቅድልኝ ኃላፊዬን ለመጠየቅ ተስማማን። ኃላፊዬ ጥያቄዬን የተቀበለው ሲሆን በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ በአዲሱ ፕሮግራም መሠረት ሥራዬን ማከናወን ጀመርኩ።” ሪቻርድ በአሁኑ ወቅት ምን ይሰማዋል?

15 እንዲህ ብሏል፦ “የማገኘው ገቢ ከቀድሞው 20 በመቶ ያነሰ ቢሆንም በዓመት ውስጥ ከቤተሰቤ ጋር የምሆንባቸውና ልጆቼን የማሠለጥንባቸው 50 ተጨማሪ ቀናት አግኝቻለሁ። በመስክ አገልግሎት የማሳልፈውን ሰዓት በእጥፍ ማሳደግና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቼን ቁጥር በሦስት እጥፍ መጨመር ችያለሁ፤ እንዲሁም ጉባኤውን ይበልጥ የማገልገል መብት አግኝቻለሁ። ልጆቻችንን በመንከባከብ ረገድ ሩትን ከበፊቱ የበለጠ ስለማግዛት በተለያዩ ጊዜያት ረዳት አቅኚ መሆን ችላለች። ሁኔታዎች እስከፈቀዱልኝ ድረስ በዚሁ ለመቀጠል ቆርጫለሁ።”

16 ከሴት ልጃቸው ጋር የሚኖሩት ሮይ እና ፐቲና በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ለመሳተፍ ሲሉ ሰብዓዊ ሥራ የሚሠሩባቸውን ቀናት ቀንሰዋል። ሮይ እንዲህ ብሏል፦ “እኔ በሳምንት ሦስት ቀን፣ ፐቲና ደግሞ ሁለት ቀን ትሠራለች። ግቢ ያለው ትልቅ ቤት የነበረን ቢሆንም እሱን ትተን ለመንከባከብ በሚቀል አፓርታማ ውስጥ መኖር ጀመርን። ልጆች ከመውለዳችን በፊት በአቅኚነት እናገለግል የነበረ ሲሆን የአቅኚነት መንፈስ ከውስጣችን ጨርሶ አልጠፋም ነበር። በመሆኑም ልጆቻችን ሲያድጉ እንደገና ወደ ሙሉ ጊዜ አገልግሎት ገባን። ያገኘነው በረከት በገንዘብ ሊተመን የማይችል ነው።”

“የአምላክ ሰላም” ልባችሁን ይጠብቅ

17. ነገ ምን እንደሚሆን የማይታወቅ ቢሆንም ቅዱሳን መጻሕፍት በግለሰብ ደረጃ አንተን ያጽናኑህ እንዴት ነው?

17 ሁላችንም “መጥፎ ጊዜና ያልተጠበቁ ክስተቶች” ስለሚያጋጥሙን ነገ ምን ሊመጣ እንደሚችል አናውቅም። (መክ. 9:11 NW) ይሁንና ነገ ስለሚሆነው ነገር በእርግጠኝነት ማወቅ አለመቻላችን ዛሬ የአእምሮ ሰላም እንድናጣ ሊያደርገን አይገባም፤ ምክንያቱም ከአምላክ ጋር የጠበቀ ዝምድና በመመሥረት የሚገኘው የደኅንነት ስሜት እንደሌላቸው ሰዎች አይደለንም። (ማቴ. 6:34) ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ስለ ምንም ነገር አትጨነቁ፤ ከዚህ ይልቅ ስለ ሁሉም ነገር በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር ልመናችሁን ለአምላክ አቅርቡ፤ ከማሰብ ችሎታ ሁሉ በላይ የሆነው የአምላክ ሰላም በክርስቶስ ኢየሱስ አማካኝነት ልባችሁንና አእምሯችሁን ይጠብቃል።”​—ፊልጵ. 4:6, 7

18, 19. አምላክ በየትኞቹ መንገዶች ያበረታታናል? ምሳሌ ስጥ።

18 በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ለሚገኙ በርካታ ወንድሞችና እህቶች ይሖዋ ውስጣዊ መረጋጋትና ሰላም ሰጥቷቸዋል። አንዲት እህት እንዲህ ብላለች፦ “አንድ የቀዶ ሕክምና ባለሞያ፣ ደም እንድወስድ በተደጋጋሚ ጊዜ ጫና ያደርግብኝ ነበር። በአንድ ወቅት ወደ እኔ ሲመጣ ከአፉ የወጣው የመጀመሪያ ነገር ‘ደም አልወስድም ብሎ ነገር ደግሞ ምንድን ነው?’ የሚል ነበር፤ እንዲህ ዓይነት አባባሎች የተለመዱ ነበሩ። በዚያ ወቅትም ሆነ በሌሎች ጊዜያት በልቤ ወደ ይሖዋ እጸልይ የነበረ ሲሆን እሱም ሰላም ሰጥቶኛል። እንደ ዓለት የሆንኩ ያህል ተሰማኝ። የደሜ መጠን በመውረዱ የተነሳ ድካም ቢሰማኝም አቋሜን በተመለከተ ከቅዱሳን መጻሕፍት ግልጽ ማስረጃ ማቅረብ ችዬ ነበር።”

19 አምላክ፣ በሚያበረታቱን የእምነት ባልንጀሮቻችን ወይም በተገቢው ጊዜ በሚመጣ መንፈሳዊ ምግብ አማካኝነት አስፈላጊውን ድጋፍ የሚያደርግልን ጊዜ አለ። አንድ ወንድም ወይም አንዲት እህት “ይህ ርዕስ የወጣው ልክ በሚያስፈልገኝ ሰዓት ነው። የተጻፈው ለእኔ ነው!” በማለት ሲናገሩ ሰምተህ ይሆናል። ያለንበት ሁኔታ ወይም የሚያስፈልገን ነገር ምንም ይሁን ምን ይሖዋ በእሱ እስከታመንን ድረስ እንደሚወደን የሚያሳይ ነገር ያደርግልናል። ደግሞም በስሙ የምንጠራ የእሱ “በጎች” ነን።​—መዝ. 100:3፤ ዮሐ. 10:16፤ ሥራ 15:14, 17

20. የሰይጣን ዓለም በሚጠፋበት ጊዜ የይሖዋ አገልጋዮች ያለ ሥጋት የሚቀመጡት ለምንድን ነው?

20 በፍጥነት እየቀረበ ባለው “በእግዚአብሔር የቍጣ ቀን” የሰይጣን ዓለም የሚታመንበት ነገር ሁሉ ድምጥማጡ ይጠፋል። ወርቅ፣ ብር ወይም ሌላ ውድ ነገር ምንም ፋይዳ አይኖረውም። (ሶፎ. 1:18፤ ምሳሌ 11:4) ብቸኛው መጠጊያ “የዘላለም ዐምባ” የሆነው አምላካችን ነው። (ኢሳ. 26:4) እንግዲያው በታዛዥነት በይሖዋ የጽድቅ ጎዳና በመመላለስ፣ ሰዎች ግዴለሽ ቢሆኑም ወይም ተቃውሞ ቢያጋጥመንም የመንግሥቱን መልእክት በማወጅ እንዲሁም ጭንቀታችንን ሁሉ በእሱ ላይ በመጣል በአሁኑ ጊዜ ሙሉ በሙሉ በይሖዋ እንደምንታመን እናሳይ። እነዚህን ነገሮች የምናደርግ ከሆነ በእርግጥም ‘ክፉን ሳንፈራ ያለ ሥጋት እንቀመጣለን።’​—ምሳሌ 1:33

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ‘ከአምላክ ፍቅር አትውጡ’ የተባለውን መጽሐፍ ከገጽ 102-106 ተመልከት።

ልታብራራ ትችላለህ?

• መጥፎ ነገር እንድንሠራ ስንፈተን፣

• ሰዎች ግዴለሽ ሲሆኑ ወይም ተቃውሞ ሲያጋጥመን፣

• የሚያስጨንቁን ነገሮች ሲያጋጥሙን

በአምላክ መታመን የምንችለው እንዴት ነው?

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የአምላክን መመሪያዎች መጠበቅ ደስታ ያስገኛል

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ይሖዋ “የዘላለም ዐምባ ነው”

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ