የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w12 1/1 ገጽ 19-21
  • መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2012
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2012
  • መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2012
  • መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2009
  • መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2011
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2012
w12 1/1 ገጽ 19-21

መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል

እጅግ የሚያሳዝን የልጅነት ሕይወት ያሳለፈች ወጣት እውነተኛ ትርጉም ያለው ሕይወት መምራት የቻለችው እንዴት ነው? ዓመፀኛ የነበረ የፖለቲካ ሰው ሰላማዊ የሆነ ወንጌላዊ ሊሆን የቻለው እንዴት ነው? የእነዚህን ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት ቀጥሎ የቀረቡትን የሕይወት ታሪኮች እንድታነብ እንጋብዝሃለን።

“ፍቅር ለማግኘት በጣም እጓጓ ነበር።”​—ኢና ሌዥኒና

የትውልድ ዘመን፦ 1981

የትውልድ አገር፦ ሩሲያ

የኋላ ታሪክ፦ አሳዛኝ የልጅነት ሕይወት የነበራት

የቀድሞ ሕይወቴ፦ ወላጆቼ መስማት የተሳናቸው ሲሆኑ እኔም ስወለድ ጀምሮ መስማት አልችልም። ስድስት ዓመት እስኪሆነኝ ድረስ ሕይወቴ አስደሳች ነበር። ከዚያ በኋላ ግን ወላጆቼ በፍቺ ተለያዩ። በወቅቱ ገና ለጋ የነበርኩ ቢሆንም እንኳ ፍቺ ምን ማለት እንደሆነ ስለገባኝ ስሜቴ በጥልቅ ተጎዳ። ወላጆቼ ከተፋቱ በኋላ አባቴና ታላቅ ወንድሜ በትሮይትስክ መኖር የቀጠሉ ሲሆን እናቴ እኔን ይዛ ወደ ቼልያቢንስክ ሄደች። ከጊዜ በኋላም በድጋሚ አገባች። እንጀራ አባቴ ሰካራም ከመሆኑም ሌላ ብዙ ጊዜ እኔንም ሆነ እናቴን ይደበድበን ነበር።

የምወደው ታላቅ ወንድሜ በ1993 ውኃ ውስጥ ሰጥሞ ሞተ። አደጋው ለቤተሰባችን በጣም አስደንጋጭ ነበር። ከዚያ በኋላ እናቴ ጠጪ ሆነች፤ እሷም ከእንጀራ አባቴ ጋር ተደርባ ትበድለኝ ነበር። በመሆኑም የተሻለ ሕይወት ለማግኘት ጥረት ማድረግ ጀመርኩ። ፍቅር ለማግኘት በጣም እጓጓ ነበር። መጽናኛ ፍለጋ ወደተለያዩ ቤተ ክርስቲያኖች ብሄድም የፈለግሁትን ነገር አላገኘሁም።

መጽሐፍ ቅዱስ ሕይወቴን የለወጠው እንዴት ነው? አሥራ ሦስት ዓመት ሲሆነኝ የይሖዋ ምሥክር የሆነች የክፍሌ ልጅ ከመጽሐፍ ቅዱስ አንዳንድ ታሪኮችን ነገረችኝ። እንደ ኖኅና ኢዮብ ስላሉት አስቸጋሪ በሆኑ ሁኔታዎች ሥር አምላክን ያገለገሉ ሰዎች ከመጽሐፍ ቅዱስ የተማርኩትን ነገር በጣም ወደድሁት። ብዙም ሳይቆይ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናትና በስብሰባዎቻቸው ላይ መገኘት ጀመርኩ።

መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናቴ በርካታ አስደሳች እውነቶችን ለመገንዘብ ረድቶኛል። አምላክ ስም እንዳለው መማሬ ልቤን በጥልቅ ነካው። (መዝሙር 83:18 NW) መጽሐፍ ቅዱስ “በመጨረሻዎቹ ቀኖች” ስለሚኖረው ሁኔታ የተናገረው ትንቢት ትክክለኛነት በጣም አስገረመኝ። (2 ጢሞቴዎስ 3:1-5) ስለ ትንሣኤ ተስፋ ስማር ደግሞ ልቤ በሐሴት ተሞላ። ከወንድሜ ጋር እንደገና እንደምንገናኝ ማወቄ ምን ያህል እንዳስደሰተኝ መገመት ትችላላችሁ!​—ዮሐንስ 5:28, 29

ይሁን እንጂ ባገኘሁት እውነት ሁሉም ሰው እንደ እኔ አልተደሰተም። እናቴና የእንጀራ አባቴ የይሖዋ ምሥክሮችን ይጠሉ ነበር። በመሆኑም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቴን እንዳቆም ጫና ሊያሳድሩብኝ ሞከሩ። ሆኖም የምማረውን ነገር ስለወደድኩት ማጥናቴን ላለማቆም ቆርጬ ነበር።

ከቤተሰብ የሚያጋጥመኝን ተቃውሞ መቋቋም ቀላል አልነበረም። በዚያ ላይ ደግሞ ቤተሰባችን ሌላ አስደንጋጭ ነገር ገጠመው፤ በይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባ ላይ አብሮኝ ይገኝ የነበረው ታናሽ ወንድሜም ውኃ ውስጥ ሰጥሞ ሞተ። ይሁንና የይሖዋ ምሥክሮች ከጎኔ አልተለዩም። ሕይወቴን በሙሉ ስናፍቀው የኖርኩትን ፍቅር ከይሖዋ ምሥክሮች አገኘሁ። ይህ ትክክለኛው ሃይማኖት እንደሆነ ገባኝ። ስለዚህ በ1996 ተጠምቄ የይሖዋ ምሥክር ሆንኩ።

ያገኘሁት ጥቅም፦ ድሚትሪ የሚባል ጥሩ ሰው ያገባሁ ሲሆን በትዳር ውስጥ ስድስት ዓመታት አሳልፈናል። ከድሚትሪ ጋር ሆነን በሴንት ፒተርስበርግ በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ እናገለግላለን። ጊዜ እያለፈ ሲሄድ ደግሞ ወላጆቼ ስለ እምነቴ የነበራቸው አመለካከት እየተለወጠ መጥቷል።

ይሖዋን በማወቄ በጣም አመስጋኝ ነኝ! እሱን ማገልገሌ ሕይወቴ እውነተኛ ትርጉም እንዲኖረው አድርጓል።

“አእምሮዬን የሚረብሹ ብዙ ጥያቄዎች ነበሩኝ።”​—ራውዴል ሮድሪጌዝ ሮድሪጌዝ

የትውልድ ዘመን፦ 1959

የትውልድ አገር፦ ኩባ

የኋላ ታሪክ፦ ዓማፂ የነበረ

የቀድሞ ሕይወቴ፦ የተወለድኩት በሃቫና፣ ኩባ በሚገኝ የድሆች ሰፈር ነው፤ በአካባቢያችን የሰፈር ጠብ የተለመደ ነበር። እያደግሁ ስሄድ ጁዶና ትግል ያለባቸው ሌሎች ስፖርቶች ይማርኩኝ ጀመር።

ጎበዝ ተማሪ ስለነበርኩ ወላጆቼ ዩኒቨርሲቲ እንድገባ አበረታቱኝ። በዩኒቨርሲቲ እያለሁ የአገራችን የፖለቲካ ሥርዓት መለወጥ እንደሚያስፈልገው ተሰማኝ። በመሆኑም በመንግሥት ላይ ለማመፅ ወሰንኩ። በአንድ ወቅት አብሮኝ ከሚማር ልጅ ጋር ሆነን በአንድ ፖሊስ ላይ ጥቃት በመሰንዘር መሣሪያውን ለመንጠቅ ሞከርን። በግብግቡ መሃል ፖሊሱ ጭንቅላቱ ላይ ከባድ ጉዳት ደረሰበት። በዚህም ምክንያት እኔና አብሮኝ የሚማረው ልጅ ወኅኒ የወረድን ሲሆን እንድንረሸን ተፈረደብን። ገና በ20 ዓመቴ የሞትን ጽዋ ልጎነጭ ነው!

በወኅኒ ቤት ውስጥ ብቻዬን ተቀምጬ እያለሁ በሚረሽኑኝ ወታደሮች ፊት እንዴት እንደምሆን እየመላለስኩ አስብ ነበር። ፍርሃት የሚባል ነገር እንዲታይብኝ አልፈለግሁም። በሌላ በኩል ደግሞ አእምሮዬን የሚረብሹ ብዙ ጥያቄዎች ነበሩኝ። ‘በዓለም ላይ የፍትሕ መጓደል ይህን ያህል የበዛው ለምንድን ነው? ሕይወት ማለት ይህ ብቻ ነው?’ እያልኩ አስብ ነበር።

መጽሐፍ ቅዱስ ሕይወቴን የለወጠው እንዴት ነው? በኋላ ላይ የሞት ፍርዱ ተቀይሮ በ30 ዓመት እስራት እንድንቀጣ ተወሰነ። በሃይማኖታቸው ምክንያት ከታሰሩ የይሖዋ ምሥክሮች ጋር የተገናኘሁት በዚህ ወቅት ነበር። እነዚህ ሰዎች ደፋሮች ሆኖም ሰላማውያን መሆናቸው አስገረመኝ። ያለጥፋታቸው ቢታሰሩም ንዴት ወይም ምሬት አይታይባቸውም።

የይሖዋ ምሥክሮች፣ አምላክ ለሰው ዘር ስላለው ዓላማ አስተማሩኝ። አምላክ ምድርን ከወንጀልና ከፍትሕ መጓደል የጸዳች ገነት እንደሚያደርጋት ከመጽሐፍ ቅዱስ አሳዩኝ። ምድር በጥሩ ሰዎች እንደምትሞላና እነዚህ ሰዎች ፍጹም በሆነ ሁኔታ ውስጥ ለዘላለም የመኖር አጋጣሚ እንደሚያገኙም አስተማሩኝ።​—መዝሙር 37:29

ከይሖዋ ምሥክሮች የተማርኩትን ነገር ብወድደውም እንደ እነሱ ለመሆን ግን ብዙ እንደሚቀረኝ ይሰማኝ ነበር። በፖለቲካዊ ጉዳዮች ገለልተኛ መሆን ወይም ጉንጬን ለሚመታኝ ሌላኛውን ማዞር ለእኔ የማይቻል ነገር እንደሆነ አስብ ነበር። በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስን በራሴ ለማንበብ ወሰንኩ። አንብቤ ስጨርስ፣ የጥንቶቹ ክርስቲያኖች ዓይነት ምግባር ያላቸው የይሖዋ ምሥክሮች ብቻ እንደሆኑ ተገነዘብኩ።

በሕይወቴ ውስጥ ትልልቅ ለውጦች ማድረግ እንዳለብኝ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቴ ተገንዝቤ ነበር። ለምሳሌ፣ መጥፎ ቃላትን የመጠቀም ልማድ ስለነበረኝ በአነጋገሬ ረገድ ለውጥ ማድረግ ይጠበቅብኝ ነበር። በተጨማሪም ማጨሴን ማቆም ነበረብኝ። በፖለቲካ ጉዳዮች ደግሞ ወገንተኛ መሆንን መተው ያስፈልገኝ ነበር። እነዚህን ለውጦች ማድረግ ቀላል ባይሆንም በይሖዋ እርዳታ ከጊዜ በኋላ ተሳክቶልኛል።

በቀላሉ ደሜ የሚፈላ ሰው ስለነበርኩ ቁጣዬን መቆጣጠር በጣም ፈትኖኛል። አሁንም ቢሆን በዚህ ረገድ ራሴን ለመግዛት እጸልያለሁ። በ⁠ምሳሌ 16:32 ላይ እንደሚገኘው ያሉ ጥቅሶች በጣም ጠቅመውኛል፤ ጥቅሱ “ታጋሽ ሰው ከጦረኛ፣ ስሜቱን የሚገዛም ከተማን በጕልበቱ ከሚይዝ ይበልጣል” ይላል።

በ1991 ተጠምቄ የይሖዋ ምሥክር ሆንኩ። የጥምቀት ሥነ ሥርዓቱ የተፈጸመው በእስር ቤት በሚገኝ በውኃ የተሞላ በርሜል ውስጥ ነበር። በቀጣዩ ዓመት ከእስረኞቹ መካከል አንዳንዶቻችን ተፈታን፤ ከዚያም በስፔን ዘመዶች ስለነበሩን ወደዚያ ተላክን። ስፔን እንደደረስኩ ወዲያውኑ በይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባ ላይ ተገኘሁ። እነሱም አብሬያቸው ለብዙ ዓመታት የኖርኩ ያህል ጥሩ አቀባበል ያደረጉልኝ ሲሆን በስፔን ሕይወቴን ሀ ብዬ እንድጀምር ረዱኝ።

ያገኘሁት ጥቅም፦ በሕይወቴ ደስተኛ ነኝ፤ በአሁኑ ጊዜ ከባለቤቴና ከሴቶች ልጆቻችን ጋር አምላክን አገለግላለሁ። አብዛኛውን ጊዜዬን ለሌሎች መጽሐፍ ቅዱስን በማስተማሩ ሥራ ማሳለፍ መቻሌን እንደ መብት እቆጥረዋለሁ። አንዳንድ ጊዜ፣ ገና በወጣትነቴ ለመሞት ተቃርቤ የነበርኩበትን ወቅት አስታውስና ከዚያ ወዲህ ያገኘኋቸውን በረከቶች አደንቃለሁ። በሕይወት መኖር ከመቻሌም ሌላ ለወደፊቱ ጊዜ ተስፋ አለኝ። አምላክ ቃል በገባው ገነት ውስጥ ፍትሕ የሚሰፍንበትንና ‘ሞት የማይኖርበትን’ ጊዜ በጉጉት እጠባበቃለሁ።​—ራእይ 21:3, 4

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

“አምላክ ስም እንዳለው መማሬ ልቤን በጥልቅ ነካው”

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

እኔና ባለቤቴ መስማት ለተሳናቸው ሰዎች በሚዘጋጁ የማስተማሪያ መሣሪያዎች ተጠቅመን ሌሎችን መርዳት ያስደስተናል

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ