የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w11 6/1 ገጽ 9-11
  • እንደ አቅም መኖር የሚቻለው እንዴት ነው?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • እንደ አቅም መኖር የሚቻለው እንዴት ነው?
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2011
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ጠቃሚ የሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች
  • ከሌሎች መማር
  • እንደ አቅምህ መኖር ትችላለህ
  • ጥሩ የገንዘብ አጠቃቀም ችሎታ አዳብር
    ንቁ!—2009
  • የገንዘብ አያያዝ
    ንቁ!—2019
  • የገንዘብ ችግርና ዕዳ​—መጽሐፍ ቅዱስ ሊረዳህ ይችላል?
    የመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው
  • አባካኝ ከመሆን መቆጠብ የምችለው እንዴት ነው?
    ንቁ!—2006
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2011
w11 6/1 ገጽ 9-11

እንደ አቅም መኖር የሚቻለው እንዴት ነው?

የተበሳ ፊኛ ቢኖርህና ፊኛው ሳይተነፍስ እንዲቆይ ማድረግ ቢኖርብህ ምን ታደርጋለህ? ወደ ፊኛው የምታስገባው አየር በቀዳዳው በኩል ከሚወጣው አየር እስካላነሰ ድረስ ፊኛው ሳይተነፍስ እንዲቆይ ማድረግ ትችላለህ።

ይህ ምሳሌ እንደ አቅም መኖር ሲባል ምን ማለት እንደሆነ ለመረዳት ያስችለናል። ገቢህ፣ ፊኛው ውስጥ ከምታስገባው አየር ጋር ሊመሳሰል ይችላል። ወጪዎችህ ደግሞ በቀዳዳው በኩል ከሚወጣው አየር ጋር ይመሳሰላሉ። ፈታኝ የሆነው ነገር ወጪህ ከገቢህ እንዳይበልጥ ማድረጉ ነው።

እንደ አቅም መኖር ሲባል ቀላል ቢመስልም ይህን በማድረግ ጥቅም ማግኘቱ ግን እንደምናወራው ቀላል አይደለም። ሰዎች ይህን መሠረታዊ ሐሳብ በተግባር ለማዋል ጥረት ቢያደርጉ ከገንዘብ ጋር በተያያዘ ከሚፈጠሩ በርካታ ችግሮች መዳን ይችላሉ። ታዲያ ይህን ማድረግ የሚቻለው እንዴት ነው? ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉ መመሪያዎች ከየት ማግኘት እንችላለን? በዚህ ረገድ መጽሐፍ ቅዱስ ጠቃሚ የሆነ ብዙ ሐሳብ ይዟል። ከሚሰጣቸው ምክሮች መካከል እስቲ አንዳንዶቹን እንመልከት።

ጠቃሚ የሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች

መጽሐፍ ቅዱስ፣ ገንዘብህን በአግባቡ እንድትጠቀምበት የሚረዱህ በርካታ ጠቃሚ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ይዟል። ከእነዚህ መካከል ጥቂቶቹን ከዚህ ቀጥሎ እንመለከታለን። አንተም እነዚህ መሠረታዊ ሥርዓቶች እንደ አቅምህ ለመኖር ይረዱህ እንደሆነ እንድትመረምር እንጋብዝሃለን።

ዕቅድ ወይም በጀት አውጣ።

ገንዘብህን በአግባቡ እንድትጠቀምበት ገቢህ ምን ያህል እንደሆነና በምን ላይ እንደምታውለው ማወቅ ያስፈልግሃል። መጽሐፍ ቅዱስ “የትጕህ ሰው ዕቅድ ወደ ትርፍ ያመራል፤ ችኰላም ወደ ድኽነት ያደርሳል” ይላል። (ምሳሌ 21:5) አንዳንዶች ገንዘባቸውን የሚያወጡበትን መንገድ ለማቀድ እንዲያመቻቸው ፖስታዎችን ያዘጋጃሉ። ከዚያም በእያንዳንዱ ፖስታ ውስጥ እንደ “ምግብ፣” “ኪራይ” ወይም “ልብስ” ላሉ የተለያዩ ወጪዎች የሚያስፈልጋቸውን ገንዘብ ያስቀምጣሉ። አንተ የምትጠቀመው እንዲህ ባለው ቀላል ዘዴም ይሁን ይበልጥ በተደራጀ መንገድ ዋናው ነገር ገንዘብህን በምን ላይ እያዋልከው እንዳለ ማወቅህ ነው፤ ምንጊዜም ቅድሚያ መስጠት የሚኖርብህ ለቅንጦት ሳይሆን መሠረታዊ ለሆኑ ነገሮች ነው።

በሌሎች አትቅና።

በማደግ ላይ ባሉ አገሮች የሚኖሩ ብዙዎች ባደጉ አገሮች ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ያሏቸውን ነገሮች ለማግኘት ይጓጓሉ። በግለሰብ ደረጃ ደግሞ ብዙ ሰዎች፣ ጎረቤቶቻቸው ለታይታ ብለው የሚያደርጓቸውን ነገሮች ለማድረግ ይፈተናሉ። ይህ ወጥመድ ሊሆንባቸው ይችላል። ምናልባትም ጎረቤታቸው ራሱ ያን ነገር የሚያደርገው አቅሙ ስለፈቀደለት ላይሆን ይችላል። ታዲያ ጎረቤትህ የሚከተለውን የሞኝነት አካሄድ በመከተል ለምን ችግር ውስጥ ትገባለህ? መጽሐፍ ቅዱስ “ስስታም፣ ሀብት ለማከማቸት ይስገበገባል፤ ድኽነት እንደሚጠብቀውም አያውቅም” ይላል።​—ምሳሌ 28:22

አኗኗርህ ቀላል ይሁን።

ኢየሱስ፣ ዓይናቸው “አጥርቶ የሚያይ” ወይም ቀላል እንዲሆን ተከታዮቹን መክሯቸዋል። (ማቴዎስ 6:22) አቅምህ የሚፈቅደው፣ ሽሮ መብላት ሆኖ ሳለ ጮማ ለመቁረጥ የሚቃጣህ ከሆነ ለችግር ትዳረጋለህ። አንድ የእስያ ልማት ባንክ ባወጣው ሪፖርት መሠረት ከፊሊፒንስ ሕዝብ መካከል አንድ ሦስተኛ ገደማ ያህሉ እንዲሁም ከሕንድ ሕዝብ መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆነው የሚኖረው በእስያ በቀን ውስጥ መሠረታዊ ነገሮችን ለማሟላት ከሚያስፈልገው አነስተኛ ገንዘብ (1.35 የአሜሪካ ዶላር) ባነሰ ገቢ ነው። እንዲህ ያለ ከእጅ ወደ አፍ የሆነ ገቢ ያላቸው ሰዎች መሠረታዊ በሆኑ ነገሮች ላይ ማተኮራቸው የጥበብ አካሄድ ነው። ይሁንና ሀብታም በሆኑ አገሮች የሚኖሩ ሰዎችም ቢሆኑ ይህንኑ መሠረታዊ ሥርዓት ተግባራዊ ማድረጋቸው ከገንዘብ ጋር በተያያዘ ችግር ውስጥ ከመዘፈቅ ይጠብቃቸዋል።

መሠረታዊ በሆኑት ነገሮች ረክተህ ኑር።

ይህ ሐሳብ አኗኗርህን ቀላል እንድታደርግ ከሚያበረታታው ምክር ጋር ይስማማል። መጽሐፍ ቅዱስ በ⁠1 ጢሞቴዎስ 6:8 ላይ “ምግብ እንዲሁም ልብስና መጠለያ ካለን በእነዚህ ነገሮች ረክተን መኖር ይገባናል” የሚል ምክር ይሰጣል። በዓለም ላይ እጅግ ደስተኛ ከሆኑት ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ ብዙ ቁሳዊ ንብረት ባይኖራቸውም ባሏቸው ነገሮች ረክተው ይኖራሉ፤ እነዚህ ሰዎች ያሏቸው ነገሮች፣ ቁሳዊ ንብረትን ብቻ ሳይሆን ከቤተሰባቸውና ከወዳጆቻቸው ጋር ያላቸውን ፍቅር የተሞላበት ግንኙነትም ይጨምራሉ።​—ምሳሌ 15:17

አላስፈላጊ ዕዳ ውስጥ አትግባ።

“ባለጠጋ ድኻን ይገዛል፤ ተበዳሪም የአበዳሪ ባሪያ ነው” የሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳብ ምንኛ እውነት ነው! (ምሳሌ 22:7) መበደር የግድ አስፈላጊ የሚሆንበት ጊዜ ቢኖርም እንዲያው የፈለጉትን ነገር ለመግዛት ሲሉ አላስፈላጊ ብድር ውስጥ የሚገቡ ሰዎች አብዛኛውን ጊዜ በዕዳ ተተብትበው ያርፉታል። በተለይ በዱቤ የምትገዛ ወይም በክሬዲት ካርድ የምትጠቀም ከሆነ የዚህን ሐሳብ እውነተኝነት በግልጽ ትመለከታለህ። ታይም መጽሔት “ክሬዲት ካርድ ሲኖረን ማመዛዘን ያቅተናል” በማለት ይናገራል። በፊሊፒንስ የሚኖረው ኤሪክ እንዲህ ብሏል፦ “ብዙውን ጊዜ በክሬዲት ካርድ ስጠቀም እጅ በእጅ ከፍዬ ከምገዛው ይበልጥ ብዙ ነገሮችን እሸምታለሁ። ዕዳውን መክፈሉ ደግሞ በጀቴን ያቃውስብኛል።” እንግዲያው በዱቤ በመግዛት ረገድ በጣም ጠንቃቃ መሆናችን ጥበብ የተሞላበት አካሄድ ነው!​—2 ነገሥት 4:1፤ ማቴዎስ 18:25

ከመግዛትህ በፊት ገንዘብ አጠራቅም።

አንድን ነገር ከመግዛትህ በፊት የሚያስፈልገውን ገንዘብ ማጠራቀም ጊዜ ያለፈበት አካሄድ ቢመስልም እንደ እውነቱ ከሆነ ግን ከገንዘብ ጋር በተያያዘ ችግር ውስጥ ላለመግባት ከሚረዱት የጥበብ እርምጃዎች አንዱ ነው። ብዙዎች እንዲህ ማድረጋቸው ዕዳ ውስጥ ከመዘፈቅ ያዳናቸው ከመሆኑም ሌላ ከዕዳ ጋር ተያይዘው ከሚመጡ እንደ ከፍተኛ ወለድ ያሉ ችግሮች ጠብቋቸዋል፤ ነገሮችን በዱቤ ስንገዛ ወለድም ጭምር ስለምንከፍል መጨረሻ ላይ የምናወጣው ገንዘብ ከፍተኛ ይሆናል። ጉንዳን ‘በመከር ወቅት’ ለወደፊት የሚሆነውን ‘ቀለብ ስለሚሰበሰብ’ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ጠቢብ” ተብሎ ተጠርቷል።​—ምሳሌ 6:6-8፤ 30:24, 25

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

“ምን ያህል ማውጣት እንደምንችል በዝርዝር እንወያያለን”

ከሌሎች መማር

ከላይ ያየናቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ምክሮች በሙሉ ጠቃሚ ቢሆኑም በእርግጥ ሰዎች እንደ አቅማቸው እንዲኖሩ እየረዷቸው ነው? እነዚህን ምክሮች ተግባራዊ በማድረግ ከገንዘብ ጋር በተያያዘ ለሚፈጠሩ ችግሮች መፍትሔ ማግኘት የቻሉ አንዳንድ ሰዎችን ተሞክሮ እስቲ እንመልከት።

የአራት ልጆች አባት የሆነው ዲኦስዳዶ በቅርቡ በተፈጠረው የኢኮኖሚ ቀውስ ሳቢያ ቤተሰቡ የሚያስፈልገውን ነገር ማሟላት በጣም ከባድ እንደሆነበት ተናግሯል። ያም ሆኖ በጀት የማውጣትን ጠቀሜታ ተገንዝቧል። እንዲህ ብሏል፦ “የማገኘውን ገቢ በሙሉ ምን ላይ እንደማውለው በጀት አወጣለሁ። ገንዘቤን እንዴት እንደማወጣው በዝርዝር አሰፍራለሁ።” ዳኒሎም ተመሳሳይ ዘዴ ይጠቀማል። እሱና ባለቤቱ የነበራቸው አነስተኛ ንግድ ከስሮባቸው ነበር። ያም ሆኖ በጥንቃቄ በጀት በማውጣታቸው መሠረታዊ ወጪዎቻቸውን መሸፈን ችለዋል። እንዲህ ብሏል፦ “በየወሩ ገቢያችን ምን ያህል እንደሆነና ቋሚ ወጪያችን ምን ያህል እንደሆነ እናውቃለን። በዚህ ላይ ተመሥርተን ለሌሎች ነገሮች ምን ያህል ማውጣት እንደምንችል በዝርዝር እንወያያለን።”

[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

“ወደ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ለመሄድ በሕዝብ መጓጓዣ ከመጠቀም ይልቅ በእግራችን እንጓዛለን”

ሌሎች ደግሞ በበጀታቸው መሠረት ለመኖር በአንዳንድ ነገሮች ረገድ ወጪያቸውን መቀነስ አስፈልጓቸዋል። ሦስት ልጆች ያሏት መርነ የተባለች መበለት እንዲህ ብላለች፦ “እኔና ልጆቼ ወደ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ለመሄድ በሕዝብ መጓጓዣ ከመጠቀም ይልቅ በእግራችን እንጓዛለን።” መርነ፣ አኗኗርን ቀላል ማድረግ ያለውን ጥቅም ለልጆቿ ለማስተማር ጥረት አድርጋለች። “በ⁠1 ጢሞቴዎስ 6:8-10 ላይ የሚገኘውን ባለን የመርካትን አስፈላጊነት የሚያጎላውን መሠረታዊ ሥርዓት ተግባራዊ በማድረግ ረገድ ጥሩ ምሳሌ ለመሆን እጥራለሁ” በማለት ተናግራለች።

የሁለት ልጆች አባት የሆነው ጄራልድም ተመሳሳይ ነገር አድርጓል። እንዲህ ብሏል፦ “የቤተሰብ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ስናደርግ በጣም አስፈላጊ በሆኑት ነገሮች ይኸውም በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ ባተኮሩ ክርስቲያኖች ተሞክሮ ላይ እንወያያለን። ይህን በማድረጋችን ጥሩ ውጤት አግኝተናል፤ ምክንያቱም ልጆቻችን ያን ያህል አስፈላጊ ያልሆኑ ነገሮች እንዲገዙላቸው አይወተውቱንም።”

[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

“አስቀድሜ ያላሰብኩበትን ነገር እንዲሁ ስላየሁት ብቻ አልገዛም”

በፊሊፒንስ የምትኖረውና ነጠላ የሆነችው ጃኔት የሙሉ ጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስ አስተማሪ ሆና በፈቃደኝነት ታገለግላለች። በቅርቡ ከሥራ ብትወጣም እንደ አቅሟ ትኖራለች። ጃኔት “ይህን ማድረግ የቻልኩት ራሴን በመግዛትና ያለኝን ገንዘብ በጥንቃቄ ለመጠቀም ዕቅድ በማውጣት ነው” ብላለች። አክላም እንዲህ በማለት ተናግራለች፦ “ወደ ትልልቅ የገበያ ማዕከሎች ከመሄድ ይልቅ ረከስ ባለ ዋጋ የሚሸጥባቸውን ሱቆች ለማግኘት እሞክራለሁ። ነገሮችን በርካሽ መግዛት ስችል ለምን ውድ ዋጋ እከፍላለሁ? በተጨማሪም አስቀድሜ ያላሰብኩበትን ነገር እንዲሁ ስላየሁት ብቻ አልገዛም።” ጃኔት አስቀድሞ ገንዘብ ማጠራቀም የጥበብ እርምጃ እንደሆነ ተገንዝባለች። “ገንዘብ ከተረፈኝ ትንሽም እንኳ ቢሆን አስቀምጠዋለሁ፤ ያልተጠበቀ ወጪ ቢያጋጥመኝ በዚህ ገንዘብ እጠቀማለሁ” ብላለች።

ክሬዲት ካርድን በተመለከተ ደግሞ ቀደም ሲል የተጠቀሰው ኤሪክ “አጣዳፊ ሁኔታ እስካላጋጠመኝ ድረስ በክሬዲት ካርድ ላለመጠቀም ወስኛለሁ” ብሏል። ዲኦስዳዶም በዚህ ይስማማል፤ “ራሴን ለመግዛት ስል ብዙውን ጊዜ ክሬዲት ካርዴን ቢሮ እተወዋለሁ” በማለት ተናግሯል።

እንደ አቅምህ መኖር ትችላለህ

አዎን፣ መጽሐፍ ቅዱስ በዋነኝነት በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ ያተኮረ መጽሐፍ ቢሆንም በቁሳዊ ነገሮች ረገድም የሚጠቅሙን መመሪያዎች እንደያዘ ብዙዎች ተገንዘበዋል። (ምሳሌ 2:6፤ ማቴዎስ 6:25-34) በዚህ ርዕስ ውስጥ የተብራሩትን የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች ተግባራዊ በማድረግ እንዲሁም እነዚህን መመሪያዎች በመከተል ከተጠቀሙ ሰዎች ተሞክሮ ትምህርት በመውሰድ አንተም እንደ አቅምህ መኖር ትችላለህ። እንዲህ ካደረግህ በዛሬው ጊዜ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የሚያጋጥማቸው ዓይነት መከራና ጭንቀት እንዳይደርስብህ መከላከል ትችላለህ።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ