አስቸጋሪ ሁኔታዎች ሲያጋጥሟችሁ እንደ ፊንሐስ ዓይነት እርምጃ ትወስዳላችሁ?
የጉባኤ ሽማግሌ ሆኖ ማገልገል ትልቅ መብት ነው። ያም ሆኖ ሽማግሌዎች አስቸጋሪ ሁኔታዎች ሊያጋጥሟቸው እንደሚችሉ የአምላክ ቃል ይናገራል። አምላክን ወክለው ‘ፍርድ በሚሰጡበት ጊዜ’ መጥፎ ድርጊት ከመፈጸም ጋር የተያያዙ የፍርድ ጉዳዮችን መመልከት የሚኖርባቸው ጊዜ አለ። (2 ዜና 19:6) ወይም ደግሞ አንድ የበላይ ተመልካች አንድ ኃላፊነት ሲሰጠው ልክ እንደ ሙሴ ብቃቱ እንደሌለው ሆኖ ሊሰማው ይችላል፤ በአንድ ወቅት ሙሴ ተልእኮ በተሰጠው ጊዜ “ወደ ፈርዖን የምሄድ . . . እኔ ማን ነኝ?” ሲል በትሕትና ጠይቆ ነበር።—ዘፀ. 3:11
ቅዱሳን መጻሕፍት የተጻፉት በመንፈስ ቅዱስ መሪነት እንደሆነ ሁሉ ሽማግሌዎች የሚሾሙትም በዚሁ መንፈስ አማካኝነት ነው፤ ቅዱሳን መጻሕፍት አስቸጋሪ ሁኔታዎችን በብቃት መወጣት ስለቻሉ የበላይ ተመልካቾች የሚገልጹ ሕያው ምሳሌዎችን ይዘዋል። ፊንሐስ የአልዓዛር ልጅና የአሮን የልጅ ልጅ በመሆኑ ሊቀ ካህናት የመሆን መብት ነበረው። ፊንሐስ በሕይወቱ ውስጥ ያጋጠሙት ሦስት ሁኔታዎች በዛሬው ጊዜ የሚገኙ ሽማግሌዎች አስቸጋሪ ሁኔታዎች በሚያጋጥሟቸው ጊዜ ድፍረትና ማስተዋል ማሳየት እንዲሁም በይሖዋ መታመን እንዳለባቸው ይጠቁማሉ።
ወዲያውኑ ‘ጦሩን በእጁ ይዞ’ ተነሣ
እስራኤላውያን በሞዓብ ሜዳ በሰፈሩበት ጊዜ ፊንሐስ ገና ወጣት ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “እስራኤላውያን . . . ከሞዓብ ሴቶች ጋር ማመንዘር ጀመሩ። . . . ሕዝቡም መሥዋዕቱን በላ፤ ለአማልክቱም ሰገደ።” (ዘኍ. 25:1, 2) በመሆኑም ይሖዋ ኃጢአት የሠሩትን ሰዎች ቀሠፋቸው። ፊንሐስ እነዚህ ሰዎች ስለሠሩት ኃጢአትና ስላስከተለው መቅሰፍት ሲሰማ ምን ያህል ስሜቱ ተነክቶ ሊሆን እንደሚችል አስብ!
ዘገባው በመቀጠል እንዲህ ይላል፦ “ሙሴና መላው የእስራኤል ማኀበር በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ላይ እያለቀሱ ሳለ፣ አንድ እስራኤላዊ እነርሱ እያዩት አንዲት ምድያማዊት ሴት ይዞ ወደ ቤተ ሰቡ መጣ።” (ዘኍ. 25:6) ካህኑ ፊንሐስ ምን ያደርግ ይሆን? በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ ፊንሐስ በዕድሜ ወጣት ነበር፤ ጥፋት የፈጸመው እስራኤላዊ ግን በአምልኮ ረገድ ቀዳሚ በመሆን ሕዝቡን የመምራት ኃላፊነት የነበረው የቤተሰብ አለቃ ነበር።—ዘኍ. 25:14
ይሁንና ፊንሐስ ይፈራ የነበረው ሰዎችን ሳይሆን ይሖዋን ነበር። በመሆኑም እስራኤላዊውን ሰውና ምድያማዊቷን ሲመለከት ወዲያውኑ ጦሩን በማንሳት ሰውየውን ተከትሎ ወደ ድንኳኑ ገባ፤ ከዚያም ጦሩን ወርውሮ ሁለቱንም አጣምሮ ወጋቸው። ይሖዋ፣ ፊንሐስ በድፍረትና በቆራጥነት የወሰደውን እርምጃ እንዴት ተመለከተው? ይሖዋ መቅሠፍቱ ወዲያውኑ እንዲቆም ያደረገ ሲሆን ለፊንሐስ፣ የክህነት አገልግሎቱ ‘ለዘለቄታው’ ከዘሮቹ ሳይወጣ እንደሚኖር ቃል ኪዳን በመግባት ወሮታ ከፍሎታል።—ዘኍ. 25:7-13
እርግጥ ነው፣ በዛሬው ጊዜ ያሉ ክርስቲያን ሽማግሌዎች በሌሎች ላይ የኃይል እርምጃ አይወስዱም። ይሁንና ሽማግሌዎች ልክ እንደ ፊንሐስ ቆራጥና ደፋር መሆን ይኖርባቸዋል። ለምሳሌ ያህል፣ ጊልየርመ ሽማግሌ ሆኖ ከተሾመ ከጥቂት ወራት በኋላ በፍርድ ኮሚቴ ውስጥ እንዲሠራ ተመደበ። ኃጢአት የፈጸመው ግለሰብ ጊልየርመ ልጅ በነበረበት ጊዜ በመንፈሳዊ የረዳው አንድ ሽማግሌ ነበር። ጊልየርመ እንዲህ ብሏል፦ “ሁኔታው በጣም ረበሸኝ፤ ሌሊት እንኳ ሳይቀር እንቅልፍ ከልክሎኝ ነበር። ለወንድም ያለኝ ስሜት መንፈሳዊ እይታዬን ሳይጋርድብኝ ጉዳዩን በተገቢው መንገድ እንዴት መያዝ እንደምችል ሳወጣ ሳወርድ ቆየሁ። ለበርካታ ቀናት ጸለይኩ፤ እንዲሁም በመጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች ላይ ምርምር አደረግሁ።” ይህ ደግሞ ያጋጠመውን አስቸጋሪ ሁኔታ ለመወጣት ድፍረት እንዲያገኝ የረዳው ሲሆን ኃጢአት የሠራውን ወንድም በመንፈሳዊ ለመርዳት አስችሎታል።—1 ጢሞ. 4:11, 12
ሽማግሌዎች አስፈላጊ ሆኖ በሚገኝበት ጊዜ ድፍረትና ቆራጥነት የተሞላበት እርምጃ በመውሰድ የእምነትና የታማኝነት ምሳሌ ይሆናሉ። እውነት ነው፣ ሌሎች ክርስቲያኖችም ከበድ ያለ መጥፎ ድርጊት መፈጸሙን ሲያውቁ ጉዳዩን ለሚመለከታቸው በመናገር ድፍረት የተሞላበት እርምጃ መውሰድ ይኖርባቸዋል። በተመሳሳይም ከተወገደ ጓደኛችን አሊያም የቤተሰባችን አባል ጋር የነበረንን ግንኙነት ማቋረጥ ታማኝነትን ይጠይቃል።—1 ቆሮ. 5:11-13
ማስተዋል ከችግር ይጠብቃል
ወጣቱ ፊንሐስ ድፍረት የተሞላበት እርምጃ የወሰደው እንዲያው በግብታዊነት ተነሳስቶ አልነበረም። በሌላ ወቅት ፊንሐስ አንድ ወሬ በሰማበት ጊዜ ጥንቃቄና ማመዛዘን የተሞላበት እርምጃ በመውሰድ አስተዋይ መሆኑን ያሳየው እንዴት እንደሆነ ተመልከት። የሮቤልና የጋድ ነገዶች እንዲሁም የምናሴ ነገድ እኩሌታ በዮርዳኖስ ወንዝ አጠገብ መሠዊያ ሠሩ። ይሁንና ሌሎቹ የእስራኤል ነገዶች፣ መሠዊያውን የሠሩት ለሐሰት አምልኮ እንደሆነ አድርገው ስላሰቡ እነሱን ለመውጋት ተዘጋጁ።—ኢያሱ 22:11, 12
በዚህ ጊዜ ፊንሐስ ምን አደረገ? ፊንሐስ ከሌሎች እስራኤላውያን አለቆች ጋር በመሆን መሠዊያውን የሠሩትን ነገዶች ጥበብ በሚንጸባረቅበት መንገድ ስለ ጉዳዩ አነጋገራቸው። ክስ የተሰነዘረባቸው ነገዶችም መሠዊያውን የሠሩት ‘ለእግዚአብሔር አምልኮ’ መሆኑን ገለጹላቸው። በዚህ መንገድ ችግሩ እልባት አገኘ።—ኢያሱ 22:13-34
አንድ ክርስቲያን፣ ስለ ሌላ የይሖዋ አገልጋይ አንድ ዓይነት ክስ ወይም መጥፎ ነገር በሚሰማበት ጊዜ የፊንሐስን ምሳሌ መከተሉ ጥበብ የሚንጸባረቅበት አካሄድ ነው። አስተዋዮች መሆናችን ሌሎች በተናገሩት ነገር ቅር ከመሰኘት ወይም ስለ ወንድሞቻችን ደግነት የጎደለው ነገር ከመናገር እንድንቆጠብ ያደርገናል።—ምሳሌ 19:11
ሽማግሌዎች አስተዋይ መሆናቸው ፊንሐስ የወሰደው ዓይነት እርምጃ እንዲወስዱ የሚረዳቸው እንዴት ነው? ከአሥር ለሚበልጡ ዓመታት በሽምግልና ያገለገለው ሃይሜ እንዲህ ብሏል፦ “አንድ አስፋፊ በእሱና በሌላ ወንድም መካከል አለመግባባት እንደተፈጠረ በሚነግረኝ ጊዜ ለአንዱ ወገን እንዳላደላና አስፈላጊውን ቅዱስ ጽሑፋዊ መመሪያ መስጠት እንድችል ወዲያውኑ ወደ ይሖዋ እጸልያለሁ። አንድ ቀን አንዲት እህት በሌላ ጉባኤ ውስጥ የሚያገለግል ኃላፊነት ያለው ወንድም እንዳስቀየማት ነገረችኝ። ወንድም የቅርብ ጓደኛዬ ስለነበር ስለ ጉዳዩ በቀጥታ ላነጋግረው እችል ነበር። ይሁንና ከእህት ጋር በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን እያነሳን ተወያየን። ከዚያም እህት፣ ከሁሉ በፊት ወንድምን ራሷ ሄዳ ለማነጋገር ወሰነች። (ማቴ. 5:23, 24) ያም ሆኖ ጉዳዩ እልባት ሊያገኝ አልቻለም። ስለሆነም ሌሎች መሠረታዊ ሥርዓቶችን ግምት ውስጥ እንድታስገባ ነገርኳት። እሷም በጉዳዩ ላይ በድጋሚ በጸሎት እንደምታስብበትና ወንድምን ይቅር ለማለት ጥረት እንደምታደርግ ገለጸችልኝ።”
ታዲያ ውጤቱ ምን ሆነ? ሃይሜ እንዲህ ይላል፦ “ከበርካታ ወራት በኋላ እህት ወደ እኔ መጣች። ወንድም በተናገረው ነገር መጸጸቱን ከጊዜ በኋላ እንደነገራት ገለጸችልኝ። ቀጠሮ ይዘው አብረው እንዳገለገሉና ወንድም ለእሷ ያለውንም አድናቆት እንደገለጸላት ነገረችኝ። በጉዳዩ ላይ ሳያስፈልግ እጄን አስገብቼ ቢሆን ኖሮ ከዚህ የተሻለ ውጤት ማምጣት እችል ነበር? በውዝግቡ ውስጥ ብገባ ኖሮ ለአንደኛው ወገን ያደላሁ ያስመስልብኝ ነበር።” መጽሐፍ ቅዱስ “[ጉዳይህን] ወደ ፍርድ አደባባይ በችኰላ አታውጣ” ይላል። (ምሳሌ 25:8) አስተዋይ የሆኑ ሽማግሌዎች፣ ክርስቲያኖች በመካከላቸው አለመግባባት ሲፈጠር የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን በተግባር እንዲያውሉና ሰላም እንዲፈጥሩ ጥበብ የተሞላበት ምክር ይሰጧቸዋል።
ይሖዋን ጠይቋል
ፊንሐስ፣ አምላክ ለመረጣቸው ሕዝቦች ካህን ሆኖ የማገልገል መብት አግኝቶ ነበር። ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው ፊንሐስ በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ ወጣት በነበረበት ጊዜም እንኳ በጣም ደፋርና አስተዋይ ነበር። ያም ሆኖ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን መወጣት የቻለው በይሖዋ ይታመን ስለነበር ነው።
ከብንያም ነገድ የሆኑት የጊብዓ ሰዎች፣ የአንድን ሌዋዊ ቁባት ደፍረው በመግደል አሳዛኝ ድርጊት ከፈጸሙ በኋላ ሌሎቹ ነገዶች የብንያምን ነገድ ለመውጋት ዘምተው ነበር። (መሳ. 20:1-11) ለውጊያ ከመውጣታቸው በፊት የይሖዋን እርዳታ ለማግኘት ጸልየው የነበረ ቢሆንም ሁለት ጊዜ ትልቅ ሽንፈት ደረሰባቸው። (መሳ. 20:14-25) በዚህ ጊዜ ጸሎታቸው ተቀባይነት እንዳላገኘ ተሰምቷቸው ይሆን? ለተፈጸመው መጥፎ ድርጊት የአጸፋ እርምጃ ለመውሰድ በመነሳታቸው ይሖዋ አልተደሰተም ነበር ማለት ነው?
በዚያን ወቅት የእስራኤላውያን ሊቀ ካህናት የሆነውና የማይናወጥ እምነት የነበረው ፊንሐስ በድጋሚ ቅድሚያውን በመውሰድ “ወንድሞቻችንን ብንያማውያንን እንደ ገና ሄደን ጦርነት እንግጠማቸው ወይስ ይቅር?” በማለት ወደ ይሖዋ ጸለየ። በምላሹም ይሖዋ ብንያማውያንን በእጃቸው አሳልፎ የሰጣቸው ከመሆኑም ሌላ ጊብዓን በእሳት አቃጥለው አወደሟት።—መሳ. 20:27-48
ከዚህ ምን ትምህርት እናገኛለን? ሽማግሌዎች ብርቱ ጥረት ቢያደርጉና አምላክ እንዲረዳቸው ደጋግመው ቢጸልዩም በጉባኤ ውስጥ ያሉት እንዳንድ ችግሮች ቶሎ አይወገዱ ይሆናል። እንዲህ ያለ ሁኔታ ሲያጋጥም ሽማግሌዎች ኢየሱስ የተናገረውን የሚከተለውን ሐሳብ ማስታወሳቸው ተገቢ ነው፦ “ደጋግማችሁ ለምኑ [ወይም ጸልዩ]፣ ይሰጣችኋል፤ ሳታሰልሱ ፈልጉ፣ ታገኛላችሁ፤ ደጋግማችሁ አንኳኩ፣ ይከፈትላችኋል።” (ሉቃስ 11:9) ሽማግሌዎች ያቀረቡት ጸሎት ቶሎ መልስ እንዳላገኘ ቢሰማቸውም እንኳ ይሖዋ በራሱ ጊዜ መልስ እንደሚሰጣቸው ሊተማመኑ ይገባል።
ለምሳሌ ያህል፣ በአየርላንድ የሚገኝ አንድ ጉባኤ የመንግሥት አዳራሽ በጣም ያስፈልገው የነበረ ቢሆንም በአካባቢው የሚገኘው የግንባታ ጉዳዮች መምሪያ ኃላፊ ለወንድሞች ፈቃድ ለመስጠት ሳይስማማ ቀረ። ወንድሞች ባሰቡት ቦታ ላይ የመንግሥት አዳራሽ ለመሥራት ያቀረቧቸውን የተለያዩ የግንባታ ፕላኖች ኃላፊው ውድቅ አደረገባቸው። ላቀረቡት ጥያቄ ፈቃድ ሊሰጣቸው የሚችለው ሌላው ባለሥልጣን የመላ አገሪቱን የከተማ ልማት የሚቆጣጠረው ዋና ኃላፊ ብቻ ነበር። ታዲያ ወንድሞች፣ ጉዳዩን አስመልክተው መጸለያቸው በፊንሐስ ጊዜ እንደነበረው ሁሉ ጥሩ ውጤት አስገኝቶላቸው ይሆን?
በአካባቢው ያለ አንድ ሽማግሌ እንዲህ ብሏል፦ “ደጋግመን ከጸለይንና ብርቱ ልመና ካቀረብን በኋላ ወደ ዋናው ቢሮ አመራን። ከፍተኛ ባለሥልጣኑን ለማነጋገር በርካታ ሳምንታት መጠበቅ እንዳለብኝ ተነገረኝ። ያም ሆኖ ለአምስት ደቂቃ ያህል ብቻ እንድናነጋግረው ፈቃድ አገኘን። ባለሥልጣኑ ማስተካከያ የተደረገበትን ፕላን ከተመለከተ በኋላ የሕንፃውን ግንባታ ለመጀመር የሚያስችል ፈቃድ ወዲያውኑ ሰጠን፤ ከዚያን ጊዜ አንስቶ የአካባቢው የግንባታ ጉዳዮች መምሪያ ኃላፊ ብዙ ትብብር አደረገልን። ይህ ሁኔታ ጸሎት ምን ያህል ኃይል እንዳለው እንድንገነዘብ አስችሎናል።” አዎ፣ ይሖዋ በእሱ ላይ የሚታመኑ ሽማግሌዎች የሚያቀርቧቸውን ልመናዎች ይሰማል።
ፊንሐስ በጥንቷ እስራኤል ከባድ ኃላፊነት የነበረበት ሰው ቢሆንም በድፍረት፣ በማስተዋልና በአምላክ ላይ በመታመን የገጠሙትን አስቸጋሪ ሁኔታዎች በብቃት መወጣት ችሏል። ፊንሐስ የአምላክን ጉባኤ ለመንከባከብ ትጋት የተሞላበት ጥረት ማድረጉ የአምላክን ሞገስ አስገኝቶለታል። ከ1,000 ዓመታት ገደማ በኋላ ዕዝራ በመንፈስ መሪነት “በቀድሞ ጊዜ የበር ጠባቂዎቹ አለቃ የአልዓዛር ልጅ ፊንሐስ ነበረ፤ እግዚአብሔርም ከእርሱ ጋር ነበረ” በማለት ጽፏል። (1 ዜና 9:20) አምላክ፣ በዛሬው ጊዜ ሕዝቦቹን ግንባር ቀደም ሆነው ከሚመሩት ወንድሞችም ሆነ እሱን በታማኝነት ከሚያገለግሉት ክርስቲያኖች ሁሉ ጋር እንዲሆን ምኞታችን ነው።