“የመጽናናት ሁሉ አምላክ” በሆነው በይሖዋ ታመኑ
“ከርኅራኄ የመነጨ ምሕረት አባትና የመጽናናት ሁሉ አምላክ የሆነው የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት የተባረከ ይሁን።”—2 ቆሮ. 1:3
1. በየትኛውም ዕድሜ የሚገኙ ሰዎች ምን ይፈልጋሉ?
ከተወለድንበት ጊዜ አንስቶ ሁላችንም ማጽናኛ ማግኘት እንፈልጋለን። አንድ ሕፃን እንድናባብለው ወይም እንድናጽናናው ሲፈልግ ያለቅሳል። ሕፃኑ የሚያለቅሰው መታቀፍ ፈልጎ አሊያም ርቦት ሊሆን ይችላል። ትልቅ ሰው ከሆንንም በኋላ ብዙ ጊዜ ማጽናኛ ማግኘት እንሻለን። በተለይ ደግሞ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን ማጽናኛ መፈለጋችን አይቀርም።
2. ይሖዋ በእሱ የሚታመኑትን እንደሚያጽናና ምን ማረጋገጫ ሰጥቷል?
2 ብዙውን ጊዜ ቤተሰቦቻችንና ወዳጆቻችን በተወሰነ ደረጃ ሊያጽናኑን ይችላሉ። አንዳንድ ጊዜ ግን የሚያስጨንቁን ሁኔታዎች ከሰው አቅም በላይ ይሆናሉ። ያለንበት ሁኔታ የቱንም ያህል አስጨናቂ ቢሆን አምላክ ሊያጽናናን ይችላል። የአምላክ ቃል “እግዚአብሔር ለሚጠሩት ሁሉ፣ . . . ቅርብ ነው። . . . ጩኸታቸውን ይሰማል” የሚል ማረጋገጫ ይሰጠናል። (መዝ. 145:18, 19) በእርግጥም “የእግዚአብሔር ዐይኖች ወደ ጻድቃን ናቸው፤ ጆሮዎቹም ለጩኸታቸው ክፍት ናቸው።” (መዝ. 34:15) ይሁንና አምላክ እንዲደግፈንና እንዲያጽናናን ከፈለግን በእሱ መታመን ይኖርብናል። መዝሙራዊው ዳዊት እንደሚከተለው ብሎ ሲዘምር ይህን ግልጽ አድርጎታል፦ “እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW] ለተጨቈኑት አምባ ነው፤ በመከራም ጊዜ መጠጊያ ይሆናቸዋል። ስምህን የሚያውቁ ይታመኑብሃል፤ እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW] ሆይ፤ የሚሹህን አትተዋቸውምና።”—መዝ. 9:9, 10
3. ኢየሱስ፣ ይሖዋ ለሕዝቡ ያለውን ፍቅር ለመግለጽ ምን ምሳሌ ተጠቅሟል?
3 የይሖዋ አገልጋዮች በእሱ ዘንድ ውድ ናቸው። ኢየሱስ እንደሚከተለው ብሎ በተናገረ ጊዜ ይህን አመልክቷል፦ “አምስት ድንቢጦች አነስተኛ ዋጋ ባላቸው ሁለት ሳንቲሞች ይሸጡ የለም? ሆኖም አንዷም እንኳ በአምላክ ፊት አትረሳም። የእናንተ የራሳችሁ ፀጉር እንኳ በሙሉ የተቆጠረ ነው። ስለዚህ አትፍሩ፤ እናንተ ከብዙ ድንቢጦች የላቀ ዋጋ አላችሁ።” (ሉቃስ 12:6, 7) ይሖዋ በነቢዩ ኤርምያስ አማካኝነት የጥንት ሕዝቦቹን “በዘላለማዊ ፍቅር ወድጄሻለሁ፤ ስለዚህም በርኀራኄ ሳብሁሽ” ብሏቸው ነበር።—ኤር. 31:3
4. ይሖዋ የገባውን ቃል እንደሚፈጽም መተማመን የምንችለው ለምንድን ነው?
4 በይሖዋ መታመናችንና እሱ የሰጣቸው ተስፋዎች እንደሚፈጸሙ ሙሉ እምነት ማሳደራችን መከራ ሲገጥመን ሊያጽናናን ይችላል። በመሆኑም እኛም እንደ ኢያሱ በአምላክ መታመን ይኖርብናል፤ ኢያሱ እንዲህ ብሏል፦ “አምላካችሁ እግዚአብሔር ከሰጣችሁ መልካም ተስፋ ሁሉ አንዲቱን እንኳ [አላስቀረባችሁም]፤ . . . አንዱም ሳይቀር ሁሉም ተፈጽሞአል።” (ኢያሱ 23:14) በተጨማሪም በደረሱብን አስቸጋሪ ሁኔታዎች የተነሳ ለጊዜው ብንደቆስም እንኳ “አምላክ ታማኝ” በመሆኑ ታማኝ አገልጋዮቹን ፈጽሞ እንደማይጥላቸው መተማመን እንችላለን።—1 ቆሮንቶስ 10:13ን አንብብ።
5. ሌሎችን ለማጽናናት የሚያስችለን ምንድን ነው?
5 ሐዋርያው ጳውሎስ፣ ይሖዋን “የመጽናናት ሁሉ አምላክ” በማለት ጠርቶታል። “ማጽናናት” ማለት በመከራ ወይም በሐዘን ውስጥ የወደቀን ሰው መንፈሱ እንዲረጋጋ ማድረግ ማለት ነው። ይህንንም ማድረግ የሚቻለው ግለሰቡ የደረሰበት መከራ ወይም ሐዘን እንዲቀልልለት በመርዳት ብሎም ሰውየውን በማበረታታት ነው። ይሖዋ ይህን እንደሚያደርግ ምንም ጥርጥር የለውም። (2 ቆሮንቶስ 1:3, 4ን አንብብ።) ሰማያዊ አባታችንን ማንም ወይም ምንም ነገር ሊገድበው ስለማይችል የሚወዱትን ሰዎች ለማጽናናት ሲል የሚያስፈልጋቸውን ነገር ሁሉ ሊያደርግላቸው ይችላል። እኛም በበኩላችን “በማንኛውም ዓይነት መከራ” ውስጥ ያሉትን የእምነት ባልንጀሮቻችንን ማጽናናት እንችላለን። “አምላክ እኛን እያጽናናበት ባለው ማጽናኛ” አማካኝነት ይህን ማድረግ እንችላለን። ይሖዋ በመከራ የተደቆሱትን ለማጽናናት ያለውን ተወዳዳሪ የሌለው ችሎታ የሚገልጽ እንዴት ያለ ግሩም ሐሳብ ነው!
ለመከራ መንስኤ የሚሆኑ ነገሮች
6. አንድን ሰው ለጭንቀት ሊዳርጉ የሚችሉ ነገሮችን ጥቀስ።
6 በሕይወታችን ውስጥ በሚያጋጥሙን የተለያዩ ነገሮች ሳቢያ ማጽናኛ ያስፈልገናል። በሐዘን እንድንደቆስ ከሚያደርጉን ነገሮች አንዱ የምንወዳቸውን ሰዎች በተለይም የትዳር ጓደኛን ወይም ልጅን በሞት መነጠቅ ነው። ከዚህም ሌላ አንድ ሰው መድሎ ሲደረግበት ወይም የጭፍን ጥላቻ ዒላማ ሲሆንም ማጽናኛ ሊያስፈልገው ይችላል። በተጨማሪም የጤና እክል፣ እርጅና፣ ድህነት፣ በትዳር ውስጥ የሚፈጠር ችግር ወይም በዓለም ላይ ያሉት አስጨናቂ ሁኔታዎች አንድ ሰው ማጽናኛ እንዲያስፈልገው ሊያደርጉ ይችላሉ።
7. (ሀ) ከባድ መከራ ሲያጋጥመን ምን ዓይነት ማጽናኛ ማግኘት እንፈልጋለን? (ለ) ይሖዋ “የተሰበረውንና የተዋረደውን” ወይም የተደቆሰውን ልብ ለመፈወስ ምን ያደርጋል?
7 በመከራ ወቅት ልባችንን፣ አእምሯችንን እና ስሜታችንን የሚያረጋጋልን እንዲሁም አካላዊም ሆነ መንፈሳዊ ጤንነታችን እንዲጠበቅ የሚያደርግ ማጽናኛ ማግኘት እንፈልጋለን። ለምሳሌ ልባችንን እንመልከት። የአምላክ ቃል ልባችን ‘ሊሰበርና ሊዋረድ’ ወይም ሊደቆስ እንደሚችል ይናገራል። (መዝ. 51:17) ይሖዋ ይህን ሁኔታ ማስተካከል እንደሚችል ምንም ጥርጥር የለውም፤ ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ፣ ይሖዋ “ልባቸው የተሰበረውን ይፈውሳል፤ ቍስላቸውንም ይጠግናል” ይላል። (መዝ. 147:3) በጣም ከባድ መከራ በሚያጋጥመን ጊዜም እንኳ በሙሉ እምነት ወደ ይሖዋ የምንጸልይና ትእዛዛቱን የምንጠብቅ ከሆነ እሱ የተደቆሰው ልባችን እፎይታ እንዲያገኝ ሊያደርግ ይችላል።—1 ዮሐንስ 3:19-22ን እና 1 ዮሐንስ 5:14, 15ን አንብብ።
8. አእምሯችንን የሚያስጨንቅ ነገር ሲያጋጥመን ይሖዋ ሊረዳን የሚችለው እንዴት ነው?
8 የሚደርሱብን የተለያዩ መከራዎች አእምሯችንን ሊያስጨንቁት ስለሚችሉ ብዙውን ጊዜ አእምሯችን ማጽናኛ ያስፈልገዋል። እነዚህን የእምነት ፈተናዎች በራሳችን ኃይል መወጣት አንችል ይሆናል። ይሁንና መዝሙራዊው “የውስጤ ጭንቀት በበዛ መጠን፣ ማጽናናትህ ነፍሴን ደስ አሰኛት” በማለት ዘምሯል። (መዝ. 94:19) በተጨማሪም ጳውሎስ እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “ስለ ምንም ነገር አትጨነቁ፤ ከዚህ ይልቅ ስለ ሁሉም ነገር በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር ልመናችሁን ለአምላክ አቅርቡ፤ ከማሰብ ችሎታ ሁሉ በላይ የሆነው የአምላክ ሰላም በክርስቶስ ኢየሱስ አማካኝነት ልባችሁንና አእምሯችሁን ይጠብቃል።” (ፊልጵ. 4:6, 7) ቅዱሳን መጻሕፍትን ማንበብና ባነበብነው ላይ ማሰላሰል አእምሯችንን የሚያስጨንቀውን ነገር ለመቋቋም ይረዳናል።—2 ጢሞ. 3:15-17
9. በስሜታችን ላይ ጫና የሚያሳድሩ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን እንዴት ልንቋቋማቸው እንችላለን?
9 አንዳንድ ጊዜ በጣም ተስፋ ከመቁረጣችን የተነሳ አፍራሽ በሆኑ ስሜቶች ልንዋጥ እንችላለን። ምናልባት አንዳንድ ቅዱስ ጽሑፋዊ ኃላፊነቶቻችንን ወይም የአገልግሎት መብቶቻችንን መወጣት እንደተሳነን ሆኖ ሊሰማን ይችላል። በዚህ ጊዜም ቢሆን ይሖዋ ሊያጽናናን እና ሊረዳን ይችላል። ለምሳሌ ኢያሱ፣ እስራኤላውያንን እየመራ ኃይለኛ ከሆኑት ጠላቶቻቸው ጋር እንዲዋጋ ተልእኮ በተሰጠው ወቅት ሙሴ ለሕዝቡ እንዲህ ብሏቸው ነበር፦ “ብርቱና ደፋር ሁኑ፤ አትፍሯቸው ወይም አትደንግጡላቸው። አምላክህ እግዚአብሔር ካንተ ጋር ይሄዳልና፤ አይተውህም፤ አይጥልህምም።” (ዘዳግም 31:6) ኢያሱ በይሖዋ ድጋፍ የአምላክን ሕዝቦች እየመራ ወደ ተስፋይቱ ምድር ማስገባትና ጠላቶቻቸውን ሁሉ ድል ማድረግ ችሏል። ከዚያ ቀደም ብሎ በቀይ ባሕር አካባቢ በነበሩበት ጊዜም ሙሴ ተመሳሳይ መለኮታዊ እርዳታ አግኝቷል።—ዘፀ. 14:13, 14, 29-31
10. አስጨናቂ ሁኔታዎች በአካላዊ ጤንነታችን ላይ ጉዳት ቢያስከትሉብን ምን ዓይነት እርዳታ ማግኘት እንችላለን?
10 አስጨናቂ ሁኔታዎች በአካላዊ ጤንነታችንም ላይ ጉዳት ሊያስከትሉ ይችላሉ። ተገቢ አመጋገብ፣ በቂ እረፍት ማግኘት፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግና ንጽሕናችንን መጠበቅ ጤናማ እንድንሆን አስተዋጽኦ ሊያደርጉ እንደሚችሉ የታወቀ ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ትክክለኛ መንፈሳዊ አመለካከት መያዛችን በአካላዊ ጤንነታችን ላይ በጎ ተጽዕኖ ሊኖረው ይችላል። ስለሆነም አንዳንድ አስጨናቂ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን ጳውሎስ የደረሰበትን ችግርና እንደሚከተለው በማለት የተናገረውን የሚያጽናና ሐሳብ ማስታወሳችን ጠቃሚ ነው፦ “በየአቅጣጫው ብንደቆስም መፈናፈኛ አናጣም፤ ግራ ብንጋባም መውጫ ቀዳዳ አናጣም፤ ስደት ቢደርስብንም ያለ ረዳት ተጥለን አንቀርም፤ ተገፍትረን ብንወድቅም አንጠፋም።”—2 ቆሮ. 4:8, 9
11. መንፈሳዊ ሕመምን መቋቋም የምንችለው እንዴት ነው?
11 አንዳንድ መከራዎች መንፈሳዊ ጤንነታችንን ሊያቃውሱ ይችላሉ። በዚህ ጊዜም ቢሆን ይሖዋ ሊረዳን ይችላል። ቃሉ “እግዚአብሔር የሚንገዳገዱትን ሁሉ ይደግፋል፤ የወደቁትንም ሁሉ ያነሣል” የሚል ማረጋገጫ ይሰጠናል። (መዝ. 145:14) መንፈሳዊ ሕመምን ለመቋቋም እንድንችል የክርስቲያን ሽማግሌዎችን እርዳታ መሻታችን ጠቃሚ ነው። (ያዕ. 5:14, 15) ከዚህም በተጨማሪ በቅዱሳን መጻሕፍት ላይ የተመሠረተውን የዘላለም ሕይወት ተስፋ ምንጊዜም በአእምሯችን መያዛችን የእምነት ፈተና ሲያጋጥመን ጸንተን እንድቆም ይረዳናል።—ዮሐ. 17:3
አምላክ እንደሚያጽናና የሚያሳዩ ምሳሌዎች
12. ይሖዋ አብርሃምን እንዴት እንዳጽናናው ግለጽ።
12 አንድ መዝሙራዊ ለይሖዋ እንዲህ በማለት ተናግሯል፦ “ለአገልጋይህ የገባኸውን ቃል አስብ፤ በዚያ ተስፋ ሰጥተኸዋልና። ቃልህ ሕያው ያደርገኛልና፣ ይህች በመከራዬ መጽናኛዬ ናት።” (መዝ. 119:49, 50) አምላክ እንደሚያጽናና የሚያሳዩ በርካታ ምሳሌዎችን የያዘው በጽሑፍ የሰፈረው የይሖዋ ቃል አለን። ለምሳሌ አብርሃም፣ ይሖዋ ሰዶምንና ገሞራን እንደሚያጠፋ ሲያውቅ በጣም አዝኖ ነበር። ይህ ታማኝ የአምላክ አገልጋይ ይሖዋን “በእርግጥ ጻድቁን ከኀጢአተኛው ጋር አብረህ ታጠፋለህን?” በማለት ጠየቀው። ይሖዋም 50 ጻድቃን ብቻ እንኳ ቢያገኝ ሰዶምን እንደማያጠፋ በመግለጽ አብርሃምን አጽናናው። አብርሃም ግን 45፣ 40፣ 30፣ 20 ወይም 10 ጻድቃን ቢገኙ ይሖዋ ሰዶምን ይምር እንደሆነ ደጋግሞ ጠየቀው። አብርሃም እነዚህን አምስት ጥያቄዎች ሲያቀርብ ይሖዋ ሰዶምን እንደማያጠፋ በትዕግሥትና በደግነት አረጋግጦለታል። በሰዶም አሥር ጻድቃን እንኳ አልተገኙም፤ ሆኖም ይሖዋ ሎጥንና ሴት ልጆቹን አድኗቸዋል።—ዘፍ. 18:22-32፤ 19:15, 16, 26
13. ሐና በይሖዋ እንደምትተማመን ያሳየችው እንዴት ነው?
13 የሕልቃና ሚስት ሐና፣ ልጅ የመውለድ ከፍተኛ ፍላጎት ነበራት። ይሁን እንጂ መሃን መሆኗ ጭንቀት አስከትሎባት ነበር። ሐና ጉዳዩን አስመልክታ ወደ ይሖዋ ጸለየች፤ ሊቀ ካህናቱ ዔሊም “የእስራኤል አምላክ የለመንሺውን ይስጥሽ” አላት። ይህ ሐናን ያጽናናት ሲሆን “ከዚያም በኋላ በፊቷ ላይ ሐዘን አልታየም።” (1 ሳሙ. 1:8, 17, 18) ሐና ሁኔታውን ይሖዋ እንደሚያስተካክለው በመተማመን ጉዳዩን ሙሉ በሙሉ ለእሱ ተወችው። ጸሎቷ እንዴት ምላሽ እንደሚያገኝ ባታውቅም እንኳ ውስጣዊ ሰላም አግኝታ ነበር። ውሎ አድሮም ይሖዋ ለጸሎቷ ምላሽ ሰጣት። ሐና የጸነሰች ሲሆን ወንድ ልጅ ወለደች፤ ልጇንም ሳሙኤል ብላ ሰየመችው።—1 ሳሙ. 1:20
14. ዳዊት ማጽናኛ ያስፈለገው ለምን ነበር? ማጽናኛ ለማግኘትስ ወደ ማን ዘወር ብሏል?
14 አምላክ ያጽናናው ሌላው ሰው ደግሞ የጥንቷ እስራኤል ንጉሥ የነበረው ዳዊት ነው። ይሖዋ ‘ልብን ስለሚያይ’ ዳዊትን የእስራኤል ንጉሥ እንዲሆን ሲያጨው ይህ ሰው ቅንና ለእውነተኛው አምልኮ ያደረ መሆኑን ያውቅ ነበር። (1 ሳሙ. 16:7፤ 2 ሳሙ. 5:10) ከጊዜ በኋላ ግን ዳዊት ከቤርሳቤህ ጋር ምንዝር የፈጸመ ከመሆኑም ሌላ ኃጢአቱን ለመደበቅ ሲል ባሏን አስገደለው። ዳዊት የሠራው ኃጢአት ምን ያህል ከባድ እንደሆነ ሲገነዘብ ወደ ይሖዋ እንዲህ ሲል ጸለየ፦ “እንደ ቸርነትህ መጠን፣ ምሕረት አድርግልኝ፤ እንደ ርኅራኄህም ብዛት፣ መተላለፌን ደምስስ። በደሌን ፈጽሞ እጠብልኝ፤ ከኀጢአቴም አንጻኝ። እኔ መተላለፌን አውቃለሁና፤ ኀጢአቴም ዘወትር በፊቴ ነው።” (መዝ. 51:1-3) ዳዊት ከልቡ ንስሐ የገባ ሲሆን ይሖዋም ይቅር ብሎታል። እርግጥ ነው፣ ዳዊት ኃጢአት መሥራቱ ካስከተለበት መዘዝ አላመለጠም። (2 ሳሙ. 12:9-12) እንደዚያም ሆኖ ትሑት የሆነው ይህ የአምላክ አገልጋይ ይሖዋ መሐሪ መሆኑን መገንዘቡ አጽናንቶታል።
15. ኢየሱስ ክርስቶስ ከመሞቱ በፊት ይሖዋ ምን ድጋፍ ሰጥቶታል?
15 ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረበት ጊዜ በርካታ አስቸጋሪ ሁኔታዎች አጋጥመውታል። አምላክ እነዚህ የእምነት ፈተናዎች በኢየሱስ ላይ እንዲደርሱ የፈቀደ ሲሆን ኢየሱስም ታማኝነቱን ጠብቋል፤ ፍጹም ሰው የነበረው ኢየሱስ ምንጊዜም በይሖዋ ላይ ይተማመንና የአምላክን ሉዓላዊነት ይደግፍ ነበር። ኢየሱስ አልፎ የሚሰጥበትና የሚገደልበት ጊዜ ሲቃረብ “የእኔ ሳይሆን የአንተ ፈቃድ ይፈጸም” በማለት ወደ ይሖዋ ጸለየ። በዚህ ጊዜ አንድ መልአክ ከሰማይ ተገልጦለት አበረታታው። (ሉቃስ 22:42, 43) አምላክ ለኢየሱስ በወቅቱ የሚያስፈልገውን ማጽናኛ፣ ማበረታቻና ድጋፍ ሰጥቶታል።
16. ታማኝነታችንን በመጠበቃችን ምክንያት ከሞት ጋር በምንፋጠጥበት ጊዜ የሚያጋጥመንን ጭንቀት እንድንቋቋም አምላክ የሚረዳን እንዴት ነው?
16 ክርስቲያኖች በመሆናችን ባለን ቁርጥ አቋም የተነሳ ከሞት ጋር ብንፋጠጥም እንኳ ይሖዋ ለእሱ ያለንን ታማኝነት እንድንጠብቅ ሊረዳን ይችላል፤ ደግሞም ይረዳናል። በተጨማሪም የትንሣኤ ተስፋ ያጽናናናል። የመጨረሻው ጠላት የሆነው ‘ሞት የሚደመሰስበትን’ ጊዜ በጉጉት እንጠብቃለን! (1 ቆሮ. 15:26) በሞት ያንቀላፉት የአምላክ ታማኝ አገልጋዮችም ሆኑ ሌሎች ሰዎች በይሖዋ የመታሰቢያ መጽሐፍ ላይ የተመዘገቡ ሲሆን እሱም ፈጽሞ አይዘነጋቸውም፤ በትንሣኤ ያስባቸዋል። (ዮሐ. 5:28, 29፤ ሥራ 24:15) ይሖዋ ትንሣኤ እንደሚኖር በገባው ቃል ላይ መተማመናችን ስደት በሚደርስብን ጊዜ ሊያጽናናን እንዲሁም እርግጠኛ የሆነ ተስፋ እንዲኖረን ሊረዳን ይችላል።
17. የምንወደው ሰው ሲሞት ይሖዋ የሚያጽናናን እንዴት ነው?
17 በሞት ያንቀላፉት የምንወዳቸው ሰዎች ግሩም በሆነና በዛሬው ጊዜ ካሉት የሚያስጨንቁ ነገሮች ሁሉ በጸዳ አዲስ ዓለም ውስጥ ትንሣኤ አግኝተው በሕይወት የመኖር ተስፋ እንዳላቸው ማወቁ ምንኛ የሚያጽናና ነው! ይህ ክፉ ሥርዓት ሲጠፋ በሕይወት የሚተርፉት የይሖዋ አገልጋዮች የሆኑ “እጅግ ብዙ ሕዝብ፣” ከሞት ተነስተው በምድር ላይ የሚኖሩትን ሰዎች የመቀበልና የማስተማር ታላቅ መብት ይኖራቸዋል!—ራእይ 7:9, 10
የአምላክ ዘላለማዊ ክንዶች ከሥርህ ናቸው
18, 19. የአምላክ አገልጋዮች ስደት ሲደርስባቸው ማጽናኛ ያገኙት እንዴት ነው?
18 ሙሴ ኃይለኛ መልእክት ባዘለውና ልብን የሚያስደስቱ ቃላት በያዘው መዝሙር ላይ ለእስራኤላውያን “ዘላለማዊ አምላክ መኖርያህ ነው፤ የዘላለም ክንዶቹም ከሥርህ ናቸው” የሚል ማረጋገጫ ሰጥቷቸዋል። (ዘዳ. 33:27) ከጊዜ በኋላ ነቢዩ ሳሙኤል፣ እስራኤላውያንን “በፍጹም ልባችሁ አምልኩት እንጂ እግዚአብሔርን [“ይሖዋን፣” NW] ከመከተል ፈቀቅ አትበሉ። . . . ስለ ታላቅ ስሙ ሲል እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW] ሕዝቡን አይተውም” ብሏቸዋል። (1 ሳሙ. 12:20-22) እውነተኛውን አምልኮ በመከተል ከይሖዋ ጋር እስከተጣበቅን ድረስ እሱ ፈጽሞ አይጥለንም። ምንጊዜም የሚያስፈልገንን እርዳታ ይሰጠናል።
19 አምላክ በዓይነታቸው ልዩ በሆኑት በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት፣ ለሕዝቦቹ የሚያስፈልገውን እርዳታና ማጽናኛ ከመስጠት ወደኋላ ብሎ አያውቅም። በዓለም ዙሪያ የሚገኙ በሺዎች የሚቆጠሩ የእምነት ባልንጀሮቻችን ይሖዋን በማገልገላቸው የተነሳ ከመቶ ዓመት ለሚበልጥ ጊዜ ስደት ሲደርስባቸው እንዲሁም ወደ ወኅኒ ሲጣሉ ቆይተዋል። የእነሱ ተሞክሮ ይሖዋ በመከራ ወቅት አገልጋዮቹን በእርግጥ እንደሚያጽናናቸው ማስረጃ ይሆነናል። ለምሳሌ ያህል፣ በቀድሞዋ ሶቪየት ኅብረት የሚኖር አንድ ወንድማችን በእምነቱ ምክንያት የ23 ዓመት እስራት ተፈርዶበት ነበር። ያም ሆኖ ይህ ወንድማችን የሚያበረታታውና የሚያጽናናው መንፈሳዊ ምግብ ማግኘት ችሏል። እንዲህ ብሏል፦ “በእነዚያ ዓመታት ሁሉ በይሖዋ መታመንን ተምሬያለሁ፤ እሱም አበረታትቶኛል።”—1 ጴጥሮስ 5:6, 7ን አንብብ።
20. ይሖዋ እንደማይተወን እርግጠኞች መሆን የምንችለው ለምንድን ነው?
20 ወደፊት ምንም ዓይነት መከራ ቢያጋጥመን መዝሙራዊው የተናገረውን “እግዚአብሔር ሕዝቡን አይጥልም” የሚለውን የሚያጽናና ሐሳብ ማስታወሳችን ጠቃሚ ነው። (መዝ. 94:14) በግለሰብ ደረጃ ማጽናኛ ቢያስፈልገንም እኛም ሌሎችን የማጽናናት ታላቅ መብት አግኝተናል። በሚቀጥለው ርዕስ ላይ እንደምንመለከተው በዚህ በመከራ በተሞላ ዓለም ውስጥ ያዘኑትን ማጽናናት እንችላለን።
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
• ለጭንቀት ሊዳርጉን የሚችሉ አንዳንድ ነገሮች ምንድን ናቸው?
• ይሖዋ አገልጋዮቹን የሚያጽናናው እንዴት ነው?
• ከሞት ጋር በምንፋጠጥበት ጊዜ ምን ሊያጽናናን ይችላል?
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕሎች]
ከታች ባሉት ነገሮች ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን መቋቋም የምንችልበት መንገድ
▪ ልብ መዝ. 147:3፤ 1 ዮሐ. 3:19-22፤ 5:14, 15
▪ አእምሮ መዝ. 94:19 የ1980 ትርጉም፤ ፊልጵ. 4:6, 7
▪ ስሜት ዘፀ. 14:13, 14፤ ዘዳ. 31:6
▪ አካላዊ ጤንነት 2 ቆሮ. 4:8, 9
▪ መንፈሳዊ ጤንነት መዝ. 145:14፤ ያዕ. 5:14, 15